ድፍረት አግኝተዋል
ለመስበክ ድፍረት ማግኘት ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት “በብዙ ገድል” እንደሰበከ ተናግሯል። (1 ተሰሎንቄ 2:2) ለመስበክ ‘መጋደል’ የሚክስ ነውን? ሁልጊዜ አስደናቂ ተሞክሮዎችን እናገኛለን ማለት ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም የአምላክ አገልጋዮች በድፍረት በመስበካቸው ደስታ አግኝተዋል። አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።
ታር የምትባል አንዲት የስምንት ዓመት ልጅ አስተማሪዋ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የታሰሩ አይሁዶች መለያ ምልክት እንዲሆን ቢጫ ቀለም ያለው የዳዊት ኮከብ በልብሳቸው ላይ ይሰፋላቸው እንደነበር ስትናገር በትኩረት ትከታተል ነበር። ታር ልናገር አልናገር ብላ አመነታች። “ዓይኔን ሳልጨፍን ጸለይኩ” በማለት ታስታውሳለች። ከዚያም እጅዋን አውጥታ በእነዚያ ካምፖች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮችም እንደነበሩና የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ባለ ሦስት ማዕዘን ምልክት ልብሳቸው ላይ ይሰፋላቸው እንደነበር ተናገረች። አስተማሪዋም ተደሰተችና አመሰገነቻት። ታር የሰጠችው ሐሳብ ከአስተማሪዋ ጋር ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ መንገድ ከፈተ። እንዲያውም በኋላ አስተማሪዋ የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተቋቁመዋል የተባለውን የቪዲዮ ካሴት ጠቅላላ የክፍሏ ተማሪዎች እንዲያዩት አደረገች።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በጊኒ የምትኖር ኢረን የምትባል አንዲት ወጣት ያልተጠመቀች አስፋፊ አገልግሎቷን ለማሻሻል ፈለገች። ኢረንን መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠናት ሚስዮናዊት እህት ኢረን በትምህርት ቤቷ ላሉ ተማሪዎች የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን ለማበርከት እንድትሞክር አበረታታቻት። የክፍሏ ተማሪዎች ተቀባይ ስላልሆኑ ኢረን ይህን ማድረጉ ያስፈራት ነበር። ሆኖም ሚስዮናዊቷ እህት በምትሰጣት ማበረታቻ በመደፋፈር ኢረን በመጀመሪያ ከሁሉም ይበልጥ ተቃዋሚ ትመስላት ለነበረችው ተማሪ ለማበርከት ወሰነች። የሚያስገርመው ግን ተማሪዋ ፍላጎት ከማሳየቷም በላይ መጽሔቶችን በጉጉት ተቀበለች። ሌሎች ተማሪዎችም መጽሔቶችን ወሰዱ። ኢረን በዚያ ወር ያበረከተችው የመጽሔት ብዛት ባለፉት አምስት ወራት ካበረከተቻቸው መጽሔቶች የሚበልጥ ነበር።
በትሪንዳድ የሚገኝ አንድ ሽማግሌ ለአንዲት የትምህርት ቤት አስተዳዳሪ ንቁ! ትምህርታዊ መጽሔት መሆኑን ለመንገር ፈራ ተባ ይል ነበር። ሆኖም አንድ ቀን ድፍረት አገኘ። “ወደ ቅጥር ግቢው ስገባ ጸለይኩ። የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ በጣም ጥሩ ሰው ሆና ሳገኛት ማመን አቃተኝ” ሲል ተናግሯል። “ዛሬ ያሉ ወጣቶች ምን ተስፋ አላቸው?” የተባለውን ንቁ! መጽሔት ወሰደች፤ እንዲያውም በክፍል ውስጥ ለማስተማሪያነት እንዲያገለግል ተስማማች። ከዚያን ወዲህ በተለያዩ ርዕሶች የወጡ 40 መጽሔቶችን ወስዳለች።
ወጣቱ ቮን መስበክ በጣም ያስፈራው ነበር። “በጣም እረበሻለሁ፣ ውስጥ እጄን ያልበኛል፣ ቀስ ብዬ መናገር ስለማልችል በጣም እፈጥናለሁ።” ያም ሆኖ ግን የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነ። አሁንም ቢሆን በድፍረት መናገር ያስቸግረው ነበር። አንድ ቀን ሥራ ፍለጋ ሲባዝን ውሎ ሳይሳካለት ይቀራል። “እንዲያው በዚህ እንኳ ብካስ” ብሎ በማሰብ ባቡር ላይ ለአንድ ሰው ለመመሥከር ያስባል። ሆኖም ባቡሩ ውስጥ ያሉትን ትላልቅ የንግድ ሰዎች ያይና መናገር ይፈራል። በመጨረሻም እንደምንም ብሎ ጎኑ የተቀመጡትን አንድ ትልቅ ሰው ማነጋገር ይጀምራል። ከዚያም ረዥም ውይይት አደረጉ። “ከወጣት የማይጠበቁ ጥሩ ጥሩ ጥያቄዎችን ትጠይቃለህ። የሃይማኖት ምሁር ነህ እንዴ?” ሲል አንዱ ነጋዴ ጠየቀው። ቮን “አይ፣ የሃይማኖት ምሁር እንኳን አይደለሁም። እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ” ሲል መለሰ። ሰውዬውም ፈገግ በማለት “አሃ፣ አሁን ገባኝ” አለ።
እነዚህም ሆኑ ሌሎች በርካታ ምሥክሮች ለመመሥከር የሚያስችል ድፍረት በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው። አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቮን