ጥናት 2
ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል
1–5. የአገልግሎት ትምህርት ቤቱ ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት እኛን ለመርዳት ምን ማሠልጠኛ ይሰጣል?
1 አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ በአገልግሎቱ ጥሩ ውጤት እንድናገኝ የሚያሠለጥነን እንዴት ነው? ሥልጠናውን የምናገኘው በድርጅቱ በኩል ነው። በብዙ አገሮች ይህ ሥልጠና የሚጀምረው ማንበብና መጻፍን የመሰለ መሠረታዊ ትምህርት በመስጠት ነው። ማንበብና መጻፍ የቻሉ ሁሉ ቀጥሎ የሚወስዱት እርምጃ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዝግበው መሠልጠን ነው።
2 ይህ ትምህርት ቤት ለአገልግሎት የሚጠቅም ሥልጠና በነፃ ይሰጣል። ጉባኤውንም በሁለት መንገዶች ያገለግላል:- (1) ግለሰብ ተማሪው ልዩ ልዩ ሐሳብ አሰባስቦ፣ አዳብሮና አቀነባብሮ ለሌሎች ሰዎች የማቅረብ ችሎታውን እንዲያሻሽል የሚረዳው የሥልጠና ፕሮግራም ያገኛል። (2) መላው ጉባኤ በየሳምንቱ ከሚቀርበው ፕሮግራም ብዙ ጠቃሚ ትምህርት ያገኛል። በዚህ ትምህርት ቤት አማካኝነት የመላው ጉባኤ መንፈሳዊ ግንዛቤ እንደሚያድግና የአገልግሎት እንቅስቃሴውም እንደሚጨምር የታወቀ ነው።
3 በየአገሩ የሚቀርበው ፕሮግራም የሚዘጋጀው በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ሲሆን በየጊዜው ዓመታዊ ፕሮግራም ይዘጋጃል። የፕሮግራሙ ይዘት በአገሩ በሚነገረው ቋንቋ ወይም ቋንቋዎች በተዘጋጁት ጽሑፎች ላይ የተመካ ነው። ትምህርቱ በአብዛኛው የሚያተኩረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይሆናል።
4 ተማሪዎቹ በየሳምንቱ ጠቃሚ ንግግሮችን ያቀርባሉ። ዋነኛው ንግግር መምሪያ ንግግር ተብሎ ሲጠራ ከሌሎቹ ንግግሮች የበለጠ ረዘም ያለ ጊዜ ይመደብለታል። መላው ጉባኤ ከዚህ ንግግር የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንዲችል ይህ ንግግር የሚሰጠው ጥሩ ችሎታ ላለው ወንድም ነው። ሌሎቹ ንግግሮች አጠር ያሉ ሲሆኑ በፕሮግራሙ ላይ በተገለጸው መሠረት ለወንዶች ወይም ለሴቶች ሊመደቡ ይችላሉ። አጠር ካሉት ንግግሮች አንዱ በአገሩ ፕሮግራም መሠረት የሚቀርብ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ሊሆን ይችላል። ሌሎቹ ንግግሮች የተወሰነ መልእክት የሚያብራሩ ሊሆኑና ለትምህርቱ የሚያመች ከሆነ ተግባራዊ አጠቃቀሙን በሚያሳይ ትዕይንት ሊቀርቡ ይችላሉ። እህቶች የሚያቀርቧቸው ክፍሎች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ ወይም ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርጉ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በኋላ ውይይት ሲያደርጉ ወይም መደበኛ ባልሆነ ምሥክርነት ሰው ሲያነጋግሩ ወይም ከራሳቸው የቤተሰብ አባል ወይም ከሌላ አስፋፊ ጋር ሲነጋገሩ የሚያሳይ ትዕይንት ይኖራቸዋል።
5 እህቶች ብቻ በሚገኙባቸው ትናንሽ ጉባኤዎችም ቢሆን ሙሉው ትምህርት ሊቀርብ ይችላል። እንዴት? መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንደ ሪፖርት አድርጎ በማቅረብ፣ በሁለት እህቶች መካከል በሚደረግ ውይይት አማካኝነት ወይም ትምህርቱ የሚገኝበትን ጽሑፍ በቀጥታ በማንበብ ሊቀርብ ይችላል።
6. የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ምን ዓይነት ብቃቶች እንዲኖሩት ይፈለጋል?
