የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ጥቅምት 2019
ከጥቅምት 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ያዕቆብ 3-5
“አምላካዊ ጥበብን አንጸባርቁ”
(ያዕቆብ 3:17) ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው።
‘ላይኛይቱን ጥበብ’ በአኗኗርህ እያንጸባረቅህ ነው?
9 “በመጀመሪያ ንጽሕት ናት።” ንጽሕት የሚለው አባባል ውጫዊ ንጽሕናን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ንጽሕናንም ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብን ከልብ ጋር ያዛምደዋል። ይሁን እንጂ ሰማያዊ ጥበብ በክፉ አሳብ፣ ምኞትና ፍላጎት ወደተበከለ ልብ ሊገባ አይችልም። (ምሳሌ 2:10፤ ማቴዎስ 15:19, 20) ሆኖም አለፍጽምናችን በፈቀደልን መጠን ልባችንን ንጹሕ ለማድረግ የምንጥር ከሆነ ‘ከክፉ እንሸሻለን፣ መልካምንም እናደርጋለን።’ (መዝሙር 37:27፤ ምሳሌ 3:7) ንጽሕና የጥበብ የመጀመሪያ መለያ ባሕርይ ተደርጎ መጠቀሱ ተገቢ አይደለም? ደግሞስ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕ ካልሆንን የላይኛይቱን ጥበብ ሌሎች ገጽታዎች እንዴት ማንጸባረቅ እንችላለን?
10 “በኋላም ታራቂ።” ሰማያዊ ጥበብ የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆነውን ሰላምን አጥብቀን እንድንሻ ይገፋፋናል። (ገላትያ 5:22) የይሖዋን ሕዝብ ‘አንድ የሚያደርገውን ሰላም’ ከማደፍረስ እንቆጠባለን። (ኤፌሶን 4:3) ሰላም በሚደፈርስበት ጊዜ ደግሞ ዳግመኛ ሰላም እንዲሰፍን የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በሰላም ኑሩ፣ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል” በማለት ይገልጻል። (2 ቆሮንቶስ 13:11) ስለዚህ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እስከኖርን ድረስ የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል። ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት የምናሳየው ባሕርይ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በቀጥታ ይነካል። ሰላም ፈጣሪዎች መሆናችንን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
(ያዕቆብ 3:17) ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው።
‘ላይኛይቱን ጥበብ’ በአኗኗርህ እያንጸባረቅህ ነው?
12 “ምክንያታዊ።” ምክንያታዊ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ምሑራን እንደሚሉት ከሆነ በያዕቆብ 3:17 ላይ “ምክንያታዊ” የሚል ፍቺ የተሰጠውን የግሪክኛ ቃል መተርጎም አስቸጋሪ ነው። ተርጓሚዎች ይህን ቃል “ገር፣” “ታጋሽ” እና “አሳቢ” የሚል ፍቺ ሰጥተውታል። የግሪክኛው ቃል ጥሬ ትርጉም “ግትር አለመሆን” የሚል ነው። ይህን የላይኛይቱን ጥበብ ገጽታ በአኗኗራችን ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?
‘ላይኛይቱን ጥበብ’ በአኗኗርህ እያንጸባረቅህ ነው?
14 “እሺ ባይ።” “እሺ ባይ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሌላ ቦታ ላይ አይገኝም። አንድ ምሑር እንደገለጹት ከሆነ ይህ ቃል “አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀሰው ከወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ነው።” “በቀላሉ እሺ ብሎ የሚቀበል” እና “ታዛዥ” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። በላይኛይቱ ጥበብ የሚመራ ሰው ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡትን መመሪያ ያለ ምንም ማንገራገር ይታዘዛል። አንዴ አንድ ውሳኔ ላይ ከደረሰ ምንም ዓይነት ሐሳብ ቢቀርብለት የማይቀበል ሰው አይደለም። ከዚህ ይልቅ የተሳሳተ እርምጃ እንደወሰደ ወይም የተሳሳተ ውሳኔ እንደወሰነ የሚያሳይ አሳማኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ሲቀርብለት ወዲያውኑ አቋሙን ይለውጣል። እንዲህ ዓይነት ስም አትርፈሃል?
“ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት”
15 “ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት።” ላይኛይቱ ጥበብ ‘ምሕረት የሞላባት’ እንደሆነች ስለተገለጸ ምሕረት የላይኛይቱ ጥበብ ዋና ገጽታ ነው። “ምሕረት” እና “በጎ ፍሬ” አንድ ላይ እንደተጠቀሱ ልብ በል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ምሕረት የሚለው ቃል ለሌሎች ከልብ ማሰብንና በርኅራኄ መልካም ማድረግን የሚያመለክት በመሆኑ ከበጎ ፍሬ ጋር ተያይዞ መገለጹ የተገባ ነው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ምሕረት የሚለው ቃል “አንድ ሰው በደረሰበት መጥፎ ሁኔታ ማዘንንና ያን ሰው ለመርዳት መሞከርን” እንደሚያመለክት ገልጿል። ስለሆነም የአምላክ ጥበብ ርኅራኄና አዘኔታ የሌለው ወይም እንዲሁ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ጥበብ ያለው ሰው አፍቃሪና ርኅሩኅ ከመሆኑም በላይ የሌሎችን ስሜት ይረዳል። ምሕረት የተሞላን መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
(ያዕቆብ 3:17) ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው።
‘ላይኛይቱን ጥበብ’ በአኗኗርህ እያንጸባረቅህ ነው?
