የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2023 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከግንቦት 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ዜና መዋዕል 17–19
“ለሌሎች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ይኑራችሁ”
አስቀድሞ ለተጻፉት ነገሮች ትኩረት ትሰጣላችሁ?
7 የአሳ ልጅ ስለሆነው ስለ ኢዮሳፍጥስ ምን ማለት ይቻላል? ኢዮሳፍጥ በርካታ ግሩም ባሕርያት ነበሩት። በአምላክ በመታመን ብዙ መልካም ነገሮች አከናውኗል። ይሁን እንጂ ኢዮሳፍጥ ጥበብ የጎደላቸው ውሳኔዎችም አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰሜናዊውን መንግሥት ያስተዳድር ከነበረው ከክፉው ንጉሥ ከአክዓብ ጋር በጋብቻ ተዛምዷል። ከዚህም ሌላ ነቢዩ ሚካያህ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት ከአክዓብ ጎን ተሰልፎ በሶርያውያን ላይ ዘምቷል። በውጊያው ላይ ኢዮሳፍጥ ከሞት የተረፈው ለጥቂት ነው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። (2 ዜና 18:1-32) በዚያ ወቅት ነቢዩ ኢዩ “ለክፉ ሰው እርዳታ መስጠት ይገባሃል? ይሖዋን የሚጠሉትንስ መውደድ ይገባሃል?” ሲል ጠይቆታል።—2 ዜና መዋዕል 19:1-3ን አንብብ።
በይሖዋ ጽኑ ፍቅር ላይ አሰላስሉ
8 ይሖዋ፣ የሚወደንና ከጉድለታችን ባሻገር የሚመለከት አምላክ እንደሆነ እንድገነዘብ ይፈልጋል። በእኛ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ለማግኘት ይጥራል። (2 ዜና 16:9) ለምሳሌ ያህል፣ ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮሳፍጥ ጋር በተያያዘ ይህን አድርጓል። በአንድ ወቅት የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ፣ ራሞትጊልያድን ከሶርያውያን ለማስመለስ ባደረገው ዘመቻ አብሮት እንዲሄድ ለኢዮሳፍጥ ጥያቄ አቀረበለት፤ እሱም ተስማማ። ይህ ግን ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ነበር። ምንም እንኳ 400 የሚያህሉ የሐሰት ነቢያት ክፉው አክዓብ ድል እንደሚያደርግ ቢናገሩም አክዓብ መሸነፉ እንደማይቀር እውነተኛው የይሖዋ ነቢይ ሚካያህ ተንብዮ ነበር። አክዓብ በጦርነቱ የሞተ ሲሆን ኢዮሳፍጥም ሕይወቱ የተረፈው ለጥቂት ነው። ኢዮሳፍጥ ከአክዓብ ጋር ጥምረት በመፍጠሩ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ተግሣጽ ተሰጥቶታል። ያም ሆኖ ባለ ራእዩ የሃናኒ ልጅ ኢዩ፣ ኢዮሳፍጥን “መልካም ነገር ተገኝቶብሃል” ብሎታል።—2 ዜና 18:4, 5, 18-22, 33, 34፤ 19:1-3
9 ኢዮሳፍጥ በሥልጣን ዘመኑ መጀመሪያ ላይ መኳንንት፣ ሌዋውያንና ካህናት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ እየተዘዋወሩ የይሖዋን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምሩ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር። ዘመቻው በጣም ውጤታማ በመሆኑ በይሁዳ ዙሪያ የነበሩ ብሔራት ይሖዋን መፍራት ጀመሩ። (2 ዜና 17:3-10) በእርግጥ ኢዮሳፍጥ የሞኝነት ድርጊት ፈጽሟል፤ ሆኖም ቀደም ሲል ያከናወናቸውን መልካም ነገሮች ይሖዋ አልረሳም። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፣ ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ይሖዋን ለማስደሰት በሙሉ ልባችን የምንጥር ከሆነ እሱም ለእኛ ጽኑ ፍቅር እንደሚኖረው ያስታውሰናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ይሖዋን በሙሉ ልብ አገልግሉ!
10 የአሳ ልጅ የሆነው ኢዮሳፍጥ “በአባቱ በአሳ መንገድ [ሄዷል]።” (2 ዜና 20:31, 32) ይህን ያደረገው እንዴት ነው? እንደ አባቱ ሁሉ ኢዮሳፍጥም ሕዝቡ ይሖዋን እንዲፈልግ አበረታቷል። “የይሖዋን ሕግ መጽሐፍ” የሚያስተምሩ ሰዎችን ወደ ይሁዳ ከተሞች ልኳል። (2 ዜና 17:7-10) ከዚህም በላይ ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት በሚያስተዳድረው ክልል ይኸውም በተራራማው የኤፍሬም ምድር የሚኖረውን ሕዝብ እንኳ ‘ወደ ይሖዋ ለመመለስ’ እዚያ ድረስ ሄዷል። (2 ዜና 19:4) በእርግጥም ኢዮሳፍጥ “ይሖዋን በሙሉ ልቡ የፈለገ” ንጉሥ ነበር።—2 ዜና 22:9
11 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ታላቅ የማስተማር ዘመቻ እያካሄደ ሲሆን ሁላችንም በዚህ ሥራ መካፈል እንችላለን። በየወሩ ሌሎችን ስለ አምላክ ቃል በማስተማር ይሖዋን ለማገልገል እንዲነሳሱ የመርዳት ግብ አለህ? አንተ በምታደርገው ጥረት ላይ የይሖዋ በረከት ታክሎበት ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ትችል ይሆናል። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ወደ ይሖዋ ትጸልያለህ? ከራስህ ጊዜ ላይ የተወሰነውን መሥዋዕት አድርገህም እንኳ ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ፈቃደኛ ነህ? ኢዮሳፍጥ፣ ሕዝቡን ወደ እውነተኛው አምልኮ ለመመለስ ወደ ኤፍሬም ክልል እንደሄደ ሁሉ እኛም ከጉባኤ የራቁትን ለመርዳት ጥረት ማድረግ እንችላለን። የጉባኤ ሽማግሌዎች ደግሞ በክልላቸው ውስጥ የሚገኙ የተወገዱ ሰዎችን ለማግኘትና ለመርዳት ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ፤ እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል ይፈጽሙት የነበረውን መጥፎ ድርጊት ትተው ሊሆን ይችላል።
ከግንቦት 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ዜና መዋዕል 20–21
“በአምላካችሁ በይሖዋ እመኑ”
በዚህ አሮጌ ዓለም መጨረሻ አንድነታችንን ማጠናከር
8 በንጉሥ ኢዮሣፍጥ ዘመን፣ በአምላክ ሕዝቦች ዙሪያ የነበሩ ጠላቶች እነሱን ለመውጋት ብርቱ የሆነ “ግዙፍ ሰራዊት” አሰልፈው መጡ። (2 ዜና 20:1, 2) የአምላክ አገልጋዮች ግን ጠላቶቻቸውን በራሳቸው ኃይል ለመመከት አልሞከሩም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን እርዳታ ጠየቁ። (2 ዜና መዋዕል 20:3, 4ን አንብብ።) ይህንን ያደረጉት ደግሞ እያንዳንዳቸው መልካም መስሎ እንደታያቸው ወይም እንዳሰኛቸው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃኖቻቸው ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር” ይላል። (2 ዜና 20:13) ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች በይሖዋ በመታመን የእሱን መመሪያ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል፤ ይሖዋም ከጠላቶቻቸው ታድጓቸዋል። (2 ዜና 20:20-27) ታዲያ ይህ የአምላክ ሕዝቦች በአንድነት ሆነው ፈታኝ ሁኔታዎችን እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ አይደለም?
