የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2023 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከኅዳር 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 13–14
“ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል?”
የሰው ልጅ ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚያደርገው ጥረት
ምንም እንኳ 3,500 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት የተጻፈ ቢሆንም ስለ ሕይወት አጭርነት በሚገልጸው በዚህ ሐሳብ ዛሬ አብዛኛው ሰው ይስማማል። ሰዎች ሕይወትን ገና በወጉ አጣጥመው ሳይጨርሱ የሚያረጁበትና የሚሞቱበት ምክንያት ፈጽሞ ሊዋጥላቸው አልቻለም። በዚህም የተነሳ ሕይወት ያራዝማሉ የሚባሉ እጅግ በርካታ የሆኑ ዘዴዎች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሲሞከሩ ቆይተዋል።
በኢዮብ ዘመን የነበሩ ግብፃውያን የእንስሳ ቆለጥ በመብላት ወደ ወጣትነት ለመመለስ ያደረጉት ሙከራ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል። የመካከለኛው ዘመን ኬሚስትሪ ዋና ዓላማ ሕይወት ሊያራዝም የሚችል ንጥረ ነገር ማግኘት ነበር። የመካከለኛው ዘመን ኬሚስቶች ሰው ሠራሽ የሆነ ወርቅ ያለመሞትን ባሕርይ ያላብሳል እንዲሁም በወርቅ ሳህን መብላት ዕድሜን ያራዝማል ብለው ያምኑ ነበር። ጥንታዊ ቻይናውያን ታኦይስቶች እንደ ማሰላሰል፣ የአተነፋፈስ ልምምድ ማድረግና ጥሩ የአመጋገብ ሥርዓትን የመሰሉ ዘዴዎችን መጠቀም የሰውነትን ኬሚካላዊ ሂደት ለመለወጥና ዘላለማዊነትን ለማግኘት ያስችላል የሚል እምነት ነበራቸው።
ስፔናዊው አሳሽ ጁዋን ፖንክ ደ ሊዮን የወጣትነትን ምንጭ ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት እንደነበረው ይነገርለታል። አንድ የ18ኛው መቶ ዘመን ሐኪም ሄርሚፐስ ሪዳይቪቨስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በጸደይ ወቅት ወጣት ልጃገረዶች በጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲቀመጡ ከተደረገ በኋላ ትንፋሻቸው በጠርሙሶች ቢሰበሰብ ለሕይወት ማራዘሚያነት ሊያገለግል እንደሚችል ሐሳብ ሰጥተው ነበር። ያም ሆነ ይህ ከእነዚህ ዘዴዎች ውስጥ አንዱም የተሳካ ውጤት አላስገኘም።
ዛፍ ቢቆረጥ መልሶ ሊያቆጠቁጥ ይችላል?
በሊባኖስ ከሚገኘውና ግርማ ሞገስ ካለው አርዘ ሊባኖስ ጋር ሲወዳደር ጉጥ የበዛበትና ጥምም ያለው የወይራ ዛፍ ያን ያህል ላይማርክ ይችላል። ይሁን እንጂ የወይራ ዛፍ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታን የመቋቋም አስደናቂ ችሎታ አለው። አንዳንድ የወይራ ዛፎች የ1,000 ዓመት ዕድሜ እንዳላቸው ይገመታል። የወይራ ዛፍ ሥሩን በስፋት ስለሚዘረጋ ግንዱ ቢደርቅም እንኳ ዛፉ ሊያንሠራራ ይችላል። ሥሮቹ እስካልሞቱ ድረስ ዛፉ እንደገና ያቆጠቁጣል።
ኢዮብ፣ ቢሞትም እንኳ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር እንደሚችል እርግጠኛ ነበር። (ኢዮብ 14:13-15) ኢዮብ፣ አምላክ ከሞት እንደሚያስነሳው ያለውን እምነት ለመግለጽ ዛፍ ምናልባትም የወይራ ዛፍ እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። “ዛፍ እንኳ ተስፋ አለውና። ቢቆረጥ መልሶ ያቆጠቁጣል” በማለት ተናግሯል። ከከባድ ድርቅ በኋላ ዝናብ ሲጥል፣ ደርቆ የነበረ የወይራ ዛፍ ጉቶ እንደገና ሊያንሰራራ ይችላል፤ ከዛፉ ሥሮች ላይ ቀንበጥ ማቆጥቆጥ ስለሚጀምር ዛፉ “እንደ አዲስ [ተክል] ቅርንጫፎች ያወጣል።”—ኢዮብ 14:7-9
“የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ”
ኢዮብ የተናገራቸው ቃላት ይሖዋ ምን ያህል አፍቃሪ እንደሆነ ያስተምሩናል፦ ይሖዋ በእሱ ዘንድ ተፈላጊ የሆኑ ሰዎች ተደርገው እንዲቀረጹ በእጁ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ልዩ ዝምድና ይመሠርታል። (ኢሳይያስ 64:8) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደ ውድ ሀብት አድርጎ ይመለከታቸዋል። በሞት ያንቀላፉ ታማኝ አገልጋዮቹን ‘ይናፍቃቸዋል።’ አንድ ምሑር እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “የመናፈቅን ከፍተኛ ደረጃ ለመግለጽ ከሚያገለግሉት ቃላት መካከል አንዱ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም” ብለዋል። አዎን፣ ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚያስታውስ ከመሆኑም በላይ እነሱን ከሞት ለማስነሳትም ከፍተኛ ጉጉት አለው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 191
አመድ
አመድ የማይረባ ወይም ዋጋ የሌለው ነገርን ለማመልከትም ተሠርቶበታል። ለምሳሌ አብርሃም በይሖዋ ፊት “እኔ ትቢያና አመድ [ነኝ]” በማለት ተናግሯል። (ዘፍ 18:27፤ በተጨማሪም ኢሳ 44:20፤ ኢዮብ 30:19ን ተመልከት።) ኢዮብም የሐሰት አጽናኞቹ የተናገሯቸውን ነገሮች “የአመድ ምሳሌዎች” በማለት ጠርቷቸዋል።—ኢዮብ 13:12 ግርጌ
ከኅዳር 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 15–17
“ሌሎችን ስናጽናና ምን ማድረግ እንደሌለብን ከኤሊፋዝ እንማራለን”
መጥፎ አስተሳሰብን ተዋጉ!
ኤልፋዝ በሦስቱም ንግግሮቹ ላይ አምላክ ከአገልጋዮቹ ብዙ ነገር ስለሚጠብቅ በሚያደርጉት ነገር አይደሰትም የሚል ሐሳብ አቅርቧል። ኤልፋዝ ለኢዮብ ‘እግዚአብሔር በአገልጋዮቹ ላይ እምነት አይጥልም፣ መላእክቱንም በስህተታቸው ይወቅሳቸዋል’ ብሎታል። (ኢዮብ 4:18) ቆየት ብሎም “እግዚአብሔር በቅዱሳኑ እንኳ አይታመንም፤ ሰማያትም በእርሱ ፊቱ ንጹሓን አይደሉም” ብሏል። (ኢዮብ 15:15) “አንተ ጻድቅ ብትሆን ሁሉን የሚችለውን አምላክ ምን ደስ ታሰኘዋለህ?” በማለትም ጠይቆታል። (ኢዮብ 22:3) በልዳዶስም ይህን ሐሳብ በመጋራት ‘በፊቱ ጨረቃ እንኳ ብሩህ አይደለችም፣ ከዋክብትም ንጹሓን አይደሉም’ በማለት አክሎ ተናገረ።—ኢዮብ 25:5
እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያደርግብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይህ ካልሆነ አምላክ ከእኛ በጣም ብዙ ነገር እንደሚፈልግ አድርገን ወደ ማሰብ ሊመራን ይችላል። ይህ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና ያበላሸዋል። ከዚህም በላይ፣ እንዲህ ባለው አመለካከት ከተሸነፍን አስፈላጊ የሆነ ተግሣጽ ቢሰጠን እንኳ የምንሰጠው ምላሽ ምን ይሆናል? የተሰጠንን ተግሣጽ በትሕትና ከመቀበል ይልቅ ልባችን ‘በእግዚአብሔር ላይ ማማረር’ ሊጀምርና በእርሱ ቅር ልንሰኝ እንችላለን። (ምሳሌ 19:3) ይህ ደግሞ አስከፊ መንፈሳዊ አደጋ ያስከትልብናል!
ኢየሱስን በትሕትናውና በርኅራኄው ምሰሉት
16 ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት ንግግራችን፦ ለሌሎች ከርኅራኄ የመነጨ አሳቢነት ካለን ‘የተጨነቁትን ነፍሳት ለማጽናናት’ እንነሳሳለን። (1 ተሰ. 5:14) እንዲህ ያሉ ሰዎችን ለማበረታታት ምን ማለት እንችላለን? ከልባችን እንደምናስብላቸው በመግለጽ መንፈሳቸው እንዲታደስ እናደርጋለን። ከልብ እንደምናደንቃቸው በመናገር መልካም ባሕርያትና ችሎታዎች እንዳሏቸው እንዲያስተውሉ ማድረግ ይቻላል። ይሖዋ ወደ ልጁ የሳባቸው ውድ እንደሆኑ አድርጎ ስለሚመለከታቸው እንደሆነ ልናስታውሳቸው እንችላለን። (ዮሐ. 6:44) እንዲሁም ይሖዋ “ልባቸው ለተሰበረ” ወይም ‘መንፈሳቸው ለተሰበረ’ አገልጋዮቹ በጥልቅ እንደሚያስብ በእርግጠኝነት እንግለጽላቸው። (መዝ. 34:18) በርኅራኄ የምንናገረው ነገር ማጽናኛ ለሚፈልጉ ሰዎች ፈውስ ሊያስገኝላቸው ይችላል።—ምሳሌ 16:24
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የኢዮብ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
7:9, 10፤ 10:21፤ 16:22—እነዚህ ጥቅሶች ኢዮብ በትንሣኤ እንደማያምን ያሳያሉ? እነዚህ ጥቅሶች ኢዮብ በቅርብ የሚያጋጥመውን ሁኔታ አስመልክቶ የተናገራቸው ሐሳቦች ናቸው። ታዲያ ምን ማለቱ ነበር? እንደዚህ ያለው ቢሞት በዘመኑ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳቸውም እንደማያዩት ለማመልከት ሊሆን ይችላል። በእነርሱ አስተሳሰብ እርሱ ወደ ቤቱ በፍጹም አይመለስም አሊያም አምላክ የወሰነው ጊዜ እስኪመጣ ድረስ የሚያውቀው አይኖርም። ወይም ደግሞ ኢዮብ ይህን ሲናገር በራሱ ጥረት ከሲኦል መውጣት የሚችል ሰው የለም ማለቱ ይሆናል። ኢዮብ ወደ ፊት ትንሣኤ እንደሚኖር ያምን እንደነበር ኢዮብ 14:13-15 በግልጽ ያሳያል።
ከኅዳር 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 18–19
“የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ፈጽሞ አትተዉአቸው”
ኢየሱስ እንባውን ማፍሰሱ ምን ያስተምረናል?
9 ሐዘን የደረሰባቸውን መደገፍ ትችላለህ። ኢየሱስ ከማርታና ከማርያም ጋር አልቅሷል፤ ከዚህም በተጨማሪ አዳምጧቸዋል እንዲሁም በሚያጽናና መንገድ አነጋግሯቸዋል። እኛም ሐዘን ለደረሰባቸው ይህን ማድረግ እንችላለን። በአውስትራሊያ የሚኖር ዳን የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴን በሞት ካጣሁ በኋላ የሌሎች ድጋፍ አስፈልጎኝ ነበር። ብዙ ባለትዳሮች ቀንም ሆነ ማታ ጊዜያቸውን ሰጥተው ያዳምጡኝ ነበር። ሐዘኔን እንድገልጽ አጋጣሚ ሰጥተውኛል፤ ማልቀሴም አላሳፈራቸውም። ከዚህ በተጨማሪ ተግባራዊ እርዳታ ለማድረግ ራሳቸውን ያቀርቡ ነበር። ለምሳሌ እኔ እንደማልችል በሚሰማኝ ጊዜ መኪናዬን ያጥቡልኝ፣ አስቤዛ ይገዙልኝ እንዲሁም ምግብ ያበስሉልኝ ነበር። ደግሞም ብዙ ጊዜ አብረውኝ ይጸልዩ ነበር። እውነተኛ ወዳጆች እንዲሁም ‘ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም’ ሆነውልኛል።”—ምሳሌ 17:17
የቤተሰባችሁ አባል ይሖዋን ሲተው
16 ታማኝ የሆኑትን የቤተሰብ አባላት ማበረታታታችሁን አታቋርጡ። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በዚህ ወቅት የእናንተ ፍቅርና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። (ዕብ. 10:24, 25) የቤተሰባቸው አባል የተወገደባቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ጉባኤው እነሱንም ጭምር እንዳገለላቸው የተሰማቸው ጊዜ አለ። እነዚህ ክርስቲያኖች እንዲህ እንዲሰማቸው ልናደርግ አይገባም። በተለይም እውነትን የተዉ ወላጆች ያሏቸው ወጣቶች ምስጋናና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ማሪያ ባለቤቷ የተወገደ ከመሆኑም ሌላ ቤተሰቡን ጥሎ ሄዷል፤ ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጓደኞቼ ወደ ቤቴ መጥተው ምግብ ያበስሉ እንዲሁም አብረውን የቤተሰብ ጥናት ያደርጉ ነበር። ሐዘኔን ተጋርተውኛል፤ እንዲሁም አብረውኝ አልቅሰዋል። ስለ እኔ አሉባልታ ሲናፈስ ጥብቅና ቆመውልኛል። እነዚህ ወዳጆቼ በእጅጉ አበረታተውኛል!”—ሮም 12:13, 15
w90 9/1 22 አን. 20
የአገልግሎት መብቶችን ለማግኘት እየተጣጣርክ ነው?
