የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • እውነተኛ ክርስቲያናዊ አንድነት—እንዴት?
    የመንግሥት አገልግሎት—2003 | ታኅሣሥ
    • እውነተኛ ክርስቲያናዊ አንድነት—እንዴት?

      1 በ234 አገሮች የሚኖሩና ወደ 380 የሚጠጉ ቋንቋዎች የሚናገሩ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን አንድ ሊያደርግ የሚችለው ምንድን ነው? የይሖዋ አምልኮ ብቻ ነው። (ሚክ. 2:12፤ 4:1-3) የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛው የክርስትና አንድነት በዛሬው ጊዜ እውን እንደሆነ ከግል ተሞክሯቸው የሚያውቁት ጉዳይ ነው። ‘በአንድ እረኛ’ የምንመራ ‘አንድ መንጋ’ እንደመሆናችን መጠን ከፋፋይ የሆነውን የዓለም መንፈስ ለመቋቋም ቆርጠናል።—ዮሐ. 10:16፤ ኤፌ. 2:2

      2 አምላክ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ በእውነተኛው አምልኮ አንድ እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህን ዓላማውን ከግብ ያደርሳል። (ራእይ 5:13) ኢየሱስ የዚህን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ስለነበረ ተከታዮቹ አንድነት እንዲኖራቸው ከልብ የመነጨ ጸሎት አቅርቧል። (ዮሐ. 17:20, 21) እያንዳንዳችን ለክርስቲያን ጉባኤ አንድነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

      3 አንድነቱ ሊደረስበት የሚችለው እንዴት ነው? ክርስቲያኖች ያለ አምላክ ቃልና ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ወደ አንድነት መድረስ አይችሉም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናነበውን ተግባራዊ ማድረጋችን የአምላክ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ እንዲሠራ ያስችላል። ይህ ደግሞ “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” ያስችለናል። (ኤፌ. 4:3) መንፈሱ እርስ በርስ በፍቅር ተቻችለን እንድንኖር ይገፋፋናል። (ቆላ. 3:13, 14፤ 1 ጴጥ. 4:8) አንተስ በየዕለቱ በአምላክ ቃል ላይ በማሰላሰል አንድነቱን ለማጠናከር የበኩልህን ታደርጋለህ?

      4 እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠን ተልእኮም አንድ ያደርገናል። ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ‘ስለ ወንጌል እየተጋደልን’ አንድ ላይ ስናገለግል ‘ለእውነት አብረን የምንሠራ’ እንሆናለን። (ፊልጵ. 1:27፤ 3 ዮሐ. 8) እንዲህ ስናደርግ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር እርስ በርስ ያስተሳሰረን ፍቅር ይበልጥ ይጠናከራል። ታዲያ በዚህ ሳምንት አገልግሎት ስትወጣ በቅርቡ አብሮህ አገልግሎ የማያውቅን አንድ ክርስቲያን ለምን አትጋብዘውም?

      5 በዛሬው ጊዜ የእውነተኛው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር አካል በመሆናችን ምንኛ የታደልን ነን! (1 ጴጥ. 5:9) በቅርቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “ለአምላክ ክብር ስጡት” በተሰኙት ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተው ይህን ዓለም አቀፋዊ አንድነት በዓይናቸው ለመመልከት ችለዋል። እንግዲያው እያንዳንዳችን በየዕለቱ የአምላክን ቃል በማንበብ፣ አለመግባባቶችን በፍቅር በመፍታትና “በአንድ አሳብ” ምሥራቹን በመስበክ ለዚህ ውድ አንድነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ የምናበረክት እንሁን።—ሮሜ 15:5, 6

  • የሚገባቸውን ሰዎች መፈለግ
    የመንግሥት አገልግሎት—2003 | ታኅሣሥ
    • የሚገባቸውን ሰዎች መፈለግ

      1 ኢየሱስ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ አንድ ከባድ ኃላፊነት ጥሎብናል። እንዲህ ብሎ ነበር:- “በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፣ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ።” (ማቴ. 10:11) ሰዎች በቤታቸው የሚያሳልፉት ጊዜ እያነሰ በሄደበት በዚህ ጊዜ የሚገባቸውን ሰዎች ለመፈለግ በምናደርገው ጥረት ስኬታማ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

      2 የአገልግሎት ክልላችሁን በሚገባ አጥኑት:- በክልላችሁ ውስጥ ማገልገል ከመጀመራችሁ በፊት በሚገባ አጥኑት። ሰዎች በአብዛኛው በቤታቸው የሚገኙት መቼ ነው? ቀን ቀን የት ልናገኛቸው እንችላለን? በጥሩ መንፈስ ተቀብለው ሊያነጋግሩን የሚችሉት በየትኛው የሳምንቱ ቀን ወይም ሰዓት ብንሄድ ነው? አገልግሎትህን በጉባኤው ክልል ውስጥ ካሉት ሰዎች ዕለታዊ እንቅስቃሴና ሁኔታ ጋር ማስማማትህ ይበልጥ ስኬታማ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል።—1 ቆሮ. 9:23, 26

      3 በርካታ አስፋፊዎች ሰዎችን በቤታቸው ለማግኘት አመሻሹ ላይ መሄዱን ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። አንዳንድ ሰዎች በዚህ ሰዓት ላይ ይበልጥ ተረጋግተው የማዳመጥ ዝንባሌ አላቸው። የንግድ እንቅስቃሴዎች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎችና ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ማገልገልም ለሰዎች ምሥራቹን ማዳረስ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶች ናቸው። እርግጥ ነው፣ ምክንያታዊነት ከሚጎድላቸውና ከቅዱሳን ጽሑፎች የምናቀርብላቸውን ማስረጃዎች ለመቀበል ከማይፈልጉ ሰዎች ጋር ፍሬ ቢስ ውይይት በማድረግ ጊዜ ማባከን አስፈላጊ እንዳልሆነ መዘንጋት አይኖርብንም። በተጨማሪም ለሰዎች መጽሔቶችንና መጽሐፎችን ከመስጠታችን በፊት ለማንበብ ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ማረጋገጣችን ተገቢ ነው።

      4 አንድ ጉባኤ ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ በሚካሄድበት ወር ላይ ቅዳሜና እሁድ ከሰዓት በኋላ ረቡዕና አርብ ደግሞ አመሻሹ ላይ አስፋፊዎች አገልግሎት መውጣት የሚችሉበት ዝግጅት አደረገ። በተጨማሪም በስልክ ምሥክርነት ለመስጠትና የንግድ እንቅስቃሴዎች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች ለማገልገል እቅድ አወጡ። የጉባኤው የአገልግሎት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ ጉባኤው ይህ ዝግጅት ወደፊትም እንዲቀጥል ወስኗል።

      5 ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ትጉዎች ሁኑ:- በጉባኤያችሁ ክልል ውስጥ በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ሰዎችን በቤታቸው ለማግኘት አስቸጋሪ ከሆነ በመጀመሪያው ውይይትም ሆነ በእያንዳንዱ ተመላልሶ መጠየቅ ወቅት እንደገና የምትገናኙበትን ቁርጥ ያለ ቀጠሮ ያዙ። ከዚያም ቀጠሯችሁን አክብራችሁ መሄዳችሁን አትርሱ። (ማቴ. 5:37) የሚቻል ከሆነም የቤቱ ባለቤት ስልክ ቁጥሩን እንዲሰጣችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ይህም ግለሰቡን በድጋሚ ለማግኘት ያስችላችኋል።

      6 የሚገባቸውን ሰዎች ለማግኘትና ፍላጎት ያሳዩትን ተከታትለን ለመርዳት ትጋት የተሞላበት ጥረት የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ እንደሚባርከን አንጠራጠርም።—ምሳሌ 21:5

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