አዲስ ባለትዳሮች—ሕይወታችሁ ይሖዋን በማገልገል ላይ ያተኮረ ይሁን
7 ይሖዋ ያሃዚኤል በተባለ ሌዋዊ አማካኝነት ኢዮሳፍጥን አነጋገረው። እንዲህ አለው፦ “ቦታ ቦታችሁን ይዛችሁ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚወስደውን የማዳን እርምጃ ተመልከቱ።” (2 ዜና 20:13-17) ይህ ከተለመደው የውጊያ ስልት በጣም የተለየ ነው! ይሁንና ይህ መመሪያ የመጣው ከሰው ሳይሆን ከይሖዋ ነው። ኢዮሳፍጥ በአምላኩ ሙሉ በሙሉ በመታመን የታዘዘውን አደረገ። እሱና ሕዝቡ ጠላቶቻቸውን ለመግጠም ሲወጡ ከፊት ያሰለፈው ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ወታደሮች ሳይሆን ምንም መሣሪያ ያልታጠቁትን ዘማሪዎች ነው። ይሖዋ ኢዮሳፍጥን አላሳፈረውም፤ ጠላቶቹን ድል አድርጎለታል።—2 ዜና 20:18-23
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 1271 አን. 1-2
ኢዮራም
ኢዮራም እንደ አባቱ እንደ ኢዮሳፍጥ የጽድቅን ጎዳና አልተከለም፤ ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት ሚስቱ ጎቶልያ ያሳደረችበት መጥፎ ተጽዕኖ ነው። (2ነገ 8:18) ኢዮራም ስድስት ወንድሞቹንና ከይሁዳ መኳንንት መካከል አንዳንዶቹን የገደለ ከመሆኑም ሌላ ሕዝቡ ይሖዋን በመተው የሐሰት አማልክትን እንዲያመልኩ አደረገ። (2ዜና 21:1-6, 11-14) በመላው ግዛቱ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ችግር አጋጥሞት ነበር። በመጀመሪያ ኤዶም ዓመፀበት፤ ከዚያም ሊብና በይሁዳ ላይ ዓመፀ። (2ነገ 8:20-22) ነቢዩ ኤልያስ ለኢዮራም በላከለት ደብዳቤ ላይ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶት ነበር፦ “ይሖዋ ሕዝብህን፣ ልጆችህን፣ ሚስቶችህንና ንብረትህን ሁሉ በታላቅ መቅሰፍት ይመታል። አንተም የአንጀት በሽታን ጨምሮ በብዙ ሕመም ትሠቃያለህ፤ ከበሽታው የተነሳ አንጀትህ እስኪወጣ ድረስ ሕመሙ ዕለት ተዕለት እየጠናብህ ይሄዳል።”—2ዜና 21:12-15
ትንቢቱ በትክክል ተፈጽሟል። ይሖዋ ዓረቦችና ፍልስጤማውያን በምድሪቱ ላይ እንዲነሱና የኢዮራምን ሚስቶችና ልጆች ማርከው እንዲወስዱ ፈቀደ። አምላክ እንዲተርፍ የፈቀደው የኢዮራም የመጨረሻ ልጅ የሆነው ኢዮዓካዝ (አካዝያስ ተብሎም ይጠራል) ብቻ ነው፤ ሆኖም ይህንንም ቢሆን የፈቀደው ከዳዊት ጋር በገባው የመንግሥት ቃልኪዳን የተነሳ ነው። “ከዚህ ሁሉ በኋላ ይሖዋ [ኢዮራምን] በማይድን የአንጀት በሽታ ቀሰፈው።” ከሁለት ዓመት በኋላ “አንጀቱ ወጣ”፤ በመጨረሻም ሞተ። ይህ ክፉ ሰው “ሲሞት ማንም አላዘነለትም።” “በነገሥታቱ የመቃብር ስፍራ ሳይሆን” በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝያስ በእሱ ምትክ ነገሠ።—2ዜና 21:7, 16-20፤ 22:1፤ 1ዜና 3:10, 11
ከግንቦት 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ዜና መዋዕል 22–24
“ይሖዋ የድፍረት እርምጃን ይባርካል”
ኢዮአስ መጥፎ ጓደኝነት በመመሥረቱ ይሖዋን ተወ
የአምላክ ቤተ መቅደስ በነበረባት በኢየሩሳሌም ከተማ ሁኔታዎች አስጨናቂ የሆኑበት ጊዜ ነበር። ንጉሥ አካዝያስ ከተገደለ ብዙም አልቆየም። የአካዝያስ እናት ጎቶልያ፣ ልጇ ከተገደለ በኋላ ያደረገችው ነገር ለማሰብ እንኳ ይከብዳል። ጎቶልያ የአካዝያስ ልጆች የሆኑትን የልጅ ልጆቿን አስገደለቻቸው! ይህን ያደረገችው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?—በእነሱ ፋንታ እሷ መንገሥ ስለፈለገች ነበር።
ይሁንና ከጎቶልያ የልጅ ልጆች መካከል አንዱ የሆነው ሕፃኑ ኢዮአስ ከሞት ተርፎ ነበር፤ ይህ መሆኑን አያቱም እንኳ አላወቀችም። ኢዮአስ ከሞት የተረፈው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ?— ሕፃኑ፣ ዮሳቤት የምትባል አክስት ነበረችው፤ ይህቺ ሴት ኢዮአስን ወስዳ በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ ደበቀችው። ዮሳቤት ይህንን ማድረግ የቻለችው ባሏ ዮዳሄ ሊቀ ካህናት ስለነበር ነው። እነዚህ ባልና ሚስት ኢዮአስን ጉዳት እንዳይደርስበት ሸሸጉት።
ኢዮአስ መጥፎ ጓደኝነት በመመሥረቱ ይሖዋን ተወ
ኢዮአስ ለስድስት ዓመታት ያህል በቤተ መቅደሱ ውስጥ ተደብቆ ቆየ። እዚያ እያለ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ሕጎቹ ብዙ ነገር ተማረ። ኢዮአስ ሰባት ዓመት ሲሆነው ዮዳሄ እሱን ለማንገሥ አንዳንድ እርምጃዎችን ወሰደ። ዮዳሄ፣ ኢዮአስን ያነገሠው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የኢዮአስ አያት የሆነችው ክፉዋ ንግሥት ጎቶልያ ምን እንደደረሰባት ማወቅ ትፈልጋለህ?—
ዮዳሄ፣ በወቅቱ በኢየሩሳሌም የነበሩ ነገሥታትን የሚጠብቁ ልዩ ዘብ ጠባቂዎችን በሚስጥር ጠራ። ከዚያም እሱና ሚስቱ የንጉሥ አካዝያስን ልጅ በሕፃንነቱ እንዴት እንዳዳኑት ነገራቸው። ቀጥሎም ኢዮአስን ለዘብ ጠባቂዎቹ አሳያቸው፤ እነሱም ንጉሥ መሆን የሚገባው ኢዮአስ መሆኑን ተስማሙ። ስለዚህ ምን እንደሚያደርጉ እቅድ አወጡ።
