የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 4/09 ገጽ 4-7
  • ጊዜያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙበት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጊዜያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙበት
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2009
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ዓላማችንን ባለመዘንጋት
  • የመስበክ ችሎታችንን በማሻሻል
  • ሰዎች ላይ በማተኮር
  • የተደራጀን በመሆን
የመንግሥት አገልግሎታችን—2009
km 4/09 ገጽ 4-7

ጊዜያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙበት

እነዚህ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦች የተወሰዱት ከዚህ በፊት ከወጡ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎታችን እትሞች ነው

1. (ሀ) ከስምሪት ስብሰባ ጋር በተያያዘ ጊዜያችንን በሚገባ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ጊዜ እንዳናጠፋ ወይም የሚባክነውን ጊዜ ለመቀነስ ጥንቃቄ የምናደርገው ለምንድን ነው?

1 ሁሉም ሰው በሳምንት ውስጥ ያለው ጊዜ እኩል ነው። በተለይ ምሥራቹን በማስፋፋት የምናሳልፈው ጊዜ ሕይወት አድን ለሆነ ሥራ የሚውል ስለሆነ ከፍ ያለ ግምት ይሰጠዋል። (ሮም 1:16) ለዚህ ጊዜ ያለንን አድናቆት የምናሳየው ደግሞ ለአገልግሎት ጥሩ ዝግጅት በማድረግ፣ በስምሪት ስብሰባ ላይ በሰዓቱ በመገኘትና ስምሪቱ እንዳለቀ ወዲያውኑ ወደ ክልላችን በመሄድ ነው። ወዲያው ወደ ክልላችን በመሄድ የስብከቱን ሥራ እንጀምራለን እንጂ ጊዜ አናጠፋም። ይሖዋ ‘ለሁሉም ጊዜ እንዳለው’ ስላስተማረን ለአገልግሎት የመደብነውን ጊዜ በአግባቡ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል።—መክ. 3:1 (km 6/99 ገጽ 4 አን. 1)

ዓላማችንን ባለመዘንጋት

2. ቅዱሳን መጻሕፍት ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የትኛውን ዓላማ በአእምሯችን እንድንይዝ ያሳስቡናል?

2 በምሳሌ 24:11, 12 ላይ ያሉት ቃላት የምናገለግልበትን አንዱን አንገብጋቢ ምክንያት ጠንከር አድርገው ይገልጹልናል፤ በአጭሩ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው። ይህንን ሐሳብ ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ ከሰጠን ተልእኮ ጋር ማያያዝ እንችላለን። የእውነትን ዘር ለማሳደግ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው። (1 ቆሮ. 3:6, 7) ተመላልሶ መጠየቅ ማድረጋችን በመጀመሪያው ውይይት ወቅት የተዘራውን ዘር ዲያብሎስ እንዳይነጥቀው ይከላከላል። (km 6/95 ገጽ 8 አን. 1, 5)

3. (ሀ) በመንገድ ላይ በምናገለግልበት ጊዜ ምን ነገር ማስወገዳችን አስፈላጊ ነው? (ለ) የበለጠ ደስታ ለማግኘት ጊዜያችንን እንዴት መጠቀም ይኖርብናል?

3 ጥንቃቄ ካላደረግን አገልግሎት ከወጣን በኋላ ውድ የሆነውን ጊዜያችንን ልናባክን እንችላለን። በመንገድ ላይ በምናገለግልበት ጊዜ በወሬ ባንጠመድ የተሻለ ነው። ከዚህ ይልቅ ሰዎችን ቀርበን ለማነጋገር እንጣር። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ጊዜውን ውጤታማ በሆነ መንገድ የምንጠቀምበት ከመሆኑም በላይ ከሥራው የበለጠ ደስታ ልናገኝ እንችላለን። (km 6/99 ገጽ 4 አን. 4, 6)

