የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 6/15 ገጽ 8-11
  • እንደ ንስር በክንፍ መውጣት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እንደ ንስር በክንፍ መውጣት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የንስር ምስል ያለበት አርማ አንግበው
  • የንስር ዓይን
  • “የንስር መንገድ በሰማይ”
  • በንስር ክንፎች ጥላ ሥር መሆን
  • ማምለጫ መንገድ
  • ይሖዋ ለደከመው ኃይል ይሰጣል
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2017
  • ከሰማይ ወፎች የምናገኘው ትምህርት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016
  • ኢሳይያስ 40:31—‘ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ኃይላቸው ይታደሳል’
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
  • ሃርፒ ንስር—ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ የሚኖር አዳኝ ወፍ
    ንቁ!—2009
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 6/15 ገጽ 8-11

እንደ ንስር በክንፍ መውጣት

አንድ ሰው በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ አምስት ዓመት ካሳለፈ በኋላ ምን ይሰማዋል? ተስፋ መቁረጥ? ምሬት? በቀል?

እንግዳ ነገር ሊመስል ቢችልም ይህ ሁኔታ የደረሰበት አንድ ሰው “ከጠበቅሁት በላይ ጥሩ ሕይወት እመራለሁ” በማለት ጽፏል። እንደዚህ የተሰማው ለምንድን ነው? እንዲህ አለ፦ “በልዑሉ አምላክ ክንፎች ሥር መጠለያ ከማግኘቴም በተጨማሪ ‘እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ . . . ይሄዳሉ፣ አይደክሙም’ የሚሉት የነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት ሲፈጸሙ ተመልክቼአለሁ”—ኢሳይያስ 40:31

በጣም አሠቃቂ ግርፋት የደረሰበት ይህ ክርስቲያን በምሳሌያዊ ሁኔታ ሞራሉ ወደ ላይ ከፍ ከፍ ብሎ ነበር፤ ናዚ የፈጸመበት ጭካኔ ሞራሉን ሊሰብረው አልቻለም። እንደ ዳዊት በአምላክ “ክንፍ” ጥላ ተጠልሎ ነበር። (መዝሙር 57:1) ይህ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጥንካሬውን ወደ ሰማይ ተወንጭፎ ከሚወጣ ንስር ጋር በማወዳደር ነቢዩ ኢሳይያስ በተናገረው ማነጻጸሪያ ተጠቅሟል።

ችግሮች አንገትህን እንድትደፋ አድርገውህ ያውቃሉን? አንተም በልዑል አምላክ ክንፎች ለመከለልና ‘እንደ ንስር በክንፍ ለመውጣት’ እንደምትፈልግ አያጠራጥርም። ይህ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ በተደጋጋሚ ስለተጠቀሰው ንስር አንዳንድ ነገሮችን ማወቁ ጠቃሚ ነው።

የንስር ምስል ያለበት አርማ አንግበው

የጥንት ሰዎች ከሚያውቋቸው ወፎች ሁሉ ባለው ኃይልና ማራኪ በሆነ የመብረር ችሎታው በጣም ይደነቅ የነበረው ንስር ሳይሆን አይቀርም። የባቢሎን፣ የፋርስና የሮም ወታደሮችን ጨምሮ ሌሎች አያሌ የጥንት የጦር ሠራዊቶች የንስር ምስል ያለበትን አርማ አንግበው ይዘምቱ ነበር። የታላቁ ቂሮስ ጦር ሠራዊት ከእነዚህ አንዱ ነው። ይህ የፋርስ ንጉሥ የባቢሎንን ግዛት ለመቀራመት ከምሥራቅ የሚመጣ ነጣቂ ወፍ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮ ነበር። (ኢሳይያስ 45:1፤ 46:11) ይህ ትንቢት ከተጻፈ ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ በጦር ሜዳ ባንዲራቸው ላይ የንስር ምስል ያለበት አርማ የነበራቸው የቂሮስ ወታደሮች አንድ ንስር ትኩረቱ ያረፈበትን ነገር ጅው ብሎ ወርዶ እንደሚይዝ ሳይታሰብ ባቢሎንን በቁጥጥራቸው ሥር አደረጉ።