6 የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች። በእያንዳንዱ ጉባኤ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች ይሾማል። ይህ ወንድም ጥሩ ብቃት ያለው አስተማሪ መሆን ይኖርበታል። ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ አብዛኞቹ ተማሪዎች የሚናገሩትን ቋንቋ በሚገባ የሚያውቅ መሆን ይኖርበታል። በአነጋገሩ ዘዴኛና ደግ ሊሆን ይገባዋል። በመንፈሳዊ ሁኔታም “የሸመገለ ሰው” መሆን ይገባዋል። አንተን በተማሪነት መመዝገብ፣ ንግግር እንድትሰጥ መመደብና ገንቢ የሆነ ምክር በደግነት መስጠት እርሱ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ የሚጠቃለሉ ተግባራት ናቸው።
7. ለአንድ ተማሪ የንግግር ምድብ በሚሰጥበት ጊዜ ስለምን ነገሮች ማሰብ ያስፈልገዋል?
7 የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በትምህርት ቤቱ የሚካፈሉትን ተማሪዎች ዝርዝር መዝግቦ ይይዛል። ይህንንም መዝገብ በአብዛኛው የሚጠቀምበት የንግግር ምድብ ለመስጠት ነው። እነዚህ የንግግር ምድቦች አብዛኛውን ጊዜ ንግግሩ ከሚሰጥበት ቀን ሦስት ሳምንት አስቀድሞ በጽሑፍ ይሰጣሉ። ይህ መሆኑም የምታቀርበውን ትምህርት ለመመርመርና ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ እንድታገኝ ያስችልሃል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በጉባኤ ውስጥ በትምህርት ደረጃቸው የሚለያዩ ሰዎች እንዳሉ ግምት ውስጥ ያስገባል። የተለያዩ መሆናቸውን ይገነዘባል። በዚህም ምክንያት ንግግሮቹን በሚመድብበት ጊዜ ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገባል። አነስተኛ ዕድሜ ያለው ሰው ሊያቀርብ የሚያዳግተውን መልዕክት ለትንሽ ልጅ አይሰጥም። እያንዳንዱ ተማሪ በፕሮግራሙ ውስጥ እኩል እንዲካፈል ለማድረግ ይጥራል።
8. ተማሪ ተናጋሪዎች የተመደበላቸውን ጊዜ ሲጨርሱ ምልክት የሚሰጠው ለምንድን ነው?
8 ትምህርት ቤቱ በሚካሄድበት ጊዜም የፕሮግራሙ ሰዓት መጠበቅ ይኖርበታል። በዚህም ምክንያት የአንድ ተማሪ ንግግር ከተመደበለት ጊዜ ሲያሳልፍ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ወይም የእርሱ ረዳት ምልክት ይሰጣል። በዚህ ጊዜ ተማሪው መናገር የጀመረውን አረፍተ ነገር ጨርሶ መድረኩን መልቀቅ ይኖርበታል።
9–12. የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ንግግር የሚሰጡትም ሆኑ በጉባኤው ውስጥ ያሉ በሙሉ እድገት እንዲያሳዩ ከልብ የሚፈልግ መሆኑን በምን መንገዶች ሊያሳይ ይችላል?
9 የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች መላው ጉባኤ እያዳመጠ ለእያንዳንዱ ተማሪ ምክር ይሰጣል። ይህም የሆነው ከተናጋሪው በተጨማሪ ሌሎች አድማጮችም ከሚሰጠው ምክር ሊጠቀሙ ስለሚችሉ ነው። ሁልጊዜም ቢሆን ማመስገን ይገባል። እንዲያውም ምክር ሰጪው ሊያበረታታህ ከልቡ ይፈልጋል። በምክር መስጫ ቅጹ ላይ በተዘረዘሩትና እንድትሠራበት አስቀድሞ በተነገረህ የተወሰነ ነጥብ ላይ ምክር ይሰጣል። (በጥናት 20 ላይ የሚገኘውን ዝርዝር ተመልከት።) የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በተማሪነትህ ምን ችግር እንዳለብህ ለማወቅ ብርቱ ጥረት ያደርጋል። አስፈላጊውን መሻሻል እንድታሳይም ከልቡ ይፈልጋል።
10 በተጨማሪም እያንዳንዱ የትምህርት ቤቱ ስብሰባ በጉባኤው ውስጥ ላሉት ሁሉ በረከት የሚያስገኝ እንዲሆን ብርቱ ጉጉት አለው። በሚቻልህ ሁሉ በትምህርት ቤቱ እንድትካፈልና በቃል ዘወትር በሚደረገው ክለሣ ላይ ሐሳብ እንድትሰጥ እንዲሁም በየወቅቱ በሚቀርበው የጽሑፍ ክለሳ ጊዜ እንድትሳተፍ ያበረታታሃል። በትምህርት ቤቱ ለመካፈል አልተመዘገብክ እንደሆነ በሚቸግርህ ሁሉ በመርዳትና አንተም ውጤታማ በሆነ መንገድ ይሖዋን የምታወድስ የምትሆንበትን መንገድ በማሳየት እንድትመዘገብ ያበረታታሃል።
