ክርስቲያኖች አረጋውያንን ሊረዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
“ስለዚህም አንታክትም፣ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፣ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፣ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።” ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ያለው ለቆሮንቶስ በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤው ላይ ነው። — 2 ቆሮንቶስ 4:16–18
በጥንት ዘመን የነበሩ የእምነት ወንዶችና ሴቶች ዓይናቸውን በማይታዩት ነገሮች ላይ አድርገው ነበር። ይህም ይሖዋ አምላካቸው በጊዜው አደርግላችኋለሁ ብሎ ቃል የገባላቸውን ነገሮች ሁሉ ይጨምራል። ጳውሎስ በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ እስከሞቱባት ጊዜ ድረስ እምነታቸውን አጥብቀው ስለያዙት ስለ እነዚህ ዓይነት ሰዎች በማሞገስ ጽፏል። ከእነዚህም አንዳንዶቹ በጣም እስኪያረጁ ድረስ በሕይወት ኖረዋል። እንደሚከተለው በማለት እነሱን ለእኛ እንደምሳሌ አድርጎ ይጠቅሳቸዋል:- “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት።” — ዕብራውያን 11:13
እኛ ዛሬ ወደ እነዚህ ተስፋዎች ፍጻሜ በጣም ቀርበናል። ይሁን እንጂ የዚህን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ እንደሚያዩ እርግጠኝነት የማይሰማቸው ታማሚዎችና አረጋውያን በመካከላችን አሉ። ምናልባትም ከእነዚህ አንዳንዶቹ በአሁኑ የሕይወት ጊዜያቸው እነዚህ ተስፋዎች ሲፈጸሙ ሳያዩ በእምነት ይሞቱ ይሆናል። ለእነዚህ ዓይነቶቹ ወንድሞችና እኅቶች በ2 ቆሮንቶስ 4:16–18 ላይ ያሉት የጳውሎስ ቃላት ትልቅ ማበረታቻ ሊሆኑላቸው ይችላሉ።
ይሖዋ የታመሙትንና ያረጁትን ጨምሮ በታማኝነት ከጎኑ የቆሙትን ሁሉ ያስታውሳል። (ዕብራውያን 6:10) የታመኑ አረጋውያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታ ላይ በክብር ተወስተዋል። እንዲሁም የሙሴ ሕግ ለአረጋውያን ማሳየት ስለሚገባው ክብር ለይቶ ይጠቅሳል። (ዘሌዋውያን 19:32፤ መዝሙር 92:12–15፤ ምሳሌ 16:31) በጥንት ክርስቲያኖች ውስጥ አረጋውያን ከፍ ተደርገው ይያዙ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:1–3፤ 1 ጴጥሮስ 5:5) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ አንዲት ወጣት ሴት ላረጀችው አማቷ ስላሳየችው ፍቅራዊ እንክብካቤና ስለከፈለችው ልብ የሚነካ መስዋዕትነት ውብ የሆነ መግለጫ ይዟል። መጽሐፉ ሩት የሚለውን የዚህችን ወጣት ሴት ስም ይዟል። ስያሜውም ተገቢ ነው።