በቅርቡም እንደ ሻርለማኝ እና ናፖሊዮን ያሉ ጦረኞች እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስንና ጀርመንን የመሳሰሉ አገሮች መለያ አርማቸው ንስር እንዲሆን መርጠዋል። እስራኤላውያን የንስርም ሆነ የሌላ የማንኛውም ፍጥረት ምስል እንዳያመልኩ ታዘዋል። (ዘጸአት 20:4, 5) ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መልእክታቸውን ግልጽ ለማድረግ የንስርን ባሕርያት በምሳሌነት ተጠቅመዋል። ስለዚህ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሌሎቹ ወፎች ይልቅ ተደጋግሞ የተጠቀሰው ንስር እንደ ጥበብ፣ መለኮታዊ ጥበቃና ፍጥነት ያሉትን ነገሮች ለማመልከት አገልግሏል።

የንስር ዓይን

ንስር ስላለው ጥሩ የማየት ችሎታ ብዙ ተብሏል። ምንም እንኳ ወርቃማው ንስር አብዛኛውን ጊዜ ክብደቱ ከአምስት ኪሎ ግራም በታች ቢሆንም የዓይኑ መጠን ከሰው ዓይን ከመብለጡም በላይ የማየት ችሎታው በጣም ከፍተኛ ነው። ይሖዋ ራሱ ንስር ምግቡን በመፈለግ በኩል ስላለው ችሎታ ለኢዮብ ሲነግረው “ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች” ብሏል። (ኢዮብ 39:27, 29) አሊስ ፓርሜሊ ኦል ዘ በርድስ ኦቭ ዘ ባይብል (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “በአንድ ሐይቅ ላይ የሚንሳፈፍ የሞተ ዓሣ ከአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተመለከተ አንድ ንስር አቅጣጫውን ሳይስት ወደተመለከተው ነገር በሰያፍ ተምዘግዝጎ ይወርዳል። ንስሩ ከሩቅ ሆኖ አንድን አነስተኛ ነገር ከሰው በተሻለ ሁኔታ መመልከት ብቻ ሳይሆን አምስቱን ኪሎ ሜትሮች ወደታች በሚምዘገዘግበት ጊዜ ሳያቋርጥ ዓሣውን ይመለከተዋል።”

ንስር ባለው ጥሩ የማየት ችሎታ የተነሳ ይሖዋ ካሉት መሠረታዊ ጠባዮች መካከል አንዱ የሆነውን ጥበብን ማመልከቱ ተስማሚ ነው። (ከሕዝቅኤል 1:10፤ ራእይ 4:7 ጋር አወዳድር።) ንስር ጥበብን ለማመልከት ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው? ጥበብ አንድ እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት የሚያስከትለውን ውጤት እንድናመዛዝን ያደርገናል። (ምሳሌ 22:3) ንስር ከረጅም ርቀት የማየት ችሎታ ስላለው ኢየሱስ በምሳሌው ላይ እንደጠቀሰው ጎርፍ ሊመጣ እንደሚችል በማሰብ ቤቱን በዓለት ላይ እንደገነባው ልባም ሰው አደገኛ ሁኔታዎችን ከሩቁ አይቶ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይችላል። (ማቴዎስ 7:24, 25) እንዲያውም በስፓንኛ እከሌ ንስር ነው ከተባለ አስተዋይ ነው ማለት ነው።

ንስርን በቅርበት የማየት አጋጣሚ ካገኘህ አስተያየቱን ልብ ብለህ ተመልከት። እንደነገሩ አየት አድርጎ አይተውህም፤ ከዚህ ይልቅ አስተያየቱ ስለሁኔታህ እያንዳንዷን ነገር የሚመረምር ይመስላል። እንደዚሁ ሁሉ አንድ ጥበበኛ ሰው በራሱ የተፈጥሮ ችሎታ ወይም አስተሳሰብ ከመመካት ይልቅ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ነገሮችን በጥንቃቄ ይመረምራል። (ምሳሌ 28:26) ንስር ያለው ጥሩ የማየት ችሎታ ከአምላክ ጠባዮች አንዱ የሆነውን ጥበብ ለማመልከት ተስማሚ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አስገራሚ የመብረር ችሎታውንም በምሳሌ ለመግለጽ ተጠቅመውበታል።

“የንስር መንገድ በሰማይ”

‘ንስር በሰማይ ላይ በሚያደርገው ጉዞ’ ያለው ፍጥነትም ሆነ በጣም ዘና ብሎ የሚያደርገው በረራ ትኩረት የሚስብ ነው፤ በሚበርበት ጊዜ የተወሰነ መስመር የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ የበረረበትን አቅጣጫ ለመጠቆም የሚያስችል ምንም ዓይነት ምልክት ከበስተኋላው አይተውም። (ምሳሌ 30:19) በሰቆቃወ ኤርምያስ 4:19 ላይ የንስር ፈጣንነት አንድ ነገር ለማመልከት አገልግሏል፤ ይህ ጥቅስ ስለ ባቢሎን ወታደሮች ሲናገር “አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፣ በምድረ በዳ ሸመቁብን” ይላል። አንድ ንስር ሊይዘው የፈለገውን ነገር ነጥሎ በማየት በሰማይ ላይ ካንዣበበ በኋላ ክንፎቹን አጠፍ አድርጎ ቁልቁል ይምዘገዘጋል፤ በዚህ ጊዜ ፍጥነቱ በሰዓት 130 ኪሎ ሜትር ሊደርስ እንደሚችል አንዳንድ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። ቅዱሳን ጽሑፎች ንስርን በተለይ ከወታደራዊ ኃይል ጋር በተያያዘ ሁኔታ ፍጥነትን ለማመልከት መጠቀማቸው አያስደንቅም።—2 ሳሙኤል 1:23፤ ኤርምያስ 4:13፤ 49:22

በሌላ በኩል ኢሳይያስ ንስር ስላለው ዘና ብሎ የመብረር ችሎታ ተናግሯል። “እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፣ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙም።” (ኢሳይያስ 40:31) ንስር ክንፉን ሳያርገበግብ ለመንሳፈፍ የሚያስችለው ምንድን ነው? ንስሩ ቴርማልስ ወይም ሙቅ አየር ወደ ላይ የሚወጣባቸውን መስመሮች ተከትሎ ስለሚበር ወደ ላይ ለመውጣት ብዙ ጉልበት አያባክንም። ቴርማልስ በዓይን የማይታዩ ቢሆኑም ንስሩ ያሉበትን ቦታ ፈልጎ በማግኘት በኩል የተካነ ነው። ንስሩ አንድ ቴርማል ካገኘ በኋላ ክንፎቹንና ጅራቱን ዘርግቶ ሙቁ አየር በሚገኝበት ክልል ውስጥ ያንዣብባል፤ ይህም ሙቅ አየር ንስሩን ወደ ላይ ይገፋዋል። ተፈላጊው ከፍታ ላይ ሲደርስ ቀጥሎ ወዳለው ቴርማል ይሻገራል፤ እዚያም እንደዚሁ ያደርጋል። ንስሩ በዚህ መንገድ ብዙ ጉልበት ሳያባክን በአየር ላይ አያሌ ሰዓታት መቆየት ይችላል።

እስራኤል ውስጥ በተለይ በቀይ ባሕር ዳርቻ ከሚገኘው ዔጽዮንጋብር ጀምሮ በሰሜን እስከሚገኝው ዳን በተዘረጋው ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ንስሮች እንደልብ ይታያሉ። በተለይ ከሌላ ቦታ ፈልሰው በሚመጡባቸው የጸደይና የመከር ወቅቶች ብዛት ይኖራቸዋል። ወደ 100,000 የሚጠጉ ንስሮች የተቆጠሩባቸው ዓመታት አሉ። የጠዋቱ ፀሐይ አየሩን ሲያሞቀው በመቶ የሚቆጠሩ አዳኝ ንስሮች ስምጥ ሸለቆውን በሚያዋስነው ገደል ላይ ሲበሩ ማየት ይቻላል።

ንስር ብዙ ኃይል ሳያባክን የሚያደርገው በረራ ይሖዋ የሚያደርግልን ድጋፍ ሥራችንን ለማከናወን የሚረዳ መንፈሳዊና ስሜታዊ ብርታት ሊሰጠን እንደሚችል የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። አንድ ንስር በራሱ ጥንካሬ ይህን የሚያክል ከፍታ ላይ መድረስ እንደማይችል ሁሉ እኛም በራሳችን ችሎታዎች የምንመካ ከሆነ ሥራችንን ማከናወን አንችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 4:13) አንድ ንስር በዓይን የማይታዩትን ቴርማልስ ያለማቋረጥ እንደሚፈልግ ሁሉ እኛም በልባዊ ጸሎቶች አማካይነት የማይታየውን የይሖዋ አንቀሳቃሽ ኃይል እንድናገኝ ‘መለመናችንን መቀጠል’ አለብን።—ሉቃስ 11:9, 13

ከሌላ ቦታ ፈልሰው የመጡ ንስሮች ብዙውን ጊዜ ቴርማልሱን የሚያገኙት ሌሎች አዳኝ ወፎችን በመመልከት ነው። የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ የሆኑት ዲ አር ማክንቶሽ አንድ ጊዜ 250 ንስሮችና ጥንብ አንሣዎች በአንድ ቴርማል ውስጥ ሲያንዣብቡ እንደታዩ ሪፖርት አድርገዋል። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ሌሎች አምላካዊ አገልጋዮች ትተው ያለፏቸውን የታማኝነት ምሳሌዎች በመኮረጅ ይሖዋ በሚሰጠው ኃይል መመካትን ከዚህ ሊማሩ ይችላሉ።—ከ1 ቆሮንቶስ 11:1 ጋር አወዳድር።

በንስር ክንፎች ጥላ ሥር መሆን

በአንድ ንስር የሕይወት ዘመን ውስጥ በጣም አደገኛ ከሆኑት ጊዜያት አንዱ እንዴት መብረር እንደሚችል የሚማርበት ጊዜ ነው። ለመብረር በሚያደርጉት ሙከራ ሕይወታቸውን የሚያጡ ንስሮች ጥቂት አይደሉም። አዲስ የተዋቀረው የእስራኤል ብሔር ከግብፅ ሲወጣ አደጋ አጋጥሞት ነበር። ስለዚህ ይሖዋ “በግብፃውያን ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ እንደ ተሸከምኋችሁ፣ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል” በማለት ለእስራኤላውያን የተናገራቸው ቃላት በጣም ተስማሚ ናቸው። (ዘጸአት 19:4) ጫጩት ንስሮች ለመብረር በሚያደርጓቸው የመጀመሪያ ሙከራዎች እንዳይከሰከሱ ለመርዳት ትልልቆቹ ንስሮች ጀርባቸው ላይ ተሸክመዋቸው ለአጭር ጊዜ እንደሚበሩ በተለያዩ ጊዜያት ሪፖርት ተደርጓል። ጂ አር ድራይቨር ፓልስታይን ኤክስፕሎሬሽን ኳርተርሊ (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደዚህ ስላሉት ሪፖርቶች ሲናገሩ “[በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሰጠው] ሥዕላዊ መግለጫ የሐሳብ ፈጠራ ሳይሆን በእውነት ላይ የተመሠረተ ነው” ብለዋል።

ንስሮች በሌሎች ሁኔታዎችም ምሳሌ የሚሆኑ ወላጆች ናቸው። ጎጆአቸው ውስጥ ለሚኖረው ጫጩት ያለማቋረጥ ምግብ በማቅረብ ብቻ ሳይወሰኑ ሴቷ ንስር ወንዱ ያመጣውን ሥጋ በመቆራረጥ ጫጩቱ ለመዋጥ እንዳይቸገር ትረዳዋለች። ብዙውን ጊዜ ጎጆአቸውን የሚሠሩት ገደል ወይም ረጃጅም ዛፎች ላይ ስለሆነ ጫጩት ንስሮች ለመጥፎ የአየር ጠባይ ይጋለጣሉ። (ኢዮብ 39:27, 28) ወላጆቹ ንስሮች ካልተንከባከቧቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተጠቀሱት አገሮች ውስጥ የተለመደው የሚያቃጥል ፀሐይ ጫጩቶቹን ሊገድላቸው ይችላል። ትልቁ ንስር ጨቅላ ጫጩቱን ለመጋረድ ሲል ለብዙ ሰዓታት ክንፎቹን ዘርግቶ ይቀመጣል።

ስለዚህ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የንስር ክንፎች መለኮታዊ ጥበቃን ለማመልከት መጠቀሳቸው በጣም ተስማሚ ነው። እስራኤላውያን አስቸጋሪውን የምድረ በዳ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት ይሖዋ ጥበቃ ያደረገላቸው እንዴት እንደነበረ ዘዳግም 32:9-12 (የ1980 ትርጉም) እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል፦ “የያዕቆብን ዘሮች ግን የራሱ ወገን አድርጎ መረጠ። እነርሱንም በበረሓ፣ ነፋስ በሚነዳውና በተበላሸ ምድረ በዳ ሲባዝኑ አገኛቸው። እንደ ዐይን ብሌን ጥንቃቄ በማድረግና በመከባከብ ጠበቃቸው። ንስር ጫጩቶችዋን በክንፍ የመብረርን ጥበብ እንደምታለማምድና በተዘረጉ ክንፎችዋ ተጠንቅቃ እንደምትይዛቸው፣ እግዚአብሔርም እስራኤልን እንደዚሁ ከውድቀት ጠብቆአል። እግዚአብሔር የማንንም ባዕድ አምላክ ዕርዳታ ሳይፈልግ ብቻውን ሆኖ ሕዝቡን መራ።” በይሖዋ ከታመንን ለእኛም ይህን የመሰለ ፍቅራዊ ጥበቃ ያደርግልናል።

ማምለጫ መንገድ

አንዳንዴ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ካሉብን ችግሮች ሁሉ ለማምለጥ እንመኛለን። ዳዊትም ልክ እንደዚሁ ተሰምቶት ነበር። (ከመዝሙር 55:6, 7 ጋር አወዳድር።) ምንም አንኳ ይሖዋ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ፈተና እና ሥቃይ ሲደርስብን እንደሚረዳን ቃል ቢገባልንም ሙሉ በሙሉ ከችግራችን አያላቅቀንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል፦ “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:13

“መውጫ” ወይም “ማምለጫ” (ኪንግ ጄምስ ቨርሽን) በይሖዋ መታመንን ያጠቃልላል። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ የሰጠው ማክስ ሌይብስተር ይህ እውነት መሆኑን አይቷል። በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ባሳለፋቸው ዓመታት ይሖዋን ይበልጥ ከማወቁም በተጨማሪ በእርሱ ላይ ተደግፎ ነበር። ማክስ በተሞክሮ እንዳየው ይሖዋ እኛንም በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ አማካይነት ያበረታናል። በማጎሪያ ካምፖች እንኳ ሳይቀር ምሥክሮቹ የእምነት ወንድሞቻቸውን ፈልገው መንፈሳዊ እርዳታ አድርገውላቸዋል፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችንና የነበሯቸውን ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አካፍለዋቸዋል። እንዲሁም በታማኝነት ጸንተው ከሞት የተረፉ ወንድሞች ደጋግመው እንደሚናገሩት ይሖዋ አጠንክሯቸው ነበር። ማክስ “ይሖዋ እንዲረዳኝ በተደጋጋሚ እጠይቀው የነበረ ሲሆን መንፈሱ ደግፎኛል” ብሏል።

ማንኛውም ዓይነት መከራ ሲያጋጥመን ሳናቋርጥ በመጸለይ የምናገኘው የአምላክ መንፈስ ቅዱስ እንደሚረዳን ትምክህት ሊኖረን ይችላል። (ማቴዎስ 7:7-11) በዚህ “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” በመበረታታት ባሉብን ችግሮች አንገታችንን ከመድፋት ይልቅ ከፍተኛ ብርታት እናገኛለን። በይሖዋ መንገዶች እየተመላለስን ከመቀጠላችንም በተጨማሪ አንታክትም። እንደ ንስር በክንፍ እንወጣለን።—2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ኢሳይያስ 40:31

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እንደነገሩ አየት አድርጎ አይተውህም

[ምንጭ]

ፎቶ፦ Cortesía de GREFA

[ምንጭ]

ፎቶ፦ Cortesía de Zoo de Madrid

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