የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2024 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከመጋቢት 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 3
በይሖዋ እንደምትታመኑ አሳዩ
ምሳሌ 3:5, 6—“በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ”
“በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን።” ማንኛውንም ነገር አምላክ በሚፈልገው መንገድ የምናከናውን ከሆነ በእሱ እንደምንታመን እናሳያለን። ሙሉ በሙሉ በአምላክ መታመን ይኖርብናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልብ የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት ነው፤ ይህም ስሜቱን፣ አስተሳሰቡን፣ ዝንባሌውንና አንድን ነገር ለማድረግ የሚገፋፋውን ስሜት ያጠቃልላል። ስለዚህ በሙሉ ልባችን በአምላክ መታመን እንዲሁ የስሜት ጉዳይ ብቻ አይደለም። በሙሉ ልባችን በአምላክ የምንታመነው ፈጣሪያችን ለእኛ የተሻለውን ነገር እንደሚያውቅ እርግጠኞች ስለሆንን ነው።—ሮም 12:1
“በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ።” ኃጢአተኞች ስለሆንን በራሳችን የማመዛዘን ችሎታ መመካት አንችልም፤ ስለዚህ በአምላክ መታመን ይኖርብናል። ሙሉ በሙሉ በራሳችን ችሎታ ተማምነን ወይም በስሜት ተገፋፍተን አንድ ውሳኔ እናደርግ ይሆናል፤ እንዲህ ያለው ውሳኔ መጀመሪያ ላይ ጥሩ መስሎ ቢታየንም የኋላ ኋላ መጥፎ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። (ምሳሌ 14:12፤ ኤርምያስ 17:9) የአምላክ ጥበብ ከእኛ ጥበብ እጅግ የላቀ ነው። (ኢሳይያስ 55:8, 9) ሕይወታችንን የምንመራው ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር በሚስማማ መንገድ ከሆነ ስኬታማ እንሆናለን።—መዝሙር 1:1-3፤ ምሳሌ 2:6-9፤ 16:20
ምሳሌ 3:5, 6—“በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ”
“በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ።” በእያንዳንዱ የሕይወታችን እንቅስቃሴ እንዲሁም በምናደርገው በእያንዳንዱ ትላልቅ ውሳኔ የአምላክን አመለካከት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። እንዲህ የምናደርገው መመሪያ ለማግኘት ወደ እሱ በመጸለይና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን ሐሳብ በሥራ ላይ በማዋል ነው።—መዝሙር 25:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
“እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።” አምላክ ሕይወታችንን ከእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ እንድንመራ በመርዳት ጎዳናችንን ቀና ያደርግልናል። (ምሳሌ 11:5) ይህም ሳያስፈልግ ችግር ውስጥ ከመግባት እንድንርቅና ይበልጥ ደስተኛ ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል።—መዝሙር 19:7, 8፤ ኢሳይያስ 48:17, 18
እድገት አድርግ
አንድ ሰው በሕይወቱ ብዙ ነገር ስላየ ‘ይህ ነገር ከአሁን ቀደም አጋጥሞኛል። ስለዚህ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አውቃለሁ’ ሊል ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ጥበብ ይሆናልን? ምሳሌ 3:7 “በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን” በማለት ያስጠነቅቃል። እርግጥ በሕይወታችን ያካበትነው ተሞክሮ አንዳንድ ነገሮች ሲገጥሙን ጉዳዩን አእምሮአችንን ሰፋ አድርገን እንድንመለከተው እንደሚረዳን የታወቀ ነው። ሆኖም መንፈሳዊ እድገት የምናደርግ ሰዎች ከሆንን ያገኘነው ተሞክሮ በይሖዋ የመታመንን አስፈላጊነት ከልብ እንድንገነዘብ ይረዳናል። እንዲህ ከሆነ መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችን የሚታየው የሚያጋጥሙንን ነገሮች በራሳችን ታምነን በመጋፈጣችን ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ከይሖዋ መመሪያ ለማግኘት በመጣራችን ነው። ያለ ይሖዋ ፈቃድ ምንም ነገር ሊፈጸም እንደማይችል ያለን እምነት እንዲሁም ከሰማያዊ አባታችን ጋር የመሠረትነውን በፍቅርና በመተማመን ላይ የተገነባ ወዳጅነት መጠበቃችን እድገታችንን የሚያንጸባርቅ ይሆናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የምሳሌ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
3:3፦ ፍቅራዊ ደግነትንና እውነትን ከፍ አድርገን ልንመለከታቸውና ልክ እንደ ውድ ሐብል በግልጽ ልናሳያቸው ይገባል። እነዚህ ባሕርያት በልባችን ላይ መቀረጽና ከእኛ ጋር ሙሉ በሙሉ መዋሃድ ይኖርባቸዋል።
ከመጋቢት 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 4
“ልብህን ጠብቅ”
ልብህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
4 በምሳሌ 4:23 ላይ የሚገኘው “ልብ” የሚለው ቃል “የውስጥ ሰውነትን” ለማመልከት ተሠርቶበታል። (መዝሙር 51:6ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) በሌላ አባባል “ልብ” የሚለው ቃል የውስጥ ሐሳብን፣ ስሜትን፣ ዝንባሌንና ምኞትን ያመለክታል። ቃሉ ከውጭ ስንታይ የምንመስለውን ሳይሆን ውስጣዊ ማንነታችንን ይጠቁማል።
ልብህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
10 ልባችንን በመጠበቅ ረገድ እንዲሳካልን ከፈለግን አደጋዎችን ለይተን ማወቅና ራሳችንን ለመጠበቅ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። በምሳሌ 4:23 ላይ “ጠብቅ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ጠባቂዎች የሚያከናውኑትን ሥራ ያስታውሰናል። በንጉሥ ሰለሞን ዘመን የነበሩ ጠባቂዎች በከተማዋ ቅጥር ላይ የሚቆሙ ሲሆን አደጋ መቅረቡን ሲያዩ የማስጠንቀቂያ ድምፅ ያሰሙ ነበር። ይህን ሁኔታ በአእምሯችን መሣላችን ሰይጣን አስተሳሰባችንን እንዳያበላሸው ለመከላከል ምን ማድረግ እንዳለብን እንድንገነዘብ ይረዳናል።
11 በጥንት ዘመን የነበሩ ጠባቂዎች፣ ከከተማዋ በር ጠባቂዎች ጋር ተባብረው ይሠሩ ነበር። (2 ሳሙ. 18:24-26) ሁለቱ ጠባቂዎች፣ ጠላት በሚቃረብበት ጊዜ ሁሉ የከተማዋ በሮች መዘጋታቸውን በማረጋገጥ የከተማዋን ደህንነት በጋራ ይጠብቁ ነበር። (ነህ. 7:1-3) ሰይጣን ልባችንን ለመውረር በሌላ አባባል በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችን፣ በዝንባሌያችን ወይም በምኞታችን ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ሲሞክር በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናችን እንደ ጠባቂ በመሆን ያስጠነቅቀናል። ሕሊናችን የማስጠንቀቂያ ድምፅ በሚያሰማበት ጊዜ ሁሉ ማስጠንቀቂያውን መስማትና ምሳሌያዊ በሮቻችንን መዝጋት ይኖርብናል።
ልብህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
14 ልባችንን ለመጠበቅ በምሳሌያዊ ሁኔታ የልባችንን በር በመዝጋት መጥፎ ተጽዕኖዎችን መከላከላችን ብቻ በቂ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የልባችንን በር በመክፈት በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብንን ነገሮች ማስገባትም ይኖርብናል። እስቲ ዙሪያውን ስለታጠረ ከተማ የጠቀስነውን ምሳሌ በድጋሚ እንመልከት። በር ጠባቂዎቹ የጠላት ወረራን ለመከላከል የከተማዋን በሮች ይዘጉ ነበር፤ ሆኖም በሌሎች ጊዜያት የከተማዋን በሮች ከፍተው ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ማስገባት ይኖርባቸዋል። በሮቹ ሁሌም ዝግ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ለረሃብ መዳረጋቸው አይቀርም። እኛም በተመሳሳይ የአምላክ አስተሳሰብ ለሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ ምንጊዜም ልባችንን ክፍት ማድረግ ይኖርብናል።
“ልብህን ጠብቅ!”
ምሳሌያዊውን ልባችንን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው? ንጉሥ ሰለሞን በአምላክ መንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ነውና።” (ምሳሌ 4:23) ምሳሌያዊው ልባችን ያለበት ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በምንመራው ሕይወትም ሆነ በወደፊቱ ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አምላክ የሚያየው ልባችንን ስለሆነ ነው። (1 ሳሙኤል 16:7) አምላክ ለእኛ ያለው አመለካከት የሚወሰነው በውስጣዊ ማንነታችን ይኸውም ‘በተሰወረው የልብ ሰው’ ነው።—1 ጴጥሮስ 3:4
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነህ?
