የማሳመን ችሎታ ተጠቅሞ የሰዎችን ልብ መንካት
ብዙ ሰዎች “ማሳመን” ተብሎ ለተተረጎመው ፐርሱዌዥን ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ያላቸው አመለካከት አሉታዊ ነው። ይህ ቃል ዕቃው እንዲሸጥለት የሚያግባባን አሻሻጭ ወይም ተጠቃሚውን ክፍል ለማታለልና መጠቀሚያ ለማድረግ ተብሎ የተዘጋጀን ማስታወቂያ የሚያስታውሳቸው ሰዎች ይኖራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ሳይቀር ማሳመን የሚለው ሐሳብ መበከል ወይም ከመስመር ማስወጣት በሚል አሉታዊ ስሜት በሚያስተላልፍ መልኩ ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች “በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል [ፐርሱዌዥን] ከሚጠራችሁ አልወጣም” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 5:7, 8) በተጨማሪም ጳውሎስ የቆላስይስ ሰዎች ማንም ሰው ‘በሚያባብል ቃል እንዳያስታቸው’ አስጠንቅቋቸዋል። (ቆላስይስ 2:4) እንዲህ ዓይነቱ ማባበል እውነተኛ መሠረት የሌላቸውን ነገሮች አቀነባብሮ ማቅረብ ነው።
ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤው ላይ ማሳመን የሚለውን ሐሳብ ለየት ባለ መንገድ ተጠቅሞበታል። “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት [“እንድታምን በተደረግህበት፣” NW] ነገር ጸንተህ ኑር፣ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:14) ጢሞቴዎስ ‘እንዲያምን ተደረገ’ ማለት ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ያስተማሩት እናቱና አያቱ አግባብቶ ያልፈለገውን ነገር እንዲያምን አደረጉት ማለት አልነበረም።—2 ጢሞቴዎስ 1:5a
ጳውሎስ በሮም በቁም እስር ላይ በነበረበት ጊዜ ለብዙ ሰዎች የተሟላ ምሥክርነት በመስጠት “ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው [“እያሳመናቸው፣” NW]፣ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር።” (ሥራ 28:23) ጳውሎስ አድማጮቹን እያታለለ ነበርን? በፍጹም! በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ማሳመን ሁልጊዜ ስህተት ነው ሊባል አይችልም።
“ማሳመን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አዎንታዊ በሆነ መልኩ ሲሠራበት ነገሩን እንዲቀበለው ማድረግ፣ አእምሮን የሚያረካና ምክንያታዊ መረጃ በማቅረብ ማስረዳት የሚል ትርጉም አለው። በዚህ መንገድ አንድ አስተማሪ ሌሎች በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ የጸና እምነት እንዲኖራቸው ሲል በማሳመን ችሎታ ተጠቅሞ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ያለው ሐሳብ ያቀርባል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) እንዲያውም ይህ የጳውሎስ አገልግሎት ተለይቶ የሚታወቅበት ባሕርይ ነበር። ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ስህተት ናቸው ብሎ ያምን የነበረው አንጥረኛው ድሜጥሮስ እንኳን ሳይቀር “ይህም ጳውሎስ በእጅ የተሠሩት አማልክት አይደሉም ብሎ፣ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና [“እንዳሳመነና፣” NW] እንደ አሳተ” ተናግሯል።—ሥራ 19:26
በአገልግሎት የማሳመን ችሎታን መጠቀም
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን እንደሚከተለው በማለት አዝዟል:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ትእዛዝ በመፈጸም ላይ ናቸው። በ1997 ባሳለፉት የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ በየወሩ በአማካይ 4,552,589 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርተዋል።
የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመምራት መብት አግኝተህ ከሆነ የማሳመን ችሎታ እንድትጠቀም የሚያስገድዱህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥምህ ልትጠብቅ ትችል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል በሚቀጥለው የጥናት ክፍለ ጊዜ ላይ ሥላሴን በሚመለከት ጥያቄ ተነሣ እንበል። ተማሪህ በዚህ መሠረተ ትምህርት እንደሚያምን የምታውቅ ከሆነ ምን ታደርጋለህ? ስለ ጉዳዩ የሚያብራራ ጽሑፍ ልትሰጠው ትችላለህ። ካነበበው በኋላ እግዚአብሔር ኢየሱስ ማለት እንዳልሆነ ማመኑን ትገነዘብ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ካሉት እንዴት መቀጠል ትችላለህ?
