የ2015 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል ይረዳናል
መዝሙራዊው ዳዊት “መጠጊያዬና አዳኜ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፌ ቃልና የልቤ ሐሳብ፣ በፊትህ ያማረ ይሁን” በማለት ጽፏል። (መዝ. 19:14) እኛም ቃላችን ይሖዋን ደስ የሚያሰኘው እንዲሆን እንፈልጋለን፤ ምክንያቱም በጉባኤም ሆነ በአገልግሎት እውነትን ለሌሎች የመናገር መብታችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ይሖዋ ለአገልግሎት እኛን ከሚያሠለጥንባቸው መንገዶች አንዱ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ነው። ይህ ሥልጠና በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከ111,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ በየሳምንቱ ይሰጣል። ትምህርት ቤቱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ውጤታማ የምሥራቹ አገልጋዮች ብሎም በሚያሳምን መንገድ እንዲሁም በዘዴና በድፍረት በማስተማር ረገድ ብቁ እንዲሆኑ ረድቷል።—ሥራ 19:8፤ ቆላ. 4:6
2 የ2015 የትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ከተለያዩ ጽሑፎች የተወሰዱ ትምህርቶችን ያካተተ ነው። በተጨማሪም ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች እና ለክፍል ቁ. 1 የተመደበው ጊዜ ላይ ማስተካከያ ተደርጓል። እነዚህ ለውጦችና የትምህርት ቤቱ ክፍሎች እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው የሚገልጹት መመሪያዎች ከታች ባሉት አንቀጾች ውስጥ ተዘርዝረዋል።
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች፦ ይህ ክፍል የተሰጣቸው ወንድሞች ከሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ውስጥ ትኩረት የሚሰብና ጠቃሚ የሆነ አንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥብ በሁለት ደቂቃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ጥሩ ዝግጅት ከተደረገ በተመደበው ጊዜ ውስጥ ለጉባኤው አንድ ጠቃሚ ነጥብ ማካፈል ይቻላል። ከዚያም እንደተለመደው ስድስት ደቂቃውን አድማጮች ከሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ትኩረታቸውን የሳበውን ነጥብ በ30 ሴኮንድ ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለመናገር ይጠቀሙበታል። ትርጉም ያለው ሐሳብ በ30 ሴኮንድ ውስጥ ማቅረብ ጥሩ ዝግጅትና ራስን መግዛት ይጠይቃል፤ ያም ቢሆን እንዲህ ማድረግ ጥሩ ሥልጠና ነው። በተጨማሪም ሌሎች ወንድሞች ምርምር ሲያደርጉ ያገኙትን ሐሳብ ለማካፈል የሚያስችል ዕድል እንዲያገኙ ያደርጋል።
4 ክፍል ቁ. 1፦ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የተመደበው ጊዜ ተቀንሶ ክፍሉ በሦስት ደቂቃ ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዲቀርብ ተደርጓል፤ ንባቡም ተቀንሷል። የንባብ ክፍል የሚሰጣቸው ወንድሞች ጮክ ብለው በማንበብ ደጋግመው መለማመድ አለባቸው፤ በዚህ ጊዜ ትምህርቱ እንደገባቸው በሚያሳይ መንገድ ክፍሉን ማቅረብ እንዲችሉ የቃላትን ትክክለኛ አጠራር ለማወቅ እንዲሁም በቅልጥፍና ለማንበብ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ንባብ በአምልኳችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር በመሆኑ ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች ጥሩ አንባቢ ለመሆን ጥረት ማድረግ አለባቸው። አብዛኞቹ ልጆቻችን ጎበዝ አንባቢዎች መሆናቸው በጣም ያስደስተናል! ወላጆችም፣ ልጆቻቸው ጥሩ አንባቢ እንዲሆኑ በመርዳት ረገድ ለሚያደርጉት ልባዊ ጥረት ሊመሰገኑ ይገባል።
5 ክፍል ቁ. 2፦ ይህ ክፍል የሚሰጠው ለእህቶች ሲሆን አምስት ደቂቃ ይወስዳል። ተማሪዋ በፕሮግራሙ ላይ የሚገኘውን ጭብጥ መጠቀም አለባት። ትምህርቱ የተወሰደው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሚገኙ ክፍሎች በሚሆንበት ጊዜ ክፍሉ በአንድ የመስክ አገልግሎት ዘርፍ ላይ የሚያጋጥም የተለመደ ሁኔታን የሚያሳይና ለጉባኤው የአገልግሎት ክልል የሚሠራ መሆን ይኖርበታል። ትምህርቱ የተመሠረተው በተለያዩ ጽሑፎች ላይ በሚገኝ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ላይ በሚሆንበት ወቅት ተማሪዋ፣ ባለታሪኩን አስመልክቶ የተሰጠውን ጽሑፍ በደንብ ማጥናት፣ ክፍሉ ላይ የምትጠቀምባቸውን ተስማሚ ጥቅሶች መምረጥ እንዲሁም ከተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ምን ትምህርት እንደሚገኝ ግልጽ ማድረግ ይኖርባታል። ከጭብጡ ጋር የሚያያዙ ተጨማሪ ጥቅሶች መጠቀም ይቻላል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች አንድ ረዳት ይመድብላታል።
6 ክፍል ቁ. 3፦ ይህ የአምስት ደቂቃ ክፍል ለአንድ ወንድም ወይም ለአንዲት እህት ሊሰጥ ይችላል። ክፍሉ ለአንዲት እህት በሚሰጥበት ጊዜ ለክፍል ቁ. 2 በተሰጠው መመሪያ መሠረት መቅረብ ይኖርበታል። በተለያዩ ጽሑፎች ላይ የተመሠረተው ይህ ክፍል ለአንድ ወንድም በሚሰጥበት ጊዜ አድማጮቹን ግምት ውስጥ በማስገባት በንግግር መልክ ያቀርበዋል። ተማሪው የተሰጠውን ጭብጥ ማዳበር፣ ክፍሉ ላይ የሚጠቀምባቸውን ተስማሚ ጥቅሶች መምረጥ እንዲሁም ከተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ምን ትምህርት እንደምናገኝ ግልጽ ማድረግ ይኖርበታል።
7 ክፍል ቁ. 3 ለወንድሞች በሚሰጥበት ጊዜ፦ ትምህርቱ የተወሰደው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሚገኙ ክፍሎች በሚሆንበት ጊዜ ክፍሉ መቅረብ ያለበት የቤተሰብ ጥናት ሲመራ ወይም ለመስክ አገልግሎት ልምምድ ሲደረግ በሚያሳይ መንገድ መሆን አለበት። ረዳት የሚሆነውን ሰውና መቼቱን የሚመርጠው በአብዛኛው የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ነው። ረዳት ሆኖ የሚመደበው፣ የተማሪው ቤተሰብ አባል ወይም በጉባኤው ውስጥ ያለ ሌላ ወንድም መሆን ይኖርበታል። ከጭብጡ ጋር የሚያያዙና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ጎላ አድርገው የሚገልጹ ተጨማሪ ጥቅሶችን መጠቀም ይቻላል። አልፎ አልፎ ይህ ክፍል ለጉባኤ ሽማግሌዎችም ሊሰጥ ይችላል። ሽማግሌው፣ ረዳቱንና መቼቱን ራሱ መምረጥ ይችላል። ሽማግሌዎች ከቤተሰባቸው አባል ወይም ከሌላ ወንድም ጋር በሚያደርጉት ውይይት የማስተማር ጥበብን ሲጠቀሙ ማየት ጉባኤውን እንደሚያበረታታ ምንም ጥርጥር የለውም።
8 ምክር፦ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች እያንዳንዱ ክፍል ከቀረበ በኋላ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ተማሪውን ያመሰግነዋል፤ እንዲሁም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም በተባለው መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ገንቢ ምክር ይሰጠዋል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ክፍሉን ሲያስተዋውቅ ተማሪው የሚሠራበትን ምክር መስጫ ነጥብ አይናገርም። ተማሪው ክፍሉን አቅርቦ ሲጨርስ ከልብ ካመሰገነው በኋላ ለተማሪው የተሰጠውን ምክር መስጫ ነጥብ መናገር ይኖርበታል፤ ከዚያም ተማሪው ነጥቡን በጥሩ መንገድ ሠርቶበታል ያለበትን ምክንያት ለይቶ መናገር ወይም ተማሪው ይህን ነጥብ በሌላ ጊዜ ይበልጥ ቢሠራበት ሊጠቀም የሚችለው እንዴት እንደሆነ በደግነት መግለጽ ይኖርበታል።
9 የተማሪው ምክር መስጫ ቅጽ በመማሪያ መጽሐፉ ከገጽ 79 እስከ 81 ላይ ይገኛል። ተማሪው ክፍሉን ካቀረበ በኋላ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በተማሪው መጽሐፍ ላይ ተገቢውን ምልክት ያደርግለታል፤ እንዲሁም በምክር መስጫው ላይ የሚገኘውን መልመጃ ሠርቶበት እንደሆነ በግል ይጠይቀዋል። ከስብሰባ በኋላ ወይም በሌላ ጊዜ ምስጋና እና ተጨማሪ ጠቃሚ ሐሳብ ሊያካፍለው ይችላል። እያንዳንዱ ተማሪ በትምህርት ቤቱ የሚያገኘውን ልዩ ትኩረት በመንፈሳዊ እድገት ለማድረግ እንደሚያስችለው አጋጣሚ አድርጎ ሊመለከተው ይገባል።—1 ጢሞ. 4:15
10 ተማሪዎች ሰዓት ካሳለፉ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ወይም የእሱ ረዳት ምልክት መስጠት ይኖርበታል፤ ለምሳሌ ደወል በመጠቀም ወይም በማንኳኳት ለተማሪው የተሰጠው ሰዓት ማለቁን በዘዴ መጠቆም ይቻላል። ተማሪው ይህን ምልክት እንደሰማ የጀመረውን ዓረፍተ ነገር ጨርሶ ከመድረክ መውረድ ይኖርበታል።—የአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፍ ገጽ 282 አን. 4ን ተመልከት።
11 ብቃቶቹን የሚያሟሉ ሁሉ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እንዲመዘገቡ ይበረታታሉ። (የአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፍ ገጽ 282 አን. 6ን ተመልከት።) ከዚህ ትምህርት ቤት የሚገኘው ሥልጠና የይሖዋ ሕዝቦች የመንግሥቱን ምሥራች በልበ ሙሉነት፣ ክብር ባለው መንገድና በፍቅር ለመስበክና ለማስተማር አስችሏቸዋል። ይሖዋ ከቲኦክራሲያዊ ሥልጠና ጥቅም ያገኙ ሁሉ እሱን ሲያወድሱት ማየት እንደሚያስደስተው ምንም ጥያቄ የለውም!—መዝ. 148:12, 13፤ ኢሳ. 50:4
ምክር በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ እድገት አድርጉ