‘በእምነት እንጂ በማየት አትመላለሱ’
ኢየሩሳሌም ከመከበቧና ከመጥፋቷ ጥቂት ቀደም ብሎ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ወታደሮች እንደመሆናቸው መጠን ችግር እንደሚያጋጥማቸው መጠበቅ እንዳለባቸው እንዲሁም ለራሳቸው ምቾትና ደስታ ቅድሚያ መስጠት እንደማይኖርባቸው ጽፎ ነበር። (2 ጢሞ. 2:3, 4) ከአምላክ የራቀው ይህ ዓለም ሊጠፋ በተቃረበበት በዚህ ጊዜ፣ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ለማድረግ ጠንካራ እምነት ያስፈልገናል። (2 ቆሮ. 4:18፤ 5:7) ‘በእምነት እንጂ በማየት አትመላለሱ’ (በአማርኛ አይገኝም) የሚለውን ቪዲዮ ተመልከቱ። (jw.orgን ክፈቱ፤ ከዚያም የሕትመት ውጤቶች > ቪዲዮዎች በሚለው ሥር ተመልከቱ።) ከቁሳዊ ነገሮች ጋር ከልክ ያለፈ ቁርኝት መፍጠር ለነሐምና ለአቢጣል አደገኛ ወጥመድ የሆነባቸው እንዴት እንደሆነ ልብ በሉ። ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ከልሱ።
(1) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ‘በተቀደሰ ስፍራ የቆመው ጥፋት የሚያመጣ ርኩስ ነገር’ ምንድን ነው? በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ምን ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው? (ማቴ. 24:15, 16) (2) ከከተማዋ ሸሽቶ መውጣት እምነት የሚጠይቀው ለምንድን ነው? (3) ከከተማዋ ሸሽቶ መውጣት ምን መሥዋዕቶችን መክፈል ይጠይቃል? (4) ነሐምና አቢጣል የዘገዩት ለምን ነበር? (ማቴ. 24:17, 18) (5) ራሔል ኢየሩሳሌምን ለቃ ስትወጣ እምነቷን የሚፈትኑ ምን ተጨማሪ ችግሮች አጋጥመዋት ነበር? (ማቴ. 10:34-37፤ ማር. 10:29, 30) (6) ኤታን በእምነትና በይሖዋ በመታመን ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሆነው እንዴት ነው? (7) ክርስቲያኖች በፔላ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጠመዋቸው ነበር? (8) የነሐምና የአቢጣል እምነት ቀስ በቀስ እየተዳከመ የመጣው እንዴት ነበር? (9) ይሖዋ በፔላ ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች የተንከባከባቸው እንዴት ነበር? (ማቴ. 6:33፤ 1 ጢሞ. 6:6-8) (10) የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ እየተጠባበቅን ባለንበት በዚህ ወቅት የአብርሃምንና የሣራን አርዓያ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ዕብ. 11:8-10) (11) ነሐምና አቢጣል ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ እንዲወስኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ይህ አመለካከታቸው ስህተት የነበረው ለምንድን ነው? (ሉቃስ 21:21) (12) ነሐምና አቢጣል ሲመለሱ በኢየሩሳሌም የጠበቃቸው ሕይወት ምን ይመስል ነበር? (13) የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት ከአሁኑ እምነታችንን ማጠናከር ያለብን ለምንድን ነው?—ሉቃስ 17:31, 32፤ 21:34-36
በእምነት መመላለስ ሲባል (1) ይሖዋ በሚሰጠን አመራር ላይ ሙሉ እምነት መጣል፣ (2) ከእሱ አመራር ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ እና (3) ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ እንደምንሰጥ ማሳየት ማለት ነው። “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በሚለው ሐሳብ ላይ ሙሉ በሙሉ በመተማመን በእምነት ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—1 ዮሐ. 2:17