በጥንቃቄ አዳምጥ። ይህ ተማሪህ በአንድ ጉዳይ ላይ ምን ብሎ እንደሚያምን ሊያስገነዝብህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ተማሪህ “በሥላሴ አምናለሁ” ቢልህ ይህን መሠረተ ትምህርት ለማፍረስ ወዲያውኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ልትጀምር ትችላለህ። ነገር ግን ሰዎች ለሥላሴ የሚሰጡት ትርጉም ይለያያል። ተማሪህ የሚያምነው አንተ ለሥላሴ መሠረተ ትምህርት ከምትሰጠው ትርጉም ፍጹም የተለየ ሊሆን ይችላል። እንደ ሪኢንካርኔሽን፣ የነፍስ አለመሞትና መዳን የመሳሰሉትን ሌሎች እምነቶችም በሚመለከት ሁኔታው ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ከመናገርህ በፊት በጥንቃቄ አዳምጥ። ተማሪው ስለሚያምነው ነገር ግምታዊ የሆነ ነገር አትናገር።—ምሳሌ 18:13
ጥያቄዎችን ጠይቅ። ይህ እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች ሊጨምር ይችላል:- ‘ከድሮም ጀምሮ በሥላሴ ታምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚል ለማወቅ ጥልቅ ጥናት አድርገሃል? እግዚአብሔር የሥላሴ ክፍል ከሆነ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽና በቀጥታ ሊነግረን አይገባም ነበር?’ ተማሪውን በምታስተምርበት ጊዜ በየጊዜው ቆም እያልክ እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች ጠይቅ:- ‘እስከ አሁን የተወያየንበት ነገር ምክንያታዊ ይመስልሃል?’ ‘በዚህ ማብራሪያ ትስማማለህ?’ ጥያቄዎችን በጥበብ በመጠቀም ተማሪው በመማሩ ሒደት ውስጥ እንዲሳተፍ ታደርገዋለህ። አንተ ስለ አንድ ጉዳይ ማብራሪያ ስትሰጥ እሱ አድማጭ ብቻ ሊሆን አይገባም።
አሳማኝ ምክንያት አቅርብ። ለምሳሌ ያህል ስለ ሥላሴ መሠረተ ትምህርት ስትወያይ ተማሪህን እንዲህ ልትለው ትችላለህ:- ‘ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፣ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰምቶ ነበር። ምድር ላይ ሆኖ እየተጠመቀ ያለው አምላክ ቢሆን ኖሮ ድምፁን ወደ ሰማይ ልኮ በምድር ላይ ያሉት እንዲሰሙት ሲል ወደ ምድር ተመልሶ እንዲመጣ ያደርግ ነበርን? ይህ ማታለል አይሆንም? “የማይዋሽ” አምላክ እንዲህ ያለውን የማታለል ተግባር ይፈጽማል?’—ሉቃስ 3:21, 22፤ ቲቶ 1:1, 2
በዘዴ የቀረበ አሳማኝ ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ውጤታማ ይሆናል። ባርባራ ብለን የምንጠራትን የአንዲትን ሴት ምሳሌ ተመልከት። በሕይወት ዘመኗ በሙሉ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል እንደሆነ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ሦስተኛ አካል የሆነለት የሥላሴ ክፍል እንደሆነ ታምን ነበር። ነገር ግን አንድ የይሖዋ ምሥክር እግዚአብሔርና ኢየሱስ ሁለት የተለያዩ አካላት መሆናቸውን ነገራት። ለተናገረውም ነገር ድጋፍ የሚሆን ሐሳብ ከቅዱሳን ጽሑፎች አሳያት።b ባርባራ መጽሐፍ ቅዱስን ልታስተባብል አልቻለችም። የዚያኑ ያህል ደግሞ አዘነች። ለሥላሴ መሠረተ ትምህርት ከፍተኛ ግምት ነበራት።