4. ጊዜያችንን በአግባቡ ለመጠቀም በምን ላይ ማተኮር ይኖርብናል? ምሳሌ ስጥ።

4 አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች የታዘበውን እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ሦስት አስፋፊዎች ሰው በሚበዛበት መንገድ ላይ መጽሔቶቻቸውን ይዘው ቆመው እርስ በርስ ሲያወሩ አየሁ፤ በአጠገባቸው ብዙ ሰዎች ያልፉ ነበር።” እነዚህ አስፋፊዎች በመንገድ ላይ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ውጤታማ ነበሩ? ይበልጥ ትኩረት የሰጡ የሚመስለው ለሰዎች ነው ወይስ ለአገልግሎት ሰዓታቸው? አብዛኞቹ አስፋፊዎች መጽሔቶቻችንን ለማበርከት አንድ ቦታ ላይ መቆም ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ አይሰማቸውም። ከሃምሳ ዓመታት በፊት ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜም እንኳ የሚሠራ ምክር ሰጥቶ ነበር፦ “በመንገድ ላይ እየተዘዋወራችሁ በቆሙ መኪናዎች ውስጥ ለተቀመጡና በመንገድ ላይ ለምታገኟቸው ሰዎች መጽሔት አበርክቱ። ፈገግ ብላችሁ ሰውየውን እያያችሁ አነጋግሩት።” (km 3/84 [እንግሊዝኛ] ገጽ 5 አን. 25)

5. በሕዝብ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ከሰዎች ጋር ጥሩ ውይይት ካደረግን በኋላ በሌላ ጊዜ ለመገናኘት ምን ዘዴ መጠቀም እንችላለን?

5 በሕዝብ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ለምታገኟቸው ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ክትትል አድርጉ። ብዙዎቻችን በመንገድ ላይ፣ በሕዝብ መጓጓዣዎች፣ በገበያ፣ በመናፈሻዎችና በሌሎች ሥፍራዎች እንሰብካለን። ለሰዎች ጽሑፍ ከማበርከታችን በተጨማሪ ይበልጥ ፍላጎት እንዲያድርባቸው መርዳት ያስፈልገናል። ይህን ዓላማ በመያዝ አንድ ሰው ፍላጎት ካሳየ ስሙን፣ አድራሻውንና ከተቻለም የስልክ ቁጥሩን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ያለውን መረጃ ማግኘት አንተ እንደምታስበው ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም። በውይይታችሁ መደምደሚያ ላይ የማስታወሻ ደብተርህን አውጥተህ “ይህን ውይይታችንን መቀጠል የምንችልበት መንገድ ይኖር ይሆን?” ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። አንድ ወንድም በቀላሉ “ስልክ ቁጥርዎ ስንት ነው?” ብሎ ይጠይቃል። ይህ ወንድም በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ካነጋገራቸው ሰዎች መካከል ከሦስቱ በስተቀር ሁሉም የስልክ ቁጥራቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ እንደነበሩ ጽፏል። (km 3/97 ገጽ 9 አን. 21)

6. በየትኛው የሰይጣን ወጥመድ እንዳንያዝ መጠንቀቅ አለብን?

6 የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ሰዎች እንዲድኑ አይፈልግም። በዚህም ምክንያት ተስፋ ቆርጠን የስብከት ሥራችንን እንድናቆም ለማድረግ ይጥራል። ይህ ካልተሳካለት ሌላ የተንኮል ዘዴ ይሸርባል፤ ይህም ያገኘናቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች እንድንረሳ ማድረግ ነው። ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ በማድረጉ ወሳኝ የአገልግሎት ዘርፍ ረገድ ግዴለሾች በመሆን በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ ንቁዎች መሆን አለብን። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ብዙ አስፋፊዎች “ይህንን ሰው አልረሳውም” ብለው ራሳቸውን በማሞኘት ፍላጎት ስላሳየው ግለሰብ ማስታወሻ እንደማይዙ ተስተውሏል። አእምሯችን በብዙ አዳዲስ ሐሳቦች ሲያዝ አንረሳቸውም ብለን ያሰብናቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ልንረሳቸው እንችላለን። ይሁን እንጂ ሰይጣን ሌላም ዘዴ ሊጠቀም ይችላል። አንድ ወንድም ከአራት ዓመታት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ በአገልግሎት ያገኛቸውን ሰዎች ዝርዝር የጻፈበት ማስታወሻ እንዳለውና ለአንዱም እንኳ ተመላልሶ መጠየቅ አድርጎ እንደማያውቅ ለአንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ነግሮታል። የአምላክ ጠላት ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች ችላ እንደተባሉ ሲመለከት አይደሰትም? (km 6/95 ገጽ 8 አን. 2, 3)

7. ሰዎች ፍላጎታቸው እንዲጨምር የመርዳት ኃላፊነታችንን እንዳንረሳ ምን ሊረዳን ይችላል?

7 ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር በኩል የተሳካላቸው ወንድሞች ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት ማሳየትና ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይት ከተደረገ በኋላ ባሉት ጊዜያት ስለ ሰዎቹ ማሰብ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። በተጨማሪም አንድን ሰው ሊማርክ የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ ማንሳትና ውይይት አድርገን ከመለያየታችን በፊት በሌላ ጊዜ ለመገናኘት የሚያስችል መሠረት መጣል አስፈላጊ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ፍላጎታቸውን ለማሳደግ ቶሎ ተመልሶ መሄድ ጠቃሚ ነው። ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግበትን ዓላማ ማለትም ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ የማድረግን ግብ ዘወትር ማስታወስ ይገባል። (km 3/97 ገጽ 10 አን. 29)

የመስበክ ችሎታችንን በማሻሻል

8. የሰዎችን ትኩረት የሚስብ መግቢያ መጠቀማችን በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

8 በመስክ አገልግሎት ዘወትር መካፈላችን የመስበክ ችሎታችን እያደገ እንዲሄድ ይረዳናል። የበለጠ ውጤታማ መግቢያ በመጠቀም ከቤት ወደ ቤት ውይይት የማስጀመር ችሎታችሁን ማሻሻል ትችላላችሁ? የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ረገድ የማስተማር ችሎታችሁን ማሳደግ ትችሉ ይሆን? እንዲህ በማድረግ በአገልግሎት የምታሳልፉትን ጊዜ በአግባቡ ልትጠቀሙበትና አገልግሎታችሁን የበለጠ ፍሬያማ ልታደርጉት ትችላላችሁ።—1 ጢሞ. 4:16 (km 6/99 ገጽ 4 አን. 9)

9. አንድ እድገት የሚያደርግ አስፋፊ በምን ተለይቶ ይታወቃል?

9 ፊልጵስዩስ 3:16 እንደሚጠቁመው ሁላችንም እድገት ለማድረግ መጣጣር ይገባናል። “እድገት” የሚለው ቃል “ወደፊት መግፋት፣ ማሻሻያ ማድረግ” ማለት ነው። እድገት የሚያደርጉ ሰዎች “ስለ አዳዲስ ሐሳቦች፣ ግኝቶች ወይም አጋጣሚዎች የማወቅ ፍላጎት አላቸው።” ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ሰዎች ክርስትና ምንም ለውጥ የማይታይበት እንዳልሆነ ከዚህ ይልቅ ተከታዮቹ እድገት ማድረጋቸውን መቀጠል እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ ፈልጎ ነበር። ራሳቸውን ለመመርመር ፈቃደኛ መሆናቸው፣ ደካማ ጎናቸውን አምነው መቀበላቸው እንዲሁም የበለጠ መሥራት ወይም የሥራቸውን ጥራት ማሻሻል የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ለማግኘት መጣጣራቸው እድገት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ድርጅት የእንቅስቃሴ አድማሱንም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ግንዛቤ በማስፋት እድገት ማድረጉን ቀጥሏል። እያንዳንዳችን ድርጅቱ ባደረጋቸው ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ በመጠቀምና በሚያከናውናቸው እንቅስቃሴዎች ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ከድርጅቱ ጋር እኩል መራመድ ይገባናል። (km 8/94 ገጽ 3 አን. 4)

10. እድገት የሚያደርጉ አገልጋዮች ምን ግብ ላይ ለመድረስ ይጣጣራሉ?

10 እድገት የሚያደርጉ አገልጋዮች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚያስችሏቸውን እያንዳንዱን አጋጣሚ ጥሩ አድርገው ይጠቀማሉ። አንዳንድ አስፋፊዎች ሰዎችን በሚያነጋግሩበት በመጀመሪያው ቀን ጥናት ማስጀመር ችለዋል። ለቤቱ ባለቤት ጽሑፎችን ስታስተዋውቁ አስቀድማችሁ የመረጣችኋቸውን አንቀጾች ተጠቀሙ። አንቀጾቹ ከምታነሱት ርዕሰ ጉዳይ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ያላቸው መሆን አለባቸው፤ እንዲሁም የምታነጋግሩትን ሰው የማወቅ ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ጥያቄዎችን መጠቀም ይኖርባችኋል። እንዲህ ለማድረግ በደንብ የሚዘጋጁ አስፋፊዎች ጥናት በማስጀመር ረገድ ይበልጥ ይሳካላቸዋል። (km 6/86 [እንግሊዝኛ] ገጽ 3 አን. 7)

ሰዎች ላይ በማተኮር

11. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስኬታማ የሆኑ አስፋፊዎች በዋነኝነት የሚያተኩሩት በምን ላይ ነው?

11 ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ይበልጥ የሚሳካላቸው ከሰዓት ወይም ጽሑፎችን ከማበርከት በበለጠ ለሰዎች ትኩረት የሚሰጡ አስፋፊዎች እንደሆኑ ማስተዋል ተችሏል። እነዚህ አስፋፊዎች በዋነኝነት የሚያተኩሩት ‘በሰዎች’ እንዲሁም ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት’ በማስጀመር ላይ ነው። ከእነዚህ አስፋፊዎች መካከል አንዳንዶቹ ከተቻለ እያንዳንዱን በር ካንኳኩ በኋላ የቤቱን ባለቤት እንዲህ ይሉታል፦ “ለሰዎች በነፃ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ግብዣ እያቀረብንላቸው ነበር፤ ለእርስዎም ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ በአጭሩ ብናሳይዎ ደስ ይለናል።” ይህ ዘዴ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። በአንድ ወቅት አንድ አስፋፊ ከቤት ወደ ቤት እያገለገለ እያለ ገና መግቢያውን መናገር እንደጀመረ የቤቱ ባለቤት “ምን ፈልገህ ነው? ነጥቡን ንገረኝ” በማለት ጠየቀው። በዚህ ጊዜ አስፋፊው “የመጣሁት መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ ማጥናት ትፈልግ እንደሆነ ለመጠየቅ ነው” በማለት መለሰለት። የቤቱ ባለቤትም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና የቀረበለትን ጥያቄ ተቀበለ። (km 4/79 [እንግሊዝኛ] ገጽ 1 አን. 7)

12. ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ መነሳሳት ያለብን ለምንድን ነው?

12 አብዛኞቻችን በአሁኑ ጊዜ በእውነት ቤት ልንኖር የቻልነው አንድ አስፋፊ በትዕግሥት ተመላልሶ መጠየቅ ስላደረገልን ነው። ይህን እርዳታ ካገኙት አንዱ ከሆንክ ራስህን እንዲህ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ፦ ‘ለዚህ አስፋፊ መጀመሪያ ላይ ያሳየሁት ስሜት ምን ዓይነት ነበር? የመንግሥቱን መልእክት እንደሰማሁ ወዲያው ተቀበልኩ? ምንም ፍላጎት የሌለኝ እመስል ነበር?’ አስፋፊው ተመላልሶ መጠየቅ ሊደረግልን የሚገባ ሰዎች እንደሆንን አድርጎ በመቁጠር ‘በአምላክ እርዳታ ድፍረት አግኝቶ’ ተመልሶ በመምጣቱና እውነትን ማስተማሩን በመቀጠሉ መደሰት ይኖርብናል። (1 ተሰ. 2:2) የሚከተለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን በጣም አስፈላጊ ነው።

13. ፍላጎት ባሳዩ ሰዎች ቶሎ ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

13 አንድ ቀን ማለዳ ሁለት አስፋፊዎች በመንገድ ላይ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ላይ እየተካፈሉ ሳለ ሕፃን ጋሪ ላይ አስቀምጣ እየገፋች ከምትሄድ አንዲት ሴት ጋር ተገናኙ። ሴትየዋ መጽሔት የተቀበለች ሲሆን በሚቀጥለው እሁድ ቤቷ እንዲመጡ እህቶችን ጋበዘቻቸው። እህቶች በተባሉት ሰዓት ቤቷ ደረሱ፤ ይሁን እንጂ ሴትየዋ ለመነጋገር ጊዜ እንደሌላት ገለጸችላቸው። በሚቀጥለው ሳምንት ግን እንደሚመቻት ነገረቻቸው። እህቶች በቀጠሮዋ ስለመገኘቷ ጥርጣሬ አድሮባቸው ነበር። ሆኖም ተመልሰው በሄዱ ጊዜ ሴትየዋ እየጠበቀቻቸው ነበር። ሴትየዋ ጥናት የተጀመረላት ሲሆን አስገራሚ እድገት ማድረግ ጀመረች። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ አዘውትራ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም በመስክ አገልግሎት መካፈል ጀመረች። ይህች ሴት በአሁኑ ጊዜ የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር ናት። (km 3/97 ገጽ 8 አን. 5, 6)

የተደራጀን በመሆን

14-16. ጥሩ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ወሳኝ የሆነው ነገር ምንድን ነው?

