የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 6 ገጽ 101-ገጽ 104 አን. 3
  • ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅ
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጥቅስ ስታነብብ ተፈላጊውን ነጥብ ማጉላት
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ማጥበቅና ድምፅን መለዋወጥ
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ውጥረትን መቆጣጠር የምንችልበት መንገድ
    ንቁ!—2010
  • ጥሩና መጥፎ ውጥረት
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 6 ገጽ 101-ገጽ 104 አን. 3

ጥናት 6

ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅ

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

አድማጮች እየተብራራ ያለውን ሐሳብ እንዲረዱ በሚያስችል መንገድ ቃላትንና ሐረጎችን ማጉላት።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አንድ ተናጋሪ ቁልፍ ቃላትን ወይም ሐረጎችን በተገቢው ሁኔታ የሚያጠብቅ ከሆነ አድማጮቹ በትኩረት እንዲከታተሉት ማድረግ ከመቻሉም ሌላ ሊያሳምናቸውና ለሥራ ሊያነሳሳቸው ይችላል።

ንግግር በምትሰጥበትም ሆነ ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ እያንዳንዱን ቃል በትክክል መጥራትህ ብቻ ሳይሆን ቁልፍ የሆኑትን ቃላትና መልእክት አዘል አገላለጾች፣ ሐሳቡን በግልጽ ለማስተላለፍ በሚያስችል መንገድ ጠበቅ አድርገህ ማንበብህም በጣም አስፈላጊ ነው።

ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅ ሲባል ጥቂት ወይም ብዙ ቃላትን ማጉላት ማለት ብቻ አይደለም። መጥበቅ ያለባቸው ትክክለኛዎቹ ቃላት ናቸው። የተሳሳቱ ቃላትን የምታጠብቅ ከሆነ አድማጮች የምትናገረው ነገር ትርጉም ግልጽ ላይሆንላቸው ይችላል። ይህ ደግሞ አእምሯቸው እንዲባዝን ምክንያት ይሆናል። ትምህርቱ ጥሩ ቢሆንም እንኳ ተናጋሪው ቁልፍ ቃላትን ወይም ሐረጎችን በሚገባ የማያጠብቅ ከሆነ አቀራረቡ አድማጮቹን ለሥራ የመቀስቀስ ኃይል አይኖረውም።

የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ግነቱን መጨመር የሚቻል ሲሆን ብዙ ጊዜ የሚከተሉት ዘዴዎች በአንድነት ሲሠራባቸው እናገኛለን:- የድምፅን መጠን ከፍ ማድረግ፣ ግለትን መጨመር፣ ዝግና ረጋ ብሎ መናገር፣ ከአንድ ሐሳብ በፊት ወይም በኋላ (ወይም በሁለቱም ቦታ) ቆም ማለትና አካላዊ መግለጫ ናቸው። በአንዳንድ ቋንቋዎች ድምፅን ከፍ ወይም ዝቅ በማድረግ ማጉላት ይቻላል። ይበልጥ ተስማሚ የሚሆነው የትኛው ዘዴ እንደሆነ ለመወሰን ትምህርቱንና ሌሎች ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ አስገባ።

የት ላይ ማጉላት እንዳለብህ ለመወሰን የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል። (1) በየትኛውም ዓረፍተ ነገር ውስጥ ቢሆን መጥበቅ ያለባቸውን ቃላት ለመወሰን የሚረዳህ ዓረፍተ ነገሩ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያለው ሐሳብ ጭምር ነው። (2) አንድ ዋና ነጥብ የሚጀምርበት ወይም የሐሳብ ለውጥ የሚደረግበት ቦታ ጎላ ብሎ እንዲታይ ለማድረግ ቁልፍ ቃላትንና ሐረጎችን የማጥበቅን ዘዴ ልትጠቀም ትችላለህ። ይህንኑ ዘዴ በመጠቀም አድማጮች የአንድ ነጥብ ማጠቃለያ ላይ እንደደረስክ እንዲገነዘቡ ማድረግም ይቻል ይሆናል። (3) አንድ ተናጋሪ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚሰማው ለማንጸባረቅም ተስማሚ የሆኑትን ቃላት ወይም ሐረጎች ሊያጠብቅ ይችላል። (4) ይህ ዘዴ የአንድን ንግግር ዋና ዋና ነጥቦች ለማጉላትም ሊሠራበት ይችላል።

አንድ ሰው ንግግር ሲሰጥም ሆነ ለሌሎች ሲያነብ በእነዚህ መንገዶች ለማጥበቅ እንዲችል በመጀመሪያ ራሱ ትምህርቱን በግልጽ ሊረዳው እንዲሁም አድማጮቹ እንዲገባቸው የመርዳት ልባዊ ፍላጎት ሊኖረው ይገባል። በዕዝራ ዘመን የተሰጠውን ትምህርት በተመለከተ ነህምያ 8:​8 እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፣ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር።” በወቅቱ የአምላክን ሕግ ያነብቡና ያብራሩ የነበሩት ሰዎች አድማጮቻቸው የሚነበበውን ነገር ትርጉም እንዲያስተውሉና አስታውሰውም ተግባራዊ እንዲያደርጉት መርዳት እንዳለባቸው ተገንዝበው እንደነበር ግልጽ ነው።

ችግሩ ምን ሊሆን ይችላል? አብዛኛዎቹ ሰዎች በዕለት ተዕለት ንግግራቸው ሐሳባቸውን ቁልጭ አድርገው መግለጽ አይቸግራቸውም። ይሁን እንጂ ሌላ ሰው የጻፈውን ጽሑፍ በሚያነብቡበት ጊዜ የትኛው ቃል ወይም ሐሳብ መጥበቅ እንዳለበት ለመወሰን ይቸገራሉ። ለዚህ ዋነኛ መፍትሔው መልእክቱን በግልጽ መረዳት ነው። ይህም ጽሑፉን በደንብ ማጥናትን ይጠይቃል። በመሆኑም በጉባኤ ስብሰባ ላይ አንድ ጽሑፍ እንድታነብብ ከተመደብህ ጥሩ አድርገህ መዘጋጀት ይኖርብሃል።

አንዳንድ ሰዎች ቁልፍ ቃላትን ወይም ሐረጎችን ብቻ ከማጥበቅ ይልቅ ትርጉም ኖረውም አልኖረው እንዲሁ አለፍ አለፍ እያሉ አንዳንድ ቃላትን ያጠብቃሉ። ሌሎች ደግሞ መስተዋድዶችንና መስተጻምሮችን ሳይቀር ከልክ በላይ ያጠብቃሉ። የምናጎላው ነገር ሐሳቡን ግልጽ ለማድረግ የሚረዳ ካልሆነ የአድማጮችን ትኩረት ከመስረቅ በቀር ፋይዳ አይኖረውም።

አንዳንድ ተናጋሪዎች ቁልፍ ቃላትን ለማጥበቅ በማሰብ ጮክ ብለው ስለሚናገሩ አድማጮች ንግግሩ ወቀሳ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ይህ ደግሞ የሚያመጣው ጥሩ ውጤት አይኖርም። ተናጋሪው የሚያጠብቅበት መንገድ የተጋነነ ከሆነ አድማጮቹን የናቃቸው ሊያስመስልበት ይችላል። ከዚህ ይልቅ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በመናገር ትምህርቱ ቅዱስ ጽሑፋዊና ምክንያታዊ መሆኑን እንዲያስተውሉ መርዳቱ ምንኛ የተሻለ ይሆናል!

ማሻሻል የሚቻልበት መንገድ። ብዙውን ጊዜ ቁልፍ ቃላትን ወይም ሐረጎችን በማጥበቅ ረገድ ችግር ያለበት ሰው ችግሩ እንዳለበት እንኳ አይታወቀውም። ምናልባት ሌላ ሰው ይህን ድክመቱን እንዲጠቁመው ያስፈልግ ይሆናል። በዚህ ረገድ ማሻሻል የሚያስፈልግህ ከሆነ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ይረዳሃል። ጥሩ ተናጋሪ የሆነ ሌላ ወንድምም ቢሆን ምክር እንዲሰጥህ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። ስታነብብ እና ስትናገር በጥሞና አዳምጦ ልታሻሽል የምትችልባቸውን አቅጣጫዎች እንዲጠቁምህ ጠይቀው።