4 ምሳሌ 4:18 እንዲህ ይላል፦ “የጻድቃን መንገድ . . . ፍንትው ብሎ እንደሚወጣ የማለዳ ብርሃን ነው፤ እንደ ቀትር ብርሃን ቦግ ብሎ እስኪበራም ድረስ እየደመቀ ይሄዳል።” ይህ ሐሳብ ይሖዋ ዓላማውን ለሕዝቡ የሚገልጸው ቀስ በቀስ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ይሁንና ጥቅሱን አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ መንፈሳዊ እድገት የሚያደርግበትን መንገድ ለመግለጽም ልንጠቀምበት እንችላለን። መንፈሳዊ እድገት ጊዜ የሚወስድ ነገር ስለሆነ ልናጣድፈው አንችልም። ከአምላክ ቃልና ከድርጅቱ የምናገኘውን ምክር በትጋት የምናጠናና በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ ቀስ በቀስ የክርስቶስ ዓይነት ባሕርይ ማዳበር እንችላለን። ስለ አምላክ ያለን እውቀትም እያደገ ይሄዳል። ኢየሱስ ይህን ለማብራራት የተጠቀመበትን ምሳሌ እንመልከት።
ከመጋቢት 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 5
ከፆታ ብልግና ራቁ
በሥነ ምግባር በረከሰ ዓለም ውስጥ ንጽህናህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ
በዚህ ምሳሌ ውስጥ ሥነ ምግባር የጎደላት ሴት ‘በጋለሞታ’ ወይም በዝሙት አዳሪ ተመስላለች። ሰለባዋን ለማጥመድ የምትጠቀምባቸው ቃላት ከማር ወለላ ይጣፍጣሉ፣ ከወይራ ዘይት ይልቅም ይለሰልሳሉ። አብዛኛውን ጊዜ የጾታ ብልግና ወደ መፈጸም የሚጋብዙ ሁኔታዎች የሚጀምሩት በዚህ መንገድ አይደለምን? ለምሳሌ ያህል በጸሐፊነት የምትሠራ ኤሚ የምትባል አንዲት የ27 ዓመት ቆንጆ ያጋጠማትን ሁኔታ ተመልከት። እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “የሥራ ባልደረባዬ የሆነው ይህ ሰው ለእኔ ልዩ ትኩረት እንዳለው ከማሳየቱም በላይ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያሞግሰኛል። የሌሎችን ትኩረት ማግኘቱ ደስ ያሰኛል። ሆኖም እኔን የፈለገኝ ለጾታ ግንኙነት ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነበር። እኔ እንደሆንኩ ለእሱ የቃላት መደለያ እጄን አልሰጥም።” የተነገሩበትን ዋነኛ ዓላማ ለይተን ካላወቅን በስተቀር አንድ አታላይ ወንድ ወይም አንዲት አታላይ ሴት ለሽንገላ የሚጠቀሙባቸው ቃላት በአብዛኛው ማራኪ ናቸው። ይህን ለማድረግ የማሰብ ችሎታችንን ማዳበር ያስፈልገናል።
በሥነ ምግባር በረከሰ ዓለም ውስጥ ንጽህናህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ
የሥነ ምግባር ብልግና የሚያስከትለው መዘዝ እንደ እሬት የመረረ እንዲሁም በሁለት ወገን ከተሳለ ሰይፍ ይልቅ ስል በመሆኑ ወደ ከፍተኛ ሥቃይ ብሎም ወደ ሞት የሚመራ ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ድርጊት ብዙውን ጊዜ የህሊና ወቀሳ፣ ያልተፈለገ እርግዝና ወይም በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች እንደመለከፍ ያሉ መራራ መዘዞችን ያስከትላል። እንዲሁም ታማኝ ያልሆነው ወገን በትዳር ጓደኛው ላይ የሚያመጣውን ይህ ነው የማይባል የስሜት ቀውስ እስቲ አስበው። ለትዳር ጓደኛው ያለውን ታማኝነት የሚያጎድል ድርጊት መፈጸም ዕድሜ ልክ የማይሽር ቁስል ሊያስከትል ይችላል። አዎን፣ የሥነ ምግባር ብልግና ጉዳት አለው።
በሥነ ምግባር በረከሰ ዓለም ውስጥ ንጽህናህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ
ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሰዎች ከሚያደርሱት ተጽዕኖ በተቻለ መጠን መራቅ ያስፈልገናል። ወራዳ ሙዚቃዎችን በማዳመጥ፣ በካይ የመዝናኛ ዓይነቶችን በመከታተል ወይም ወሲባዊ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን በማንበብ እንዲሁም በመመልከት በገዛ እጃችን ለምን በር እንከፍትላቸዋለን? (ምሳሌ 6:27፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ኤፌሶን 5:3-5) እንዲሁም አጉል በመሽኮርመም ወይም ልከኛ ባልሆነ አለባበስና አጋጌጥ ትኩረታቸውን መጋበዝ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!—1 ጢሞቴዎስ 4:8፤ 1 ጴጥሮስ 3:3, 4
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በሥነ ምግባር በረከሰ ዓለም ውስጥ ንጽህናህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ
ሰሎሞን የሥነ ምግባር ብልግና ከባድ ኪሳራ እንደሚያስከትል አጉልቶ ተናግሯል። ዝሙትና ለራስ አክብሮት ማጣት የሚነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም። ራስን ሥነ ምግባር ለጎደለው ሰው ወይም የራስ ፍላጎት ማርኪያ አድርጎ ማቅረብ ውርደት አይደለምን? የትዳር ጓደኛችን ካልሆነ ሰው ጋር ጾታዊ ቅርርብ መፍጠር ለራስ አክብሮት ማጣት እንደሆነ አያሳይምን?
ከመጋቢት 24-30
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 6
ከጉንዳን ምን ትምህርት እናገኛለን?
it-1 115 አን. 1-2
ጉንዳን
‘የደመ ነፍስ ጥበብ።’ የጉንዳኖች ‘ጥበብ’ የተገኘው በማሰብና በማመዛዘን ሳይሆን ፈጣሪያቸው በሰጣቸው የደመ ነፍስ ችሎታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጉንዳኖች ‘ምግባቸውን በበጋ እንደሚያዘጋጁና ቀለባቸውንም በመከር ወቅት እንደሚሰበስቡ’ ይናገራል። (ምሳሌ 6:8) ፓለስቲና ውስጥ በብዛት ከሚገኙት የጉንዳን ዝርያዎች አንዱ ማለትም የመከር ወይም የግብርና ጉንዳን (ሜሰር ሰሚረፈስ) በጸደይና በበጋ ወቅት ብዙ እህል ካከማቸ በኋላ ክረምትን ጨምሮ በቀላሉ ምግብ በማይገኝባቸው ወቅቶች ይጠቀምበታል። ይህ ጉንዳን በአብዛኛው የሚገኘው ዘርና እህል በሚትረፈረፍባቸው አውድማዎች አቅራቢያ ነው። የመከር ጉንዳን ያከማቸው እህል በዝናብ ምክንያት ከረጠበ እህሉን ተሸክሞ በማውጣት ፀሐይ ላይ ያደርቀዋል። እንዲያውም እህሉ ተከማችቶ ባለበት እንዳይበቅል ሲል የሚበቅለውን ክፍል ይቆርጠዋል። የጉንዳን መንጋ ያለበት አካባቢ የሚታወቀው በምልልስ ብዛት በሠሩት መንገድና በመኖሪያቸው መግቢያ ላይ በሚተዉት የእህል ቅርፊት ነው።
ምሳሌ የሚሆኑ ባሕርያት። ስለ ጉንዳኖች በአጭሩ መመርመራችን “አንተ ሰነፍ፣ ወደ ጉንዳን ሂድ፤ መንገዷንም በጥሞና ተመልክተህ ጥበበኛ ሁን” የሚለው ምክር በደንብ እንዲገባን ያደርጋል። (ምሳሌ 6:6) ትኩረት የሚስበው ለወደፊቱ ጊዜ መዘጋጀታቸው ብቻ ሳይሆን ጽናታቸውና ቁርጠኝነታቸውም ጭምር ነው፤ ከራሳቸው ክብደት በእጥፍ ወይም ከዚያ በላይ የሚበልጥ ሸክም ይሸከማሉ ወይም ይጎትታሉ፤ የተመደበላቸውን ሥራ ለማከናወን የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ቢወድቁ፣ ቢንሸራተቱ ወይም ከዳገት ላይ ቢንከባለሉም እንኳ ወደ ኋላ ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም። በአስደናቂ ሁኔታ እርስ በርስ ይተባበራሉ፤ መኖሪያቸውን በንጽሕና ይይዛሉ፤ እንዲሁም ለሥራ ባልደረቦቻቸው አሳቢነት ያሳያሉ፤ አንዳንድ ጊዜ የተጎዱ ወይም የደከሙ ጉንዳኖችን ደግፈው ወደ መኖሪያቸው ይወስዳሉ።