18 ‘አድልዎ የሌለባት።’ የአምላክ ጥበብ ያለው ሰው ለዘር መድልዎና ለብሔራዊ ኩራት ቦታ የለውም። በዚህ ጥበብ የምንመራ ከሆነ ማንኛውንም ዓይነት የአድልዎ ስሜት ከልባችን ውስጥ ነቅለን ለማስወገድ እንጥራለን። (ያዕቆብ 2:9) የሰዎችን የትምህርት ደረጃ፣ የኑሮ ሁኔታ ወይም የጉባኤ ኃላፊነት በማየት አናዳላም። በተጨማሪም የእምነት ባልንጀሮቻችን የኑሮ ደረጃቸው የቱንም ያህል ዝቅተኛ ቢሆን አንንቃቸውም። እነዚህን ሰዎች ይሖዋ እስከወደዳቸው ድረስ እኛም ልንወዳቸው ይገባል።
19 “ግብዝነት የሌለባት።” “ግብዝ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አንድን ገጸ ባሕርይ ወክሎ የሚጫወትን ተዋናይ” ሊያመለክት ይችላል። በጥንት ዘመን የግሪክና የሮም ተዋናዮች በሚተውኑበት ወቅት ትላልቅ ጭምብሎችን ያጠልቁ ነበር። በመሆኑም “ግብዝ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አስመስሎ መጫወትን ለማመልከት ይሠራበት ነበር። ይህ የአምላክ ጥበብ ገጽታ ለሌሎች የምናደርገውን ነገር ብቻ ሳይሆን ለእነሱ ያለንን አመለካከትም ሊነካው ይገባል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ያዕቆብ 4:5) ወይስ ቅዱስ መጽሐፉ “በውስጣችን ያደረው መንፈስ በቅናት ሁልጊዜ ይመኛል” ያለው ያለምክንያት ይመስላችኋል?
የያዕቆብና የጴጥሮስ ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
4:5—ያዕቆብ እዚህ ላይ የጠቀሰው የትኛውን ጥቅስ ነው? ያዕቆብ በቀጥታ የጠቀሰው ጥቅስ የለም። ይሁን እንጂ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተናገራቸው እነዚህ ቃላት እንደ ዘፍጥረት 6:5፤ 8:21፤ ምሳሌ 21:10 እና ገላትያ 5:17 ያሉት ጥቅሶች በያዙት አጠቃላይ ሐሳብ ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይችላሉ።
(ያዕቆብ 4:11, 12) ወንድሞች፣ አንዳችሁ ሌላውን መንቀፋችሁን ተዉ። ወንድሙን የሚነቅፍ ወይም በወንድሙ ላይ የሚፈርድ ሁሉ ሕግን ይነቅፋል እንዲሁም በሕግ ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ የምትፈርድ ከሆነ ደግሞ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን ፈጻሚ አይደለህም። 12 ሕግ የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እሱ ማዳንም ሆነ ማጥፋት ይችላል። ታዲያ በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
እምነት እንድንታገሥና በጸሎት እንድንተጋ ያደርገናል
8 የእምነት ወንድማችንን መንቀፍ ኃጢአት ነው። (ያዕቆብ 4:11, 12) ይሁንና አንዳንዶች ራሳቸውን የማመጻደቅ ባሕርይ ስላላቸው ወይም ደግሞ ሌሎችን በማጣጣል ራሳቸውን ማዋደድ ስለሚፈልጉ ሊሆን ይችላል፣ መሰል ክርስቲያኖችን ይተቻሉ። (መዝሙር 50:20፤ ምሳሌ 3:29) ‘መንቀፍ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጥላቻን የሚያንጸባርቅ ሲሆን የተጋነነ ወይም የሐሰት ክስ መሰንዘርን ያመለክታል። ይህም በአንድ ወንድም ላይ የተጣመመ ፍርድ ከማስተላለፍ ተለይቶ አይታይም። ይህስ ‘የአምላክን ሕግ መተቸትና በሕጉ ላይ መፍረድ’ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ጻፎችና ፈሪሳውያን ‘የአምላክን ትእዛዝ በብልሃት ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው’ በራሳቸው የአቋም ደረጃዎች መሠረት ይፈርዱ ነበር። (ማርቆስ 7:1-13) በተመሳሳይም ይሖዋ የማይኮንነውን ወንድም እኛ የምንኮንነው ከሆነ ‘በአምላክ ሕግ ላይ መፍረዳችንና’ ሕጉ ብቁ አይደለም ማለታችን አይሆንምን? ወንድማችንን አግባብነት በሌለው መንገድ የምንተች ከሆነ የፍቅርን ሕግ ፈጽመናል ማለት አንችልም።—ሮሜ 13:8-10
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ያዕቆብ 3:1-18) ወንድሞቼ ሆይ፣ ከእናንተ መካከል ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛ የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁ። 2 ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለንና። በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው መላ ሰውነቱንም መቆጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው። 3 ፈረሶች እንዲታዘዙልን አፋቸው ውስጥ ልጓም ካስገባን መላ ሰውነታቸውንም መምራት እንችላለን። 4 መርከቦችንም ተመልከቱ፦ በጣም ትልቅና በኃይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ሁሉ ይመራቸዋል። 5 ልክ እንደዚሁም ምላስ ትንሽ የአካል ክፍል ሆና ሳለ ጉራዋን ትነዛለች። በጣም ሰፊ የሆነን ጫካ በእሳት ለማያያዝ ትንሽ እሳት ብቻ ይበቃል! 6 ምላስም እሳት ናት። ምላስ በአካል ክፍሎቻችን መካከል የክፋትን ዓለም ትወክላለች፤ መላ ሰውነትን ታረክሳለችና፤ እንዲሁም መላውን የሕይወት ጎዳና ታቃጥላለች፤ እሷም በገሃነም ትቃጠላለች። 7 ማንኛውም ዓይነት የዱር እንስሳ፣ ወፍ፣ በምድር ላይ የሚሳብ ፍጥረትና በባሕር ውስጥ የሚኖር ፍጥረት በሰዎች ሊገራ ይችላል፤ ደግሞም ተገርቷል። 8 ምላስን ግን ሊገራ የሚችል አንድም ሰው የለም። ምላስ ገዳይ መርዝ የሞላባት፣ ለመቆጣጠር የምታስቸግር ጎጂ ነገር ናት። 9 በምላሳችን አባት የሆነውን ይሖዋን እናወድሳለን፤ ይሁንና በዚህችው ምላሳችን “በአምላክ አምሳል” የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። 