የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2023 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከጥር 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 32–33
በጭንቀት የተዋጡትን አጽናኑ
it-1 710
ኤሊሁ
ኤሊሁ ከአድልዎ የጸዳ ነበር፤ ማንንም አልሸነገለም። እሱም እንደ ኢዮብ የተሠራው ከሸክላ እንደሆነና እውነተኛው አምላክ ፈጣሪው እንደሆነ አምኖ ተቀብሏል። ኤሊሁ ኢዮብን የማስፈራት ዓላማ አልነበረውም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ እውነተኛ ወዳጅ ስሙን እየጠራ አነጋግሮታል፤ ኤሊፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር ግን እንዲህ አላደረጉም።—ኢዮብ 32:21, 22፤ 33:1, 6
ደካሞችን የምትመለከቱት በይሖዋ ዓይን ነው?
8 አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደካማ የሆኑት ከባድ ችግር ስለገጠማቸው ለምሳሌ በጤና እክል፣ በሃይማኖት የተከፋፈለ ቤት ውስጥ በመኖራቸው ወይም በመንፈስ ጭንቀት ምክንያት መሆኑን ካስታወስን ይበልጥ ስሜታቸውን ልንረዳላቸው እንችላለን። በተጨማሪም ‘ነግ በኔ’ ማለት ይኖርብናል። በግብፅ ምድር ሳሉ ድሆችና ደካሞች የነበሩት እስራኤላውያን ለተቸገሩ ወንድሞቻቸው ‘ልባቸውን እንዳያጨክኑባቸው’ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር። ይሖዋ ለድሆች እርዳታ እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸው ነበር።—ዘዳ. 15:7, 11፤ ዘሌ. 25:35-38
9 ተቺ ወይም ነቃፊ ከመሆን ይልቅ በችግር ውስጥ ላሉ ወንድሞቻችን መንፈሳዊ ማበረታቻ መስጠት ይኖርብናል። (ኢዮብ 33:6, 7፤ ማቴ. 7:1) ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ሰው የሞተር ብስክሌት ሲያሽከረክር አደጋ ቢደርስበትና ወደ ድንገተኛ ሕክምና ክፍል ቢገባ የሕክምና ባለሙያዎቹ አደጋውን ያደረሰው እሱ መሆን አለመሆኑን ለማጣራት የሚሞክሩ ይመስልሃል? በፍጹም፣ ከዚህ ይልቅ ወዲያውኑ አስፈላጊውን የሕክምና እርዳታ ያደርጉለታል። በተመሳሳይም አንድ የእምነት ባልንጀራችን በገጠመው ችግር የተነሳ ቢደክም በቅድሚያ ጥረት ማድረግ ያለብን እሱን በመንፈሳዊ ለመርዳት ነው።—1 ተሰሎንቄ 5:14ን አንብብ።
10 ወንድሞቻችንን ከላይ ስንመለከታቸው ደካማ ይመስሉ ይሆናል፤ ሆኖም ሕይወታቸውን ቀረብ ብለን ለመመልከት ከሞከርን ሁኔታው እንዳሰብነው ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ለበርካታ ዓመታት የሚደርስባቸውን የቤተሰብ ተቃውሞ በጽናት ያሳለፉ እህቶችን ማሰብ ይቻላል። አንዳንዶች አንገታቸውን የደፉና ምስኪን ይመስሉ ይሆናል፤ ይሁንና ያላቸውን አስደናቂ እምነትና ውስጣዊ ጥንካሬ ለምን አትመለከትም? ልጆቿን አዘውትራ ወደ ስብሰባ ይዛ የምትመጣ ነጠላ ወላጅ የሆነች አንዲት እህት ያላትን እምነትና ቁርጠኝነት ስትመለከት አትደነቅም? በትምህርት ቤት መጥፎ ተጽዕኖዎች ቢደርሱባቸውም እውነትን አጥብቀው የያዙ ወጣቶች ስትመለከት አትደሰትም? በእርግጥም ወንድሞቻችን የሚያደርጉትን ጥረት ስንመለከት ደካማ የሚመስሉ ወንድሞችና እህቶች በአንጻራዊ ሁኔታ በተመቻቸ ሁኔታ ሥር ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሌሎች ክርስቲያኖች እኩል “በእምነት ባለጸጋ” እንደሆኑ እናስተውላለን።—ያዕ. 2:5
ለመናገር ትክክለኛው ጊዜ መቼ ነው?
17 ኢዮብን ሊጠይቅ የመጣው አራተኛው ሰው የአብርሃም ዘመድ የሆነው ኤሊሁ ነው። ኤሊሁ ኢዮብና ሦስቱ ሰዎች ሲነጋገሩ ያዳምጥ ነበር። ኤሊሁ ኢዮብ አመለካከቱን እንዲያስተካክል የሚረዳ ቀጥተኛ ምክር ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ መስጠት መቻሉ የተነጋገሩትን ነገር በጥሞና እንዳዳመጠ ያሳያል። (ኢዮብ 33:1, 6, 17) የኤሊሁ ዋነኛ ዓላማ ራሱን ወይም ሌሎች ሰዎችን ሳይሆን ይሖዋን ከፍ ከፍ ማድረግ ነበር። (ኢዮብ 32:21, 22፤ 37:23, 24) የኤሊሁ ምሳሌ ዝም ብለን ማዳመጥ የሚያስፈልገን ጊዜ እንዳለ ያሳያል። (ያዕ. 1:19) በተጨማሪም ምክር በምንሰጥበት ጊዜ ዋናው ዓላማችን ወደ ራሳችን ትኩረት መሳብ ሳይሆን ይሖዋን ከፍ ከፍ ማድረግ መሆን እንዳለበት እንማራለን።
18 መጽሐፍ ቅዱስ መቼና እንዴት መናገር እንዳለብን የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ አምላክ ለሰጠን የመናገር ችሎታ አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም ነው።” (ምሳሌ 25:11) ሌሎች ሲናገሩ በጥሞና የምናዳምጥ እንዲሁም ከመናገራችን በፊት የምናስብ ከሆነ ንግግራችን እንደ ወርቅ ፖም ውድና ማራኪ ይሆናል። የምንናገረው ብዙም ይሁን ጥቂት ንግግራችን ሌሎችን የሚያንጽ ይሆናል፤ ይሖዋም ይደሰትብናል። (ምሳሌ 23:15፤ ኤፌ. 4:29) አምላክ ለሰጠን ለዚህ ስጦታ አድናቆታችንን ማሳየት የምንችልበት ከዚህ የተሻለ ምን መንገድ አለ!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ምንጊዜም ወደ ይሖዋ ቅረቡ
10 ስለ መልካችን ማሰባችንም የተገባ ነው። ይሁንና የእርጅና ምልክቶችን ሁሉ ለማጥፋት መሞከሩ አስፈላጊ አይደለም። እንዲያውም እነዚህ ምልክቶች የጉልምስና፣ የክብርና የውስጣዊ ውበት መገለጫዎች ናቸው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ይላል። (ምሳሌ 16:31) ይሖዋ የሚመለከተን እንደዚህ ነው፤ እኛም ራሳችንን በይሖዋ ዓይን ማየት አለብን። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4ን አንብብ።) ታዲያ መልካችንን ለማሳመር ብለን ጤናችንን አልፎ ተርፎም ሕይወታችንን አደጋ ላይ የሚጥል ቀዶ ሕክምና (ፕላስቲክ ሰርጀሪ) ወይም ሌሎች ሕክምናዎችን ማድረጋችን ጥበብ ነው? የዕድሜያችንና የጤንነታችን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን እውነተኛ የሆነውና ከውስጣችን የሚወጣው ውበት ምንጭ ‘የይሖዋ ደስታ’ ነው። (ነህ. 8:10) የተሟላ ጤንነትና የወጣትነት ውበት የምናገኘው በአዲሱ ዓለም ብቻ ነው። (ኢዮብ 33:25፤ ኢሳ. 33:24) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ጥበበኞች መሆናችንና እምነት ማዳበራችን አሁን ያለንበትን ሁኔታ ከሁሉ በተሻለ መንገድ በመጠቀም ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር ይረዳናል።—1 ጢሞ. 4:8
ከጥር 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 34–35
ሕይወት ፍትሐዊ እንዳልሆነ ሲሰማን
አምላክ ምን ባሕርያት አሉት?
