የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ
የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2023 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከመጋቢት 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 16-17
“ይሖዋ . . . ለእኔ የጥሩ ነገሮች ምንጭ አንተ ነህ”
ወጣቶች፣ እርካታ ያለው ሕይወት መምራት ትችላላችሁ
እውነተኛ ጓደኞችን አፍሩ
11 መዝሙር 16:3ን አንብብ። ዳዊት እውነተኛ ጓደኞችን ለማግኘት ቁልፉ ምን እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር መሆን ‘እጅግ ደስ ያሰኘው’ ነበር። “ቅዱሳን” ተብለው የተገለጹት እነዚህ ሰዎች በሥነ ምግባር ንጹሕና ነቀፋ የሌለባቸው ናቸው። አንድ ሌላ መዝሙራዊም ስለ ጓደኛ ምርጫ ተመሳሳይ አመለካከት ነበረው። “አንተን ለሚፈሩ ሁሉ፣ መመሪያዎችህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 119:63) ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው እናንተም ይሖዋን ከሚፈሩና ከሚታዘዙ አገልጋዮቹ መካከል በርካታ ጥሩ ጓደኞችን ማግኘት ትችላላችሁ። እነዚህ ሰዎች በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግልጽ ነው።
‘ይሖዋ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን በትኩረት ተመልከቱ’
ዳዊት እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “[ይሖዋ] የርስት ድርሻዬና ጽዋዬ ነው፤ ዕጣዬም በእጅህ ናት። መካለያ ገመድ ባማረ ስፍራ ተጥሎልኛል።” (መዝ. 16:5, 6) ዳዊት ለተሰጠው ‘ድርሻ’ ይኸውም ከይሖዋ ጋር ለመሠረተው ዝምድና እና እሱን የማገልገል መብት አመስጋኝ ነበር። እኛም እንደ ዳዊት ልዩ ልዩ መከራ ሊደርስብን ይችላል፤ ሆኖም በርካታ መንፈሳዊ በረከቶች አግኝተናል! እንግዲያው በእውነተኛው አምልኮ ደስ መሰኘታችንን እንቀጥል፤ እንዲሁም የይሖዋን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምንጊዜም ‘በአድናቆት እንይ።’
ይሖዋን ዘወትር በፊትህ አድርግ
2 ሁላችንም እንደ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴ፣ ሩት፣ ዳዊት፣ አስቴርና ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታዋቂ ሰዎች ካሳለፉት የሕይወት ተሞክሮ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። እምብዛም ታዋቂ ያልነበሩ ግለሰቦችን ታሪክ ማንበባችንም ቢሆን ጥቅም ያስገኝልናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ ማሰላሰላችን መዝሙራዊው “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ሁልጊዜ በፊቴ አድርጌአለሁ፤ እርሱ በቀኜ ስላለ አልናወጥም” ሲል ከገለጸው ሐሳብ ጋር ተስማምተን እንድንኖር ይረዳናል። (መዝ. 16:8) እነዚህ ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?
3 በውጊያ ላይ ያለ አንድ ወታደር በአብዛኛው ሰይፍ የሚይዘው በቀኝ እጁ ስለሆነ፣ በግራ እጁ የሚይዘው ጋሻ በቀኝ በኩል ያለውን የሰውነቱን ክፍል አይሸፍንለትም። ሆኖም ከእሱ በስተቀኝ ሆኖ የሚዋጋ ጓደኛ ካለው ከለላ ይሆነዋል። ይሖዋን ሁልጊዜ የምናስብና ፈቃዱን የምናደርግ ከሆነ ከጥቃት ይጠብቀናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን መመርመራችን እምነታችንን የሚያጠናክርልን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን ‘ይሖዋን ሁልጊዜ በፊታችን እንድናደርግ’ ይረዳናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ይሖዋ እጅግ ይወድሃል
ዘካርያስ 2:8ን አንብብ። ይሖዋ ስለሚወደን ስሜታችንን ይረዳልናል፤ እንዲሁም ጥበቃ ሊያደርግልን ይጓጓል። ስንጎዳ ያዝናል። በመሆኑም “እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቀኝ” ብለን በልበ ሙሉነት መጸለይ እንችላለን። (መዝ. 17:8) ዓይናችን የምንሳሳለትና ውድ የሆነ የአካላችን ክፍል ነው። ስለዚህ ይሖዋ ከዓይኑ ብሌን ጋር ሲያመሳስለን ‘እናንተን የነካ ውድ ንብረቴን እንደነካ ይቆጠራል’ ያለን ያህል ነው።
ከመጋቢት 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 18
“ይሖዋ . . . ታዳጊዬ ነው”
የይሖዋ ደስታ ምሽጋችን ነው
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ከግዑዛን ነገሮች ጋር ያነጻጽረዋል። ይሖዋ ‘የእስራኤል ዐለት፣’ “መጠጊያ” እንዲሁም “ዐምባ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። (2 ሳሙኤል 23:3፤ መዝሙር 18:2፤ ዘዳግም 32:4) ይሖዋን ከእነዚህ ግዑዛን ነገሮች ጋር የሚያመሳስለው ነጥብ ምንድን ነው? አንድ ትልቅ ዐለት ከቦታው ንቅንቅ እንደማይል ሁሉ ይሖዋ አምላክም አስተማማኝ ከለላ እንደሚሆንልህ ያሳያል።
5 የመዝሙር መጽሐፍ የይሖዋን ባሕርያት የተለያዩ ገጽታዎች ጎላ አድርገው በሚገልጹ ዘይቤያዊ አነጋገሮች የተሞላ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የብርሃን፣ የሕይወትና የኃይል ምንጭ እንዲሁም ጥበቃ የሚገኝበት በመሆኑ መዝሙር 84:11 “ፀሓይና ጋሻ” እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ መዝሙር 121:5 ይሖዋ “በቀኝህ በኩል ይከልልሃል” ይላል። ጥላ ያለው ቦታ ከጠራራ ፀሐይ እንደሚከልል ሁሉ ይሖዋም አገልጋዮቹን ‘በእጁ’ ወይም “በክንፎቹ” ጥላ በመጋረድ ከመከራ ትኩሳት ይጠብቃቸዋል።—ኢሳይያስ 51:16፤ መዝሙር 17:8፤ 36:7
ይሖዋ በደስታ እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው?
ዛሬም “እርዳታ ለማግኘት በምትጮኹበት ጊዜ በእርግጥ ሞገስ ያሳያችኋል” ከሚለው ጥቅስ ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን። (ኢሳ. 30:19) ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ወደ እሱ ስንጮኽ በጥሞና እንደሚያዳምጠንና ለምናቀርበው ምልጃ በአፋጣኝ መልስ እንደሚሰጠን አረጋግጦልናል። አክሎም “ጩኸታችሁን እንደሰማም ይመልስላችኋል” ብሏል። እነዚህ የሚያበረታቱ ቃላት፣ አባታችን ወደ እሱ የሚጮኹትን ለመርዳት እንደሚፈልግ አልፎ ተርፎም እንደሚጓጓ ያስታውሱናል። ይህን ማወቃችን በደስታ ለመጽናት ይረዳናል።
የጸሎት መብታችሁን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱት
የሰማይና የምድር ፈጣሪ ወደሆነው አምላክ በጸሎት የመቅረብ አስደናቂ መብት አግኝተናል። ቀጠሮ መያዝ ሳያስፈልገን በማንኛውም ሰዓት፣ ማንኛውንም ቋንቋ ተጠቅመን ልባችንን ለይሖዋ ማፍሰስ እንችላለን። የሆስፒታል አልጋ ላይም እንሁን እስር ቤት ውስጥ፣ የሚወደን አባታችን እንደሚሰማን ተማምነን ወደ እሱ መጸለይ እንችላለን። ይህን መብት በፍጹም አቅልለን አንመለከተውም።
ጭንቀትን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
2. አሰላስል። እስቲ ሕይወትህን መለስ ብለህ አስብ፤ ‘ይሖዋ ባይረዳኝ ኖሮ ይህን ፈተና ልወጣው አልችልም ነበር’ ያልክበት ወቅት አለ? ይሖዋ እኛንም ሆነ የጥንት አገልጋዮቹን እንዴት እንደረዳቸው ስናሰላስል ውስጣዊ ጥንካሬ እናገኛለን፤ በእሱም ይበልጥ እንተማመናለን። (መዝ. 18:17-19) ጆሹዋ የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ የመለሰልኝ ጸሎቶች ዝርዝር አለኝ። ይህም ይሖዋን አንድ ነገር ለምኜው ልክ የሚያስፈልገኝን ነገር የሰጠኝን ጊዜያት እንዳስታውስ ይረዳኛል።” አዎ፣ ይሖዋ ባደረገልን ነገር ላይ ማሰላሰላችን ኃይላችንን ስለሚያድሰው ጭንቀታችንን ለመቋቋም ብርታት እናገኛለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 432 አን. 2
ኪሩብ
አንዳንዶች እንደሚሉት፣ እነዚህ ኪሩቦች በአካባቢው የነበሩ አረማውያን ብሔራት ያመልኳቸው ከነበሩት ክንፍ ያላቸው አስፈሪና አስቀያሚ ምስሎች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የተሠሩ አይደሉም። ሁሉም የአይሁዳውያን ጥንታዊ ወጎች እንደሚመሠክሩት (እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚገልጸው ነገር የለም) እነዚህ ኪሩቦች በሰው ቅርጽ የተሠሩ ነበሩ። የሚያስደንቅ ውበት ያላቸውን መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚወክሉ ድንቅ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ሲሆኑ ሙሴ ከይሖዋ በተቀበለው ዝርዝር “ንድፍ መሠረት” የተሠሩ ናቸው። (ዘፀ 25:9) ሐዋርያው ጳውሎስ “የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱ ክብራማ ኪሩቦች” ሲል ገልጿቸዋል። (ዕብ 9:5) እነዚህ ኪሩቦች ከይሖዋ መገኘት ጋር ተያይዘው ተገልጸዋል፦ “እኔም በዚያ እገለጥልሃለሁ፤ ከመክደኛውም በላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ። በምሥክሩ ታቦት ላይ በሚገኙት በሁለቱ ኪሩቦች መካከል ሆኜ [አነጋግርሃለሁ]።” (ዘፀ 25:22፤ ዘኁ 7:89) በመሆኑም ይሖዋ “ከኪሩቤል በላይ [ወይም በኪሩቤል መካከል] የተቀመጠው” ተብሎ ተገልጿል። (1ሳሙ 4:4፤ 2ሳሙ 6:2፤ 2ነገ 19:15፤ 1ዜና 13:6፤ መዝ 80:1፤ 99:1፤ ኢሳ 37:16) በምሳሌያዊ አባባል ኪሩቦች፣ ይሖዋ ራሱ የሚነዳው ‘ሠረገላ ምስል’ ሆነው አገልግለዋል (1ዜና 28:18)፤ የኪሩቦቹ ክንፎች ከለላ ሆነው ያገለግላሉ፤ እንዲሁም በፍጥነት ለመጓዝ ያስችላሉ። በመሆኑም ዳዊት፣ ይሖዋ እሱን ለመርዳት በምን ዓይነት ፍጥነት እንደመጣ ሲገልጽ “በኪሩብ ላይ ተቀምጦ እየበረረ መጣ። በመንፈስ ክንፎችም ላይ ሆኖ ይታይ ነበር” በማለት ዘምሯል።—2ሳሙ 22:11፤ መዝ 18:10
ከመጋቢት 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 19-21
“ሰማያት የአምላክን ክብር ይናገራሉ”
ሰው ሁሉ የይሖዋን ክብር ያውጅ
የእሴይ ልጅ ዳዊት ያደገው በቤተ ልሔም አካባቢ እረኛ ሆኖ ነበር። ፀጥ እረጭ ባለ ምሽት የአባቱን መንጎች ሲጠብቅ በከዋክብት የተሞላውን የተንጣለለ ሰማይ በመመልከት ብዙ ጊዜ ሳይደመም አልቀረም! በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አነሳሽነት በ19ኛው መዝሙር ላይ የሚገኙትን ግሩም ቃላት ባቀናበረበትና በዘመረበት ወቅት ይህ አስደናቂ እይታ ወደ አእምሮው እንደመጣ አያጠራጥርም። እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፣ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።”—መዝሙር 19:1, 4
2 ይሖዋ ግርማ ሞገስ አላብሶ የፈጠራቸው ሰማያት ንግግርም ሆነ ቃል እንዲሁም ድምፅ ሳያሰሙ ቀንና ሌሊት የእርሱን ክብር ያውጃሉ። ፍጥረት ያለማቋረጥ የይሖዋን ክብር የሚያውጅ ሲሆን ሁሉም ሰው እንዲሰማው “ወደ ምድር ሁሉ” በወጣው በዚህ ምስክርነት ላይ ማሰላሰላችን ከቁጥር የማንገባ መሆናችንን እንድናስተውል ያደርጋል። ሆኖም ፍጥረት ያለ ድምፅ የሚሰጠው ምስክርነት በቂ አይደለም። ታማኝ የሰው ልጆችም ድምፃቸውን በማሰማት ተፈጥሮ ለሚሰጠው ምስክርነት ድጋፍ እንዲሰጡ ተበረታተዋል። ስሙ ያልተገለጸ አንድ መዝሙራዊ በመንፈስ አነሳሽነት ታማኝ አምላኪዎችን “ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ” ብሏቸዋል። (መዝሙር 96:7, 8) ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና ያላቸው ሰዎች ለዚህ ማበረታቻ በደስታ ምላሽ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ ለአምላክ ክብር ማምጣት ምን ነገሮችን ይጨምራል?
ፍጥረት የአምላክን ክብር ያውጃል!
8 ከዚህ በመቀጠል ዳዊት ይሖዋ ስለፈጠረው ሌላ አስደናቂ ነገር ገልጿል፦ “እርሱ በሰማያት ለፀሓይ ድንኳን ተክሎአል፤ ፀሓይም ከእልፍኙ እንደሚወጣ ሙሽራ ይወጣል፤ ወደ ግቡም እንደሚሮጥ ብርቱ ሰው ደስ ይለዋል። መውጫው ከሰማያት ዳርቻ ነው፤ ዑደቱም እስከ ሌላኛው ዳርቻ ነው፤ ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም።”—መዝሙር 19:4-6
9 ፀሐይ ከሌሎች ከዋክብት ጋር ስትታይ መጠኗ መካከለኛ ነው። ሆኖም አስደናቂ ኮከብ ከመሆኗ የተነሳ በዙሪያዋ የሚሽከረከሩት ፕላኔቶች ከእርሷ አንጻር ሲታዩ ኢምንት ይመስላሉ። አንድ ምንጭ የፀሐይ ክብደት “2 ቢሊዮን ሲባዛ በቢሊዮን ሲባዛ በቢሊዮን ቶን” እንደሆነ ገልጿል። ይህም እኛ ካለንበት ሥርዓተ ፀሐይ መጠነ ቁስ ውስጥ 99.9 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል! ፀሐይ ያላት የስበት ኀይል 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ምድር ከፀሐይ ሳትርቅም ሆነ ወደ ፀሐይ ሳትቀርብ ምኅዋሯን ጠብቃ እንድትዞር ያስችላታል። ፀሐይ ከምታመነጨው ኃይል ውስጥ ወደ ፕላኔታችን የሚደርሰው ከሁለት ቢሊዮን አንድ እጅ ብቻ ነው። ይሁንና ይህ መጠን በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር ለማስቻል በቂ ነው።
10 መዝሙራዊው ፀሐይን በቀን ከአንዱ አድማስ ወደ ሌላው እንደሚሮጥና ሲመሽ ደግሞ ‘ድንኳኑ’ ውስጥ እንደሚገባ “ብርቱ ሰው” አድርጎ ይገልጻታል። ይህች ግዙፍ ኮከብ ከአድማስ ባሻገር ስትጠልቅ፣ ምድር ሆኖ ለሚያያት ሰው ለእረፍት ወደ “ድንኳን” የምትገባ፤ ጎህ ሲቀድ ደግሞ “ከእልፍኙ እንደሚወጣ ሙሽራ” በድንገት ቦግ ብላ የምትወጣ ትመስላለች። ዳዊት እረኛ ስለነበር ማታ ማታ በጣም እንደሚቀዘቅዝ ያውቃል። (ዘፍጥረት 31:40) የፀሐይ ጨረር እርሱንም ሆነ አካባቢውን ወዲያውኑ እንደሚያሞቅም ትዝ ይለዋል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ፀሐይ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የምታደርገው “ጉዞ” ታክቷት አያውቅም፤ እንዲያውም እንደ “ብርቱ ሰው” ጉዞውን ለመድገም ምንጊዜም ዝግጁ ነች።
አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር ይገልጣሉ
የይሖዋን የእጅ ሥራዎች “ልብ ብላችሁ ተመልከቱ”፦ ኢየሱስ ‘የሰማይ ወፎችን’ እና ‘የሜዳ አበቦችን’ ልብ ብለን እንድንመለከት አበረታቶናል። (ማቴ. 6:26, 28) እንዲህ ማድረጋችን በይሖዋ ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከር፣ በፈጣሪ እንድንተማመን እንዲሁም ለጥበቡ፣ ለማዳን ኃይሉና ለፍቅሩ ያለን አድናቆት ከፍ እንዲል ይረዳናል። በመሆኑም ሰዎች ለሚሠሯቸው ነገሮች የበለጠ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ አስደናቂ የሆኑትን የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች ለመመልከትና እነዚህ ፍጥረታት ስለ ታላቁ አምላካችን ስለሚናገሩት ነገር በጥሞና ለማሰብ ጊዜ መመደብ ይኖርብናል።—መዝ. 19:1
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የይሖዋ ዓላማ ይፈጸማል!
ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ለሁሉም የፍጥረት ሥራዎቹ ገደብ አበጅቷል። ሁሉም ነገር እርስ በርስ ተቀናጅቶ መሥራት እንዲችል የተፈጥሮ ሕጎችንና የሥነ ምግባር ደንቦችን አውጥቷል። (መዝ. 19:7-9) በመሆኑም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የየራሳቸው ቦታና ድርሻ አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የስበት ሕግ ከባቢ አየር ምንጊዜም በምድር ዙሪያ እንዲኖር ያደርጋል፤ እንዲሁም የባሕር ሞገድንና ውቅያኖሶችን ይቆጣጠራል። የስበት ኃይል ባይኖር ኖሮ በምድር ላይ ሕይወት አይኖርም ነበር። ይሖዋ ለፍጥረት ሥራዎቹ ያወጣቸው ገደቦች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ፍጹም የሆነ ሥርዓት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ አድርገዋል። እንዲህ ያለ ሥርዓት መኖሩ አምላክ ምድርንም ሆነ የሰውን ዘር ሲፈጥር ዓላማ እንዳለው በግልጽ ያሳያል። በአገልግሎታችን ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች፣ ይህን አስደናቂ አጽናፈ ዓለም የፈጠረውን አምላክ እንዲያውቁ ልንረዳቸው እንችላለን።—ራእይ 4:11
ከመጋቢት 25-31
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 22
ከኢየሱስ ሞት ጋር የተያያዙ ትንቢቶች
መሲሑን አገኙት!
16 መሲሑን አምላክ የተወው ይመስላል። (መዝሙር 22:1ን አንብብ።) ልክ በትንቢት እንደተነገረው “[በዘጠነኛው] ሰዓት ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ‘ኤሊ፣ ኤሊ፣ ላማ ሳባቅታኒ?’ ብሎ ጮኸ፤ ትርጉሙም ‘አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?’ ማለት ነው።” (ማር. 15:34) ኢየሱስ ይህን ማለቱ በሰማይ በሚገኘው አባቱ ላይ ያለው እምነት እንደጠፋ የሚያሳይ አይደለም። አምላክ፣ የክርስቶስ ታማኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈተን ሲል ለእሱ ጥበቃ ማድረጉን በማቆሙ ኢየሱስን በጠላቶቹ እጅ ትቶታል ማለት ይችላል። ኢየሱስ ከላይ እንደተገለጸው ብሎ መጮኹ መዝሙር 22:1 እንዲፈጸም አድርጓል።
መሲሑን አገኙት!
13 ዳዊት፣ መሲሑ እንደሚሰደብ ትንቢት ተናግሯል። (መዝሙር 22:7, 8ን አንብብ።) ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በሚሠቃይበት ወቅት ሰዎች ይሰድቡትና ያፌዙበት እንደነበር ማቴዎስ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በመንገድ የሚያልፉም ይሰድቡት ጀመር፤ ራሳቸውን እየነቀነቁም ‘አይ አንተ፣ ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን መልሼ እሠራለሁ ባይ፣ እስቲ ራስህን አድን! የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት ላይ ውረድ!’ ይሉት ነበር።” በተጨማሪም የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፦ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም! የእስራኤል ንጉሥ እኮ ነው፤ እስቲ አሁን ከተሰቀለበት እንጨት ይውረድና እኛም እንመንበት። በአምላክ ታምኗል፤ ‘የአምላክ ልጅ ነኝ’ ስላለ ከወደደው እስቲ አሁን ያድነው።” (ማቴ. 27:39-43) ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ኢየሱስ ፍጹም እርጋታ ይነበብበት ነበር። ኢየሱስ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!
መሲሑን አገኙት!
14 በመሲሑ ልብሶች ላይ ዕጣ ይጣጣላሉ። መዝሙራዊው “ልብሶቼን ተከፋፈሉ፤ በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 22:18) የተፈጸመውም ይኸው ነበር፤ ኢየሱስን “ከሰቀሉት በኋላ” የሮም ወታደሮች “ዕጣ ተጣጥለው መደረቢያዎቹን ተከፋፈሉ።”—ማቴ. 27:35፤ ዮሐንስ 19:23, 24ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎቻችን አክብሮት ማሳየት
7 ለስብሰባዎቻችን ያለንን አክብሮት በግልጽ ማሳየት የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ በሰዓቱ ተገኝተን የመንግሥቱን መዝሙሮች በመዘመር ነው። አብዛኞቹ መዝሙሮች የጸሎት ይዘት ስላላቸው በአክብሮት ልንዘምራቸው ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ መዝሙር 22ን በመጥቀስ ስለ ኢየሱስ “ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፤ በጒባኤም መካከል ምስጋናህን እዘምራለሁ” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 2:12) በመሆኑም የስብሰባው ሊቀ መንበር መዝሙሩን ከማስተዋወቁ በፊት ስፍራችንን የመያዝና የመዝሙሩ ቃላት ያላቸውን ትርጉም እያሰብን የመዘመር ልማድ ማዳበር ይኖርብናል። አዘማመራችን “በቅኖች ሸንጎ፣ በጉባኤም መካከል፣ ለእግዚአብሔር በፍጹም ልቤ ምስጋና አቀርባለሁ” በማለት የጻፈውን መዝሙራዊ ስሜት የሚያንጸባርቅ እንዲሆን እንጣር። (መዝሙር 111:1) አዎን፣ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር የማቅረብ ፍላጎታችን በጉባኤ ላይ ቀድመን ለመገኘትና እስከ መደምደሚያው ድረስ ለመቆየት የሚገፋፋን አንድ ጥሩ ምክንያት ነው።
ይሖዋን ‘በጉባኤ መካከል’ አመስግኑት
በጥንት ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ ‘በጉባኤ መካከል’ እምነታቸውን መግለጽ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች አሉ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ተሳትፎ ማድረግ ሁሉም ክርስቲያኖች እምነታቸውን መግለጽ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ነው። በስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ያለውን ጥቅም አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። ለምሳሌ ያህል ችግሮችን እንዴት መቋቋም ወይም ማስወገድ እንደሚቻል የሚገልጹ ሐሳቦች ወንድሞቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተል ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክሩላቸዋል። ምዕራፋቸውና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የሚያብራሩ ወይም በግል ምርምር የተገኙ መረጃዎችን ያካተቱ ሐሳቦችን መስጠት ሌሎች ወንድሞችም ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ ሊያበረታታቸው ይችላል።
ከሚያዝያ 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 23-25
“ይሖዋ እረኛዬ ነው”
“ይሖዋ እረኛዬ ነው”
ይሖዋ በጎቹን ይመራል። በጎች እረኛቸው ከሌለ ባዝነው ይጠፋሉ። እኛም በተመሳሳይ ትክክለኛውን የሕይወት ጎዳና ለማግኘት እርዳታ ያስፈልገናል። (ኤርምያስ 10:23) ዳዊት እንደገለጸው ይሖዋ ሕዝቡን ወደ ‘ለመለመ መስክ’ እና ወደ ‘ዕረፍት ውኃ’ ይመራቸዋል። በተጨማሪም “በጽድቅ መንገድ” እየመራ ይወስዳቸዋል። (ቁጥር 2, 3) ውብ ስለሆነው የመሰማሪያ ስፍራ የሚናገረው ይህ መግለጫ በይሖዋ መታመን እንደምንችል ማረጋገጫ ይሰጠናል። አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በገለጸው መሠረት የመንፈሱን አመራር የምንከተል ከሆነ ሕይወታችን እርካታ ያለው ይሆናል፤ እንዲሁም እፎይታና ደኅንነት ይሰማናል።
“ይሖዋ እረኛዬ ነው”
ይሖዋ በጎቹን ይጠብቃል። በጎች ድንጉጦችና አቅመ ቢስ ስለሆኑ የግድ እረኛ ያስፈልጋቸዋል። ይሖዋ ፈጽሞ መፍራት እንደሌለባቸው ለሕዝቡ ነግሯቸዋል፤ ሌላው ቀርቶ “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ” ቢሄዱም በሌላ አማርኛ ሕይወታቸው ምንም ተስፋ የሌለው ጨለማ መስሎ በሚታያቸው ጊዜም እንኳ መፍራት አንደማይገባቸው ገልጾላቸዋል። (ቁጥር 4) ይሖዋ ሁልጊዜም እነሱን ለመርዳት ዝግጁ ስለሆነ በዓይኑ ይከታተላቸዋል። አገልጋዮቹ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ለመወጣት የሚያስችላቸውን ጥበብና ጥንካሬ ሊሰጣቸው ይችላል።—ፊልጵስዩስ 4:13፤ ያዕቆብ 1:2-5
“ይሖዋ እረኛዬ ነው”