10 ከአንድ አፍ በረከትና እርግማን ይወጣሉ። ወንድሞቼ፣ ይህ መሆኑ ተገቢ አይደለም። 11 አንድ ምንጭ ከዚያው ጉድጓድ ጣፋጭና መራራ ውኃ ያፈልቃል? 12 ወንድሞቼ፣ የበለስ ዛፍ ወይራን ወይም ደግሞ የወይን ተክል በለስን ሊያፈራ ይችላል? ከጨዋማ ውኃም ጣፋጭ ውኃ ሊገኝ አይችልም። 13 ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ ሰው ማን ነው? ሥራውን የሚያከናውነው ከጥበብ በመነጨ ገርነት መሆኑን በመልካም ምግባሩ ያሳይ። 14 ሆኖም በልባችሁ ውስጥ መራራ ቅናትና ጠበኝነት ካለ አትኩራሩ፤ እንዲሁም በእውነት ላይ አትዋሹ። 15 ይህ ከሰማይ የሚመጣ ጥበብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምድራዊ፣ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው። 16 ቅናትና ጠበኝነት ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገሮችም ይኖራሉ። 17 ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው። 18 ከዚህም በላይ የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ይዘራል።
ከጥቅምት 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ጴጥሮስ 1-2
“ቅዱሳን ሁኑ”
(1 ጴጥሮስ 1:14, 15) ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን አቁሙ፤ 15 ከዚህ ይልቅ የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤
ቤዛው—ከአባታችን የተገኘ “ፍጹም ገጸ በረከት”
5 እኛስ የይሖዋን ስም እንደምንወድ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በአኗኗራችን ይህን ማሳየት እንችላለን። ይሖዋ ቅዱስ እንድንሆን ይጠብቅብናል። (1 ጴጥሮስ 1:15, 16ን አንብብ።) ይህም ሲባል እሱን ብቻ እንድናመልክና በሙሉ ልባችን እንድንታዘዘው ይፈልጋል ማለት ነው። ስደት ቢደርስብንም እንኳ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶችና ሕጎች ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። የይሖዋን መመሪያዎች በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ በማዋል ብርሃናችን በሰው ፊት እንዲበራ እናደርጋለን፤ ይህ ደግሞ ለይሖዋ ስም ክብር ያመጣል። (ማቴ. 5:14-16) የአምላክ ቅዱስ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን፣ የይሖዋ ሕጎች ትክክለኛ መሆናቸውንና የሰይጣን ክስ ሐሰት መሆኑን በአኗኗራችን እናሳያለን። እርግጥ ነው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ስህተት መሥራታችን አይቀርም፤ በዚህ ጊዜ ከልባችን ንስሐ በመግባት ይሖዋን ከሚያስነቅፉ ድርጊቶች እንርቃለን።—መዝ. 79:9
(1 ጴጥሮስ 1:16) “እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፏልና።
ጥሩ መዝናኛ መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ “እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብሎናል። (1 ጴጥሮስ 1:14-16፤ 2 ጴጥሮስ 3:11) ይሖዋ ለእሱ የምናቀርበውን አምልኮ የሚቀበለው አምልኳችን ቅዱስ ወይም ንጹሕ ከሆነ ብቻ ነው። (ዘዳግም 15:21) እንደ ሥነ ምግባር ብልግና፣ ዓመፅ ወይም አጋንንታዊ ድርጊቶች ያሉ ይሖዋ የሚጠላቸው ነገሮችን የምንፈጽም ከሆነ አምልኳችን ንጹሕ እንደማይሆን የታወቀ ነው። (ሮም 6:12-14፤ 8:13) እንዲህ ያሉ ነገሮች በሚንጸባረቁበት መዝናኛ የምንካፈል ከሆነም ይሖዋ ያዝንብናል። እንደዚህ ባለው መዝናኛ መካፈል አምልኳችን ንጹሕ እንዳይሆንና በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኝ ያደርጋል፤ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድናም ያበላሽብናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ጴጥሮስ 1:10-12) ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ የተነበዩት ነቢያት ይህን መዳን በተመለከተ ትጋት የተሞላበት ምርምርና ጥልቅ ጥናት አካሂደዋል። 11 በውስጣቸው ያለው መንፈስ በክርስቶስ ላይ ስለሚደርሱት መከራዎችና ከዚያ በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ ሲመሠክር ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ስለ የትኛው ጊዜ ወይም ወቅት እያመለከተ እንዳለ ይመረምሩ ነበር። 12 እነሱ ራሳቸውን እያገለገሉ እንዳልሆነ ተገልጦላቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ምሥራቹን ባበሰሩላችሁ ሰዎች አማካኝነት ከተነገሯችሁ ነገሮች ጋር በተያያዘ እናንተን እያገለገሉ ነበር። መላእክትም እነዚህን ነገሮች ለማየት ይጓጓሉ።
የያዕቆብና የጴጥሮስ ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
1:10-12፦ መላእክት የጥንቶቹ የአምላክ ነቢያት ስለ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ የጻፏቸውን ጥልቀት ያላቸው መንፈሳዊ እውነቶች በቅርበት ለማየትና ለመረዳት ይመኙ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ግልጽ የሆኑት ይሖዋ ከጉባኤው ጋር ግንኙነት ከመሠረተ በኋላ ነው። (ኤፌ. 3:10) እኛስ የመላእክትን ምሳሌ በመከተል “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” ለመመርመር ጥረት ማድረግ አይኖርብንም?—1 ቆሮ. 2:10
(1 ጴጥሮስ 2:25) እናንተ እንደባዘኑ በጎች ነበራችሁና፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።
it-2 565 አን. 3
የበላይ ተመልካች
ከሁሉ የላቀው የበላይ ተመልካች። አንደኛ ጴጥሮስ 2:25 “እንደባዘኑ በጎች” ስለሆኑ ሰዎች ሲናገር ኢሳይያስ 53:6ን መጥቀሱ ሳይሆን አይቀርም፤ አክሎም ጴጥሮስ “አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ [የበላይ ተመልካች፣ ግርጌ] ተመልሳችኋል” ብሏል። ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ይሖዋ አምላክ መሆን አለበት። ምክንያቱም ጴጥሮስ የጻፈላቸው ሰዎች ከክርስቶስ ኢየሱስ ርቀው አልባዘኑም፤ ከዚህ ይልቅ የሕዝቡ ታላቅ እረኛ ወደሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት ተመልሰዋል። (መዝ 23:1፤ 80:1፤ ኤር 23:3፤ ሕዝ 34:12) በተጨማሪም ይሖዋ የበላይ ተመልካች ነው፤ በሕዝቦቹ ላይ ምርመራ ያደርጋል። (መዝ 17:3) ይህ ምርመራ (ግሪ. ኤፒስኮፔ) ከባድ የፍርድ እርምጃ ሊያስከትል ይችላል፤ ለምሳሌ በእሷ ላይ “ምርመራ [ግሪ. ኤፒስኮፔስ] የተካሄደበትን” ጊዜ ያልተገነዘበችው ኢየሩሳሌም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንዲህ ያለ ዕጣ ደርሶባታል። (ሉቃስ 19:44) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ የሚያደርገው ምርመራ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል፤ ለምሳሌ “አምላክ ለመመርመር [ግሪ. ኤፒስኮፔስ] በሚመጣበት ቀን” እሱን የሚያከብሩ ሰዎች እንዲህ በማድረጋቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ።—1ጴጥ 2:12
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(1 ጴጥሮስ 1:1-16) የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጴጥሮስ፤ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢቲኒያ ተበትነው ለሚገኙ፣ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ለሆኑ የአምላክ ምርጦች፣ 2 ይኸውም አባት የሆነው አምላክ አስቀድሞ ባወቀው መሠረት ለተመረጡት ደግሞም ታዛዥ እንዲሆኑና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንዲረጩ በመንፈስ ለተቀደሱት፦ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 3 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤ እሱ በታላቅ ምሕረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ወልዶናልና፤ 4 እንዲሁም ለማይበሰብስ፣ ለማይረክስና ለማይጠፋ ርስት ወልዶናል። ይህም በሰማይ ለእናንተ ተጠብቆላችኋል፤ 5 እናንተንም አምላክ በዘመኑ መጨረሻ ለሚገለጠው መዳን በእምነት አማካኝነት በኃይሉ እየጠበቃችሁ ነው። 6 አሁን ለአጭር ጊዜ በልዩ ልዩ ፈተናዎች መጨነቃችሁ የግድ ቢሆንም በእነዚህ ሁሉ ነገሮች የተነሳ እጅግ እየተደሰታችሁ ነው፤ 7 እነዚህ ፈተናዎች የሚደርሱባችሁ፣ በእሳት የተፈተነ ቢሆንም እንኳ ሊጠፋ ከሚችለው ወርቅ እጅግ የላቀ ዋጋ ያለውና ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ግርማንና ክብርን ያስገኝ ዘንድ ነው። 8 እሱን አይታችሁት ባታውቁም ትወዱታላችሁ። አሁን ባታዩትም እንኳ በእሱ ላይ እምነት እያሳያችሁና በቃላት ሊገለጽ በማይችል ታላቅ ደስታ እጅግ ሐሴት እያደረጋችሁ ነው፤ 9 ምክንያቱም የእምነታችሁ ግብ ላይ እንደምትደርሱ ይኸውም ራሳችሁን እንደምታድኑ ታውቃላችሁ። 10 ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ የተነበዩት ነቢያት ይህን መዳን በተመለከተ ትጋት የተሞላበት ምርምርና ጥልቅ ጥናት አካሂደዋል። 11 በውስጣቸው ያለው መንፈስ በክርስቶስ ላይ ስለሚደርሱት መከራዎችና ከዚያ በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ ሲመሠክር ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ስለ የትኛው ጊዜ ወይም ወቅት እያመለከተ እንዳለ ይመረምሩ ነበር። 12 እነሱ ራሳቸውን እያገለገሉ እንዳልሆነ ተገልጦላቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ምሥራቹን ባበሰሩላችሁ ሰዎች አማካኝነት ከተነገሯችሁ ነገሮች ጋር በተያያዘ እናንተን እያገለገሉ ነበር። መላእክትም እነዚህን ነገሮች ለማየት ይጓጓሉ። 13 በመሆኑም አእምሯችሁን ዝግጁ በማድረግ ለሥራ ታጠቁ፤ የማስተዋል ስሜታችሁን በሚገባ ጠብቁ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በምታገኙት ጸጋ ላይ አድርጉ። 14 ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን አቁሙ፤ 15 ከዚህ ይልቅ የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ 16 “እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፏልና።
ከጥቅምት 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ጴጥሮስ 3-5
“የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል”
(1 ጴጥሮስ 4:7) ሆኖም የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል። ስለዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ፤ እንዲሁም በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ።
“በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ”
የሌሊት ፈረቃ ሠራተኛ የነበረ አንድ ሰው “ከሌሊቱ ክፍለ ጊዜ በእንቅልፍ ሳይሸነፉ በንቃት ለማሳለፍ እጅግ የሚከብደው ጎህ ከመቅደዱ በፊት ያለው ሰዓት ነው” ሲል ተናግሯል። ሌሊቱን ሙሉ ምንም ሳይተኙ ለማሳለፍ የሚገደዱ ሌሎች ሰዎችም በዚህ ሐሳብ መስማማታቸው አይቀርም። ይህ ሁኔታ እኛ ከምንኖርበት ዘመን ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አሁን የምንገኘው የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ማብቂያ በተቃረበበት ወቅት ላይ ነው። ይህ ሥርዓት በታሪክ ዘመን በሙሉ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ በከፍተኛ ጨለማ ተውጧል፤ በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ንቁ ሆነው ለመኖር ከፍተኛ ትግል ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። (ሮም 13:12) በዚህ የመጨረሻ ሰዓት ላይ በእንቅልፍ ብንሸነፍ የሚደርስብን አደጋ ምንኛ አስከፊ ይሆናል! “ጤናማ አስተሳሰብ” መያዛችንና “በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረጋችን ወሳኝ ነገር ነው።—1 ጴጥ. 4:7
(1 ጴጥሮስ 4:8) ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።
ማንኛውንም መንፈሳዊ ድካም ማወቅና ማሸነፍ የሚቻልበት መንገድ
በመጨረሻም የሐዋርያው ጴጥሮስን ፍቅራዊ ምክር ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም፦ “የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፣ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።” (1 ጴጥሮስ 4:7, 8) የሌሎች ሰዎችም ሆነ የራሳችን ሰብዓዊ አለፍጽምና ልባችንና አእምሯችን ውስጥ ሰርጎ በመግባት እንቅፋት ወይም የመሰናከያ ድንጋይ እንዲሆንብን መፍቀዱ በጣም ቀላል ነው። ሰይጣን ይህን ሰብዓዊ ድካም አሳምሮ ያውቃል። ከፋፍለህ ግዛ የሚለው መርኅ ከሚጠቀምባቸው መሰሪ ዘዴዎች አንዱ ነው። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ኃጢአቶችን አንዳችን ለሌላው ባለን የጠበቀ ፍቅር ለመሸፈን ፈጣን መሆንና ‘ለዲያብሎስ ፈንታ ከመስጠት’ መራቅ አለብን።—ኤፌሶን 4:25-27
(1 ጴጥሮስ 4:9) ሳታጉረመርሙ አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ።
እንግዳ ተቀባይነት—በጣም አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ!
2 ጴጥሮስ ለእነዚያ ክርስቲያኖች ከሰጣቸው ማበረታቻዎች መካከል “አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ” የሚል ሐሳብ ይገኝበታል። (1 ጴጥ. 4:9) “እንግዳ ተቀባይነት” የሚለው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ለእንግዶች ፍቅር ወይም ደግነት ማሳየት” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ሆኖም ጴጥሮስ፣ ክርስቲያን ወንድሞቹንና እህቶቹን ያበረታታቸው ‘አንዳቸው ሌላውን’ በእንግድነት እንዲቀበሉ በሌላ አባባል በደንብ የሚያውቋቸውንና የሚቀርቧቸውን ሰዎች እንዲያስተናግዱ መሆኑን ልብ እንበል። የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየታቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
3 እርስ በርስ ያቀራርባቸዋል። አንተስ በግልህ ይህን አልተመለከትክም? ሌሎች ቤታቸው በእንግድነት ጋብዘውህ ያውቃሉ? በዚያ ወቅት ምን ያህል አስደሳች ጊዜ እንዳሳለፋችሁ ታስታውሳለህ? በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የጉባኤህን አባላት አንተ ስትጋብዛቸው ወዳጅነታችሁ አልተጠናከረም? ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በእንግድነት ስንቀበል እነሱን በቅርበት ለማወቅ የተሻለ አጋጣሚ እናገኛለን። በጴጥሮስ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ሁኔታዎች እየተባባሱ ሲሄዱ ይበልጥ መቀራረብ ያስፈልጋቸው ነበር። በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ከሚኖሩ ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—2 ጢሞ. 3:1
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ጴጥሮስ 3:19, 20) በዚህ ሁኔታ እያለም ሄዶ በእስር ላሉት መናፍስት ሰበከላቸው፤ 20 እነዚህ መናፍስት ቀደም ሲል ማለትም በኖኅ ዘመን ጥቂት ሰዎች ይኸውም ስምንት ነፍሳት በውኃው መካከል አልፈው የዳኑበት መርከብ እየተሠራ በነበረበት ጊዜ፣ አምላክ በትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ ሳይታዘዙ የቀሩ ናቸው።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ኢየሱስ “በእስር ላሉት መናፍስት ሰበከላቸው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ጴጥ. 3:19) ይህ ምን ማለት ነው?