ምሥክሩ በርጋታና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ባርባራን አስረዳት። “ሁለት ሰዎች እኩል መሆናቸውን ልታስተምሪኝ ብትፈልጊ የትኛውን የቤተሰብ ዝምድና በምሳሌነት ትጠቀሚያለሽ?” ሲል ጠየቃት። ለትንሽ ጊዜ አሰብ ካደረገች በኋላ “የሁለት ወንድማማቾችን ምሳሌ እጠቀም ይሆናል” ስትል መለሰች። “ትክክል ነሽ” ሲል ምሥክሩ መለሰላት። “ምናልባትም ተመሳሳይ መንታዎችን ልትጠቀሚ ትችያለሽ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እንደ አባት ራሱን ደግሞ እንደ ልጅ እንድንመለከታቸው ሲያስተምረን ምን መልእክት እያስተላለፈ ነበር?” ባርባራ ፊቷ ፈካ ብሎ “ገባኝ። አንደኛው በዕድሜና በሥልጣን የሚበልጥ መሆኑን እየገለጸ ነበር” ስትል መለሰች።
“አዎን፣ በተለይ ደግሞ የእምነት አባቶች በነበሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያኑ የኢየሱስ አዳማጮች ወደዚህ መደምደሚያ ደርሰው መሆን አለበት” ሲል መለሰላት። ምሥክሩ ነጥቡን ለማጉላት በሚከተለው መደምደሚያ ተጠቀመ:- “እኛ እኩልነትን ለማስተማር የወንድማማቾችን ወይም የተመሳሳይ መንታዎችን ተስማሚ ምሳሌ መጠቀም ከቻልን ታላቅ አስተማሪ የነበረው ኢየሱስም እንዲህ ማድረግ ይችል ነበር። ከዚህ ይልቅ በእሱና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ግንኙነት ለመግለጽ ‘አባት’ እና ‘ልጅ’ በሚሉት ቃላት ተጠቅሟል።”
በመጨረሻ ባርባራ ነጥቡ ስለገባት ተቀበለችው። ምሥክሩ በማሳመን ችሎታ ልቧን መንካት ችሏል።
ስሜታቸውን መረዳት
ሥር የሰደዱ ሃይማኖታዊ እምነቶች ብዙውን ጊዜ ከስሜት ጋር የተዛመዱ ይሆናሉ። አጥባቂ ካቶሊክ የሆነችውን የኤድናን ሁኔታ ተመልከት። በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት የልጅ ልጆችዋ ግልጽ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ በማቅረብ እግዚአብሔር ማለት ኢየሱስ አለመሆኑን አስረዷት። ኤድና የሰማችው ነገር ገብቷታል። ያም ሆኖ በቅንነት ግን ፈርጠም ብላ “በቅዱስ ሥላሴ አምናለሁ” ስትል ተናገረች።
ምናልባት አንተም ተመሳሳይ የሆነ ተሞክሮ አጋጥሞህ ይሆናል። ብዙዎች ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶቻቸውን የማንነታቸው መግለጫ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። እንደነዚህ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማሳመን ድርቅ ያለ ማስረጃ ማቅረብ ወይም የሰውየው አመለካከት ስህተት መሆኑን የሚያሳዩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶችን መደርደር ብቻ አይበቃም። በማሳመን ችሎታ ላይ ርኅራኄ ከታከለበት እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን በተገቢው መንገድ መያዝ ይችላል። (ከሮሜ 12:15 ጋር አወዳድር፤ ቆላስይስ 3:12) እርግጥ ነው አንድ ውጤታማ አስተማሪ ጽኑ እምነት ሊኖረው ይገባል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ “ተረድቼአለሁ” እና “በጌታ በኢየሱስ ሆኜ አውቄአለሁ ተረድቼአለሁም [“እንዳምን ተደርጌያለሁም፣” NW]” በሚሉት ሐረጎች ተጠቅሟል። (ሮሜ 8:38፤ 14:14) ይሁን እንጂ ያመንንበትን ነገር ስንገልጽ ግትሮች ወይም ራሳችንን የምናመጻድቅ ሰዎች እንደሆንን አድርጎ የሚያስገምተን ሊሆን አይገባም። መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን ስናቀርብም የምጸት ወይም የሌላውን ክብር የሚቀንሱ ቃላት ልንጠቀም አይገባም። ተማሪውን በፍጹም ልናስከፋውም ሆነ ልንዘልፈው አንፈልግም።—ምሳሌ 12:18
