ከሚያምኑት ወገን እንሁን
“እኛ . . . ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን።”—ዕብራውያን 10:39
1. የእያንዳንዱ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ እምነት ውድ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
በሚቀጥለው ጊዜ የይሖዋ አምላኪዎች በተሰበሰቡበት የመንግሥት አዳራሽ ስትገኝ ትንሽ ቆም በልና በዙሪያህ ያሉትን ወንድሞችና እኅቶች ተመልከት። እምነት ያሳዩባቸውን በርካታ ሁኔታዎች አስብ። ለብዙ አሥርተ ዓመታት አምላክን ያገለገሉ አረጋውያንን፣ በየዕለቱ የሚደርስባቸውን የእኩዮች ተጽዕኖ እየተቋቋሙ ያሉ ወጣቶችንና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ልጆች ለማሳደግ ከፍተኛ ትግል እያደረጉ ያሉ ወላጆችን ልትመለከት ትችላለህ። ብዙ ኃላፊነቶችን የተሸከሙ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮችም አሉ። አዎን፣ ይሖዋን ለማገልገል ሲሉ ብዙ ዓይነት መሰናክሎችን ያለፉ በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞችንና እህቶችን ትመለከታለህ። የእያንዳንዳቸው እምነት እንዴት ውድ ነው!—1 ጴጥሮስ 1:7
2. በዕብራውያን ምዕራፍ 10 እና 11 ላይ የሚገኘው የጳውሎስ ምክር ዛሬ ለእኛ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች መካከል የጳውሎስን ያክል የእምነትን አስፈላጊነት የተገነዘበ ሰው ይኖራል ለማለት ያዳግታል። እንዲያውም ጳውሎስ እውነተኛ እምነት ‘ነፍስን ሊያድን’ እንደሚችል ተናግሯል። (ዕብራውያን 10:39) ሆኖም ጳውሎስ በዚህ እምነት የለሽ ዓለም ውስጥ እምነት ጥቃት ሊደርስበትና ሊሸረሸር እንደሚችል ያውቅ ነበር። እምነታቸውን ለመጠበቅ ይታገሉ የነበሩት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የሚገኙ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሁኔታ ጳውሎስን በእጅጉ አሳስቦት ነበር። ዕብራውያን ምዕራፍ 10 እና 11ን በከፊል በምንመረምርበት ጊዜ ጳውሎስ እምነታቸውን ለመገንባት የተጠቀመበትን ዘዴ ልብ እንበል። እግረ መንገዳችንንም የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን እምነት እንዴት መገንባት እንደምንችል እንማራለን።
በሌሎች ላይ ትምክህት እንዳላችሁ ግለጹላቸው
3. በዕብራውያን 10:39 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ጳውሎስ በወንድሞቹና በእህቶቹ እምነት ላይ ትምክህት እንደነበረው የሚያሳዩት እንዴት ነው?
3 በመጀመሪያ የምናስተውለው ጳውሎስ ለአድማጮቹ የነበረውን አዎንታዊ አመለካከት ነው። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።” (ዕብራውያን 10:39) ጳውሎስ የታማኝ ክርስቲያን ወንድሞቹን ደካማ ጎን ሳይሆን ጠንካራ ጎን ተመልክቶ ነበር። በተጨማሪም “እኛ” የሚል መግለጫ እንደተጠቀመ ልብ በሉ። ጳውሎስ ጻድቅ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ራሱን ያለ ልክ ጻድቅ አድርጎ በማቅረብ አድማጮቹን ዝቅ ዝቅ አላደረገም። (ከመክብብ 7:16 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ይልቅ ራሱንም ከእነሱ ጋር ደምሮ ገልጿል። እሱም ሆነ ታማኝ ክርስቲያን አንባቢዎቹ ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ እንቅፋቶች ቢገጥሟቸውም ወደ ጥፋት ላለማፈግፈግ ቆራጦች በመሆን እምነት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን እንደሚያስመሰክሩ ገልጿል።
4. ጳውሎስ በእምነት አጋሮቹ ላይ ትምክህት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው?
4 ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ትምክህት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? የዕብራውያን ክርስቲያኖችን ድክመት ማየት ተስኖት ነበር ማለት ነውን? በፍጹም። እንዲያውም መንፈሳዊ ድክመቶቻቸውን እንዲያሸንፉ ለመርዳት ቀጥተኛ የሆነ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ዕብራውያን 3:12፤ 5:12-14፤ 6:4-6፤ 10:26, 27፤ 12:5) ያም ሆኖ ግን ጳውሎስ በወንድሞቹ ላይ ትምክህት እንዲኖረው ያደረጉት ቢያንስ ሁለት ጥሩ ምክንያቶች ነበሩት። (1) ጳውሎስ የይሖዋን ምሳሌ በመኮረጅ የአምላክን አገልጋዮች በይሖዋ ዓይን ለመመልከት ጥረት አድርጓል። ይህም ማለት ድክመቶቻቸውን ብቻ ከመመልከት ይልቅ መልካም ባሕርያቶቻቸውንና ወደፊት መልካም ለማድረግ ሊመርጡ የሚችሉ መሆናቸውን ተመልክቷል። (መዝሙር 130:3፤ ኤፌሶን 5:1) (2) ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ ባለው ኃይል ላይ ጠንካራ እምነት ነበረው። ይሖዋ እሱን በታማኝነት ለማገልገል ለሚጥር ማንኛውም ክርስቲያን “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” እንዳይሰጥ ሊያግደው የሚችል እንቅፋት ወይም ሰብዓዊ ድክመት እንደማይኖር ያውቅ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 4:7 NW፤ ፊልጵስዩስ 4:13) ስለዚህ ጳውሎስ በወንድሞቹና በእህቶቹ ላይ የነበረው ትምክህት የተሳሳተ፣ ከእውነታው የራቀ ወይም ጭፍን አልነበረም። ጽኑ መሠረትና ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው ነበር።
5. በወንድሞቻችን ላይ ትምክህት በማሳደር ረገድ የጳውሎስን ምሳሌ ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
5 ጳውሎስ ያሳየው ትምክህት ወደ ሌሎችም ተጋብቶ ተመሳሳይ ባሕርይ እንዲያሳዩ እንዳነሳሳቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ጳውሎስ እንዲህ በሚያበረታታ መንገድ መናገሩ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ለነበሩት ጉባኤዎች ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቶ መሆን አለበት። ከአይሁድ ተቃዋሚዎቻቸው የሚሰነዘርባቸውን ቅስም የሚሰብር ፌዝና ንቀት ለመቋቋም እየታገሉ ባሉበት ወቅት የተሰጣቸው ይህ ማበረታቻ ዕብራውያን ክርስቲያኖች እምነት ያላቸው ሰዎች ሆነው ለመገኘት ከልብ ቆርጠው እንዲነሱ ረድቷቸዋል። እኛስ እርስ በርሳችን እንዲህ መበረታታት እንችል ይሆን? የሌሎችን ስህተትና የባሕርይ ጉድለት መዘርዘር በጣም ቀላል ነው። (ማቴዎስ 7:1-5) ሆኖም እያንዳንዱ ሰው ያለውን በዓይነቱ ልዩ የሆነ እምነት ብንመለከትና ብናደንቅ እርስ በርሳችን ይበልጥ ልንበረታታ እንችላለን። እንዲህ ያለው ማበረታቻ እምነትን ይበልጥ እንደሚያጎለብት የታወቀ ነው።—ሮሜ 1:11, 12
በአምላክ ቃል በጥሩ ሁኔታ መጠቀም
6. ጳውሎስ በዕብራውያን 10:38 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ቃላት የጠቀሰው ከየት ነው?
