የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ዘመኑ በጣም አስከፊ የሆነው ለምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1997 | ሚያዝያ 1
    • በዓለም ውስጥ በሚታዩ ሌሎች ሰቆቃዎችም ረገድ ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። ስለ ረሃብ ማንበብና የረሃብ ሰለባ በመሆኗ ሳቢያ ሆዷ የተነፋና እግሮቿ እንደ ክብሪት እንጨት የሰለሉ በሞት አፋፍ ላይ የምትገኝ የአምስት ዓመት ልጅ ፎቶግራፍ ማየት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለ ወንጅል አኃዛዊ ማስረጃዎችን ማንበብና አንዲት በዕድሜ የገፋች መበለት በጭካኔ ተደብድባ ንብረቷን ሁሉ ከተዘረፈች በኋላ ተገዳ በጾታ እንደተደፈረች መስማት ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። የቤተሰብ ተቋም እየተዳከመ እንዳለ ማንበብና አንዲት እናት ሆን ብላ የገዛ ልጆቿን በረሃብ እንደምታሠቃይና በጭካኔ እንደምታንገላታ ማወቅ ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

      እንዲህ ስላሉት ነገሮች ማንበብ ይሰቀጥጣል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ምድር አቀፍ መቅሰፍቶች አንዱ እኛ ላይ ሲደርስ ምንኛ ይበልጥ ከባድ ይሆናል! አንድ ክፉ ነገር እኛ ላይ ሲደርስብን በዓለም የዜና ማሠራጫዎች የሚስተጋባው ነገር ይበልጥ ጉልህ ሆኖ ይታየናል። ወንጀል፣ ጦርነት፣ ረሃብና ሕመም የሚያስከትሉት ሰቆቃ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማያውቅ ከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን አምኖ መቀበል በጣም ያስፈራል። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ውስጥ ከሚታዩት ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር መታገል የሚያስከትለው ውጤት በእርግጥም በጣም አስከፊ ሊሆን ይችላል፤ ግራ መጋባት፣ ፍርሃትና የመንፈስ ጭንቀት የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል።

      በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ዛሬ ሁኔታዎች በጣም አስከፊ የሆኑት ለምንድን ነው? የሰው ልጅ ወዴት እያመራ ይሆን? ለሚሉት የሚያስጨንቁ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይጥራሉ።

      የሚያሳዝነው ግን በዛሬ ጊዜ አርኪ መልስ የሚሰጡ ሃይማኖቶች እምብዛም ናቸው። መጀመሪያ እዚህ መጽሔት ሽፋን ላይ ያለውን ጥያቄ ስትመለከት መልስ ይገኝለት ይሆን የሚል ጥርጣሬ አድሮብህ ሊሆን ይችላል፤ ይህ የሚጠበቅ ነገር ነው። ብዙውን ጊዜ የአክራሪነት አቋም ያላቸው ሃይማኖቶች መጽሐፍ ቅዱስ ያላለውን እንዳለ አድርገው በማቅረብ ስለዚህ ዓለም መጥፊያ ትክክለኛ ቀንና ሰዓት ለማብራራት ይሞክራሉ። (ማቴዎስ 24:⁠36ን ተመልከት።) የዚህ መጽሔት አዘጋጆች ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ መልስ ቢሰጥ የተሻለ እንደሆነ ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው ቀን የሚናገረው ነገር እውነተኛና ምክንያታዊ መሆኑን ስታውቅ ትገረም ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያብራራው ሁኔታዎቹ ለምን በጣም አስከፊ እንደሆኑ ብቻ አይደለም። የወደፊቱን ጊዜ በሚመለከት በጣም የሚያጽናና ተስፋ ይሰጣል። ይህንን ሁኔታ ለመረዳት የሚቀጥሉትን ርዕሶች እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

  • በእርግጥ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ነውን?
    መጠበቂያ ግንብ—1997 | ሚያዝያ 1
    • በእርግጥ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ነውን?

