ጥሩና መጥፎ ውጥረት
“ውጥረት ሰውነት ማንኛውም ዓይነት ችግር ሲያጋጥመው የሚሰጠው ምላሽ በመሆኑ ሁሉም ሰው በማንኛውም ጊዜ መጠኑ ይለያይ እንጂ ውጥረት ይኖርበታል።”—ዶክተር ሐንስ ሴልይ
አንድ የማሲንቆ ተጫዋች የማሲንቆው ክር በሚገባ የተወጠረ ካልሆነ ምንም ዓይነት ሙዚቃ ሊጫወት አይችልም። በሚወጠርበት ጊዜም ቢሆን ትክክለኛውን መጠን የጠበቀ መሆን ይኖርበታል። በጣም ከተወጠረ የሙዚቃው ድምፅ በጣም የሰለለ ይሆናል። በጣም ከረገበ ደግሞ ምንም ዓይነት ድምፅ ሊያወጣ አይችልም። ስለዚህ ክሩ በጣምም መወጠር በጣምም መላላት የለበትም።
ውጥረትም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። ከበዛ ቀደም ብለን እንዳየነው ጎጂ ሊሆን ይችላል። ውጥረት የሚባል ነገር ፈጽሞ ካልኖረስ? ከውጥረት ነፃ መሆን የሚለው ሐሳብ ጥሩ ነገር ቢመስልም ቢያንስ መጠነኛ የሆነ ውጥረት አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ መንገድ ልታቋርጥ ስትል በድንገት ከፊት ለፊትህ በከፍተኛ ፍጥነት የሚመጣ መኪና ትመለከታለህ። ከፊትህ ከመጣብህ አደጋ ፈጥነህ እንድታመልጥ የሚያስችልህ ውጥረት ነው!
ይሁን እንጂ ውጥረት የሚጠቅመው ለድንገተኛ ሁኔታዎች ብቻ አይደለም። የዕለት ተዕለት ተግባሮችህንም ለመፈጸም ውጥረት ያስፈልግሃል። ሁሉም ሰው በማንኛውም ጊዜ መጠነኛ የሆነ ውጥረት ይኖርበታል። ‘ሙሉ በሙሉ ከውጥረት መላቀቅ የሚቻለው በሞት ብቻ ነው’ ይላሉ ዶክተር ሐንስ ሴልይ። አክለውም “እገሌ ውጥረት አለበት” ማለት “እገሌ አተኩሶታል” የማለት ያህል ነው። “በዚህ አነጋገራችን ግለሰቡ ያለበት ውጥረት ወይም የሰውነት ሙቀት ከመጠን ያለፈ መሆኑን መግለጻችን ነው” ብለዋል። በዚህ መሠረት በመዝናናት ጊዜም ሆነ እንቅልፍ ተኝተህ ልብህ መምታቱንና ሳንባህም መሥራቱን ስለማያቆም ውጥረት ይኖርብሃል ማለት ነው።
ሦስት የውጥረት ዓይነቶች
ውጥረት በመጠን እንደሚለያይ ሁሉ በዓይነትም ይለያያል።
ድንገተኛ ውጥረት የዕለት ተዕለት ኑሮ በሚያስከትለው ጫና ምክንያት የሚመጣ ነው። ብዙ ጊዜ መፍትሔ ማግኘት ከሚያስፈልጋቸው አስከፊ ሁኔታዎች ጋር ይዛመዳል። ይህ ዓይነቱ ውጥረት ድንገተኛና ጊዜያዊ በመሆኑ ምክንያት ብዙውን ጊዜ ለመቋቋም አስቸጋሪ አይሆንም። እርግጥ የተለያዩ ችግሮች በተደጋጋሚ የሚፈራረቁባቸውና መላ ሕይወታቸው የሚመሰቃቀልባቸው አንዳንድ ሰዎች ይኖራሉ። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ድንገተኛ ውጥረት እንኳን በቁጥጥር ሥር ሊውል ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ባለው ውጥረት የሚሰቃየው ግለሰብ ጭንቀት የነገሠበት አኗኗሩ በእርሱም ሆነ አብረውት በሚኖሩ ላይ ያስከተለውን ውጤት እስኪገነዘብ ድረስ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል።
ድንገተኛ ውጥረት ጊዜያዊ ሲሆን ሥር የሰደደ ውጥረት ግን ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ነው። ሥር የሰደደ ውጥረት የደረሰበት ግለሰብ እንደ ድህነት ወይም እንደ መጥፎ ሥራ ወይም እንደ ሥራ ማጣት ባለ ችግር የሚሠቃይ ስለሆነ ከችግሩ የሚወጣበት መንገድ ፈጽሞ ይጨልምበታል። በተጨማሪም ለረዥም ጊዜ የቆየ የቤተሰብ ችግር ሥር የሰደደ ውጥረት ሊያስከትል ይችላል። ሕመምተኛ ለሆነ የቤተሰብ አባል እንክብካቤ ማድረግም ውጥረት ሊያስከትል ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ሥር