የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በፖላንድ “የተመረጡትን ዕቃዎች” መሰብሰብ
    መጠበቂያ ግንብ—1992 | ሐምሌ 15
    • ኤልዛቤታ ስታብራራ “ቤተሰቦቼ በመጀመሪያ እቤት ውስጥ ደበደቡኝ። ከዚያም ወደ መንግሥት አዳራሽ ዘለው ገብተው . . . ወደ ቤት ወሰዱኝና በዱላ ደበደቡኝ። ከምሥክሮቹ ጋር ስለተባበርኩ ብቻ ከራስ ፀጉሬ እስከ እግር ጥፍሬ ተደበደብኩ። በጣም በመደብደቤ አስቸኳይ ህክምና ማግኘት ስላስፈለገኝ ወደ ሆስፒታል ተወሰድኩ። በይሖዋ እርዳታ አገገምኩ። ወላጆቼም አባረሩኝ። ይህንን ሁኔታ ለቄሱ ስነግራቸው በጣም አንቋሽሸው “ትንሽ ጥፊ ተመታሁ ብለሽ ነው አቤቱታ ለማቅረብ የመጣሽው?” አሉኝ።

      ሌላዋ እህት ደግሞ በየዓመቱ የመስቀል ጉዞ ለማድረግ ወደ ቼስቶኮዋ እሄድ ነበር። ማንኛውም እውነተኛ ካቶሊክ ይህን ጉዞ ማድረግ ይኖርበታል ብዬ አስብ ነበር። አሁንም በጉልበቶቼ ላይ ያሉት ጠባሳዎች አልጠፉም” ስትል ታስታውሳለች። በ18 ዓመቷ እውነትን አወቀችና ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደማትመለስ ለቄሱና ለቤተሰቦቿ ነገረቻቸው። “በጣም አድርገው ስለ ደበደቡኝ የአእምሮ መናወጥ ደረሰብኝ” ስትል ትናገራለች። “ይሁን እንጂ ሆስፒታል ቆይቼ በሚገባ ስለ ተሻለኝ ‘በነፃነት አፍቃሪዎች’ የወረዳ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ቻልኩ። በዚህ ስብሰባ ላይ በቼስቶኮዋ አይቼ የማላውቀውን ግብዝነት የሌለበት እውነተኛ አንድነትና ፍቅር ለማየት በመቻሌ በደስታ አለቀስኩ። የይሖዋን ጥሩነት በመቅመሴና በእሱ ላይ መታመንን በመማሬ ከፍተኛ ደስታ ተሰማኝ።” ይሖዋ ጭንቀታቸውን በእርሱ ላይ የሚጥሉትን ሁሉ ያጠነክራቸዋል፣ ይደግፋቸዋል።—መዝሙር 55:22

      ብዙ የታላቂቱ ባቢሎን ምርኮኞች በዚህች ካቶሊክ አገርም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሚኖሩ “ከመካከልዋ ውጡ” የሚለውን ጥሪ በመቀበል ላይ ናቸው። የይሖዋ ፈቃድ ከሆነ ደፋር ሕዝቦቹ ገና በፖላንድ አገር ውስጥ ተበትነው የሚገኙትን “የተመረጡ ዕቃዎች” ይሰበስባሉ። በእርግጥም ብዙዎች፦ “ና . . . የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” የሚለውን ጥሪ በመቀበል ላይ ናቸው።—ራእይ 18:4፤ 22:17

  • ከሁሉ የሚበልጠውን የፍቅር መንገድ መከተል
    መጠበቂያ ግንብ—1992 | ሐምሌ 15
    • ከሁሉ የሚበልጠውን የፍቅር መንገድ መከተል

      ይሖዋ አምላክ ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስም አምላክንና ጎረቤቶቻችንን መውደድ እንዳለብን ተናግሮአል። (ማቴዎስ 22:37-40) አምላክ ጠቅላላውን ጽንፈ ዓለም የሚያንቀሳቅሰው ይህንን ባሕርይ መሠረት በማድረግ ነው። ስለዚህ በሰማይም ሆነ በምድር የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ከፈለግን ይህንን የፍቅር መንገድ መከተል ይገባናል።

      አምላክ ለእስራኤል ሕዝብ ፍቅር አሳይቶ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ታማኝ ሆነው ስላላገኛቸው ይህን የእስራኤል ሕዝብ ድርጅት ፈጽሞ ትቶታል። ከዚያ በኋላ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ጉባኤ አዲስ ድርጅቱ መሆኑን አሳወቀ። እንዴት? በልሳናት እንዲናገሩና ትንቢት እንዲናገሩ የሚያስችል ልዩ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመስጠት ነው። በዚህም ምክንያት በ33 እዘአ በዋለው የጰንጤቆስጤ ቀን 3,000 አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተቀየሩ ሰዎች አማኝ ሆነው የጥንቱን ድርጅት በመተው ወደ አዲሱ የአምላክ ድርጅት ገቡ። (ሥራ 2:1-41) ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የመንፈስ ስጦታዎች የሚተላለፉት በኢየሱስ ሐዋርያት በኩል ስለነበረ ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ ይህም የመንፈስ ቅዱስ አሠራር አቆመ። (ሥራ 8:5-18፤ 19:1-6) ይሁን እንጂ እነዚህ ሥጦታዎች አምላክ ሞገሱን ያሳረፈው በመንፈሳዊ እስራኤል ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል።—ገላትያ 6:16

      በመንፈስ ስጦታዎች አማካኝነት የሚከናወኑት ተአምራት ጥቅም ነበራቸው። ይሁን እንጂ እነዚህን መንፈሳዊ ስጦታዎች ከማግኘት ይልቅ ፍቅርን ወይም ራስ ወዳድነት የሌለበትን አሳቢነት ለሌሎች ማሳየት ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ (በ55 እዘአ አካባቢ) ይህንን ቁምነገር ገልጾአል። በዚህ ደብዳቤ ላይ ፍቅር “ከሁሉም የሚበልጥ መንገድ” መሆኑን ተናግሮአል። (1 ቆሮንቶስ 12:31) ይህ መንገድ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ላይ ተብራርቶአል።

      ፍቅር ከሌለን ከንቱ ነን

      ጳውሎስ እንዲህ በማለት ያስረዳል፦ “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽው ጸናጽል ሆኜአለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 13:1) ፍቅር ከሌለ በመንፈስ ስጦታ አማካኝነት በሰዎች ቋንቋና በሰማያዊ መላእክት ልሳን መናገር ምንም ዋጋ አይኖረውም። ጳውሎስ ሰዎች በማይረዱት ልሳን አሥር ሺህ ቃላት ከመናገር ይልቅ አምስት የሚያንጹ ቃላትን መናገር እንደሚሻለው መርጦአል። (1 ቆሮንቶስ 14:19) ፍቅር የሌለው ሰው “እንደሚጮኽ ናስ” ማለትም እንደሚንጫጫና፣ እንደሚያውክ ደወል ወይም ጣዕም እንደሌለው “የሚንሸዋሸው ጸናጽል” ነው። ከፍቅር ውጪ የሆነ የልሳን ንግግር አምላክን ለማክበርም ሆነ ሕዝቦቹን ለመርዳትና በመንፈሳዊ ለማነጽ የሚያስችል አርኪ መንገድ አይደለም። በዛሬው ጊዜ በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ግልጽ በሆነና ሊገባ በሚችል ንግግር በመጠቀም ፍቅራችንን እናሳያለን።

      በመቀጠልም ሐዋርያው እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ትንቢትም ቢኖረኝ፣ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፣ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።” (1 ቆሮንቶስ 13:2) ተአምራዊ ትንቢት፣ ቅዱስ ምሥጢርን የመረዳት ልዩ ችሎታና በመንፈስ የተሰጠ እውቀት ሌሎችን ሊጠቅም ይችላል። ነገር ግን እነዚህ ስጦታዎች የተሰጡት ሰው ፍቅር ከሌለው ስጦታዎቹ ምንም ዓይነት ዋጋ አይኖራቸውም። ጳውሎስ ቅዱስ ምሥጢሮችን ለመረዳት በሚያስችለው ልዩ ሥጦታ በመጠቀም ሌሎች ሰዎችን ረድቶአል። የነበረው የእውቀት ስጦታም ከመርከብ መስጠም አደጋ ለመዳን ያስቻለ ትንቢት እንዲናገር አስችሎታል። (ሥራ 27:20-44፤ 1 ቆሮንቶስ 4:1, 2) ቢሆንም ጳውሎስ ‘እውቀት ሁሉና እምነት ሁሉ’ ቢኖረውና ፍቅር ግን ባይኖረው በይሖዋ ዓይን ከንቱ ይሆን ነበር።

      በዘመናችን የይሖዋ መንፈስ ምሥክሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችንና ቅዱስ ምሥጢሮችን እንዲረዱና ይህንንም እውቀት ለሌሎች እንዲነግሩ አስችሎአቸዋል። (ኢዩኤል 2:28, 29) በተጨማሪም መንፈሱ እንደ ተራራ ያሉ እንቅፋቶችን እንዲወጡ የሚያስችላቸውን እምነት አስገኝቶላቸዋል። (ማቴዎስ 17:20) እነዚህን ነገሮች የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ የግል ክብር ለማግኘት መፈለግ ስህተት ነው። ማንኛውንም ነገር የምናደርገው ለአምላክ ክብርና ለሰዎች ባለን ፍቅር ተገፋፍተን ካልሆነ ሥራችን ዋጋ አይኖረውም።—ገላትያ 5:6

      ፍቅር የሌለበት መሥዋዕትነት ሁሉ ጥቅም አይኖረውም

      ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።” (1 ቆሮንቶስ 13:3) ጳውሎስ ሌሎችን ለመመገብ ሲል ያለውን ሁሉ ቢሰጥ እንኳን ፍቅር ግን ከሌለው ምንም ትርፍ አይኖረውም። አምላክ ዋጋ የሚሰጠው ስጦታ እንድንሰጥ ላነሳሳን ፍቅር እንጂ ሥጦታው ባለው የዋጋ ውድነት ወይም እንደ ውሸታሞቹ ሐናንያና ሰጲራ ክብር ለማግኘት ስንል በምንሰጠው ስጦታ አይደለም። (ሥራ 5:1-11) ጳውሎስ በይሁዳ ለሚኖሩ አማኞች ይሰበሰብ ለነበረው እርዳታ በፍቅር ራሱን አሳልፎ በመስጠቱ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል።—1 ቆሮንቶስ 16:1-4፤ 2 ቆሮንቶስ 8:1-24፤ 9:7

      ለእውነት ምሥክርነት ለመስጠት ሲባል ሰማዕት መሆን እንኳን ፍቅር የጎደለው ከሆነ በአምላክ ፊት ምንም ትርጉም አይኖረውም። (ምሳሌ 25:27) ኢየሱስ መስዋዕት እንደሚሆን ተናግሮአል። ነገር ግን በዚህ ኩራት አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ በፍቅር ተነሳስቶ ራሱን በፈቃደኝነት አሳልፎ ሰጠ። (ማርቆስ 10:45፤ ኤፌሶን 5:2፤ ዕብራውያን 10:5-10) መንፈሳዊ ወንድሞቹም ‘ሰውነታቸውን ሕያው መስዋዕት’ አድርገው ለአምላክ አገልግሎት ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ ይህን የሚያደርጉት ራሳቸውን ሰማዕት አድርገው ክብር ለማግኘት ሳይሆን ይሖዋን ለማስከበርና ለሱ ያላቸውን ፍቅር ለማሳየት ነው።—ሮሜ 12:1, 2

      በፍቅር ተገፋፍተን የምናደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች

      ጳውሎስ ሲጽፍ “ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል” ብሎአል። (1 ቆሮንቶስ 13:4ሀ) አምላክ አዳም ኃጢአት ከሠራበት ጊዜ ጀምሮ ያሳየው ትዕግስት ብዙዎች ንሥሐ ገብተው ደህንነት እንዲያገኙ አስችሎአቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:9, 15) እኛም ፍቅር ካለን እውነትን ለሌሎች በትዕግሥት እናስተምራለን። በስሜት ግንፋሎት ከመቆጣት ይልቅ ለሰዎች አሳቢዎችና ይቅር ባዮች እንሆናለን። (ማቴዎስ 18:21, 22) በተጨማሪም ፍቅር ቸር ነው። ወደ አምላክ ለመቅረብ የቻልነው እርሱ ቸር ስለሆነ ነው። የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆነው ቸርነት አምላክ ከኛ ከሚጠብቅብን በላይ ከሌሎች እንዳንጠብቅ ይከላከልልናል። (ኤፌሶን 4:32) ፍቅር አመስጋኝ ላልሆኑ ሰዎች እንኳን ቸር እንድንሆን ያደርገናል።—ሉቃስ 6:35

      በተጨማሪም ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም።” (1 ቆሮንቶስ 13:4ለ) ቅንዓት አንድን ሰው ከአምላክ መንግሥት ውጪ የሚያደርግ የሥጋ ሥራ ነው። (ገላትያ 5:19-21) ፍቅር በአንድ ሰው ሀብት ወይም ባገኘው ጥሩ ስም እንዳንቀና ይጠብቀናል። ለአንድ ሰው እኛ እንመኘው የነበረ የአገልግሎት መብት ቢሰጠው ፍቅር ከእርሱ ጋር እንድንደሰትና እርዳታችንን እንድንሰጠው ያደርገናል። እንዲሁም ጉባኤውን ለመርዳት ስለሚጠቀምበት አምላክን እናመሰግነዋለን።

      ፍቅር ስለማይመካ አምላክ በአገልግሎቱ እንድንሠራ ስላስቻለን ሥራ ጉራችንን እንድንነዛ አይገፋፋንም። አንዳንድ የቆሮንቶስ ሰዎች የመንፈስ ስጦታዎችን እነርሱ እንዳመነጩ በማድረግ ጉራቸውን ይነዙ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ የመንፈስ ሥጦታዎችም ሆኑ በዘመናዊው ድርጅቱ ውስጥ የሚሰጡት መብቶች ከአምላክ የሚገኙ ናቸው። በአምላክ ድርጅት ውስጥ ባለን አቋም ከመኩራራት ይልቅ እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ። (1 ቆሮንቶስ 1:31፤ 4:7፤ 10:12) ፍቅር “አይታበይም።” ፍቅር የሌለው ሰው አእምሮ ግን እሱ ብቻ ተፈላጊ እንደሆነ እንዲሰማው ሊያደርገው ይችላል። ፍቅር ያላቸው ሰዎች በሌሎች ላይ የበላይነት ስሜት አይሰማቸውም።—1 ቆሮንቶስ 4:18, 19፤ ገላትያ 6:3

      ፍቅር የማይገባውን አያደርግም፣ ራስ ወዳድ አይደለም፣ አይቆጣም

      ፍቅር “የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም።” (1 ቆሮንቶስ 13:5ሀ) ፍቅር ጥሩ ምግባርን፣ አምላካዊ ጠባዮችን፣ ለባለስልጣን አክብሮት የማሳየትን ባሕርይ ከማስፋፋቱም በላይ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የማይገባ ነገር እንዳናደርግ ይገፋፋናል። (ኤፌሶን 5:3-5፤ 1 ቆሮንቶስ 11:17-34፤ 14:40፤ ከይሁዳ 4, 8-10 ጋር አወዳድር።) ፍቅር እያንዳንዱ ሰው እንደ አንድ የሰውነት ብልት ተፈላጊ መሆኑ እንዲሰማው ስለሚያደርግ ፍቅር ያለበት ጉባኤ ሰላም የሰፈነበትና እረፍት የሚገኝበት ሥፍራ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 12:22-25) ፍቅር በራስ ወዳድነት ስሜት ‘የራሳችንን ጥቅም ከመፈለግ ይልቅ’ የራሳችንን መብት እንድንሰዋና ለሌሎች ሰዎችና ለደህንነታቸው አሳቢዎች እንድንሆን ይቀሰቅሰናል። (ፊልጵስዩስ 2:1-4) ፍቅር አንዳንዶችን በአገልግሎታችን ለማዳን እንድንችል ‘ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ እንድንሆን’ ያደርገናል።—1 ቆሮንቶስ 9:22, 23

      “ፍቅር አይበሳጭም።” በቁጣ መገንፈል የኃጢአተኛው ሥጋ ሥራ ነው። ፍቅር ግን ‘ለቁጣ የዘገየን’ እንድንሆን ያደርገናል። (ያዕቆብ 1:19፤ ገላትያ 5:19, 20) ተገቢ ምክንያት ኖሮን ብንቆጣ እንኳን ለረዥም ጊዜ ተቆጥተን በመቆየት ለዲያብሎስ ቦታ እንድንሰጥ አይፈቅድልንም። (ኤፌሶን 4:26, 27) በተለይ ሽማግሌዎች የእምነት ጓደኞቻቸው የተሰጡአቸውን አንዳንድ ሐሳቦች ሳይሰሩበት በመቅረታቸው ምክንያት መቆጣት አይገባቸውም።

      በተጨማሪም ጳውሎስ ስለ ፍቅር እንዲህ ብሎአል፦ “በደልን አይቆጥርም።” (1 ቆሮንቶስ 13:5ለ) ፍቅር በደሎችን የሚመዘግብበት የሂሣብ ደብተር የለውም። የእምነት ጓደኞቹን ጥሩነት ብቻ ስለሚመለከት ለተሠራበትም ሆነ ተሠርቶብኛል ብሎ ለሚያስበው በደል በቀል ወይም ብድር አይመልስም። (ምሳሌ 20:22፤ 24:29፤ 25:21, 22) ፍቅር “ሰላም የሚቆምበትን” ለመከተል እንድንችል ይረዳናል። (ሮሜ 14:19) ጳውሎስና በርናባስ በመጣላታቸው ምክንያት ተለያይተው አምላክን ማገልገል ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ ፍቅር በመካከላቸው የተፈጠረውን ቅሬታ ስለፈወሰላቸው ተቀያይመው አልቀሩም።—ዘሌዋውያን 19:17, 18፤ ሥራ 15:36-41

      ጽድቅንና እውነትን ይወድዳል

      ጳውሎስ ስለ ፍቅር የሚከተለውን ተናግሮአል፦ “ፍቅር . . . ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም።” (1 ቆሮንቶስ 13:6) አንዳንዶች በክፋት በጣም ስለሚደሰቱ “ክፉ ካላደረጉ አይተኙም።” (ምሳሌ 4:16) በአምላክ ድርጅት ውስጥ ግን እርስ በርሳችን አንፎካከርም ወይም አንድ ሰው በኃጢአት ወጥመድ ውስጥ ቢወድቅ አንደሰትም። (ምሳሌ 17:5፤ 24:17, 18) የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለአምላክና ለጽድቅ በቂ የሆነ ፍቅር ቢኖራቸው ኖሮ በጉባኤው ውስጥ መጥፎ ሥነ ምግባር አይስፋፋም ነበር። (1 ቆሮንቶስ 5:1-13) ጽድቅ ወዳዶች ከሆንን ጽድቅ ያልሆኑ ድርጊቶችን በቴሌቪዥን፣ በሲኒማ ወይም በቲያትር በመመልከት አንደሰትም።

      ፍቅር “ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል።” እዚህ ላይ እውነት ከአመጽ ጋር ተነጻጽሮአል። ይህም ማለት ፍቅር ሰዎች በእውነት ምክንያት ተለውጠው ጽድቅ አድራጊዎች ሲሆኑ እንድንደሰት ያደርገናል ማለት ነው። ሰዎችን በሚያንጹና እውነትና ጽድቅ እንዲስፋፋ በሚያስችሉ ነገሮች እንደሰታለን። ፍቅር ውሸት ከመናገር ይጠብቀናል። ቅን የሆኑ ሰዎች ንጹሕ መሆናቸው ሲረጋገጥና የአምላክ እውነት ድል ሲያደርግ እንድንደሰት ያደርገናል።—መዝሙር 45:4

      ፍቅር ለነገሮች ያለው አመለካከት

      ጳውሎስ ስለ ፍቅር የሚሰጠውን መግለጫ በመቀጠል እንዲህ ሲል ጽፎአል፦ “ፍቅር . . . ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል።” (1 ቆሮንቶስ 13:7) ፍቅር ‘ሁሉን ስለሚታገስ’ አንድ ጥሩ የሆነ የቤት ጣሪያ ከዝናብ እንደሚያድን ሰዎችን ከመቀየም ያድነናል። ማንም ሰው ካስቀየመን በኋላ ይቅርታ እንድናደርግለት ቢጠይቀን ፍቅር በደሉን እንድንሸከምና የበደለንን ሰው ከማማት ይልቅ ይቅር እንድንለው ይረዳናል። በፍቅር ወንድማችንን ለማትረፍ እንጥራለን።—ማቴዎስ 18:15-17፤ ቆላስይስ 3:13

      ፍቅር በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን ነገሮች ‘ሁሉ እንድናምንና’ “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል ለሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ አመስጋኞች እንድንሆን ያደርገናል። (ማቴዎስ 24:45-47) በቀላሉ የምንታለል ሰዎች ባንሆንም ፍቅር የማያምን ልብ እንዳይኖረንና የእምነት ባልደረቦቻችን ለሚያደርጉአቸው ነገሮች መጥፎ ትርጉም እንዳንሰጥ ያደርገናል። (መክብብ 7:21, 22) በተጨማሪም ፍቅር በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተመዘገቡትን ለምሳሌ ስለ አምላክ መንግሥት የተነገሩትን እውነቶች “ተስፋ ያደርጋል።” ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ በፍቅር ተገፋፍተን የመጨረሻው ውጤት ጥሩ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፣ እንጸልያለን። በተጨማሪም ፍቅር የተስፋችንን ምክንያት ለሌሎች እንድንነግር ይገፋፋናል። (1 ጴጥሮስ 3:15) ከዚህም በላይ ፍቅር በራሳችን ላይ የሚደርሱ ኃጢአቶችን ጨምሮ “በሁሉ ይጸናል።” (ምሳሌ 10:12) ለአምላክ ያለን ፍቅር ስደትንና የተለያዩ መከራዎችን ለመቋቋም እንድንችል ይረዳናል።

      ጳውሎስ በመቀጠል፦ “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም” ብሎአል። (1 ቆሮንቶስ 13:8ሀ) ይሖዋ መጨረሻ እንደሌለው ሁሉ ፍቅርም ፍጻሜ ሊኖረው ወይም ሊወድቅ አይችልም። በፍቅር ረገድ ፍጹም አርዓያ የሚሆነን ዘላለማዊው አምላካችን ስለሆነ የፍቅር ባህርይ ሊወድቅ አይችልም። (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ 1 ዮሐንስ 4:16) ጽንፈ ዓለሙ ምን ጊዜም ቢሆን የሚመራው በፍቅር ነው። ስለዚህ አምላክ የራስ ወዳድነትን ባህርይ ለማሸነፍ እንዲረዳንና ይህን የማይወድቅ የመንፈስ ፍሬ እንዲሰጠን እንጸልይ።—ሉቃስ 11:13

      የሚያልፉ ነገሮች

      ጳውሎስ የወደፊቱን በማመልከት እንዲህ አለ፦ “ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖችም ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል።” (1 ቆሮንቶስ 13:8ለ) የትንቢት ስጦታዎች ስጦታዎቹን የተቀበሉት ሰዎች አዲስ ትንቢት እንዲናገሩ አስችሎአቸዋል። እንደነዚህ ያሉት ሥጦታዎች የክርስቲያን ጉባኤ የአምላክ ድርጅት ሆኖ ከተቋቋመ በኋላ የቀሩ ቢሆኑም የአምላክ ትንቢት የመናገር ችሎታ ግን ፈፅሞ አይሻርም። በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጉን ትንቢቶች በሙሉ በአምላክ ቃል ውስጥ ይገኛሉ። ከመንፈስ የሚገኘው በልሳን የመናገር ስጦታም ቆሞአል። አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረውም ልዩ እውቀት የማግኘት ሥጦታም ተሽሮአል። ይሁን እንጂ የተሟላው የይሖዋ ቃል ለደህንነት የሚያስፈልገንን እውቀት ይሰጠናል። (ሮሜ 10:8-10) ከዚህም በላይ የአምላክ ሕዝቦች በመንፈስ የተሞሉ በመሆናቸው የመንፈስን ፍሬዎች ያፈራሉ።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