የአንባብያን ጥያቄዎች
ኢየሱስ “በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፣ እላችኋለሁና ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ፣ አይችሉምም” ሲል አጥብቆ መክሯል። (ሉቃስ 13:24) እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? በዛሬው ጊዜስ የሚሠራው እንዴት ነው?
ይህን ምንባብ በተሻለ መንገድ መረዳት የምንችለው የተነገረበትን ጊዜ መለስ ብለን ስንመረምር ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ ከስድስት ወራት ያህል ጊዜ በፊት ቤተ መቅደሱ በድጋሚ የተመረቀበት ቀን በሚከበርበት ወቅት በኢየሩሳሌም ተገኝቶ ነበር። በዚህ ጊዜ እርሱ የአምላክ በጎች እረኛ መሆኑን ተናግሯል። ይሁን እንጂ አይሁዳውያን ለመስማት አሻፈረኝ በማለታቸው ከእነዚህ በጎች መካከል እንደማይቆጠሩ አመልክቷል። ከአባቱ ጋር “አንድ” መሆኑን በተናገረ ጊዜ አይሁዳውያን ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ። አምልጧቸው ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ፍርግያ ሄደ።—ዮሐንስ 10:1-40
በዚህ ቦታ አንድ ሰው “ጌታ ሆይ፣ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?” ብሎ ጠየቀው። (ሉቃስ 13:23) በተለይ በዚያ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን የመዳን ብቃት የሚያገኙት ጥቂቶች ብቻ እንደሚሆኑ ያምኑ ስለነበረ ይህ ተገቢ ጥያቄ ነበር። በእነርሱ አመለካከት እነዚህ የሚድኑ ጥቂት ሰዎች እነማን ይሆናሉ ብለው ያስቡ እንደነበረ መገመት አያቅትም። ቀጥሎ የደረሱት ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት ምንኛ ስህተት ላይ ወድቀው ነበር!
ኢየሱስ ሁለት ዓመት ለሚያክል ጊዜ በእነርሱ መካከል ሆኖ ሲያስተምር፣ ተአምራት ሲያደርግና የሰማያዊው መንግሥት ወራሾች የመሆንን አጋጣሚ ሲዘረጋላቸው ቆይቷል። ግን ውጤቱ ምን ሆነ? እነርሱም ሆኑ በተለይም ደግሞ መሪዎቻቸው የአብርሃም ዘሮችና የአምላክ ሕግ በአደራ የተሰጣቸው በመሆኑ ይኩራሩ ነበር። (ማቴዎስ 23:2፤ ዮሐንስ 8:31-44) ይሁን እንጂ የመልካሙን እረኛ ድምፅ ሰምተው ምላሽ አልሰጡም። በፊታቸው የመንግሥቱ አባሎች የመሆን ታላቅ ሽልማት የሚያስገኝ በር ተከፍቶላቸው ነበር። እነርሱ ግን በበሩ ለመግባት አሻፈረኝ አሉ። የኢየሱስን የእውነት መልእክት ሰምተው የተቀበሉትና ከእርሱም ጋር የጸኑት በአብዛኛው ከዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል የሆኑ ጥቂት አይሁዳውያን ብቻ ነበሩ።—ሉቃስ 22:28-30፤ ዮሐንስ 7:47-49
በ33 እዘአ በዋለው በጰንጠቆስጤ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ለመቀባት ዝግጁ ሆነው የተገኙት እነዚሁ ነበሩ። (ሥራ 2:1-38) ኢየሱስ ዓመፀኞች ብሎ ከጠራቸውና በተከፈተላቸው አጋጣሚ ሳይጠቀሙ በመቅረታቸው ከሚያለቅሱትና ጥርሳቸውን ከሚያፋጩት መካከል አልሆኑም።—ሉቃስ 13:27, 28
በዚህም መሠረት በመጀመሪያው መቶ ዘመን “ብዙዎች” የተባሉት አይሁዳውያን በአጠቃላይ በተለይም የሃይማኖት መሪዎች ነበሩ። እነዚህ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። ሆኖም ይህን የሚያደርጉት ራሳቸው ባወጡት መሥፈርትና መንገድ እንጂ አምላክ ባወጣው መሥፈርት ወይም መንገድ አይደለም። በተቃራኒው ደግሞ የመንግሥቱ ክፍል ለመሆን በቅን ልቦና ምላሽ የሰጡት በአንጻራዊ ሁኔታ “ጥቂቶች” የተባሉት የክርስቲያን ጉባኤ ቅቡዕ አባላት ሆነዋል።
አሁን ደግሞ ጥቅሱ በዘመናችን የሚኖረውን ሰፊ ፍጻሜ እንመልከት። በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የሚሰበሰቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ተምረዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ምኞት በቅዱሳን ጽሑፎች ትክክለኛ ትምህርት ላይ የተመሠረተ አይደለም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩ አይሁዳውያን እነዚህም የአምላክን ሞገስ በራሳቸው መንገድ ማግኘት ይፈልጋሉ።
በጊዜያችንም ለመንግሥቱ መልእክት በትሕትና ምላሽ የሰጡና ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ እንዲሁም የርሱን ሞገስ ያገኙ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂት ሰዎች አሉ። እነዚህም “የመንግሥት ልጆች” ለመባል በቅተዋል። (ማቴዎስ 13:38) እነዚህን ቅቡዕ “ልጆች” መጥራት የተጀመረው በ33 በጴንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ ነው። አምላክ ከሕዝቦቹ ጋር የነበረው ግንኙነት እንደሚያሳየው ለሰማያዊ ሕይወት ይደረግ የነበረው አጠቃላይ ግብዣ በአሁኑ ጊዜ እንደቆመ የይሖዋ ምሥክሮች ከረዥም ጊዜ በፊት ሲናገሩ ቆይተዋል። በቅርብ ዓመታት እውነትን ያወቁ ግለሰቦች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አስደሳች ተስፋ እንዳላቸው ይረዳሉ። ወደ ሰማይ ለመሄድ ተስፋ ያላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቁጥር እየቀነሰ ሲሄድ የእነዚህ ቁጥር ግን እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። ሉቃስ 13:24 ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ለሌላቸው ሰዎች ተፈጻሚነት አይኖረውም። ይሁን እንጂ የሚጠቅማቸው ጥሩ ምክር ይዟል።
ኢየሱስ ተጋደሉ ብሎ ሲያሳስብ እርሱም ሆነ አባቱ እንዳንገባ የሚያግዱን በርካታ እንቅፋቶች ከፊታችን እንደሚያስቀምጡ መናገሩ አልነበረም። ይሁን እንጂ ከሉቃስ 13:24 እንደምንረዳው ብቃት የሌላቸው ሰዎች እንዳይገቡ የሚያግዱት አምላክ ራሱ የወሰናቸው ብቃቶች ናቸው። “ተጋደሉ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው መታገልንና አቅም የፈቀደውን ሁሉ ማድረግን ነው። ይሁን እንጂ ‘እየተጋደልኩ ነኝን?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። ሉቃስ 13:24ን ‘ለመግባት የሚፈልጉት ብዙዎች ስለሆኑና የሚችሉት ግን ጥቂቶች ስለሆኑ በጠባቡ በር ለመግባት መጋደል አለብኝ። በእርግጥ እየተጋደልኩ ነኝን? ባለ በሌለ አቅሙ ሽልማት ለማግኘት እንደሚጥረው የጥንት ዘመን ስፖርተኛ ነኝን? እንዲህ ያለው ስፖርተኛ በግድየለሽነት ወይም በግማሽ ልብ አይሮጥም። እኔስ?’
አንዳንዶች በሚያመቻቸው ጊዜ ወይም እነርሱ በሚመርጡት በተዝናናና ቀላል በሆነ አካሄድ በበሩ ለመግባት እንደሚፈልጉ የኢየሱስ ቃላት ያመለክታሉ። ግለሰብ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ባለው ዝንባሌ ሊነኩ ይችላሉ። አንዳንዶች ‘ለብዙ ዓመታት ራሳቸውን ያቀረቡና ብዙ መሥዋዕቶችን የከፈሉ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖችን አውቃለሁ፤ ሆኖም በሞቱበት ወቅት የዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ ገና አልመጣም ነበር። ስለዚህ ጥቂት ዘና ብል፣ ኑሮዬን ይበልጥ ባመቻች ይሻላል’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ።
እንዲህ ብሎ ማሰብ ቀላል ቢሆንም ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ጥበብ ነው? ለምሳሌ ያህል ሐዋርያት አስተሳሰባቸው እንደዚህ ዓይነት ነበርን? በጭራሽ። እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ሁለመናቸውን ለእውነተኛው አምልኮ ሰጥተው ነበር። ለምሳሌ ያክል ጳውሎስ “እኛም . . . የምንሰብከው እርሱ [ክርስቶስ] ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፣ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፣ እደክማለሁ” ሊል ችሏል። ከጊዜ በኋላም እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ይህን ለማግኘት እንደክማለንና፣ ስለዚህም እንሰደባለን፤ ይህም ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ ነው።”—ቆላስይስ 1:28, 29፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:10
ጳውሎስ በመጋደሉ ፍጹም ትክክል የሆነ ነገር እንዳደረገ እናውቃለን። ጳውሎስ “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ” ብሎ እንደተናገረው እያንዳንዳችን እንዲህ ብለን መናገር ብንችል ምንኛ የሚያረካ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 4:7) ሉቃስ 13:24 ላይ ከሰፈረው ከኢየሱስ ቃላት ጋር በመስማማት ‘በትጋትና ከሙሉ ልብ እየሠራሁ ነውን? ኢየሱስ “በጠባቡ በር ለመግባት ተጋደሉ” ሲል የሰጠውን ምክር ልብ እንዳልኩና ሥራ ላይ በማዋል እንዳለሁ በተግባር አሳያለሁን?’ ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ ጥሩ ይሆናል።