የሰደደ ውጥረት አንድን ግለሰብ ከቀን ወደ ቀን፣ ከሳምንት ወደ ሳምንት፣ ከወር ወደ ወር ውስጥ ውስጡን እየበላ ይጨርሰዋል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተጻፈ አንድ መጽሐፍ እንዳለው “ሥር የሰደደ ውጥረት ከሁሉ የከፋ ገጽታው ሰዎች የሚላመዱት መሆኑ ነው። ድንገተኛ ውጥረት አዲስ ነገር በመሆኑ ሰዎች ወዲያው ያውቁታል። ሥር የሰደደ ውጥረት ግን ለረጅም ጊዜ የቆየ፣ የተለመደና አንዳንድ ጊዜም እምብዛም የማይጎረብጥ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ችላ ይባላል።”
ተገድዶ እንደመደፈር፣ እንደ ድንገተኛ አደጋ ወይም እንደ ተፈጥሮ አደጋ ያሉ ዘግናኝ ሁኔታዎች በሚፈጥሩት የስሜት መቃወስ ምክንያት የሚመጣ ውጥረትም (traumatic stress) አለ። በጦርነት የተካፈሉና በማጎሪያ ካምፖች ታስረው የነበሩ ብዙ ሰዎች ይህን የመሰለው ውጥረት ያጋጥማቸዋል። እንዲህ ዓይነት ውጥረት መኖሩን ከሚያሳዩት ምልክቶች መካከል ለስሜት ቀውሱ ምክንያት የሆነውን ዘግናኝ ሁኔታ ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንኳን በዝርዝር ለማስታወስ መቻልና ለጥቃቅን ሁኔታዎች ከልክ በላይ ድንጉጥ መሆን ይገኙበታል። በስሜት መቃወስ ምክንያት የሚመጣ ውጥረት መኖሩን ከሚያመለክቱ ምልክቶች መካከል ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ሐኪሞች በዚህ ዓይነቱ ውጥረት የሚሰቃየው ሰው ፖስት ትራውማቲክ ስትሬስ ዲስኦርደር (ፒ ቲ ኤስ ዲ) የተባለ በሽታ ይዞታል ይላሉ።—ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።
ለውጥረት በቀላሉ መሸነፍ
አንዳንዶች በአሁኑ ጊዜ ያለን ውጥረት የመቋቋም ችሎታ ከአሁኑ በፊት ባጋጠሙን የውጥረት ዓይነቶችና መጠን ላይ የተመካ እንደሆነ ይናገራሉ። የስሜት መቃወስ የሚያስከትሉ ሁኔታዎች በአንጎል ኬሚካላዊ “ጥንቅር” ላይ ለውጥ ስለሚያስከትሉ የአንድን ሰው ውጥረት የመቋቋም ችሎታ በጣም ያዳክማሉ። ለምሳሌ ያህል ዶክተር ሎረንስ ብራስ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ውጊያ ላይ ተሰማርተው በነበሩ 556 የቀድሞ ተዋጊዎች ላይ ባደረጉት ጥናት የጦር እስረኛ የነበሩት ተዋጊዎች የስሜት ቀውሱ ከገጠማቸው ከ50 ዓመት በኋላም እንኳን በስትሮክ በሽታ የመያዛቸው እድል የጦር እስረኛ ካልነበሩት በስምንት እጥፍ በልጦ ተገኝቷል። “የጦር እስረኛ መሆን የሚያስከትለው ውጥረት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ እነዚህ ሰዎች በወደፊቱ ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ውጥረቶች የሚቋቋሙበትን አቅም በጣም አድክሞባቸዋል።”
በልጅነት ዕድሜ ያጋጠሙ ውጥረት የሚያስከትሉ ሁኔታዎችም በጣም ከባድ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ስለሚችሉ ችላ መባል እንደሌለባቸው ሊቃውንቱ ይናገራሉ። “የስሜት መቃወስ ከሚደርስባቸው ሕፃናት መካከል አብዛኞቹ ወዲያው ወደ ሐኪም አይወሰዱም” ይላሉ ዶክተር ጂን ኪንግ። “ከችግራቸው ጋር ሲታገሉ ኖረው ከበርካታ ዓመታት በኋላ ከባድ ጭንቀት ወይም የልብ ሕመም ሲያሰቃያቸው ወደ ቢሮአችን ይመጣሉ።” ለምሳሌ ያህል ወላጅ ማጣት የሚያስከትለውን የስሜት መቃወስ እንመልከት። ዶክተር ኪንግ “ይህን የሚያክል ውጥረት ገና በጨቅላ ዕድሜ ላይ ሲደርስ በአንጎል የኬሚካልና የነርቭ አወቃቀር ላይ ዘላቂ የሆነ ቀውስ ስለሚፈጠር የተለመዱ የዕለት ተዕለት ውጥረቶችን መቋቋም አስቸጋሪ ይሆናል” ብለዋል።
እርግጥ የአንድ ሰው ውጥረት የመቋቋም ችሎታ በአካላዊ ጥንካሬው፣ ውጥረት የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን እንዲቋቋም የሚያስችሉ እርዳታዎችን በማግኘቱና በሌሎች ነገሮች የሚመካ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የውጥረቱ ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ ውጥረትን መቋቋም ይቻላል። እርግጥ ይህ ቀላል እንዳልሆነ አይካድም። ዶክተር ሬቸል የሁደ “ውጥረት የመቋቋም አቅሙ የተዳከመበትን ሰው አትጨነቅ፣ ዘና በል ማለት እንቅልፍ አልወስድህ ያለውን ሰው እንቅልፍ ተኛ ብሎ እንደመምከር ነው” ብለዋል። ቢሆንም የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚገልጸው አንድ ሰው ያጋጠመውን ውጥረት ለመቀነስ ሊያደርግ የሚችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሥራ ውጥረት—“ዓለም አቀፍ ችግር”
አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት “ውጥረት ከ20ኛው መቶ ዘመን እጅግ አሳሳቢ የጤና ችግሮች አንዱ ሆኗል” ይላል። በሥራ ቦታዎች በግልጽ የሚታይ ችግር ሆኗል።
• በአውስትራሊያ የመንግሥት ሠራተኞች ለሚደርስባቸው ውጥረት የሚጠይቁት ካሣ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 90 በመቶ አድጓል።
• በፈረንሳይ አገር የተደረገ አንድ ጥናት 64 በመቶ የሚሆኑ ነርሶችና 61 በመቶ የሚሆኑ አስተማሪዎች የሚሠሩበት አካባቢ በሚያሳድርባቸው ውጥረት ምክንያት በጣም እንደሚበሳጩ አረጋግጧል።
• ዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ በውጥረት ምክንያት በሚደርሱ በሽታዎች የ200 ቢልዮን ዶላር ኪሣራ ይደርስባታል። በኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል ከ75 እስከ 85 በመቶ የሚሆኑት ከውጥረት ጋር ዝምድና እንዳላቸው ይገመታል።
• በተለያዩ አገሮች ሴቶች ከወንዶች ይበልጥ በውጥረት እንደሚሰቃዩ ታውቋል። ይህም የሆነው የቤቱንም ሆነ የውጭውን ኃላፊነት ለመሸከም ስለሚገደዱ ሳይሆን አይቀርም።
በእርግጥም የሥራ ውጥረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንዳለው “ዓለም አቀፍ ችግር” ነው።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ፒ ቲ ኤስ ዲ—አስከፊ ለሆነ ገጠመኝ ጤናማ ምላሽ መስጠት
‘መኪናችን ከተጋጨች ሦስት ወር አልፏል። እኔ ግን አሁንም ማልቀሴን መተው ወይም ማታ መተኛት አልቻልኩም። ከቤት መውጣት እንኳን ያስፈራኛል።’—ሉዊዝ
ሉዊዝን የሚያሰቃያት ፖስት ትራውማቲክ ዲስኦርደር (ፒ ቲ ኤስ ዲ) የተባለው በሽታ ነው። ይህ በሽታ ቀስ በቀስ የሚያዳክም ሲሆን ግለሰቡ ያጋጠመውን አሰቃቂ ሁኔታ ደጋግሞ እንዲያስታውስ ወይም እንዲቃዥ ያደርገዋል። በተጨማሪም ፒ ቲ ኤስ ዲ ያለበት ሰው በቀላሉ ይበረግጋል። ለምሳሌ ያህል ማይክል ዴቪስ የተባሉት የአእምሮ ጤና ሊቅ አንድ በቬትናም ውጊያ ላይ ተሰማርቶ የነበረ ሰው በሠርጉ ዕለት አንድ የመኪና ጭስ መውጫ ባሰማው ኃይለኛ ድምፅ በርግጎ በአካባቢው ባለ ቁጥቋጦ ውስጥ እንደተሸጎጠ ተናግረዋል። “በዚያ አካባቢ ምንም የሚያስፈራ ነገር እንደሌለ ሊያሳምኑት የሚችሉ ብዙ ነገሮች ነበሩ” ይላሉ ዴቪስ። “ጦርነቱ ካበቃ 25 ዓመት አልፏል። ያለው በዩናይትድ ስቴትስ እንጂ በቬትናም አይደለም። . . . የለበሰው የሙሽራ ልብስ እንጂ የወታደር ካኪ አይደለም። ያን አስደንጋጭ ድምፅ ሲሰማ ግን የሚሸሸግበት ለመፈለግ ተሯሯጠ።”