      በአንዲት ታንኳ የፊተኛ ክፍል ተቀምጣችሁ ስትሄዱ ወደሚናወጠው የወንዙ ክፍል ትደርሳላችሁ። እየዘለለ በሚረጨውና አረፋ በሚደፍቀው ውኃ መሃል ያፈጠጡ ትላልቅ አለቶች ይታዩአችኋል። እንዳትጋጩ በመቅዘፊያው ተጠቅማችሁ ከዚያ አካባቢ ለመራቅ ትሞክራላችሁ። ከኋላችሁ የተቀመጠው ሰው በመቅዘፊያው ታንኳውን በማንቀሳቀስ ሊረዳችሁ ይችል ነበር፤ ግን ምንም ተሞክሮ የለውም። ከሁሉ የከፋው ደግሞ ምንም ካርታ ስላልያዛችሁ የዚህ ወራጅ ውኃ መጨረሻው ፀጥ ያለ ኩሬ ይሁን ፏፏቴ ምንም ማወቅ አልቻላችሁም።

      በጣም ያስፋራል፤ አይደለም? እንግዲያው በሌላ ምሳሌ እንቀይረው። ይህን ወንዝ ጠንቅቆ የሚያውቅ ተሞክሮ ያለው አንድ መንገድ መሪ አላችሁ እንበል። ገና ከሩቁ ወደዚህ የሚናወጥ ውኃ እየተዳረሳችሁ እንደሆነ ያውቃል፤ የወንዙ መጨረሻ ምን እንደሆነ እንዲሁም የሚናወጠውን ውኃ እንዴት ሊያልፈው እንደሚችልም ያውቃል። ይህ ከበፊቱ የበለጠ የመተማመን ስሜት እንዲኖራችሁ አያደርግምን?

      እውነት ነው፣ ሁላችንም ያለነው ከዚህ ጋር በሚመሳሰል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው። ያለ ጥፋታችን በሰው ልጅ ታሪክ በጣም አስቸጋሪ ወደሆነው ዘመን ገብተናል። አብዛኞቹ ሰዎች ሁኔታዎቹ እስከ መቼ ድረስ በዚህ መልኩ እንደሚቀጥሉ፣ ወደፊት ይሻሻሉ አይሻሻሉ ወይም ደግሞ እስከዚያው ድረስ ለመኖር የተሻለ መንገድ ይኑር አይኑር ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። ይሁን እንጂ መውጫ እንደሌለን ወይም ብቻችንን እንደተተውን ሊሰማን አይገባም። አምላካችን አንድ መንገድ መሪ አዘጋጅቶልናል፤ ይህም መሪ የዛሬው በጨለማ የተዋጠ የታሪክ ወቅት እንደሚመጣና እንዴት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ አስቀድሞ ትንቢት የተናገረ ሲሆን በሕይወት ለመትረፍ የሚያስፈልገንንም መመሪያ ይሰጠናል። መንገድ መሪ የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የመጽሐፉ ደራሲ ይሖዋ አምላክ ራሱን ታላቅ አስተማሪ ብሎ ከመጥራቱም ሌላ በኢሳይያስ በኩል እንደሚከተለው በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል:- “ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ።” (ኢሳይያስ 30:​20, 21) እንዲህ ያለውን አመራር ትቀበላለህን? እንግዲያውስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለጊዜያችን ሁኔታ አስቀድሞ የተናገረውን ነገር እንመርምር።

      የኢየሱስ ተከታዮች ትርጉም ያለው ጥያቄ አነሡ

      የኢየሱስ ተከታዮች ተገርመው መሆን አለበት። ኢየሱስ ውብ የሆነው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ሕንጻ ሙሉ በሙሉ እንደሚወድም በእርግጥኝነት ተናግሮ ነበር! እንዲህ ያለው ትንበያ በጣም የሚያስደንቅ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሄደው አረፍ እንዳሉ አራቱ ደቀ መዛመርት “ንገረን እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ሲሉ ኢየሱስን ጠየቁት። (ማቴዎስ 24:​3 NW፤ ማርቆስ 13:​1-4) እነርሱ ቢገነዘቡትም ባይገነዘቡትም ኢየሱስ የሰጠው መልስ ድርብ ተፈጻሚነት ነበረው።

      የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ጥፋትና የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ከክርስቶስ መገኘትና ከመላው ዓለም የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ የተለዩ ነገሮች ናቸው። የሆነ ሆኖ ኢየሱስ በሰጠው ረዘም ያለ መልስ ውስጥ ጥያቄው የሚዳስሳቸውን እነዚህን ሁሉ ዘርፎች ጠቅሷል። የኢየሩሳሌም ጥፋት ከመምጣቱ በፊት ምን ነገሮች እንደሚፈጸሙ ነግሯቸዋል፤ እንዲሁም በሚገኝበት ማለትም በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበትና ጠቅላላውን የዓለም የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ለማምጣት በሚዘጋጅበት ጊዜ ነገሮች ምን መልክ ይኖራቸዋል ብለው መጠበቅ እንደሚችሉ ነግሯቸዋል።

      የኢየሩሳሌም ጥፋት

      በመጀመሪያ ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌምና በዚያ ስለሚገኘው ቤተ መቅደስ ምን እንደተናገረ ልብ በል። ከዓለም ታላላቅ ከተሞች አንዷ በነበረችው በኢየሩሳሌም ላይ አስከፊ መከራ ስለሚመጣበት ጊዜ ከሦስት አሥርተ ዓመታት ቀደም ብሎ ትንቢት ተናግሯል። በተለይ በሉቃስ 21:​20, 21 ላይ የሚገኙትን ቃላት ልብ በል:- “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ።” ኢየሩሳሌም በጭፍራ የምትከበብ ከሆነ ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት “በመካከልዋ ያሉ” በቀላሉ ‘ፈቀቅ ሊሉ’ የሚችሉት እንዴት ነበር? ኢየሱስ ማምለጫ መንገድ እንደሚከፈትላቸው መናገሩ እንደነበር ግልጽ ነው። ታዲያ ተከፍቶላቸው ነበርን?

      በ66 እዘአ በሴስቲየስ ጋለስ የሚመራው የሮማ ሠራዊት የአይሁዳውያንን ዓማፂ ኃይሎች መክቶ ወደ ኢየሩሳሌም እያሳደደ ካባረራቸው በኋላ መውጫ አሳጣቸው። ሮማውያን ከተማዋ ውስጥ ሳይቀር ገፍተው በመግባት እስከ ቤተ መቅደሱ ቅጥር ድረስ ገሰገሱ። ይሁን እንጂ ጋለስ ለሠራዊቱ በጣም ግራ የሚያጋባ ትእዛዝ አስተላለፈ። ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አዘዛቸው! ይህ ሁኔታ ያስፈነደቃቸው አይሁዳውያን ወታደሮች የሸሹትን ሮማውያን ጠላቶቻቸውን እያሳደዱ ወጓቸው። አዎን፣ ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረለት ማምለጫ መንገድ ተከፈተ። እውነተኛ ክርስቲያኖች የእርሱን ማስጠንቀቂያ በመስማት ከኢየሩሳሌም ወጡ። እንዲህ ማድረጋቸው ጥበብ ነበር፤ ምክንያቱም ልክ ከአራት ዓመታት በኋላ የሮማ ሠራዊት በጄነራል ቲቶ እየተመራ እንደገና መጣ። በዚህ ጊዜ ለማምለጥ መሞከር የማይታሰብ ነበር።

      የሮማ ሠራዊት እንደገና ኢየሩሳሌምን ከበበ፤ በዙሪያዋም ቅጥር ቀጠረ። ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን አስመልክቶ “ወራት ይመጣብሻልና፣ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል” ሲል ትንቢት ተናግሮ ነበር።a (ሉቃስ 19:​43) ወዲያው ኢየሩሳሌም ተያዘች፤ ክብራማው ቤተ መቅደስ የፍርስራሽ ክምር ሆነ። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት አንድ በአንድ ፍጻሜያቸውን አገኙ!