6 በተጨማሪም ጳውሎስ ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥበብ በመጠቀም የእምነት አጋሮቹን እምነት ገንብቷል። ለምሳሌ ያህል “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፣ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 10:38) እዚህ ላይ ጳውሎስ ነቢዩ ዕንባቆም የተናገረውን መጥቀሱ ነበር።a እነዚህ ቃላት የትንቢት መጻሕፍትን ጠንቅቀው ለሚያውቁት የጳውሎስ አንባቢዎች ማለትም ለዕብራውያን ክርስቲያኖች እንግዳ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። በ61 እዘአ በኢየሩሳሌምና በአቅራቢያዋ የሚገኙ ክርስቲያኖችን እምነት ለማጠንከር ከነበረው ግብ አንጻር ጳውሎስ የዕንባቆምን ምሳሌ ለመጠቀም መምረጡ የተገባ ነበር። ለምን?
7. ዕንባቆም ትንቢቱን የመዘገበው መቼ ነው? በዚያን ወቅት በይሁዳ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
7 ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ዕንባቆም መጽሐፉን የጻፈው ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከመጥፋቷ ከሁለት አሥርተ ዓመታት በፊት ነበር። ‘መራርና ፈጣን’ ሕዝብ የሆኑት ከለዳውያን (ወይም ባቢሎናውያን) ድንገት በይሁዳ ላይ እንደሚነሱና ኢየሩሳሌምን እንደሚያጠፉ እንዲሁም ሕዝቡንም ሆነ ነገሥታቶቻቸውን እንደሚውጡ ነቢዩ በራእይ ተመልክቶ ነበር። (ዕንባቆም 1:5-11) ሆኖም እንዲህ ዓይነት ጥፋት እንደሚመጣ ትንቢት የተነገረው ከአንድ መቶ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በፊት ማለትም ከኢሳይያስ ዘመን ጀምሮ ነበር። በዕንባቆም ዘመን ጥሩ ንጉሥ በነበረው በኢዮስያስ ምትክ ኢዮአቄም ነግሦ የነበረ ሲሆን ይህም በይሁዳ ክፋት እንደገና እንዲስፋፋ አደረገ። ኢዮአቄም በይሖዋ ስም የሚናገሩ ሰዎችን ያሳድድ አልፎ ተርፎም ይገድል ነበር። (2 ዜና መዋዕል 36:5፤ ኤርምያስ 22:17፤ 26:20-24) በጭንቀት የተዋጠው ነቢዩ ዕንባቆም “አቤቱ፣ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?” በማለት ሮሮ ማሰማቱ አያስገርምም።—ዕንባቆም 1:2
8. የዕንባቆም ምሳሌ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩትም ሆነ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
8 ዕንባቆም የኢየሩሳሌም ጥፋት ምን ያህል እንደቀረበ አያውቅም ነበር። በተመሳሳይም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ መቼ እንደሚሆን አያውቁም ነበር። እኛም ብንሆን በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ የይሖዋ ፍርድ የሚጀምርበትን ‘ቀንና ሰዓት’ አናውቅም። (ማቴዎስ 24:36) እንግዲያው ይሖዋ ለዕንባቆም የሰጠውን ድርብ መልስ ልብ እንበል። በመጀመሪያ ደረጃ ፍጻሜው ከተቀጠረለት ጊዜ ዝንፍ እንደማይል ለነቢዩ አረጋገጠለት። በሰብዓዊ አመለካከት የዘገየ ቢመስልም እንኳ አምላክ “አይዘገይም” ሲል ተናግሯል። (ዕንባቆም 2:3) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ “ጻድቅ በእምነቱ በሕይወት ይኖራል” በማለት ለዕንባቆም ነገረው። (ዕንባቆም 2:4) ይህ እንዴት ያለ ግሩምና ለመረዳት የማይከብድ እውነት ነው! ትልቅ ለውጥ የሚያመጣው መጨረሻው የሚመጣበት ጊዜ ሳይሆን የእኛ በእምነት መቀጠል አለመቀጠል ነው።