ፒ ቲ ኤስ ዲን የሚያስከትለው በጦር ሜዳ ላይ የሚያጋጥም አሰቃቂ ሁኔታ ብቻ አይደለም። ዘ ሃርቫርድ ሜንታል ኸልዝ ሌተር እንደሚለው ይህ ቀውስ “ሞት ባስከተለ ወይም ሊያስከትል በሚችል ወይም ከባድ የአካል ጉዳት ባስከተለ ወይም ሊያስከትል በሚችል አንድ ሁኔታ ወይም ተከታታይ ሁኔታዎች ምክንያት ሊመጣ ይችላል። የተፈጥሮ አደጋ፣ ድንገተኛ አደጋ ወይም ደግሞ ሰዎች የሚፈጽሙት ድርጊት ሊሆን ይችላል:- ጎርፍ፣ እሳት፣ የምድር መናወጥ፣ የመኪና አደጋ፣ የቦምብ ፍንዳታ፣ ተኩስ፣ ማሰቃየት፣ አፈና፣ አካላዊ ጥቃት፣ አስገድዶ መድፈር ወይም በሕፃናት ላይ የሚፈጸም በደል ሊሆን ይችላል። እነዚህን ለመሰሉ አእምሮ የሚያቆስሉ ሁኔታዎች የዓይን ምሥክር መሆን ወይም ሌሎች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል ወይም በፎቶግራፍ አማካኝነት እንደነዚህ ስላሉት ሁኔታዎች ለማወቅ መቻል፣ በተለይ ድርጊቶቹ የተፈጸሙት በቤተሰብ አባሎች ላይ ወይም በቅርብ ወዳጆች ላይ በሚሆንበት ጊዜ የፒ ቲ ኤስ ዲ ሕመም ምልክቶች እንዲታዩ ሊያደርግ ይችላል።
እርግጥ ነው፣ ሰዎች ለአሰቃቂ ሁኔታዎች የሚያሳዩት ምላሽ አንድ ዓይነት አይሆንም። “አብዛኞቹ ሰዎች አእምሮ ላይ ጠባሳ የሚጥል አሰቃቂ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ከባድ የሆነ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ አይታይባቸውም። ቢታይባቸውም እንኳን የፒ ቲ ኤስ ዲ መልክ ያለው አይሆንም” በማለት ዘ ሃርቫርድ ሜንታል ኸልዝ ሌተር ያብራራል። በደረሰባቸው ውጥረት ምክንያት ፒ ቲ ኤስ ዲ የተከሰተባቸው ሰዎችስ? አንዳንዶቹ ባዩት አሰቃቂ ሁኔታ ምክንያት የደረሰባቸውን የስሜት መቃወስ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለማሸነፍ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ እንኳን ያጋጠማቸው አሰቃቂ ሁኔታ በየጊዜው ትውስ ይላቸዋል።
በዚያም ሆነ በዚህ በፒ ቲ ኤስ ዲ በመሰቃየት ላይ የሚገኙትም ሆኑ እነዚህን ሕመምተኞች ለመርዳት የሚፈልጉ ሁሉ ከሕመሙ ለመዳን ትዕግሥት አስፈላጊ መሆኑን ማስታወስ አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘የተጨነቁትን ነፍሳት እንዲያጽናኑና ሰውን ሁሉ እንዲታገሱ’ አጥብቆ ይመክራል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ሉዊዝ መኪና መንዳት የቻለችው ከአምስት ወራት በኋላ ነው። አደጋው ካጋጠማት ከአራት ዓመት በኋላ “ከዚያ ወዲህ ብዙ የተሻለኝ ቢሆንም መኪና መንዳት እንደ ድሮው ሊያስደስተኝ አይችልም። ማድረግ ስላለብኝ ብቻ የማደርገው ነገር ነው። ቢሆንም አደጋው በደረሰበት ጊዜ ከነበርኩበት አሳዛኝ ሁኔታ በጣም ተሻሽያለሁ” ብላለች።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ብዙ የቢሮ ሠራተኞች ውጥረት ይኖርባቸዋል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁሉም ዓይነት ውጥረት መጥፎ ላይሆን ይችላል