▪ ሐዋርያው ጴጥሮስ “እነዚህ መናፍስት በኖኅ ዘመን . . . አምላክ በትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ ሳይታዘዙ የቀሩ ናቸው” በማለት ተናግሯል። (1 ጴጥ. 3:20) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጴጥሮስ እዚህ ላይ የተናገረው በአምላክ ላይ በማመፅ ከሰይጣን ጋር ስለተባበሩት መንፈሳዊ ፍጥረታት ወይም መላእክት ነው። ይሁዳ እንደተናገረው “መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ ያልጠበቁትንና ትክክለኛ መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት” አምላክ “በታላቁ ቀን ለሚፈጸምባቸው ፍርድ በዘላለም እስራት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አቆይቷቸዋል።”—ይሁዳ 6
በኖኅ ዘመን መንፈሳዊ ፍጥረታት ሳይታዘዙ የቀሩት እንዴት ነበር? ከጥፋት ውኃ በፊት እነዚህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ሥጋዊ አካል ለብሰው ምድር ላይ መኖር ጀምረው ነበር፤ ይህ ድርጊታቸው ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚጋጭ ነው። (ዘፍ. 6:2, 4) ከዚህም በላይ እነዚህ መላእክት ከሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ነገር ነበር። አምላክ መላእክትን ሲፈጥር ከሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ዓላማው አልነበረም። (ዘፍ. 5:2) እነዚህ ታዛዥ ያልሆኑ ክፉ መላእክት አምላክ በወሰነው ጊዜ ይጠፋሉ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ይሁዳ እንደተናገረው “በድቅድቅ ጨለማ” ውስጥ ናቸው፤ በሌላ አባባል በመንፈሳዊ ሁኔታ ወኅኒ ቤት ውስጥ ያሉ ያህል ነው።
ታዲያ ኢየሱስ “በእስር ላሉት መናፍስት” የሰበከላቸው መቼና እንዴት ነው? ጴጥሮስ እንደገለጸው ይህ የሆነው ኢየሱስ “መንፈስ ሆኖ ሕያው” ከሆነ በኋላ ነው። (1 ጴጥ. 3:18, 19) ጴጥሮስ “ሰበከላቸው” እንዳለ ልብ በል። እዚህ ላይ የተጠቀመው ግስ አላፊ ጊዜን የሚያመለክት መሆኑ ኢየሱስ የሰበከው ጴጥሮስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን ከመጻፉ በፊት እንደሆነ ይጠቁማል። ከዚህ አንጻር ኢየሱስ ለእነዚህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን የሰበከላቸው ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ይመስላል፤ ክርስቶስ ያወጀው መላእክቱ የተወሰነላቸውን ተገቢ የቅጣት ፍርድ ነው። የሰበከው መልእክት ተስፋ የሚሰጥ ሳይሆን ስለሚጠብቃቸው ፍርድ የሚገልጽ ነበር። (ዮናስ 1:1, 2) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን ትንሣኤ ማግኘቱ ዲያብሎስ በእሱ ላይ ምንም ኃይል እንደሌለው ያረጋግጣል፤ በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን የፍርድ መልእክት ለማወጅ ብቃት ይኖረዋል።—ዮሐ. 14:30፤ 16:8-11
ወደፊት ኢየሱስ፣ ሰይጣንንና እነዚያን ክፉ መላእክት አስሮ ወደ ጥልቁ ይወረውራቸዋል። (ሉቃስ 8:30, 31፤ ራእይ 20:1-3) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን እነዚህ ያልታዘዙ መላእክት ድቅድቅ በሆነ መንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እንዲቆዩ ተወስኖባቸዋል፤ በመጨረሻም መጥፋታቸው አይቀርም።—ራእይ 20:7-10
(1 ጴጥሮስ 4:6) እንዲያውም ምሥራቹ ለሙታንም የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ በመሆኑም ከሰው አመለካከት አንጻር በሥጋ የሚፈረድባቸው ቢሆንም ከአምላክ አመለካከት አንጻር ከመንፈስ ጋር በሚስማማ ሁኔታ መኖር ይችላሉ።
የያዕቆብና የጴጥሮስ ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
4:6—‘ወንጌል የተሰበከላቸው ሙታን’ እነማን ናቸው? እነዚህ ሰዎች ወንጌሉን ከመስማታቸው በፊት ‘በበደላቸውና በኃጢአታቸው ሙታን’ የነበሩ ወይም በመንፈሳዊ ሙት የነበሩ ናቸው። (ኤፌ. 2:1) በምሥራቹ ላይ እምነት ካሳደሩ በኋላ ግን በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘መኖር’ ጀምረዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(1 ጴጥሮስ 3:8-22) በመጨረሻም ሁላችሁም የአስተሳሰብ አንድነት ይኑራችሁ፤ የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ፤ የወንድማማች መዋደድ ይኑራችሁ፤ ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ ትሑታን ሁኑ። 9 ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ። ከዚህ ይልቅ ባርኩ፤ የተጠራችሁት ይህን ጎዳና በመከተል በረከትን እንድትወርሱ ነውና። 