የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2024 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከግንቦት 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 36–37
“በክፉዎች አትበሳጭ”
የአምላክ መንግሥት ሲመጣ የትኞቹ ነገሮች ይወገዳሉ?
4 ክፉ ሰዎች በዛሬው ጊዜ በእኛ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የምንኖርበት ጊዜ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” እንደሚሆን ትንቢት ከተናገረ በኋላ “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ” ሲል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (2 ጢሞ. 3:1-5, 13) ይህ ትንቢት እየተፈጸመ እንደሆነ አስተውለሃል? ብዙዎቻችን በክፉ ሰዎች ይኸውም በጉልበተኞች፣ ጭፍን ጥላቻ ባላቸው ግለሰቦችና ጨካኝ በሆኑ ወንጀለኞች ጥቃት ደርሶብን ያውቃል። ከእነዚህ አንዳንዶቹ የክፋት ድርጊታቸውን ለመደበቅ እንኳ አይሞክሩም፤ ሌሎች ደግሞ መልካም መስለው በመቅረብ የክፋት ድርጊታቸውን ለመሸፈን የሚሞክሩ አስመሳዮች ናቸው። እንዲህ ያለ ጥቃት ደርሶብን የማያውቅ ቢሆን እንኳ ክፉ ሰዎች በእኛ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም። ክፉዎች የሚፈጽሟቸውን ዘግናኝ ድርጊቶች ስንሰማ በጣም እናዝናለን። እነዚህ ሰዎች በልጆች፣ በአረጋውያን እንዲሁም አቅመ ደካማ በሆኑ ሌሎች ሰዎች ላይ ግፍ ሲፈጽሙ ስሜታችን በጣም ይረበሻል። ክፉ ሰዎች የሚፈጽሙት ድርጊት ኢሰብዓዊ፣ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው። (ያዕ. 3:15) የሚያስደስተው ነገር የአምላክ ቃል የሚያጽናና ምሥራች ይዟል።
ይሖዋ ይቅር ባዮችን ይባርካል
10 ቂም መያዝ ራሳችንን ይጎዳናል። ቂም ከባድ ሸክም ነው፤ ይሖዋ ይህን ሸክም ከላያችን አውርደን እፎይ እንድንል ይፈልጋል። (ኤፌሶን 4:31, 32ን አንብብ።) “ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው” የሚል ምክር ሰጥቶናል። (መዝ. 37:8) ይህን ምክር መከተል በጣም ጠቃሚ ነው። ቂም መያዝ አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጤንነታችንን ሊጎዳው ይችላል። (ምሳሌ 14:30) ደግሞም ቂም ይዘን የበደለን ሰው እንዲጎዳ መጠበቅ እኛ መርዝ እየጠጣን የበደለን ሰው እንዲጎዳ ከመጠበቅ ተለይቶ አይታይም። ሌሎችን ይቅር ስንል ለራሳችን ስጦታ እየሰጠን ነው ሊባል ይችላል። (ምሳሌ 11:17) አእምሯችንና ልባችን ሰላም ያገኛል፤ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ወደፊት መግፋት እንችላለን።
‘በይሖዋ ደስ ይበላችሁ’
20 “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ” የሚለው ጥቅስ ፍጻሜውን ያገኛል። (መዝሙር 37:11ሀ) ይሁንና “ገሮች” የተባሉት እነማን ናቸው? “ገር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ማስጨነቅ፣ ማዋረድ፣ ዝቅ ማድረግ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የተገኘ ነው። አዎን፣ “ገሮች” የተባሉት የደረሰባቸውን የፍትሕ መጓደል በሙሉ ይሖዋ እንዲያስተካክልላቸው ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚጠባበቁ ሰዎች ናቸው። “በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:11ለ) በአሁኑ ጊዜም እንኳ በእውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ ገነት በማግኘታችን ብዙ ሰላም አለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 445
ተራራ
አለመናወጥ፣ ቋሚነት ወይም ከፍታ። ተራሮች የማይናወጡ እና ቋሚ ናቸው። (ኢሳ 54:10፤ ዕን 3:6፤ ከመዝ 46:2 ጋር አወዳድር።) በመሆኑም፣ መዝሙራዊው የይሖዋ ጽድቅ “እንደ አምላክ ተራሮች” (መዝ 36:6 ግርጌ) እንደሆነ ሲናገር የይሖዋ ጽድቅ ሊለዋወጥ የማይችል መሆኑን መግለጹ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ፣ ተራሮች ከፍ ያሉ ስለሆኑ ይህ ሐሳብ የአምላክ ጽድቅ ከሰዎች ጽድቅ በእጅጉ የላቀ እንደሆነ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። (ከኢሳ 55:8, 9 ጋር አወዳድር።) ራእይ 16:20 የአምላክን ቁጣ የያዘው ሰባተኛ ጽዋ ስለመፍሰሱ ሲናገር “ተራሮችም ሊገኙ አልቻሉም” ይላል። ይህም እንደ ተራራ ከፍ ያሉ ነገሮችም እንኳ ከአምላክ ቁጣ ሊያመልጡ እንደማይችሉ ይጠቁማል።—ከኤር 4:23-26 ጋር አወዳድር።
ከግንቦት 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 38-39
ከመጠን ያለፈ የበደለኝነት ስሜትን ማስወገድ
የወደፊቱን ጊዜ “በትኩረት ተመልከት”
12 አንደኛ ዮሐንስ 3:19, 20ን አንብብ። ሁላችንም አልፎ አልፎ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች እውነትን ከመስማታቸው በፊት ባደረጓቸው ነገሮች የተነሳ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ እንዲህ የሚሰማቸው ከተጠመቁ በኋላ በፈጸሟቸው ስህተቶች የተነሳ ነው። እንዲህ ያለው ስሜት የተለመደ ነው። (ሮም 3:23) ማናችንም ብንሆን ትክክለኛውን ነገር ማድረግ እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።” (ያዕ. 3:2፤ ሮም 7:21-23) የጥፋተኝነት ስሜት ደስ የሚል ነገር ባይሆንም ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የጥፋተኝነት ስሜት አካሄዳችንን እንድናስተካክልና ስህተታችንን ላለመድገም እንድንጥር ስለሚያነሳሳን ነው።—ዕብ. 12:12, 13
