መጽሐፍ ቅዱስ አንብበን እንድንረዳው ተብሎ የተጻፈ መጽሐፍ
አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል ሊከተሉት የሚገባ ግልጽ የሆነ የአምላክ ቃል ነው ብለው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ “የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በእጅጉ የሚያሻማ ይሆንባቸዋል።” ይህን ያለው 12 አባላት ያሉት የካናዳ ትልቁ የፕሮቴስታንት እምነት ክፍል የሃይማኖታዊ ትምህርት ኮሚቴ ነው። የተባበሩት ቤተ ክርስቲያን ቄስ የሆኑት ክሊፎርድ ኤልዩት ለአንዳንዶች “መጽሐፍ ቅዱስ በጣም የረቀቀ፣ የማይጨበጥና ኖረም አልኖረ ምንም ለውጥ የማያመጣ መጽሐፍ ይሆንባቸዋል” የሚል ስሜት አድሮባቸዋል።
እነዚህን የመሰሉ አመለካከቶች መልስ ማግኘት የሚያሻቸውን ከዚሁ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያስነሣሉ። ከእነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ለምንድን ነው? ለመረዳት የሚያስቸግር እጅግ የተወሳሰበና እንቆቅልሽ ነውን? ማንኛውም ተራ ሰው ሊረዳው ይችላልን? አንድ ሰው ቅዱሳን ጽሑፎች የያዙት ሐሳብ እንዲገባው ምን እርዳታ ማግኘት ያስፈልገዋል? በእነዚህ ተለዋዋጭ ጊዜያት ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ለምን ተጻፈ?
ሰዎች የልዑሉን አምላክ የይሖዋን ሞገስና ተቀባይነት እንዲያገኙ የአምላክን ቃል ማጥናት ሁልጊዜ ቅድመ ሁኔታ ሆኖ ቀርቦላቸዋል። ነገሥታት፣ ካህናት፣ ወላጆች፣ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች ከዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳዮች ላይ ጊዜ ዋጅተው በጽሑፍ የሚገኘውን የአምላክ ቃል በጥልቀትና በቁም ነገር እንዲመረምሩ መመሪያ ይሰጣቸው ነበር።—ዘዳግም 6:6, 7፤ 17:18–20፤ 31:9–12፤ ነህምያ 8:8፤ መዝሙር 1:1, 2፤ 119:7–11, 72, 98–100, 104, 142፤ ምሳሌ 3:13–18
ለምሳሌ ያህል ኢያሱ እንዲህ የሚል መመሪያ ተሰጥቶት ነበር፦ “የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።” (ኢያሱ 1:8) የአምላክን ሕግ በዚህ መንገድ በጥልቀት ማጥናትና በሥራ ላይ ማዋል ስኬታማነትንና ደስታን ያስገኝ ነበር። ይሖዋ “ሰዎች ሁሉ” ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲረዱ ብቻ ሳይሆን የሕይወትን ስጦታ ያገኙ ዘንድ ይህን ቃሉን እንዲታዘዙም ይፈልጋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4፤ ዮሐንስ 17:3
ለመረዳት የሚያስቸግር እጅግ የተወሳሰበ መጽሐፍ ነውን?
ኢየሱስ በምድር ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሰፊ ፕሮግራም እንዲካሄድ መፈለጉን ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ግልጽ አድርጎ ነበር። (ሥራ 1:8) መጽሐፍ ቅዱስ አንብበን እንድንረዳው ተብሎ የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑን ያውቅ ነበር። ይሖዋ በሰማይና በምድር ላይ ሙሉ ሥልጣን እንደሰጠው ከገለጸ በኋላ የሚከተለውን ቀጥተኛ ትእዛዝ ሰጠ፦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት [ወይም ተማሪዎች] አድርጓቸው።”—ማቴዎስ 28:19, 20
አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ከመጠመቃቸው በፊት ስለ ይሖዋ፣ ስለ ልጁና ስለ መንፈስ ቅዱስ የሥራ እንቅስቃሴ መማር አለባቸው። በተጨማሪም የክርስትናን ሕግ መማር አለባቸው። (1 ቆሮንቶስ 9:21፤ ገላትያ 6:2) ይህን ውጤት ለማግኘት መልእክቱ ሊነገራቸው የሚገባቸው ሰዎች አንደኛ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ቃል መሆኑን ሁለተኛ ደግሞ አንብበን እንድንረዳው ተብሎ የተጻፈ መሆኑን ማመን ያስፈልጋቸዋል።—ማቴዎስ 10:11–13
መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት እንዲችሉ ምን ማድረግ ይጠበቅብዎታል? የአምላክ ልጅ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማብራራት ልዩ ጥረት አድርጓል። ቅዱሳን ጽሑፎች እውነተኛ እንደሆኑና ለሰው የተገለጸውን የይሖዋን ፈቃድ የያዙ መሆናቸውን ያውቅ ነበር። (ዮሐንስ 17:17) ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሠራው የተሰጠውን ሥራ አስመልክቶ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” ብሏል። (ዮሐንስ 18:37፤ ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ ለመማር ፈቃደኛ የሆነ ልብና አእምሮ ያላቸውን ሰዎች ከማስተማር ወደ ኋላ አላለም። በሉቃስ 24:45 ላይ “በዚያን ጊዜም [ክርስቶስ ኢየሱስ] መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው” ተብሎ ተነግሮናል።
ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት “በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም” ያሉትን ጥቅሶች በማብራራትና በማጣቀስ የተጻፈውን ቃል ብዙ ጊዜ ይጠቅስ ነበር። (ሉቃስ 24:27, 44) ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያዎቹን የሰሙ ሰዎች ነገሮችን ጠንቅቆ የሚረዳ በመሆኑና በማስተማር ችሎታው በጣም ተገርመው ነበር። (ማቴዎስ 7:28, 29፤ ማርቆስ 1:22፤ ሉቃስ 4:32፤ 24:32) ቅዱሳን ጽሑፎች ለኢየሱስ ድፍን ያሉ መጻሕፍት አልነበሩም።
መጽሐፍ ቅዱስና የኢየሱስ ተከታዮች
ኢየሱስ ክርስቶስን ይኮርጅ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ቅዱሳን ጽሑፎች ያዘሏቸውን ነገሮች ለሌሎች ማስተማር አስፈላጊ መሆኑን ተረድቶ ነበር። እርሱም ቢሆን አንብበን እንድንረዳቸው ተብለው የተጻፉ እንደሆኑ ያውቅ ነበር። በአደባባይ ያስተምር የነበረውና ቅዱሳን ጽሑፎችን መረዳት ይፈልጉ ለነበሩ ሰዎች ቤታቸው ድረስ ሄዶ ያብራራላቸው የነበረው በዚህ ምክንያት ነው። “በአደባባይም ሆነ በየቤታችሁ ሳስተምራችሁ የሚጠቅማችሁን ሁሉ ነገርኋችሁ እንጂ ምንም ነገር አላስቀረሁባችሁም” ብሎ በተናገረ ጊዜ ጳውሎስ አቋሙን ግልጽ አድርጓል። (ሥራ 20:20 የ1980 ትርጉም) ውይይት ያደርግ በነበረበት ጊዜ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሰ የሚያቀርባቸውን ነጥቦች በማብራራትና እውነተኝነታቸውን በማረጋገጥ ያስረዳ ነበር። (ሥራ 17:2, 3) ሌሎች ሰዎች የቅዱሳን ጹሑፎች ትርጉም እንዲገባቸው መርዳት ያስደስተው ነበር።
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያስተማሯቸውን ነገሮች ለመረዳት ከፍተኛ ጉጉት አለዎትን? (1 ጴጥሮስ 2:2) የጥንቷ ቤሪያ ነዋሪዎች እንዲህ ዓይነት ፍላጎት ነበራቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ያስተምራቸው የነበሩትን ነገሮች ለማመን ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው። ስለዚህ ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ እንዲያጠኑና በዚህ መንገድ የሰሙት ምሥራች በእርግጥም እውነት መሆኑን እንዲያረጋግጡ ማበረታቻ ተሰጣቸው። አእምሮአቸው ለመቀበል ፈቃደኛ ስለነበረ “ከእነርሱ ብዙ . . . አመኑ።”—ሥራ 17:11, 12
አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲገባው ከተፈለገ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ፣ ልባዊ የሆነ የማወቅ ፍላጎትና ‘መንፈሳዊ ጉድለቱ የሚታወቀው’ መሆን ያስፈልገዋል። (ማቴዎስ 5:3) ኢየሱስ “ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም” በማለት መልስ ሰጥቷል። ‘በምሳሌ አፉን ይከፍታል፣ የተሰወረውንም ይናገራል’ ተብሎ አስቀድሞ ተነግሮለት ነበር። (ማቴዎስ 13:10, 11, 35) ስለዚህ ኢየሱስ እንዲሁ ለወሬ ብለው የቆሙትን ሰዎች በጉጉት ከሚያዳምጡትና በቅንነት ጥያቄ ከሚያቀርቡለት ለመለየት ሲል ምሳሌዎችን ይናገር ነበር። በአንድ ወቅት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አብረውት ወደ አንድ ቤት ከገቡ በኋላ “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጉምልን” ባሉት ጊዜ ቅን መሆናቸውን አሳይተዋል።—ማቴዎስ 13:36
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲገባን ከተፈለገ አጋዥ እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው። በተባበሩት ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ትምህርት፣ የእምነትና ሁሉም የክርስትና እምነት ክፍሎች መዋሃድ አለባቸው የሚለው ንድፈ ሐሳብ ጸሐፊ የሆኑት ቄስ ሃል ሌውሊን “መጽሐፍ ቅዱስ ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው፣ እንዴት እንደሚነበብና ምን ፍቺ እንደሚሰጠው ግልጽ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰው ይህን ባይገነዘበውም መጽሐፍ ቅዱስን ራሳችን በራሳችን ልንረዳው የማንችል መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። እርዳታ ያስፈልገናል።
ምን እርዳታ አለልን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ እንቆቅልሽ የሆኑ አነጋገሮች፣ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎችና መብራራት የሚያስፈልጋቸው ጥልቅ ትርጉም ያላቸው አባባሎች አሉ። ሰምና ወርቅ የመሰሉ አነጋገሮችና በተጻፉበት ጊዜ ሆን ተብሎ ሰዎች አንብበው እንዳይረዷቸው ተደርገው የተጻፉ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን የይሖዋን ዓላማዎች የሚመለከቱ ቁም ነገሮችን ያዘሉ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ራእይ 13:18 “ቁጥሩም [የአውሬው ቁጥር] ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው” ይላል። ጥቅሱ “ጥበብ በዚህ አለ” ቢልም እንኳ ቁጥሩ የሚያመለክተውን ነገር አልገለጸም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ በድርጅቱ በኩል ታማኝ አገልጋዮቹ ትርጉሙን መረዳት እንዲችሉ አድርጓል። (“መጽሐፍ ቅዱስን ለማስረዳት የተዘጋጀ መገናኛ መስመር” የሚለውን ሣጥን ይመልከቱ።) እርስዎም “የእውነትን ቃል በትክክል በማብራራት” ረገድ ልምድ ያላቸው ሰዎች በሚሰጥዎት እርዳታ ይህን ማስተዋል ማግኘት ይችላሉ።—2 ጢሞቴዎስ 2:2, 15, 23–25 አዓት፤ 4:2–5፤ ምሳሌ 2:1–5
ኢየሱስ ለመንግሥቱ መልእክት የሚሰጠው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ምላሽ ገሃድ እንዲወጣ አንዳንድ ጊዜ በምሳሌዎች ይጠቀም ነበር። አንዳንዶች ከጓደኞቻቸውና ከዘመዶቻቸው በሚደርስባቸው ተቃውሞ ተስፋ ስለሚቆርጡ ብዙም እንደማይገፉ አመልክቷል። ሌሎች “መከራ ወይም ስደት” ለመንግሥቱ መልእክት ያላቸውን አድናቆት እንዲያጠፋባቸው ይፈቅዱለታል። ሌሎቹ ደግሞ “የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል” የተባሉት የዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳዮች ለምሥራቹ ያላቸውን ማንኛውንም ዓይነት ፍቅር ገፍትረው እንዲያስወጡት በር ይከፍታሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በደስታ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡና ውድ የሆነውን ቃል ለመስማትና ትርጉሙን ለመረዳት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችም አሉ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እየተፈጸመ ባለው ‘ርኩሰት ሁሉ እያለቀሱና እየተከዙ’ ናቸው። እነዚህን የመሰሉ ሰዎች በይሖዋ መንገድ ለመመራት በጣም ይፈልጋሉ፤ ስለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያነቡትን ነገር ለመረዳት ከፍተኛ ጉጉት አላቸው።—ማቴዎስ 13:3–9, 18–23፤ ሕዝቅኤል 9:4፤ ኢሳይያስ 2:2–4
በግለሰብ ደረጃ የይሖዋን ዓላማዎች ጠለቅ ብለው ለማስተዋል ለሚፈልጉ ሰዎች ይሖዋ አስፈላጊውን እርዳታ ያዘጋጅላቸዋል። ለምሳሌ ያህል ከኢየሩሳሌም ሲመለስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የኢሳይያስ መጽሐፍ በጥልቀት ያነብ የነበረውን ኢትዮጵያዊ እንዲረዳው የይሖዋ መንፈስ ፊልጶስን እንደመራው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይህ ሰው ወደ አገሩ ሲመለስ በሰረገላው ላይ ተቀምጦ እያነበበ ነበር። ፊልጶስ የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ አመራር በመታዘዝ በሰረገላው አጠገብ ሮጠና “በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ሲል ጠየቀው። ሰውዬው ትሑትና ሐቀኛ ስለነበረ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አልሸሸገም። ፊልጶስ ይህን በመንፈሳዊ የተራበና ትሑት ሰው ደስ እያለው አስተማረው። ትምህርቱ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመረዳት አስችሎታል። የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት እንዲችል ከይሖዋ ጋር ተቀባይነት ያለው ግንኙነት ለመመሥረት ምን ማድረግ እንዳለበት አወቀ። አምላክን የሚያስደስት አኗኗር የሚከተል ደስተኛና የተጠመቀ የይሖዋ አገልጋይ ሆነ።—ሥራ 8:26–39
ቤትዎ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ሊኖር ይችላል፤ ብዙ ጊዜ አንብበውትም ሊሆን ይችላል። ቅንና ትሑት የነበረው ኢትዮጵያዊ ያጋጠመው ዓይነት የመረዳት ችግር እርስዎም ሳያጋጥምዎት አይቀርም። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የሚያነበውን መረዳት አልቻለም ነበር። እርዳታ አስፈልጎት ነበር፤ ይሖዋ አምላክ በደስታ ሊሰጠው የፈለገውንም እርዳታ ያላንዳች ማወላወል ተቀብሏል። ልክ እንደ ፊልጶስ የይሖዋ ምሥክሮችም ስለ አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉትን ነገሮች ማስተዋል እንዲችሉ እርስዎን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳዘጋጀና አንብበን እንድንረዳው ብሎ እንዳስጻፈው ያውቃሉ።—1 ቆሮንቶስ 2:10፤ ኤፌሶን 3:18፤ 2 ጴጥሮስ 3:16
መጽሐፍ ቅዱስ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በአጣዳፊነቱ ተወዳዳሪ በሌለው ጊዜ ላይ እንገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጊዜ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ዘመን ብሎ ይጠራዋል። (ማቴዎስ 24:3 አዓት) ከ1914 ጀምሮ እየተከናወኑ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ የሆኑት ብዙ ክስተቶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ‘ሌሎቹን መንግሥታት በሙሉ እንደምትፈጫቸውና እንደምታጠፋቸው’ ያሳያሉ።—ዳንኤል 2:44
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማቴዎስ ምዕራፍ 24, በማርቆስ ምዕራፍ 13ና በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ አስቀድመው የተነገሩትን ነገሮች ራስዎ ያንብቧቸው። የተገለጹት ክስተቶች ዓለም አቀፍ ይዘት እንዳላቸው ያስተውላሉ። እነዚህ ምልክቶች ከሌሎች ጦርነቶች ሁሉ ልዩ የሆኑትን የዓለም ጦርነቶች ያካተቱ ናቸው። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ አስቀድሞ የተነገሩትን የምግብ እጥረት፣ የመሬት መንቀጥቀጥና የዓመፃ መብዛት በዓይናችን አይተናል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ መንግሥታት የዓለም ጥፋት በቅርቡ እንደሚጀምር የማያሻማ ምልክት የሚሆነውን ነጋሪት ለማስጎሰም ምንም የቀራቸው አይመስልም። ይህን አስመልክቶ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የጌታ ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ” ይመጣልና። “ሰላምና ደህንነት ነው ሲሉ . . . ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።” (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3) ከጥፋቱ የማያመልጡት እነማን ናቸው? ጳውሎስ ‘እግዚአብሔርን የማያውቁ፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙት’ ናቸው ሲል ገልጿል። (2 ተሰሎንቄ 1:7–9) ከጥምሩ ምልክት ከፊሉ በማቴዎስ 24:14 ላይ ‘የመንግሥቱ ወንጌል በዓለም ሁሉ እንዲሰበክ’ የተሰጠውን ትእዛዝ በሚታዘዙ ሰዎች ፍጻሜውን ያገኛል።
በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ትእዛዝ በ231 አገሮችና ደሴቶች ላይ እያከናወኑ ነው። ሰዎችን ቤታቸው ድረስ ሄደው ያነጋግሯቸዋል፤ በግለሰብ ደረጃም ስለ ይሖዋ ንጉሣዊ መስተዳድር እንዲማሩ ይጋብዟቸዋል። ከዚህ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት ከሚተርፉት መካከል ለመሆንና ልቅሶ፣ ሐዘን፣ በሽታ ወይም ሞት በማይኖሩባት ገነት ምድር ላይ ለመኖር እያንዳንዱ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት መገንዘብ እንዲችል በደግነት ይረዱታል።—ራእይ 21:3, 4
ይህ ክፉ ዓለም የቀረው ጊዜ እየተሟጠጠ ነው። ከዚህ ዓለም ጥፋት ለመትረፍ የሚፈልጉ ሁሉ ‘ወንጌሉን መታዘዝና’ እንዲህ በማድረግም ከጥፋቱ ማምለጥ ምን ምን ነገሮችን ያካተተ መሆኑን መማራቸው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በሚቀጥለው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች እቤትዎ መጥተው ሲያነጋግሩዎት ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ የሚያቀርቡልዎትን ግብዣ ለምን አይቀበሉም? መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን መረዳት ስለሚፈልጉ ለምን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኑዎት አይጠይቋቸውም? እንዲያውም እንዲህ ማድረግዎ የተሻለ ነው።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መጽሐፍ ቅዱስን ለማስረዳት የተዘጋጀ መገናኛ መስመር
ኢየሱስ ሞቶ ከተነሣ በኋላ የእርሱ መገናኛ መስመር ሆኖ የሚያገለግል “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሚያስነሣ አረጋግጦልናል። (ማቴዎስ 24:45–47) ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች “ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን [በጉባኤ አዓት] በኩል . . . ትታወቅ ዘንድ፤ ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ” ብሎ በጻፈላቸው ጊዜ ይህን የመገናኛ መስመር ለይቶ ገልጾላቸዋል። (ኤፌሶን 3:10, 11) ‘የተገለጡት ነገሮች’ በአደራ የተሰጡት በ33 እዘአ ለተወለደው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ነው። (ዘዳግም 29:29) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በቡድን ደረጃ ታማኝና ልባም ባሪያ ሆነው ያገለግላሉ። (ሉቃስ 12:42–44) ከአምላክ የተሰጣቸው ሥራ ‘የተገለጡትን ነገሮች’ ለሌሎች ማስረዳት ነው።
በቀድሞው ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ወደ መሢሑ ይጠቁም እንደነበረ ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ታማኝና ልባም ባሪያ ሆኖ በሚያገለግለውና የጠበቀ ትስስር ባለው የቅቡዓን ክርስቲያን ምሥክሮች አካልም ላይ የትኩረት አቅጣጫችንን እንድናሳርፍ ያደርገናል።a ይህ ታማኝና ልባም ባሪያ የአምላክ ቃል እንዲገባን ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት የሚፈልጉ ሁሉ “ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ” ሊታወቅ የሚችለው የይሖዋ የመገናኛ መስመር በሆነው በታማኝና ልባም ባሪያ በኩል ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።—ዮሐንስ 6:68
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የመጋቢት 1, 1981 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 24–30 ይመልከቱ።