ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ
ውድ ወንድሞችና እህቶች
“ሁላችሁንም በጸሎታችን በጠቀስን ቁጥር ሁልጊዜ አምላክን እናመሰግናለን፤ የእምነት ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨ ድካማችሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተስፋ በማድረጋችሁ የተነሳ የምታሳዩትን ጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን።” (1 ተሰ. 1:2, 3) እነዚህ ቃላት ለእናንተ ያለንን ስሜት በሚገባ የሚገልጹ ናቸው! ስለ እናንተ እንዲሁም እያከናወናችሁት ስላለው ሥራ ይሖዋን እናመሰግናለን። ለምን?
ባለፈው ዓመት ከመንግሥቱ ሥራዎች ጋር በተያያዘ “የእምነት ሥራችሁን” እንዲሁም “ከፍቅር የመነጨ ድካማችሁን” የሚያሳይ ብዙ ነገር አከናውናችኋል። ብዙዎቻችሁ አጋጣሚዎችን በመፈለግ አገልግሎታችሁን ለማስፋት ጥረት አድርጋችኋል። አንዳንዶች ወደ ሌሎች አካባቢዎች አልፎ ተርፎም ከአገራቸው ውጭ ወደሚገኙ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ተዛውረው እያገለገሉ ነው። ሌሎች ደግሞ በአደባባይ ምሥክርነት በመካፈል አገልግሎታቸውን አስፍተዋል። ብዙዎች በመታሰቢያው በዓል ሰሞን፣ በወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት ወይም በነሐሴ 2014 በተደረገው ልዩ ዘመቻ ወቅት ረዳት አቅኚ ሆነው አገልግለዋል። ያላችሁበት ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም ሁላችሁም ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችሁ ለማገልገል ጥረት እያደረጋችሁ እንደሆነ ተገንዝበናል፤ በመሆኑም ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። (ቆላ. 3:23, 24) በእርግጥም “የእምነት ሥራችሁ” ይሖዋን ለማመስገን ምክንያት ሆኖናል!
በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ከሚካሄዱ የቲኦክራሲያዊ ሕንፃ ግንባታዎች ጋር በተያያዘ ያሳያችሁትን “ከፍቅር የመነጨ ድካማችሁን” ከልብ እናደንቃለን። የይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ እንዲህ ያሉ ሕንፃዎችን መገንባት አጣዳፊ ሆኗል። (ኢሳ. 60:22) እስቲ አስቡት፣ ባለፈው ዓመት የነበረን ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር 8,201,545 ሲሆን በየወሩ በአማካይ 9,499,933 የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ይመሩ ነበር። እንዲህ ያለ እድገት መኖሩ በርካታ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የማስፋፊያ ግንባታ ማካሄድ ወይም ነባሮቹን ሕንፃዎች በአዲስ መልክ መገንባት አስፈልጓቸዋል። እድገቱ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች እንደሚያስፈልጉንም የሚጠቁም ነው! በሌላ በኩል ደግሞ ተርጓሚዎቻችን፣ ቋንቋቸው በሚነገርበት አካባቢ እየኖሩ ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ቦታዎች የርቀት የትርጉም ቢሮዎችን ማቋቋም አስፈላጊ ሆኗል።
በመሆኑም ‘እነዚህን ሕንፃዎች በመገንባት ረገድ ምን ድጋፍ ማድረግ እችላለሁ?’ ብለን ራሳችን መጠየቅ እንችላለን። አንዳንዶቻችን በግንባታ ሥራው ላይ በቀጥታ ለመሳተፍ ራሳችንን ማቅረብ እንችል ይሆናል። የግንባታ ሙያ ይኑረንም አይኑረን ለዚህ አስፈላጊ ሥራ ውድ ነገሮቻችንን የመስጠት መብት አለን። (ምሳሌ 3:9, 10) የማደሪያው ድንኳን በተሠራበት ወቅት እስራኤላውያን ስጦታ የመስጠት ከፍተኛ ተነሳሽነት ነበራቸው፤ ስለሆነም ያመጡት ስጦታ ከሚፈለገው በላይ በመሆኑ ማንም ሰው ተጨማሪ ስጦታ እንዳያመጣ የሚከለክል ማስታወቂያ መናገር አስፈልጎ ነበር። (ዘፀ. 36:5-7) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እንዲህ ያሉ ምሳሌዎች ልባችንን እንደሚነኩትና ለተግባር እንደሚያነሳሱን እሙን ነው። የቅዱስ አገልግሎት ክፍል ከሆነው ከዚህ አስፈላጊ ሥራ ጋር በተያያዘ የምታሳዩት ‘ከፍቅር የመነጨ ድካም’ ይሖዋን ለማመስገን የሚገፋፋን ሌላው ምክንያት ነው!
የወንድሞቻችንን ጽናት መመልከታችን ልዩ ደስታ እንዲሰማን አድርጓል። ለምሳሌ በደቡብ ኮሪያ ያሉትን ውድ ወንድሞቻችንን መጥቀስ ይቻላል። ከ1950 ጀምሮ በዚያ አገር የሚገኙ ወጣት ወንድሞች ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገዋል። ወንድሞቻችን ለበርካታ ዘመናት እንዲህ ያለውን ግፍ በጽናት ተቋቁመዋል። እነሱ የተዉት ምሳሌ እምነታችንን ያጠናክረዋል!
በኤርትራ ያሉ ሦስት ወንድሞቻችን ከ20 ለሚበልጥ ዓመታት በእስር ላይ ይገኛሉ። እህቶቻችንና ልጆቻቸውን ጨምሮ ሌሎች ወንድሞቻችንም ለተወሰነ ጊዜ ታስረዋል። ከእስር እንዲለቀቁ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም አንዳቸውም ውጤት አላስገኙም። ወንድሞቻችን ግን አቋማቸውን አላላሉም። ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም ታማኝነታቸውን ጠብቀዋል። እነዚህን ታማኝ ወንድሞች ምንጊዜም በጸሎታችን እናስታውሳቸዋለን።—ሮም 1:8, 9
እርግጥ ነው፣ ብዙዎቻችሁ በእምነታችሁ ምክንያት እስር ቤት አልገባችሁ ይሆናል። ያም ቢሆን አብዛኞቻችሁ ከዕድሜ መግፋት፣ ከከባድ የጤና ችግር፣ የማያምን የትዳር ጓደኛ ወይም ዘመድ ከሚያደርስባችሁ ተቃውሞና እናንተ ብቻ ከምታውቋቸው የግል ችግሮቻችሁ ጋር እየታገላችሁ ነው። እንደዚያም ሆኖ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችሁን ቀጥላችኋል! (ያዕ. 1:12) በጣም እናመሰግናችኋለን። በታማኝነት መጽናታችሁ ይሖዋን እንድናመሰግነው የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ነው።
በእርግጥም የእምነት ሥራችሁ፣ ከፍቅር የመነጨ ድካማችሁና ጽናታችሁ ‘ይሖዋን ለጥሩነቱ እንድናመሰግነው’ የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት ነው። (መዝ. 106:1) ሁላችሁንም እንወዳችኋለን እንዲሁም ይሖዋ፣ እሱን ለዘላለም ማገልገል ትችሉ ዘንድ እንዲያበረታችሁ፣ እንዲያጸናችሁና እንዲባርካችሁ እንጸልያለን።
ወንድሞቻችሁ
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል