የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ዳግመኛ መወለድ መዳን የሚገኝበት መንገድ ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | ሚያዝያ 1
    • ዳግመኛ መወለድ​—መዳን የሚገኝበት መንገድ ነው?

      “ዳግም ተወልደሃል?” ተብለህ ብትጠየቅ ምን መልስ ትሰጣለህ? በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሕዝበ ክርስትና አማኞች “እንዴታ!” በማለት ይመልሳሉ። ዳግመኛ መወለድ የሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክትና መዳን የሚገኝበት ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች “አንድ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ . . . ክርስቲያን አይደለም” በማለት እንደጻፈው እንደ ሮበርት ስፕራውል ያሉ የሃይማኖት መሪዎችን አመለካከት ይጋራሉ።

      አንተም፣ ዳግመኛ መወለድ መዳን የሚገኝበት መንገድ እንደሆነ ታምናለህ? እንዲህ ብለህ የምታምን ከሆነ ዘመዶችህና ወዳጆችህ ይህን መንገድ እንዲያውቁትና እንዲመላለሱበት ልትረዳቸው እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። እንዲህ ማድረግ እንዲችሉ ግን ዳግመኛ በተወለደና ባልተወለደ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ዳግመኛ መወለድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንዴት ልታስረዳቸው ትችላለህ?

      ብዙዎች “ዳግመኛ መወለድ” የሚለው ሐሳብ አንድ ሰው አምላክንና ክርስቶስን ለማገልገል ቃል በመግባቱ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሙት መሆኑ ቀርቶ ሕያው መሆኑን እንደሚያመለክት ይናገራሉ። አንድ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው ዳግመኛ የተወለደ ሰው የሚባለው “በተለይ ከአንድ ሃይማኖታዊ ክንውን በኋላ [መንፈስ መቀበል ሊሆን ይችላል] የእምነቱን ቃል ኪዳን እንደገና ያደሰ ወይም በአዲስ መልክ ያረጋገጠ ክርስቲያን” ነው።—ሚርያም-ዌብስተርስ ኮሊጂየት ዲክሽነሪ—11ኛ እትም

      ይህ መዝገበ ቃላት የሰጠው ፍቺ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደማይስማማ ብታውቅ ትገረም ይሆን? ዳግመኛ ስለመወለድ የአምላክ ቃል የሚሰጠው ትክክለኛ ትምህርት ምን እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ? ስለዚህ ጉዳይ በጥልቀት ማጥናትህ እንደሚጠቅምህ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ዳግመኛ ስለመወለድ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘትህ ሕይወትህንም ሆነ ስለወደፊቱ ጊዜ ያለህን አመለካከት ይነካል።

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

      “ዳግመኛ መወለድ” የሚለው ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው፣ ኢየሱስ ከአንድ የሃይማኖት መሪ ጋር በኢየሩሳሌም ያደረገውን አስገራሚ ውይይት በሚተርከው በ⁠ዮሐንስ 3:1-12 ላይ ብቻ ነው። ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በገጽ 4 ላይ ባለው ሣጥን ላይ ማግኘት ትችላለህ። ጥቅሱን ትኩረት ሰጥተህ እንድታነበው እናበረታታሃለን።

      በዚህ ዘገባ ላይ ኢየሱስ ‘እንደ አዲስ ከመወለድ’ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ነገሮችን ተናግሯል።a ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ለሚከተሉት አምስት አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ እንድናገኝ ይረዳናል፦

      ◼ ዳግመኛ መወለድ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

      ◼ ዳግመኛ መወለድ በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ ነው?

      ◼ ዓላማው ምንድን ነው?

      ◼ አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው እንዴት ነው?

      ◼ አንድ ሰው ዳግመኛ መወለዱ ከአምላክ ጋር ባለው ዝምድና ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?

      እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች አንድ በአንድ እንመርምር።

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a ‘እንደ አዲስ መወለድ’ የሚለው ሐረግ በ⁠1 ጴጥሮስ 1:3, 23 ላይ የሚገኝ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ “ዳግመኛ መወለድ” የሚለውን ሐሳብ ለመግለጽ የሚጠቀምበት ሌላው ሐረግ ነው። ሁለቱም አገላለጾች የናኦ ከሚለው የግሪክኛ ግስ የተገኙ ናቸው።

      [በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

      “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ”