ዮዳሄ፣ ኢዮአስን ከተደበቀበት አወጣውና ዘውዱን ጫነለት። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ “‘ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ’ እያሉ በማጨብጨብ ደስታቸውን ከፍ ባለ ድምፅ ገለጹ።” ዘብ ጠባቂዎቹ በኢዮአስ ዙሪያ በመሆን አደጋ እንዳይደርስበት ይጠብቁት ነበር። ጎቶልያ ይህንን የደስታ ጩኸት ስትሰማ ካለችበት ሮጣ በመምጣት ተቃውሞዋን አሰማች። ይሁንና ዮዳሄ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ዘብ ጠባቂዎቹ ጎቶልያን ገደሏት።—2 ነገሥት 11:1-16
it-1 379 አን. 5
ቀብር፣ የመቃብር ቦታ
ጻድቅ የነበረው ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ “በዳዊት ከተማ ከነገሥታት ጋር” የመቀበር ክብር አግኝቷል፤ እንዲህ ያለ ክብር እንደተሰጠው የተገለጸው ከንጉሣዊ ቤተሰብ ያልሆነ ሰው እሱ ብቻ ነው።—2ዜና 24:15, 16
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 1223 አን. 13
ዘካርያስ
12. የሊቀ ካህናቱ የዮዳሄ ልጅ። ዮዳሄ ከሞተ በኋላ ንጉሥ ኢዮዓስ የይሖዋን ነቢያት ከመስማት ይልቅ ሌሎች የሰጡትን መጥፎ ምክር በመከተሉ ከእውነተኛው አምልኮ ዞር አለ። የኢዮዓስ አክስት ልጅ የነበረው ዘካርያስ (2ዜና 22:11) ስለዚህ ጉዳይ ሕዝቡን አስጠነቀቀ፤ እነሱ ግን ንስሐ ከመግባት ይልቅ በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት። ዘካርያስ ሊሞት ሲል “ይሖዋ ይየው፤ የእጅህንም ይስጥህ” ብሎ ነበር። ይህ እርግማን ደርሷል፤ ሶርያ በይሁዳ ላይ ከባድ ጉዳት ከማድረሷ በተጨማሪ ኢዮዓስ “የካህኑን የዮዳሄን ልጆች ደም በማፍሰሱ” በሁለት አገልጋዮቹ ተገደለ። የግሪክኛው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም እና የላቲኑ ቩልጌት ኢዮዓስ የተገደለው የዮዳሄን “ልጅ” ደም በማፍሰሱ የተነሳ እንደሆነ ይገልጻሉ። ሆኖም የማሶሬቶች ጽሑፍና ሲሪያክ ፐሺታ “ልጆች” የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ፤ እዚህ ላይ ብዙ ቁጥር የተጠቀሙት ነቢይና ካህን የነበረው የዮዳሄ ልጅ ዘካርያስ ያለውን የላቀ ቦታና ክብር ለማመልከት ሊሆን ይችላል።—2ዜና 24:17-22, 25
ከግንቦት 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ዜና መዋዕል 25–27
“ይሖዋ ከዚህ እጅግ የሚበልጥ ሊሰጥህ ይችላል”
it-1 1266 አን. 6
ኢዮዓስ
በተጨማሪም ኢዮዓስ ከኤዶማውያን ጋር እንዲዋጉ ከሠራዊቱ መካከል አንድ መቶ ሺህ ወታደሮችን ለይሁዳ ንጉሥ አስቀጥሮ ነበር። ሆኖም አንድ “የእውነተኛው አምላክ ሰው” በሰጠው ምክር የተነሳ እነዚህ ተዋጊዎች ተሰናበቱ፤ ምንም እንኳ እነዚህ ሰዎች አንድ መቶ የብር ታላንት (660,600 የአሜሪካ ዶላር) አስቀድሞ ተከፍሏቸው የነበረ ቢሆንም ወደ ቤታቸው በመሰናበታቸው ተቆጡ፤ ምናልባትም የተበሳጩት ከምርኮው የመካፈል አጋጣሚያቸውን በማጣታቸው ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ወደ ሰሜን ከተመለሱ በኋላ ከሰማርያ (የእንቅስቃሴያቸው ማዕከል ሊሆን ይችላል) ተነስተው እስከ ቤትሆሮን ድረስ ያሉትን በደቡባዊው መንግሥት የሚገኙ ከተሞች ወረሩ።—2ዜና 25:6-10, 13
የይሖዋን ጥሩነት “ቅመሱ”—እንዴት?
16 ለይሖዋ ስትል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ሁን። ይሖዋን ለማስደሰት፣ የምንወደውን ነገር ሁሉ መሥዋዕት ማድረግ አለብን ማለት አይደለም። (መክ. 5:19, 20) ሆኖም የምንወደውን ነገር መሥዋዕት ማድረግ ስለማንፈልግ ብቻ በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ነገር ከማድረግ ወደኋላ ካልን ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ሰው የሠራውን ዓይነት ስህተት ልንፈጽም እንችላለን፤ ይህ ሰው የተመቻቸ ሕይወት ለመምራት ጥረት ሲያደርግ አምላክን ችላ ብሏል። (ሉቃስ 12:16-21ን አንብብ።) ክርስቲያን የተባለ በፈረንሳይ የሚኖር አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ለይሖዋና ለቤተሰቤ ጊዜዬንና ጉልበቴን በበቂ መጠን እየሰጠሁ አልነበረም።” ከጊዜ በኋላ ግን እሱና ባለቤቱ አቅኚ ለመሆን ወሰኑ። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ግን ሥራቸውን መልቀቅ ነበረባቸው። ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር በጽዳት ሥራ መካፈል ጀመሩ፤ እንዲሁም በትንሽ ገንዘብ ረክቶ መኖርን ተማሩ። ታዲያ ይህን መሥዋዕት በመክፈላቸው ተክሰዋል? ክርስቲያን እንዲህ ብሏል፦ “አሁን አገልግሎታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው ሆኗል። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እና ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግላቸው ሰዎች ስለ ይሖዋ ሲማሩ በማየት እንደሰታለን።”
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በመንፈሳዊ የሚረዳህ ጥሩ አማካሪ አለህ?
