የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2023 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከሐምሌ 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዕዝራ 4–6
“በአምላክ ቤት ሥራ ጣልቃ አትግቡ”
ዘካርያስ ያየው ይታያችኋል?
13 ቤተ መቅደሱን መልሶ በመገንባቱ ሥራ ላይ እገዳ ተጥሎ ነበር። ያም ሆኖ ሥራውን እንዲመሩ የተሾሙት ሊቀ ካህናቱ የሆሹዋ (ኢያሱ) እና ገዢው ዘሩባቤል “የአምላክን ቤት መልሰው መገንባት ጀመሩ።” (ዕዝራ 5:1, 2) አንዳንድ አይሁዳውያን ይህ ውሳኔ ጥበብ የጎደለው እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ቤተ መቅደሱን የመገንባቱ ሥራ ከጠላት እይታ ሊሰወር አይችልም፤ ጠላቶቻቸው ደግሞ ሥራውን ለማስቆም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ኃላፊነት የተጣለባቸው ሁለቱ ወንዶች ማለትም ኢያሱና ዘሩባቤል ይሖዋ ውሳኔያቸውን እንደሚደግፍ የሚያሳይ ማረጋገጫ ያስፈልጋቸው ነበር። ደግሞም ማረጋገጫ አግኝተዋል። እንዴት?
w86 2/1 29 ሣጥን አን. 2-3
የይሖዋ ‘ዓይን በሽማግሌዎቹ ላይ ነበር’
አይሁዳውያን ቀሪዎች ከባቢሎን ከተመለሱ በኋላ ለ16 ዓመታት ያህል ምንም ሥራ አላከናወኑም። ነቢያቱ ሐጌና ዘካርያስ አይሁዳውያኑ ግዴለሽነታቸውን እንዲያስወግዱ ስለረዷቸው የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሶ የመገንባቱ ሥራ ቀጠለ። ብዙም ሳይቆይ ግን የፋርስ ባለሥልጣናት ይህን ሥራ ተቃወሙ። ተቃዋሚዎቹ “ይህን ቤት እንድትገነቡ . . . ማን ትእዛዝ ሰጣችሁ?” በማለት ጠየቁ።—ዕዝራ 5:1-3
ሽማግሌዎቹ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። በፍርሃት ከተሽመደመዱ ቤተ መቅደሱን የማደሱ ሥራ ወዲያውኑ ይቋረጣል። ሽማግሌዎቹ ባለሥልጣናቱን የሚያበሳጭ ነገር ከተናገሩ ደግሞ በሥራው ላይ ወዲያውኑ እገዳ ሊጣል ይችላል። በመሆኑም ሽማግሌዎቹ (በገዢው ዘሩባቤልና በሊቀ ካህናቱ ኢያሱ አመራር ሳይሆን አይቀርም) ውጤታማ የሆነ ምላሽ በዘዴ ሰጡ። ከረጅም ጊዜ በፊት ቂሮስ አይሁዳውያን ይህን ሥራ እንዲያከናውኑ የሰጣቸውን ንጉሣዊ ፈቃድ ለባለሥልጣናቱ አስታወሷቸው። እነዚህ ባለሥልጣናት ፋርሳውያን ያወጡትን ሕግ መቼም እንደማይሽሩ ስለሚያውቁ ንጉሣዊውን አዋጅ ላለመቃወም መረጡ። በመሆኑም አይሁዳውያኑ ሥራውን ቀጠሉ፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ንጉሥ ዳርዮስ ሥራውን እንዲቀጥሉ ሕጋዊ ፈቃድ ሰጣቸው።—ዕዝራ 5:11-17፤ 6:6-12
ዘካርያስ ያየው ይታያችኋል?
7 ከጊዜ በኋላ ቤተ መቅደሱን የሚገነቡትን ሰዎች የሚጠቅም አንድ ለውጥ ተከሰተ። ይህ ለውጥ ምንድን ነው? በ520 ዓ.ዓ. ፋርስን ያስተዳድር የነበረው ቀዳማዊ ዳርዮስ የተባለ አዲስ ንጉሥ ነበር። ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት በቤተ መቅደሱ ግንባታ ላይ የተጣለው እገዳ ሕጋዊ እንዳልሆነ ተገነዘበ። በመሆኑም የግንባታ ሥራው እንዲጠናቀቅ ፈቃድ ሰጠ። (ዕዝራ 6:1-3) ይህ ውሳኔ በራሱ በጣም አስደናቂ ነው፤ ሆኖም ንጉሡ በዚህ ብቻ አልተወሰነም። በአይሁዳውያኑ ዙሪያ ያሉ ሰዎች በግንባታ ሥራው ላይ ጣልቃ መግባታቸውን እንዲያቆሙ እንዲሁም ገንዘብና ቁሳቁስ በማቅረብ ለግንባታው ሥራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ትእዛዝ ሰጠ! (ዕዝራ 6:7-12) በዚህም የተነሳ አይሁዳውያኑ ከአራት ዓመት ገደማ በኋላ ማለትም በ515 ዓ.ዓ. የቤተ መቅደሱን ግንባታ ማጠናቀቅ ቻሉ።—ዕዝራ 6:15
ዘካርያስ ያየው ይታያችኋል?
16 ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያ የሚሰጥበት ሌላው መንገድ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ነው። (ማቴ. 24:45) አንዳንድ ጊዜ ታማኙ ባሪያ የሚሰጠውን መመሪያ ሙሉ በሙሉ መረዳት ሊከብደን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚረዱ ዝርዝር መመሪያዎች ይሰጡን ይሆናል፤ ሆኖም ይህ አደጋ በእኛ አካባቢ እንደማያጋጥም ሊሰማን ይችላል። አሊያም ደግሞ ታማኙ ባሪያ በወረርሽኝ ወቅት የሚሰጠው መመሪያ ከልክ በላይ ጥብቅ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። የሚሰጡን መመሪያዎች እኛ ላለንበት ሁኔታ እንደማይሠሩ በሚሰማን ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? እስራኤላውያን በኢያሱና በዘሩባቤል በኩል የተሰጣቸውን መመሪያ በመታዘዛቸው ምን ጥቅም እንዳገኙ እናስብ። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበብናቸውን ሌሎች ዘገባዎችም ልናስብ እንችላለን። የአምላክ ሕዝቦች ከሰብዓዊ እይታ አንጻር ጥበብ የጎደለው የሚመስል መመሪያ የተሰጣቸው ጊዜ ነበር፤ መታዘዛቸው ግን የኋላ ኋላ ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል።—መሳ. 7:7፤ 8:10
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
መጽሐፍ ቅዱስን ልትተማመንበት ትችላለህን?