አምላክ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ምንጊዜም ትክክል ነው። እንዲያውም “‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!” (ኢዮብ 34:10) የይሖዋ ፍርዶች ሁሌም ትክክል ናቸው፤ መዝሙራዊው ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “በሕዝቦች ላይ በትክክል ትፈርዳለህ” ብሏል። (መዝሙር 67:4) ይሖዋ “የሚያየው ልብን” ስለሆነ በሰዎች ግብዝነት ሊታለል አይችልም፤ ምንጊዜም ቢሆን እውነቱን ማወቅና ትክክለኛ ፍርድ መስጠት ይችላል። (1 ሳሙኤል 16:7) ከዚህም በላይ አምላክ በምድር ላይ የሚፈጸመውን የፍትሕ መጓደልና ምግባረ ብልሹነት በሙሉ ጠንቅቆ የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ በቅርቡ ‘ክፉዎች ከምድር ገጽ እንደሚጠፉ’ ቃል ገብቷል።—ምሳሌ 2:22
የአምላክ መንግሥት ሲመጣ የትኞቹ ነገሮች ይወገዳሉ?
5 ይሖዋ ምን እርምጃ ይወስዳል? ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ክፉ ሰዎች እንዲለወጡ አጋጣሚውን ሰጥቷቸዋል። (ኢሳ. 55:7) በግለሰብ ደረጃ ፍርድ አልተበየነባቸውም። ጥፋት የተፈረደበት ይህ ሥርዓት ነው። ይሁንና ለመለወጥ እምቢተኛ የሆኑና ታላቁ መከራ እስኪጀምር ድረስ ይህን ሥርዓት የሚደግፉ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆናል? ይሖዋ ክፉ ሰዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድር ላይ እንደሚያስወግዳቸው ቃል ገብቷል። (መዝሙር 37:10ን አንብብ።) ክፉዎች ከዚህ ፍርድ ማምለጥ እንደሚችሉ ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች፣ የሚሠሩት መጥፎ ድርጊት እንዳይታወቅባቸው ማድረግ በመቻላቸው አብዛኛውን ጊዜ ከቅጣት ያመልጣሉ። (ኢዮብ 21:7, 9) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ዓይኖች የሰውን መንገድ ይመለከታሉና፤ ደግሞም እርምጃውን ሁሉ ያያል። ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች የሚደበቁበት ጨለማም ሆነ ፅልማሞት የለም።” (ኢዮብ 34:21, 22) ከይሖዋ አምላክ መሰወር አይቻልም። ማንኛውም አስመሳይ እሱን ማታለል አይችልም፤ የትኛውም ዓይነት ድርጊት ከእሱ እይታ ውጪ አይደለም። በመሆኑም ከአርማጌዶን በኋላ ክፉዎችን በቀድሞ ቦታቸው ብንፈልጋቸው ልናገኛቸው አንችልም። ከዚያ በኋላ ደብዛቸው አይገኝም!—መዝ. 37:12-15
በኢየሱስ ምክንያት ትሰናከላለህ?
19 በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። ብዙዎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ በመሆናችን ይሰናከሉብናል። ምርጫ ሲካሄድ ድምፅ እንድንሰጥ ይጠብቁብናል። ይሁንና ሰብዓዊ መሪ እንዲገዛን መምረጥ የይሖዋን አገዛዝ አንቀበልም ማለት ይሆንብናል። (1 ሳሙ. 8:4-7) አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታሎችን መገንባት እንዲሁም ሌሎች የበጎ አድራጎት ተግባራትን መፈጸም እንዳለብን ይሰማቸዋል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ በስብከቱ ሥራ ላይ ትኩረት በማድረጋችን ይሰናከሉብናል።
20 እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? (ማቴዎስ 7:21-23ን አንብብ።) በዋነኝነት ትኩረት ልናደርግ የሚገባው ኢየሱስ የሰጠንን ሥራ በማከናወን ላይ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በዚህ ዓለም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ትኩረታችን እንዲከፋፈል ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም። ሰዎችን እንወዳለን፤ ችግሮቻቸውም ያሳስቡናል። ያም ቢሆን ሰዎችን መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ እነሱን ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማርና ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ መርዳት እንደሆነ እናውቃለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የምታሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል!
3 ኤሊሁ “ጻድቅ ብትሆን ለእሱ [ለአምላክ] ምን ትጨምርለታለህ? ከአንተ እጅ ምን ይቀበላል?” ብሏል፤ በእርግጥ ይህን በማለቱ ይሖዋ አልገሠጸውም። (ኢዮብ 35:7) ኤሊሁ ይህን ሲል አምላክን ለማገልገል የምናደርገው ጥረት ዋጋ የለውም ማለቱ ነበር? በፍጹም። ኤሊሁ፣ ይሖዋ እኛ ባናመልከውም ምንም የሚጎድልበት ነገር እንደሌለ መግለጹ ነው። ይሖዋ በራሱ ምሉዕ ነው። እኛ የምናደርገው ማንኛውም ነገር ለይሖዋ ብልጽግና ወይም ኃይል ሊጨምርለት አይችልም። እንዲያውም ያለንን ማንኛውም መልካም ባሕርይ፣ ተሰጥኦ ወይም ችሎታ ያገኘነው ከይሖዋ ነው፤ እሱም ይህን እንዴት እንደምንጠቀምበት በትኩረት ይመለከታል።
ከጥር 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 36–37
አምላክ በሰጠው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
አምላክን ፈልገን ማግኘት እንችላለን?