ዖዝያን የ16 ዓመት ወጣት ሳለ በደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ላይ ንጉሥ እንዲሆን የተሾመ ሲሆን ከ829 እስከ 778 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድረስ ማለትም ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ገዝቷል። ይህ ንጉሥ ገና ከወጣትነት ዕድሜው አንስቶ ‘በአምላክ ፊት ቅን የሆነውን ነገር ያደርግ’ ነበር። ዖዝያን ቅን መንገድ እንዲከተል ተጽዕኖ ያሳደረበት ማን ነበር? የታሪክ ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “[ዖዝያን] እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።”—2 ዜና መዋዕል 26:1, 4, 5
የንጉሡ አማካሪ ስለነበረው ስለ ዘካርያስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከላይ ከሰፈረው ዘገባ ውጪ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም። ይሁንና ዘካርያስ ለወጣቱ ገዢ ‘አምላክን መፍራት በማስተማር’ ይህ ንጉሥ ትክክል የሆነውን ማድረግ እንዲችል በጎ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። ዚ ኤክስፖዚተርስ ባይብል የተባለው መጽሐፍ ዘካርያስ “የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት ያለው፣ ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ ተሞክሮ ያካበተና እውቀቱን ለሌሎች የማካፈል ችሎታ ያለው ሰው” እንደነበር እሙን ነው በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ዘካርያስን በሚመለከት እንደሚከተለው ብለዋል፦ “ትንቢቶችን ጠንቅቆ የሚያውቅ . . . አስተዋይ፣ ለአምላክ ያደረ እንዲሁም ጥሩ ሰው ነበር፤ ይህም በዖዝያን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረ ይመስላል።”
ከግንቦት 29–ሰኔ 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ዜና መዋዕል 28–29
“አስተዳደጋችሁ ጥሩ ባይሆንም ይሖዋን ማገልገል ትችላላችሁ”
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸውን ምሰሉ
8 ከሩት በተለየ ሁኔታ ወጣቱ ሕዝቅያስ የተወለደው ይሖዋን ለማገልገል በወሰነ ብሔር ውስጥ ነው። ከዚህ ውሳኔ ጋር ተስማምተው የኖሩት ግን ሁሉም እስራኤላውያን አይደሉም። የሕዝቅያስ አባት የሆነውን ንጉሥ አካዝን ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ይህ ክፉ ሰው የይሁዳ ሕዝብ በጣዖት አምልኮ እንዲዘፈቅ ከማድረግም አልፎ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የይሖዋን ቤተ መቅደስ አርክሷል። አካዝ፣ ከሕዝቅያስ ወንድሞች አንዳንዶቹን በሕይወት እያሉ በእሳት በማቃጠል ለሐሰት አምላክ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧቸዋል! በመሆኑም የሕዝቅያስ የልጅነት ሕይወት ምን ያህል ከባድ እንደነበር መገመት አያዳግትም።—2 ነገ. 16:2-4, 10-17፤ 2 ዜና 28:1-3
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸውን ምሰሉ
9 ሕዝቅያስ በምሬትና በቁጣ ሊሞላ ብሎም በአምላክ ላይ ሊያምፅ ይችል ነበር። የዚህን ያህል የከፋ ሁኔታ ያላጋጠማቸው ሰዎች እንኳ ‘በይሖዋ ላይ ለመቆጣት’ ወይም በድርጅቱ ለመማረር የሚያበቃ ምክንያት እንዳላቸው ተሰምቷቸዋል። (ምሳሌ 19:3) አንዳንዶች ደግሞ አስተዳደጋቸው መጥፎ በመሆኑ እነሱም የወላጆቻቸውን ስህተት በመድገም መጥፎ ሕይወት መምራታቸው እንደማይቀር ያስባሉ። (ሕዝ. 18:2, 3) እንዲህ ያሉት አመለካከቶች ትክክል ናቸው?
10 በፍጹም! የሕዝቅያስ ሕይወት ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ይሆናል። በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ሰዎች ለሚደርሱባቸው መጥፎ ነገሮች ተጠያቂው ይሖዋ ስላልሆነ እሱን ለማማረር የሚያበቃ ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም። (ኢዮብ 34:10) እርግጥ ነው ወላጆች፣ በበጎም ይሁን በመጥፎ በልጆቻቸው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። (ምሳሌ 22:6፤ ቆላ. 3:21) ይህ ሲባል ግን አንድ ሰው በሕይወቱ የሚከተለው ጎዳና በአስተዳደጉ ላይ የተመካ ነው ማለት አይደለም። ይሖዋ ለሁላችንም ውድ ስጦታ ይኸውም የመምረጥ ችሎታ ሰጥቶናል፤ በመሆኑም ምን ዓይነት አካሄድ መከተል ወይም ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደምንፈልግ መምረጥ እንችላለን። (ዘዳ. 30:19) ሕዝቅያስ ይህን ስጦታ የተጠቀመበት እንዴት ነው?
11 ሕዝቅያስ፣ በጣም መጥፎ ከሆኑት የይሁዳ ነገሥታት መካከል የአንዱ ልጅ ቢሆንም በጣም ጥሩ ንጉሥ መሆን ችሏል። (2 ነገሥት 18:5, 6ን አንብብ።) አባቱ መጥፎ ምሳሌ እንደነበረ ባይካድም ሕዝቅያስ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩበትን ሰዎች ምሳሌ ለመከተል መርጧል። በወቅቱ ኢሳይያስ፣ ሚክያስና ሆሴዕ በነቢይነት ያገለግሉ ነበር። ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ እነዚህ ታማኝ ነቢያት በመንፈስ መሪነት የሚያውጁትን መልእክት በጥሞና በማዳመጥ የይሖዋ ምክርና እርማት ወደ ልቡ ጠልቆ እንዲገባ ፈቅዶ እንደነበር ማሰብ እንችላለን። በመሆኑም ሕዝቅያስ አባቱ የፈጸማቸውን መጥፎ ነገሮች ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። ይህንንም ያደረገው ቤተ መቅደሱን በማንጻት፣ ለሕዝቡ ኃጢአት ማስተሰረያ በማቅረብ እንዲሁም የአረማውያንን ጣዖታት ለማጥፋት ቅንዓት የተንጸባረቀበት ሰፊ ዘመቻ በማካሄድ ነው። (2 ዜና 29:1-11, 18-24፤ 31:1) ሕዝቅያስ፣ ከባድ ፈተናዎች ባጋጠሙት ጊዜ ለምሳሌ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በሞከረበት ወቅት ታላቅ ድፍረትና እምነት እንዳለው አሳይቷል። አምላክ እንደሚያድነው የተማመነ ከመሆኑም ሌላ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ሕዝቡን አበረታቷል። (2 ዜና 32:7, 8) ከጊዜ በኋላ ሕዝቅያስ ልቡ በመታበዩ እርማት ሲሰጠው ራሱን ዝቅ በማድረግ ንስሐ ገብቷል። (2 ዜና 32:24-26) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሕዝቅያስ፣ ያለፈው ሕይወቱ የአሁኑን ሕይወቱን እንዲያበላሽበት ወይም ጥሩ የወደፊት ሕይወት እንዳይኖረው እንቅፋት እንዲሆንበት አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ወዳጅ በመሆን እኛም ልንከተለው የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ትቷል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ናታን—ለንጹሕ አምልኮ በታማኝነት ጥብቅና የቆመ
ናታን ታማኝ የይሖዋ አምላኪ እንደመሆኑ መጠን ዳዊት በምድር ላይ የመጀመሪያ የሆነውን ቋሚ የአምልኮ ማዕከል ለመገንባት የነበረውን ሐሳብ እንደሚደግፍ በደስታ ገለጸ። ይሁንና ናታን በዚያ ወቅት የተናገረው የግል ስሜቱን እንጂ የይሖዋን ሐሳብ እንዳልሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። አምላክ በዚያን ዕለት ሌሊት ነቢዩን ለዳዊት የተለየ መልእክት እንዲያደርስ ማለትም የይሖዋን ቤተ መቅደስ የሚሠራው እሱ አለመሆኑን እንዲነግረው አዘዘው። ቤተ መቅደሱን የሚሠራው ከዳዊት ልጆች አንዱ ነው። ሆኖም ናታን፣ አምላክ ዙፋኑን ‘ለዘላለም ለማጽናት’ ቃል ኪዳን መግባቱን ለዳዊት ነገረው።—2 ሳሙ. 7:4-16
ቤተ መቅደሱን ከመገንባት ጋር በተያያዘ፣ የአምላክ ፈቃድ ናታን ከነበረው አመለካከት የተለየ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ትሑት ነቢይ ያላንዳች ማጉረምረም ከይሖዋ ዓላማ ጋር እንደሚተባበር አሳይቷል። እኛም አምላክ በሆነ መንገድ እርማት በሚሰጠን ወቅት ልናሳየው የሚገባንን ባሕርይ በተመለከተ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! ናታን ከዚያ በኋላ በነቢይነት የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወኑ የአምላክን ሞገስ ሳያጣ እንደኖረ ያሳያል። እንዲያውም ዳዊት ለቤተ መቅደስ አገልግሎት 4,000 ሙዚቀኞችን እንዲያደራጅ መመሪያ ለመስጠት ይሖዋ ናታንንና ባለ ራእዩ ጋድን በመንፈሱ ሳይመራቸው አልቀረም።—1 ዜና 23:1-5፤ 2 ዜና 29:25
ከሰኔ 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ዜና መዋዕል 30–31
“አንድ ላይ መሰብሰባችን ይጠቅመናል”
it-1 1103 አን. 2
ሕዝቅያስ
ለእውነተኛው አምልኮ የነበረው ቅንዓት። ሕዝቅያስ በ25 ዓመቱ ከነገሠ በኋላ ወዲያውኑ ለይሖዋ አምልኮ ያለውን ቅንዓት አሳየ። የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ቤተ መቅደሱን መልሶ መክፈትና ማደስ ነበር። ከዚያም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጠርቶ “ከእስራኤል አምላክ ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት ከልቤ ተመኝቻለሁ” አላቸው። ይህ ቃል ኪዳን ታማኝ የመሆን ቃል ኪዳን ነበር፤ የሕጉ ቃል ኪዳን በሥራ ላይ ቢሆንም ችላ ተብሎ ስለቆየ ይሁዳ ውስጥ እንደ አዲስ ሥራ ላይ የዋለ ያህል ነበር። ቀጥሎም ሕዝቅያስ በቅንዓት ሌዋውያኑን ለአገልግሎታቸው አደራጀ፤ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ በድጋሚ የሙዚቃ መሣሪያ እንዲጫወቱና የውዳሴ መዝሙር እንዲዘምሩ ዝግጅት አደረገ። ጊዜው የፋሲካ በዓል የሚከበርበት የኒሳን ወር ቢሆንም ቤተ መቅደሱ እንዲሁም ካህናቱና ሌዋውያኑ አልነጹም ነበር። ኒሳን 16 ቤተ መቅደሱን የማንጻቱና ዕቃዎቹን የመመለሱ ሥራ ተጠናቀቀ። ከዚያም ለሁሉም እስራኤላውያን ለየት ያለ የስርየት ሥርዓት ማካሄድ አስፈልጎ ነበር። በመጀመሪያ መኳንንቱ ለመንግሥቱ፣ ለመቅደሱና ለሕዝቡ የኃጢአት መባ ሆነው የሚቀርቡ መሥዋዕቶችን አመጡ፤ ከዚያም ሕዝቡ በሺዎች የሚቆጠሩ የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረቡ።—2ዜና 29:1-36
it-1 1103 አን. 3
ሕዝቅያስ
ሕዝቡ ባለመንጻታቸው ምክንያት ፋሲካን በመደበኛው ጊዜ ማክበር ስላልቻሉ ሕዝቅያስ ንጹሕ ያልሆኑ ሰዎች ፋሲካን ከአንድ ወር በኋላ ማክበር እንደሚችሉ የሚገልጸው ሕግ በሥራ ላይ እንዲውል አደረገ። ከቤርሳቤህ አንስቶ እስከ ዳን ድረስ ደብዳቤ የሚያደርሱ መልእክተኞችን በመላክ የይሁዳን ሰዎች ብቻ ሳይሆን የእስራኤልንም ሰዎች ወደ በዓሉ ጠራ። ብዙዎች በመልእክተኞቹ ላይ አፊዘውባቸው ነበር፤ ይሁን እንጂ ከአሴር፣ ከምናሴና ከዛብሎን ምድር የተወሰኑ ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ከኤፍሬምና ከይሳኮር ነገድም አንዳንዶች መጥተው ነበር። በተጨማሪም እስራኤላውያን ያልሆኑ በርካታ የይሖዋ አምላኪዎች በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል። በሰሜኑ መንግሥት ለሚገኙ ለእውነተኛው አምልኮ የቆሙ ሰዎች በበዓሉ ላይ መገኘት ቀላል እንዳልነበረ ግልጽ ነው። እነሱም እንደ መልእክተኞቹ ተቃውሞና ፌዝ እንደሚያጋጥማቸው ምንም ጥያቄ የለውም፤ ምክንያቱም አሥሩን ነገድ ያቀፈው መንግሥት በወቅቱ በሐሰት አምልኮ ከመዘፈቁም ሌላ በአሦራውያን ጭቆና ሥር ነበር።—2ዜና 30:1-20፤ ዘኁ 9:10-13
it-1 1103 አን. 4-5
ሕዝቅያስ
ከፋሲካ በኋላ ለሰባት ቀናት የቂጣ በዓል ተከበረ፤ ሕዝቡ በጣም ከመደሰቱ የተነሳ መላው ጉባኤ ለተጨማሪ ሰባት ቀናት በዓሉን ለማክበር ወሰነ። እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ጊዜም የይሖዋ በረከት ተትረፍርፎላቸው ነበር፤ በመሆኑም “ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰለሞን ዘመን አንስቶ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ ነገር ሆኖ ስለማያውቅ በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ሆነ።”—2ዜና 30:21-27
ይህ ክንውን እንዲሁ በጊዜያዊ ስሜት የተከበረ በዓል ሳይሆን የእውነተኛውን አምልኮ መልሶ መቋቋም የሚያመለክት እንደሆነ ቀጥሎ የተከናወነው ነገር ያሳያል። የበዓሉ አክባሪዎች ወደ ቤታቸው ከመመለሳቸው በፊት በመላው ይሁዳና ቢንያም እንዲሁም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የማምለኪያ ዓምዶች ሰባበሩ፤ ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎችና መሠዊያዎቹን አፈራረሱ፤ እንዲሁም የማምለኪያ ግንዶቹን ቆረጡ። (2ዜና 31:1) ሕዝቅያስ ሙሴ የሠራውን የመዳብ እባብ በማድቀቅ ምሳሌ ሆኖላቸዋል፤ ምክንያቱም ሕዝቡ እባቡን እንደ ጣዖት በማምለክ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብለት ነበር። (2ነገ 18:4) በዓሉ በድምቀት ከተከበረ በኋላ ሕዝቅያስ እውነተኛው አምልኮ በተገቢው መልኩ መከናወኑን እንዲቀጥል ሲል ካህናቱን በየምድባቸው ደለደለ፤ በቤተ መቅደሱ የሚከናወነው አገልግሎት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኝ ዝግጅት አደረገ፤ እንዲሁም ሕዝቡ ሕጉን በማክበር ለሌዋውያኑና ለካህናቱ አሥራትና የፍሬ በኩራት እንዲያመጡ አዘዘ፤ ሕዝቡም በሙሉ ልብ ምላሽ ሰጥቷል።—2ዜና 31:2-12
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
“እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ”
14 ትሕትናችን የሚፈተንበት ሌላው አቅጣጫ ደግሞ ‘ሌሎች ሲናገሩ በትዕግሥት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነን?’ የሚለው ነው። ያዕቆብ 1:19 ‘ለመስማት የፈጠንን’ መሆን እንዳለብን ይናገራል። በዚህ ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ ነው። (ዘፍ. 18:32፤ ኢያሱ 10:14) በዘፀአት 32:11-14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ዘገባ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያስተምረን እስቲ እንመልከት። (ጥቅሱን አንብብ።) ይሖዋ ከሙሴ ጋር መመካከር ባያስፈልገውም ሙሴ ሐሳቡን እንዲገልጽ አጋጣሚ ሰጥቶታል። አንተ ብትሆን ሲሳሳት ያየኸውን ሰው ሐሳብ በትዕግሥት አዳምጠህ የእሱን ሐሳብ ተግባራዊ ታደርጋለህ? ይሖዋ ግን በእምነት ወደ እሱ የሚጸልዩ ሰዎችን ሁሉ በትዕግሥት ያዳምጣል።
15 ሁላችንም ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘ይሖዋ ራሱን ዝቅ በማድረግ አብርሃምን፣ ራሔልን፣ ሙሴን፣ ኢያሱን፣ ማኑሄን፣ ኤልያስን እና ሕዝቅያስን በትዕግሥት ካዳመጠ እኔስ ከወንድሞቼ ጋር በተያያዘ እንዲህ ማድረግ የለብኝም? ወንድሞቼ ሐሳብ ሲሰጡ በማዳመጥ ብሎም የሰጡኝን ጥሩ ሐሳብ በተግባር በማዋል አክብሮት ላሳያቸውስ አይገባም? በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ ወንድሞች አሊያም ከቤተሰቤ አባላት መካከል በአሁኑ ወቅት የእኔ ትኩረት የሚያስፈልገው ሰው አለ? ግለሰቡን ለመርዳት ምን ማድረግ እችላለሁ?’—ዘፍ. 30:6፤ መሳ. 13:9፤ 1 ነገ. 17:22፤ 2 ዜና 30:20
ከሰኔ 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ዜና መዋዕል 32–33
“በችግር ጊዜ የብርታት ምንጭ ሁኑ”
it-1 204 አን. 5
አሦር
ሰናክሬም። የዳግማዊ ሳርጎን ልጅ የሆነው ሰናክሬም፣ በሕዝቅያስ 14ኛ የግዛት ዘመን (732 ዓ.ዓ.) በይሁዳ ላይ ጥቃት ሰነዘረ። (2ነገ 18:13፤ ኢሳ 36:1) ሕዝቅያስ በአሦር ላይ ዓምፆ ነበር፤ አባቱ አካዝ ባደረገው ነገር የተነሳ የተጣለባቸውን ቀንበር ለመሸከም ፈቃደኛ አልሆነም። (2ነገ 18:7) በምላሹም ሰናክሬም በይሁዳ ላይ ጥቃት ሰነዘረ፤ በዚያ ወቅት 46 ከተሞችን ድል እንዳደረገ ይነገራል (ከኢሳ 36:1, 2 ጋር አወዳድር)፤ ከዚያም በለኪሶ ካለው የጦር ሰፈር ለሕዝቅያስ መልእክት በመላክ 30 የወርቅ ታላንት (11,560,000 የአሜሪካ ዶላር ገደማ) እና 300 የብር ታላንት (1,982,000 የአሜሪካ ዶላር ገደማ) እንዲከፍል አዘዘው። (2ነገ 18:14-16፤ 2ዜና 32:1፤ ከኢሳ 8:5-8 ጋር አወዳድር።) ሕዝቅያስ ይህን ቅጣት ቢከፍልም ሰናክሬም ቃል አቀባዮቹን በመላክ ኢየሩሳሌም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እጅ እንድትሰጥ ጠየቀ። (2ነገ 18:17–19:34፤ 2ዜና 32:2-20) ሆኖም ይሖዋ በአንድ ሌሊት 185,000 ወታደሮቹን ስለገደለበት ይህ ትዕቢተኛ አሦራዊ ወደ ነነዌ ለመመለስ ተገደደ። (2ነገ 19:35, 36) በዚያም ሁለት ልጆቹ ገደሉት፤ በእሱም ምትክ ኤሳርሃደን የተባለው ሌላ ልጁ ነገሠ። (2ነገ 19:37፤ 2ዜና 32:21, 22፤ ኢሳ 37:36-38) የአሦር ሠራዊት መደምሰሱን ከሚገልጸው መረጃ በቀር እነዚህ ክንውኖች በሰናክሬም ፕሪዝምና በኤሳርሃደን ፕሪዝም ላይም ተመዝግበው ይገኛሉ።—ፎቶግራፎች፣ ጥራዝ 1 ገጽ 957
በዛሬው ጊዜ ሰባቱ እረኞችና ስምንቱ አለቆች እነማን ናቸው?
12 ይሖዋ እኛ ማድረግ የማንችለውን ነገር ለእኛ ሲል ለማድረግ ምንጊዜም ፈቃደኛ ነው፤ ይሁንና ማድረግ የምንችለውን ነገር እንድናደርግ ይጠብቅብናል። ሕዝቅያስ “ከሹማምንቱና ከጦር አለቆቹ ጋር” ከተማከረ በኋላ “ከከተማዪቱ ውጭ ያሉት የውሃ ምንጮች እንዲዘጉ” ወሰነ። “ከዚህ በኋላም ንጉሡ ጠንክሮ በመሥራት፣ ከቅጥሩ የፈራረሱትን ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ማማ ሠራበት፤ በውጭ በኩልም ሌላ ቅጥር [ገነባ]። . . . እንደዚሁም ብዙ የጦር መሣሪያዎችንና ጋሻዎችን ሠራ።” (2 ዜና 32:3-5) ይሖዋ ሕዝቡን ለመጠበቅና ለመንከባከብ በወቅቱ በነበሩ በርካታ ደፋር ሰዎች የተጠቀመ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሕዝቅያስ፣ አለቆቹና ታማኝ ነቢያት ይገኙበታል።
በዛሬው ጊዜ ሰባቱ እረኞችና ስምንቱ አለቆች እነማን ናቸው?
13 ሕዝቅያስ በመቀጠል ያደረገው ነገር ውኃውን ከመዝጋት ወይም የከተማዋን ግንቦች ከማጠናከር የበለጠ ጥቅም ያለው ነበር። ሕዝቅያስ አሳቢ እረኛ እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡን ሰብስቦ እንዲህ በማለት አበረታታቸው፦ “ከእኛ ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ስለሚበልጥ፣ የአሦርን ንጉሥና አብሮት ያለውን ብዙ ሰራዊት አትፍሩ፤ አትደንግጡም። ከእነርሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ይህ እንዴት ያለ እምነት የሚያጠናክር ማሳሰቢያ ነው! በእርግጥም ይሖዋ ለሕዝቡ ይዋጋል። ሕዝቡ ይህን ሲሰማ “የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።” ሕዝቡ እንዲበረታታ ያደረገው ‘ሕዝቅያስ የተናገረው ቃል’ መሆኑን ልብ በሉ። ይሖዋ በነቢዩ አማካኝነት አስቀድሞ እንደተናገረው ሕዝቅያስ፣ አለቆቹና ኃያላኑ ሰዎች እንዲሁም ነቢዩ ሚክያስና ነቢዩ ኢሳይያስ ጥሩ እረኞች መሆናቸውን አስመሥክረዋል።—2 ዜና 32:7, 8፤ ሚክያስ 5:5, 6ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
እውነተኛ ንስሐ ምንድን ነው?
11 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ የምናሴን ጸሎት መለሰለት። ይሖዋ የምናሴ ልብ መለወጡን ካቀረባቸው ጸሎቶች ተመልክቷል። በመሆኑም ይሖዋ፣ ምናሴ ምሕረት ለማግኘት ያቀረበውን ጸሎት በመስማት ወደ ዙፋኑ መለሰው። ምናሴም እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ለማሳየት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አደረገ። ምናሴ አክዓብ ያላደረገውን ነገር አድርጓል። ምግባሩን አስተካክሏል። የሐሰት አምልኮን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ከመሆኑም ሌላ እውነተኛውን አምልኮ አስፋፍቷል። (2 ዜና መዋዕል 33:15, 16ን አንብብ።) ምናሴ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ለቤተሰቡ፣ ለመኳንንቱ እንዲሁም ለሕዝቡ መጥፎ ምሳሌ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ለውጥ ለማድረግ ድፍረትና እምነት እንደጠየቀበት ጥርጥር የለውም። ምናሴ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ፣ የሠራቸውን መጥፎ ነገሮች ለማስተካከል ጥረት አድርጓል። ምናሴ በልጅ ልጁ በኢዮስያስ ላይ ጥሩ ተጽዕኖ አሳድሮ መሆን አለበት፤ ኢዮስያስም በጣም ጥሩ ንጉሥ ሆኗል።—2 ነገ. 22:1, 2
12 ከምናሴ ታሪክ ምን እንማራለን? ምናሴ ራሱን አዋርዷል፤ ግን በዚህ ብቻ አልተወሰነም። ምሕረት ለማግኘት ይሖዋን ለምኗል። እንዲሁም አካሄዱን ቀይሯል። የሠራቸውን መጥፎ ነገሮች ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በተጨማሪም ይሖዋን ለማምለክና ሌሎችም እንደዚያ እንዲያደርጉ ለመርዳት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። የምናሴ ታሪክ፣ በጣም ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችም ተስፋ እንዳላቸው ያሳያል። ይህ ታሪክ ይሖዋ አምላክ ‘ጥሩ እና ይቅር ለማለት ዝግጁ’ እንደሆነ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው። (መዝ. 86:5) እውነተኛ ንስሐ የሚገቡ ሰዎች ይቅር ይባላሉ።
ከሰኔ 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ዜና መዋዕል 34–36
“ከአምላክ ቃል የተሟላ ጥቅም እያገኛችሁ ነው?”
it-1 1157 አን. 4
ሕልዳና
ኢዮስያስ በቤተ መቅደሱ እድሳት ወቅት ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ ያገኘው ‘የሕጉ መጽሐፍ’ ሲነበብ ሲሰማ ይሖዋን ለመጠየቅ ሰዎችን ላከ። እነሱም ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እሷም ብሔሩ ከሃዲ በመሆኑ የተነሳ ‘በመጽሐፉ’ ላይ በሰፈረው መሠረት አለመታዘዝ የሚያስከትለውን መዘዝ እንደሚቀምስ ይሖዋ የተናገረውን ቃል ነገረቻቸው። አክላም ሕልዳና፣ ኢዮስያስ በይሖዋ ፊት ራሱን ስላዋረደ የሚመጣውን መከራ እንደማያይ ከዚህ ይልቅ ወደ አባቶቹ እንደሚሰበሰብና በሰላም በመቃብር እንደሚያርፍ ተናገረች።—2ነገ 22:8-20፤ 2ዜና 34:14-28
ለይሖዋ ቤት የምትቀኑ ሁኑ!
20 ንጉሥ ኢዮስያስ እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም ያደራጀው ሥራ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት፣ ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ “በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ።” ከዚያም መጽሐፉን ለንጉሡ ጸሐፊ ለሳፋን የሰጠው ሲሆን ሳፋንም ለኢዮስያስ አነበበለት። (2 ዜና መዋዕል 34:14-18ን አንብብ።) ታዲያ ይህ ሁኔታ ምን ውጤት አስገኘ? ንጉሡ የሕጉን ቃል ሲሰማ በጣም ከማዘኑ የተነሳ ልብሱን ቀደደ፤ እንዲሁም አገልጋዮቹ ይሖዋን እንዲጠይቁ አዘዘ። አምላክ በነቢይቱ ሕልዳና አማካኝነት በይሁዳ ይካሄዱ የነበሩትን አንዳንድ የአምልኮ ሥርዓቶች እንደሚያወግዝ ተናገረ። ያም ሆኖ ኢዮስያስ የጣዖት አምልኮን ለማስወገድ ያደረገውን መልካም ጥረት ይሖዋ ተመልክቶ ስለነበር የይሁዳ ሕዝብ እንደሚጠፋ ትንቢት ቢነገርም እሱ ግን የአምላክን ሞገስ አግኝቷል። (2 ዜና 34:19-28) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? የእኛም ፍላጎት ከኢዮስያስ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ክህደት አምልኳችንን እንዲበክል ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ ይሖዋ የሚሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ፈጣን መሆን አለብን። ይሖዋ ለኢዮስያስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ለእውነተኛው አምልኮ የምናሳየውን ቅንዓት በአድናቆት እንደሚመለከት እርግጠኛ መሆን እንችላለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
አስቀድሞ ለተጻፉት ነገሮች ትኩረት ትሰጣላችሁ?
15 ጥሩ ንጉሥ የነበረው ኢዮስያስ ካጋጠመው ሁኔታስ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ኢዮስያስ በጦርነት ተሸንፎ ሕይወቱን እንዲያጣ ምክንያት የሆነው ነገር ምን እንደሆነ እንመልከት። (2 ዜና መዋዕል 35:20-22ን አንብብ።) በአንድ ወቅት ኢዮስያስ፣ የግብፁን ንጉሥ ኒካዑን ‘ሊገጥም ወጥቶ ነበር።’ እርግጥ ይህን ለማድረግ የሚያነሳሳ ምንም ምክንያት አልነበረውም፤ ንጉሥ ኒካዑ ራሱ ከእሱ ጋር መዋጋት እንደማይፈልግ ለኢዮስያስ ነግሮት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “በኒካዑ በኩል የተነገረውን የአምላክ ቃል አልሰማም” ይላል። ታዲያ ኢዮስያስ ሊዋጋ የወጣው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ነገር የለም።
16 ኢዮስያስ፣ ኒካዑ የተናገረው ነገር ከአምላክ የመጣ መሆኑን እንዴት ማወቅ ይችል ነበር? ታማኝ ከሆኑት ነቢያት አንዱ የሆነውን ኤርምያስን መጠየቅ ይችል ነበር። (2 ዜና 35:23, 25) ይሁንና እንዲህ እንዳደረገ የሚገልጽ ዘገባ የለም። ከዚህም ሌላ ኒካዑ የሚሄደው ወደ ካርከሚሽ ነበር። ኒካዑ እየተጓዘ የነበረው ኢየሩሳሌምን ለመውጋት ሳይሆን “ከሌላ ብሔር ጋር” ለመዋጋት ነበር። በተጨማሪም ኒካዑ፣ ይሖዋንም ሆነ ሕዝቡን ስላልሰደበ ጉዳዩ ከአምላክ ስም ጋር የተያያዘ አልነበረም። ኢዮስያስ ከኒካዑ ጋር ለመዋጋት ያደረገው ውሳኔ ማስተዋል የጎደለው ነበር። እኛስ ከዚህ ዘገባ የምናገኘው ትምህርት አለ? አንድ ችግር ሲያጋጥመን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ማድረጋችን ጠቃሚ ነው።
17 ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመርመርና በተግባር ማዋል ይኖርብናል፤ በእርግጥ ይህን ስናደርግ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልገናል። አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎችን ማማከር እንፈልግ ይሆናል። ስለ ጉዳዩ ባለን እውቀት ላይ ተመሥርተን በጥሞና አስበንበት ሊሆን ይችላል፤ በተጨማሪም ጽሑፎቻችንን ተጠቅመን ምርምር እናደርጋለን። ሽማግሌዎችን ስናማክር ደግሞ ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይጠቁሙን ይሆናል። የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላትን አንዲት እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህች እህት ምሥራቹን የመስበክ ኃላፊነት እንዳለባት ታውቃለች። (ሥራ 4:20) ይሁን እንጂ በመስክ አገልግሎት ልትካፈል ባሰበችበት ቀን፣ ባለቤቷ አብረው ጊዜ ካሳለፉ እንደቆዩ በመግለጽ ከእሱ ጋር እንድትውል ጠየቃት እንበል። እህታችን ጥበብ ያዘለ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዷትን ጥቅሶች ትመረምር ይሆናል። አምላክን መታዘዝ እንዳለባት እንዲሁም ኢየሱስ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ እንዳዘዘን ታውቃለች። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 5:29) በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት ሚስት ለባሏ መገዛት እንዳለባትና የአምላክ አገልጋዮች ምክንያታዊ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ማስታወስ ይኖርባታል። (ኤፌ. 5:22-24፤ ፊልጵ. 4:5) ባለቤቷ ጨርሶ አገልግሎት እንዳትወጣ ሊከለክላት እየሞከረ ነው? ወይስ በዚያ ዕለት ብቻ አብረው አንድ ነገር እንዲያከናውኑ መጠየቁ ነው? በእርግጥም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግና ጥሩ ሕሊና ይዘን ለመኖር ስንጥር ሚዛናዊ መሆናችን አስፈላጊ ነው።
ከሰኔ 26–ሐምሌ 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዕዝራ 1–3
“ይሖዋ እንዲጠቀምባችሁ ፍቀዱለት”
ዘካርያስ ያየው ይታያችኋል?
አይሁዳውያኑ በጣም ተደስተዋል። ይሖዋ አምላክ “የፋርሱን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ [በማነሳሳት]” ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በባቢሎን ግዞት የነበሩትን እስራኤላውያን እንዲለቅ አደረገው። ንጉሡ አይሁዳውያኑ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ‘የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ቤት መልሰው እንዲገነቡ’ የሚገልጽ አዋጅ አወጣ። (ዕዝራ 1:1, 3) ይህ እንዴት የሚያስደስት ነው! አሁን የእውነተኛው አምላክ አምልኮ እሱ ለሕዝቡ በሰጠው ምድር ላይ መልሶ ሊቋቋም ነው ማለት ነው።
ጥበቃ የሚያደርጉልን ሠረገሎችና አክሊል
2 ዘካርያስ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት አይሁዳውያን እምነት የነበራቸው ሰዎች እንደሆኑ ያውቃል። የተደላደለ ኑሯቸውንና ንግዳቸውን ትተው ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት እነዚህ ወንዶችና ሴቶች “እውነተኛው አምላክ መንፈሳቸውን ያነሳሳው ሰዎች” ናቸው። (ዕዝራ 1:2, 3, 5) ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ኢየሩሳሌምን አይተዋት አያውቁም፤ ሆኖም የኖሩበትን አካባቢ ትተው ወደዚያ ለመሄድ ፈቃደኞች ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሶ የመገንባቱን ሥራ ከፍ አድርገው ባይመለከቱት ኖሮ 1,600 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ያለውን አስቸጋሪ ጉዞ ለማድረግ አይነሱም ነበር።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የዕዝራ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
1:3-6፦ ጥንት በባቢሎን እንደቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን ወይም ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት አካባቢ ሄደው ማገልገል አይችሉም። ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተሳተፉ ላሉት ድጋፍና ማበረታቻ ይሰጣሉ። ከዚህም በላይ የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበኩና ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራ በፈቃደኝነት የገንዘብ መዋጮ ያደርጋሉ።