      ይሁን እንጂ ኢየሱስ በአእምሮው በኢየሩሳሌም ላይ ከሚመጣው ጥፋት የበለጠ ነገር ይዞ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ መገኘቱን የሚጠቁሙ ምልክቶችን ጭምር እንዲሰጣቸው ጠይቀውት ነበር። በወቅቱ ባይገነዘቡትም ይህ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ የሚቀመጥበትን ጊዜ የሚያመለክት ነበር። ኢየሱስ ምን ነገሮች እንደሚፈጸሙ ተንብዮአል?

      በመጨረሻው ዘመን ጦርነት ይሆናል

      ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፣ ማርቆስ ምዕራፍ 13 እንዲሁም ሉቃስ ምዕራፍ 21ን ብታነብ ኢየሱስ ይናገር የነበረው ስለ እኛ ዘመን እንደሆነ የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ ታገኛለህ። ጦርነት እንደሚከሰት ተናግሯል፤ ይህም ጦርነት የሰውን ልጅ ታሪክ ሲያምስ የነበረው ዓይነት ‘ጦርና የጦር ወሬ’ ብቻ ሳይሆን ‘ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ’ የሚነሡበት ጦርነት ነው። አዎን፣ ታላቅ ዓለም አቀፍ ጦርነት ነው።​— ማቴዎስ 24:​6-8

      በዚህ በእኛ መቶ ዘመን ጦርነት እንዴት መልኩን እንደለወጠ እስቲ ጥቂት ቆም ብለህ አስብ። ድሮ፣ ጦርነት ማለት ሁለት ተቃራኒ ሕዝቦችን የሚወክሉ ሠራዊቶች ሰይፍ እየተማዘዙና በጠብመንጃ እየተታኮሱ የሚያደርጉት ግጭት ነበር፤ ይህም ቢሆን አሠቃቂ ነበር። ይሁን እንጂ በ1914 ታላቁ ጦርነት ፈነዳ። አንዱ ብሔር ሌላውን እየተከተለ እንደ ባቡር ፉርጎ ተያይዘው ወደሚንቀለቀው እሳት ገቡ፤ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ጦርነት ጀመረ። በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ከርቀት ለመጨረስ የሚያስችሉ አውቶማቲክ የጦር መሣሪያዎች ተሠርተው ነበር። መትረየሶች በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ጥይቶቹን ያርከፈክፉ ጀመር፤ የመርዝ ጋዞችም በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮችን አቃጥለዋል፣ በቁማቸው አሰቃይተዋቸዋል፣ አካለ ጎዶሎ አድረገዋቸዋል እንዲሁም እንደ ቅጠል አርግፈዋቸዋል፤ ታንኮች ትላልቅ ባሩዶቻቸውን እያስወነጨፉ ያለአንዳች ምሕረት የጠላቶቻቸውን ቀጠና ጥሰው ገቡ። አውሮፕላኖችና ሰርጓጅ መርከቦችም የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል፤ ይህ ወደፊት ምን ሊመጣ እንዳለ የሚጠቁም ብቻ ነበር።

      በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሰው ልጅ ሊገምተው ከሚችለው በላይ በጣም አስከፊ የሆኑ ነገሮች ተፈጽመዋል፤ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ከአንደኛው ዓለም ጦርነት እጅግ ልቆ ተገኝቷል። በጠላት ዒላማዎች ላይ ሞትን ከሰማይ የሚያዘንቡ የጦር አውሮፕላኖች የሚነሱባቸው በጣም ግዙፍ የሆኑና ተንሳፋፊ ከተማ የሚመስሉ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ባህሩን አጥለቀለቁት። ሰርጓጅ መርኮቦች የጠላት መርከቦችን እያጋዩ አሰመጧቸው። እያንዳንዳቸው በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ አቶሚክ ቦምቦች ተጣሉ! ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው በእርግጥም ይህን የጦርነት ዘመን ለይተው የሚያመለክቱ ‘የሚያስፈሩ ነገሮች’ ታይተዋል።​— ሉቃስ 21:​11

      ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ጦርነት ረገብ ብሏልን? በፍጹም። በዚህ ባለንባቸው በ1990ዎቹ አሥርተ ዓመታት ሳይቀር በየዓመቱ ቃል በቃል በደርዘን የሚቆጠሩ ጦርነቶች በመደረጋቸው በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች እልቂት ምክንያት ሆነዋል። በጦርነት ይበልጥ በሚጎዱት ወገኖች ረገድም ለውጥ ታይቷል። የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ወታደሮች መሆናቸው ቀርቷል። ዛሬ አብዛኞቹ እንዲያውም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የጦርነት ሰለባዎች ሲቪሎች ናቸው።

      የምልክቱ ሌሎች ገጽታዎች

      ጦርነት ኢየሱስ የጠቀሰው ምልክት አንዱ ዘርፍ ብቻ ነው። ‘የምግብ እጥረትም’ እንደሚኖር አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 24:​7) ምድር መላውን የሰው ልጅ ለመመገብ ከሚያስፈልገው ምግብ በላይ ማምረት ትችላለች ቢባልም፣ የግብርናው ሳይንስ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስም እንዲሁም ወደ የትኛውም የምድር ክፍል ምግብ ለማድረስ የሚያስችል ፈጣንና ቀልጣፋ የማጓጓዣ ዘዴ ቢኖርም ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። ይህ ሁሉ ነገር እያለም በዓለም ላይ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አንድ አምስተኛ የሚሆኑት በየዕለቱ ጦማቸውን ያድራሉ።

      በተጨማሪም ኢየሱስ “በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር” እንደሚሆን ትንቢት ተናግሯል። (ሉቃስ 21:​11) በሌላም በኩል ዘመናችን የተሻለ ሕክምና ያለበት፣ የቴክኖሎጂ ምጥቀት የታየበትና በሰፊው የታወቁትን ብዙ በሽታዎች የሚከላከሉ ክትባቶች የተገኙበት ጊዜ ቢሆንም ወረርሽኞች ይህ ነው የማይባል እልቂት ሲያስከትሉ አይተናል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት እግር የተተካው የኅዳር በሽታ ጦርነቱ ካጠፋው የበለጠ ሕይወት ቀጥፏል። ይህ በሽታ በቀላሉ የሚተላለፍ ከመሆኑ የተነሣ እንደ ኒው ዮርክ ባሉት ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ስላስነጠሱ ብቻ ይቀጡ ወይም ይታሰሩ ነበር! ዛሬ ካንሠርና የልብ ሕመም በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋሉ፤ በእርግጥም ቸነፈር ሆነዋል። የሕክምናው ሳይንስ ይህ ነው የሚባል ማርከሻ ያላገኘለት ኤድስም የሰዎችን ሕይወት እየቀጨ ነው።

      ኢየሱስ ስለ መጨረሻው ቀን ያብራራው በሰፊው ከሚከናወኑ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች አንጻር ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ይበልጥ ያተኮረው በማኅበራዊ ችግሮችና በእጅጉ ተስፋፍተው በሚገኙት ዝንባሌዎች ላይ ነው። ከጻፈው ትንቢት መካከል ከፊሉ እንዲህ ይነበባል:- “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ . . . ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ . . . ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።”​— 2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5

      እነዚህ ቃላት አንተ ከምታውቀው እውነታ ጋር ይስማማሉን? ለአብነት ያህል ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ ኅብረተሰቡ እየተዳከመ የሄደበትን አንዱን ዘርፍ ይኸውም የቤተሰብ ተቋም መፍረክረክን ተመልከት። በፍቺ የሚፈርሱት ቤቶች፣ ድብደባ የሚደርስባቸው ባለ ትዳሮች፣ ግፍ የሚፈጸምባቸው ልጆች፣ እንግልት የሚደርስባቸው አረጋውያን ወላጆች ቁጥር በእጅጉ እያሻቀበ መሄዱ ሰዎች “ፍቅር የሌላቸው፣” “ጨካኞች” አልፎ ተርፎም “ከዳተኞች” እና “መልካም የሆነውን የማይወዱ” እንደሆኑ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው! አዎን፣ ዛሬ እነዚህ ባሕርያት እንደ ወረርሽኝ ሲዛመቱ እያየን ነው።

      በእርግጥ ትንቢት የተነገረው ስለ እኛ ትውልድ ነውን?