9. ታዛዥ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው (ሀ) በ607 ከዘአበ (ለ) ከ66 እዘአ በኋላ በሕይወት ሊተርፉ የቻሉት እንዴት ነው? (ሐ) እምነታችንን ማጎልበታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ በጠፋችበት ወቅት ኤርምያስ፣ የእሱ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ፣ አቤሜሌክና ታማኞቹ ሬካባውያን ይሖዋ ለዕንባቆም የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም ተመልክተዋል። በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው አሰቃቂ ጥፋት ተርፈው ‘በሕይወት መኖራቸውን ቀጥለዋል።’ ለምን? ይሖዋ ለታማኝነታቸው ወሮታ ስለከፈላቸው ነው። (ኤርምያስ 35:1-19፤ 39:15-18፤ 43:4-7፤ 45:1-5) በተመሳሳይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች ለጳውሎስ ምክር አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው መሆን አለበት። ምክንያቱም በ66 እዘአ የሮማ ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ወደ ኋላ ሲያፈገፍግ በወቅቱ የነበሩት ክርስቲያኖች ኢየሱስ ወደ ተራራ ስለመሸሽ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በታማኝነት ተግባራዊ አድርገዋል። (ሉቃስ 21:20, 21) በሕይወት መኖራቸውን መቀጠል የቻሉት ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው ነው። እኛም በተመሳሳይ መጨረሻው በሚመጣበት ጊዜ ታማኝ ሆነን ከተገኘን በሕይወት መኖራችንን እንቀጥላለን። ከአሁኑ እምነታችንን እንድናጠነክር የሚያበረታታ እንዴት ያለ ግሩም ሐሳብ ነው!
የእምነት ምሳሌዎችን ሕያው አድርጎ መግለጽ
10. ጳውሎስ የሙሴን እምነት የገለጸው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ሙሴን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?
10 በተጨማሪም ጳውሎስ ጥሩ የእምነት ምሳሌዎችን በመጥቀስ የአንባቢዎቹን እምነት ገንብቷል። ዕብራውያን ምዕራፍ 11ን በምታነብበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለ ታሪኮችን እንዴት ሕያው በሆነ መንገድ እንደጠቀሰ ልብ በል። ለምሳሌ ያህል ስለ ሙሴ ሲናገር “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና” ብሏል። (ዕብራውያን 11:27 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በሌላ አነጋገር ይሖዋ ለሙሴ እውን ሆኖለት ስለነበር ሙሴ የማይታየውን አምላክ ያየው ያክል ነበር። ለእኛስ እንዲህ ሊባልልን ይችላልን? ከይሖዋ ጋር ስለሚኖር ዝምድና መናገር ቀላል ነው፤ ይህን ዝምድና መገንባትና ማጠንከር ግን ሥራ የሚጠይቅ ነገር ነው። ይህ ልንደክምለት የሚገባ ሥራ ነው! ይሖዋ ለእኛ እውን ነውን? ጥቃቅን የሚመስሉ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ ጭምር እሱን ግምት ውስጥ እናስገባለንን? እንዲህ ዓይነት እምነት ኃይለኛ ተቃውሞ ቢደርስብን እንኳ እንድንጸና ይረዳናል።
11, 12. (ሀ) የሄኖክ እምነት የተፈተነው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ስር ሊሆን ይችላል? (ለ) ሄኖክ ምን የሚያበረታታ ሽልማት ተቀብሏል?
11 በተጨማሪም የሄኖክን እምነት ተመልከት። የገጠመው ተቃውሞ ልንገምተው ከምንችለው በላይ ነው። ሄኖክ በወቅቱ የነበሩትን ክፉ ሰዎች የሚያሰቃይ የፍርድ መልእክት መናገር ነበረበት። (ይሁዳ 14, 15) በዚህ ታማኝ ሰው ላይ አረመኔያዊ የጭካኔ ተግባር እንዲፈጸምበት የሚያደርግ ስደት አንዣቦ ስለነበር በጠላቶቹ እጅ እንዳይወድቅ ሲል ይሖዋ “ወስዶታል”፤ ማለትም በሞት እንዲያንቀላፋ አድርጎታል። ስለዚህ ሄኖክ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ የመመልከት አጋጣሚ አላገኘም። ያም ሆኖ ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ሲታይ የተሻለ ሽልማት ተቀብሏል።—ዕብራውያን 11:5፤ ዘፍጥረት 5:22-24
12 “[ሄኖክ] ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና” ሲል ጳውሎስ ተናግሯል። (ዕብራውያን 11:5) ይህ ምን ማለት ነው? ሄኖክ በሞት ከማንቀላፋቱ በፊት ምናልባትም ወደፊት ከሞት ሲነሳ የሚያገኛትን ምድራዊት ገነት የሚያሳይ አንድ ራእይ አይቶ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ፣ ባሳየው ታማኝነት መደሰቱን ሄኖክ እንዲያውቅ አድርጎታል። ሄኖክ የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝቷል። (ከምሳሌ 27:11 ጋር አወዳድር።) የሄኖክን የሕይወት ተሞክሮ ማሰብ ልብን የሚነካ አይደለም? እንዲህ ዓይነት በእምነት ላይ የተመሠረተ ሕይወት እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? እንግዲያው እንዲህ ባሉ የእምነት ምሳሌዎች ላይ አሰላስል። አሁን በእውን እንዳሉ አድርገህ ተመልከታቸው። ከዕለት ወደ ዕለት በእምነት ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። በተጨማሪም እምነት ያላቸው ሰዎች ይሖዋን ለማገልገል የሚነሱት አምላክ የገባቸውን ተስፋዎች ሁሉ የሚፈጽምበትን ጊዜ በአእምሮ በመያዝ ወይም የጊዜ ገደብ በማበጀት እንዳልሆነ ማሰብ ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ለዘላለም ማገልገል ቁርጥ ውሳኔያችን ሊሆን ይገባል! እንዲህ ማድረጋችን በዚህ የነገሮች ሥርዓትም ሆነ በመጪው ጊዜ በተሻለ የሕይወት ጎዳና ላይ እንድንመላለስ ያስችለናል።
በእምነት እየጎለበቱ መሄድ የሚቻለው እንዴት ነው?
13, 14. (ሀ) በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ስብሰባዎቻችንን አስደሳች ለማድረግ ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) የክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው?
13 ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች እምነታቸውን ማጎልበት የሚችሉባቸውን በርካታ ተግባራዊ መንገዶች ጠቅሶላቸዋል። እስቲ ሁለቱን ብቻ እንመርምር። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ዘወትር እንድንገኝ ለማሳሰብ በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ የሰጠው ምክር ትዝ እንደሚለን የታወቀ ነው። ሆኖም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት እነዚህ የጳውሎስ ቃላት በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በታዛቢነት እንድንገኝ ብቻ የሚያበረታቱ እንዳልሆኑ አስታውሱ። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ እነዚህን ስብሰባዎች የገለጻቸው እርስ በርስ ለመተዋወቅ፣ አምላክን በተሻለ መንገድ ለማገልገል አንዱ ሌላውን ለማነቃቃትና እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችሉ ጥሩ አጋጣሚዎች እንደሆኑ አድርጎ ነው። በዚያ የምንገኘው ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለመስጠትም ጭምር ነው። ይህ ደግሞ ስብሰባዎቻችን አስደሳች እንዲሆኑ አስተዋጽዖ ያደርጋል።—ሥራ 20:35
14 ሆኖም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምንገኝበት ዋነኛ ዓላማ ይሖዋን ለማምለክ ነው። አብረን በመጸለይና በመዘመር፣ በጥሞና በማዳመጥ እንዲሁም በምንሰጠው ሐሳብና በስብሰባ ላይ በምናቀርባቸው ክፍሎች አማካኝነት ለይሖዋ በምናሰማው ውዳሴ “የከንፈሮችን ፍሬ” በማቅረብ አምልኮታችንን እናከናውናለን። (ዕብራውያን 13:15) እነዚህን ግቦች በአእምሮአችን የምንይዝና በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የምንጥር ከሆነ ያለ ምንም ጥርጥር እምነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ይሄዳል።
15. ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች አገልግሎታቸውን አጥብቀው እንዲይዙ ያሳሰባቸው ለምንድን ነው? ዛሬም ይህ ዓይነት ምክር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ሌላው እምነታችንን የምንገነባበት መንገድ የስብከቱ ሥራ ነው። ጳውሎስ “የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 10:23) ሰዎች አንድ ነገር ከእጃቸው ሊያመልጣቸው እንደሆነ ብታይ ጠበቅ አድርገው እንዲይዙት ማሳሰቢያ ትሰጧቸው ይሆናል። ሰይጣን ዕብራውያን ክርስቲያኖች አገልግሎታቸውን እንዲተዉ ለማድረግ ተጽእኖ ሲያደርግ ነበር፤ ዛሬ ባሉ የአምላክ ሕዝቦችም ላይ ተጽእኖ ያደርጋል። እንዲህ ዓይነት ተጽእኖ ሲያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጳውሎስ ምን እንዳደረገ ተመልከት።
16, 17. (ሀ) ጳውሎስ ለአገልግሎቱ ድፍረት ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) በአንዱ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ዘርፍ መካፈል የሚያስፈራን ከሆነ ምን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርብናል?