10 ስለዚህ “ሕይወትን የሚወድና መልካም ቀኖችን ማየት የሚፈልግ ሰው በምላሱ ክፉ ነገር ከመናገር፣ በከንፈሩም ከማታለል ይቆጠብ። 11 ክፉ ከሆነ ነገር ይራቅ፤ መልካም የሆነውንም ያድርግ፤ ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተለውም። 12 የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ ጆሮዎቹም ምልጃቸውን ይሰማሉ፤ የይሖዋ ፊት ግን ክፉ ነገሮችን በሚያደርጉ ላይ ነው።” 13 መልካም ነገር ለማድረግ ቀናተኞች ብትሆኑ ጉዳት የሚያደርስባችሁ ማን ነው? 14 ሆኖም ለጽድቅ ስትሉ መከራ ብትቀበሉ ደስተኞች ናችሁ። ይሁን እንጂ እነሱ የሚፈሩትን እናንተ አትፍሩ፤ ደግሞም አትሸበሩ። 15 ነገር ግን ክርስቶስን እንደ ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ሁኑ፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን። 16 ስለ እናንተ መጥፎ ነገር የሚናገሩ ሰዎች፣ የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችሁ መጠን በምታሳዩት መልካም ምግባር የተነሳ ስለ እናንተ በሚናገሩት በማንኛውም መጥፎ ነገር እንዲያፍሩ ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ። 17 ክፉ ነገር ሠርታችሁ መከራ ከምትቀበሉ ይልቅ የአምላክ ፈቃድ ከሆነ፣ መልካም ነገር ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉ ይሻላልና። 18 ጻድቅ የሆነው ክርስቶስ እንኳ ለዓመፀኞች ሲል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመሞት ከኃጢአት ነፃ አውጥቷቸዋልና። ይህን ያደረገው እናንተን ወደ አምላክ ለመምራት ነው። ሥጋ ሆኖ ተገደለ፤ ሆኖም መንፈስ ሆኖ ሕያው ሆነ። 19 በዚህ ሁኔታ እያለም ሄዶ በእስር ላሉት መናፍስት ሰበከላቸው፤ 20 እነዚህ መናፍስት ቀደም ሲል ማለትም በኖኅ ዘመን ጥቂት ሰዎች ይኸውም ስምንት ነፍሳት በውኃው መካከል አልፈው የዳኑበት መርከብ እየተሠራ በነበረበት ጊዜ፣ አምላክ በትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ ሳይታዘዙ የቀሩ ናቸው። 21 አሁንም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት እናንተን እያዳናችሁ ነው። ጥምቀት የሰውነትን እድፍ የሚያስወግድ ሳይሆን ጥሩ ሕሊና ለማግኘት ለአምላክ የሚቀርብ ልመና ነው። 22 ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደ ሲሆን አሁን በአምላክ ቀኝ ይገኛል፤ እንዲሁም መላእክት፣ ሥልጣናትና ኃይላት እንዲገዙለት ተደርጓል።
ከጥቅምት 28–ኅዳር 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ጴጥሮስ 1-3
“የይሖዋን ቀን መምጣት በአእምሯችሁ አቅርባችሁ ተመልከቱ”
(2 ጴጥሮስ 3:9, 10) አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤ ከዚህ ይልቅ እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው። 10 ይሁንና የይሖዋ ቀን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በነጎድጓድ ድምፅ ያልፋሉ፤ ንጥረ ነገሮቹም በኃይለኛ ሙቀት ይቀልጣሉ፤ ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ።
ይሖዋ ‘ይፈርዳል’
11 ይሁንና ይሖዋ “ፈጥኖ” እንደሚፈርድልን የሰጠውን ማረጋገጫ መረዳት ያለብን እንዴት ነው? የአምላክ ቃል፣ ይሖዋ ‘የሚታገሥ’ ቢሆንም በተገቢው ጊዜ ፈጥኖ የፍርድ እርምጃ እንደሚወስድ ያመለክታል። (ሉቃስ 18:7, 8 የ1954 ትርጉም፤ 2 ጴጥሮስ 3:9, 10) በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ በመጣ ጊዜ ክፉዎች ወዲያውኑ ጠፍተዋል። በሎጥ ዘመንም እንዲሁ እሳት ከሰማይ ሲዘንብ ክፉዎች ከሕልውና ውጭ ሆነዋል። ኢየሱስ “የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንደዚሁ ይሆናል” ብሏል። (ሉቃስ 17:27-30) በክፉዎች ላይ “ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል።” (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3) በእርግጥም ይሖዋ የሰይጣንን ዓለም ፍትሑ ከሚፈቅደው ውጭ አንድ ተጨማሪ ቀን እንኳ እንዲቆይ እንደማያደርግ ልንተማመን እንችላለን።
(2 ጴጥሮስ 3:11, 12) እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀልጡ ከሆነ ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል! 12 ሰማያት በእሳት ተቃጥለው የሚጠፉበትንና ንጥረ ነገሮቹም በኃይለኛ ሙቀት የሚቀልጡበትን የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል!
‘ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል’
18 ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘የይሖዋን ቀን መምጣት’ አቅርበን እንድንመለከት ማሳሰቡ አያስገርምም! ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ “በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት” በመኖር ነው። (2 ጴጥሮስ 3:11, 12) መንፈሳዊነታችንን ሊያጎለብቱ በሚችሉ እንቅስቃሴዎች መጠመዳችን ‘የይሖዋን ቀን’ በጉጉት እንድንጠባበቅ ይረዳናል። የይሖዋ ቀን እስከሚደርስ ድረስ ያሉትን ቀናት በቶሎ ልናሳልፋቸው ወይም ልናፋጥናቸው እንደማንችል እሙን ነው። ሆኖም በአምላክ አገልግሎት ከተጠመድን ጊዜው ሳናስበው በፍጥነት ሊያልፍና የምንጠባበቀው ቀን ሊደርስ ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:58
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(2 ጴጥሮስ 1:19) በመሆኑም ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ጎህ እስኪቀድና የንጋት ኮከብ እስኪወጣ ድረስ በጨለማ ቦታ፣ በልባችሁ ውስጥ ለሚበራ መብራት የምትጠነቀቁትን ያህል ለትንቢታዊው ቃል ትኩረት መስጠታችሁ መልካም ነው።
የያዕቆብና የጴጥሮስ ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
1:19—“የንጋት ኮከብ” ማን ነው? ይህ ኮከብ የወጣው መቼ ነው? ይህ ሁኔታ መከሰቱንስ የምናውቀው እንዴት ነው? “የንጋት ኮከብ” የተባለው ንጉሣዊ ሥልጣኑን የያዘው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ራእይ 22:16) ኢየሱስ በ1914 በፍጥረት ሁሉ ፊት መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ በመውጣት አዲስ ቀን መጥባቱን አስታውቋል። ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ መለወጡ ወደፊት የሚያገኘውን ክብርና መንግሥታዊ ሥልጣን በራእይ መልክ ለማየት ያስቻለ ሲሆን የአምላክ ትንቢታዊ ቃል አስተማማኝ መሆኑንም አረጋግጧል። ለዚህ ቃል ትኩረት መስጠታችን በልባችን ውስጥ ብርሃን እንዲፈነጥቅ የሚያደርግ ሲሆን በዚህ መንገድም የንጋት ኮከብ መውጣቱን እንገነዘባለን።
(2 ጴጥሮስ 2:4) ደግሞም አምላክ ኃጢአት የሠሩትን መላእክት ከመቅጣት ወደኋላ አላለም፤ ይልቁንም በድቅድቅ ጨለማ አስሮ በማስቀመጥ ፍርዳቸውን እንዲጠባበቁ ወደ እንጦሮጦስ ጣላቸው።
የያዕቆብና የጴጥሮስ ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
2:4 NW—“እንጦሮጦስ” ምንድን ነው? ዓመፀኞቹ መላእክት ወደዚያ የተጣሉትስ መቼ ነበር? እንጦሮጦስ ሰብዓዊ ፍጥረታት ሳይሆኑ መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚቆዩበትን እንደ እሥር ቤት ያለ ሁኔታ ያመለክታል። የአምላክን ብሩህ ዓላማ በተመለከተ አእምሯቸው በጨለማ መዋጡን ያሳያል። በእንጦሮጦስ ያሉ ሁሉ ምንም ዓይነት የወደፊት ተስፋ የላቸውም። አምላክ ታዛዥ ያልሆኑትን መላእክት ወደ እንጦሮጦስ የጣላቸው በኖኅ ዘመን ሲሆን እስከሚጠፉበት ጊዜ ድረስም በዚህ ሁኔታ እንደተዋረዱ ይቆያሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(2 ጴጥሮስ 1:1-15) የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ ከሆነው ከስምዖን ጴጥሮስ፣ በአምላካችን ጽድቅ እንዲሁም በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ አማካኝነት እኛ ያገኘነውን ዓይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉ፦ 2 ስለ አምላክና ስለ ጌታችን ኢየሱስ በምትቀስሙት ትክክለኛ እውቀት አማካኝነት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 3 መለኮታዊ ኃይሉ፣ በገዛ ክብሩና በጎነቱ ስለጠራን አምላክ ባገኘነው ትክክለኛ እውቀት ለአምላክ ያደርን ሆነን ለመኖር የሚረዱንን ነገሮች ሁሉ ሰጥቶናል። 4 በእነዚህ ነገሮች አማካኝነት ክቡርና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋ ሰጥቶናል፤ ይህን ያደረገውም የመጥፎ ምኞት ውጤት ከሆነው ከዓለም ብልሹ ምግባር አምልጣችሁ፣ በዚህ ተስፋ አማካኝነት ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ ነው። 5 በመሆኑም ልባዊ ጥረት በማድረግ በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ጨምሩ፤ በበጎነት ላይ እውቀትን፣ 6 በእውቀት ላይ ራስን መግዛትን፣ ራስን በመግዛት ላይ ጽናትን፣ በጽናት ላይ ለአምላክ ማደርን፣ 7 ለአምላክ በማደር ላይ ወንድማዊ መዋደድን፣ በወንድማዊ መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ። 8 እነዚህ ነገሮች በውስጣችሁ ቢኖሩና ቢትረፈረፉ፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን ትክክለኛ እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ይጠብቋችኋል። 9 እነዚህ ነገሮች የሚጎድሉት ማንኛውም ሰው ብርሃን ላለማየት ዓይኑን የጨፈነ ዕውር ሰው ነው፤ ደግሞም ከቀድሞ ኃጢአቱ መንጻቱን ረስቷል። 10 በመሆኑም ወንድሞች፣ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን አስተማማኝ ለማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ ትጉ፤ እነዚህን ነገሮች የምታደርጉ ከሆነ ፈጽሞ አትወድቁምና። 11 እንዲያውም በእጅጉ ትባረካላችሁ፤ ጌታችንና አዳኛችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥትም ትገባላችሁ። 12 ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች የምታውቁና በተማራችሁት እውነት ጸንታችሁ የቆማችሁ ብትሆኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች ሁልጊዜ እናንተን ከማሳሰብ ወደኋላ አልልም። 13 በዚህ ድንኳን እስካለሁ ድረስ እናንተን በማሳሰብ ማነቃቃት ተገቢ ይመስለኛል፤ 14 ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ እንዳሳወቀኝ ይህ ድንኳን የሚወገድበት ጊዜ እንደቀረበ አውቃለሁ። 15 እኔ ከሄድኩ በኋላ እነዚህን ነገሮች ማስታወስ እንድትችሉ ሁልጊዜ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ።