ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ የሚደረግ ልዩ ዘመቻ!
1. የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከመጋቢት 21, 2009 ጀምሮ በዓለም ዙሪያ በሚደረገው በየትኛው ዘመቻ ላይ ይካፈላሉ? ለምንስ?
1 ሐሙስ፣ ሚያዝያ 9, 2009 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላክ ለሰው ልጆች ያሳየውን ታላቅ የፍቅር መግለጫ ለማስታወስ ይሰበሰባሉ። (ሮም 5:6-8) የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በምናከብርበት በዚህ ቀን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችም ከእኛ ጋር አብረው እንዲገኙ እንፈልጋለን። በመሆኑም ከመጋቢት 21 ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ልዩ የመጋበዣ ወረቀት ይሰራጫል።
2. የመጋበዣውን ወረቀት በምታሰራጭበት ጊዜ ምን ነገሮችን መዘንጋት አይኖርብህም?
2 ልትዘነጋቸው የማይገቡ ነጥቦች፦ በመጋበዣው ወረቀት ላይ ያሉትን ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ ጥያቄዎችና ጥቅሶች በጥሩ መንገድ ልትጠቀምባቸው ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ በሽፋኑ ላይ ያለውን ሥዕል በማሳየት እንደሚከተለው ማለት ትችላለህ፦ “ሐሙስ፣ ሚያዝያ 9, 2009 በምናከብረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ ጋብዘንዎታል።” ከዚያም በመጋበዣው ወረቀት ላይ ያለውን ርዕስና ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎች አሳየው። የቤቱ ባለቤት ቤተሰቡንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ይዞ መምጣት እንደሚችል መናገርህን አትዘንጋ።
3. በዘመቻው ወቅት የመጋበዣውን ወረቀት ቀደም ብለህ የሰጠሃቸው ሰዎች ጉዳዩን እንዳይዘነጉት መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?
3 የጉባኤያችሁ ክልል ሰፊ ከሆነ፣ ሽማግሌዎች ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች የመጋበዣ ወረቀቱን በራቸው ላይ እንድታስቀምጡላቸው ሊወስኑ ይችላሉ። ቅዳሜና እሁድ ከመጋበዣ ወረቀቱ ጋር መጽሔቶችን ማበርከት ይቻላል። ተመላልሶ የምታደርግላቸውን ሰዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችህን፣ ዘመዶችህን፣ አብረውህ የሚማሩትን ልጆች፣ የሥራ ባልደረቦችህን፣ ጎረቤቶችህን እንዲሁም የምታውቃቸውን ሌሎች ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ግብ አውጣ። ባለፈው ዓመት አንዲት እህት 30 የሚሆኑ ዘመዶቿን ቀደም ብላ ከጋበዘቻቸው በኋላ በበዓሉ ላይ መገኘታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በየጊዜው ታስታውሳቸው ነበር። ከጋበዘቻቸው ዘመዶቿ መካከል 25 የሚሆኑት በበዓሉ ላይ ሲገኙና ቆየት ብሎም አራቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ሲጀምሩ ማየቷ ምንኛ አስደስቷት ይሆን!
4. አሁኑኑ ምን ዕቅድ ማውጣት ይኖርብናል? ለምንስ?
4 አሁኑኑ ዕቅድ አውጣ፦ ብዙ አስፋፊዎች በመጋቢትና በሚያዝያ የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ማውጣት ይችሉ ይሆናል። መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ላይ የሚገኝ ልጅ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካላችሁ ይህ ዘመቻ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ ለማገልገል ምቹ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። ይህ በዓል ይሖዋና ልጁ ለሰው ዘር ያሳዩትን ታላቅ የፍቅር መግለጫ የምናስታውስበት ሲሆን ሰዎች በዚህ በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው ዘመቻ ላይ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀት ያለብን ከአሁን ጀምሮ ነው።—ዮሐ. 3:16፤ 15:13