የአምላክ ዘላለማዊ ሕልውና፦ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” እንደሚኖር ይናገራል። (መዝሙር 90:2) በሌላ አባባል አምላክ መጀመሪያ አልነበረውም፣ መጨረሻም የለውም። ከሰው አመለካከት አንጻር ሲታይ ‘የዘመኑ ቁጥር ከመረዳት ችሎታ በላይ ነው።’—ኢዮብ 36:26
ይህን ማወቅህ እንዴት ይጠቅምሃል? አምላክ፣ እሱን በሚገባ ካወቅከው የዘላለም ሕይወት እንደምታገኝ ቃል ገብቶልሃል። (ዮሐንስ 17:3) አምላክ ራሱ ለዘላለም የሚኖር ባይሆን ኖሮ ይህ ተስፋ ምን ያህል ተአማኒነት ይኖረው ነበር? እንዲህ ዓይነቱን ተስፋ መፈጸም የሚችለው ‘የዘላለሙ ንጉሥ’ ብቻ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 1:17
ከአምላክ ላገኘሃቸው ስጦታዎች አድናቆት አለህ?
6 ውኃ በምድር ላይ በፈሳሽ መልክ ሊገኝ የቻለው ፕላኔታችን ከፀሐይ በትክክለኛው ርቀት ላይ ስለተቀመጠች ነው። ፕላኔታችን ወደ ፀሐይ ትንሽ ቀረብ ብትል ኖሮ በምድር ላይ ያለው ውኃ በሙሉ ተንኖ ያልቅ ነበር፤ በመሆኑም ምድራችን ሕይወት የሌለባት ደረቅ ስፍራ ትሆን ነበር። ምድር ከፀሐይ ትንሽ ራቅ ብትል ኖሮ ደግሞ ውኃው በሙሉ ስለሚረጋ ምድራችን በበረዶ ትሸፈን ነበር። ይሖዋ ምድርን ያስቀመጣት ትክክለኛው ቦታ ላይ ነው፤ በመሆኑም የምድር የውኃ ዑደት ሕይወት እንዲቀጥል አስችሏል። ፀሐይ የምታመነጨው ሙቀት በውቅያኖሶችና በምድር ገጽ ላይ ያለው ውኃ እንዲተን ያደርጋል፤ ከዚያም ደመና ይፈጠራል። በየዓመቱ በፀሐይ ሙቀት የተነሳ የሚተንነው ውኃ 500,000 ኪሎ ሜትር ኩብ ገደማ (በምድር ላይ ባሉት በሁሉም ሐይቆች ውስጥ ካለው ውኃ የሚበልጥ) ይሆናል። የተነነው ውኃ ከባቢ አየር ላይ ለአሥር ቀናት ያህል ከቆየ በኋላ በዝናብ መልክ ይወርዳል። ውሎ አድሮም ውኃው ወደ ውቅያኖሶች ወይም ወደ ሌሎች የውኃ አካላት ይገባል፤ ከዚያም ይኸው ዑደት እንደገና ይደገማል። ይህ ውጤታማና የማይቋረጥ ዑደት ይሖዋ ጥበበኛና ኃያል አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል።—ኢዮብ 36:27, 28፤ መክ. 1:7
ክርስቲያናዊ ተስፋችሁን አጠናክሩ
16 የዘላለም ሕይወት ተስፋችን ከአምላክ ያገኘነው ውድ ስጦታ ነው። ወደፊት ግሩም ሕይወት ይጠብቀናል፤ እንደምናገኘውም እርግጠኞች ነን። ተስፋችን እንደ መልሕቅ በመሆን ፈተናዎችን እንድንወጣ፣ ስደትን እንድንቋቋም አልፎ ተርፎም ሞትን እንድንጋፈጥ ይረዳናል። እንደ ራስ ቁር በመሆን አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል፤ ይህም መጥፎ የሆነውን ለመጸየፍና ጥሩ የሆነውን አጥብቀን ለመያዝ ይረዳናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ተስፋችን ወደ አምላክ እንድንቀርብ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ እሱ ምን ያህል እንደሚወደን ያሳየናል። ተስፋችን ጠንካራ ከሆነ በእጅጉ እንጠቀማለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 492
የመረጃ ልውውጥ
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን መረጃዎችና ሐሳቦች ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉት በተለያየ መንገድ ነበር። የአገር ውስጥና የውጭ ዜናዎች በአብዛኛው የሚሰራጩት በቃል ነበር። (2ሳሙ 3:17, 19፤ ኢዮብ 37:20) ብዙውን ጊዜ በቡድን የሚጓዙት ተጓዦች ምግብ፣ ውኃ ወይም ሌላ ነገር ለማግኘት በከተሞች ወይም መንገድ ላይ ሲቆሙ ከሩቅ ቦታ ያመጡትን ዜና ይናገሩ ነበር። የፓለስቲና ምድር ከእስያ፣ ከአፍሪካ እና ከአውሮፓ አንጻር የሚገኝበት ቦታ አመቺ ስለነበር ከሩቅ ቦታ ተነስተው ወደ ሩቅ ቦታ የሚሄዱ ተጓዦች ያቋርጡታል። በመሆኑም ነዋሪዎቹ በውጭ አገራት ስለተፈጸሙ ጉልህ ክንውኖች የሚሰሙበት ሰፊ አጋጣሚ ነበራቸው። በከተማው የገበያ ቦታ ውስጥ ብዙውን ጊዜ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ዜና መስማት ይቻል ነበር።
ከጥር 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 38–39
ተፈጥሮን ለመመልከት ጊዜ ትመድባላችሁ?
ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነህ?
7 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ምድርን ስለፈጠረበት መንገድ ሲናገር ‘መለኪያዎቿን እንደወሰነ፣’ ‘ምሰሶዎቿን እንደተከለ’ እንዲሁም ‘የማዕዘኗን ድንጋይ እንዳኖረ’ ይገልጻል። (ኢዮብ 38:5, 6) ይሖዋ የሠራውን ሥራ መለስ ብሎ ለማየትም ጊዜ ወስዷል። (ዘፍ. 1:10, 12) መላእክት የይሖዋ የፍጥረት ሥራ ቀስ በቀስ መልክ እየያዘ ሲሄድ ሲያዩ ምን ተሰምቷቸው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ? በጣም ተደንቀው መሆን አለበት! እንዲያውም ‘በደስታ እንደጮኹ’ ተገልጿል። (ኢዮብ 38:7) ከዚህ ምን እንማራለን? ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን ለማከናወን ብዙ ሺህ ዓመታት ወስዶበታል፤ ደግሞም በጥንቃቄ የፈጠረውን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ “እጅግ መልካም” እንደሆነ ተናግሯል።—ዘፍ. 1:31
ትንሣኤ የአምላክን ፍቅር፣ ጥበብና ትዕግሥት ያሳያል
2 ይሖዋ መጀመሪያ የፈጠረው ልጁን ኢየሱስን ነው። ከዚያም በበኩር ልጁ አማካኝነት፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸውን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጨምሮ ‘ሌሎች ነገሮችን በሙሉ’ ፈጠረ። (ቆላ. 1:16) ኢየሱስ ከአባቱ ጋር አብሮ የመሥራት መብት በማግኘቱ ደስተኛ ነበር። (ምሳሌ 8:30) የአምላክ ልጆች የሆኑት መላእክትም ደስተኛ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ነገር ነበረ። ይሖዋ እና ዋና ሠራተኛው የሆነው ኢየሱስ፣ ሰማያትንና ምድርን ሲፈጥሩ መላእክት በቀጥታ የመመልከት አጋጣሚ አግኝተዋል። ታዲያ ይህን ሲያዩ ምን ተሰማቸው? ምድር ስትፈጠር ‘በደስታ ጮኸዋል’፤ ይሖዋ የፍጥረት ሥራው ቁንጮ የሆነውን የሰው ልጅን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን ሲፈጥርም ደስታቸውን ገልጸው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። (ኢዮብ 38:7፤ ምሳሌ 8:31) እያንዳንዱ የይሖዋ የፍጥረት ሥራ የእሱን ፍቅርና ጥበብ ያሳያል።—መዝ. 104:24፤ ሮም 1:20
ፍጥረትን በማየት ስለ ይሖዋ ይበልጥ ተማሩ
8 ይሖዋ እምነት የሚጣልበት አምላክ ነው። ይሖዋ፣ ኢዮብ በእሱ ላይ ያለውን እምነት እንዲያጠናክር ረድቶታል። (ኢዮብ 32:2፤ 40:6-8) ከኢዮብ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ከዋክብትን፣ ደመናትንና መብረቅን ጨምሮ የተለያዩ ፍጥረታትን ጠቅሶለታል። ይሖዋ እንደ ዱር በሬና ፈረስ ስላሉ እንስሳትም ተናግሯል። (ኢዮብ 38:32-35፤ 39:9, 19, 20) እነዚህ የፍጥረት ሥራዎች አምላክ ያለውን አስደናቂ ኃይል ብቻ ሳይሆን ፍቅሩንና ወደር የለሽ ጥበቡንም ያሳያሉ። ይህ ውይይት ኢዮብ በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት ከምንጊዜውም ይበልጥ እንዲያጠናክር ረድቶታል። (ኢዮብ 42:1-6) እኛም ፍጥረትን በትኩረት መመልከታችን ይሖዋ ገደብ የሌለው ጥበብ እንዳለውና ከእኛ ይበልጥ እጅግ ኃያል እንደሆነ እንድናስታውስ ይረዳናል። አሁን ያሉብንን ችግሮች ሁሉ ማስወገድም ይችላል፤ ደግሞም እንዲህ ያደርጋል። ይህን መገንዘባችን በእሱ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክረዋል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 222
ሕግ አውጪ
ይሖዋ ሕግ አውጪ ነው። በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ያለው ብቸኛው እውነተኛ ሕግ አውጪ ይሖዋ ነው። ግዑዛን ፍጥረታትም (ኢዮብ 38:4-38፤ መዝ 104:5-19) ሆኑ እንስሳት (ኢዮብ 39:1-30) የሚመሩባቸውን የተፈጥሮ ሕጎች ያወጣው እሱ ነው። ሰዎችም የይሖዋ ፍጥረታት እንደመሆናቸው መጠን ይሖዋ ላወጣቸው የተፈጥሮ ሕጎች ተገዢ ናቸው፤ በተጨማሪም ማመዛዘንና መንፈሳዊ ነገሮችን መረዳት የሚችሉ አስተዋይ ፍጥረታት ስለሆኑ አምላክ ላወጣቸው የሥነ ምግባር ሕጎችም መገዛት ይጠበቅባቸዋል። (ሮም 12:1፤ 1ቆሮ 2:14-16) ከዚህም ሌላ መንፈሳዊ ፍጥረታት የሆኑት መላእክትም ለይሖዋ ሕጎች ተገዢ ናቸው።—መዝ 103:20፤ 2ጴጥ 2:4, 11
ይሖዋ ያወጣቸውን የተፈጥሮ ሕጎች ማፍረስ አይቻልም። (ኤር 33:20, 21) በመላው ጽንፈ ዓለም ሕጎቹ አስተማማኝና የማይለዋወጡ ከመሆናቸው የተነሳ ሳይንቲስቶች በሚያውቋቸው የተፈጥሮ ሕጎች ላይ ተመሥርተው የጨረቃን፣ የፕላኔቶችንና የሌሎች የሕዋ ፍጥረታትን እንቅስቃሴ ዝንፍ በማይል መንገድ ማስላት ይችላሉ። የተፈጥሮ ሕጎችን ለመጣስ የሚሞክር ሰው ወዲያውኑ መዘዙን መቅመሱ አይቀርም። አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር ሕጎችም መቀልበስ ወይም እነዚህን ሕጎች ጥሶ ከቅጣት አመልጣለሁ ማለት አይቻልም። ከተፈጥሮ ሕጎች ጋር ሲወዳደር የሥነ ምግባር ሕጎችን የሚጥሱ ሰዎች ወዲያውኑ መዘዙን ሲቀምሱ ላይታይ ቢችልም ተፈጻሚነታቸው የተፈጥሮ ሕጎችን ያህል የተረጋገጠ ነው። “አትታለሉ፤ አምላክ አይዘበትበትም። አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።”—ገላ 6:7፤ 1ጢሞ 5:24
ከጥር 29–የካቲት 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢዮብ 40–42
ከኢዮብ ታሪክ የምናገኛቸው ትምህርቶች
“የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?”
4 በይሖዋ ሥራዎች ላይ ስናሰላስል ይሖዋን በሰዎች መሥፈርት እንዳንለካው መጠንቀቅ አለብን። ይሖዋ እንዲህ ስላለው ዝንባሌ ሲገልጽ በመዝሙር 50:21 ላይ “እንዳንተም የሆንሁ መሰለህ” ብሏል። ከ175 ዓመታት በፊት የኖሩ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ይህን ዝንባሌ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “የሰው ልጆች በራሳቸው መሥፈርት በአምላክ ላይ የመፍረድ ብሎም እነሱ ሊከተሏቸው እንደሚገቡ የሚያስቧቸውን ሕግጋት አምላክም ሊከተል እንደሚገባ የማሰብ ዝንባሌ አላቸው።”
5 የራሳችን መሥፈርትና ፍላጎታችን ለይሖዋ በሚኖረን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር መጠንቀቅ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ቅዱሳን መጻሕፍትን ስናጠና የምናገኛቸውን አንዳንድ ዘገባዎች ፍጽምና በሚጎድለንና ነገሮችን ሙሉ በሙሉ መረዳት በማንችለው በእኛ አመለካከት በምንገመግምበት ጊዜ ይሖዋ የወሰደው እርምጃ ትክክል እንዳልሆነ ይሰማን ይሆናል። በጥንት ጊዜ የነበሩት እስራኤላውያን እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ያዳበሩ ሲሆን ይሖዋ እነሱን የሚይዝበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ይሖዋ ምን እንዳላቸው እንመልከት፦ “እናንተ ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስማ፤ መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነውስ የእናንተ መንገድ አይደለምን?”—ሕዝ. 18:25
6 ከራሳችን መሥፈርት አንጻር በይሖዋ ላይ የመፍረድን አዝማሚያ እንዳናዳብር የሚረዳን ቁልፍ፣ ነገሮችን በተሟላ መንገድ መረዳት እንደማንችል ብሎም አንዳንድ ጊዜ አመለካከታችን ሊዛባ እንደሚችል መገንዘብ ነው። ኢዮብ ይህን መማር አስፈልጎት ነበር። ኢዮብ መከራ በደረሰበት ወቅት በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠ ከመሆኑም ሌላ ስለ ራሱ ብቻ ማሰብ ጀምሮ ነበር። ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ አልቻለም። ይሁንና ኢዮብ ሰፋ ያለ አመለካከት እንዲይዝ ይሖዋ በፍቅር ረድቶታል። ይሖዋ፣ ኢዮብ ሊመልሳቸው ያልቻላቸውን ከ70 የሚበልጡ ጥያቄዎች በማንሳት ኢዮብ መረዳት የማይችላቸው ነገሮች እንዳሉ እንዲገነዘብ ረድቶታል። ኢዮብም ትሑት በመሆን አመለካከቱን አስተካክሏል።—ኢዮብ 42:1-6ን አንብብ።
ትኩረታችሁን አንገብጋቢ በሆነው ጉዳይ ላይ አድርጉ
12 ይሖዋ፣ ኢዮብ ያንን ሁሉ መከራ በጽናት ከተቋቋመ በኋላ እንዲህ ያለ ቀጥተኛ ምክር መስጠቱ አሳቢነት እንደጎደለው የሚያሳይ ነው? በፍጹም፤ ኢዮብም ቢሆን እንዲህ አልተሰማውም። ኢዮብ ይሖዋ የሰጠውን ምክር ማስተዋል ችሎ ነበር። እንዲያውም “በተናገርኩት ነገር እጸጸታለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬም ንስሐ እገባለሁ” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ የሰጠው ቀጥተኛ ሆኖም ፍቅር የተንጸባረቀበት ምክር እንዲህ ያለ ውጤት አስገኝቷል። (ኢዮብ 42:1-6) ወጣቱ ኤሊሁም ቀደም ሲል ለኢዮብ እርማት ሰጥቶታል። (ኢዮብ 32:5-10) ኢዮብ፣ አምላክ የሰጠውን እርማት ተቀብሎ አመለካከቱን ካስተካከለ በኋላ ይሖዋ ኢዮብ ታማኝነቱን በመጠበቁ እንደተደሰተ ገልጿል።—ኢዮብ 42:7, 8
“ይሖዋን ተስፋ አድርግ”
17 ኢዮብ ከባድ መከራ ቢያጋጥማቸውም ደፋርና ብርቱ መሆናቸውን ካሳዩ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል አንዱ ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሌሎች በርካታ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችን ጠቅሷል፤ እነዚህን ሰዎች “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” በማለት ጠርቷቸዋል። (ዕብ. 12:1) ሁሉም ከባድ መከራ አጋጥሟቸው ነበር፤ ሆኖም ዕድሜያቸውን በሙሉ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ኖረዋል። (ዕብ. 11:36-40) ታዲያ ጽናታቸውና ትጋታቸው ከንቱ ሆኗል? በጭራሽ! አምላክ የገባቸው ቃሎች በሙሉ ሲፈጸሙ በሕይወት ዘመናቸው ማየት ባይችሉም እንኳ ይሖዋን ተስፋ ማድረጋቸውን ቀጥለው ነበር። ደግሞም የይሖዋን ሞገስ እንዳገኙ እርግጠኞች ስለነበሩ ይሖዋ የገባቸው ቃሎች ሲፈጸሙ ማየታቸው እንደማይቀር ቅንጣት ታክል አልተጠራጠሩም። (ዕብ. 11:4, 5) የእነሱ ምሳሌ ይሖዋን ተስፋ ማድረጋችንን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል።
18 የምንኖርበት ዓለም ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደ ነው። (2 ጢሞ. 3:13) ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች መፈተኑን አላቆመም። ከፊታችን የሚጠብቀን ፈተና ምንም ይሁን ምን ‘ተስፋችንን የጣልነው ሕያው በሆነው አምላክ ላይ’ እንደሆነ በመተማመን ይሖዋን በትጋት ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (1 ጢሞ. 4:10) አምላክ ለኢዮብ የሰጠው በረከት “ይሖዋ እጅግ አፍቃሪና መሐሪ እንደሆነ” እንደሚያረጋግጥ ልንዘነጋ አይገባም። (ያዕ. 5:11) እኛም ይሖዋ “ከልብ ለሚፈልጉት” ወሮታቸውን እንደሚከፍላቸው በመተማመን ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንጽና።—ዕብራውያን 11:6ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 808
ፌዝ