11 በተጨማሪም የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች የተሰጠህን ንግግር በማዘጋጀት ረገድ ችግር ቢያጋጥምህ ሊረዳህ ዝግጁ ነው። አመቺ ከሆነም እቤትህ ድረስ መጥቶ ይጠይቅሃል። ለዚህ ጉዳይ የሚያውለው በቂ ጊዜ ከሌለውም የጎለመሱ ወንድሞችና ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው ተናጋሪዎች እንዲረዱህ ይጠይቃቸዋል። ወላጆችም ይህን የመሰለውን እርዳታ ለልጆቻችሁ በመስጠት ልትረዱት ትችላላችሁ። ንግግሩን ባትዘጋጁላቸውም ማድረግ ስለሚኖርባቸው ጥናትና ዝግጅት ሐሳብና መመሪያ ልትሰጧቸው ትችላላችሁ። አዲስ አስፋፊ ለመስክ አገልግሎት በማሰልጠን ላይ ካላችሁ ይህንኑ አስፋፊ በአገልግሎት ትምህርት ቤት የተሰጠውን ንግግር እንዲዘጋጅ እንድትረዱት ልትጠየቁ ትችላላችሁ።
12 በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የሚገኘውን የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ቤተ መጻሕፍት የሚቆጣጠረው የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ነው። አዳዲስ ሰዎች በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ተከማችቶ ከሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዴት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ለማሳየትና ለማለማመድ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ተማሪዎችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች በቀላሉ ሊያገኟቸው እንዲችሉ በቅርቡ የወጡትን የማኅበሩን ጽሑፎችና ሌሎች ጠቃሚ የምርምር ጽሑፎች በሙሉ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ እንዲገኙ ለማድረግ የተቻለውን ጥረት ያደርጋል።
13–17. ተማሪዎች የሚያደርጉትን እድገትና መሻሻል ሌሎች ሰዎች በቶሎ የሚያስተውሉት እንዴት ነው?
13 ተማሪዎቹ የሚያገኟቸው ጥቅሞች። በትምህርት ቤቱ ውስጥ የንግግር ምድብ ሲሰጥህ ምድቡ በቀጥታ ከይሖዋ ድርጅት እንደመጣልህ መብት አድርገህ በማየት በጉጉት ተቀበለው። የሚሰጥህንም ምክር በትሕትና ተቀብለህ በሥራ አውለው። ምክር ሰጪው የሚሰጥህን ሐሳብ በዕለታዊ ንግግርህም ሆነ በአገልግሎትህ በሥራ ላይ ልታውል ትችላለህ። በዚህ ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ትምህርት ለመማርና በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ብታደርግ ብዙ ጥቅም ታገኛለህ።
14 በዚህ ትምህርት ቤት ፕሮግራሞች በንቃት የሚካፈሉ ሁሉ በስብሰባዎች ላይ የሚሰጡአቸው ሐሳቦች በጣም እንደተሻሻሉላቸውና በመስክ አገልግሎት የሚያደርጉት ተሳትፎም በጣም ውጤታማ እንደሆነላቸው ተገንዝበዋል። በተጨማሪም ይህ ትምህርት ቤት በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል የሚያቀርቡ ወይም የሕዝብ ንግግር የሚሰጡ ወንድ ተማሪዎች አድማጮችን የሚያነቃቃና የሚገፋፋ ንግግር ለመስጠት የሚችሉበትን ብቃት ያስገኝላቸዋል። ብዙዎች ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም ማሠልጠኛ በማግኘታቸው ምክንያት ስለ እምነታቸው በፍርድ ቤቶችና በገዥዎች ፊት በጥሩ ሁኔታ መልስ ለመስጠት ችለዋል። ሌሎችም በትምህርት ቤቶችና በማኅበራዊ ስብሰባዎች ላይ ለመናገር ችለዋል።
15 በተጨማሪም አንድ ተማሪ ባቀረባቸው የተማሪ ንግግሮች ላይ የተሰጡትን ምክሮች በዕለታዊ ንግግሩ ላይ ሲጠቀምባቸው ሥር ሰድደው የነበሩ መጥፎ የንግግር ልማዶች ከጊዜ በኋላ ሲወገዱ ይመለከታል። በይሖዋ ምሥክርነታችን የምናገኘው ሥልጠና ብዙ ሳይቆይ በሥራ ቦታችን፣ በትምህርት ቤታችን ወይም በሌላ በማንኛውም ቦታ መስተዋል ይጀምራል። አንድ ዕውቅ የሆነ ጋዜጣ እንደገለጸው “አዲስ ምሥክሮች በጥቂት ወራት ውስጥ ሌሎች ክርስቲያኖች ዕድሜያቸውን በሙሉ ያላጠኑትን ያህል መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ያጠናሉ። ሁሉም የተዋጣላቸው ተናጋሪዎችና አንደበተ ርቱዕ መሆናቸው በአጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም።”
16 በጉባኤው ውስጥ ያለነው በሙሉ በአገልግሎት ምን ያህል እድገት በማሳየት ላይ መሆናችንን ለማወቅ እንድንችል የየራሳችን ግብ ቢኖረን ጥሩ ነው። ይህም ያወጣነው ግብ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከምናሳየው እድገት ጋር በቅርብ የተሳሰረ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመላልሰህ ለመጠየቅና ጥያቄያቸውን ለመመለስ ብቃት እንደሌለህ ይሰማሃልን? በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡት ትምህርቶችና ትዕይንቶች በአብዛኛው እንደነዚህ ላሉ ሁኔታዎች የሚጠቅሙ ናቸው።
17 ከትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት ከተፈለገ ትምህርት ቤቱ እንዲሁ ለ45 ደቂቃ እንደሚደረግ ሳምንታዊ ስብሰባ ብቻ መታየት የለበትም። ትጉህ ተማሪ ከሆንክ ሙሉውን ፕሮግራም እቤትህ ተዘጋጅተህና አጥንተህ ትመጣለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቡን ታነባለህ። ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ምርምሮችንም ታደርጋለህ። ንግግር የሚሰጡት ብቻ ሳይሆኑ በስብሰባው ላይ የተገኘነው ሁሉ በየሣምንቱ የሚቀርበውን ትምህርት አስቀድመን ከተዘጋጀን እውቀትና ችሎታ ለማግኘት እንችላለን።
18–20. የግል ችሎታ ማነስ በትምህርት ቤቱ ሙሉ በሙሉ እንዳንካፈል ሊያግደን የማይገባው ለምንድን ነው?
18 ሁሉም የትምህርት ቤቱን ዓላማ በመገንዘብ የሚቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ እናበረታታለን። የእያንዳንዳችን የንግግር ችሎታ ወይም የሌሎች ችግርና ደካማነት የሚታይበት ስብሰባ አይደለም። ከትምህርት ቤቱ የምናገኘው ጥቅም በአብዛኛው የትምህርት ቤቱን እንቅስቃሴዎች በምንከታተልበት ዝንባሌና ዓላማ ላይ የተመካ ነው። ይህ ትምህርት ቤት ይሖዋ የሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም አንዱ ክፍል ነው። ለራሱ ዓላማ የሚያሠለጥነንና የሚያስተምረንም እርሱ ነው። ሰዎችን ለማስደሰት ወይም ሰዎች ያወጡትን የንግግርና የማስተማር ብቃት ለማሟላት የምንጥር ስላልሆንን ማንኛውም ተማሪ ሌሎች ምን ይሉኛል ብሎ መጨነቅ የለበትም። በአገልግሎት እንቅስቃሴያችን ለማግኘት የምንፈልገው የይሖዋን ሞገስና በረከት ነው።
19 እውነት ነው፣ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች እንደ ሙሴ “ቀድሞም ሆነ አሁን አንተ ከእኔ ጋር መነጋገር ከጀመርህበት ጊዜ አንስቶ የንግግር ችሎታ የለኝም” ሊሉ ይችላሉ። (ዘጸ. 4:10 አዓት) ይሁን እንጂ ለአምላክ የሚሳነው ነገር እንደሌለ ካመንህ ይህን መጀመሪያ ላይ የተሰማህን ስሜት ልታሸንፍ ትችላለህ። (ማቴ. 19:26) በተጨማሪም የሕይወትን ቃል በመናገር ረገድ ያሳየኸው እድገት ካለ ያንን እድገት ለማግኘት ያደረግኸው ጥረት ሁሉ አለዋጋ የቀረ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልግሃል። በጣም አነስተኛ እድገት ቢሆንም እንኳ አንድን ሰው ወደ ሕይወት ሊያመጣ ይችል ይሆናል። ታዲያ ይህ ብቻውን በጣም የሚያስደስት ነገር አይሆንምን?
20 የቲኦክራሲያዊው የአገልግሎት ትምህርት ቤት ቀዳሚ ዓላማ ሰዎችን ለአገልግሎት ማሠልጠን ነው። አዘውትረው በዚህ ትምህርት ቤት ከሚገኙትና ሙሉ ጥቅሙን ከሚያገኙት እጅግ ብዙ ሰዎች መካከል እንድትሆንና ለመሻሻል የምታደርገው ጥረት ይሖዋ ሲባርከው እንድትመለከት ከልባችን እንመኛለን። — ፊልጵ. 3:16