ሳንቲሙ የተሠራው ዛሬ ቱርክ ተብላ ከምትጠራው አገር ደቡባዊ ምሥራቅ በምትገኝ ጠርሴስ በምትባል ከተማ ነው። ሳንቲሙ የተቀረጸው በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የፋርስ ገዥ በነበረው በማዛዩስ ዘመነ መንግሥት ነበር። እሱንም “በወንዙ ማዶ” ማለትም ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ያለው ክፍለ ሀገር ገዥ በማለት ይጠቅሰዋል።
ይህን ሐረግ መጥቀስ ለምን አስፈለገ? ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ ተመሳሳይ አጠራር ስለምታገኝ ነው። ዕዝራ 5:6 እስከ 6:13 በፋርሱ ንጉሥ በዳርዮስ እና ተንትናይ በተባለው ገዥ መካከል ስለተደረገ መጻጻፍ ይጠቅሳል። ተነሥቶ የነበረው አጨቃጫቂ ጉዳይ አይሁዶች በኢየሩሳሌም ውስጥ ቤተ መቅደሳቸውን እንደገና መሥራታቸው ነበር። ዕዝራ የአምላክ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ (ገልባጭ) ስለነበረ በሚጽፋቸው ነገሮች ሁሉ ጠንቃቃና ትክክለኛ እንደሚሆን አያጠራጥርም። በዕዝራ 5:6 እና 6:13 ላይ ተንትናይን “በወንዙ ማዶ የነበረው ገዥ” ብሎ እንደጠራው ትመለከታለህ።
ዕዝራ ይህን የጻፈው ሳንቲሙ ከመቀረጹ ከ100 ዓመት በፊት ማለትም በ460 ከዘአበ ነበር። አንዳንድ ሰዎች የአንድ ጥንታዊ ባለ ሥልጣን መጠቀስ ያን ያህል ትልቅ ነገር አይደለም ብለው በማሰብ አቃልለው ይናገሩ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን እንደዚህ በመሳሰሉ ጥቃቅን ነገሮች እንኳ ሳይቀር ልትተማመንባቸው ከቻልክ እነሱ በጻፏቸው ሌሎች የመጽሐፉ ክፍሎች ላይ ያለህ ትምክህት ሊጨምር አይገባውምን?
ከሐምሌ 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዕዝራ 7–8
“ዕዝራ በምግባሩ ይሖዋን አስከብሯል”
ጥናት—አስደሳችና የሚክስ ሥራ ነው
8 አዎን፣ ለይሖዋ ቃል ያለን ፍቅር የስሜት መቀመጫ ከሆነው ከልባችን የሚወጣ መሆን ይኖርበታል። አንድ ክፍል ካነበብን በኋላ ባነበብነው ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። ጥልቀት ባላቸው መንፈሳዊ ሐሳቦች መመሰጥ፣ ሙሉ በሙሉ መዋጥና ማሰላሰል ይኖርብናል። ይህ ደግሞ በጸጥታ ማብላላትንና ጸሎትን ይጠይቃል። እንደ ዕዝራ የአምላክን ቃል ለማንበብና ለማጥናት ልባችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል። ስለ እርሱ እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።” (ዕዝራ 7:10) ዕዝራ ለሦስት ነገሮች ማለትም ለማጥናት፣ በሕይወቱ ላይ በተግባር ለማዋልና ለማስተማር ልቡን እንዳዘጋጀ ልብ በል። እኛም የእርሱን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል።
si 75 አን. 5
የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 13—1 ዜና መዋዕል
5 ይህን እውነተኛና ትክክለኛ ታሪክ ለማጠናቀር ከዕዝራ የተሻለ ብቃት ያለው ሰው አልነበረም። “ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።” (ዕዝራ 7:10) ይሖዋም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እገዛ አድርጎለታል። ፋርሳዊው የዓለም ገዥ በዕዝራ ላይ የተንጸባረቀውን የአምላክ ጥበብ በማስተዋል በይሁዳ አውራጃ ከፍተኛ የሕዝብ ሥልጣን ሰጥቶታል። (ዕዝራ 7:12-26) በዚህ መንገድ ከአምላክና ከንጉሡ ሥልጣን የተቀበለው ዕዝራ በጊዜው የነበሩትን ምርጥ መዛግብት በመጠቀም ዘገባውን ማጠናቀር ችሏል።
it-1 1158 አን. 4
ትሕትና
ትክክለኛ አመራር ያስገኛል። ራሱን በአምላክ ፊት የሚያዋርድ ሰው የአምላክን አመራር እንደሚያገኝ መጠበቅ ይችላል። ዕዝራ ከ1,500 በላይ ወንዶችን፣ ካህናትን፣ ናታኒምን እንዲሁም ሴቶችንና ልጆችን ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም የመውሰድ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎበት ነበር። በተጨማሪም በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ለማስዋብ የሚያገለግል ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅና ብር ይዘው ነበር። በጉዞው ወቅት ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፤ ሆኖም ዕዝራ የፋርስ ንጉሥ ወታደራዊ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው በመጠየቅ በሰብዓዊ ኃይል መታመን አልፈለገም። በዚያ ላይ ደግሞ “መልካም የሆነው የአምላካችን እጅ እሱን በሚሹት ሁሉ ላይ ነው” በማለት ለንጉሡ አስቀድሞ ነግሮት ነበር። በመሆኑም ሕዝቡ በይሖዋ ፊት ራሳቸውን እንዲያዋርዱ ጾም አወጀ። የአምላክን እርዳታ ጠየቁ፤ እሱም ልመናቸውን በመስማት በመንገዳቸው ላይ ከጠላት ጥቃት ስለጠበቃቸው አደገኛውን ጉዞ በሰላም አጠናቀቁ። (ዕዝራ 8:1-14, 21-32) በባቢሎን ግዞት የነበረው ነቢዩ ዳንኤል የአምላክን አመራርና ጥበብ ለማግኘት ራሱን በአምላክ ፊት ስላዋረደ ይሖዋ በመልአኩ አማካኝነት ራእይ በማሳየት ሞገሱን አሳይቶታል።—ዳን 10:12
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የዕዝራ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
7:28 እስከ 8:20—በባቢሎን ይኖሩ የነበሩ ብዙ አይሁዳውያን ከዕዝራ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ ያልፈለጉት ለምንድን ነው? የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ 60 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም በኢየሩሳሌም ውስጥ በቂ ነዋሪዎች አልነበሩም። ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ ማለት ምቹ ባልሆነና በአደገኛ ሁኔታ ሥር አዲስ ኑሮ መመሥረት ማለት ነው። በወቅቱ በኢየሩሳሌም የነበረው በቁሳዊ የማደግ ሁኔታ በባቢሎን የተደላደለ ኑሮ ለነበራቸው አይሁዳውያን የሚስብ አልነበረም። አደገኛ የሆነው ጉዞም ሳይጠቀስ አይታለፍም። ተመላሾቹ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት፣ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት እንዲሁም ጉዞውን ለማድረግ ድፍረት ሊኖራቸው ይገባ ነበር። ዕዝራም ቢሆን የበረታው የይሖዋ እጅ በእርሱ ላይ ስለነበረች ነው። ዕዝራ በሰጣቸው ማበረታቻ 1,500 ቤተሰቦች፤ ምናልባትም ቁጥራቸው 6,000 የሚደርሱ ሰዎች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ዕዝራ ባደረገው ተጨማሪ ቅስቀሳ ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑ 38 ሌዋውያን እና 220 ናታኒሞች ሊገኙ ችለዋል።
ከሐምሌ 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዕዝራ 9–10
“አለመታዘዝ የሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ”
የዕዝራ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
9:1, 2—በምድሪቱ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር መጋባት ምን አደጋ ነበረው? ተመልሶ የተቋቋመው ይህ ብሔር መሲሑ እስኪመጣ ድረስ የእውነተኛው አምልኮ ባለአደራ ነበር። በአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች ጋር በጋብቻ መጣመር በእውነተኛው አምልኮ ላይ ከባድ ስጋት ይፈጥራል። አንዳንድ አይሁዳውያን ጣዖት አምላኪ ከሆኑ ሰዎች ጋር ጋብቻ መስርተው ስለነበር መላው ብሔር ቀስ በቀስ በአረማውያን ብሔራት የመዋጥ አደጋ ተደቅኖበት ነበር። በዚህ ዓይነት እውነተኛ አምልኮ ከምድር ገጽ ሊጠፋ ይችላል። እንዲህ ቢሆን ኖሮ ደግሞ መሲሑ ለእነማን መምጣት ያስፈልገው ነበር? ዕዝራ በድርጊታቸው ቢደነግጥ ምንም አያስገርምም!
ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
ለይሖዋ በፈቃደኝነት መታዘዛችን በረከት ያስገኝልናል። ሙሴ ‘መልካም እንዲሆንልህ ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞች ጠብቅ’ በማለት ጽፏል። (ቁጥር 13) አዎን፣ ይሖዋ ማንኛውንም ትእዛዝ የሚሰጠን ማለትም ከእኛ የሚፈልገውን ማንኛውንም ነገር እንድንፈጽም የሚጠብቅብን ለእኛ መልካም እንዲሆንልን በማሰብ ነው። እንዲህ ብለን ማመናችን ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ እነዚህን ትእዛዛት የሰጠው ዘላቂ ጥቅም እንድናገኝ በማሰብ ብቻ ነው። (ኢሳይያስ 48:17) ይሖዋ እንድናደርግ ያዘዘውን ነገር ሁሉ መፈጸማችን በአሁኑ ወቅት ተስፋ ከሚያስቆርጡ ብዙ ችግሮች የሚጠብቀን ሲሆን ወደፊት ደግሞ መንግሥቱ ምድርን በሚያስተዳድርበት ጊዜ ማለቂያ የሌለው በረከት ያስገኝልናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የዕዝራ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
10:3, 44—ሚስቶቻቸውን ከነልጆቻቸው ያሰናበቷቸው ለምንድን ነው? ልጆቻቸው እዚያው ቢቀሩ ኖሮ የተባረሩት ሚስቶች ልጆቻቸውን ብለው የመመለሳቸው አጋጣሚ ሰፊ ይሆን ነበር። በተጨማሪም፣ ትንንሽ ልጆች በአብዛኛው የእናታቸው እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው።