ኢዮብ ይህ ነው የማይባል ፌዝ ቢሰነዘርበትም ንጹሕ አቋሙን የጠበቀ ጻድቅ ሰው ነበር። ይሁንና የተሳሳተ አመለካከት በማዳበሩ ስህተት ሠርቷል፤ በዚህም የተነሳ እርማት ተሰጥቶታል። ኤሊሁ ስለ እሱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ፌዝን እንደ ውኃ የሚጠጣ፣ እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?” (ኢዮብ 34:7) ኢዮብን ያሳሰበው ከአምላክ ይልቅ የራሱ ትክክለኝነት ነበር፤ እንዲሁም ከአምላክ ይልቅ የራሱን ጽድቅ ከፍ ከፍ አድርጓል። (ኢዮብ 35:2፤ 36:24) ሦስቱ “ጓደኞቹ” የሰነዘሩትን ፌዝ በአምላክ ላይ ሳይሆን በእሱ ላይ እንደተሰነዘረ አድርጎ ቆጥሮታል። በዚህ መንገድ፣ ውኃን በደስታ የመጠጣት ያህል ራሱን ለፌዝ አሳልፎ እንደሚሰጥና እንደሚደሰትበት ዓይነት ሰው ሆኗል። አምላክ በኋላ ለኢዮብ እንደነገረው እነዚህ ፌዘኞች ውሸት የተናገሩት በአምላክ ላይ ነው። (ኢዮብ 42:7) በተመሳሳይም እስራኤላውያን ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ነቢዩ ሳሙኤልን ሲጠይቁት ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ ብሎታል፦ “አልቀበልም ያሉት አንተን አይደለም፤ ይልቁንም ንጉሣቸው አድርገው መቀበል ያልፈለጉት እኔን ነው።” (1ሳሙ 8:7) ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ “[በእናንተ ምክንያት ሳይሆን] በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴ 24:9) አንድ ክርስቲያን እነዚህን ነጥቦች በአእምሮው መያዙ ፌዝን በትክክለኛ መንፈስ እንዲቋቋም የሚረዳው ከመሆኑም ሌላ ለጽናቱ በረከት ለማግኘት ብቁ ያደርገዋል።—ሉቃስ 6:22, 23
ከየካቲት 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 1–4
ከአምላክ መንግሥት ጎን ቁሙ
“ብሔራትንም ሁሉ አናውጣለሁ”
8 ሰዎች ለዚህ መልእክት ምን ምላሽ ሰጥተዋል? አብዛኞቹ ሰዎች በመልእክቱ አልተደሰቱም። (መዝሙር 2:1-3ን አንብብ።) ብሔራት ይህን መልእክት ሲሰሙ ታውከዋል። ይሖዋ የሾመውን ገዢ ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። የምንሰብከውን የመንግሥቱን መልእክት እንደ “ምሥራች” አድርገው አልተመለከቱትም። እንዲያውም አንዳንድ መንግሥታት የስብከቱን ሥራ አግደውታል። የብዙዎቹ ብሔራት ገዢዎች አምላክን እናገለግላለን ቢሉም ሥልጣናቸውን ማስረከብ አይፈልጉም። በመሆኑም በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት ገዢዎች ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ገዢዎችም በኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች ላይ ጥቃት በመሰንዘር፣ ይሖዋ የቀባውን ንጉሥ እየተቃወሙ ነው።—ሥራ 4:25-28
በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የገለልተኝነት አቋማችሁን ጠብቁ
11 ፍቅረ ንዋይ። ላሉን ቁሳዊ ነገሮች ከልክ ያለፈ ፍቅር ካዳበርን ፈታኝ ሁኔታዎች ሲደርሱብን የገለልተኝነት አቋማችንን ልናላላ እንችላለን። በማላዊ የምትኖረው ሩት በ1970ዎቹ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ስደት በደረሰባቸው ወቅት አንዳንድ ወንድሞች ይህን ሲያደርጉ ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “የተመቻቸ ኑሯቸውን መተው ፈተና ሆነባቸው። አንዳንዶች ከእኛ ጋር ቢሰደዱም ከጊዜ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲውን በመቀላቀል ወደ ቤታቸው ተመለሱ፤ ይህን ያደረጉት በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ያለው ያልተመቻቸ ሕይወት ስለከበዳቸው ነው።” ከዚህ በተለየ አብዛኞቹ የአምላክ ሕዝቦች፣ የገለልተኝነት አቋማቸውን በመጠበቃቸው ምክንያት በኢኮኖሚ ቢቸገሩ አሊያም ንብረታቸውን በሙሉ ቢያጡም እንኳ አቋማቸውን አላላሉም።—ዕብ. 10:34
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 425
ገለባ
እንደ ገብስና ስንዴ ያሉ እህሎች ፍሬውን ከጉዳት የሚጠብቅ ስስ ገለባ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ገለባን የሚጠቅሰው ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ቢሆንም በጥንት ዘመን የተለመደውን እህል የመውቃት ሥራ ያስታውሰናል። እህሉ ከታጨደ በኋላ ለምግብነት የማይውለው ገለባ ምንም ጥቅም ስለሌለው ይወገዳል፤ በመሆኑም ገለባ ቀላል፣ የማይጠቅም፣ የማይፈለግና ከጥሩው ተለይቶ መወገድ ያለበትን ነገር የሚያመለክት ጥሩ ምሳሌ ነው።
በመጀመሪያ፣ እህሉ ሲወቃ ገለባው ከፍሬው ይለያል። ከዚያም እህሉን በማዝራት ቀላል የሆነው ገለባ በነፋስ እንዲወሰድ ይደረጋል። (ማዝራት የሚለውን ተመልከት።) ይህ ሂደት ይሖዋ አምላክ ከሃዲዎችን ከሕዝቡ የሚለይበትን እንዲሁም ክፉ ሰዎችንና ተቃዋሚ ብሔራትን የሚያስወግድበትን መንገድ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። (ኢዮብ 21:18፤ መዝ 1:4፤ 35:5፤ ኢሳ 17:13፤ 29:5፤ 41:15፤ ሆሴዕ 13:3) የአምላክ መንግሥት ጠላቶቹን ስለሚያደቃቸው እንደ ገለባ በቀላሉ በነው ይጠፋሉ።—ዳን 2:35
ምንም ጥቅም የሌለው ገለባ ወደተከመረው እህል በነፋስ ተመልሶ እህሉን እንዳይበክለው ብዙውን ጊዜ ተሰብስቦ ይቃጠል ነበር። በተመሳሳይም አጥማቂው ዮሐንስ ክፉ የሆኑት የሐሰት ሃይማኖት አባላት ስለሚጠብቃቸው እሳታማ ጥፋት ሲገልጽ ኢየሱስን እህል በሚወቃ ሰው በመመሰል ስንዴውን ወደ ጎተራ እንደሚያስገባ “ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት” እንደሚያቃጥለው ተናግሯል።—ማቴ 3:7-12፤ ሉቃስ 3:17፤ መውቃት የሚለውን ተመልከት።