ታማኝ ረዳት
አርጅታ ለነበረችው ኑኃሚን ኑሮው መራራ ሆኖባት ነበር። ድርቅ ያስከተለው ረሃብ ከትንሽ ቤተሰቧ ጋር ወዳጆቿንና ርስቷን በይሁዳ ትታ በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምስራቅ በሚገኘው በሞዓብ ምድር እንድትኖር አስገደዳት። በዚያም ባሏ ከሁለት ወንዶች ልጆቻቸው ጋር ትቷት ሞተ። እነዚህ ወንዶች ልጆችም ከጊዜ በኋላ አደጉና አገቡ። ነገር ግን እነሱም ሞቱ። ኑኃሚን ያለምንም ጧሪ ቀረች።
አርጅታ ስለነበረ እንደገና አግብታ አዲስ ቤተሰብ ለመጀመር አትችልም። ስለዚህ ኑሮው ጠቦባት ነበር። የሁለቱን ልጆቿን ሚስቶች ሩትንና ዖርፋን ባል እንዲያገኙ በማለት ያለምንም ራስ ወዳድነት ወደ እናታቸው ቤት ልትልካቸው ፈለገች። ብቻዋን ወደ ትውልድ አገሯ ልትመለስ ነበር። ዛሬም አንዳንዶቹ አረጋውያን በተለይ የሚወዱትን ዘመድ በሞት ሲያጡ ጭንቀት ይሰማቸዋል። እንደ ኑኃሚን የሚጦራቸው ሰው ሊፈልጉ ይችላሉ። ነገር ግን ሸክም መሆን አይፈልጉም።
ሆኖም ሩት አማቷን ትታ አልሄደችም። ሩት ይህችን አረጋዊት ሴትና እሷ የምታመልከውን አምላክ ይሖዋን ትወድ ነበር። (ሩት 1:16) ስለዚህ ሁለቱም ወደ ይሁዳ ለመመለስ ጉዞ ጀመሩ። በዚያ አገር ድሆች አዝመራው ከተሰበሰበ በኋላ በማሳው ላይ የቀረውን እንዲቃርሙ ወይም እንዲለቅሙ የሚፈቅድ በይሖዋ ሕግ ሥር አንድ ፍቅራዊ ዝግጅት ነበረ። በዚያን ጊዜ ወጣት የነበረችው ሩትም “እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ” ስትል ይህን ሥራ ለመሥራት ራሷን በፈቃደኝነት አቀረበች። ሩት ለሁለቱ ጥቅም ስትል ያለመታከት ሠራች። — ሩት 2:2, 17, 18
የሩት ታማኝነትና ለይሖዋ የነበራት ፍቅር ቀናና ገንቢ በሆነ መንገድ ማሰብ ለጀመረችው ኑኃሚን ትልቅ ማበረታቻ ነበር። ኑኃሚን ሕጉንና የአገሩን ባሕል ማወቋ እዚህ ላይ ጠቀማት። ይህች ወጣት ሴት ባል በሚሞትበት ጊዜ የባል ወንድም እንዲያገባ በሚያዘው የጋብቻ ዝግጅት አማካኝነት የቤተሰቡን ርስት መልሳ እንድታስገኝና የቤተሰቡ የዘር ሐረግ እንዲቀጥል የሚያደርግ ልጅ እንድትወልድ ስትል ኑኃሚን ታማኝ ለሆነችው ረዳቷ የጥበብ ምክር ሰጠቻት። (ሩት ምዕራፍ 3) የታመሙትን ወይም አረጋውያንን ለመንከባከብ ሲሉ መሥዋዕትነት እየከፈሉ ላሉት ሩት ግሩም ምሳሌ ነች። (ሩት 2:10–12) ዛሬም በጉባኤዎች ውስጥ የታመሙትንና አረጋውያንን ለመርዳት ብዙ ለማድረግ ይቻላል። እንዴት?
በተደራጀ መልክ መሥራት ጠቃሚ ነው
በጥንቱ ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቁሳዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መበለቶች ስም ዝርዝር ይያዝ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:9, 10) ዛሬም በተመሳሳይ ሽማግሌዎች ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን በሽተኞችና አረጋውያን ስም ዝርዝር ሊይዙ ይችላሉ። በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ አንድ ሽማግሌ ይህ እንደ ልዩ ኃላፊነት አድርጎ እንዲከታተል ይመደባል። እንደ ኑኃሚን ያሉ አንዳንድ አረጋውያን እርዳታ ይደረግልን ብለው አፍ አውጥተው ስለማይጠይቁ በዚህ ቦታ ላይ የተመደበ ወንድም ሁኔታውን በመመርመር ረገድ ጥሩ ችሎታ ያለው መሆን ያስፈልገዋል። በዘዴና በልባምነት አስፈላጊ ነገሮች መደረጋቸውን ማረጋገጥ አለበት። ለምሳሌ ያህል ጉባኤው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ለበሽተኞችና ለአረጋውያን በቂ ዝግጅት እንዳለው ማየት ይችላል። ለአካባቢው የሚሠራ ከሆነ የመንግሥት አዳራሹ ተሽከርካሪ ወንበሮች የሚያስገባ ዘቅዘቅ ብሎ የተሠራ በር እንዳለው፣ አመቺ የማረፊያ ቦታዎች፣ የመስማት ችግር ላለባቸው ደግሞ የጆሮ ማዳመጫዎችና ለልዩ ወንበሮች መቀመጫ ቦታ ያለው መሆኑን ማየት ይችላል። በተጨማሪም ይህ ወንድም ወደ መንግሥት አዳራሹ መምጣት ያልቻሉ በሽተኞችና አረጋውያን ሁሉ ስብሰባው የተቀዳባቸውን ካሴቶች ተውሰው መስማታቸውን ወይም በስልክ አማካኝነት ስብሰባውን ለመከታተል መቻላቸውን ማረጋገጥ ይችላል።
እንዲሁም ወደ ጉባኤ ስብሰባዎችና ወደ ትልልቅ ስብሰባዎች ለመውሰድ መጓጓዣ ማዘጋጀት ሊያስፈልግ ይችላል። አንዲት አረጋዊት እኅት ዘወትር ወደ ስብሰባዎች ይዟቸው የሚሄደው ወንድም በመቅረቱ ተቸግረው ነበር። እኚህ አረጋዊት እኅት ለብዙ ግለሰቦች ስልክ ከደወሉ በኋላ ይዟቸው የሚሄድ ሰው አገኙ። ከዚያም በኋላ ግን ሸክም እንደሆኑ ተሰማቸው። እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮችን የሚመለከት ሽማግሌ ተመድቦ ቢሆን ኖሮ ችግራቸው ይቃለል ነበር።
በተጨማሪም ይህ ሽማግሌ የተለያዩ ቤተሰቦች አረጋውያንን ለመጎብኘት ተራ እንዲገቡ ሊጠይቅ ይችላል። በዚህ መንገድ ልጆችም አረጋውያንን መንከባከብ የክርስቲያናዊ ሕይወት ክፍል መሆኑን ይማራሉ። ልጆች ይህንን ኃላፊነት መሸከምን ቢማሩ ጥሩ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:4) አንድ የክልል የበላይ ተመልካች “በእኔ ተሞክሮ እንዳየሁት በራሳቸው ፍላጎት ተነሳስተው አረጋውያንን ወይም በሽተኞችን የሚጠይቁ ልጆች ወይም ወጣቶች በጣም ጥቂት ናቸው” ሲል ገልጿል። ምናልባትም አያስቡት ይሆናል፤ ወይም ምን ማድረግ ወይም ምን መናገር እንዳለባቸው አያውቁ ይሆናል። ወላጆች ይህን ሊያስተምሯቸው ይችላሉ።
ሆኖም አረጋውያን አንድ ወዳጃቸው መጥቶ እንደሚጠይቃቸው ቀደም ብሎ ቢነገራቸው ደስ እንደሚላቸው አስታውስ። ይህም አንድ የሚጎበኛቸው ሰው እንዳለ መጠበቅ የሚያስገኘውን ደስታ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል። ጠያቂዎቹ እንደ ቡናና ኬክ የመሳሰሉትን አንዳንድ የሚበሉና የሚጠጡ ነገሮች ይዘው ከሄዱ ከዚያም ሁሉንም ነገር ወዲያው ካጸዱት በአረጋውያኑ ላይ የሚኖር ተጨማሪ የሥራ ጫና አይኖርም። አንድ ያረጁ ባልና ሚስት በዘንቢል አንዳንድ ነገሮችን ይዘው በጉባኤ ውስጥ ያሉትን አረጋውያን በየተራ የሚጠይቁበት በሳምንቱ ውስጥ አንድ ቋሚ የሆነ ቀን አላቸው። ተጠያቂዎቹ በዚህ ዓይነቱ ጥየቃ በጣም ደስ ይላቸዋል።
አንዳንድ ጉባኤዎች ለአረጋውያን ጥቅም ሲሉ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናታቸውን ቀን ላይ ያደርጋሉ። በአንድ ቦታ አንዳንድ ቤተሰቦችና ነጠላ አስፋፊዎች እንዲህ ዓይነቱን ቡድን ለመርዳት ፈቃደኛ እንደሆኑና ይችሉ እንደሆነ ተጠይቆ ነበር። ከዚህም የተነሳ አረጋውያንና ወጣቶች እርስ በርስ የሚረዳዱበት መጽሐፍ ጥናት ተገኘ።
በዚህ ረገድ ቀዳሚ መሆን ለሽማግሌዎች ብቻ መተው አይገባውም። ሁላችንም ብንሆን አረጋውያንና በሽተኞች ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ንቁዎች መሆን ያስፈልገናል። በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ሄደን ልንጨብጣቸውና ጥቂት ልናጨዋውታቸው እንችላለን። እስቲ ዛሬ ማታ አብረን እንጫወት ብላችሁ ብትጋብዟቸው ግብዣውን በደስታ ሊቀበሉት ይችሉ ይሆናል። ወይም ለሽርሽር ወይም ለእረፍት ስንሄድ አብረውን እንዲሄዱ ልንጋብዛቸው እንችላለን። አንድ ምስክር ለሥራ ጉዳይ ከከተማ ወጣ በሚልበት ጊዜ አረጋውያን አስፋፊዎችን በመኪናው ይዞ ይሄዳል። አረጋውያን በሁሉም እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። ኑኃሚን ተሰምቷት እንደነበረው ራሳቸውን እንዲያገሉ አታድርጉ። ይህም እርጅናን ወይም መጃጀትን ያፋጥነዋል።
አካለ ስንኩል የሆኑ ወይም የታመሙ ወጣቶችም ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል። የማይድን በሽታ የያዛቸው ሦስት ልጆች የነበሩት አንድ ምስክር (በኋላ ሁለቱ ሞተዋል) እንደሚከተለው ብሏል:- “አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ የሚቆይ በሽታ ካለው አንድ ጉባኤ እንክብካቤ ማድረጉን ለመቀጠል አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል። ጉባኤው የአልጋ ቁራኛ ለሆነው ጓደኛቸው በየቀኑ የዕለት ጥቅሱን እንዲያወያዩትና ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ምዕራፍ እንዲያነቡለት አንዳንድ ታማኝ ወጣት አስፋፊዎችን ለምን አይመድብም? አቅኚዎችን ጨምሮ ወጣቶች ተራ ሊገቡ ይችላሉ።”
ሞት የማይቀር በሚመስልበት ጊዜ
የይሖዋ አገልጋዮች በሕመምም ሆነ በስደት ምክንያት የሚመጣውን ሞት በድፍረት ሲጋፈጡት ቆይተዋል። በሕመም እየተሰቃዩ ያሉ ሰዎች የሚሞቱበት ጊዜ የደረሰ ሲመስላቸው የተለያዩ ስሜቶችን ማሳየታቸው የተለመደ ነው። እነሱ ከሞቱም በኋላ ዘመዶቻቸው ማስተካከያ ለማድረግ፣ ሐዘናቸውን ለመተውና ነገሩን ለመቀበል የተወሰነ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ስለዚህ ያዕቆብ፣ ዳዊትና ጳውሎስ እንዳደረጉት የታመመው ሰው ስለ ሞት በግልጽ ቢናገር ብዙ ጊዜ ጥሩ ይሆናል። — ዘፍጥረት ምዕራፍ 48 እና 49፤ 1 ነገሥት 2:1–10፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:6–8
አንድ ሐኪም የሆነ የይሖዋ ምስክር “ስለዚህ ጉዳይ በጣም ግልጽ መሆን አለብን። እኔ በሙያዬ እንዳየሁት ለእሱ ወይም ለእሷ በሽታው ለሞት የሚያደርስ መሆኑን መደበቅ ምንም አይጠቅምም” ሲል ጽፏል። የሆነ ሆኖ በሽተኛው ራሱ ምን ለማወቅ እንደሚፈልግና ይህንንስ መቼ ለማወቅ እንደሚፈልግ ማስተዋል ያስፈልገናል። አንዳንድ በሽተኞች ሞታቸው እንደቀረበ እንደሚያውቁ በግልጽ ይናገራሉ። ስለሆነም ይህን በተመለከተ ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን ማጫወት ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ ለመዳን ተስፋ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ ወዳጆቻቸውም አብረዋቸው ተስፋ ቢያደርጉ ጥሩ ነው። — ከሮሜ 12:12–15 ጋር አወዳድር።
አንድ ሊሞት የተቃረበ ሰው ምናልባትም ስለሚደክመው ወይም ግራ ስለሚገባው መጸለይ ሊከብደው ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ በሽተኛ ‘በመቃተት የሚነገረውንም’ አምላክ እንደሚረዳ ከሮሜ 8:26, 27 በማወቁ ሊጽናና ይችላል። አንድ ሰው በእንዲህ ዓይነት ውጥረት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ ለጸሎት ቃላት ማግኘት እንደሚያዳግተው ይሖዋ ያውቃል።
የሚቻል ከሆነ ከበሽተኛው ጋር አብሮ መጸለይ በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ይናገራል:- “እናቴ ለሞት በተቃረበችበትና መናገር ባቃታት ጊዜ እጆቿን በማጣጠፍ አብረናት እንድንጸልይ እንደምትፈልግ አመለከተች። እናቴ ሙዚቃ በጣም ትወድ ስለነበረ ከጸሎታችን በኋላ ከመንግሥቱ መዝሙሮች አንዱን ዘመርን። በመጀመሪያ ዜማውን አንጎራጎርን ከዚያም የመዝሙሩን ቃላት በቀስታ ዘመርን። በመዝሙሩ እንደተደሰተች ግልጽ ነበር። የይሖዋ ምስክር ሆነን ካሳለፍነው ሕይወት ጋር የምናያይዛቸው እነዚህ መዝሙሮች በቃላት ልንገልጻቸው የሚያዳግቱን አብረዋቸው የሚሄዱ ስሜቶች እንዳሏቸው አያጠራጥርም።”
ሊሞት የተቃረበ ሰው ማናገር ፍቅር፣ ዘዴና የአሳቢነት ስሜት ይጠይቃል። የሚጠይቀው ሰው የሚናገራቸውን የሚገነቡና እምነት የሚያጠነክሩ ነገሮች ሊያዘጋጅ ይችላል። ስለሌሎች ሰዎችና ስለችግሮቻቸው አፍራሽ የሆኑ ነገሮችን ከመናገር መጠንቀቅ ይኖርበታል። በጥየቃ ላይም የሚያልፈው የጊዜ ርዝመት ምክንያታዊና ተስማሚ ሆኖ መሆን ይኖርበታል። በሽተኛው ራሱን የሳተ ቢመስልም አሁንም ሊሰማ እንደሚችል ማስታወሱ ጥሩ ነው። ስለዚህ ስለምትናገረው ነገር ተጠንቀቅ።
የሁላችንም ኃላፊነት
የታመሙትንና አረጋውያንን መንከባከብ ከባድ ኃላፊነት ነው። ለበሽተኛው ቅርብ የሆኑት ሰዎች የሚያደርጉት እንክብካቤ በአካልም ሆነ በስሜት የሚያደክም ሥራ ነው። ሌሎቹ የጉባኤው አባሎች ችግራቸውን ሊረዱላቸውና ሊያግዟቸው ያስፈልጋቸዋል ደግሞም ይገባቸዋል። ለበሽተኛ የቤተሰብ አባል ወይም የእምነት ጓደኛ እንክብካቤ እያደረጉ ያሉ ከአንዳንድ ስብሰባዎች ቢቀሩ ወይም ለተወሰነ ጊዜ በመስክ አገልግሎት ያላቸው ድርሻ ቢቀንስ እንኳን ትክክለኛውን ነገር እያደረጉ ነው። (ከ1 ጢሞቴዎስ 5:8 ጋር አወዳድር።) ጉባኤው ችግራቸውን ከተረዳላቸው ይበረታታሉ። ዘወትር በሽተኛውን የሚንከባከበው ሰው አንዳንድ ስብሰባዎችን ለመካፈል እንዲችል ወይም በስብከቱ ሥራ ትንሽ እንዲደሰት አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት አንዳንድ ጊዜ ሊረዱት ይችላሉ።
እርግጥ ታማሚው አንተው ራስህ ከሆንክ አንተም ማድረግ የምትችለው ነገር ይኖራል። በሽታህ ያስከተለብህ ተስፋቢስነትና ድካም በጣም ሕይወትህን መራራ ሊያደርጉት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ምሬት አንድን ሰው ብቸኛ ሊያደርገውና ሌሎችን ሊያርቅ ይችላል። ከዚህ ይልቅ አድናቆትህን ለመግለጽና እሺ ባይ ለመሆን ጣር። (1 ተሰሎንቄ 5:18) በስቃይ ላይ ለሚገኙ ለሌሎች ጸልይ። (ቆላስይስ 4:12) አስደናቂ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አሰላስል፤ ከሚጎበኙህ ሰዎች ጋር ስለ እነዚህ እውነቶች ተወያይ። (መዝሙር 71:17, 18) የአምላክ ሕዝቦች የሚያደርጉትን እምነት የሚያጠነክር እድገት እየተመለከትክ አንተም አብረህ ለመጓዝ ጉጉት ይኑርህ። (መዝሙር 48:12–14) ስለ እነዚህ አስደሳች ነገሮች ይሖዋን አመስግን። በእነዚህ ነገሮች ላይ ማሰላሰል ፀሐይ በቀተር ከምትሰጠው ሙቀትና ብርሃን ይልቅ በምትጠልቅበት ጊዜ የምትፈነጥቀው ሙቀትና ብርሃን ይበልጥ ጠልቆ እንደሚገባ ሁሉ እነዚህ ነገሮች በድንግዝግዝታ ላይ ላለው ሕይወታችን የራሳቸውን ውበት ይሰጡታል።
ሁላችንም በተለይ ፈታኝ በሆኑት ጊዜያት እንደ ራስ ቁር ሊጠብቀን የሚችለውን ተስፋን ለመያዝ መታገል አለብን። (1 ተሰሎንቄ 5:8) በትንሳዔ ተስፋና ይህ ተስፋ ባለው ጠንካራ መሠረት ላይ ማሰላሰል ጥሩ ነው። ወደፊት በእርጅና ምክንያት ሕመም ወይም ድካም የማይኖርበትን ጊዜ በእርግጠኝነትና በጉጉት መጠበቅ እንችላለን። በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ጤናማ ይሆናል። የሞቱት እንኳን ሳይቀሩ ተመልሰው ይመጣሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29) እነዚህን ‘የማይታዩትን ነገሮች’ በእምነት ዓይናችንና ልባችን እናያቸዋለን። ለእነዚህ ነገሮች ያላችሁ እይታ አይጨልም። — ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24፤ ራእይ 21:3, 4