የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 15 ገጽ 131-ገጽ 134 አን. 5
  • ንጹሕና ሥርዓታማ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ንጹሕና ሥርዓታማ
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አለባበሳችንና ውጫዊ ገጽታችን ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
  • ሥርዓታማ አለባበሳችን ለአምላክ አክብሮት እንዳለን ያሳያል
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2003
  • አለባበሳችሁ አምላክን ያስከብራል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • አለባበሳችሁና የሰውነታችሁ አቋም ስለ እናንተ ይናገራል
    ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 15 ገጽ 131-ገጽ 134 አን. 5

ጥናት 15

ንጹሕና ሥርዓታማ

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ልብስህ ያልተዝረከረከ፣ ንጹሕና ሥርዓታማ ይሁን። ፀጉርህ በሥርዓት የተበጠረ ሊሆን ይገባል። ነቃ ብለህ ቁም።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አለባበስህና አበጣጠርህ ሰዎች ለምታምንባቸው ክርስቲያናዊ ትምህርቶችም ሆነ ለምትከተለው የሕይወት ጎዳና ባላቸው አመለካከት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይኖራል።

የሚመለከቱህ ሰዎች ከአለባበስህና ከአበጣጠርህ ስለ አንተ የሚረዱት ብዙ ነገር ይኖራል። ይሖዋ የሚያየው ልባችንን ቢሆንም ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚፈርዱት ‘ከውጭ በሚያዩት’ ነገር ነው። (1 ሳሙ. 16:​7) ሰዎች ፊት ስትቀርብ ንጹሕና ሥርዓታማ ከሆንክ ለራስህ ጥሩ ግምት እንዳለህ ስለሚያስቡ የምትናገረውንም ለመስማት ጆሮአቸውን ሊሰጡህ ይችላሉ። አለባበስህ ሥርዓታማ መሆኑ የምትወክለውን ድርጅት ከማስከበሩም በተጨማሪ አድማጮችህ ስለምታመልከው አምላክ በጎ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋል።

ልንሠራባቸው የሚገቡ መመሪያዎች። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ አለባበስና አበጣጠር የሚገልጽ ዝርዝር ደንብ አናገኝም። ይሁንና ጥሩ ውሳኔዎች ለማድረግ የሚረዱ ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶች አሉት። እነዚህን በአንድ ላይ የሚጠቀልለው “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ነው። (1 ቆሮ. 10:​31) አለባበሳችንንና አበጣጠራችንን በተመለከተ ልብ ልንላቸው የሚገቡ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

በመጀመሪያ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰውነታችንም ሆነ ልብሳችን ንጹሕ እንዲሆን ይመክረናል። ይሖዋ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር በሰጠው ሕግ ውስጥ ንጽሕናን በተመለከተ አንዳንድ መመሪያዎችን አስፍሮ ነበር። ለምሳሌ ያህል ካህናቱ ሥራቸውን ሲያከናውኑ በተወሰነ ጊዜ ገላቸውን መታጠብና ልብሳቸውን ማጠብ ነበረባቸው። (ዘሌ. 16:​4, 24, 26, 28) ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም ከዚያ ሕግ በስተጀርባ ያሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች እስከ ዛሬም ድረስ ይሠራሉ። (ዮሐ. 13:​10፤ ራእይ 19:​8) በተለይ አምልኮአችንን በምናካሂድባቸው ቦታዎች ስንገኝ ወይም በመስክ አገልግሎት ስንካፈል ሌሎችን ቅር እንዳናሰኝ ሰውነታችንና ልብሳችን ንጹሕ መሆን አለበት፤ እንዲሁም መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳይኖረን መጠንቀቅ አለብን። በጉባኤ ንግግር ወይም ሠርቶ ማሳያ የሚያቀርቡ ሁሉ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል። ስለ አለባበሳችንና አበጣጠራችን ከልብ ማሰባችን ለይሖዋና ለድርጅቱ ያለንን አክብሮት ያሳያል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጨዋነትንና ጤናማ አስተሳሰብን እንድናዳብር ያበረታታናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ሴቶችን ሲመክር ‘ሴቶች ከጨዋነትና ከጤናማ አስተሳሰብ ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ ይሖዋን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፣ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቊ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ’ ብሏል። (1 ጢሞ. 2:​9, 10) በአለባበስና በአጋጌጥ ጨዋነትንና ጤናማ አስተሳሰብን ማንጸባረቅ ያለባቸው ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም ናቸው።

ጨዋ የሆነ ሰው ሌሎችን የሚያስከፋ ወይም ወደ ራሱ ትኩረት የሚስብ ነገር ላለማድረግ ይጠነቀቃል። ጤናማ አስተሳሰብ ደግሞ ማስተዋል ወይም ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዲኖረን ይረዳል። እነዚህ ባሕርያት ያሉት ሰው ለአምላክ የአቋም ደረጃዎች አክብሮት ስለሚኖረው ሚዛኑን ይጠብቃል። እነዚህን ባሕርያት ለማንጸባረቅ እንጥራለን ማለት ጨርሶ መዘነጥ አንችልም ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ስለ አለባበሳችንና አበጣጠራችን እንድንጠነቀቅና አጋጌጣችን አለቅጥ የተብለጨለጨ እንዳይሆን ይረዳናል። (1 ዮሐ. 2:​16) አምልኮአችንን በምናካሂድባቸው ቦታዎች ስንገኝም ይሁን በመስክ አገልግሎት ስንካፈል ወይም በሌሎች አጋጣሚዎች እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። በሌላውም ጊዜ የምንለብሰው ልብስ ቢሆን ጨዋነትንና ጤናማ አስተሳሰብን የሚያንጸባርቅ እንዲሆን እንፈልጋለን። በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታችን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎች መኖራቸው አይቀርም። ስለዚህ ጉባኤ ላይ ወይም ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ የምንለብሰው ዓይነት ልብስ ይኑረን ማለት ባይሆንም አለባበሳችን ንጹሕና ሥርዓታማ ሊሆን ይገባል።

የሁላችንም አለባበስ ተመሳሳይ ይሆናል ማለት አይደለም። ደግሞ እንደዚያ እንዲሆን አይጠበቅብንም። ሰዎች የየራሳቸው ምርጫ አላቸው። ይህ ምንም ስህተት የለበትም። ይሁን እንጂ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ልንከተል ይገባል።

ሐዋርያው ጴጥሮስ ፀጉርን ከመሸረብና ከውጫዊው ልብስ ይበልጥ ዋጋ ያለው ‘የተሰወረው የልብ ሰው’ መሆኑን ገልጿል። (1 ጴጥ. 3:​3, 4) ልባችን በፍቅር፣ በደስታ፣ በሰላም፣ በደግነት እና በጠንካራ እምነት የተሞላ ከሆነ እነዚህ ባሕርያት አምላክን እንደሚያስከብር ልብስ ይሆኑልናል።

በሦስተኛ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አለባበሳችንና አበጣጠራችን ሥርዓታማ ስለመሆኑ እንድናስብ አጥብቆ ይመክረናል። በ⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​9 [NW ] ላይ ስለ ‘ሥርዓታማ አለባበስ’ ተጠቅሷል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይናገር የነበረው ስለ ሴቶች አለባበስ ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለወንዶችም ይሠራል። ሥርዓታማ የሚባለው ንጹሕና ያልተዝረከረከ ሲሆን ነው። ሀብታምም ሆንን ድሃ ንጹሕ አለባበስ ሊኖረን ይችላል።

ሰዎች ሲመለከቱን በቅድሚያ ከሚያስተውሏቸው ነገሮች አንዱ ፀጉራችን ነው። ንጹሕና ሥርዓት ባለው መንገድ የተያዘ ሊሆን ይገባል። የአካባቢው ባሕልና ተፈጥሮአችን የፀጉራችንን አሠራርና አበጣጠር ሊወስነው ይችላል። በ⁠1 ቆሮንቶስ 11:​14, 15 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ፀጉር አያያዝ የሰጠውን ምክር እናገኛለን። ምክሩ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ግምት ውስጥ ያስገባ ነው። ይሁንና አንድ ሰው በፀጉር አሠራሩ ተቃራኒ ፆታን ለመምሰል እየጣረ ከሆነ ይህ አድራጎቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይጋጫል።​—⁠ዘዳ. 22:​5

ወንዶች ንጹሕና ሥርዓታማ ለመሆን ጢማቸውንም በደንብ መላጨት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ከአፍንጫ ሥር ያለውን ጢም ማሳደግ በተለመደባቸው አካባቢዎች ይህንን ጢማቸውን የሚያሳድጉ ካሉ በሚገባ መከርከም ይኖርባቸዋል።

በአራተኛ ደረጃ፣ አለባበሳችንና አበጣጠራችን ዓለምንና የዓለምን የአኗኗር ዘይቤ እንደምንወድድ የሚያሳይ ሊሆን አይገባም። ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ” ሲል አስጠንቅቋል። (1 ዮሐ. 2:​15-17) ይህ ዓለም በኃጢአት ምኞቶች የተዋጠ ነው። ከእነዚህ መካከል ዮሐንስ የጠቀሰው የኃጢአተኛውን ሥጋ ምኞትና የይታይልኝ ባይነትን መንፈስ ነው። በሌሎች ጥቅሶች ላይ ደግሞ የዓመፀኝነት መንፈስ ወይም ለሥልጣን ለመገዛት እምቢተኛ የመሆን ዝንባሌ ተጠቅሶ እናገኛለን። (ምሳሌ 17:​11፤ ኤፌ. 2:​2) ብዙውን ጊዜ እነዚህ ምኞቶችና ዝንባሌዎች በአለባበስና በአጋጌጥ ይገለጻሉ። ከዚህ የተነሳ አለባበሳቸውና አጋጌጣቸው ጨዋነት የጎደለው፣ የፆታ ስሜት የሚያነሳሳ፣ አለቅጥ የተብለጨለጨ፣ የተዝረከረከ ወይም ቅጥ ያጣ ነው። የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን እንዲህ ያለውን ክርስቲያናዊ ያልሆነ መንፈስ ከሚያንጸባርቅ ፋሽን እንርቃለን።

በአለባበስና በአጋጌጥ ረገድ ዓለምን ከመኮረጅ ይልቅ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንዶችና ሴቶችን ግሩም ምሳሌ መከተሉ ምንኛ የተሻለ ይሆናል! ወደፊት የሕዝብ ተናጋሪ የመሆን ግብ ያላቸው ወጣቶች የሕዝብ ንግግር የሚሰጡ ወንድሞችን አለባበስ ልብ ሊሉ ይገባል። ሁላችንም ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ካገለገሉት ወንዶችና ሴቶች ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።​—⁠1 ጢሞ. 4:​12፤ 1 ጴጥ. 5:​2, 3

በአምስተኛ ደረጃ ደግሞ ተገቢ የሆነ ውሳኔ ማድረግ እንድንችል ‘ክርስቶስ እንኳ ራሱን ደስ እንዳላሰኘ’ ማስታወስ ይኖርብናል። (ሮሜ 15:​3) ኢየሱስን ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስበው የአምላክን ፈቃድ መፈጸሙ ነበር። ከራሱ ምቾት ይልቅ የሌሎችን ጥቅም ያስቀድም ነበር። በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን ረገድ በምናገለግልበት አካባቢ ያሉትን ሰዎች ቅር የሚያሰኝ ነገር ካለ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ክርስቶስ ያሳየውን የትሕትና መንፈስ መኮረጃችን ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ጠቅሷል። (2 ቆሮ. 6:3) ከዚህ የተነሣ የምንመሠክርላቸውን ሰዎች ላለማሰናከል ስንል አንዳንድ አለባበሶችን ወይም የፀጉር አሠራሮችን እንተው ይሆናል።

ትክክለኛ አቋቋም። አድማጮች ፊት ስንቀርብ ስለ አቋቋማችን ጭምር ማሰብ ይኖርብናል። እርግጥ ሁላችንም አንድ ዓይነት አቋቋም ይኖረናል ማለት አይደለም፤ ተመሳሳይ አቋቋም እንዲኖረን መጣርም አያስፈልገንም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጠቁመው ቀጥ ብሎ መቆም አንድ ሰው ያለውን የመተማመን መንፈስና አዎንታዊ አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። (ዘሌ. 26:​13፤ ሉቃስ 21:​28) የሆነ ሆኖ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ለዓመታት ብዙ አጎንብሰው ከመሥራታቸው የተነሣ ወይም ዕድሜያቸው በመግፋቱ አሊያም በጤና እክል ምክንያት ቀጥ ብለው መቆም ሊቸገሩ ወይም ደግሞ የሚደገፉት ነገር ሊፈልጉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ሁሉ ግዴለሽነት ወይም መቅለስለስ እንዳይመስልባቸው ከሌሎች ጋር ሲነጋገሩ በተወሰነ መጠን ቀጥ ብለው መቆማቸው አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይም አንድ ተናጋሪ አልፎ አልፎ እጁን አትራኖሱ ላይ ማሳረፉ ስህተት ባይሆንም አትራኖሱን ተመርኩዞ አለመቆሙ አድማጮች ለተናጋሪው አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ይረዳል።

በሥርዓት የተያዙ ጽሑፎች። በዚህ ዋና ርዕስ ሊታሰብበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ ለአገልግሎት የምንጠቀምባቸው ጽሑፎች ንጹሕና በሥርዓት የተያዙ መሆናቸው ነው።

መጽሐፍ ቅዱስህን እንደ ምሳሌ እንጥቀስ። ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱሳችን ሲያረጅ አዲስ መተካት እንችላለን ማለት አይደለም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሳችንን የቱንም ያህል ለረጅም ዓመት ብንጠቀምበት በጥንቃቄ እንደያዝነው የሚያሳይ ሊሆን ይገባል።

ለአገልግሎት የምንጠቀምበትን ቦርሳ በተለያዩ መንገዶች ማደራጀት ቢቻልም የተዝረከረከ መሆን የለበትም። አንድ አስፋፊ ለሚያነጋግረው ሰው ጥቅስ ለማንበብ ሲዘጋጅ ወይም አንድ ወንድም በጉባኤ ውስጥ ክፍል ሲያቀርብ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ ወረቀቶች ሲወዳድቁ አይተህ ታውቃለህ? ይህ ሁኔታ ትኩረትህን ሰርቆት መሆን አለበት። አይደለም? መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ ያስቀመጥካቸው ወረቀቶች የሌሎችን ትኩረት እንዳይሰርቁ ስትል ሌላ ቦታ ካስቀመጥህ ጽሑፎችህን በሥርዓት ይዘሃል ማለት ነው። በአንዳንድ ባሕሎች መጽሐፍ ቅዱስህን ወይም ሌሎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን ወለል ላይ ማስቀመጥ ጽሑፎቹን እንደማቃለል ተደርጎ እንደሚታይም መዘንጋት አይኖርብህም።

ለተመልካች ሥርዓታማ ሆነን መታየታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ሌሎች ለእኛ የሚኖራቸውንም አመለካከት ይነካል። ከሁሉ በላይ ግን ለዚህ ጉዳይ ለየት ያለ ትኩረት የምንሰጠው ‘አዳኛችን ከሆነው አምላክ ያገኘነው ትምህርት በሌሎች ዘንድ ውብ ሆኖ እንዲታይ’ ማድረግ ስለምንፈልግ ነው።​—⁠ቲቶ 2:9-11

ራስህን ፈትሽ

  • ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው?

  • ሁለንተናህ ጨዋነትንና ሚዛናዊ አስተሳሰብን የሚያንጸባርቅ ነው?

  • ሁሉም ነገር በሥርዓት የተያዘ ነው?

  • ፀጉርህ በሥርዓት ተበጥሯል?

  • በአለባበስህና በአጋጌጥህ ረገድ ዓለምን እንደምትወድድ የሚያሳይ ነገር አለ?

  • አለባበስህና አጋጌጥህ ሌሎችን ሊያሰናክል ይችላል የሚያሰኝ ምክንያት ይኖራል?

መልመጃ:- የዕለቱ ውሎህ ምንም ይሁን ምን ለአንድ ሙሉ ሳምንት በየቀኑ በገጽ 132 ላይ በሚገኘው “ራስህን ፈትሽ” በሚለው ሣጥን ተጠቅመህ ራስህን ገምግም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