ይሖዋ በጎቹን ይመግባቸዋል። በጎች በራሳቸው ምግብ ወዳለበት ስፍራ መሄድ ስለማይችሉ የግድ የእረኛቸውን እጅ ይጠብቃሉ። እኛም መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካት የምንችለው አምላክ በሚሰጠን እርዳታ አማካኝነት ብቻ ነው። (ማቴዎስ 5:3) የሚያስደስተው ነገር ይሖዋ ለጋስ አምላክ በመሆኑ ለአገልጋዮቹ የተትረፈረፈ ማዕድ አዘጋጅቶላቸዋል። (ቁጥር 5) መጽሐፍ ቅዱስና አሁን እያነበብከው እንዳለኸው ያሉ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች፣ የሕይወትን ትርጉምና አምላክ ለእኛ ያለውን ዓላማ ለማወቅ የሚያስችለንን መንፈሳዊ ምግብ ያቀርቡልናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በሙሉ ልብህ ጽድቅን ውደድ
ይሖዋ በቃሉና በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ሕዝቡን “በጽድቅ መንገድ” እየመራቸው ነው። (መዝ. 23:3) ይሁንና ፍጹማን ባለመሆናችን ከዚህ መንገድ መውጣት ይቀናናል። ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመመለስ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። በዚህ ረገድ እንዲሳካልን ምን ሊረዳን ይችላል? እኛም እንደ ኢየሱስ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግን ልንወድ ይገባል።—መዝሙር 45:7ን አንብብ።
2 ‘የጽድቅ መንገድ’ ምንድን ነው? ይህ “መንገድ” በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ላይ የተመሠረተ ነው። በዕብራይስጥና በግሪክኛ “ጽድቅ” የሚለው ቃል “ቀና” የሆነውን ነገር የሚያመለክት ሲሆን ይህም የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን በጥብቅ መከተልን ያመለክታል። ይሖዋ ‘የጽድቅ ማደሪያ’ ስለሆነ አምላኪዎቹ በሥነ ምግባር ረገድ ሊከተሉት የሚገባውን ቀና የሆነውን ጎዳና ለማወቅ ወደ እሱ ዘወር ማለት ይፈልጋሉ።—ኤር. 50:7 የ1954 ትርጉም
3 አምላክን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት የምንችለው ከእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር በፍጹም ልባችን ጥረት የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው። (ዘዳ. 32:4) ይህን ለማድረግ በቅድሚያ ስለ ይሖዋ አምላክ ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምንችለውን ያህል እውቀት መቅሰም ያስፈልገናል። ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቅን መጠን በየዕለቱ ወደ እሱ እየቀረብን የምንሄድ ሲሆን ይህም ጽድቁን ይበልጥ እንድንወድ ይረዳናል። (ያዕ. 4:8) ከዚህም በተጨማሪ በሕይወታችን ውስጥ ከባድ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ወቅት በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ መከተል ይኖርብናል።
ከሚያዝያ 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 26-28
ዳዊት ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ያጠናከረው እንዴት ነው?
በጽኑ አቋምህ ቀጥል
8 ዳዊት “ይሖዋ ሆይ፤ ፈትነኝ፤ መርምረኝ፤ ኩላሊቴንና ልቤን አጥራልኝ” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 26:2 NW) ኩላሊት የሚገኘው በሰውነታችን ውስጠኛው ክፍል ነው። ኩላሊት በምሳሌያዊ አነጋገር የአንድን ሰው ውስጣዊ ሐሳብና ስሜት ያመለክታል። ምሳሌያዊው ልብም በአጠቃላይ የሰውን ውስጣዊ ሁለንተና ማለትም ዝንባሌውን፣ ስሜቱንና ችሎታውን ይወክላል። ዳዊት ይሖዋ እንዲፈትነው ሲለምን ውስጣዊ ሐሳቡንና ስሜቱን በጥልቀትና በጥንቃቄ እንዲያይለት መጠየቁ ነበር።
9 ዳዊት ይሖዋ ኩላሊቱንና ልቡን እንዲያጠራለት ለምኗል። ይሖዋ ውስጣችንን የሚያጠራልን እንዴት ነው? ዳዊት “የመከረኝን እግዚአብሔርን እባርካለሁ፤ ደግሞም በሌሊት ኩላሊቶቼ ይገሥጹኛል” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 16:7 የ1954 ትርጉም) ይህ ምን ማለት ነው? ይሖዋ የሰጠው ምክር ወደ ውስጣዊ ማንነቱ ዘልቆ በመግባትና እዚያ በመቀመጥ ውስጣዊ ሐሳቡንና ስሜቱን እንዳስተካከለለት የሚያሳይ ነው። እኛም በቃሉ፣ እርሱ በሚጠቀምባቸው ሰዎችና በድርጅቱ በኩል የምናገኘውን ምክር በአድናቆት የምናሰላስልበትና በውስጣችን እንዲቆይ የምንፈቅድ ከሆነ ውስጣዊ ማንነታችንን ያስተካክልልናል። በዚህ መንገድ እንዲያጠራን ዘወትር ወደ ይሖዋ መጸለያችን በጽኑ አቋም መሄዳችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።
በጽኑ አቋምህ ቀጥል
12 ዳዊት በጽኑ አቋሙ እንዲሄድ የረዳውን ሌላ ነገር ሲገልጽ “ከማይረቡ ጋር አልተቀመጥሁም፤ ከግብዞችም ጋር አልተባበርሁም። የክፉዎችን ማኅበር ተጸየፍሁ፤ ከዐመፀኞችም ጋር አልቀመጥም” ብሏል። (መዝሙር 26:4, 5) በአጭር አነጋገር ዳዊት ከክፉዎች ጋር አልተቀመጠም። ክፉ ባልንጀርነትን ጠልቷል።
13 እኛስ? በቴሌቪዥን፣ በቪዲዮ፣ በሲኒማ፣ በኢንተርኔት ወይም በሌሎች መንገዶች ከሚቀርቡ ክፉ ሰዎች ጋር ለመቀመጥ እምቢ እንላለን? ከግብዞች ወይም ማንነታቸውን ከሚደብቁ ሰዎች እንርቃለን? በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ አንዳንዶች ስውር ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ወዳጅ መስለው ሊቀርቡን ይችላሉ። በአምላክ እውነት ከማይሄዱ ሰዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንፈልጋለን? ከሃዲዎች ቅን ወይም ምንም ተንኮል የሌላቸው መስለው ለመቅረብ ቢሞክሩም ዋናው ዓላማቸው እኛን ከይሖዋ ማራቅ ነው። በጉባኤ ውስጥ ሁለት ዓይነት ሕይወት የሚመሩ ክርስቲያኖች ቢኖሩስ? እነርሱም ቢሆኑ እውነተኛ ማንነታቸውን ይደብቃሉ። በአሁኑ ጊዜ በጉባኤ አገልጋይነት እያገለገለ ያለው ጄሰን በወጣትነቱ እንዲህ ያሉ ጓደኞች ነበሩት። እነርሱን በሚመለከት እንዲህ ይላል፦ “አንድ ቀን ከእነዚህ ጓደኞቼ መካከል አንዱ ‘አዲሱ ሥርዓት ሲመጣ መጥፋታችን ስለማይቀር አሁን ምንም አደረግን ምን የሚያመጣው ለውጥ የለም። አንዴ ከሞትን ደግሞ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ምን እንዳመለጠን እንኳ አናውቅም’ አለኝ። እንዲህ ዓይነቱ አነጋገር አንድ እርምጃ መውሰድ እንዳለብኝ አስገነዘበኝ። እኔ ደግሞ አዲሱ ሥርዓት ሲመጣ መሞት አልፈልግም።” ጄሰን እንዲህ ካሉ ወጣቶች ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ። ሐዋርያው ጳውሎስ “አትሳቱ፤ ‘መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል’” ሲል አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ከክፉ ባልንጀርነት መራቃችን በእጅጉ አስፈላጊ ነው!
በጽኑ አቋምህ ቀጥል
17 መሠዊያው የሚገኝበት የማደሪያው ድንኳን በእስራኤል የይሖዋ አምልኮ ማዕከል ነበር። ዳዊት በዚያ ሥፍራ ደስ እንደሚሰኝ ሲገልጽ “እግዚአብሔር ሆይ፤ የምትኖርበትን ቤት፣ የክብርህን ማደሪያ ቦታ ወደድሁ” በማለት ጸልዮአል።—መዝሙር 26:8
18 ስለ ይሖዋ ትምህርት በሚሰጥባቸው ቦታዎች መሰብሰብ ያስደስተናል? ዘወትር መንፈሳዊ ትምህርት የሚሰጥበት እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክሮች አዳራሽ በየአካባቢው የአምልኮ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። ከዚህም በተጨማሪ በየዓመቱ የአውራጃ፣ የወረዳና ልዩ ስብሰባ እናደርጋለን። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ‘ምስክሩን’ ወይም ማሳሰቢያውን እንማራለን። የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ‘እጅግ የምንወድ’ ከሆነ በስብሰባዎች ላይ ዘወትር ለመገኘትና በጥሞና ለማዳመጥ ጉጉት ያድርብናል። (መዝሙር 119:167) ስለ ደኅንነታችን ከሚያስቡልንና በጽኑ አቋማችን መሄዳችንን እንድንቀጥል ከሚያበረታቱን የእምነት ወንድሞቻችን ጋር መሰብሰብ እንዴት የሚያስደስት ነው።—ዕብራውያን 10:24, 25
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ይሖዋ መከራ የደረሰባቸውን ያድናል
15 መዝሙራዊው ዳዊት “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 27:10) የይሖዋ ፍቅር ከማንኛውም ወላጅ ፍቅር እንደሚልቅ ማወቁ ምንኛ ያጽናናል! ወላጆችህ ችላ ያሉህ፣ የበደሉህ ወይም የተዉህ መሆኑ የስሜት ስቃይ የሚያስከትልብህ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ያለው ሁኔታ ይሖዋ ለአንተ ያለውን አሳቢነት አይቀንሰውም። (ሮሜ 8:38, 39) አምላክ የሚወዳቸውን ሰዎች ወደ ራሱ እንደሚስባቸው አስታውስ። (ዮሐንስ 3:16፤ 6:44) ሰዎች አንተን የሚይዙበት መንገድ ምንም ይሁን ምን የሰማዩ አባትህ ይወድሃል!
ከሚያዝያ 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 29-31
ተግሣጽ—የአምላክ ፍቅር መግለጫ
it-1 802 አን. 3
ፊት
‘ፊትን መሰወር’ የሚለው አገላለጽ እንደየአገባቡ የተለያየ ትርጉም አለው። ይሖዋ አምላክ ፊቱን ሰወረ ሲባል ብዙውን ጊዜ ሞገሱን ወይም ድጋፉን እንደነሳ ያመለክታል። ይህን የሚያደርገው ሰዎቹ በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ (ለምሳሌ የእስራኤል ብሔር) ባለመታዘዛቸው የተነሳ ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 34:29፤ መዝ 30:5-8፤ ኢሳ 54:8፤ 59:2) አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ፣ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ እርምጃ በመውሰድ ወይም ምላሽ በመስጠት ራሱን ከመግለጥ መቆጠቡን ሊያመለክት ይችላል። (መዝ 13:1-3) ዳዊት “ፊትህን ከኃጢአቴ መልስ” ሲል አምላክ በደሉን እንዲተውለት ወይም ይቅር እንዲለው መጠየቁ ነበር።—መዝ 51:9፤ ከመዝ 10:11 ጋር አወዳድር።
ይሖዋን በደስታ መጠበቅ
ይሖዋ ከሚሰጠን ተግሣጽ የምናገኘው ጥቅም አንድ ፍሬ ከሚበስልበት መንገድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው፣ አምላክ የሚሰጠው ተግሣጽ “ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል።” (ዕብራውያን 12:11) አንድ ፍሬ ለመብሰል ጊዜ እንደሚወስድ ሁሉ እኛም አምላክ የሚሰጠንን ሥልጠና ተቀብለን አመለካከታችንን ለመለወጥ ጊዜ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል፣ መጥፎ ድርጊት በመፈጸማችን በጉባኤ ውስጥ ያሉንን አንዳንድ ኃላፊነቶች ብናጣ አምላክን ለመጠበቅ ፈቃደኛ መሆናችን ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን ዳዊት በመንፈስ አነሳሽነት እንደሚከተለው ብሎ የጻፈው ሐሳብ ያበረታታናል፦ “[የአምላክ ቍጣ] ለዐጭር ጊዜ ነው፤ ቸርነቱ ግን እስከ ዕድሜ ልክ ነውና፤ ሌሊቱን በልቅሶ ቢታደርም፣ በማለዳ ደስታ ይመጣል።” (መዝሙር 30:5) ይሖዋን በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ካዳበርንና ከአምላክ ቃል እንዲሁም ከድርጅቱ የምናገኘውን ምክር በተግባር የምናውል ከሆነ “ደስታ” የምናገኝበት ጊዜ ይመጣል።
እውነተኛ ንስሐ ምንድን ነው?