      “ከፈሪሳውያን ወገን፣ የአይሁድ ገዥ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው በማታ ወደ ኢየሱስ መጥቶ እንዲህ አለው፦ ‘ረቢ፣ አንተ ከአምላክ ዘንድ የመጣህ አስተማሪ እንደሆንክ እናውቃለን፤ ምክንያቱም አምላክ ከእሱ ጋር ካልሆነ በቀር አንተ የምትፈጽማቸውን ተአምራዊ ምልክቶች መፈጸም የሚችል አንድም ሰው የለም።’ ኢየሱስም መልሶ ‘እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ማንም ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የአምላክን መንግሥት ሊያይ አይችልም’ አለው። ኒቆዲሞስም ‘ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግም ወደ እናቱ ማህፀን ገብቶ ሊወለድ አይችልም፤ ይችላል እንዴ?’ አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ ‘እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ማንም ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ አምላክ መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ ደግሞ መንፈስ ነው። ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ ስላልኩህ አትገረም። ነፋስ ወደፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ሆኖም ከየት እንደሚመጣና ወዴት እንደሚሄድ አታውቅም። ከመንፈስ የተወለደም ሁሉ እንደዚሁ ነው።’ ኒቆዲሞስም መልሶ ‘እነዚህ ነገሮች እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ?’ አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ የእስራኤል አስተማሪ ሆነህ ሳለህ እነዚህን ነገሮች አታውቅም? እውነት እውነት እልሃለሁ፣ እኛ የምናውቀውን እንናገራለን፣ ያየነውንም እንመሠክራለን፤ እናንተ ግን እኛ የምንሰጠውን ምሥክርነት አትቀበሉም። ስለ ምድራዊ ነገሮች ነግሬያችሁ የማታምኑ ከሆነ ስለ ሰማያዊ ነገሮች ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?’”—ዮሐንስ 3:1-12

  • ዳግመኛ መወለድ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | ሚያዝያ 1
    • ዳግመኛ መወለድ​—ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

      ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ እንደ አዲስ ወይም ዳግመኛ መወለድ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይህን ያደረገው እንዴት ነበር?

      ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ዳግመኛ መወለድ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የገለጸበትን መንገድ ልብ በል። “ማንም ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የአምላክን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ብሏል። (ዮሐንስ 3:3) “በቀር” እና “አይችልም” የሚሉት ቃላት እንደ አዲስ መወለድ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን የሚያጎሉ ናቸው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ሰው “ፀሐይ ካልወጣች በቀር ብርሃን ሊኖር አይችልም” ቢል ብርሃን እንዲኖር ፀሐይ መውጣቷ የግድ አስፈላጊ መሆኑን መግለጹ ነው። በተመሳሳይም ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ለማየት ዳግመኛ መወለድ የግድ አስፈላጊ መሆኑን መናገሩ ነበር።

      ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ሊነሳ የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት ጥርጣሬ ለማስወገድ ይመስላል “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” በማለት በድጋሚ ተናገረ። (ዮሐንስ 3:7) ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ዳግመኛ መወለድ፣ ወደ አምላክ መንግሥት ‘ለመግባት’ የግድ መሟላት ያለበት ብቃት ነው።—ዮሐንስ 3:5

      ኢየሱስ ዳግመኛ መወለድ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ስለገለጸ ክርስቲያኖች ስለዚህ ጉዳይ ትክክለኛ ግንዛቤ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፣ ‘እንደ አዲስ መወለድ በአንድ ክርስቲያን ምርጫ ላይ የተመካ ጉዳይ ነው?’ የሚለውን ጥያቄ እንመርምር።

      [በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      “ፀሐይ ካልወጣች በቀር ብርሃን ሊኖር አይችልም”

  • ዳግመኛ መወለድ በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | ሚያዝያ 1
    • ዳግመኛ መወለድ በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ ነው?

      አንድን ሰው ዳግመኛ እንዲወለድ የሚያደርገው ማን ነው? አንዳንድ ሰባኪዎች አድማጮቻቸው ዳግመኛ የተወለዱ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ለማሳሰብ ኢየሱስ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” ሲል የተናገረውን ሐሳብ ይጠቅሳሉ። (ዮሐንስ 3:7) እነዚህ ሰባኪዎች ይህን ሐሳብ የሚናገሩት በትእዛዝ መልክ ስለሆነ “ዳግመኛ ተወለዱ!” የሚሉ ያህል ነው። በሌላ አነጋገር ኢየሱስን በመታዘዝ እንደ አዲስ ለመወለድ የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰድ ያለበት እያንዳንዱ አማኝ እንደሆነ ያስተምራሉ። እነዚህ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ ዳግመኛ መወለድ በግለሰቦች ምርጫ ላይ የተመካ ነው። ይሁንና ይህ አመለካከት ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ከሰጠው ትምህርት ጋር ይስማማል?

      ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ልብ ብለን ካነበብን ዳግመኛ መወለድ፣ በግለሰቦች ምርጫ ላይ የተመካ መሆኑን እንዳላስተማረ መገንዘብ እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? “ዳግመኛ መወለድ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ሐረግ “ከላይ መወለድ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።a በዚህ አተረጓጎም መሠረት አንድ ሰው እንደ አዲስ መወለድን ማግኘት የሚችለው “ከላይ” ማለትም በሰማይ ከሚኖረው “አባት” ነው። (ዮሐንስ 19:11፤ ያዕቆብ 1:17) አዎን፣ አንድ ሰው ዳግመኛ እንዲወለድ የሚያደርገው አምላክ ነው።—1 ዮሐንስ 3:9

      “ከላይ” የሚለው ቃል የሚያስተላልፈውን ሐሳብ ከተረዳን ዳግመኛ መወለድ አንድ ሰው በራሱ የሚያደርገው ምርጫ እንዳልሆነ ግልጽ ይሆንልናል። በተፈጥሮ የምንወለድበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንመልከት። የተወለድከው በራስህ ምርጫ ነው? አይደለም! እንድትወለድ ያደረገው ወይም ለመወለድህ ምክንያት የሆነው አባትህ ነው። በተመሳሳይም ዳግመኛ መወለድ የምንችለው በሰማይ የሚኖረው አባታችን እንደ አዲስ እንድንወለድ ካደረገን ብቻ ነው። (ዮሐንስ 1:13) በመሆኑም ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው ማለቱ የተገባ ነው፦ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ምክንያቱም እሱ በታላቅ ምሕረቱ . . . እንደ አዲስ ወልዶናል።”—1 ጴጥሮስ 1:3

      ትእዛዝ ነው?

      አንዳንዶች ‘ዳግመኛ መወለድ በግለሰቦች ምርጫ ላይ የተመካ ካልሆነ ኢየሱስ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” የሚል ትእዛዝ የሰጠው ለምንድን ነው?’ በማለት ሊጠይቁ ይችላሉ። ደግሞም እንዲህ ብለው መጠየቃቸው ተገቢ ነው። ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ትእዛዝ ከሆነ ልናደርገው የማንችለውን ነገር እንድንፈጽም እየጠየቀን ነው ማለት ይሆናል። ይህ ደግሞ ምክንያታዊ አይደለም። ታዲያ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” የሚለውን ሐሳብ መረዳት ያለብን እንዴት ነው?

      ይህ ዓረፍተ ነገር፣ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ የተገለጸው ትእዛዝ በሚያስተላልፍ መንገድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድን እውነታ የሚገልጽ ዓረፍተ ነገር ነው። በሌላ አነጋገር ኢየሱስ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” ሲል አንድ ሐቅ እየገለጸ እንጂ ትእዛዝ እየሰጠ አልነበረም። “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል” ማለቱ ነበር።—ዮሐንስ 3:7 የ1954 ትርጉም

      ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ብዙ ትምህርት ቤቶች ያሉትን አንድ ከተማ አስብ። አንደኛው ትምህርት ቤት ከከተማው በጣም ርቆ በሚገኝ ቦታ ለሚኖሩ የአንድ አካባቢ ተወላጆች የተዘጋጀ ነው። አንድ ቀን፣ የዚያ አካባቢ ተወላጅ ያልሆነ አንድ ወጣት የትምህርት ቤቱን ዳይሬክተር “እዚህ ትምህርት ቤት መግባት እፈልጋለሁ” አለው። ዳይሬክተሩም “በትምህርት ቤቱ ለመማር የዚያ አካባቢ ተወላጅ መሆን አለብህ” በማለት መለሰለት። ዳይሬክተሩ የተናገረው ነገር ትእዛዝ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ወጣቱን የዚያ አካባቢ ተወላጅ እንዲሆን እያዘዘው አልነበረም። ዳይሬክተሩ፣ ወጣቱ እዚያ ትምህርት ቤቱ ለመግባት ማሟላት ያለበትን ብቃት እየተናገረ ነበር። በተመሳሳይም ኢየሱስ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” ሲል ‘ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት’ መሟላት ያለበትን ብቃት መግለጹ ነበር።

      ኢየሱስ ዳግመኛ ከመወለድ ጋር በተያያዘ ያነሳው ሌላው ጉዳይ የአምላክ መንግሥት ነው። ይህ ደግሞ ‘አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለድበት ዓላማ ምንድን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል። ለዚህ ጥያቄ የምናገኘው መልስ ዳግመኛ መወለድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ትክክለኛ ግንዛቤ ለማግኘት ያስችለናል።

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ዮሐንስ 3:3⁠ን በዚህ መንገድ ተርጉመውታል። ለምሳሌ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፍ ጋር ይህን ጥቅስ እንደሚከተለው በማለት አስቀምጦታል፦ “ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ [‘ከላይ ካልተወለደ፣’ የግርጌ ማስታወሻ] በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም።”

      [በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      በተፈጥሮ በምንወለድበት መንገድና እንደ አዲስ በመወለድ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

  • ዳግመኛ መወለድ ዓላማው ምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | ሚያዝያ 1
    • ዳግመኛ መወለድ​—ዓላማው ምንድን ነው?

      ብዙ ሰዎች፣ ዘላለማዊ መዳን ለማግኘት ዳግመኛ መወለድ አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ራሱ አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለድበት ዓላማ ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ማንም ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የአምላክን መንግሥት ሊያይ አይችልም።” (ዮሐንስ 3:3) በመሆኑም፣ አንድ ሰው ዳግመኛ መወለድ የሚያስፈልገው መዳን ለማግኘት ሳይሆን ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት ነው። ይሁንና አንዳንዶች ‘ወደ አምላክ መንግሥት መግባትም ሆነ መዳን ማግኘት ተመሳሳይ ነገር አይደሉም እንዴ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ተመሳሳይ አይደሉም። ልዩነታቸውን ለመገንዘብ በመጀመሪያ ‘የአምላክ መንግሥት’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።

      መንግሥት ሲባል እውን የሆነ መስተዳድር ማለት ነው፤ ስለዚህ ‘የአምላክ መንግሥት’ ሲባል ‘የአምላክ መስተዳድር’ ማለት ነው። የአምላክ መንግሥት ንጉሥ “የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነና ከእሱ ጋር አብረው የሚገዙ ሰዎች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (ዳንኤል 7:1, 13, 14፤ ማቴዎስ 26:63, 64) ከዚህም በተጨማሪ ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚገዙት ሰዎች “ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ” የተውጣጡ እንደሆኑና “በምድርም ላይ ነገሥታት ሆነው [እንደሚገዙ]” ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 5:9, 10፤ 20:6) የአምላክ ቃል፣ ነገሥታት ሆነው የሚገዙት ‘ከምድር የተዋጁ’ ሰዎች 144,000 እንደሆኑና “ትንሽ መንጋ” ተብለው እንደሚጠሩ ይገልጻል።—ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 14:1, 3

      የአምላክ መንግሥት መቀመጫ የት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክን መንግሥት” በሌላ ቦታ ላይ “መንግሥተ ሰማያት” ብሎ የሚጠራው መሆኑ ኢየሱስና አብረውት የሚነግሡት ሰዎች የሚገዙት ከሰማይ እንደሆነ ያሳያል። (ሉቃስ 8:10፤ ማቴዎስ 13:11) ስለዚህ የአምላክ መንግሥት፣ በኢየሱስ ክርስቶስና ከሰው ልጆች በተመረጡት ተባባሪ ገዢዎች የተዋቀረ በሰማይ ያለ መስተዳድር ነው።

      ታዲያ ኢየሱስ፣ አንድ ሰው ‘ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት’ ዳግመኛ መወለድ እንዳለበት ሲናገር ምን ማለቱ ነው? አንድ ሰው በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ለመግዛት ዳግመኛ መወለድ እንደሚያስፈልገው መግለጹ ነው። በቀላል አነጋገር፣ ዳግመኛ የመወለድ ዓላማ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በሰማይ ነገሥታት እንዲሆኑ ማዘጋጀት ነው።

      ዳግመኛ መወለድ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንዲሁም በአምላክ ምርጫ ላይ የተመካ መሆኑን ተመልክተናል፤ ከዚህም በላይ ዓላማው የተወሰኑ ሰዎችን በሰማይ ነገሥታት እንዲሆኑ ማዘጋጀት መሆኑን አይተናል። ሆኖም አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው እንዴት ነው?

      [በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      ዳግመኛ የመወለድ ዓላማ፣ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በሰማይ ነገሥታት እንዲሆኑ ማዘጋጀት ነው

      [በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      የአምላክ መንግሥት፣ በኢየሱስ ክርስቶስና ከሰው ልጆች በተመረጡት ተባባሪ ገዢዎች የተዋቀረ መስተዳድር ነው

  • ዳግመኛ መወለድ የሚከናወነው እንዴት ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | ሚያዝያ 1
    • ዳግመኛ​—መወለድ የሚከናወነው እንዴት ነው?

      ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ፣ እንደ አዲስ መወለድ አስፈላጊ መሆኑንና በአምላክ የሚወሰን ጉዳይ መሆኑን እንዲሁም ዳግመኛ የመወለድን ዓላማ በመጥቀስ ብቻ አልተወሰነም፤ አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው እንዴት እንደሆነም ጭምር ተናግሯል። ኢየሱስ “ማንም ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ አምላክ መንግሥት ሊገባ አይችልም” ብሏል። (ዮሐንስ 3:5) ስለዚህ አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው በውኃና በመንፈስ አማካኝነት ነው። ይሁንና ‘ውኃና መንፈስ’ የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል?

      ‘ውኃና መንፈስ’—ምንድን ናቸው?

      ኒቆዲሞስ የአይሁድ ሃይማኖት ምሑር ስለነበረ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ‘የአምላክ መንፈስ’ የሚለውን ሐረግ እንዴት እንደሚጠቀሙበት ያውቅ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ኒቆዲሞስ ‘የአምላክ መንፈስ’ የሚለው ሐረግ፣ ሰዎች አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸውን በሥራ ላይ የዋለ የአምላክ ኃይል እንደሚያመለክት ያውቅ ነበር። (ዘፍጥረት 41:38፤ ዘፀአት 31:3፤ 1 ሳሙኤል 10:6) ስለሆነም ኢየሱስ “መንፈስ” ሲል በሥራ ላይ ስለዋለው የአምላክ ኃይል ማለትም ስለ መንፈስ ቅዱስ እየተናገረ መሆኑን ኒቆዲሞስ እንደሚረዳ ግልጽ ነው።

      ኢየሱስ “ውኃ” ሲልስ ምን ማለቱ ነበር? ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ስላደረገው ውይይት ከተጻፈው ዘገባ በፊትና በኋላ ያሉትን ሐሳቦች እንመልከት። እነዚህ ዘገባዎች አጥማቂው ዮሐንስም ሆነ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በውኃ ያጠምቁ እንደነበረ ይገልጹልናል። (ዮሐንስ 1:19, 31፤ 3:22፤ 4:1-3) በውኃ ማጥመቅ በኢየሩሳሌም የታወቀ ነገር ሆኖ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ስለ ውኃ ሲጠቅስ፣ በአጠቃላይ ስለ ውኃ ሳይሆን በውኃ ስለ መጠመቅ እየተናገረ እንደነበረ ኒቆዲሞስ ለመረዳት አያስቸግረውም።a

      “በመንፈስ ቅዱስ” መጠመቅ

      ‘ከውኃ መወለድ’ በውኃ ከመጠመቅ ጋር የተያያዘ ከሆነ ‘ከመንፈስ መወለድስ’ ምን ትርጉም አለው? ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ከመነጋገሩ በፊት፣ አጥማቂው ዮሐንስ ውኃ ብቻ ሳይሆን መንፈስም በጥምቀት ረገድ የሚጫወተው ሚና እንዳለ ገልጾ ነበር። ዮሐንስ “እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ፤ እሱ [ኢየሱስ] ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል” ብሏል። (ማርቆስ 1:7, 8) የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ማርቆስ እንዲህ ዓይነት ጥምቀት ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነበትን ሁኔታ ሲዘግብ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ተጠመቀ። ወዲያው ከውኃ እንደወጣ ሰማያት ተከፍተው መንፈስ እንደ ርግብ በእሱ ላይ ሲወርድ አየ።” (ማርቆስ 1:9, 10) ኢየሱስ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በጠለቀ ጊዜ በውኃ የተጠመቀ ሲሆን መንፈስ ከሰማይ በወረደበት ጊዜ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቋል።

      ኢየሱስ ከተጠመቀ ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ከጥቂት ቀናት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” ብሏቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:5) ታዲያ ይህ ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነው?

      በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጴንጤቆስጤ ዕለት 120 የሚሆኑ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር። “ድንገትም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ ተቀምጠውበት የነበረውንም ቤት ሞላው። የእሳት ነበልባል የሚመስሉ ምላሶች ታዩአቸው፤ . . . ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) በዚያኑ ዕለት በኢየሩሳሌም የነበሩ ሌሎች ሰዎች በውኃ እንዲጠመቁ ማበረታቻ ተሰጣቸው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ተሰብስቦ ለነበረው ሕዝብ እንዲህ አለ፦ “ንስሐ ግቡ፤ እያንዳንዳችሁም ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ነፃ ስጦታ ትቀበላላችሁ።” የሰዎቹስ ምላሽ ምን ነበር? “ቃሉን ከልባቸው የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ ገደማ የሚሆኑ ነፍሳት ተጨመሩ።”—የሐዋርያት ሥራ 2:38, 41

      ዳግመኛ መወለድ የሚያካትታቸው ሁለት ነገሮች

      እነዚህ ሁለት ጥምቀቶች ዳግመኛ ስለ መወለድ ምን እንድናስተውል ይረዱናል? ዳግመኛ መወለድ ሁለት ነገሮችን እንደሚያካትት ይጠቁሙናል። ኢየሱስ በመጀመሪያ በውኃ እንደተጠመቀ ልብ በል። ከዚያም መንፈስ ቅዱስ ወረደበት። በተመሳሳይም የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት መጀመሪያ በውኃ የተጠመቁ ሲሆን (አንዳንዶቹን ያጠመቃቸው አጥማቂው ዮሐንስ ነው) ከዚያ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ወርዶባቸዋል። (ዮሐንስ 1:26-36) አዲሶቹ 3,000 ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በውኃ የተጠመቁ ሲሆን ከዚያም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል።

      በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጴንጤቆስጤ ዕለት ከተከናወኑት ጥምቀቶች አንጻር በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው እንዴት ነው? የኢየሱስ ሐዋርያትም ሆኑ የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት ዳግመኛ ከተወለዱበት ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነው። በመጀመሪያ አንድ ሰው ከኃጢአቱ ንስሐ ይገባል፣ ከመጥፎ ምግባሩ ይመለሳል፣ አምላክን ለማምለክና ለማገልገል ራሱን ለይሖዋ ይወስናል፤ ከዚያም በውኃ በመጠመቅ ውሳኔውን በሕዝብ ፊት ያሳያል። ቀጥሎ ደግሞ አምላክ በመንግሥቱ ላይ ገዢ እንዲሆን ከመረጠው በመንፈስ ቅዱስ ይቀባል። ዳግመኛ መወለድ ከሚያካትታቸው ሁለት ነገሮች መካከል የመጀመሪያው (ይኸውም በውኃ መጠመቅ) በግለሰቡ ውሳኔ ላይ የተመካ ነው፤ ሁለተኛው (ይኸውም በመንፈስ መጠመቅ) ግን በአምላክ ምርጫ ላይ የተመካ ነው። አንድ ሰው በውኃና በመንፈስ ሲጠመቅ ዳግመኛ ተወልዷል ማለት ነው።