ከሐምሌ 24-30
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ነህምያ 1–2
“ወዲያውኑ ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይኩ”
ይሖዋን ዘወትር በፊትህ አድርግ
5 አንዳንድ ጊዜ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ወዲያውኑ መጸለይ ይኖርብን ይሆናል። በአንድ ወቅት፣ የፋርሱ ንጉሥ አርጤክስስ ነህምያ የተባለ የወይን ጠጅ አሳላፊው በሐዘን ፊቱ ጠቁሮ ተመለከተ። በመሆኑም ንጉሡ ነህምያን “ምን ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ነህምያም ወዲያውኑ ‘ወደ ሰማይ አምላክ ጸለየ።’ ነህምያ በልቡ ያቀረበው ጸሎት አጭር እንደነበር መገመት እንችላለን። ይሁንና አምላክ ለጸሎቱ መልስ ሰጥቶታል። የኢየሩሳሌምን ቅጥር ዳግም ለመገንባት የሚያስችል ድጋፍ ከንጉሡ አግኝቷል። (ነህምያ 2:1-8ን አንብብ።) አዎን፣ በልብ የቀረበ አጭር ጸሎት እንኳ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።
በራስ አባባል መናገር
ስለ እምነትህ ማብራሪያ እንድትሰጥ ድንገት በምትጠየቅበት ጊዜ ጥሩ መልስ ለመስጠት የሚረዳህ ምንድን ነው? ንጉሥ አርጤክስስ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ ከመስጠቱ በፊት በልቡ ጸሎት ያቀረበውን የነህምያን ምሳሌ ተከተል። (ነህ. 2:4) ከዚያም የምትሰጠውን መልስ ጊዜ ሳታጠፋ በአእምሮህ አቀናብረህ ለማስቀመጥ ሞክር። ቀጥሎ የቀረቡትን ነጥቦች መነሻ አድርገህ ልትጠቀምባቸው ትችል ይሆናል፦ (1) በማብራሪያህ ልታካትታቸው የሚገቡ አንድ ወይም ሁለት ነጥቦች ምረጥ (ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱ ነጥቦችን መጠቀም ትፈልግ ይሆናል።) (2) ላነሳኻቸው ነጥቦች ማስረጃ አድርገህ የምትጠቀምባቸውን ጥቅሶች አስብ። (3) ጠያቂህ በጥሞና እንዲያዳምጥህ ማብራሪያህን እንዴት ብለህ እንደምትጀምር አስብ። ከዚህ በኋላ መልስ መስጠት ልትጀምር ትችላለህ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
w86 2/15 25
እውነተኛው አምልኮ ድል ያደርጋል
አልነበረም፤ ምክንያቱም ነህምያ ኢየሩሳሌም ያለችበትን አሳዛኝ ሁኔታ አስመልክቶ ረዘም ላለ ጊዜ “ቀን ከሌት” ሲጸልይ ቆይቷል። (1:4, 6) ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ ለመገንባት ያለውን ፍላጎት ለንጉሥ አርጤክስስ የመናገር አጋጣሚ ባገኘ ጊዜ ከዚያ በፊት በተደጋጋሚ እንዳደረገው አሁንም ጸለየ። ይሖዋ ጸሎቱን ስለመለሰለት የከተማዋን ቅጥሮች እንዲገነባ ተልእኮ ተሰጠው።
የምናገኘው ትምህርት፦ ነህምያ መመሪያ ለማግኘት ይሖዋን ጠይቋል። እኛም ከባድ ውሳኔ ሲደቀንብን ‘ሳንታክት መጸለይ’ እንዲሁም ከይሖዋ አመራር ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።—ሮም 12:12
ከሐምሌ 31–ነሐሴ 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ነህምያ 3–4
“ለጉልበት ሥራ ንቀት አለህ?”
የነህምያ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
3:5, 27፦ የቴቁሐ ‘መኳንንቶች’ እንደተሰማቸው እኛም እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ብለን የጉልበት ሥራ ብንሠራ ክብራችን እንደሚነካ ሊሰማን አይገባም። ከዚህ ይልቅ የጉልበት ሥራ ለመሥራት ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡትን ተራ ቴቁሐውያን መምሰል እንችላለን።
ይሖዋ ምን እንድትሆን ያደርግሃል?
11 ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ፣ የኢየሩሳሌም ቅጥር በተጠገነበት ወቅት ይሖዋ ለሥራው ከተጠቀመባቸው ሰዎች መካከል የሻሉም ሴቶች ልጆች ይገኙበታል። (ነህ. 2:20፤ 3:12) የሻሉም ልጆች አባታቸው ገዢ ቢሆንም ከባድና አደገኛ የሆነውን ሥራ ለማከናወን ፈቃደኞች ሆነዋል። (ነህ. 4:15-18) እነዚህ ሴቶች፣ “ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ” በሥራው መካፈል ካልፈለጉት ታዋቂ የሆኑ የተቆአ ሰዎች የተለየ መንፈስ አሳይተዋል! (ነህ. 3:5) የሻሉም ሴቶች ልጆች ሥራው በ52 ቀናት ውስጥ ብቻ ሲጠናቀቅ ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን አስቡት! (ነህ. 6:15) በዘመናችንም ፈቃደኛ የሆኑ እህቶች ለየት ባለ የቅዱስ አገልግሎት ዘርፍ ይኸውም ለይሖዋ አምልኮ የሚውሉ ሕንፃዎችን በመገንባቱና በመጠገኑ ሥራ መካፈላቸው ያስደስታቸዋል። የእነዚህ እህቶች ችሎታ፣ ቅንዓትና ታማኝነት ለሥራው መሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ታላቅ መሆንን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አመለካከት አዳብሩ