18 ከጉባኤ የተወገደ አንድ ግለሰብ እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ለማሳየት አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም የሽማግሌዎችን ምክር በመከተል አዘውትሮ መጸለይ እና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይኖርበታል። በተጨማሪም ወደ ኃጢአት ከመሩት ነገሮች ለመራቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለበት። ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለማደስ በርትቶ ከሠራ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር እንደሚለው እንዲሁም ሽማግሌዎች ወደ ጉባኤው እንደሚመልሱት እርግጠኛ መሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች አንድ ኃጢአተኛ ከልቡ ንስሐ መግባቱን ለማረጋገጥ በሚሞክሩበት ወቅት የእያንዳንዱ ሰው ሁኔታ የተለያየ እንደሆነ ከግምት ያስገባሉ። ስለዚህ ጉዳዩን በጥንቃቄ ይመረምራሉ እንዲሁም ግለሰቡ ወደ ጉባኤ መመለስ እንዲችል ከሚጠብቁበት ነገር ጋር በተያያዘ ከልክ በላይ ጥብቅ ላለመሆን ጥረት ያደርጋሉ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ጸሎት—‘የሚያስጨንቃችሁን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ’
ወደ ይሖዋ መጸለያችን እሱ እንደሚያስብልን ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። “ጉስቁልናዬን አይተሃልና፤ በጭንቀት መዋጤን ታውቃለህ” በማለት የጸለየውን መዝሙራዊ ስሜት እንጋራለን። (መዝሙር 31:7) ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ በትኩረት እንደሚመለከት ማወቃችን በራሱ ያጋጠመንን አስቸጋሪ ሁኔታ በጽናት ለመቋቋም ይረዳናል። ሆኖም ይሖዋ ጭንቀታችንን በመመልከት ብቻ አይወሰንም። ያጋጠመንን ችግር ከማንም በተሻለ ይረዳል፤ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ማጽናኛና ማበረታቻ እንድናገኝ ይረዳናል።
ከሚያዝያ 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 32-33
ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን መናዘዝ ያለብን ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምሕረት ተስፋ ከመቁረጥ ያድነናል
7 የአምላክን ሕግ በከባድ ሁኔታ ተላልፈን ከነበረ ኃጢአታችንን ለይሖዋ እንኳን መናዘዝ አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። እንደነዚህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ስንወድቅ ምን ሊደርስብን ይችላል? ዳዊት በመዝሙር 32 ላይ የሚከተለውን የእምነት ቃል ሰጥቶአል፦ “ሁልጊዜ ከመጮሄ የተነሳ [መናዘዝ ስችል] ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፤ በቀንና በሌሊት እጅህ [የይሖዋ እጅ] ከብዳብኛለችና፣ እርጥበቴም ለበጋ ትኩሳት ተለወጠ።” (ቁጥር 3, 4) ከአምላክ መንገድ ወጥቶ የነበረው ዳዊት ኃጢአቱን ለመሰወርና የሕሊናውን ወቀሳ ለማፈን ያደረገው ጥረት በጣም አድክሞት ነበር። ያደረበት የጭንቀት ስሜት ጉልበቱን በሙሉ ስላሟጠጠበት እርጥበት እንደሌለው በድርቅ የተመታ ዛፍ ሆኖ ነበር። እንዲያውም የአእምሮውና የአካሉ ጤንነት ሳይታወክበት አልቀረም። ያም ሆነ ይህ ደስታ አጥቶ ነበር። ማናችንም እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ብንወድቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
“ይቅር ባይ” አምላክ
8 ዳዊት ንስሐ በገባ ጊዜ ‘ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ ’ ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 32:5) እዚህ ላይ “ተውህልኝ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ማንሳት” ወይም “መሸከም” የሚል ትርጉም አለው። ቃሉ እዚህ ጥቅስ ላይ የተሠራበት “የጥፋተኝነት ስሜትን፣ ኃጢአትንና በደልን” ማስወገድ የሚለውን ሐሳብ በሚያስተላልፍ መንገድ ነው። በመሆኑም ይሖዋ የዳዊትን ኃጢአት ከላዩ አንስቶ ያስወገደለት ያህል ነበር። ይህም ዳዊት እንደ ሸክም ሆኖበት የነበረውን የጥፋተኝነት ስሜት እንዳቀለለለት ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 32:3) እኛም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን ምሕረቱን ለማግኘት የሚጥሩ ሰዎችን ኃጢአት ከላያቸው በሚያስወግደው አምላክ ሙሉ በሙሉ መታመን እንችላለን።—ማቴዎስ 20:28
መናዘዝ ፈውስ ያስገኛል
ዳዊት ኃጢአቱን ከተናዘዘ በኋላ የማልረባ ነኝ በሚል ስሜት አልተዋጠም። ኃጢአትን ስለ መናዘዘ በጻፈው መዝሙር ውስጥ የተጠቀመባቸው አገላለጾች እፎይታ እንደተሰማውና አምላክን በታማኝነት ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረገ የሚያሳዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 32ን ተመልከት። በቁጥር 1 ላይ “መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው” የሚል እናነባለን። አንድ ሰው የሠራው ኃጢአት የቱንም ያህል ከባድ ቢሆን ከልቡ ንስሐ ከገባ የኋላ ኋላ ደስታ ማግኘቱ የማይቀር ነው። ንስሐው ልባዊ መሆኑን ማሳየት የሚቻልበት አንደኛው መንገድ ልክ እንደ ዳዊት ለፈጸመው ጥፋት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂው እርሱ መሆኑን አምኖ በመቀበል ነው። (2 ሳሙኤል 12:13) ምንም ስህተት እንዳልፈጸመ ለማሳመን በመሞከር በይሖዋ ፊት ራሱን ንጹሕ አድርጎ ለማቅረብ ወይም ስህተቱን በሌሎች ላይ ለማላከክ አልሞከረም። ቁጥር 5 “ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ” ይላል። እውነተኛ ንስሐ ግለሰቡ ቀደም ሲል የሠራው ኃጢአት ከሚያሳድርበት የህሊና ወቀሳ ስለሚያሳርፈው እፎይታ ያስገኝለታል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የመዝሙር አንደኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
33:6—ከይሖዋ አፍ የሚወጣው “እስትንፋስ” ምንድን ነው? ይህ እስትንፋስ አምላክ ግዑዙን ሰማይ ለመፍጠር የተጠቀመበትን ኃይል ወይም መንፈስ ቅዱስን ያመለክታል። (ዘፍጥረት 1:1, 2) በአፉም እስትንፋስ ተብሎ መጠራቱ እንደ ኃይለኛ እስትንፋስ ሩቅ ድረስ ተልኮ የተፈለገውን ነገር ሊያከናውን እንደሚችል ያሳያል።
ከሚያዝያ 29–ግንቦት 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 34-35
“ይሖዋን ሁልጊዜ አወድሰዋለሁ”
የይሖዋን ስም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ
11 “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፤ ምስጋናውም ዘወትር ከአፌ አይለይም።” (መዝሙር 34:1) ዳዊት ከማኅበረሰቡ ርቆ ይኖር ስለነበር በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ብዙ የሚያሳስቡት ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሆኖም በዚህ ጥቅስ ላይ ካለው ሐሳብ መመልከት እንደምንችለው ዕለታዊ ፍላጎቶቹ ይሖዋን ለማወደስ እንቅፋት እንዲሆኑበት አልፈቀደም። እኛም ችግሮች ሲያጋጥሙን ልንኮርጀው የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! በትምህርት ቤትም ይሁን በሥራ ቦታ እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር እያለን ወይም በአገልግሎት ስንካፈል በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ይሖዋን ማወደስ መሆን አለበት። እንዲህ እንድናደርግ የሚያነሳሱንን በርካታ ምክንያቶች አስብ! ለአብነት ያህል፣ የይሖዋን ድንቅ የፍጥረት ሥራዎች በማወቅ የምናገኘው ደስታ መጨረሻ የለውም። እንዲሁም በድርጅቱ ምድራዊ ክፍል አማካኝነት ስለሚያከናውናቸው ነገሮች አስብ! ይሖዋ በዘመናችን ፍጹማን ያልሆኑ ታማኝ ሰዎችን ከፍተኛ ሥራ ለማከናወን ተጠቅሞባቸዋል። እነዚህ የአምላክ ሥራዎች ዓለም ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች ከሚያከናውኗቸው ተግባሮች ጋር ሲወዳደሩ ምን ይመስላሉ? “ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ የለም፤ ከአንተም ሥራ ጋር የሚወዳደር ሥራ የለም” በማለት ከጻፈው ከዳዊት ጋር አትስማማም?—መዝሙር 86:8
የይሖዋን ስም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ
13 “ነፍሴ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ተመካች፤ ትሑታንም ይህን ሰምተው ሐሤት ያደርጋሉ።” (መዝሙር 34:2) እዚህ ላይ እንደምናየው ዳዊት ባገኘው ስኬት አልተመካም። ለምሳሌ፣ የጌትን ንጉሥ እንዴት እንዳታለለው በጉራ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ በጌት በነበረበት ወቅት ይሖዋ ጥበቃ እንዳደረገለትና ከሞት የተረፈውም በእርሱ እርዳታ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ምሳሌ 21:1) በመሆኑም ዳዊት በራሱ ሳይሆን በይሖዋ ላይ ተመክቷል። ዳዊት አምላክን ማወደሱ ትሑት የሆኑ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ አድርጓቸዋል። ኢየሱስም በተመሳሳይ የአምላክን ስም ሁልጊዜ ያወድስ የነበረ ሲሆን ይህም ትሑትና ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲመጡ አድርጓል። በዛሬው ጊዜ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ትሑት ሰዎች በቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደተገነባው ዓለም አቀፍ ጉባኤ እየጎረፉ ሲሆን የዚህ ጉባኤ ራስ ደግሞ ኢየሱስ ነው። (ቈላስይስ 1:18) ከብሔራት የተውጣጡት እነዚህ ሰዎች፣ ትሑት የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ስሙን ሲያወድሱ ሲሰሙ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሲረዱ ልባቸው ይነካል።—ዮሐንስ 6:44፤ የሐዋርያት ሥራ 16:14
የይሖዋን ስም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ
15 “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ፈለግሁት፤ እርሱም መለሰልኝ፤ ከፍርሀቴም ሁሉ አዳነኝ።” (መዝሙር 34:4) ዳዊት፣ ይሖዋ ያደረገለትን ነገር ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር። በዚህም ምክንያት “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም [“ይሖዋም፣” NW] ሰማው፤ ከመከራውም ሁሉ አዳነው” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 34:6) እኛም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በምንሰበሰብበት ወቅት ይሖዋ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንድንወጣ እንዴት እንደረዳን የሚያወሱ አበረታች ተሞክሮዎችን ለማውራት ሰፊ አጋጣሚ እናገኛለን። ዳዊት የተናገራቸው ነገሮች አብረውት የነበሩትን ሰዎች እምነት እንዳጠናከሩላቸው ሁሉ እኛም እንዲህ ማድረጋችን የክርስቲያን ባልንጀሮቻችንን እምነት ይገነባል። ከዳዊት ጋር የነበሩት ሰዎች ‘ወደ ይሖዋ በመመልከት አብርተዋል፤ ፊታቸውም ከቶ አላፈረም።’ (መዝሙር 34:5) እነዚህ ሰዎች ከንጉሥ ሳኦል ይሸሹ የነበረ ቢሆንም አላፈሩም። አምላክ፣ ከዳዊት ጋር እንደሆነ እርግጠኞች ስለነበሩ ፊታቸው ያበራ ነበር። በተመሳሳይም ፍላጎት ያላቸው አዲስ ሰዎችም ሆኑ ለረጅም ጊዜ ጸንተው የቆዩ እውነተኛ ክርስቲያኖች እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ይላሉ። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ስለረዳቸው በታማኝነት ለመጽናት ያደረጉት ቁርጥ ውሳኔ በሚያበራው ፊታቸው ላይ ይንጸባረቃል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የመዝሙር አንደኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
35:19—ዳዊት ጠላቶቹ በዐይናቸው እንዳይጣቀሱበት ሲለምን ምን ማለቱ ነበር? ጠላቶቹ በዐይናቸው መጣቀሳቸው በዳዊት ላይ የጠነሰሱት የክፋት ሤራ በመሳካቱ እንደተደሰቱ የሚያሳይ ሲሆን ዳዊትም የጸለየው ይህ እንዳይሆን ነበር።