      ይሁንና ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ‘ከውኃና ከመንፈስ መወለድ’ የሚለውን አገላለጽ የተጠቀመው ለምንድን ነው? ይህን ያለው በውኃና በመንፈስ የሚጠመቁ ሰዎች አስገራሚ ለውጥ እንደሚያደርጉ ለማጉላት ነው። የሚቀጥለው ርዕስ ስለዚህ ጉዳይ ያብራራል።

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት በተከናወነበት አንድ አጋጣሚ “ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው?” ብሎ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 10:47 የ1954 ትርጉም

      [በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      አጥማቂው ዮሐንስ ንስሐ የገቡ እስራኤላውያንን በውኃ አጥምቋል

  • ዳግመኛ መወለድ ምን ዓይነት ለውጥ ያስከትላል?
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | ሚያዝያ 1
    • ዳግመኛ መወለድ​—ምን ዓይነት ለውጥ ያስከትላል?

      ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ስለ መጠመቅ ሲናገር ‘ከመንፈስ መወለድ’ የሚል አገላለጽ የተጠቀመው ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 3:5) “መወለድ” የሚለው ቃል በምሳሌያዊ አነጋገር ሲሠራበት “መጀመሪያ” የሚል ፍቺ ይኖረዋል። በመሆኑም “ዳግመኛ መወለድ” ወይም “እንደ አዲስ መወለድ” የሚለው ሐረግ “አዲስ ጅምርን” የሚያመለክት ነው። “መወለድ” እና “እንደ አዲስ መወለድ” የሚሉት ምሳሌያዊ አነጋገሮች በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁት ክርስቲያኖች ከአምላክ ጋር የነበራቸው ዝምድና አዲስ መልክ እንደሚኖረው የሚጠቁሙ ናቸው። ዝምድናቸው አዲስ መልክ ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?

      ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አምላክ የተወሰኑ ሰዎችን በሰማይ ነገሥታት እንዲሆኑ የሚያዘጋጃቸው እንዴት እንደሆነ ሲያብራራ ከቤተሰብ ሕይወት ጋር ተዛማጅነት ያለው ምሳሌ ተጠቅሟል። ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩት ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ እነሱን ‘እንደ ልጆቹ አድርጎ እንደወሰዳቸው’ ገልጿል፤ በዚህም ምክንያት አምላክ “እንደ ልጆቹ አድርጎ” እንደሚይዛቸው ጽፎላቸዋል። (ገላትያ 4:5፤ ዕብራውያን 12:7) ጳውሎስ የተጠቀመው ምሳሌ አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቅ የሚከናወነውን ለውጥ ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት እንደሆነ ለማየት፣ የአንድ አካባቢ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች ብቻ በሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመግባት ስለፈለገው ወጣት የሚናገረውን ምሳሌ መለስ ብለን እንመልከት።

      እንደ ልጅ ተደርጎ መወሰድ የሚያስከትለው ለውጥ

      ቀደም ሲል ባየነው ምሳሌ ላይ፣ ወጣቱ የአንድ አካባቢ ተወላጅ ለሆኑ ተማሪዎች ብቻ በተከፈተው ትምህርት ቤት መግባት ያልቻለው የዚያ አካባቢ ተወላጅ ስላልሆነ ነበር። ሆኖም አንድ ቀን ትልቅ ለውጥ ተከሰተ። የዚያ አካባቢ ተወላጅ የሆነ አንድ የቤተሰብ ኃላፊ፣ ይህን ወጣት ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰደው። ታዲያ ይህ በወጣቱ ሁኔታ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? ይህ ወጣት በትምህርት ቤቱ ውስጥ መግባትን ጨምሮ የዚያ አካባቢ ተወላጅ የሆኑት ተማሪዎች የሚያገኟቸው መብቶች ሁሉ ሊያገኝ ይችል ይሆናል። የዚያ አካባቢ ተወላጅ የሆነ ሰው እንደ ልጁ አድርጎ የወሰደው መሆኑ የወጣቱን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ለውጦታል።

      ይህ ምሳሌ ዳግመኛ መወለድ በአንድ ሰው ላይ የሚያስከትለውን ጉልህ ለውጥ ለመረዳት ያስችላል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ወጣት እና ዳግመኛ የሚወለዱት ክርስቲያኖች ባላቸው ሁኔታ መካከል የሚታየውን ተመሳሳይነት እንመልከት። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ወጣት በትምህርት ቤቱ መመዝገብ የሚችለው አስፈላጊውን ብቃት ካሟላ ማለትም ራቅ ብሎ የሚገኘው አካባቢ ተወላጅ ከሆነ ብቻ ነው። ሆኖም ይህንን ብቃት በራሱ ማሟላት አይችልም። በተመሳሳይም የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአምላክ መንግሥት ወይም በሰማይ በሚገኘው መስተዳድር ውስጥ መግዛት የሚችሉት የሚያስፈልገውን ብቃት ካሟሉ ይኸውም ‘ዳግመኛ ከተወለዱ’ ብቻ ነው። ሆኖም እንደ አዲስ መወለድ በአምላክ ምርጫ ላይ የተመካ ስለሆነ እነዚህ ሰዎች ብቃቱን በራሳቸው ማሟላት አይችሉም።

      የወጣቱ ሁኔታ እንዲቀየር ያደረገው ምንድን ነው? ራቅ ያለው አካባቢ ተወላጅ የሆነ ሰው እንደ ልጁ አድርጎ የወሰደው መሆኑ ነው። እርግጥ ነው፣ ወጣቱ የሌላ ቤተሰብ አባል መሆኑ ማንነቱን አይቀይረውም። ያም ቢሆን የዚያ አካባቢ ተወላጅ የሆነው ሰው ይህን ወጣት ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ከወሰደው በኋላ የወጣቱ ሁኔታ ተቀይሯል። በሌላ አባባል፣ ወጣቱ እንደገና የተወለደ ያህል አዲስ የሕይወት ጎዳና ጀምሯል። ሰውየው እንደ ልጁ አድርጎ ስለወሰደው በትምህርት ቤቱ የመመዝገብና የዚህ ሰው ቤተሰብ አባል የመሆን መብት አግኝቷል።

      በተመሳሳይም ይሖዋ፣ ሕጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ፍጹማን ያልሆኑ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የሰው ልጆችን እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል፤ ይህም ሁኔታቸው እንዲቀየር አድርጓል። የዚህ ቡድን አባል የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል፦ “እንደ ልጅ የመቆጠር መብት የሚያስገኝ መንፈስ ተቀብላችኋል፤ ይህም መንፈስ ‘አባ፣ አባት!’ ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል። የአምላክ ልጆች መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።” (ሮም 8:15, 16) አዎን፣ አምላክ እነዚህን ክርስቲያኖች እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለተቀበላቸው የእሱ ቤተሰብ አባላት ወይም “የአምላክ ልጆች” መሆን ችለዋል።—1 ዮሐንስ 3:1፤ 2 ቆሮንቶስ 6:18

      እርግጥ ነው፣ እነዚህ ክርስቲያኖች አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለተቀበላቸው ማንነታቸው ተቀይሯል ማለት አይደለም፤ አሁንም ቢሆን ፍጹማን አይደሉም። (1 ዮሐንስ 1:8) ያም ቢሆን፣ ጳውሎስ እንዳብራራው አምላክ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንደ ልጆቹ አድርጎ ከወሰዳቸው በኋላ ሁኔታቸው ተቀይሯል። አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ ሲቀበላቸው፣ የአምላክ መንፈስ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንደሚኖሩ እርግጠኛ የሆነ እምነት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። (1 ዮሐንስ 3:2) መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ያለ እርግጠኛ እምነት እንዲያድርባቸው ስላደረገ ለሕይወት ያላቸው አመለካከት በእጅጉ ይለወጣል። (2 ቆሮንቶስ 1:21, 22) አዎን፣ እነዚህ ክርስቲያኖች እንደ አዲስ የተወለዱ ያህል አዲስ የሕይወት ጎዳና ጀምረዋል።

      መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለወሰዳቸው ክርስቲያኖች ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ነገሥታት ሆነው ለአንድ ሺህ ዓመት ይገዛሉ።” (ራእይ 20:6) አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ የተቀበላቸው ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር በአምላክ መንግሥት ወይም በሰማይ በሚገኘው መስተዳድር ውስጥ ነገሥታት የመሆን መብት ያገኛሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለእምነት ባልንጀሮቹ እንደጻፈው ‘በሰማይ ለእነሱ የተጠበቀላቸው’ ይህ የመግዛት መብት ‘የማይበሰብስ፣ የማይረክስና የማይጠፋ ርስት ነው።’ (1 ጴጥሮስ 1:3, 4) ይህ በእርግጥም የላቀ ርስት ነው!

      ይሁን እንጂ እነዚህ ክርስቲያኖች ያገኙት የመግዛት መብት አንድ ጥያቄ ያስነሳል። ዳግመኛ የተወለዱት ሰዎች በሰማይ ነገሥታት የሚሆኑ ከሆነ የሚገዙት በእነማን ላይ ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ ማብራሪያ ይሰጣል።

      [በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ጳውሎስ፣ አንድን ሰው እንደ ራስ ልጅ አድርጎ መውሰድን በተመለከተ ምን ብሏል?

  • የሚገዙት ጥቂቶች ቢሆኑም ብዙዎች ይጠቀማሉ
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | ሚያዝያ 1
    • የሚገዙት ጥቂቶች ቢሆኑም ብዙዎች ይጠቀማሉ

      ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ አምላክ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ታማኝ ክርስቲያኖች ከሰው ልጆች መካከል በመምረጥ እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። በእነዚህ ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የሚከሰተው ለውጥ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የአምላክ ቃል ሁኔታውን እንደ አዲስ ከመወለድ ጋር አመሳስሎታል። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች እንደ አዲስ የተወለዱበት ዓላማ በሰማይ ገዥዎች እንዲሆኑ ማዘጋጀት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:12) በሰማይ እንዲገዙ ደግሞ ከሞት ተነስተው በሰማይ ሕይወት ያገኛሉ። (ሮም 6:3-5) በዚያም ከክርስቶስ ጋር ‘ነገሥታት ሆነው በምድር ላይ ይገዛሉ።’—ራእይ 5:10፤ 11:15

      የአምላክ ቃል ዳግመኛ ከተወለዱት ክርስቲያኖች በተጨማሪ ሌሎችም ዘላለማዊ መዳን እንደሚያገኙ ይናገራል። በመጽሐፍ ቅዱስ (በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትም ሆነ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት) ውስጥ አምላክ በሁለት ቡድን የተከፈሉ ሰዎችን የማዳን ዓላማ እንዳለው ተገልጿል። አንደኛው ቡድን በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን በሰማይ ሆነው የሚገዙ ሰዎች ያቀፈ ሲሆን ሌላው ቡድን ደግሞ በምድር የሚኖሩ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ተገዢዎች ያካትታል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ዮሐንስ ዳግመኛ ለተወለዱት የእምነት ባልንጀሮቹ የጻፈውን ሐሳብ ልብ በል። ኢየሱስን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “እሱ ለእኛ ኃጢአት የቀረበ የማስተሰረያ መሥዋዕት ነው፤ ሆኖም ለእኛ [አነስተኛ ሰዎችን ላቀፈው ቡድን] ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ [ብዙ ሰዎችን ላቀፈው ቡድን] ኃጢአት ጭምር ነው።”—1 ዮሐንስ 2:2

      በተመሳሳይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “ፍጥረት [ብዙ ሰዎችን ያቀፈው ቡድን] የአምላክን ልጆች [አነስተኛ ሰዎችን ያቀፈውን ቡድን] መገለጥ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ ነው።” (ሮም 8:19-21) ሐዋርያው ዮሐንስና ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፉትን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል? በዚህ መንገድ ልንረዳው ይገባናል፦ ዳግመኛ የተወለዱት ክርስቲያኖች በሰማይ ያለው አገዛዝ ክፍል ይሆናሉ። ለምን? በምድር ላይ ለሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ዘላለማዊ በረከቶችን ለማምጣት ነው። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚከተለው ብለው እንዲጸልዩ ያስተማራቸው በዚህ ምክንያት ነው፦ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።”—ማቴዎስ 6:10

      የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትም መዳን የሚያገኙት በሁለት ቡድን የተከፈሉ ሰዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የኢየሱስ ቅድመ አያት ለሆነው ለአብርሃም “የምድር ሕዝቦች ሁሉ [ብዙ ሰዎችን ያቀፈው ቡድን] በዘርህ [አነስተኛ ሰዎችን ባቀፈው ቡድን] ይባረካሉ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 22:18) አዎን፣ በአብርሃም “ዘር” አማካኝነት የምድር ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ።

      ይህ “ዘር” ማን ነው? ይህ “ዘር” ኢየሱስ ክርስቶስንና አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ የተቀበላቸውን ዳግመኛ የተወለዱ ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የክርስቶስ ከሆናችሁ በእርግጥም የአብርሃም ዘር ናችሁ” ብሏል። (ገላትያ 3:16, 29) ታዲያ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዚህ “ዘር” አማካኝነት የሚያገኟቸው በረከቶች ምንድን ናቸው? በአምላክ ፊት ተቀባይነት የማግኘትና ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር መብት ይሰጣቸዋል። መዝሙራዊው ዳዊት “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ተንብዮአል።—መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 45:18፤ ራእይ 21:1-5

      እውነት ነው፣ በሰማይ የመግዛት መብት ያገኙት ጥቂቶች ናቸው፤ ይህ አገዛዝ ከሚያስገኘው በረከት የሚጠቀሙት ይኸውም በምድር ላይ የዘላለም ሕይወትና ሌሎች ብዙ በረከቶችን የሚያገኙት ግን ብዙዎች ናቸው። አንተም ሆንክ ቤተሰብህ የአምላክ መንግሥት ከሚያስገኛቸው ዘላለማዊ በረከቶች ተቋዳሽ እንድትሆኑ እንመኛለን።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