በመጀመሪያ ምክር ሰጪህ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እያነበብህ እንድትለማመድ ሐሳብ ሊያቀርብልህ ይችል ይሆናል። መልእክቱን ግልጽ ለማድረግ የሚረዱትን ቃላትና ሐረጎች መርጠህ ማጉላት እንድትችል እያንዳንዱን ዓረፍተ ነገር ማጤን እንደሚያስፈልግህ ሊመክርህ ይችላል። በሰያፍ ለተጻፉት አንዳንድ ቃላት ለየት ያለ ትኩረት እንድትሰጥ ያሳስብህ ይሆናል። በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ያሉ ቃላት እርስ በርስ እንደሚደጋገፉ አትዘንጋ። ብዙ ጊዜ ማጉላት ያለብህ በርከት ያሉ ቃላትን እንጂ አንድን ቃል አይደለም። በአንዳንድ ቋንቋዎች ተማሪዎቹ ቁልፍ ቃላትን ወይም ሐረጎችን በተገቢው ሁኔታ ለማጥበቅ የሚረዱ አናባቢ ምልክቶችን ልብ ብለው እንዲያነቡ ምክር ሊሰጣቸው ይችላል።

በመቀጠል ደግሞ ማጉላት ያለብህን ነገር መወሰን እንድትችል በዓረፍተ ነገሩ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ሰፋ አድርገህ እንድትመለከት ይመክርህ ይሆናል። የአንቀጹ ዋና ነጥብ ምንድን ነው? ይህስ በእያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ጎላ አድርገህ መግለጽ ያለብህን ሐሳብ በተመለከተ ወሳኝነት ያለው እንዴት ነው? ዋናውን ርዕስና ነጥቡ የተጠቀሰበትን ንዑስ ርዕስ ተመልከት። ይህስ የምታጎላውን ሐሳብ ለመምረጥ የሚረዳህ እንዴት ነው? እነዚህ ሁሉ ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። ይሁንና የምታጎላቸው ቃላት በጣም ብዙ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርብሃል።

ምክር ሰጪህ አስተዋጽኦ ይዘህ ንግግር ስትሰጥም ይሁን በቀጥታ ከአንድ ጽሑፍ በምታነብበት ጊዜ ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ለማጥበቅ ነጥቡ እየተብራራ ያለበትን አቅጣጫ ልብ እንድትል ያሳስብህ ይሆናል። እያንዳንዱ ነጥብ የሚያበቃበትን ወይም ትምህርቱ ከአንዱ ሐሳብ ወደሌላ አስፈላጊ ነጥብ የሚሸጋገርበትን ቦታ ልብ ማለት ያስፈልግሃል። አቀራረብህ እነዚህን ነጥቦች በደንብ ለመለየት የሚያስችል ከሆነ አድማጮችህ ከትምህርቱ እንዲጠቀሙ እንደረዳሃቸው ይሰማቸዋል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ከዚህ ቀጥሎ፣ በመጨረሻ እና እንግዲያው እንደሚሉት ያሉትን ቃላት ለየት ባለ ቃና በመጥራት ይህንን ማድረግ ትችል ይሆናል።

እንዲሁም ምክር ሰጪህ በተለየ ስሜት መግለጽ የምትፈልጋቸው ነጥቦች ላይ እንድታተኩር ሐሳብ ይሰጥህ ይሆናል። ይህንንም ለማድረግ በጣም፣ በፍጹም፣ በምንም ዓይነት፣ የማይታሰብ ነው፣ በጣም አስፈላጊ፣ እና ምንጊዜም የሚሉትን ቃላት ጎላ አድርገህ ልትገልጻቸው ትችል ይሆናል። እንዲህ ማድረግህ አድማጮች ለመልእክቱ በሚኖራቸው ስሜት ረገድ የራሱ ድርሻ አለው። ይህ ጉዳይ “ወዳጃዊ ስሜት የሚያንጸባርቅ” በሚለው በ11ኛው ጥናት ላይ ተጨማሪ ሐሳብ ይሰጥበታል።

ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ በማጥበቅ ረገድ መሻሻል ከፈለግህ አድማጮችህ እንዲያስታውሷቸው የምትፈልጋቸው ዋና ዋና ነጥቦች በቅድሚያ ለአንተ ግልጽ ሊሆኑልህ ይገባል። ይህ ነጥብ “ዋና ዋና ነጥቦችን አጽንዖት ሰጥቶ ማንበብ” በሚለው ጥናት 7 ውስጥ ለሌሎች ከማንበብ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጥበታል። “ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ” በሚለው ጥናት 37 ውስጥ ደግሞ ከንግግር ጋር በተያያዘ ይብራራል።

በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን እየጣርክ ከሆነ ጥቅሶችን ስለምታነብበት መንገድ አጥብቀህ ልታስብ ይገባል። ‘ይህን ጥቅስ የማነብበት ምክንያት ምንድን ነው?’ እያልክ ራስህን የመጠየቅ ልማድ ይኑርህ። አንድ አስተማሪ ቃላቱን አስተካክሎ መናገሩ ብቻውን በቂ ላይሆን ይችላል። ሐሳቡን በስሜት ማንበቡም ቢሆን በቂ ነው ማለት አይደለም። አንድ ሰው ላነሳው ጥያቄ መልስ እየሰጠህ ወይም ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እያስተማርህ ከሆነ እየተብራራ ያለውን ነጥብ የሚደግፉትን የጥቅሱን ቃላት ወይም ሐሳቦች ጎላ አድርጎ መግለጹ ተገቢ ይሆናል። አለበለዚያ ግን ጥቅሱን የምታነብብለት ሰው መልእክቱን ሳይጨብጠው ሊቀር ይችላል።

ብዙም ልምድ የሌለው አንድ ተናጋሪ ለማጉላት በማሰብ አንዳንድ ቃላትን ወይም ሐረጎችን ከልክ በላይ ያጠብቅ ይሆናል። ሁኔታውን የሙዚቃ ኖታዎችን አቀናጅቶ ለመጫወት እየሞከረ ካለ ጀማሪ ሙዚቀኛ ጋር ማመሳሰል ይቻላል። ሰውዬው ልምድ እያገኘ ሲሄድ “ኖታዎቹን” ጥሩ አድርጎ በመጫወት ውብ የሆነ “ሙዚቃ” ማውጣት ይችላል።

አንዴ መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች ከተማርክ በኋላ ተሞክሮ ያላቸውን ተናጋሪዎች በመመልከት ተጨማሪ ልምድ መቅሰም ትችላለህ። በዚህ መንገድ በተለያየ መጠን ቃላትንና ሐረጎችን ማጉላት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ማስተዋልህ አይቀርም። እንዲሁም የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ነጥቡን ማጉላት መልእክቱን ግልጽ ለማድረግ ምን ያህል ጉልህ ድርሻ እንዳለው እየተገነዘብህ ትሄዳለህ። ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅን መማር የንባብህንም ሆነ የንግግርህን ውጤታማነት ያሻሽልልሃል።

በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅን መማር ያለብህ ለምታቀርበው ክፍል ስትል ብቻ መሆን የለበትም። ውጤታማ ተናጋሪ ሆነህ እንድትገኝ ይህ የንግግር ባሕርይ ተዋህዶህ ለሌሎች ጆሮ በሚጥም መንገድ ተፈላጊውን ነጥብ ማጥበቅ እስክትችል ድረስ መለማመድህን ቀጥል።

እንዴት ልታዳብረው ትችላለህ?

  • በዓረፍተ ነገር ውስጥ የሚገኙትን ቁልፍ ቃላት ነጥለህ ማውጣትን ተማር። ቁልፍ የሆኑትን ቃላት ለመለየት በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ልብ በል።

  • (1) የሐሳብ ለውጥ የተደረገበትን ቦታ ለመጠቆም እንዲሁም (2) ስለ ጉዳዩ ያለህን ስሜት ለማንጸባረቅ የማጉላትን ዘዴ ለመጠቀም ሞክር።

  • ጥቅስ በምታነብበት ጊዜ ከተጠቀሰበት ምክንያት ጋር በቀጥታ የሚዛመዱትን ቃላት የማጉላት ልማድ ይኑርህ።

መልመጃ፦ (1) በአገልግሎት አዘውትረህ የምትጠቀምባቸውን ሁለት ጥቅሶች ምረጥ። እያንዳንዱን ጥቅስ ስትጠቀም ማስረዳት የፈለግኸው ነገር ምን እንደሆነ አስብ። ከዚያም ድምፅህን እያሰማህ ነጥቦቹን የሚደግፍልህን ቃል (ወይም ቃላት) ጎላ አድርገህ አንብብ። (2) ዕብራውያን 1:​1-14ን አጥና። በምዕራፉ ውስጥ እየተብራራ ያለውን ነጥብ ግልጽ ለማድረግ (ቁጥር 1 ላይ) “ነቢያት”፣ (ቁጥር 2 ላይ) “ልጁ” እንዲሁም (ቁጥር 4 እና 5 ላይ) “መላእክት” የሚሉት ቃላት ለየት ያለ ግነት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ዋናውን ነጥብ በሚያጎላ መንገድ በማጥበቅ መላውን ምዕራፍ እያነበብህ ተለማመድ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