ከየካቲት 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 5–7
ሌሎች ምንም ቢያደርጉ ታማኝነታችሁን ጠብቁ
ከቅዱሳን መጻሕፍት ብርታት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
7 ጓደኛህ ወይም የቤተሰብህ አባል በሆነ መንገድ ጎድቶሃል? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ ስለ ንጉሥ ዳዊት እና ስለ ልጁ ስለ አቢሴሎም የሚገልጸውን ታሪክ መመርመርህ ሊጠቅምህ ይችላል። አቢሴሎም አባቱን በመክዳት ንግሥናውን ሊነጥቀው ሞክሮ ነበር።—2 ሳሙ. 15:5-14, 31፤ 18:6-14
8 (1) መጸለይ። ዘገባውን በአእምሮህ ይዘህ፣ የደረሰብህ በደል ምን ስሜት እንደፈጠረብህ ለይሖዋ ንገረው። (መዝ. 6:6-9) ስሜትህን ግልጥልጥ አድርገህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ከዚያም ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው።
እውነትን ማግኘታችሁን አረጋግጡ
3 እምነታችን የአምላክ ሕዝቦች በሚያሳዩት ክርስቲያናዊ ፍቅር ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆን የለበትም። ለምን? ለምሳሌ አንድ የእምነት ባልንጀራችን፣ ምናልባትም አንድ ሽማግሌ ወይም አቅኚ ከባድ ኃጢአት ቢሠራስ? አሊያም አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት በሆነ መንገድ ቢጎዱህስ? ወይም ደግሞ አንድ ሰው ከሃዲ ሆኖ እምነታችን እውነት እንዳልሆነ ቢናገርስ? እንዲህ ዓይነት ነገር ቢያጋጥምህ ተሰናክለህ ይሖዋን ማገልገልህን ታቆማለህ? ነጥቡ ይህ ነው፦ በአምላክ ላይ ያለህ እምነት የተመሠረተው ከይሖዋ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች በሚያደርጉት ነገር ላይ ብቻ ከሆነ እምነትህ ጠንካራ አይሆንም። እምነትህን ለመገንባት እንደ ስሜት ያለ ደካማ ጥሬ ዕቃ ብቻ ሳይሆን እንደ እውቀትና አሳማኝ ማስረጃ ያሉ ጠንካራ ጥሬ ዕቃዎችንም መጠቀም ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ እውነቱን እንደሚያስተምረን ለራስህ ማረጋገጥ አለብህ።—ሮም 12:2
4 ኢየሱስ አንዳንዶች እውነትን “በደስታ” ቢቀበሉም ፈተና ሲደርስባቸው እምነታቸው እንደሚጠፋ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:3-6, 20, 21ን አንብብ።) ምናልባት ኢየሱስን መከተል ተፈታታኝ ሁኔታዎችና መከራ እንደሚያስከትል አልተገነዘቡ ይሆናል። (ማቴ. 16:24) ወይም ደግሞ ክርስትና በበረከት ብቻ የተሞላና ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት መስሏቸው ሊሆን ይችላል። ይሁንና በዚህ ዓለም ውስጥ ችግር ማጋጠሙ አይቀርም። ያለንበት ሁኔታ ሊቀየርና ለተወሰነ ጊዜ ያህል ደስታችን ሊቀንስ ይችላል።—መዝ. 6:6፤ መክ. 9:11
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 995
መቃብር
በሮም 3:13 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ከመዝሙር 5:9 ላይ በመጥቀስ የክፉዎችንና የአታላዮችን ጉሮሮ ‘ከተከፈተ መቃብር’ ጋር አመሳስሎታል። የተከፈተ መቃብር በሙታንና ርኩስ በሆኑ ነገሮች እንደሚሞላ ሁሉ እነሱም ጉሮሯቸውን የሚከፍቱት ገዳይና የሚያረክስ ንግግር ለመናገር ነው።—ከማቴ 15:18-20 ጋር አወዳድር።
ከየካቲት 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 8–10
“ይሖዋ ሆይ፣ በሙሉ ልቤ አወድስሃለሁ”!
በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ ያለህን ቦታ ከፍ አድርገህ ተመልከት
6 ይሖዋ ልዩ መኖሪያ አዘጋጅቶልናል። ይሖዋ የመጀመሪያውን ሰው ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ምድርን ለሰው ልጆች ተስማሚ መኖሪያ እንድትሆን አድርጎ አዘጋጅቷታል። (ኢዮብ 38:4-6፤ ኤር. 10:12) ይሖዋ አሳቢና ለጋስ ስለሆነ የሚያስደስቱንን መልካም ነገሮች አትረፍርፎ ሰጥቶናል። (መዝ. 104:14, 15, 24) የፈጠራቸውን ነገሮች መለስ ብሎ ሲመለከት ሥራው “መልካም እንደሆነ” አይቷል። (ዘፍ. 1:10, 12, 31) ይሖዋ በምድር ላይ በፈጠራቸው አስደናቂ ነገሮች ሁሉ ላይ ለሰዎች “ሥልጣን” በመስጠት አክብሯቸዋል። (መዝ. 8:6) የአምላክ ዓላማ ፍጹም የሆኑ ሰዎች እነዚህን አስደናቂ ፍጥረታት እየተንከባከቡ ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ ነው። ለዚህ ግሩም ተስፋ ይሖዋን አዘውትረህ ታመሰግነዋለህ?
ከአምላክ ላገኘሃቸው ስጦታዎች አድናቆት አለህ?
10 ከአምላክ በስጦታ ላገኘነው የመናገር ችሎታ አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ፣ በዝግመተ ለውጥ ለምን እንደማናምን ለሚጠይቁን ሰዎች አምላክ መኖሩን የምናምንበትን ምክንያት ማስረዳት ነው። (መዝ. 9:1፤ 1 ጴጥ. 3:15) ይህን ጽንሰ ሐሳብ የሚያስፋፉ ሰዎች፣ ምድርና በላይዋ ያለው ሕይወት በሙሉ በአጋጣሚ የተገኙ እንደሆኑ ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። መጽሐፍ ቅዱስን እና በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱትን አንዳንድ ነጥቦች በመጠቀም ለሰማዩ አባታችን ጥብቅና መቆም እንችላለን፤ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ደግሞ ይሖዋ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንደሆነ የምናምንበትን ምክንያት ልናስረዳቸው እንችላለን።—መዝ. 102:25፤ ኢሳ. 40:25, 26
‘በንግግርህ አርዓያ’ ነህ?