14 “እንዴት ደስ የሚል ውይይት ነው! ለዚህ ሰው ሳልረሳ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ አለብኝ።” እንዲህ ካላችሁ በኋላ ያነጋገራችሁት ሰው የት እንደሚኖር ጠፍቶባችሁ አያውቅም? እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟችሁ የሚያውቅ ከሆነ ሳትረሱ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ የምትችሉበት ብቸኛው መንገድ ማስታወሻ መያዝ ነው።

15 ሁሉንም ነገር በማስታወሻ አስፍሩ። ፍላጎት ካሳየው ሰው ጋር ያደረጋችሁት ውይይት ገና ከአእምሯችሁ ሳይጠፋ ጥቂት ጊዜ ወስዳችሁ ስለ ሰውየው አስፈላጊ የሆኑትን መረጃዎች በሙሉ በማስታወሻ ላይ አስፍሩ። የሰውየውን ስምና ልዩ ምልክቱን ያዙ። አድራሻውን ጻፉ እንጂ ለመገመት አትሞክሩ። የጻፋችሁት አድራሻ ትክክል መሆኑን አረጋግጡ። የተወያያችሁበትን ርዕሰ ጉዳይ፣ ያነበባችሁትን ጥቅስ እንዲሁም ያበረከታችሁለትን ጽሑፍ በማስታወሻችሁ አስፍሩ።

16 በሚቀጥለው ጉብኝት ወቅት የምትመልሱለትን አንድ ጥያቄ አንስታችሁ ከሆነ በማስታወሻችሁ ያዙት። ስለ ሰውየው፣ ስለ ቤተሰቡ ወይም ስለ ሃይማኖቱ የተገነዘባችሁት ነገር አለ? ካለ በማስታወሻ ያዙ። በሚቀጥለው ጊዜ ስትገናኙ ይህንን መጥቀሳችሁ ሰውየውን ለመርዳት ያላችሁን ፍላጎት የሚያሳይ ይሆናል። በመጨረሻም ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይት ያደረጋችሁበትንና ለመመለስ ቀጠሮ የያዛችሁበትን ቀንና ሰዓት በማስታወሻችሁ ላይ ጨምራችሁ አስፍሩ። ትክክለኛ ማስታወሻ ከያዛችሁ ያደረጋችሁትን ውይይት በደንብ ማስታወስ የምትችሉ ከመሆኑም በላይ ተመልሳችሁ እንደምትመጡ የገባችሁትን ቃል የመርሳት አጋጣሚያችሁ ጠባብ ይሆናል።—1 ጢሞ. 1:12

17. ፍላጎት ያሳየ ሰው የመዘገብንበት ማስታወሻ እንዳይጠፋብን ምን ማድረግ እንችላለን?

17 የተሟላ መረጃ ከያዛችሁ በኋላ ማስታወሻችሁን እንደ ቦርሳ፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማመራመርና ሌሎች ጽሑፎች ከመሳሰሉት የአገልግሎት መሣሪያዎቻችሁ ጋር ካስቀመጣችሁት ስትፈልጉት በቀላሉ ማግኘት ትችላላችሁ። እርግጥ ነው፣ ትክክለኛ ማስታወሻ ለመያዝ ጥረት ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ዋናው ቁም ነገር ተመልሳችሁ መሄዳችሁ ነው! (km 4/00 ገጽ 10 አን. 1-4)

18. ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ መደራጀት የምንችለው እንዴት ነው?

18 በየሳምንቱ ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግበት የተወሰነ ቀን መመደባችን ጥሩ እንደሆነ ሐሳብ ተሰጥቷል። ጥሩ እቅድ ማውጣት በዛ ያሉ ሥራዎችን ለማከናወን ያስችላል። ከቤት ወደ ቤት በምትሠሩበት አካባቢ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ዝግጅት አድርጉ። (km 3/97 ገጽ 10 አን. 28)

19. አንደኛ ቆሮንቶስ 7:29 ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ባለን ዝንባሌ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?

19 ‘የቀረው ጊዜ አጭር ስለሆነ’ ሕይወታችን በክርስቲያናዊ ሥራዎች የተሞላ መሆን አለበት። (1 ቆሮ. 7:29) ለስብከቱ ሥራ ጊዜ መመደብ ቅድሚያ ከምንሰጣቸው ነገሮች መካከል የመጀመሪያውን ቦታ ሊይዝ ይገባዋል። በአገልግሎቱ ጤናማ እና ቅንዓት የተሞላበት ተሳትፎ እናድርግ። ጊዜ ይሖዋ የሰጠን አስደናቂ ሀብት ነው። ሁልጊዜ በጥበብና በአግባብ ተጠቀሙበት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