20 ቀደም ሲል የጉባኤ ሽማግሌ ወይም አገልጋይ የነበረ ሰው መብቱን ያጣው በገዛ ፈቃዱ ቢሆንም እንኳ የሽማግሌዎች አካል ሁኔታው በወንድም ላይ ውጥረት ሊፈጥርበት እንደሚችል ሊገነዘብ ይገባል። ግለሰቡ ከጉባኤ ካልተወገደና ሽማግሌዎች በጭንቀት እንደተዋጠ ካስተዋሉ በፍቅር ተነሳስተው መንፈሳዊ እርዳታ ሊያደርጉለት ይገባል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) በጉባኤው ውስጥ እንደሚፈለግ እንዲሰማው ሊያደርጉ ይገባል። ግለሰቡ ምክር አስፈልጎት የነበረ ቢሆንም ትሑትና አመስጋኝ እስከሆነ ድረስ ብዙም ሳይቆይ በጉባኤው ውስጥ ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶችን ሊያገኝ ይችላል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
መልካም ቃል ያለው ኃይል
ይሁን እንጂ ኢዮብ ራሱ ማበረታቻ ባስፈለገው ጊዜ ኤልፋዝና ጓደኞቹ መልካም ቃል በመናገር አላበረታቱትም። ኢዮብ አንዳንድ የተሰወሩ ጥፋቶችን ሠርቶ ይሆናል በማለት ለደረሰበት መከራ ጥፋተኛው እሱ እንደሆነ ተናገሩ። (ኢዮብ 4:8) ዘ ኢንተርፕሬተርስ ባይብል እንዲህ በማለት አስተያየቱን ይሰጣል፦ “ኢዮብ ያስፈልገው የነበረው ነገር በርኅራኄ የተሞላ ልብ ነበር። ከሌሎች ያገኘው ግን ሙሉ በሙሉ ‘እውነት’ ተደርገው የቀረቡ አሰልቺ ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ሐሳቦችን ነበር።” ኢዮብ የኤልፋዝንና የጓደኞቹን ንግግር ሰምቶ በጣም በመበሳጨቱ እንደሚከተለው ለማለት ተገዷል፦ “ነፍሴን የምትነዘንዙ፣ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው?”—ኢዮብ 19:2
አሳቢነትና ደግነት በጎደላቸው አነጋገሮቻችን የተነሣ አብሮን አምላክን የሚያገለግለውን ሰው ማሳዘን በፍጹም አይገባንም። (ከዘዳግም 24:15 ጋር አወዳድር።) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የምትናገረው ነገር ሕይወትን ሊያድን ወይም ሊያጠፋ ይችላል፤ ስለዚህ የንግግርህን ውጤት መቀበል ይኖርብሃል” በማለት ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 18:21 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን
ከኅዳር 27–ታኅሣሥ 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 20–21
“ጽድቅ የሚለካው በሀብት ብዛት አይደለም”
‘በአምላክ ዘንድ ሀብታም’ ነህ?
12 ኢየሱስ በሰጠው ንግግር ላይ በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን ለራስ ቁሳዊ ሀብት ከማከማቸት ወይም ራስን በቁሳዊ ነገሮች ከማበልጸግ ጋር ተነጻጽሯል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ በሕይወታችን ውስጥ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ቁሳዊ ሀብት ማከማቸት ወይም በንብረታችን መደሰት መሆን እንደሌለበት እየተናገረ ነበር። ከዚህ ይልቅ ሀብታችንን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማሻሻል ወይም ለማጠናከር ልንጠቀምበት ይገባል። ይህን ማድረጋችን በአምላክ ዘንድ ሀብታም እንደሚያደርገን ጥርጥር የለውም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ከአምላክ የተትረፈረፈ በረከት እንድናገኝ መንገድ ስለሚከፍት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” ይላል።—ምሳሌ 10:22
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በሰይጣንና በሥራዎቹ ላይ ድል መቀዳጀት
19 የአምላክ አገልጋይ የነበረው ኢዮብ ሰይጣን በኤልፋዝና በሶፋር በኩል የሚያሳየውን ‘የሚያስጨንቅ ቅዠት’ መቋቋም አስፈልጎት እንደነበረ ማወቁ ትኩረትን የሚስብ ነገር ነው። (ኢዮብ 4:13–18፤ 20:2, 3 የ1980 ትርጉም) ኢዮብ አእምሮውን ስለነካው “የሚያስደነግጥ” ነገር ‘ትዕግሥት የጎደለው ንግግር’ በመናገሩ ‘በሐዘን’ ተሠቃይቷል። (ኢዮብ 6:2–4፤ 30:15, 16 የ1980 ትርጉም) ኤሊሁ ኢዮብን ጸጥ ብሎ አዳመጠውና ይሖዋ ስለ ነገሮች ያለውን ሁሉንም ነገር ግምት ውስጥ የሚያስገባ አመለካከት እንዲያስተውል ከልቡ ረዳው። ዛሬም በተመሳሳይ የሰውን ችግር የሚረዱ ሽማግሌዎች ተጨማሪ ‘ሸክም’ ባለመጨመር በሐሳብ ለሚሠቃዩ ሰዎች እንደሚያስቡ ያሳያሉ። ከዚህ ይልቅ ልክ እንደ ኤሊሁ በትዕግሥት ያዳምጧቸዋል፤ ከዚያም እፎይታ በሚሰጥ ዘይት ይኸውም በአምላክ ቃል ተጠቅመው ያረጋጓቸዋል። (ኢዮብ 33:1–3, 7፤ ያዕቆብ 5:13–15) ስለዚህ ስሜቱ እውነተኛ በሆነ ተሞክሮም ሆነ በቅዠት የስሜት ቀውስ የተረበሸ ወይም ደግሞ እንደ ኢዮብ ‘በሕልምና በቅዠት የተረበሸ’ ሰው ፈዋሽ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማጽናኛ በጉባኤው ውስጥ ማግኘት ይችላል።—ኢዮብ 7:14 የ1980 ትርጉም፤ ያዕቆብ 4:7
ከታኅሣሥ 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 22–24
“ሰው አምላክን ሊጠቅመው ይችላል?”
መጥፎ አስተሳሰብን ተዋጉ!
አምላክ ከፍጡራኑ ብዙ ይጠብቃል የሚለው አመለካከት ሰዎችን እንደማይረቡ አድርጎ ይመለከታቸዋል ከሚለው አስተሳሰብ ጋር በጣም ይዛመዳል። ኤልፋዝ በሦስተኛ ንግግሩ ላይ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርቧል፦ “ሰው እግዚአብሔርን ሊጠቅም ይችላልን? ጠቢብ እንኳ ቢሆን ምን ይጠቅመዋል?” (ኢዮብ 22:2) ኤልፋዝ፣ ሰው ለአምላክ ምንም አይጠቅመውም ማለቱ ነበር። በተመሳሳይም በልዳዶስ “ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ይሆን ዘንድ፣ ከሴትስ የተወለደ ንጹሕ ይሆን ዘንድ ይችላልን?” በማለት የመከራከሪያ ሐሳብ አቅርቧል። (ኢዮብ 25:4) በዚህ አባባል መሠረት ሟች የሆነው ኢዮብ በአምላክ ዘንድ ንጹሕ አቋም ይኖረኛል ብሎ እንዴት ሊያስብ ይችላል?
ዛሬ ብዙ ሰዎች ስለ ራሳቸው ባላቸው አፍራሽ አስተሳሰብ የተነሳ ይሠቃያሉ። ለዚህ መንስኤ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ አስተዳደግ፣ የኑሮ ውጣ ውረድ ወይም የዘር አሊያም የጎሳ ጥላቻ ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላ በኩል ሰይጣንና አጋንንቱ አንድ ሰው ተስፋ ሲቆርጥ ሲመለከቱ ደስ ይሰኛሉ። አንድ ሰው የፈለገውን ነገር ቢያደርግ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ሊያስደስተው እንደማይችል እንዲሰማው ማድረግ ከቻሉ ግለሰቡ በከንቱነት ስሜት የመሸነፉ አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል። ከጊዜ በኋላ እንዲህ ያለው ግለሰብ ከሕያው አምላክ ሊርቅ ብሎም ሊኮበልል ይችላል።—ዕብራውያን 2:1፤ 3:12
የዕድሜ መግፋትና የጤና ችግሮች አቅማችንን ሊገድቡብን ይችላሉ። ወጣት፣ ጤነኛና ጠንካሮች ሳለን እናደርገው ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አሁን በመንግሥቱ አገልግሎት የምናበረክተው ድርሻ ከቁጥር የማይገባ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ይሁን እንጂ ሰይጣንና አጋንንቱ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት በቂ አይደለም ብለን እንድናስብ እንደሚፈልጉ ማወቃችን በጣም ይጠቅመናል! እንዲህ ያለውን አመለካከት መዋጋት አለብን።
ችግሮችን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል የሚገልጽ ትምህርት
ከዚህም ሌላ ሦስቱ ጓደኞች ከአምላክ ጥበብ ይልቅ የግል አመለካከታቸውን በመግለጽ ኢዮብን ተስፋ አስቆርጠውታል። ኤልፋዝ አምላክ ‘በአገልጋዮቹ ስለማይታመን’ ኢዮብ ጻድቅ ሆነ አልሆነ ለይሖዋ ለውጥ አያመጣም እስከ ማለት ደርሷል። (ኢዮብ 4:18፤ 22:2, 3) ከዚህ የበለጠ ተስፋ አስቆራጭ ወይም ፈጽሞ ከእውነት የራቀ አስተያየት ይኖራል ብሎ መገመት ያዳግታል! ይሖዋ መጨረሻ ላይ ስለዚህ ስድብ ኤልፋዝንና ጓደኞቹን መውቀሱ አያስደንቅም። “እናንተ ስለ እኔ ትክክል የሆነውን ነገር አልተናገራችሁም” አላቸው። (ኢዮብ 42:7 የ1980 ትርጉም) ይሁን እንጂ ይበልጥ የሚጎዳው ከዚያ ቀጥሎ የተናገሩት ነው።
የይሖዋን ልብ ደስ የሚያሰኙ ወጣቶች
10 የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው ሰይጣን ጥያቄ ውስጥ የጣለው የኢዮብን ታማኝነት ብቻ ሳይሆን የአንተንም ሆነ የሌሎች የአምላክ አገልጋዮችን ታማኝነት ጭምር ነው። እንዲያውም ሰይጣን መላውን የሰው ዘር በሚመለከት “ሰው [ኢዮብ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሰው] ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል” በማለት ለይሖዋ ተናግሯል። (ኢዮብ 2:4) ይህ አከራካሪ ጉዳይ አንተንም የሚመለከት እንደሆነ ትገነዘባለህ? በምሳሌ 27:11 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ለሚሰድበው ለሰይጣን መልስ መስጠት ይችል ዘንድ ለእርሱ ልታደርግለት የምትችለው ነገር እንዳለ ገልጿል። እስቲ አስበው፣ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እስከ ዛሬ ከተነሱት አከራካሪ ጉዳዮች ሁሉ በሚበልጠው በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ እንድትሰጥ ለአንተም ግብዣ አቅርቦልሃል። እንዴት ያለ ትልቅ ኃላፊነትና መብት አግኝተሃል! ይሖዋ የሚፈልግብህን ማድረግ ትችላለህ? ኢዮብ ለጥያቄው መልስ ሰጥቷል። (ኢዮብ 2:9, 10) ኢየሱስም ሆነ በርካታ ወጣቶችን ጨምሮ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የኖሩ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሌሎች የአምላክ አገልጋዮችም መልስ ሰጥተዋል። (ፊልጵስዩስ 2:8፤ ራእይ 6:9) አንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ። በዚህ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ አቋም መያዝ ይቻላል ብለህ አታስብ። ሰይጣን ለሚሰነዝረው ስድብ ወይም ደግሞ ይሖዋ ለሚያቀርበው መልስ ድጋፍ እንደምትሰጥ በአኗኗርህ ታሳያለህ። ታዲያ የቱን ትመርጣለህ?
ይሖዋ ስለ አንተ ያስባል!
11 የምታደርገው ምርጫ ለይሖዋ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራልን? ይሖዋ ለሰይጣን አጥጋቢ መልስ መስጠት እንዲችል እስከ ዛሬ ድረስ በታማኝነት ያገለገሉት ሰዎች በቂ አይደሉም? እርግጥ ዲያብሎስ ይሖዋን ከፍቅር ተነሳስቶ የሚያገለግል ሰው አይገኝም በማለት ያነሳው ግድድር ውሸት መሆኑ ተረጋግጧል። ይሁንና ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ስለሚያስብልህ ሉዓላዊነትን በተመለከተ በተነሳው ጥያቄ ከእርሱ ጎን እንድትቆም ይፈልጋል። ኢየሱስ “ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 18:14
12 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የምትመርጠው የሕይወት ጎዳና ይሖዋን ያሳስበዋል። ከዚህም በላይ የምታደርገው ምርጫ በቀጥታ ይመለከተዋል። ሰዎች በሚያደርጉት ጥሩም ሆነ መጥፎ ተግባር የይሖዋ ስሜት በጥልቅ እንደሚነካ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ባመፁበት ጊዜ ይሖዋ ‘አዝኗል።’ (መዝሙር 78:40, 41) በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ በፊት ‘የሰው ክፋት በምድር ላይ በመብዛቱ’ ይሖዋ ‘በልቡ አዝኖ’ ነበር። (ዘፍጥረት 6:5, 6) ይህ ምን ማለት እንደሆነ ተመልከት። አካሄድህ መጥፎ ከሆነ ፈጣሪህን ታሳዝነዋለህ። እንዲህ ሲባል አምላክ ውስጣዊ ጥንካሬ ይጎድለዋል ወይም ስሜታዊ ነው ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይወድሃል እንዲሁም ስለ ደኅንነትህ ያስባል። በሌላ በኩል ትክክል የሆነውን ስታደርግ ይሖዋ ደስ ይሰኛል። የሚደሰተው ለሰይጣን መልስ መስጠት የሚያስችለው ተጨማሪ ምክንያት በማግኘቱ ብቻ ሳይሆን አንተንም ለመካስ የሚያስችል አጋጣሚ በማግኘቱ ነው። እንዲህ ማድረግ ያስደስተዋል። (ዕብራውያን 11:6) ይሖዋ አምላክ ምንኛ አፍቃሪ አባት ነው!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ፈጣሪህን ለማክበር መንፈሳዊ ግቦች አውጣ
ይሖዋ አጽናፈ ዓለምን እንዴት እንደፈጠረ ተመልከት። “መሸ፤ ነጋም” የሚሉት ቃላት ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹን ለማከናወን ተከታታይ ክፍለ ጊዜያት እንደወሰነ ያሳያሉ። (ዘፍጥረት 1:5, 8, 13, 19, 23, 31) ይሖዋ በእያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ መጀመሪያ ላይ በዚያ ቀን ለማከናወን ያወጣው በግልጽ የተቀመጠ ግብ ወይም ዓላማ ነበረው። ደግሞም አምላክ ለመፍጠር ያሰባቸውን ነገሮች በሚገባ አከናውኗል። (ራእይ 4:11) ኢዮብ “እርሱ [ይሖዋ] የፈቀደውን ያደርጋል” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 23:13) ይሖዋ “ያደረገውን ሁሉ” አይቶ “እጅግ መልካም” እንደሆነ በተናገረ ጊዜ በሥራው በጣም ረክቶ መሆን አለበት!—ዘፍጥረት 1:31
እኛም ግባችን እውን እንዲሆን ውጥናችንን ከዳር የማድረስ ከፍተኛ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። እንዲህ ያለ ጠንካራ ፍላጎት ለማዳበር ምን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋ ምድር ቅርጽ አልባና ባዶ በነበረችበት ወቅት እንኳ ለእርሱ ክብርና ምስጋና የምታመጣ ውብ እንቁ ሆና ትታየው ነበር። እኛም በተመሳሳይ እቅዳችንን ዳር ማድረሳችን በሚያስገኝልን ውጤትና ጥቅም ላይ ማሰላሰላችን ግባችንን ለመምታት ያለንን ፍላጎት ያሳድግልናል። የ19 ዓመቱ ቶኒ ይህን የመሰለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። በምዕራብ አውሮፓ የሚገኝን አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በጎበኘበት ወቅት የተሰማውን ስሜት ፈጽሞ አይረሳውም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‘ያን በመሰለ ቦታ መኖርና መሥራት ምን ይመስል ይሆን?’ የሚል ጥያቄ በአእምሮው ይጉላላ ነበር። ቶኒ ቤቴል ስለመግባት ማሰቡን አላቆመም፤ እንዲያውም እዚያ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰዱን ቀጠለ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በቅርንጫፍ ቢሮው ለማገልገል ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝ በጣም ተደሰተ!
ከታኅሣሥ 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 25–27
“ንጹሕ አቋምን ለመጠበቅ ፍጹም መሆን አያስፈልግም”
it-1 1210 አን. 4
ንጹሕ አቋም
ኢዮብ። ከዮሴፍ ሞት በኋላና ከሙሴ ዘመን በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደኖረ የሚታሰበው ኢዮብ፣ “በንጹሕ አቋም የሚመላለስ [ዕብ. ታም] ቅን ሰው እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” ተብሎ ተጠርቷል። (ኢዮብ 1:1፤ ኢዮብ የሚለውን ተመልከት።) መላእክት በሰማይ በይሖዋ ፊት በተሰበሰቡበት ጊዜ የአምላክ ጠላት ሰይጣንም በቦታው ተገኝቶ የነበረ ሲሆን ይሖዋ በወቅቱ ኢዮብን በተመለከተ ለሰይጣን ያነሳለት ጥያቄ በይሖዋ አምላክና በሰይጣን መካከል የተነሳው አከራካሪ ጉዳይ ከሰው ልጆች ንጹሕ አቋም ጠባቂነት ጋርም የተያያዘ እንደሆነ ይጠቁማል። ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው በንጹሕ ልብ ለእሱ በማደር ሳይሆን ለግል ጥቅሙ ሲል እንደሆነ በመግለጽ ኢዮብ አምላክን የሚያመልከው በትክክለኛው ውስጣዊ ግፊት ተነሳስቶ እንዳልሆነ ጠቁሟል። በዚህ መንገድ፣ ኢዮብ ለአምላክ ባለው ታማኝነት ላይ ጥያቄ አንስቷል። ሰይጣን ኢዮብ የነበረውን ከፍተኛ ሀብት፣ ሌላው ቀርቶ ልጆቹን ጭምር እንዲነጥቀው ቢፈቀድለትም የኢዮብን ንጹሕ አቋም ማላላት ሳይችል ቀርቷል። (ኢዮብ 1:6–2:3) ይህ ሳይሳካለት ሲቀር፣ ሰይጣን ኢዮብ ራስ ወዳድ እንደሆነና በራሱ ላይ ምንም እስካልደረሰ ድረስ ሀብቱንና ልጆቹን ማጣቱ የሚያስከትልበትን ሐዘን ለመቋቋም ፈቃደኛ እንደሚሆን ገለጸ። (ኢዮብ 2:4, 5) ከዚያ በኋላ ኢዮብ በሚያሠቃይ ከባድ በሽታ የተመታ፣ የገዛ ሚስቱ አቋሙን እንዲያላላ ልታግባባው የሞከረች እንዲሁም የአምላክን መሥፈርትና ዓላማ አዛብተው የሚያቀርቡ ወዳጆቹ የሚያንቋሽሽ ነቀፋና ትችት የሰነዘሩበት ቢሆንም (ኢዮብ 2:6-13፤ 22:1, 5-11)፣ ንጹሕ አቋሙን ፈጽሞ እንደማያላላ ገልጿል። “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም! ጽድቄን አጥብቄ እይዛለሁ፤ ደግሞም ፈጽሞ አለቀውም፤ በሕይወት ዘመኔም ሁሉ ልቤ አይኮንነኝም” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 27:5, 6) ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ የአምላክ ጠላት ውሸታም እንደሆነ አረጋግጧል።
ንጹሕ አቋም ሲባል ምን ማለት ነው?
3 ንጹሕ አቋም የሚለው አገላለጽ ከአምላክ አገልጋዮች ጋር በተያያዘ ሲሠራበት ይሖዋን እንደ እውን አካል በማየት እሱን በሙሉ ልብ መውደድንና ምንጊዜም ለእሱ ማደርን ያመለክታል፤ ይህም በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ የአምላክን ፈቃድ እንድናስቀድም ያነሳሳናል። እስቲ ይህ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት። ንጹሕ አቋም የሚለው አገላለጽ ከሚያስተላልፋቸው መሠረታዊ ትርጉሞች መካከል አንዱ ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ የሚል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን እንስሳትን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ የነበረ ሲሆን ሕጉ እንስሳው እንከን የሌለበት እንዲሆን ያዛል። (ዘሌ. 22:21, 22) የአምላክ ሕዝቦች እግሩ፣ ጆሮው ወይም ዓይኑ ላይ ችግር ያለበት አሊያም በበሽታ የተጠቃ እንስሳ እንዲያቀርቡ አይፈቀድላቸውም ነበር። ይሖዋ እንስሳው ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን ይፈልግ ነበር። (ሚል. 1:6-9) ይሖዋ የሚቀርብለት መሥዋዕት እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን የሚፈልገው ለምን እንደሆነ መረዳት አይከብደንም። ለምሳሌ የበሰበሰ ፍራፍሬ፣ ገጾቹ ያልተሟሉ መጽሐፍ ወይም የሆነ ዕቃ የጎደለው መሣሪያ መግዛት አንፈልግም። የምንገዛው ነገር ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን እንፈልጋለን። ይሖዋም ለእሱ ከምናሳየው ፍቅርና ታማኝነት ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገር ይጠብቃል። ፍቅራችንና ታማኝነታችን ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ መሆን ይኖርበታል።
4 ይህ ሲባል ታዲያ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ፍጹም መሆን አለብን ማለት ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ሁላችንም እንከን እንዳለብን አልፎ ተርፎም ብዙ ስህተት እንደምንሠራ ይሰማናል። ሆኖም ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ አንችልም የሚል ስጋት ሊያድርብን አይገባም፤ እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ ሁለት ምክንያቶችን እንመልከት። አንደኛ፣ ይሖዋ በጉድለቶቻችን ላይ አያተኩርም። ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “ያህ ሆይ፣ አንተ ስህተትን የምትከታተል ቢሆን ኖሮ፣ ይሖዋ ሆይ፣ ማን ሊቆም ይችል ነበር?” (መዝ. 130:3) አምላክ ኃጢአተኞችና ፍጽምና የጎደለን እንደሆንን ስለሚያውቅ ምንጊዜም እኛን ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። (መዝ. 86:5) ሁለተኛ፣ ይሖዋ ያለብንን የአቅም ገደብ ስለሚረዳ ከምንችለው በላይ እንድናደርግ አይጠብቅብንም። (መዝሙር 103:12-14ን አንብብ።) ታዲያ በእሱ ዓይን ጉድለት የሌለብን፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ መሆን ያለብን ከምን አንጻር ነው?
5 የይሖዋ አገልጋዮች ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ የሚያስፈልጋቸው ዋነኛው ነገር ፍቅር ነው። በሰማይ ላለው አባታችን ያለን ፍቅርና ታማኝነት ምንጊዜም ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ መሆን አለበት። ፈተናዎች በሚደርሱብን ጊዜም እንኳ ፍቅራችን ሙሉ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀናል ሊባል ይችላል። (1 ዜና 28:9፤ ማቴ. 22:37) መግቢያችን ላይ የጠቀስናቸውን ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታ በድጋሚ እንመልከት። እንዲህ ያለ አቋም የያዙት ለምንድን ነው? ትንሿ ልጅ አብረዋት ከሚማሩ ልጆች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ስለማትፈልግ ነው? ወጣቱ ልጅስ ጓደኛው ቢያሾፍበት ደስ ስለሚለው ነው? ወይስ የቤተሰብ ራስ የሆነው ሰው ሥራውን ማጣት ስለሚፈልግ ነው? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች እንዳሉት ስለተገነዘቡና በሰማይ ያለው አባታቸውን በማስደሰት ላይ ትኩረት ስላደረጉ ነው። ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ውሳኔ በሚያደርጉበት ወቅት ለእሱ ፈቃድ ቅድሚያ እንዲሰጡ አነሳስቷቸዋል። በዚህ መንገድ ንጹሕ አቋም እንዳላቸው አስመሥክረዋል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ከአምላክ መጽሐፍ ጋር በሚስማማ መልኩ መደራጀት
3 አምላክ ወደር የማይገኝለት አደራጅ መሆኑን የፍጥረት ሥራው ያረጋግጣል። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ በጥበብ ምድርን መሠረተ። በማስተዋል ሰማያትን አጸና” ይላል። (ምሳሌ 3:19) እኛ የምናውቀው የአምላክን ‘መንገድ ዳር ዳር’ ብቻ ነው፤ “ስለ እሱ የሰማነው የሹክሹክታ ያህል ብቻ ነው!” (ኢዮብ 26:14) ስለ ፕላኔቶች፣ ከዋክብትና ጋላክሲዎች ያለን ውስን እውቀት እንኳ አጽናፈ ዓለም አስደናቂ በሆነ መንገድ እንደተደራጀ እንድንገነዘብ ያደርገናል። (መዝ. 8:3, 4) ጋላክሲዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብትን ያቀፉ ሲሆን ሁሉም በሕዋ ውስጥ በተደራጀ መንገድ ይንቀሳቀሳሉ። በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያሉ ፕላኔቶች፣ የትራፊክ ሕግ አክብረው እንደሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ምሕዋራቸውን ጠብቀው በፀሐይ ዙሪያ ይሽከረከራሉ! በጽንፈ ዓለም ውስጥ የሚታየው አስደናቂ ሥርዓት “ሰማያትን” እና ምድርን ‘በጥበብ የሠራውን’ ይሖዋን ልናወድሰው፣ ታማኝ ልንሆንለት እንዲሁም ልናመልከው እንደሚገባ ያሳያል።—መዝ. 136:1, 5-9
ከታኅሣሥ 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 28–29
“እንደ ኢዮብ ዓይነት ስም አትርፈሃል?”
እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ፍቅራዊ ደግነት አሳዩ
19 የተወያየንባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ራሳቸው ሊያሟሉት የማይችሉት ሁኔታ የገጠማቸውን ሰዎች ለመርዳት ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት እንደሚያስፈልግ ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። አብርሃም የቤተሰቡ የዘር ሐረግ እንዲቀጥል ለማድረግ የባቱኤል ድጋፍ አስፈልጎት ነበር። ያዕቆብ አስከሬኑ ወደ ከነዓን እንዲወሰድ የዮሴፍ እርዳታ አስፈልጎት ነበር። ኑኃሚንም ወራሽ ማግኘት እንድትችል የሩት ትብብር አስፈልጓት ነበር። አብርሃምም ሆነ ያዕቆብ እንዲሁም ኑኃሚን እነዚህ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉ የግድ እርዳታ አስፈልጓቸው ነበር። በተመሳሳይ ዛሬም በተለይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት ይኖርብናል። (ምሳሌ 19:17) ‘ለሚጮኸው ችግረኛ፣ ለድሀ አደጉና ረጂ ለሌለው’ እንዲሁም ‘ወደ ጥፋት ለቀረበው’ ትኩረት የሰጠውን ፓትሪያርኩ ኢዮብን መምሰል ይኖርብናል። ከዚህም በላይ ኢዮብ ‘የባልቴቲቱን ልብ እልል ያሰኘ’ ከመሆኑም በላይ “ለዕውር ዓይን፣ ለአንካሳ እግር” ሆኖ ነበር።—ኢዮብ 29:12-15
it-1 655 አን. 10
አለባበስ
ልብሶች በምሳሌያዊ መንገድ የተሠራባቸው ሌሎች ብዙ ቦታዎችም አሉ። አንድ ዩኒፎርም ወይም ለየት ያለ ልብስ አንድ ሰው የሆነ ድርጅት አባል እንደሆነ ወይም አንድን ንቅናቄ እንደሚደግፍ እንደሚያሳይ ሁሉ ልብስም በምሳሌያዊ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ሰው ከሚወስደው አቋም ወይም ከዚያ ጋር በሚስማማ መንገድ ከሚያደርጋቸው ነገሮች በመነሳት የሚኖረውን መለያ ለማመልከት ተሠርቶበታል፤ ለምሳሌ ኢየሱስ ስለ ሠርግ ልብስ የተናገረው ምሳሌ ይህን ያሳያል። (ማቴ 22:11, 12፤ ጥምጥም፤ ነጠላ ጫማ የሚለውን ተመልከት።) ራእይ 16:14, 15 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ሰው በመንፈሳዊ ካንቀላፋ የእውነተኛው አምላክ ታማኝ አገልጋይ እንደሆነ የሚያሳየው ማንነቱ ሊገፈፍበት እንደሚችል አስጠንቅቋል። ‘ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን በሚካሄደው ጦርነት’ ዋዜማ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ቢደርስብን ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል።
ስሞች ያላቸው ትርጉም
ስንወለድ የሚወጣልንን ስም የምንመርጠው እኛ አይደለንም። ይሁን እንጂ በሌሎች ዘንድ የምናተርፈው ስም ሙሉ በሙሉ በእኛ ላይ የተመካ ነው። (ምሳሌ 20:11) ለምን እንዲህ እያልክ ራስህን አትጠይቅም፦ ‘ኢየሱስ ወይም ሐዋርያት አጋጣሚ ቢያገኙ ኖሮ ምን ስም ያወጡልኝ ነበር? የእኔን ባሕርይ ወይም ማንነት ለመግለጽ ተስማሚ የሚሆነው ምን ዓይነት ስም ነው?’
እነዚህ ጥያቄዎች በቁም ነገር ሊታሰብባቸው ይገባል። ለምን? ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “መልካም ስም ከብዙ ብልጽግና ይመረጣል” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 22:1) በምንኖርበት አካባቢ ጥሩ ስም ወይም ዝና ካተረፍን በእርግጥም ትልቅ ሀብት አግኝተናል ማለት ነው። ከዚህ ይበልጥ ደግሞ በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ማትረፋችን ዘላቂ ሀብት ያስገኝልናል። እንዴት? አምላክ እሱን የሚፈሩትን ሰዎች ስም ‘በመታሰቢያ መጽሐፉ’ ውስጥ እንደሚጽፍና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል።—ሚልክያስ 3:16፤ ራእይ 3:5፤ 20:12-15
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
g00 7/8 11 አን. 3
ፈገግታ—ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል!
በእርግጥ ፈገግታ ማሳየት ወይም አለማሳየት ይህን ያህል ለውጥ ያመጣል? አንድ ሰው ፈገግታ ሲያሳይህ ደስ የተሰኘህበትን ወይም ዘና ያልክበትን ጊዜ አታስታውስም? ወይም ደግሞ ሰዎች ፈገግታ ሲነፍጉህ ጭንቅ አይልህም? አልፎ ተርፎም ተቀባይነት እንዳጣህ አይሰማህም? አዎን፣ ፈገግታ ማሳየት ወይም አለማሳየት ልዩነት ያመጣል። ፈገግ በሚለውም ሆነ ፈገግ በሚባልለት ሰው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢዮብ ባላጋራዎቹን በተመለከተ “ፈገግ አልኩላቸው፣ እነርሱ ግን አላመኑም። የፊቴንም ብርሃን አላወረዱም” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 29:24 NW ) የኢዮብ የፊቱ “ብርሃን” ብሩህና ደስተኛ ፊቱን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ከታኅሣሥ 25-31
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 30–31
“ኢዮብ የሥነ ምግባር ንጽሕናውን የጠበቀው እንዴት ነው?”
ከንቱ ነገር ከማየት ዓይናችሁን መልሱ!
8 እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓይን አምሮትና በሥጋ ምኞት እንዳይሸነፉ የሚከላከል ክትባት አልወሰዱም። በመሆኑም የአምላክ ቃል በምናያቸውና በምንመኛቸው ነገሮች ረገድ ራሳችንን እንድንገዛ ማበረታቻ ሰጥቶናል። (1 ቆሮ. 9:25, 27፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17ን አንብብ።) ቅን ሰው የነበረው ኢዮብ፣ ዓይናችን አንድን ነገር እንድንመኝ የማድረግ ኃይል እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። “ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት፣ ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 31:1) ኢዮብ ሴትን ሥነ ምግባር በጎደለው መንገድ መንካት ይቅርና እንዲህ ዓይነቱን ሐሳብ በአእምሮው እንኳ ላለማውጠንጠን ቆርጦ ነበር። ኢየሱስ አእምሯችን ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ሐሳቦች የጸዳ መሆን እንዳለበት ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።”—ማቴ. 5:28
‘መጨረሻህ ምን እንደሚሆን’ አስተውል
እንዲህ ባለው መንገድ ላይ መጓዝ ከመጀመርህ በፊት ‘ይህ መንገድ የት ያደርሰኛል?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ‘መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል’ ላፍታ ቆም ብለህ ማሰብህ ብቻ እንኳ አስከፊ መዘዝ በሚያስከትል ጎዳና ላይ ከመጓዝ ሊጠብቅህ ይችላል። የአምላክን ማስጠንቀቂያዎች ችላ የሚሉ ሰዎች ኤድስና በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ውርጃ፣ የቤተሰብ መፈራረስና የሕሊና ወቀሳ የመሳሰሉ ችግሮች ይደርስባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች የጉዟቸው መጨረሻ ምን እንደሆነ በግልጽ ሲናገር “የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
እናንት ወጣቶች—በአምላክ ቃል ተመሩ
15 ለአምላክ ያለህ ታማኝነት ይበልጥ የሚፈተነው መቼ ይመስልሃል? ከሌሎች ጋር ስትሆን ነው ወይስ ብቻህን ስትሆን? በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ስትሆን መንፈሳዊ ጥቃትን ለመመከት ይበልጥ ዝግጁ እንደምትሆን የታወቀ ነው። በዚህ ጊዜ ሊያጋጥሙህ የሚችሉትን መንፈሳዊ አደጋዎች በንቃት ትከታተላለህ። የሚያጋጥምህን ፈተና ለመቋቋም ያን ያህል ዝግጁ በማትሆንበትና ዘና በምትልበት ጊዜ ግን የሥነ ምግባር አቋምህን እንድታላላ ለሚሰነዘርብህ ጥቃት ይበልጥ ትጋለጣለህ።
16 ብቻህን በምትሆንበት ጊዜም ይሖዋን መታዘዝ ያለብህ ለምንድን ነው? ብቻህን በምትሆንበት ወቅት የምታደርገው ነገር የይሖዋን ልብ ሊያሳዝነው አሊያም ደስ ሊያሰኘው እንደሚችል አስታውስ። (ዘፍ. 6:5, 6፤ ምሳሌ 27:11) ይሖዋ በምታደርገው ነገር ስሜቱ የሚነካው ‘ስለ አንተ ስለሚያስብ’ ነው። (1 ጴጥ. 5:7) እሱን እንድትሰማው የሚፈልገው ይህን ማድረግህ እንደሚጠቅምህ ስለሚያውቅ ነው። (ኢሳ. 48:17, 18) በጥንቷ እስራኤል የነበሩ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ምክሩን ችላ በማለታቸው እጅግ አዝኖ ነበር። (መዝ. 78:40, 41) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ መልአክ፣ ነቢዩ ዳንኤልን “እጅግ የተወደድህ” ብሎ መጥራቱ ይሖዋ ይህን ነቢይ በጣም ይወደው እንደነበር ያሳያል። (ዳን. 10:11) ይሖዋ ዳንኤልን እንዲወደው ያደረገው ምንድን ነው? ዳንኤል ከሌሎች ጋር ሲሆን ብቻ ሳይሆን ለብቻው በሚሆንበት ጊዜም ለአምላክ ታማኝ ነበር።—ዳንኤል 6:10ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ
የኢዮብ ወዳጆች እርሱ ያደረጋቸውን አሥር የሚያክሉ ንግግሮች የሰሙት ቢሆንም እንኳ “ምነው የሚሰማኝ ባገኝ!” በማለት በምሬት ተናግሯል። (ኢዮብ 31:35) ለምን? ምክንያቱም ያዳመጡበት መንገድ ለእርሱ እረፍት የሚሰጥ አልነበረም። ለኢዮብ ምንም የአሳቢነት መንፈስ አላሳዩም፤ እንዲሁም ስሜቱን አልተረዱለትም። እነዚህ ወዳጆቹ ከልባቸው እንደሚያዳምጡ ሰዎች ዓይነት የሌሎችን ችግር የመረዳት መንፈስ የሚያሳዩ አልነበሩም። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ምክር ሰጥቷል፦ “ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 3:8) እርስ በርስ እንደምንተሳሰብ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ ለሌሎች ስሜት በመጨነቅና ስሜታቸውን እንደተረዳን በማሳየት ነው። “በጣም ያሳዝናል፣” “ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እንደተረዱህ ሳይሰማህ አይቀርም” እንደሚሉ ያሉትን ስሜታቸውን እንደተረዳንላቸው የሚያሳዩ ሐሳቦች መሰንዘር አሳቢነታችንን የምንገልጽበት መንገድ ነው። ሌላው ደግሞ ግለሰቡ የነገረንን በራሳችን አባባል በመድገም እንደተረዳነው ማሳየት ነው። ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ ሲባል ቃላቱን መስማት ብቻ ሳይሆን ስሜቱንም ጭምር ማስተዋል ማለት ነው።