ተማሪው የሚያምንባቸውን ነገሮችና በእነዚህም የማመን መብቱን ማክበሩ እጅግ ውጤታማ ነው። ቁልፉ ትሕትና ነው። ትሑት የሆነ አስተማሪ በተፈጥሮው ከተማሪው እንደሚበልጥ አድርጎ አያስብም። (ሉቃስ 18:9-14፤ ፊልጵስዩስ 2:3, 4) አምላካዊ በሆነ መንገድ ሌሎችን ማሳመን ‘ይሖዋ በደግነት ይህን ነገር እንድገነዘበው ረድቶኛል። ለአንተ ደግሞ ላካፍልህ’ ብሎ በትሕትና መቅረብን ይጨምራል።
ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙት መሰል ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፣ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን።” (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሥር የሰደዱ የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን እንዲሁም አምላክን የማያስደስቱ ልማዶችንና ባሕርያትን ከሥራቸው ነቅለው ለመጣል በአምላክ ቃል ይጠቀማሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ምሥክሮቹ ይህን ሲያደርጉ ይሖዋ እነርሱን በፍቅር እንደታገሣቸው ያስታውሳሉ። ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በማግኘታቸውና የሐሰት ትምህርቶችን መንግሎ ለመጣልና በማሳመን ችሎታ አማካኝነት ልብን ለመንካት በዚህ ኃይለኛ መሣሪያ ለመጠቀም በመቻላቸው ምንኛ ደስተኞች ናቸው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ የመጠበቂያ ግንብ እትም ከገጽ 7-9 ላይ የሚገኘውን “ኤውንቄና ሎይድ—በአርዓያነት የሚጠቀሱ አስተማሪዎች” የሚለውን ክፍል ተመልከት።
b ዮሐንስ 14:28ን፤ ፊልጵስዩስ 2:5, 6ን፤ ቆላስይስ 1:13-15ን ተመልከት። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? የሚለውን ብሮሹር ተመልከት።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የተማሪህን ልብ መንካት
◻ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪውን ልብ ለመንካት የሚያስችልህን መመሪያ እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ጸልይ።—ነህምያ 2:4, 5፤ ኢሳይያስ 50:4
◻ ተማሪው ምን ብሎ እንደሚያምንና የሚያምነው ሐሰት የሆነው ትምህርት ማራኪ ሆኖ የታየው ለምን እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር።—ሥራ 17:22, 23
◻ የጋራ ነጥባችሁን ሳትለቅ በደግነትና በትዕግሥት ምክንያታዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ መከራከሪያ ነጥቦችን አቅርብ።—ሥራ 17:24-34
◻ የሚቻል ከሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን ውጤታማ በሆኑ ምሳሌዎች አጠናክር።—ማርቆስ 4:33, 34
◻ ተማሪው የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት መቀበሉ ያለውን ጥቅም እንዲገነዘብ እርዳው።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15