16 ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች፣ ሁሉም ክርስቲያኖች ታላቅነትን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በጉባኤ ውስጥ መከናወን ያለባቸው የተለያዩ ዓይነት ሥራዎች አሉ። ዝቅተኛ የሚመስሉ ሥራዎችን እንድንሠራ ብንጠየቅ ቅር መሰኘት የለብንም። (1 ሳሙኤል 25:41፤ 2 ነገሥት 3:11) ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የጉባኤ፣ የልዩ፣ የወረዳ ወይም የአውራጃ ስብሰባዎች በሚካሄዱባቸው ቦታዎች ምንም ዓይነት ሥራ ቢሰጣቸው በደስታ እንዲያከናውኑት ታበረታቷቸዋላችሁ? ትሕትና የሚጠይቁ ሥራዎችን ስትሠሩ አይተው ያውቃሉ? በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚያገለግል አንድ ወንድም የወላጆቹ ምሳሌ በደንብ ትዝ ይለዋል። እንዲህ ይላል፦ “ወላጆቼ የመንግሥት አዳራሽ ወይም አውራጃ ስብሰባ የምናደርግበትን ቦታ በማጽዳት ሥራ የሚያደርጉት ተሳትፎ ሥራውን ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት እንድገነዘብ አስችሎኛል። ሥራዎቹ በጣም ዝቅተኛ ተደርገው የሚታዩ ቢሆኑም እንኳ ለጉባኤው ወይም ለወንድሞች የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለማከናወን ፈቃደኛ ነበሩ። ለሥራ ያላቸው አመለካከት ቤቴል ውስጥ ማንኛውንም ሥራ በደስታ እንድቀበል አስችሎኛል።”
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የነህምያ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
4:17, 18—በመልሶ ግንባታው ላይ የተሠማራ አንድ ሰው በአንድ እጁ መሥራት የሚችለው እንዴት ነው? ለዕቃ ተሸካሚዎች ያን ያህል አስቸጋሪ አልነበረም። ዕቃውን በራሳቸው ወይም በትከሻቸው ላይ ከተሸከሙት በኋላ በአንድ እጃቸው ደግፈው “በሌላው እጃቸው የጦር መሣሪያቸውን [ይይዙ] ነበር።” ግንበኞቹ ግን ሁለቱንም እጃቸውን መጠቀም ስለሚያስፈልጋቸው እያንዳንዱ ግንበኛ “ቅጥሩን በሚሠራበት ጊዜ ሰይፉን በወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር።” ስለዚህ ከጠላት ጥቃት ቢሰነዘር እንኳ ለመመከት ዝግጁ ነበሩ።
ከነሐሴ 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ነህምያ 5–7
“ነህምያ ለማገልገል እንጂ ለመገልገል አልፈለገም”
የእውነተኛው አምልኮ ደጋፊዎች—ጥንትና ዛሬ
ነህምያ ለሥራው ያበረከተው ጊዜውንና የማደራጀት ችሎታውን ብቻ አልነበረም። እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ቁሳዊ ሃብቱንም ተጠቅሟል። ለባርነት የተሸጡ አይሁዳውያን ወንድሞቹን በራሱ ገንዘብ ተቤዥቷቸዋል። ገንዘቡን ያለ ወለድ አበድሯል። ለአለቃ የሚገባውን አበል እንዲሰጡት በመጠየቅ በአይሁዳውያን ላይ ሸክም ‘አላከበደባቸውም።’ ከዚህ ይልቅ ‘በዙሪያቸው ካሉት አሕዛብ ወደ እነርሱ ከመጡት ሌላ ከአይሁድና ከሹማምቱ መቶ አምሳ ሰዎች’ ለመመገብ ቤቱን ክፍት አድርጓል። “ከወፎችም በቀር ለአንድ ቀን አንድ በሬና ስድስት የሰቡ በጎች” ለእንግዶቹ ያቀርብ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በየአሥር ቀኑ በራሱ ወጪ “ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ” ያቀርብላቸው ነበር።—ነህምያ 5:8, 10, 14-18
‘እጆቻችሁ አይዛሉ’
16 ነህምያና አብረውት የነበሩት ሰዎች የይሖዋን እርዳታ በማግኘታቸው እጃቸውን አበርትተው ሥራውን ማከናወን ችለዋል። በመሆኑም የኢየሩሳሌምን ቅጥር በ52 ቀናት ውስጥ ገንብተው ማጠናቀቅ ችለዋል! (ነህ. 2:18 ግርጌ፤ 6:15, 16) ነህምያ ሥራውን በበላይነት በመከታተል ብቻ ከመወሰን ይልቅ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ በመገንባቱ ሥራ ተካፍሏል። (ነህ. 5:16) በተመሳሳይም በርካታ አፍቃሪ ሽማግሌዎች፣ በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በመካፈል ወይም የመንግሥት አዳራሻቸውን በማጽዳቱና በማደሱ ሥራ ላይ በመሳተፍ የነህምያን ምሳሌ ተከትለዋል። በተጨማሪም ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር አብረው ያገለግላሉ እንዲሁም እረኝነት ያደርጉላቸዋል፤ በዚህ መንገድ፣ በጭንቀት የተዋጠ ልብ ያላቸውን አስፋፊዎች የዛሉ እጆች ያበረታሉ።—ኢሳይያስ 35:3, 4ን አንብብ።
ይሖዋ የሚያስባችሁ እንዴት ነው?
አምላክም አንድን ሰው ‘ሲያስብ’ አዎንታዊ እርምጃ እንደሚወስድ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል ምድር ለ150 ቀናት በውኃ ከተጥለቀለቀች በኋላ “እግዚአብሔርም ኖኅን . . . አሰበ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አሳለፈ፣ ውኃውም ጎደለ።” (ዘፍጥረት 8:1) ይህ ከሆነ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን ዓይኖቹን አውጥተውና በሰንሰለት አስረውት በነበረበት ጊዜ “አምላክ ሆይ፣ እባክህ፣ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፣ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ፣ እባክህ አበርታኝ” ሲል ጸልዮአል። ሳምሶን የአምላክን ጠላቶች መበቀል እንዲችል ይሖዋ ከተለመደው የሰው አቅም በላይ የሆነ ጥንካሬ በመስጠት አስቦታል። (መሳፍንት 16:28-30) ለነህምያ ደግሞ ይሖዋ ጥረቱን ባርኮለት በኢየሩሳሌም እውነተኛው አምልኮ ዳግም ተቋቁሟል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
“ክፉን በመልካም አሸንፍ”
15 በሦስተኛ ደረጃ፣ ጠላቶቹ ነህምያ የአምላክን ሕግ እንዲጥስ ለማድረግ ከሃዲ በሆነው ሸማያ የተባለ እስራኤላዊ ተጠቀሙ። ሸማያ፣ ነህምያን እንዲህ አለው፦ “ሰዎች ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ . . . በእግዚአብሔር ቤት ባለው በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋቸው።” ሸማያ፣ ነህምያ ሊገደል እንደሆነና በቤተ መቅደሱ ውስጥ በመደበቅ ሕይወቱን ሊያተርፍ እንደሚችል ነገረው። ሆኖም ነህምያ ካህን ስላልነበረ በአምላክ ቤት ውስጥ ቢደበቅ ኃጢአት ይሆንበታል። ታዲያ ሕይወቱን ለማዳን ሲል የአምላክን ሕግ ይጥስ ይሆን? ነህምያ “እንደ እኔ ያለ ሰው . . . ሕይወቱን ለማዳን ሲል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ይገባዋልን? አልሄድም!” በማለት መለሰለት። ይህ የአምላክ አገልጋይ በተዘጋጀለት ወጥመድ ውስጥ ያልገባው ለምን ነበር? ሸማያ እስራኤላዊ ቢሆንም “እግዚአብሔር . . . እንዳልላከው” ያውቅ ስለነበረ ነው። ደግሞም እውነተኛ ነቢይ የአምላክን ሕግ እንዲጥስ ፈጽሞ አይመክረውም። በዚህ ጊዜም ቢሆን ነህምያ በክፉ ተቃዋሚዎቹ አልተሸነፈም። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “ቅጥሩም ኤሉል በተባለው ወር ሃያ አምስተኛ ቀን፣ በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጠናቀቀ” ብሎ ሊናገር ችሏል።—ነህምያ 6:10-15፤ ዘኍልቍ 1:51፤ 18:7
ከነሐሴ 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ነህምያ 8–9
“የይሖዋ ደስታ ምሽጋችሁ ነው”
በሚገባ ከታሰበበት ጸሎት የምናገኘው ትምህርት
2 ከላይ የተጠቀሰው ስብሰባ ከመካሄዱ ከአንድ ወር በፊት አይሁዳውያን የኢየሩሳሌምን ግንብ እንደገና ሠርተው አጠናቅቀው ነበር። (ነህ. 6:15) የአምላክ ሕዝቦች ይህን ሥራ ያጠናቀቁት በ52 ቀናት ውስጥ ሲሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ በመንፈሳዊ ረገድ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሟሟላት ላይ ልዩ ትኩረት አደረጉ። በመሆኑም ቲሽሪ በተባለው ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ በአደባባይ ተሰብስበው ዕዝራና ሌሎች ሌዋውያን የአምላክን ቃል ጮክ ብለው ሲያነቡና ሲያብራሩ አዳመጡ። (ሥዕል 1) ሁሉም የቤተሰብ አባላት ይኸውም “ማስተዋል የሚችሉ ሁሉ . . . ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር” ሕጉ ሲነበብ ቆመው ያዳምጡ ነበር። በዛሬው ጊዜ ምቹ በሆኑ የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ለምንሰበሰብ ክርስቲያኖች ይህ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! አንዳንድ ጊዜ ስብሰባ ላይ እያለህ አእምሮህ መባዘንና ያን ያህል አስፈላጊ ስላልሆኑ ጉዳዮች ማሰብ ይጀምራል? ከሆነ የእነዚህን እስራኤላውያን ምሳሌ መለስ ብለህ አስብ፤ ሕዝቡ የሚሰጠውን ትምህርት በማዳመጥ ብቻ ሳይወሰኑ ትምህርቱ ወደ ልባቸው ጠልቆ እንዲገባ አድርገው ነበር፤ በዚህም የተነሳ በብሔር ደረጃ የአምላክን ሕግ ባለማክበር በሠሩት ስህተት ማልቀስ ጀመሩ።—ነህ. 8:1-9
‘በመንፈስ እየኖርክ’ ነው?
9 ደስታ ከልብ የመነጨ የእርካታ ስሜት ነው። ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW፤ መዝሙር 104:31) ኢየሱስም የአባቱን ፈቃድ መፈጸም ያስደስተዋል። (መዝሙር 40:8፤ ዕብራውያን 10:7-9) የይሖዋ ‘ደስታ ለእኛም ብርታታችን ነው።’—ነህምያ 8:10
10 ከአምላክ የሚገኘው ደስታ በመከራ፣ በሐዘንና በስደት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ መለኮታዊውን ፈቃድ በመፈጸም ጥልቅ እርካታ እንድናገኝ ያስችለናል። ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት እጅግ ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል! (ምሳሌ 2:1-5) ከአምላክ ጋር ያለን አስደሳች ዝምድና የተመሠረተው በእሱም ሆነ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባለን እምነትና ስለ እነሱ ባገኘነው ትክክለኛ እውቀት ላይ ነው። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) የዓለም አቀፉ እውነተኛ የወንድማማች ኅብረት አባል መሆን ሌላው የደስታችን ምንጭ ነው። (ሶፎንያስ 3:9፤ ሐጌ 2:7) የመንግሥቱ ተስፋና ምሥራቹን እንድናውጅ የተሰጠን ታላቅ መብት ለደስታችን ምክንያት ይሆኑናል። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14) የዘላለም ሕይወት ተስፋ ያለን መሆኑም ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል። (ዮሐንስ 17:3) እንዲህ የመሰለ ድንቅ ተስፋ ስላለን ‘ፍጹም ደስተኞች መሆን’ ይገባናል።—ዘዳግም 16:15
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 145 አን. 2
አረማይክ
አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ካህኑ ዕዝራ የሕጉን መጽሐፍ በኢየሩሳሌም ለተሰበሰቡት አይሁዳውያን አነበበላቸው፤ በርካታ ሌዋውያንም ለሕዝቡ ማብራሪያ ይሰጡ ነበር፤ ነህምያ 8:8 እንደሚለው “እነሱም ከመጽሐፉ ይኸውም ከእውነተኛው አምላክ ሕግ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማንበብ ሕጉን በግልጽ ያብራሩና ትርጉሙ ምን እንደሆነ ይናገሩ ነበር፤ በዚህ መንገድ የተነበበውን ነገር ማስተዋል እንዲችል ሕዝቡን ይረዱት ነበር።” ይህ ማብራሪያ ወይም ትርጉም የዕብራይስጡን ሐሳብ በአረማይክ መግለጽን ሊያመለክት ይችላል፤ ምክንያቱም ዕብራውያኑ ባቢሎን በነበሩበት ጊዜ አረማይክ መጠቀም ጀምረው ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ማብራሪያው አይሁዳውያኑ ዕብራይስጥ መረዳት ቢችሉም እንኳ የሚነበበው ሐሳብ ያለውን ጥልቅ ትርጉም እንዲገነዘቡ የሚረዳ መሆን አለበት።
ከነሐሴ 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ነህምያ 10–11
“ለይሖዋ ሲሉ መሥዋዕት ከፍለዋል”
ከስሟ ትርጉም ጋር የምትስማማዋ ኢየሩሳሌም
13 በነህምያ ዘመን የታተመው ‘የታመነው ቃል ኪዳን’ የጥንቶቹን የአምላክ ሕዝቦች የኢየሩሳሌም ቅጥር ለሚመረቅበት ቀን አዘጋጅቷቸዋል። ሆኖም ትኩረት የሚያሻው ሌላ አስቸኳይ ጉዳይ ነበር። አሥራ ሁለት በሮች ባሉት ትልቅ ቅጥር የታጠረችው ኢየሩሳሌም ብዙ ነዋሪ ሕዝብ ያስፈልጋት ነበር። አንዳንድ እስራኤላውያን በዚያ ይኖሩ የነበረ ቢሆንም ‘ከተማይቱ ሰፊና ትልቅ ነበረች፤ በውስጥዋ የነበረው ሕዝብ ግን ጥቂት ነበር።’ (ነህምያ 7:4) ይህን ችግር ለመፍታት ሕዝቡ ‘ከአሥሩ ክፍል አንዱ በቅድስቲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም ይቀመጡ ዘንድ ዕጣ ተጣጣሉ።’ ለዚህ ዝግጅት የተሰጠው የፈቃደኝነት ምላሽ ሕዝቡ “በፈቃዳቸው በኢየሩሳሌም ለመቀመጥ የወደዱትን ሰዎች” እንዲባርኩ አነሳስቷቸዋል። (ነህምያ 11:1, 2) የጎለመሰ ክርስቲያን እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ለመዛወር ሁኔታቸው ለሚፈቅድላቸው በጊዜያችን ለሚገኙ እውነተኛ አምላኪዎች ይህ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
w86 2/15 26
እውነተኛው አምልኮ ድል ያደርጋል
ርስታቸውን ትተው ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳቸው የተወሰነ ወጪ የሚያስወጣቸው ከመሆኑም ሌላ የሚያስከትልባቸው ኪሳራ ነበር። በተጨማሪም በከተማዋ የሚኖሩ ሰዎች ለተለያዩ አደገኛ ሁኔታዎች ሊጋለጡ ይችላሉ። ከእነዚህ ሁኔታዎች አንጻር ብዙዎች ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡትን አይሁዳውያን አድንቀዋቸዋል፤ እንዲሁም ይሖዋ እንዲባርካቸው ጸልየውላቸው መሆን አለበት።
በይሖዋ ላይ እምነት ማሳደር የእሱን ሞገስ ያስገኛል
15 ሕይወታችንን ለይሖዋ ስንወስን ራሳችንን ምንም ሳንቆጥብ የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም ተስለናል። ይህን ቃል መጠበቅ የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ እንደሚጠይቅብን እናውቃለን። ይሁንና የማንወደውን ነገር እንድናደርግ ስንጠየቅ፣ የፈቃደኝነት መንፈስ ያለን መሆን አለመሆኑ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። የተጠየቅነውን በማድረግና መሥዋዕትነት በመክፈል ከለመድነው ብሎም ከሚመቸን በተለየ መንገድ አምላክን ስናገለግል እምነት እንዳለን እናሳያለን። የምንከፍለው መሥዋዕት የቱንም ያህል ከባድ ቢሆን፣ ከምናገኘው የላቀ በረከት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም። (ሚል. 3:10) ይሁንና ስለ ዮፍታሔ ልጅስ ምን ማለት ይቻላል?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የነህምያ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
10:34—ሕዝቡ እንጨት ማቅረብ የነበረበት ለምንድን ነው? የሙሴ ሕግ ሕዝቡ የእንጨት መሥዋዕት እንዲያቀርብ አያዝም። እንዲህ ለማድረግ የተገደዱት በወቅቱ በቂ የእንጨት አቅርቦት ስላልነበረ ነው። በመሠዊያው ላይ የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች ለማቃጠል በጣም ብዙ እንጨት ያስፈልግ ነበር። ምናልባትም ናታኒም ተብለው የሚጠሩት እስራኤላዊ ያልሆኑ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች በበቂ መጠን አልነበሩ ይሆናል። ስለዚህ የእንጨት አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ የሚያመጡበትን ጊዜ ለመወሰን ዕጣ ተጣጣሉ።
ከነሐሴ 28–መስከረም 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ነህምያ 12–13
“ጓደኛ ስትመርጡ ለይሖዋ ታማኝ ሁኑ”
it-1 95 አን. 5
አሞናውያን
ጦቢያ ከቤተ መቅደሱ ከተባረረ በኋላ በዘዳግም 23:3-6 ላይ የሚገኘው አሞናውያንና ሞዓባውያን ወደ እስራኤል ጉባኤ መግባት እንደማይፈቀድላቸው የሚገልጸው ሕግ ተነቦ ተግባራዊ ተደረገ። (ነህ 13:1-3) ከ1,000 ዓመታት ገደማ በፊት እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር እየተቃረቡ በነበረበት ወቅት አሞናውያንና ሞዓባውያን እነሱን ለማሳለፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት የተጣለው ይህ እገዳ እነዚህ ሕዝቦች የእስራኤል ብሔር ሕጋዊ አባል መሆንና እንዲህ ያለው አባልነት የሚያስገኘውን መብትና በረከት ማጣጣም እንደማይችሉ የሚያመለክት እንደሆነ እንረዳለን። ይሁንና አሞናዊ ወይም ሞዓባዊ የሆኑ ግለሰቦች ከእስራኤላውያን ጋር መቀላቀልና ከእነሱ ጋር መኖር እንዲሁም በዚህ መንገድ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ከሚፈሰው በረከት መቋደስ እንደማይችሉ የሚያመለክት አይደለም፤ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጼሌቅ ከዳዊት ኃያላን ተዋጊዎች መካከል መካተቱ እንዲሁም ስለ ሞዓባዊቷ ሩት የሚገልጸው ዘገባ ይህን ያሳያል።—ሩት 1:4, 16-18
ተቀድሳችኋል
5 ነህምያ 13:4-9ን አንብብ። ርኩስ በሆኑ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ነገሮች ስለተከበብን ቅድስናችንን ጠብቀን መቀጠል ቀላል አይደለም። የኤልያሴብን እና የጦብያን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኤልያሴብ ሊቀ ካህን ነበር፤ ጦብያ ደግሞ አሞናዊ ሲሆን በይሁዳ ባለው የፋርስ አስተዳደር ውስጥ ያገለግል የነበረ ይመስላል። ጦብያና አጋሮቹ፣ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ይቃወሙ ነበር። (ነህ. 2:10) የአምላክ ሕግ አሞናውያን ወደ ቤተ መቅደሱ እንዳይገቡ ይከለክላል። (ዘዳ. 23:3) ታዲያ ሊቀ ካህኑ፣ እንደ ጦብያ ዓይነት ሰው በቤተ መቅደሱ ዕቃ ቤት ውስጥ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?
6 ጦብያ የኤልያሴብ የቅርብ ወዳጅ ነበር። ጦብያ እና ልጁ የሆሐናን አይሁዳውያን ሴቶችን ያገቡ ሲሆን በርካታ አይሁዳውያን ስለ ጦብያ መልካምነት ያወሩ ነበር። (ነህ. 6:17-19) ከኤልያሴብ የልጅ ልጆች አንዱ፣ የሰማርያ ገዥና የጦብያ የቅርብ ጓደኛ የሆነውን የሰንባላጥን ልጅ አግብቶ ነበር። (ነህ. 13:28) ኤልያሴብ፣ ይሖዋን የማያመልክ እንዲያውም ተቃዋሚ የሆነ ሰው ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት የፈቀደው ከላይ ከተጠቀሱት ሰዎች ጋር ባለው ቅርርብ የተነሳ ሊሆን ይችላል። ነህምያ ግን የጦብያን የቤት ዕቃዎች በሙሉ ከቤተ መቅደሱ አውጥቶ በመጣል ለይሖዋ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል።
ታማኝነት የሚያስከትለውን ፈተና መቋቋም
6 ለይሖዋ ታማኞች ከሆንን የእርሱ ጠላቶች ከሆኑት ሰዎች ጋር ከመወዳጀት እንቆጠባለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “አመንዝሮች ሆይ፣ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው። (ያዕቆብ 4:4) ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? ስለ ጠላቶችህም የተሰቀቅሁ አይደለሁምን? ፍጹም ጥል ጠላኋቸው፣ ጠላቶችም ሆኑኝ” በማለት በተናገረበት ወቅት ያሳየው ታማኝነት እንዲኖረን እንፈልጋለን። (መዝሙር 139:21, 22) ሆን ብለው ኃጢአት ከሚሠሩ ሰዎች ጋር አንዳችም ኅብረት ስለሌለን ከእነርሱ ጋር ለመወዳጀት አንፈልግም። ለይሖዋ ታማኞች መሆናችን እንደነዚህ ካሉት የይሖዋ ጠላቶች ጋር በግል ወይም በቴሌቪዥን ከመገናኘት እንድንቆጠብ አያደርገንምን?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 452 አን. 9
ሙዚቃ
በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለመዝሙር ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። ዘማሪዎቹ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ መጠቀሳቸው እንዲሁም ሥራቸውን በሙሉ ልብ ማከናወን ይችሉ ዘንድ ሌዋውያን ከሚያከናውኗቸው “ሌሎች ሥራዎች ነፃ እንዲሆኑ” መደረጉ ይህን ያሳያል። (1ዜና 9:33) ከባቢሎን ከተመለሱት ሰዎች መካከል ለብቻቸው መጠቀሳቸው እንደ ልዩ የሌዋውያን ቡድን ሆነው መቆጠራቸውን እንደቀጠሉ ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ዕዝራ 2:40, 41) ፋርሳዊው ንጉሥ አርጤክስስ (ሎንጊማነስ) እንኳ ሥልጣኑን በመጠቀም እነሱና ሌሎች ልዩ ቡድኖች “ቀረጥ፣ ግብር ወይም የኬላ ቀረጥ” እንዳይጣልባቸው ትእዛዝ ሰጥቷል። (ዕዝራ 7:24) በኋላም ንጉሡ “ለዘማሪዎቹ በየዕለቱ የሚያስፈልገውን ነገር በማቅረብ ረገድም ቋሚ የሆነ ዝግጅት” እንዲኖር አድርጎ ነበር። ይህን ትእዛዝ ያወጣው አርጤክስስ እንደሆነ ቢገለጽም መመሪያውን ያስተላለፈው ዕዝራ ሳይሆን አይቀርም፤ ይህንንም ያደረገው አርጤክስስ የሰጠውን ሥልጣን መሠረት በማድረግ ነው። (ነህ 11:23፤ ዕዝራ 7:18-26) በመሆኑም ዘማሪዎቹ በሙሉ ሌዋውያን ቢሆኑም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ “ዘማሪዎቹና ሌዋውያኑ” በማለት እንደ ልዩ ቡድን የሚጠቅሳቸው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።—ነህ 7:1፤ 13:10