13 በሌላ በኩል ግን ንስሐ ከገባንና ይሖዋ ይቅር እንዳለን ካሳየን በኋላም እንኳ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማን ይሆናል፤ ይህ ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ነው። እንዲህ ያለው የጥፋተኝነት ስሜት ጎጂ ነው። (መዝ. 31:10፤ 38:3, 4) ለምን? ቀደም ሲል በፈጸመችው ኃጢአት የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት ትሠቃይ የነበረችን አንዲት እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህች እህት “ምሕረት እንደማላገኝ ስለተሰማኝ በይሖዋ አገልግሎት በትጋት ለመካፈል ጥረት ማድረጌ ምንም ዋጋ እንደሌለው አሰብኩ” ብላለች። ብዙዎቻችን የእህትን ስሜት መረዳት አይከብደንም። እንግዲያው ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ወጥመድ እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ። ደግሞም ይሖዋ በእኛ ተስፋ ሳይቆርጥ እኛ በራሳችን ተስፋ ቆርጠን እሱን ማገልገላችንን ብናቆም ሰይጣን ምን ያህል እንደሚደሰት አስበው!—ከ2 ቆሮንቶስ 2:5-7, 11 ጋር አወዳድር።
ሕይወታችንን በይሖዋ ፊት ትርጉም ባለው መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
የሕይወት ዘመናችን አጭርና እንደ ጥላ በቅጽበት የሚያልፍ ነው። መዝሙራዊው ዳዊት በሕይወት አጭርነት ላይ ካሰላሰለ በኋላ “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሕይወቴን ፍጻሜ፣ የዘመኔንም ቁጥር አስታውቀኝ፤ አላፊ ጠፊ መሆ[ኔ]ንም ልረዳ። እነሆ፤ ዘመኔን በስንዝር ለክተህ አስቀመጥህ፤ ዕድሜዬም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው” ብሎ ለመጸለይ ተገፋፍቷል። ዳዊትን የሚያሳስበው በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ አምላክን የሚያስደስት አኗኗር መከተሉ ነበር። እምነቱን የጣለው በአምላክ ላይ እንደሆነ ሲናገር “ተስፋዬ በአንተ ላይ ነው” ብሏል። (መዝሙር 39:4, 5, 7 አ.መ.ት ) ይሖዋም ሰምቶታል። በእርግጥም ደግሞ ይሖዋ ዳዊትን የሚያደርጋቸውን ነገሮች አንድ በአንድ በመመዘን ባርኮታል።
እያንዳንዷን ደቂቃ በሥራ ተጠምዶ ማሳለፍና በጥድፊያ የተሞላ ሕይወት መምራት ይቻላል። ብዙ ማከናወን ያለብን ነገር እንዳለና ጊዜ እንደሚያጥረን ተሰምቶን ልንጨነቅ እንችላለን። ይሁን እንጂ የሚያሳስበን ልክ እንደ ዳዊት ሕይወታችንን የአምላክን ሞገስ እንድናገኝ በሚያስችለን መንገድ መምራት ነው? ይሖዋ እያንዳንዳችንን እንደሚመለከተንና ሁኔታችንን በጥንቃቄ እንደሚመረምር የተረጋገጠ ነው። ፈሪሃ አምላክ የነበረው ኢዮብ ከዛሬ 3,600 ዓመት በፊት ይሖዋ አካሄዱን እንደሚመለከትና እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን እንደሚመረምር ተገንዝቦ ነበር። ኢዮብ “ሲጠይቀኝስ ምን መልስ እሰጣለሁ?” በማለት ጠይቋል። (ኢዮብ 31:4-6, 14 አ.መ.ት ) ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት፣ የአምላክን ትእዛዛት በመጠበቅና ጊዜያችንን በጥበብ በመጠቀም ሕይወታችንን በአምላክ ፊት ትርጉም ባለው መንገድ መምራት እንችላለን። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመርምራቸው።
ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት አድስ
ወደ ይሖዋ አዘውትረህ ጸልይ። በሰማይ ያለው አባትህ፣ የሚሰማህ የጥፋተኝነት ስሜት ወደ እሱ መጸለይ እንዲከብድህ ሊያደርግ እንደሚችል ይረዳል። (ሮም 8:26) ያም ቢሆን ‘ሳትታክት ጸልይ’፤ የእሱ ወዳጅ ለመሆን ምን ያህል እንደምትጓጓ ለይሖዋ ንገረው። (ሮም 12:12) አንድሬ እንዲህ ብሏል፦ “ከፍተኛ የጥፋተኝነትና የኀፍረት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ሆኖም ወደ ይሖዋ በጸለይኩ ቁጥር ይህ ስሜት እየቀነሰ መጣ። ውስጣዊ ሰላም እያገኘሁ ሄድኩ።” ምን ብለህ መጸለይ እንዳለብህ ግራ ከገባህ ንጉሥ ዳዊት ያቀረባቸውን የንስሐ ጸሎቶች መለስ ብለህ አንብብ፤ እነዚህ ጸሎቶች በመዝሙር 51 እና 65 ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
እምነት የሚጣልባችሁ መሆናችሁን አስመሥክሩ
16 የሌሎችን አመኔታ ማትረፍ ከፈለግን ራስን መግዛት የግድ ያስፈልገናል። በሚስጥር የተነገረንን ነገር ለማውራት ስንፈተን ይህ ባሕርይ አንደበታችንን ለመቆጣጠር ይረዳናል። (ምሳሌ 10:19ን አንብብ።) ማኅበራዊ ሚዲያ በምንጠቀምበት ጊዜ ራስን የመግዛት ባሕርያችን ሊፈተን ይችላል። ካልተጠነቀቅን ሳናስበው ሚስጥራዊ የሆኑ መረጃዎችን ለብዙ ሰዎች ልናሰራጭ እንችላለን። አንድን መረጃ ኢንተርኔት ላይ ካወጣነው በኋላ መረጃው በምን መልኩ ጥቅም ላይ እንደሚውል ወይም ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ መቆጣጠር አንችልም። ከዚህም ሌላ ራስን መግዛት ተቃዋሚዎች ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን አደጋ ላይ የሚጥል መረጃ ለማወጣጣት በሚሞክሩበት ወቅት ዝም እንድንል ይረዳናል። በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ገደብ በተጣለባቸው አገሮች ውስጥ ፖሊሶች ምርመራ ሲያደርጉብን እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። በእነዚህም ሆነ በሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‘አፋችንን ለመጠበቅ ልጓም ማስገባት’ ይኖርብናል። (መዝ. 39:1) ከቤተሰቦቻችን፣ ከጓደኞቻችን፣ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ሰው ጋር ባለን ግንኙነት እምነት የሚጣልብን መሆን ይኖርብናል። እምነት የሚጣልብን ለመሆን ደግሞ ራሳችንን መግዛት ያስፈልገናል።
ከግንቦት 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 40-41
ሌሎችን መርዳት ያለብን ለምንድን ነው?
በልግስና መስጠት ደስታ ያስገኛል
16 እውነተኛ ልግስና የሚያሳይ ሰው በምላሹ የሆነ ነገር ለማግኘት አይጠብቅም። ኢየሱስ ይህን ሐሳብ በአእምሮው በመያዝ የሚከተለውን ትምህርት ሰጥቷል፦ “ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ አንካሶችንና ዓይነ ስውራንን ጥራ፤ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ ደስተኛ ትሆናለህ።” (ሉቃስ 14:13, 14) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ለጋስ ሰው ይባረካል” ብሏል። ሌላኛው ደግሞ “ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 22:9፤ መዝ. 41:1) በእርግጥም ሌሎችን መርዳት ደስታ ስለሚያስገኝ በልግስና መስጠት ይኖርብናል።
17 ጳውሎስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ጠቅሷል፤ ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ቁሳዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ለሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ማበረታቻ፣ መመሪያና ሌላ ዓይነት ድጋፍ ስለመስጠት ጭምር ነው። (ሥራ 20:31-35) ይህ ሐዋርያ ጊዜን፣ ጉልበትን፣ ትኩረትን እና ፍቅርን በልግስና በመስጠት ረገድ በንግግሩም ሆነ በተግባሩ ምሳሌ ትቶልናል።
18 ስለ ሰዎች ባሕርይ የሚያጠኑ ተመራማሪዎችም መስጠት ሰዎችን ደስተኛ እንደሚያደርጋቸው ተገንዝበዋል። “አንዳንድ ሰዎች፣ ለሌሎች መልካም ካደረጉ በኋላ ደስታቸው በጣም እንደጨመረ ተናግረዋል” በማለት አንድ ጽሑፍ ገልጿል። ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ሰዎች ሌሎችን መርዳታቸው ሕይወታቸው “ይበልጥ ዓላማና ትርጉም ያለው እንዲሆን በማድረግ” ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፤ “ምክንያቱም መሠረታዊ የሆነው የሰው ልጆች ፍላጎት እንዲሟላ ያደርጋል።” በመሆኑም አንዳንድ ባለሙያዎች ሰዎች ጤንነታቸው እንዲሻሻልና ደስታቸው እንዲጨምር ከፈለጉ ማኅበረሰቡን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ በፈቃደኝነት እንዲሳተፉ ያበረታታሉ። እርግጥ ይህ ሐሳብ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ያስጻፈው መጽሐፍ እንደሆነ አምነው ለሚቀበሉ ሰዎች የሚያስደንቅ አይደለም።—2 ጢሞ. 3:16, 17
ይሖዋ ይደግፍሃል
7 ያም ቢሆን ጥንት የነበሩ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች እንዳደረጉት እኛም በምንታመምበት ጊዜ መጽናኛ፣ ጥበብና ድጋፍ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ማለት እንችላለን። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው፤ በመከራ ቀን ይሖዋ ይታደገዋል። ይሖዋ ይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል።” (መዝ. 41:1, 2) እርግጥ ነው፣ ዳዊት ይህን ሲል በዚያ ዘመን የኖረ ለተቸገረ የሚያስብ አንድ ሰው፣ ሞትን ፈጽሞ አያይም ማለቱ እንዳልነበረ እናውቃለን። በመሆኑም ዳዊት፣ ለተቸገረ የሚያስብ ሰው በተአምራዊ ሁኔታ ሕይወቱ እንደሚቀጥልና ለዘላለም እንደሚኖር መናገሩ አይደለም። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ አምላክ፣ ታማኝና ለሌሎች አሳቢ የሆኑ ሰዎችን እንደሚረዳ የሚጠቁም ነው። የሚረዳቸው እንዴት ነው? ዳዊት ይህን ሲያብራራ “ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ ይሖዋ ይደግፈዋል፤ በታመመበት ወቅት መኝታውን ሙሉ በሙሉ ትቀይርለታለህ” ብሏል። (መዝ. 41:3) ለተቸገረ አሳቢነት ያሳየ ሰው፣ አምላክ እሱንም ሆነ የታማኝነት አካሄዱን እንደማይረሳ እርግጠኛ መሆን ይችላል። በተጨማሪም አምላክ፣ ሰውነታችን ራሱን በራሱ የመጠገን ችሎታ እንዲኖረው አድርጎ ስለፈጠረን ግለሰቡ ከበሽታው ሊያገግም ይችላል።
እንደ ይሖዋ ሩኅሩኅ ሁኑ
17 ርኅራኄ እንድናሳይ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ራሳችንን እንደሚጠቅመን መገንዘባችን መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ የፍቅርና የርኅራኄ ምንጭ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ለመምሰልና እሱን ለማስከበር ያለን ፍላጎት መሆን ይኖርበታል። (ምሳሌ 14:31) በዚህ ረገድ ይሖዋ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። እንግዲያው እሱን በመምሰል ርኅራኄ ለማሳየት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ፤ ይህም ከወንድሞቻችን ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ይረዳናል።—ገላ. 6:10፤ 1 ዮሐ. 4:16
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 16
ይሖዋ
መላው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሚያጠነጥነው በይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ላይ ነው፤ ይህም የይሖዋ አምላክ ዋነኛ ዓላማ ምን እንደሆነ ያሳያል፤ እሱም የስሙ መቀደስ ነው። የአምላክ ስም እንዲቀደስ ስሙ ከማንኛውም ዓይነት ነቀፋ ነፃ መሆን አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በሰማይና በምድር ያሉ ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታት በሙሉ ይህን ስም ቅዱስ አድርገው መመልከትና ማክበር አለባቸው። ይህም ሲባል የይሖዋን ሉዓላዊነት መቀበልና ማክበር፣ ይህን በፈቃደኝነት ማድረግ፣ እሱን ለማገልገል መፈለግ፣ ለእሱ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው የእሱን መለኮታዊ ፈቃድ በማድረግ መደሰት አለባቸው ማለት ነው። ዳዊት በመዝሙር 40:5-10 ላይ ለይሖዋ ያቀረበው ጸሎት እንዲህ ያለውን ዝንባሌ እንዲሁም የይሖዋ ስም መቀደስ ያለውን እውነተኛ ትርጉም ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። (ሐዋርያው ዕብ 10:5-10 ላይ የዚህን መዝሙር የተወሰነ ክፍል ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አያይዞ የጠቀሰው እንዴት እንደሆነ ልብ በል።)
ከግንቦት 27–ሰኔ 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 42-44
ከመለኮታዊ ትምህርት የተሟላ ጥቅም አግኙ
የመዝሙር ሁለተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
42:4, 5, 11፤ 43:3-5፦ ከአቅማችን በላይ በሆነ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ከክርስቲያን ጉባኤ ተለይተን ከሆነ፣ ከዚህ ቀደም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባሳለፍናቸው አስደሳች ትዝታዎች ላይ ማሰላሰላችን እንድንጽናና ሊረዳን ይችላል። እንዲህ ማድረጋችን መጀመሪያ ላይ የብቸኝነት ስሜታችንን ሊያባብሰው ቢችልም እንኳ አምላክ መጠጊያችን እንደሆነና እፎይታ ለማግኘት እርሱን መጠበቅ እንደሚያስፈልገን ያስታውሰናል።
የጥናት ጊዜህን ይበልጥ አስደሳችና ውጤታማ ማድረግ
1 መጸለይ፦ የመጀመሪያው እርምጃ መጸለይ ነው። (መዝ. 42:8) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የአምላክን ቃል ማጥናት የአምልኳችን ክፍል እንደሆነ አድርገን መመልከት ይኖርብናል። ስለዚህ አእምሯችንንና ልባችንን ለጥናቱ ለማዘጋጀት እንዲረዳን ብሎም ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ይሖዋን መለመን ያስፈልገናል። (ሉቃስ 11:13) በሚስዮናዊነት ለረጅም ጊዜ ያገለገለችው ባርባራ እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ወይም ማጥናት ከመጀመሬ በፊት ሁልጊዜ እጸልያለሁ። ከዚያ በኋላ ይሖዋ ከእኔ ጋር እንደሆነና በማደርገው ጥረት እንደሚደሰት ይሰማኛል።” ጥናት ከመጀመራችን በፊት መጸለያችን ከፊታችን የቀረበልንን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ሙሉ በሙሉ ለመቀበል አእምሯችንና ልባችን ክፍት እንዲሆን ይረዳናል።
‘እጆቻችሁ አይዛሉ’
11 ከዚህም ሌላ በጉባኤ ስብሰባዎችና በትላልቅ ስብሰባዎች እንዲሁም በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች አማካኝነት ከሚሰጠን ትምህርት ብርታት እናገኛለን። የምናገኘው ሥልጠና መንፈሳዊ ግቦች እንድናወጣ እንዲሁም ያሉብንን በርካታ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶች እንድንፈጽም ያነሳሳናል። (መዝ. 119:32) አንተስ በዚህ መንገድ ከሚቀርብልን ትምህርት ብርታት ለማግኘት እንደምትጓጓ ታሳያለህ?
12 ይሖዋ፣ አማሌቃውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ድል እንዲያደርጉ እስራኤላውያንን ረድቷቸዋል፤ ለነህምያና አብረውት ለነበሩት አይሁዳውያንም የከተማዋን ቅጥር እንደገና ገንብተው ለማጠናቀቅ የሚያስችል ኃይል ሰጥቷቸዋል። ዛሬም በተመሳሳይ የሚያጋጥመንን ተቃውሞ፣ የሰዎችን ግዴለሽነትና ያለብንን ጭንቀት ተቋቁመን የስብከቱን ሥራ ማከናወን እንድንችል ብርታት ይሰጠናል። (1 ጴጥ. 5:10) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ተአምር ይፈጽምልናል ብለን መጠበቅ የለብንም። ከዚህ ይልቅ እኛ የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። ይህም የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበብን፣ ለሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን መዘጋጀትንና በስብሰባዎች ላይ መገኘትን፣ በግል ጥናትና በቤተሰብ አምልኮ አማካኝነት በመንፈሳዊ ራሳችንን መመገብን እንዲሁም በይሖዋ በመታመን አዘውትረን ወደ እሱ መጸለይን ይጨምራል። ሌሎች እንቅስቃሴዎች፣ ይሖዋ እኛን ለማበርታትና ለማጠናከር ባደረጋቸው ዝግጅቶች እንዳንጠቀም እንቅፋት እንዲሆኑብን ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም። ከላይ ከተጠቀሰው ከየትኛውም ዝግጅት ጋር በተያያዘ እጃችሁ እንደዛለ ከተሰማችሁ አምላክ እንዲረዳችሁ ጸልዩ። ከዚያም መንፈሱ “ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በማድረግ ኃይል የሚሰጣችሁ” እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ። (ፊልጵ. 2:13) በሌላ በኩል ደግሞ የሌሎችን እጆች ማበርታት የምትችሉት እንዴት ነው?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 1242
ቀበሮ
በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ቀበሮ በተደጋጋሚ ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል። ኢዮብ ስላለበት አሳዛኝ ሁኔታ ሲናገር “የቀበሮዎች ወንድም . . . ሆንኩ” ብሏል። (ኢዮብ 30:29) መዝሙራዊው የአምላክ ሕዝቦች ስለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት ሲናገር “ቀበሮዎች በሚኖሩበት ቦታ ሰባብረኸናል” ብሏል (መዝ 44:19)፤ ይህን ያለው ቀበሮዎች በጦርነቱ የሞቱትን ለመብላት በጦር አውድማው ላይ መሰብሰባቸውን ለማመልከት ሊሆን ይችላል። (ከመዝ 68:23 ጋር አወዳድር።) ባቢሎናውያን በ607 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን በከበቡበት ወቅት ከባድ ረሃብ በመከሰቱ እናቶች በገዛ ልጆቻቸው ላይ የጭካኔ ድርጊት ፈጽመው ነበር። በመሆኑም ኤርምያስ ‘የሕዝቡን’ ጭካኔ ቀበሮዎች ልጆቻቸውን ከሚይዙበት መንገድ ጋር አነጻጽሮታል።—ሰቆ 4:3, 10
ከሰኔ 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 45-47
ስለ ንጉሡ ሠርግ የሚገልጽ መዝሙር
በበጉ ሠርግ ደስ ይበላችሁ!
8 መዝሙር 45:13, 14ሀን አንብብ። ሙሽራዋ ለንጉሣዊው ሠርግ “ከላይ እስከ ታች ተሸልማ” ተዘጋጅታለች። ራእይ 21:2 ላይ ሙሽራዋ በአንዲት ከተማ ይኸውም በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ተመስላ የተገለጸች ሲሆን ‘ለባሏ አጊጣለች።’ ይህች ሰማያዊት ከተማ “የአምላክን ክብር” የተላበሰች ከመሆኑም ሌላ ብርሃኗ “እጅግ እንደከበረ ድንጋይ፣ እንደ ኢያስጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ክሪስታል ጥርት ብሎ [ያንጸባርቃል]።” (ራእይ 21:10, 11) አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የተላበሰችው ዕፁብ ድንቅ የሆነ ውበት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ማራኪ በሆነ መንገድ ተገልጿል። (ራእይ 21:18-21) መዝሙራዊው፣ ሙሽራዋ ‘ከላይ እስከ ታች እንደተሸለመች’ አድርጎ መግለጹ ምንም አያስገርምም! ደግሞም የንጉሡ ሠርግ የሚከናወነው በሰማይ ነው።
9 ሙሽራዋ የተወሰደችው ወደ ሙሽራው ይኸውም ወደ መሲሐዊው ንጉሥ ነው። “በቃሉ አማካኝነት በውኃ አጥቦ በማንጻት” ሲያዘጋጃት ቆይቷል። ሙሽራዋ “ቅዱስና እንከን የለሽ” ነች። (ኤፌ. 5:26, 27) በተጨማሪም ሙሽራዋ ለሠርጉ የሚስማማ አለባበስ ሊኖራት ይገባል። ደግሞም እጅግ ተውባለች! ‘ልብሷ ወርቀ ዘቦ’ ሲሆን ‘በጥልፍ ሥራ ባጌጠ ልብስ ወደ ንጉሡ ትወሰዳለች።’ ለበጉ ሠርግ “የሚያንጸባርቅና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቷታል፤ ምክንያቱም ይህ ጥሩ በፍታ የቅዱሳንን የጽድቅ ተግባር ያመለክታል።”—ራእይ 19:8
የራእይ መጽሐፍ፣ የወደፊት ሕይወትህን የሚመለከት ምን ሐሳብ ይዟል?
10 ይሖዋ ለዚህ የጭካኔ ጥቃት ምን ምላሽ ይሰጣል? “ታላቅ ቁጣዬ ይነድዳል” ብሏል። (ሕዝ. 38:18, 21-23) ራእይ ምዕራፍ 19 ከዚያ በኋላ ምን እንደሚከናወን ይነግረናል። ይሖዋ ሕዝቡን ለመታደግና ጠላቶቹን ለመደምሰስ ልጁን ይልከዋል። ኢየሱስ በሚወስደው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ “በሰማይ ያሉት ሠራዊቶች” አብረውት ይሆናሉ፤ እነሱም ታማኝ መላእክትና 144,000ዎቹ ናቸው። (ራእይ 17:14፤ 19:11-15) የጦርነቱ ውጤት ምን ይሆናል? ይሖዋን የሚቃወሙ ሰዎችና ድርጅቶች በሙሉ ተጠራርገው ይጠፋሉ።—ራእይ 19:19-21ን አንብብ።
11 በምድር ያሉ ታማኝ ሰዎች በአምላክ ጠላቶች ላይ ከሚደርሰው ጥፋት ሲተርፉ ምን ያህል እንደሚደሰቱ እስቲ አስበው! ያ ጊዜ ምንኛ አስደሳች ይሆናል! ታላቂቱ ባቢሎን ስትጠፋ በሰማይ ታላቅ የደስታ ጩኸት ይሰማል፤ ሆኖም ከዚያ የበለጠ ደስታ የሚያስገኝ ነገር አለ። (ራእይ 19:1-3) እሱም “የበጉ ሠርግ” ነው፤ እንዲያውም ይህ ክንውን የራእይ መጽሐፍ ታላቅ መደምደሚያ ነው።—ራእይ 19:6-9
12 የበጉ ሠርግ የሚደረገው መቼ ነው? ሁሉም የ144,000ዎቹ አባላት ከአርማጌዶን ጦርነት በፊት በሰማይ ይሆናሉ። ሆኖም የበጉ ሠርግ የሚደረገው በዚህ ወቅት አይደለም። (ራእይ 21:1, 2ን አንብብ።) ሠርጉ የሚከናወነው የአርማጌዶን ጦርነት ከተካሄደና የአምላክ ጠላቶች በሙሉ ከጠፉ በኋላ ነው።—መዝ. 45:3, 4, 13-17
it-2 1169
ጦርነት
ይህ ጦርነት ሲያበቃ በምድር ላይ ለአንድ ሺህ ዓመት ሰላም ይሰፍናል። “[ይሖዋ] ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል። ቀስትን ይሰባብራል፤ ጦርንም ያነክታል፤ የጦር ሠረገሎችን በእሳት ያቃጥላል” የሚለው መዝሙር የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው አምላክ የጠላቶቻቸውን የጦር መሣሪያዎች በመሰባበር ለእስራኤላውያን ሰላም ባመጣበት ጊዜ ነው። ክርስቶስ የጦርነት ደጋፊዎችን በአርማጌዶን ድል ካደረገ በኋላ በምድር ላይ ከዳር እስከ ዳር የተሟላና አርኪ ሰላም ይሰፍናል። (መዝ 46:8-10) የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ [የቀጠቀጡ]” እና “ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት [የማይማሩ]” ሰዎች ናቸው። “የሠራዊት ጌታ የይሖዋ አፍ ተናግሯልና።”—ኢሳ 2:4፤ ሚክ 4:3, 4
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአምላክ መንግሥት ሲመጣ የትኞቹ ነገሮች ይወገዳሉ?
9 ምግባረ ብልሹ የሆኑ ድርጅቶች በምን ይተካሉ? ከአርማጌዶን በኋላ በምድር ላይ የሚቀር ድርጅት ይኖራል? መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል” ይላል። (2 ጴጥ. 3:13) አሮጌው ሰማይና ምድር ማለትም ምግባረ ብልሹ መንግሥታትም ሆኑ በእነሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ክፉው ኅብረተሰብ ይወገዳሉ። ከዚያም ‘በአዲስ ሰማያትና በአዲስ ምድር’ ይተካሉ። “አዲስ ሰማያት” የሚለው አገላለጽ አዲስ መንግሥትን የሚያመለክት ሲሆን “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ ደግሞ በዚህ መንግሥት የሚተዳደርን በምድር ላይ የሚኖር አዲስ ኅብረተሰብ ያመለክታል። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው ይህ መንግሥት፣ ሁሉ ነገር በሥርዓት እንዲከናወን የሚፈልገውን የይሖዋ አምላክን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባርቃል። (1 ቆሮ. 14:40) “አዲስ ምድር” የተባለው በምድር ላይ የሚኖረው ኅብረተሰብም በሥርዓት የተደራጀ ይሆናል። በዚህ ኅብረተሰብ ውስጥ የተለያዩ ጉዳዮችን የሚያከናውኑ መልካም ምግባር ያላቸው ወንዶች ይሾማሉ። (መዝ. 45:16) እነዚህን ወንዶች የሚመሯቸው ክርስቶስና ከእሱ ጋር የሚገዙት 144,000ዎች ይሆናሉ። ምግባረ ብልሹ የሆኑ ድርጅቶች በሙሉ ተወግደው መልካም ምግባር ባለው አንድ ድርጅት ሲተኩ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር እስቲ አስበው!
ከሰኔ 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 48-50
ወላጆች—ቤተሰባችሁ በይሖዋ ድርጅት ላይ ያለውን እምነት አጠናክሩ
እውነተኛው አምልኮ ደስታ ይጨምርላችኋል
11 የአምላክን ቃል ስናጠናና ልጆቻችንን ስለ ይሖዋ ስናስተምር አምልኮ እያቀረብን ነው። ሰንበት እስራኤላውያን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን አቁመው ከይሖዋ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ የሚያተኩሩበት አጋጣሚ ይሰጣቸው ነበር። (ዘፀ. 31:16, 17) ታማኝ እስራኤላውያን ልጆቻቸውን ስለ ይሖዋና ስለ እሱ ጥሩነት ያስተምሯቸው ነበር። እኛም በግለሰብ ደረጃ የአምላክን ቃል የምናነብበትና የምናጠናበት ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። ይህ ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ክፍል ሲሆን ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። (መዝ. 73:28) በቤተሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ደግሞ አዲሱ ትውልድ ማለትም ልጆቻችን አፍቃሪ ከሆነው ሰማያዊው አባታችን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ እንረዳቸዋለን።—መዝሙር 48:13ን አንብብ።
ለመደሰት የሚያበቃ ምክንያት አላችሁ
“በጽዮን አካባቢ ተመላለሱ፤ ዙሪያዋንም ሂዱ፤ የጥበቃ ግንበኞቿንም ቍጠሩ፤ ለሚቀጥለው ትውልድ ትናገሩ ዘንድ፣ መከላከያ ዕርዶቿን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ መጠበቂያ ማማዎቿን እዩ።” (መዝ. 48:12, 13) እዚህ ላይ መዝሙራዊው፣ እስራኤላውያን ኢየሩሳሌምን በደንብ እንዲመለከቷት አሳስቧቸዋል። በየዓመቱ በሚከበሩት በዓላት ላይ ለመገኘት ወደ ቅድስቲቱ ከተማ የተጓዙና እጹብ ድንቅ የሆነውን ቤተ መቅደሷን የተመለከቱ እስራኤላውያን ቤተሰቦች ምን ዓይነት አስደሳች ትዝታ ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት ትችላለህ? የተመለከቱትን ነገር “ለሚቀጥለው ትውልድ” ለመናገር እንደሚነሳሱ ጥርጥር የለውም።
የሳባን ንግሥት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህች ንግሥት መጀመሪያ ላይ አስደናቂ ስለሆነው የሰለሞን ግዛትና ስለ ታላቅ ጥበቡ የሰማችውን አላመነችም ነበር። የሰማችው ነገር እውነት መሆኑን እንድታምን ያደረጋት ምን ነበር? “መጥቼ በዓይኔ እስካየሁ ጊዜ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር” ብላለች። (2 ዜና 9:6) አዎን፣ ‘በዓይናችን’ የምናየው ነገር በጥልቅ ሊነካን ይችላል።
ልጆቻችሁን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያሉትን አስደናቂ ነገሮች ‘በዓይናቸው’ እንዲመለከቱ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? በአካባቢያችሁ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ካለ ለመጎብኘት ጥረት አድርጉ። ማንዲ እና ቤተኒ ያደጉበት አካባቢ በአገራቸው ከሚገኘው ቤቴል 1,500 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል። ያም ሆኖ ወላጆቻቸው በተለይ ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ቤቴልን በተደጋጋሚ ጊዜ ለመጎብኘት ዝግጅት ያደርጉ ነበር። ልጆቹ እንዲህ በማለት ይናገራሉ፦ “ቤቴልን ከመጎብኘታችን በፊት ብዙም የማይስብና ለትልልቅ ሰዎች ብቻ የሚሆን ቦታ እንደሆነ ይሰማን ነበር። ይሁንና ይሖዋን በትጋት የሚያገለግሉና በሥራቸው ደስተኛ የሆኑ ወጣቶችን ተመለከትን! የይሖዋ ድርጅት እኛ በምንኖርበት አካባቢ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በጣም ሰፊ እንደሆነ ተገነዘብን፤ ቤቴልን በጎበኘን ቁጥር ወደ ይሖዋ ይበልጥ የቀረብን ከመሆኑም በላይ እሱን የበለጠ ለማገልገል አነሳስቶናል።” ማንዲ እና ቤተኒ በአምላክ ድርጅት ውስጥ የሚከናወኑትን ነገሮች በቅርበት መመልከታቸው አቅኚ እንዲሆኑ አነሳስቷቸዋል፤ ውሎ አድሮ በቤቴል ጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው እንዲያገለግሉ ተጋብዘዋል።
አኗኗራችሁ የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆናችሁን የሚያሳይ ይሁን!
5 ታሪኩን ማጥናት። የአንድን አገር ዜግነት ለማግኘት የሚፈልግ ሰው ስለ አገሪቱ ታሪክ በተወሰነ መጠን ማወቅ ሊኖርበት ይችላል። በተመሳሳይም የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ስለዚህ መንግሥት የተቻለውን ያህል ለማወቅ ጥረት ማድረግ አለበት። እስቲ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ያገለግሉ የነበሩት የቆሬ ልጆች የተዉትን ምሳሌ እንመልከት። ለኢየሩሳሌምና ለአምልኮ ስፍራው ልዩ ፍቅር የነበራቸው ከመሆኑም በላይ ስለ ከተማዋ ታሪክ መናገር ያስደስታቸው ነበር። የቆሬን ልጆች የማረካቸው ግንቡና ሕንፃው ሳይሆን ከተማዋና የአምልኮ ቦታው የሚያመለክቱት ነገር ነው። ኢየሩሳሌም የንጹሕ አምልኮ ማዕከል በመሆኗ “የታላቁ ንጉሥ” ማለትም የይሖዋ “ከተማ” ነበረች። ሰዎች የይሖዋን ሕግ የሚማሩት በዚያ ነበር። ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው ኢየሩሳሌም በሚኖረው ንጉሥ አማካኝነት ለሚመራቸው ሕዝቡ ነው። (መዝሙር 48:1, 2, 9, 12, 13ን አንብብ።) አንተስ የይሖዋን ድርጅት ምድራዊ ክፍል ታሪክ የማጥናትና ስለ ድርጅቱ በደስታ የመናገር ፍላጎት አለህ? ስለ አምላክ ድርጅትና ይሖዋ ሕዝቦቹን ስለሚደግፍበት መንገድ ይበልጥ ባወቅህ መጠን የአምላክ መንግሥት የበለጠ እውን ይሆንልሃል። የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ያለህ ፍላጎትም እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም።—ኤር. 9:24፤ ሉቃስ 4:43
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 805
ሀብት
እስራኤላውያን ባለጸጋ ብሔር ስለነበሩ በመብላትና በመጠጣት መደሰት ይችሉ ነበር (1ነገ 4:20፤ መክ 5:18, 19)፤ እንዲሁም ሀብታቸው ድህነት ከሚያስከትላቸው ችግሮች ጥበቃ ያስገኝላቸው ነበር። (ምሳሌ 10:15፤ መክ 7:12) ይሁንና፣ እስራኤላውያን ተግተው በመሥራት ብልጽግና ማግኘታቸው ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ቢሆንም እንኳ (ምሳሌ 6:6-11፤ 20:13፤ 24:33, 34 ጋር አወዳድር) ይሖዋ የብልጽግናቸው ምንጭ እሱ መሆኑን መዘንጋትና በሀብታቸው መታመን መጀመር ስለሚያስከትለው አደጋ አስጠንቅቋቸዋል። (ዘዳ 8:7-17፤ መዝ 49:6-9፤ ምሳሌ 11:4፤ 18:10, 11፤ ኤር 9:23, 24) ሀብት ሊጠፋ የሚችል ነገር እንደሆነ (ምሳሌ 23:4, 5)፣ አንድን ሰው ከሞት ለማዳን ቤዛ ሆኖ ለአምላክ ሊሰጥ እንደማይችል (መዝ 49:6, 7) እንዲሁም ለሙታን ምንም ዋጋ እንደሌለው ተነግሯቸዋል። (መዝ 49:16, 17፤ መክ 5:15) ለሀብት ከልክ ያለፈ ቦታ መስጠት ወደ ማጭበርበርና የይሖዋን ሞገስ ወደማጣት ሊመራ እንደሚችል ተገልጾላቸዋል። (ምሳሌ 28:20፤ ከኤር 5:26-28፤ 17:9-11 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ‘ባሏቸው ውድ ነገሮች ይሖዋን እንዲያከብሩ’ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።—ምሳሌ 3:9
ከሰኔ 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 51-53
ከባድ ስህተት እንዳንሠራ ምን ይረዳናል?
ልብህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
4 በምሳሌ 4:23 ላይ የሚገኘው “ልብ” የሚለው ቃል “የውስጥ ሰውነትን” ለማመልከት ተሠርቶበታል። (መዝሙር 51:6ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) በሌላ አባባል “ልብ” የሚለው ቃል የውስጥ ሐሳብን፣ ስሜትን፣ ዝንባሌንና ምኞትን ያመለክታል። ቃሉ ከውጭ ስንታይ የምንመስለውን ሳይሆን ውስጣዊ ማንነታችንን ይጠቁማል።
5 ውስጣዊ ማንነታችንን መጠበቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለመረዳት አካላዊ ጤንነታችንን እንደ ምሳሌ አድርገን መውሰድ እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሰውነታችን ጤናማ እንዲሆን ከፈለግን የተመጣጠነ ምግብ መመገብና አዘውትረን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብናል። በተመሳሳይም መንፈሳዊ ጤንነታችንን መጠበቅ ከፈለግን የተመጣጠነ መንፈሳዊ ምግብ መመገብና በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት አዘውትረን በተግባር ማሳየት ይኖርብናል። እምነታችንን በተግባር ማሳየት፣ የተማርናቸውን ነገሮች ተግባራዊ ማድረግንና ስለምናምንባቸው ነገሮች ለሌሎች መናገርን ይጨምራል። (ሮም 10:8-10፤ ያዕ. 2:26) በሁለተኛ ደረጃ፣ ውስጣችን በበሽታ ቢጠቃም ከውጫዊ ገጽታችን በመነሳት ጤናማ የሆንን ሊመስለን ይችላል። በተመሳሳይም በውስጣችን የተሳሳተ ምኞት እያቆጠቆጠ ቢሆንም በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ስለምንካፈል ብቻ ጠንካራ እምነት ያለን ሊመስለን ይችላል። (1 ቆሮ. 10:12፤ ያዕ. 1:14, 15) ሰይጣን በእሱ አስተሳሰብ ሊበክለን እንደሚሞክር መዘንጋት አይኖርብንም። ለመሆኑ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? እኛስ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን
5 በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደምንታመን ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ርኩስ ሐሳቦችን ለማስወገድ በምናደርገው ትግል እሱ እንዲረዳን መጸለይ ነው። በጸሎት አማካኝነት ወደ ይሖዋ ስንቀርብ እሱም ወደ እኛ ይቀርባል። ቅዱስ መንፈሱን በልግስና ስለሚሰጠን የብልግና ሐሳቦችን ለማስወገድና ንጹሕ ሆነን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። እንግዲያው በልባችን በምናሰላስለው ነገር አምላክን የማስደሰት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለን ለእሱ በጸሎት እንንገረው። (መዝ. 19:14) ታዲያ ወደ ኃጢአት ሊመራን የሚችል ማንኛውም “ጎጂ የሆነ ዝንባሌ” ይኸውም ተገቢ ያልሆነ ምኞት ወይም ሐሳብ በውስጣችን መኖሩን ማወቅ እንድንችል አምላክ እንዲመረምረን በትሕትና እንጠይቀዋለን? (መዝ. 139:23, 24) እንዲሁም ፈተና ሲያጋጥመን ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ እንዲረዳን አዘውትረን እንለምነዋለን?—ማቴ. 6:13
6 አስተዳደጋችን ወይም የቀድሞ አኗኗራችን ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች እንድንወድ ተጽዕኖ ያደርግብን ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ እሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማገልገላችንን እንድንቀጥል የሚያስፈልጉትን ለውጦች ለማድረግ ይረዳናል። ንጉሥ ዳዊት ይህን ተገንዝቦ ነበር። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ከፈጸመ በኋላ ይሖዋን “ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር” በማለት ተማጽኖታል። (መዝ. 51:10, 12) ደካማው ሥጋችን በኃጢአት ድርጊቶች በቀላሉ ሊማረክ ይችላል፤ ይሁንና ይሖዋ የፈቃደኝነት መንፈስ ይኸውም እሱን የመታዘዝ ፍላጎት በውስጣችን እንዲቀሰቀስ ሊረዳን ይችላል። መጥፎ ምኞቶች በውስጣችን ሥር ሰደው ንጹሕ ሐሳቦችን ገፍተው ለማውጣት ቢሞክሩም እንኳ ይሖዋ የእሱን መመሪያዎች በመታዘዝ በዚያ መሠረት መኖር እንድንችል አካሄዳችንን ይመራልናል። ይሖዋ ማንኛውም ጎጂ ነገር በእኛ ላይ እንዳይሠለጥን ሊከላከልልን ይችላል።—መዝ. 119:133
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 644
ዶይቅ
ዶይቅ የንጉሥ ሳኦል እረኞች አለቃ ሆኖ በኃላፊነት ቦታ የሚያገለግል ኤዶማዊ ነበር። (1ሳሙ 21:7፤ 22:9) ዶይቅ ወደ ይሁዲነት ተቀይሮ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ዶይቅ ኖብ ውስጥ “በይሖዋ ፊት እንዲቆይ በመገደዱ” (ምናልባትም በስእለት ምክንያት፣ የረከሰ ነገር ተገኝቶበት ወይም የሥጋ ደዌ በሽታ እንዳለበት ተጠርጥሮ ሊሆን ይችላል) ሊቀ ካህናቱ አሂሜሌክ ለዳዊት ገጸ ኅብስቱንና የጎልያድን ሰይፍ ሲሰጠው ተመልክቷል። ከጊዜ በኋላ ሳኦል “ደባ ፈጽማችሁብኛል” ብሎ ለአገልጋዮቹ ሲናገር ዶይቅ ኖብ ውስጥ ያየውን ነገር ተናገረ። ሳኦል ሊቀ ካህናቱንና በኖብ የነበሩትን ሌሎቹን ካህናት አስጠርቶ አሂሜሌክን ከጠየቀው በኋላ ካህናቱን እንዲገድሏቸው ጠባቂዎቹን አዘዛቸው። ጠባቂዎቹ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሲገልጹ ዶይቅ የሳኦልን ትእዛዝ ተከትሎ 85 ካህናትን ያለምንም ማመንታት ገደለ። ዶይቅ ይህን አስከፊ ድርጊት ከፈጸመ በኋላ ልጅ አዋቂ ሳይል የኖብን ነዋሪዎች በሙሉ ከነከብቶቻቸው በመግደል ከተማይቱን አጠፋ።—1ሳሙ 22:6-20
በመዝሙር 52 አናት ላይ ያለው ሐሳብ እንደሚገልጸው ዳዊት ስለ ዶይቅ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ምላስህ እንደ ምላጭ የተሳለ ነው፤ ጥፋትን ይሸርባል፤ ተንኮልንም ያቀነባብራል። መልካም ከሆነው ነገር ይልቅ ክፋትን፣ ትክክል የሆነውን ነገር ከመናገር ይልቅ ሐሰትን ትወዳለህ። አንተ አታላይ ምላስ! ጎጂ ቃልን ሁሉ ትወዳለህ።”—መዝ 52:2-4
ከሰኔ 24-30
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 54-56
አምላክ ከጎናችሁ ነው
አምላክን በመፍራት ጠቢብ ሁን!
10 በአንድ ወቅት ዳዊት፣ በንጉሥ አንኩስ ወደምትተዳደረውና የጎልያድ የትውልድ ከተማ ወደሆነችው ወደ ጌት ተሰድዶ ነበር። (1 ሳሙኤል 21:10-15) በዚያም የንጉሡ አገልጋዮች የሕዝባቸው ጠላት እንደሆነ በመናገር ዳዊትን አጋለጡት። ዳዊት በዚህ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ምን እርምጃ ይወስድ ይሆን? የልቡን ግልጽልጽ አድርጎ ወደ ይሖዋ ጸለየ። (መዝሙር 56:1-4, 11-13) ዳዊት በፊቱ ከተደቀነው አደጋ ለማምለጥ እንደ አበደ ሰው መሆን አስፈልጎት የነበረ ቢሆንም ጥረቱን በመባረክ የተሳካ እንዲሆን ያደረገለት ይሖዋ መሆኑን ያውቅ ነበር። ዳዊት በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመኑ በእርግጥም ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው እንደነበር ያሳያል።—መዝሙር 34:4-6, 9-11
11 ልክ እንደ ዳዊት እኛም፣ አምላክ ችግሮቻችንን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ እንደሚሰጠን በገባው ቃል ላይ በመታመን እርሱን እንደምንፈራ ማሳየት እንችላለን። ዳዊት “መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 37:5) ይህ ማለት ግን፣ ችግሮቻችንን ሁሉ በይሖዋ ላይ በመጣል እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጣለን ማለት አይደለም። ዳዊት አምላክ እንዲረዳው ከጸለየ በኋላ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ አልተወውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በሰጠው ጉልበትና አእምሮ ተጠቅሞ ችግሩን ተወጥቷል። ያም ቢሆን ግን ዳዊት ጥረታችን ብቻውን ውጤት እንደማያስገኝ ተገንዝቧል፤ አምላክ ከእኛ ጋር መሆን አለበት። የቻልነውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ቀሪውን ለይሖዋ ልንተውለት ይገባል። እውነት ነው፣ ብዙውን ጊዜ በይሖዋ ከመታመን ያለፈ ነገር ማድረግ አንችል ይሆናል። በዚህ ጊዜ አምላክን በእርግጥ እንደምንፈራ ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን። ዳዊት ከልብ በመነጨ ስሜት ተገፋፍቶ “እግዚአብሔር ምስጢሩን ከሚፈሩት ወዳጆቹ አይሰውርም” በማለት የተናገራቸው ቃላት ያጽናኑናል።—መዝሙር 25:14
“ከአምላክ ፍቅር ሊለየን” የሚችል ነገር የለም
9 ይሖዋ የምናሳየውን ጽናትም ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (ማቴዎስ 24:13) ሰይጣን ይሖዋን ማምለክህን እንድትተው እንደሚፈልግ አስታውስ። እያንዳንዱን ቀን ለይሖዋ ታማኝ ሆነህ የምታሳልፍ ከሆነ ይሖዋን ለሚነቅፈው ለሰይጣን መልስ በመስጠት ረገድ የበኩልህን አስተዋጽኦ ታደርጋለህ። (ምሳሌ 27:11) ይሁንና ጸንቶ መኖር ቀላል አይደለም። የጤና እክል፣ የኑሮ ውድነት፣ ጭንቀትና ሌሎች ችግሮች እያንዳንዱን ቀን ፈታኝ ሊያደርጉብን ይችላሉ። በተጨማሪም የጠበቅነው ነገር እንዳሰብነው ቶሎ አለመፈጸሙ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። (ምሳሌ 13:12) እንዲህ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ስንጸና ይሖዋ እጅግ ይደሰታል። ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን “እንባዬን በአቁማዳህ አጠራቅም” በማለት የጠየቀው ለዚህ ነው። አክሎም “ደግሞስ በመጽሐፍህ ውስጥ ሰፍሮ የለም?” ሲል በእርግጠኝነት ተናግሯል። (መዝሙር 56:8) አዎን፣ ይሖዋ ከእሱ ጎን በታማኝነት ለመቆም ስንል የምናፈስሰውን እንባና የሚደርስብንን ሥቃይ ፈጽሞ አይረሳም። እንዲህ ያለውን መከራና ሥቃይ በጽናት ለመቋቋም የምናደርገው ጥረት በይሖዋ ዘንድ ከፍ ያለ ግምት ይሰጠዋል።
ፍቅር ፍርሃትን እንድናሸንፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
16 ሰይጣን ሕይወታችንን እንደምንወድ ያውቃል። በመሆኑም ዕድሜያችንን ለማራዘም ስንል ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ጨምሮ ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ከማድረግ ወደኋላ እንደማንል ተናግሯል። (ኢዮብ 2:4, 5) ሰይጣን ምንኛ ተሳስቷል! ያም ቢሆን “ለሞት የመዳረግ አቅም ያለው” ሰይጣን፣ ለሞት ያለንን ተፈጥሯዊ ፍራቻ ተጠቅሞ ይሖዋን እንድንተው ለማድረግ ይሞክራል። (ዕብ. 2:14, 15) አንዳንድ ጊዜ የሰይጣን ወኪሎች፣ የይሖዋ አገልጋዮች እምነታቸውን ካልካዱ እንደሚገድሏቸው ይዝቱባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰይጣን፣ ያለብንን ከባድ የጤና እክል ተጠቅሞ አቋማችንን እንድናላላ ለማድረግ ይሞክራል። ሐኪሞች ወይም የማያምኑ ቤተሰቦቻችን ደም እንድንወስድ ይገፋፉን ይሆናል፤ ደም መውሰድ ደግሞ የአምላክን ሕግ መጣስ ነው። አንዳንዶች ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ሕክምና እንድንከታተል ሊያግባቡን ይሞክሩ ይሆናል።
17 መሞት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም ብንሞትም እንኳ ይሖዋ እኛን መውደዱን እንደማያቆም ማስታወስ ይኖርብናል። (ሮም 8:37-39ን አንብብ።) ይሖዋ ወዳጆቹ ቢሞቱም እንኳ በሕይወት ያሉ ያህል ያስታውሳቸዋል። (ሉቃስ 20:37, 38) በትንሣኤ ሊያስነሳቸው ይናፍቃል። (ኢዮብ 14:15) ይሖዋ ‘የዘላለም ሕይወት እንዲኖረን’ ሲል ውድ ዋጋ ከፍሏል። (ዮሐ. 3:16) ይሖዋ በጣም እንደሚወደንና እንደሚያስብልን እናውቃለን። ስለዚህ ስንታመም ወይም ከሞት ጋር ስንፋጠጥ ይሖዋን ከመተው ይልቅ ማጽናኛ፣ ጥበብና ብርታት እንዲሰጠን ወደ እሱ መቅረብ ይኖርብናል። ቫሌሪ እና ባለቤቷ ያደረጉትም ይህንኑ ነው።—መዝ. 41:3
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 857-858
አስቀድሞ ማወቅ፣ አስቀድሞ መወሰን
የአስቆሮቱ ይሁዳ የተከተለው የክህደት ጎዳና መለኮታዊ ትንቢት እንዲፈጸም ከማድረጉም በላይ ይሖዋም ሆነ ልጁ ነገሮችን አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ እንዳላቸው አሳይቷል። (መዝ 41:9፤ 55:12, 13፤ 109:8፤ ሥራ 1:16-20) ይሁን እንጂ ይሁዳ እንዲህ ዓይነት አካሄድ እንደሚከተል አምላክ አስቀድሞ ወስኖ ነበር ማለት አይቻልም። ትንቢቶቹ የሚገልጹት የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ የሆነ ሰው አሳልፎ እንደሚሰጠው እንጂ ከሚቀርቡት ሰዎች መካከል ማናቸው አሳልፈው እንደሚሰጡት አይደለም። ከዚህ ሁኔታ ጋር በተያያዘም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ ይሁዳ እንዲህ ዓይነት ድርጊት እንዲፈጽም አምላክ አስቀድሞ እንደማይወስን ያረጋግጣሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ መለኮታዊውን መሥፈርት ሲገልጽ “በማንም ሰው ላይ እጅህን ለመጫን አትቸኩል፤ እንዲሁም በሌሎች ኃጢአት ተካፋይ አትሁን፤ ራስህን በንጽሕና ጠብቅ” ብሏል። (1ጢሞ 5:22፤ ከ3:6 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት በጥበብና በተገቢው መንገድ የመምረጡ ጉዳይ በጣም ስላሳሰበው ውሳኔውን ከማሳወቁ በፊት ሙሉ ሌሊት ወደ አባቱ ሲጸልይ አድሯል። (ሉቃስ 6:12-16) አምላክ፣ ይሁዳ ከሃዲ እንደሚሆን አስቀድሞ ወስኖ ከነበረ ይህ እሱ ራሱ ከሰጠው መመሪያ ጋር የሚጋጭ ይሆን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ መሥፈርት አንጻር አምላክ በይሁዳ ኃጢአት ተካፋይ ይሆን ነበር።
በመሆኑም ይሁዳ፣ ሐዋርያ ሆኖ በተመረጠበት ጊዜ በልቡ ውስጥ ምንም ዓይነት የከዳተኝነት ዝንባሌ የታየበት አይመስልም። በልቡ ውስጥ ‘መርዛማ ሥር እንዲበቅል’ እና እንዲበክለው በመፍቀዱ ከትክክለኛው ጎዳና ወጥቶ የአምላክን ሳይሆን የዲያብሎስን አመራር ተከተለ፤ በመሆኑም ስርቆትና ክህደት ፈጸመ። (ዕብ 12:14, 15፤ ዮሐ 13:2፤ ሥራ 1:24, 25፤ ያዕ 1:14, 15፤ ይሁዳ ቁ. 4ን ተመልከት።) በዚህ አካሄዱ የተወሰነ ከገፋበት በኋላ ግን ኢየሱስ ራሱ በይሁዳ ልብ ውስጥ ያለውን ማወቅና እንደሚከዳው አስቀድሞ መናገር ችሏል።—ዮሐ 13:10, 11