13 ከልብ ዘምር። የመንግሥቱን መዝሙሮቻችንን የምንዘምርበት ዋነኛው ምክንያት ይሖዋን ማወደስ ነው። ሣራ የተባለች እህት መዝሙር ላይ ጎበዝ እንደሆነች አይሰማትም። ሆኖም ይሖዋን በመዝሙር ማወደስ ደስ ይላታል። ስለዚህ ለሌሎቹ የስብሰባው ክፍሎች እንደምትዘጋጀው ሁሉ መዝሙሮቹን አስቀድማ ቤቷ ትለማመዳለች። መዝሙሮቹን ስትለማመድ ግጥሞቹ ስብሰባው ላይ ከሚቀርቡት ክፍሎች ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ለማስተዋል ትሞክራለች። “እንዲህ ማድረጌ በመዘመር ችሎታዬ ላይ ሳይሆን በመልእክቱ ላይ ይበልጥ ማተኮር እንድችል ረድቶኛል” ብላለች።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 832
ጣት
አምላክ በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘በጣቱ’ ወይም ‘በጣቶቹ’ ተጠቅሞ የተለያዩ ነገሮችን እንዳከናወነ ተገልጿል፤ ለምሳሌ አሥርቱን ትእዛዛት በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፏል (ዘፀ 31:18፤ ዘዳ 9:10)፤ ተአምራትን ፈጽሟል (ዘፀ 8:18, 19)፤ እንዲሁም ሰማያትን ፈጥሯል (መዝ 8:3)። የአምላክ “ጣቶች” ከፍጥረት ሥራ ጋር በተያያዘ ሲጠቀሱ የሚያመለክቱት መንፈስ ቅዱስን ወይም በሥራ ላይ ያለውን ኃይሉን እንደሆነ የዘፍጥረት ዘገባ ይጠቁማል፤ እዚያ ላይ የአምላክ ኃይል (ሩአህ፣ “መንፈስ”) በውኃው ላይ ይንቀሳቀስ እንደነበር ይናገራል። (ዘፍ 1:2) ይሁንና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የዚህን ቃል ምሳሌያዊ ትርጉም በእርግጠኝነት ለማወቅ ይረዱናል፤ የማቴዎስ ዘገባ ኢየሱስ አጋንንትን ያስወጣው ‘በአምላክ ቅዱስ መንፈስ’ እንደሆነ ሲናገር የሉቃስ ዘገባ ደግሞ “በአምላክ ጣት” እንደሆነ ይገልጻል።—ማቴ 12:28፤ ሉቃስ 11:20
ከየካቲት 26–መጋቢት 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 11–15
ሰላም በሰፈነበት የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ስትኖሩ ይታያችሁ
የመዝሙር አንደኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
11:3—የተናዱት መሠረቶች የትኞቹ ናቸው? ለሰብዓዊው ኅብረተሰብ መሠረት የሆኑት ነገሮች ማለትም ሕግ፣ ሥርዓትና ፍትሕ ናቸው። ሆኖም ይህ መሠረት ከተናጋ ማኅበራዊው ሥርዓት ለውድቀት ይዳረጋል፤ እንዲሁም ፍትሕ አይኖርም። እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች ሥር “ጻድቅ” የሆነ ሰው በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን አለበት።—መዝሙር 11:4-7
ከዓመፅ የጸዳ ዓለም ይመጣል?
አምላክ በቅርቡ ምድራችንን ከዓመፅ እንደሚያጸዳት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በዛሬው ጊዜ ያለው በዓመፅ የተሞላ ዓለም ‘ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቆ ይቆያል።’ (2 ጴጥሮስ 3:5-7) ከዚያ በኋላ ዓመፀኛ ሰዎች ሌሎችን አያሠቃዩም። ታዲያ አምላክ ዓመፅን ማጥፋት እንደሚፈልግ እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ይሖዋ . . . ክፋትን የሚወዱ ሰዎችን ይጠላል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 11:5) ፈጣሪ ሰላምንና ፍትሕን ይወዳል። (መዝሙር 33:5፤ 37:28) በመሆኑም በዓመፀኛ ሰዎች ላይ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ይመጣል።
በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ናችሁ?
15 ዳዊት በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ የነበረው ለምንድን ነው? አራት ጊዜ “እስከ መቼ ነው?” ብሎ በጠየቀበት በዚያው መዝሙር ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ ሰጥቶናል። እንዲህ ብሏል፦ “እኔ በበኩሌ በታማኝ ፍቅርህ እታመናለሁ፤ ልቤ በማዳን ሥራህ ሐሴት ያደርጋል። በእጅጉ ስለካሰኝ ለይሖዋ እዘምራለሁ።” (መዝ. 13:5, 6) ዳዊት በይሖዋ ታማኝ ፍቅር ታምኗል። ዳዊት፣ ይሖዋ እሱን ለማዳን እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ በደስታ ይጠባበቅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ እንዴት እንደካሰው ያሰላስል ነበር። አዎ፣ ዳዊት በትዕግሥት መጠበቁ ፈጽሞ እንደማያስቆጨው ያውቅ ነበር።
መንግሥቱ የአምላክ ፈቃድ በምድር እንዲፈጸም ያደርጋል
16 ያለ ስጋት መኖር። በኢሳይያስ 11:6-9 ላይ የሚገኘው አስደሳች ትንቢት በመጨረሻ ቃል በቃል የተሟላ ፍጻሜውን ሲያገኝ እንመለከታለን። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንዲሁም ልጆች በምድር ላይ በየትኛውም ቦታ ከስጋት ነፃ ሆነው መንቀሳቀስ ይችላሉ። ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ለሌሎች ስጋት አይፈጥሩም። በመላዋ ምድር ላይ እንደ ልብህ መሆን ይኸውም በወንዞች፣ በሐይቆችና በባሕሮች ውስጥ መዋኘት ብሎም በተራሮችና በሣር በተሸፈኑ ሜዳዎች ላይ ያለ ምንም ስጋት መቦረቅ የምትችልበት ጊዜ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ቀኑ መሸ ብለህ የምትፈራበት ምክንያት አይኖርም። በሕዝቅኤል 34:25 ላይ ያለው ሐሳብ ፍጻሜውን ስለሚያገኝ የአምላክ ሕዝቦች “በምድረ በዳ ያለ ስጋት [መኖር]፤ በጫካዎችም ውስጥ [መተኛት]” እንኳ ይችላሉ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ተለውጣችኋል?
12 የሚያሳዝነው ዛሬም የምንኖረው ጳውሎስ የጠቀሳቸው ዓይነት ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ነው። እነዚህ ሰዎች በመሥፈርቶች ወይም በመሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት ጊዜ ያለፈበትና የማያፈናፍን እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። በርካታ አስተማሪዎችና ወላጆች ልል አቋም ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ለልጆች “ነፃነት” እንደሚሰጡ ይናገራሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎች ትክክልና ስህተት የሚባል ነገር እንደሌለና ሁሉም ነገር አንጻራዊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ብዙ ሰዎችም እንኳ አምላክንና ሕግጋቱን መታዘዝ ሳያስፈልጋቸው ትክክል ነው ብለው ያመኑበትን ነገር የማድረግ ነፃነት እንዳላቸው ይሰማቸዋል። (መዝ. 14:1) ይህ አመለካከት ለእውነተኛ ክርስቲያኖች አደገኛ ነው። አንዳንዶች ባለመጠንቀቃቸው ከቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶች ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ አመለካከት አዳብረዋል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ አሠራሮችን ለመከተል ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ፤ እንዲያውም ለእነሱ የማይጥማቸውን ነገር ሁሉ ሊተቹ ይችላሉ። አሊያም መዝናኛን፣ የኢንተርኔት አጠቃቀምን እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት መከታተልን በተመለከተ የሚሰጡትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶች ለመቀበል ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ።