ሥርዓታማ አለባበሳችን ለአምላክ አክብሮት እንዳለን ያሳያል
1. በቅርቡ ለሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
1 በቅርቡ “ለአምላክ ክብር ስጡ” በተባለው የ2003 የአውራጃ ስብሰባ ላይ ይሖዋ ከሚያቀርብልን ትምህርት የመካፈል መብት ይኖረናል። ይሖዋ እንዲህ የመሰለ ግሩም መንፈሳዊ ድግስ ስላዘጋጀልን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በስብሰባው ወቅትም ሆነ በሌሎች ጊዜያት በአለባበሳችንና በሁለመናችን ንጹሕና ሥርዓታማ በመሆን ለአምላክ አክብሮት እንዳለንና መንፈሳዊ ዝግጅቶቹን እንደምናደንቅ ማሳየት እንችላለን።—መዝ. 116:12, 17
2. ንጹሕና ሥርዓታማ መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ንጹሕና ሥርዓታማ:- በአለባበሳችንና በሁለመናችን ንጹሕና ሥርዓታማ የሆነውን የአምላክን የአቋም ደረጃዎች መከተል ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 14:33፤ 2 ቆሮ. 7:1) ሰውነታችን፣ ፀጉራችን፣ የእጃችን ጥፍሮች እንዲሁም ልብሳችን ንጹሕ መሆን አለበት። ዛሬ የተዝረከረከ አለባበስ የተለመደ ነገር ሆኗል። አንድ የታወቀ የፊልም ተዋናይ ወይም ተወዳጅ ስፖርተኛ በአለባበሱ ግድ የለሽ መሆኑ አንድ ክርስቲያንም እንደዚያ እንዲሆን ምክንያት አይሆነውም። ዘመን አመጣሽ ፋሽኖችን የምንከተል ከሆነ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ሊቸገሩ ይችላሉ።—ሚል. 3:18
3. በአለባበሳችን ረገድ በ1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
3 ለክርስቲያኖች የሚገባ አለባበስ:- ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ለሆነው ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን እንዲሸልሙና እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፣ መልካም እንዲያደርጉ’ ማበረታቻ ሰጥቷል። (1 ጢሞ. 2:9, 10) አለባበሳችን ተገቢ መሆን አለመሆኑን በጥንቃቄ ልናስብበት ይገባል። አለባበሳችን ያልተዝረከረከ፣ ንጹሕና ልከኛ መሆን ይኖርበታል። ቅጥ ያጣና የፆታ ስሜት የሚያነሳሳ ዓይነት አለባበስ ተገቢ አይደለም።—1 ጴጥ. 3:3፤
4, 5. ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ተግባራዊ ማድረግ ያለባቸው የትኛውን ማሳሰቢያ ነው?
4 ከዚህም በላይ ጳውሎስ “በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቊ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ” ከልክ በላይ እንዳይሽቀረቀሩ አሳስቧቸዋል። (1 ጢሞ. 2:9) ክርስቲያን ሴቶች በሚያደርጉት ጌጣጌጥ፣ መኳኳያና ሌሎች መጋጌጫዎች ረገድ ሚዛናዊ መሆናቸው ጥበብ ነው።—ምሳሌ 11:2
5 ጳውሎስ ለክርስቲያን ሴቶች የሰጠው ምክር በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ለክርስቲያን ወንዶችም ይሠራል። ወንድሞች የዓለምን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ፋሽን መከተል የለባቸውም። (1 ዮሐንስ 2:16) ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ አገሮች የተንቧለለ ልብስ መልበስ የተለመደ ቢሆንም እንዲህ ያለው አለባበስ ለአንድ የአምላክ አገልጋይ ተገቢ አይደለም።
6. ወደ ስብሰባው ስንጓዝም ሆነ ከዚያ ስንመለስ፣ በስብሰባው ላይ ስንሆን እንዲሁም ከእያንዳንዱ ቀን ስብሰባ በኋላ ባለው ጊዜ በአለባበሳችንና በሁለመናችን የላቀ የአቋም ደረጃ መከተል ያለብን ለምንድን ነው?
6 ከስብሰባው ውጪ ባሉት ጊዜያት:- አብዛኞቹ ወንድሞችና እህቶች በስብሰባው ላይ ሲገኙ በአለባበሳቸውና በሁለመናቸው በጣም ሥርዓታማ ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ወደ ስብሰባው ሲጓዙና ከስብሰባው ሲመለሱ ወይም ከስብሰባው በኋላ ባለው ጊዜ ለአለባበሳቸው እንደማይጠነቀቁ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። ስብሰባው በሚካሄድባቸው ቀናትም ሆነ በሌሎች ጊዜያት አለባበሳችንና ሁለመናችን ሌሎች ለአምላክ ሕዝቦች ባላቸው አመለካከት ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ የታወቀ ነው። የአውራጃ ስብሰባውን የባጅ ካርድ ስለምናደርግ አለባበሳችን ምንጊዜም ለክርስቲያን አገልጋዮች የሚገባ ዓይነት መሆን ይኖርበታል። ይህም በአብዛኛው ሰዎች እንዲያመሰግኑን የሚያነሳሳቸው ከመሆኑም በላይ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል።—1 ቆሮ. 10:31-33
7. በአለባበሳችንና በሁለመናችን ሥርዓታማ መሆናችን ሌሎች ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል?
7 ወዳጃዊ ፈገግታ ማራኪ ገጽታ እንደሚሰጠን ሁሉ አለባበሳችንና ሁለመናችን ሥርዓታማ መሆኑ መልእክታችንንና የምንወክለውን ድርጅት ያስከብራል። “ለአምላክ ክብር ስጡ” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ወቅት ወይም በዓመቱ ውስጥ በሌሎች ጊዜያት የሚያዩን አንዳንድ ሰዎች የተለየን የሆንንበትን ምክንያት ለማወቅ ሊፈልጉና ብሎም “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ” ሊሉ ይችላሉ። (ዘካ. 8:23) ሁላችንም በአለባበሳችንና በሁለመናችን ለይሖዋ አክብሮት እንዳለን እናሳይ።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]
አለባበሳችሁም ሆነ ሁለመናችሁ ክብር ያለው ይሁን
▪ በጉዞ ላይ ስትሆኑ
▪ በአውራጃ ስብሰባው ላይ
▪ ከስብሰባው በኋላ ባለው ጊዜ