16 ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚገኙ ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ሲል ጽፎላቸዋል:- “እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራ ተቀብለን ተንገላትተንም፣ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን።” (1 ተሰሎንቄ 2:2) ጳውሎስና ጓደኞቹ በፊልጵስዩስ ‘የተንገላቱት’ እንዴት ነበር? አንዳንድ ሃይማኖታዊ ምሁራን እንደሚሉት ጳውሎስ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል መሰደብን፣ መዋረድን ወይም ለሥቃይ መዳረግን ያመለክታል። በፊልጵስዩስ የሚገኙ ባለሥልጣናት በዱላ ደብድበዋቸዋል፣ ወኅኒ ቤት ጨምረዋቸዋል እንዲሁም በእግር ግንድ ውስጥ አስገብተው አስረዋቸዋል። (ሥራ 16:16-24) ጳውሎስ ይህ ሁሉ ስቃይ ሲደርስበት ምን ተሰማው? ፍርሃት፣ በሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ቀጥሎ ከሚጎበኛቸው ከተማዎች አንዷ ወደሆነችው ወደ ተሰሎንቄ እንዳይሄድ አድርጎታልን? በፍጹም፣ እንዲያውም ይበልጥ ‘ደፋር’ ሆኗል። ፍርሃትን በማሸነፍ በድፍረት መስበኩን ቀጥሏል።
17 ጳውሎስ ይህን ድፍረት ያገኘው ከየት ነው? ከራሱ? በፍጹም፤ “በአምላካችን” ደፈርን ሲል ተናግሯል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህ አባባል “አምላክ ፍርሃትን ከልባችን ውስጥ አውጥቶ ጣለልን” ተብሎም ሊተረጎም እንደሚችል ይገልጻል። በተለይ አገልግሎት ሲባል የሚያስፈራህ ከሆነ ወይም ደግሞ በተወሰኑ የአገልግሎቱ ዘርፎች ለመካፈል ድፍረቱ ከሌለህ ተመሳሳይ እርዳታ ለማግኘት ለምን ይሖዋን አትማጸነውም? ፍርሃትን ከልብህ ውስጥ አውጥቶ እንዲጥልልህ ጠይቀው። ለሥራው ድፍረትን እንዲሰጥህ ጠይቀው። በተጨማሪም አንዳንድ ሌሎች እርምጃዎችን ውሰድ። አንተን በሚያስፈራህ የአገልግሎቱ ዘርፍ በመካፈል ልምድ ካለው ሰው ጋር ለመሥራት ዝግጅት አድርግ። ይህም በንግድ አካባቢዎች ማገልገልን፣ መንገድ ላይ መመሥከርን፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መስበክን ወይም በስልክ መመሥከርን የሚመለከት ሊሆን ይችላል። መጀመሪያ ላይ ምናልባት የአገልግሎት ጓደኛህ ቀዳሚ ለመሆን ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ከሆነ እሱን በማየት መማር ትችላለህ። ሆኖም ከዚያ በኋላ ራስህ ለመሞከር አንድትችል ድፍረት ማግኘት አለብህ።
18. በአገልግሎታችን ደፋሮች ከሆንን ምን በረከቶችን እናገኛለን?
18 ድፍረት ካገኘህ ምን ውጤት ሊገኝ እንደሚችል አስብ። ተስፋ ሳትቆርጥ ከጸናህ እውነትን ለሌሎች በማካፈል ረገድ ከዚህ በፊት ያላገኘሃቸውን ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎች ልታገኝ እንደምትችል የታወቀ ነው። (ገጽ 25ን ተመልከት።) ለአንተ አስቸጋሪ የሆነ ነገር በመሥራት ይሖዋን እያስደሰትከው እንዳለህ በማወቅ እርካታ ልታገኝ ትችላላችሁ። ፍርሃትህን በማሸነፍ ረገድ የይሖዋ በረከትና ድጋፍ አይለይህም። እምነትህ ጠንካራ ይሆናል። የራስህን እምነት ሳትገነባ የሌሎችን እምነት እገነባለሁ ማለት ዘበት ነው።—ይሁዳ 20, 21
19. ‘እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ’ ምን ውድ ሽልማት ይጠብቃቸዋል?
19 የራስህንም ሆነ የሌሎችን እምነት ለማጎልበት መጣርህን ቀጥል። የአምላክን ቃል በጥበብ በመጠቀም፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሳቸውን የእምነት ምሳሌዎች የሕይወት ታሪክ በማጥናትና ሕያው አድርጎ በመመልከት፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና ተሳትፎ በማድረግ እንዲሁም ውድ መብት የሆነውን አገልግሎት አጥብቆ በመያዝ ይህን ማድረግ ትችላለህ። እንዲህ ካደረግህ በእርግጥ ‘ከሚያምኑት ወገን’ ነኝ ብለህ በእርግጠኝነት ልትናገር ትችላለህ። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች ውድ የሆነ ሽልማት እንደሚጠብቃቸው አስታውስ። “ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ” ናቸው።b እምነትህ እየጎለበተ እንዲሄድና ይሖዋ አምላክ ለዘላለም በሕይወት እንዲጠብቅህ እንመኛለን!—ዕብራውያን 10:39
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጳውሎስ የጠቀሰው በሰፕቱጀንት መሠረት “ማንም ወደ ኋላ ቢያፈገፍግ ነፍሴ በእሱ ደስ አይላትም” የሚል ሐረግ የሚጨምረውን ዕንባቆም 2:4ን ነበር። ይህ አገላለጽ አሁን በእጅ ባሉ የብራና ዕብራይስጥ ጽሑፎች ውስጥ በአንዳቸውም ላይ አይገኝም። አንዳንዶች ሰፕቱጀንት የተገለበጠው አሁን በእጅ በማይገኙ በጣም ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች ላይ ነው የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ይህን ጥቅስ በመልእክቱ ውስጥ ጨምሮታል። ስለዚህ ይህ ሐሳብ መለኮታዊ ድጋፍ አለው ማለት ነው።
b በ2000 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት ጥቅስ “እኛ ግን . . . ከሚያምኑቱ ነን እንጂ . . . ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” የሚለው ይሆናል።—ዕብራውያን 10:39
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ጳውሎስ በዕብራውያን ክርስቲያኖች ላይ ትምክህት እንዳለው የገለጸው እንዴት ነው? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
◻ ጳውሎስ ነቢዩ ዕንባቆምን መጥቀሱ ተስማሚ የነበረው ለምንድን ነው?
◻ ጳውሎስ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ የእምነት ምሳሌዎችን ሕያው አድርጎ አቅርቧል?
◻ ጳውሎስ እምነትን ለመገንባት ይረዳሉ ብሎ የጠቀሳቸው ተግባራዊ ምክሮች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ብዙ ስቃይ ከደረሰበት በኋላ በስብከቱ ሥራ እንደገና ለመቀጠል የሚያስችል ድፍረት አግኝቷል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አንተስ የተለያየ የምሥክርነቱን ዘርፍ ለመሞከር ድፍረት ማግኘት ትችላለህን?