      ይሁን እንጂ እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል:- ‘እነዚህ ሁኔታዎች በየዘመኑ የሰውን ልጅ ሲያንገላቱ የኖሩ ነገሮች አይደሉምን? በእነዚህ ጥንታዊ ትንቢቶች ውስጥ የተጠቀሰው እኛ ያለንበት ዘመናዊ ትውልድ እንደሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን?’ ኢየሱስ ስለ እኛ ዘመን አንደተናገረ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ከሦስት አቅጣጫ እንመልከት።

      በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ የተናገራቸው ትንቢቶች ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ በጠፉበት ጊዜ በከፊል የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ቢያገኙም ከዚያም አልፈው ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚናገሩ እንደነበሩ አሳማኝ ማረጋገጫ አለ። ኢየሩሳሌምን ካጠፋው መቅሰፍት በኋላ 30 ዓመታት ቆይቶ ኢየሱስ ለአረጋዊው ሐዋርያ ለዮሐንስ ራእይ ያሳየው ሲሆን ራእዩ አስቀድሞ የተነገረለት ሁኔታ እንደሚከሰት ማለትም ወደፊት በምድር ዙሪያ እልቂት የሚያስከትል ጦርነት፣ ረሃብና ቸነፈር እንደሚመጣ የሚገልጽ ነበር። አዎን፣ እነዚህ አስጨናቂ ሁኔታዎች በአንድ አካባቢ ብቻ ተወስነው የሚቀሩ ሳይሆኑ ‘በምድር’ ዙሪያ የሚታዩ ክስተቶች ናቸው።​— ራእይ 6:​2-8

      በሁለተኛ ደረጃ ኢየሱስ የሰጠው ምልክት አንዳንድ ገጽታዎች በዚህ መቶ ዘመን በጣም ከፍተኛ በሆነ መጠን እየተፈጸሙ ነው። ለምሳሌ ያህል ከ1914 ወዲህ ከተደረጉት ጦርነቶች የከፋ ጦርነት ሊኖር ይችላልን? በየአቅጣጫው መሣሪያቸውን የደገኑ የኑክሌር ባለቤት አገሮች ባሉበት በአሁኑ ጊዜ ሦስተኛ የዓለም ጦርነት ቢካሄድ ኖሮ ይህች ምድር በእሳት በጋየችና የሰው ዘርም ከምድረ ገጽ በጠፋ ነበር። በተመሳሳይም ራእይ 11:​18 በእነዚህ ቀናት ብሔራት ‘እንደሚቆጡና’ የሰው ልጆችም ‘ምድርን እንደሚያበላሹ’ ተንብዮአል። የአካባቢ ብክለትና እንደዛሬው በዚህች ፕላኔት ላይ የሚኖረውን ሕይወት ስጋት ላይ የጣለበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም! በመሆኑም ይኸኛውም የምልክቱ ገጽታ ቢሆን በከፍተኛ መጠን እየተፈጸመ አለዚያም ወደ መጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ እየተቃረበ እንዳለ ይታያል። የሰው ልጅ ራሱንም ሆነ ይህችን ፕላኔት አስኪያጠፋ ድረስ ጦርነቱና የአካባበቢው ብክለት እንዲሁ እተባባሰ ይቀጥላልን? አይቀጥልም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ምድር የጻድቃን ሰዎች መኖሪያ በመሆን ለዘላለም እንደምትኖር ይናገራል።​— መዝሙር 37:​29፤ ማቴዎስ 5:​5

      በሦስተኛው ደረጃ የመጨረሻው ቀን ምልክቶች ይበልጥ አሳማኝ ሆነው የሚገኙት በጥቅል ሲታዩ ነው። በአጠቃላይ ኢየሱስ በሦስቱ ወንጌሎች ውስጥ የጠቀሳቸውን እንዲሁም በጳውሎስ መልእክቶችና በራእይ ውስጥ የሚገኙትን ገጽታዎች ስንመረምር ምልክቱ በጣም ብዙ ገጽታዎች እንዳሉት እንረዳለን። አንድ ሰው እያንዳንዳቸውን በተናጠል በማየት ተመሳሳይ ችግሮች በሌሎች ዘመናትም ነበሩ ብሎ ሊከራከር ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ሁሉንም አንድ ላይ አጣምረን ከተመለከትናቸው ምንም በማያሻማ መንገድ የሚጠቁሙት አንድን ዘመን ይኸውም የእኛን ዘመን ነው።

      ይሁን እንጂ የዚህ ሁሉ መደምደሚያ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ዘመናችን ተስፋው የጨለመበት እንደሆነ መናገሩ ብቻ ነውን? በፍጹም አይደለም!

      ምሥራች

      ልንዘነጋው ከማይገባን የመጨረሻው ቀን ምልክቶች አንዱ ማቴዎስ 24:​14 ላይ የተጠቀሰው የምልክቱ ገጽታ ሲሆን ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” በዚህ መቶ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች እስካሁን በሰው ዘር ታሪክ ያልታየ ሥራ አከናውነዋል። የይሖዋ አምላክ መንግሥት ምን እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚያስተዳድርና ምን ነገሮችን እንደሚያከናውን የሚገልጸውን መልእክት ተቀብለው በምድር ዙሪያ አዳርሰዋል። ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች ስለዚሁ መልእክት የሚናገሩ ጽሑፎችን በማዘጋጀት ለሰዎች በየቤታቸው ወይም በመንገድ ላይ ወይም በሚሠሩበት ቦታ ባጭሩ በዓለም ዙሪያ በየአገሩ አዳርሰዋል።

      ይህንንም በማድረጋቸው ይህንን ትንቢት አስፈጽመዋል። ይሁን እንጂ ሰዎች ተስፋ እንዲያገኙም ረድተዋል። ኢየሱስ ይህንን መልእክት ‘ምሥራች’ እንጂ “መጥፎ ዜና” ብሎ እንዳልጠራው ልብ በል። ጨለማ በዋጠው በዚህ ዘመን ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ መልእክት ያተኮረው በአምላክ መንግሥት ላይ ሲሆን ይህ መንግሥት ሰላም ወዳድ የሆኑ ሰዎቸ ሁሉ የሚናፍቁትን አንድ ነገር ይኸውም መዳን እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል።

      መዳን ምንድን ነው? አንተስ ልትድን የምትችለው አንዴት ነው? እባክህ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገሩትን የሚቀጥሉትን ርዕሶች ተመልከት።

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a ቲቶ ድል እንደሚቀዳጅ ሳይታለም የተፈታ ነበር። የሆነ ሆኖ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ያሰበው ሳይሳካለት ቀርቷል። በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም የከተማዋ መሪዎች ያላንዳች ግልጽ ምክንያት በግትርነት አሻፈረኝ ብለዋል። ከዚህም ሌላ መጨረሻ ላይ የከተማይቱን ቅጥር ደርምሰው ሲገቡ ቤተ መቅደሱ እንዳይፈርስ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ በእሳት ጋየ! ኢየሱስ በተናገረው ትንቢት ውስጥ ኢየሩሳሌም ሙሉ በሙሉ እንደምትደመሰስና ቤተ መቅደሷም ጨርሶ እንደሚወድም በግልጽ ተቀምጧል።​— ማርቆስ 13:​1, 2

      [በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      ብዙ ሰዎች፣ ዛሬ ሁኔታዎች በጣም አስከፊ የሆኑት ለምንድን ነው? የሰው ልጅ ወዴት እያመራ ይሆን? ለሚሉት የሚያስጨንቁ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይጥራሉ

      [በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      ዛሬ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የጦርነት ሰለባዎች ሲቪሎች ናቸው

      [በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ኢየሱስ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት አንድ በአንድ ፍጻሜውን አግኝቷል

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