መልካም ስምህን ጠብቅ
እኛስ እንደ ጉንዳን ታታሪ መሆን አይገባንም? በቅርብ ሆኖ የሚቆጣጠረን ኖረም አልኖረ ተግተን መሥራታችንና የሥራችንን ጥራት በየጊዜው ለማሻሻል መጣራችን ጥቅሙ ለእኛው ነው። አዎን፣ በትምህርት ቤት፣ ተቀጥረን በምንሠራበት ቦታና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በምንካፈልበት ጊዜ አቅማችን የፈቀደውን መሥራት አለብን። ጉንዳን ከታታሪነቷ ጥቅም እንደምታገኘው ሁሉ አምላክ ‘በድካማችን ሁሉ ደስ እንዲለን’ ይፈልጋል። (መክብብ 3:13, 22፤ 5:18) ንፁሕ ሕሊናና የመንፈስ እርካታ ተግቶ በመሥራት የሚገኙ በረከቶች ናቸው።—መክብብ 5:12
ሰሎሞን ለማስተላለፍ የፈለገውን ነጥብ ጠንከር አድርጎ በመግለጽ ሰነፍን ከስንፍናው ለመቀስቀስ “አንተ ታካች፣ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ?” የሚሉትን ሁለት ጥያቄዎች ተጠቅሟል። ንጉሡ በማሾፍ አነጋገር አክሎ እንዲህ ይላል፦ “ጥቂት ትተኛለህ፣ ጥቂት ታንቀላፋለህ፣ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፤ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፣ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል።” (ምሳሌ 6:9-11) ሰነፍ ሰው ተንጋሎ እንደተኛ ድህነት እንደ ሽፍታ ፈጥኖ ይደርስበታል፤ ማጣትም ሰይፍ እንደታጠቀ ሰው ጥቃት ይሰነዝርበታል። የሰነፍ ሰው እርሻ ወዲያው አረምና ሳማ ይወርሰዋል። (ምሳሌ 24:30, 31) ንግዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይከስራል። አንድ አሠሪ ዳተኛ ሠራተኛን እስከ መቼ ይታገሠዋል? ማጥናት የማይወድ ተማሪ በትምህርቴ ጥሩ ውጤት አገኛለሁ ብሎ ሊጠብቅ ይችላል?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
መልካም ስምህን ጠብቅ
በዚህ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት ሰባት ነገሮች መሠረታዊ በመሆናቸው ሁሉንም ዓይነት መጥፎ ነገሮች ያጠቃልላሉ ማለት ይቻላል። “ትዕቢተኛ ዓይን” እና “ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ” በሐሳብ ደረጃ የሚፈጸሙ ኃጢአቶች ናቸው። “ሐሰተኛ ምላስ” እና “በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር” በክፋት የሚነገሩ ቃላት ናቸው። “ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ” እና “ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር” የተባሉት የክፋት ድርጊቶች ናቸው። በተለይ ይሖዋ በሰላም አብረው በሚኖሩ ሰዎች መካከል ጠብ በመዝራት የሚደሰትን ሰው ይጠላል። የሰው ልጆች የሚሠሩት ክፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለሚሄድ ቁጥሩ ከስድስት ወደ ሰባት ከፍ ማለቱ ዝርዝሩ በዚሁ የሚያበቃ እንዳልሆነ የሚያመለክት ነው።
ከመጋቢት 31–ሚያዝያ 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 7
ከፈታኝ ሁኔታዎች ራቁ
“ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ”
ሰሎሞን ወደ ውጪ የተመለከተበት የቤቱ መስኮት፣ ሰቅሰቅ ያለው ሲሆን ይህም ቄንጠኛ ሆኖ የተሠራ ጌጥ ያለው ሊሆን ይችላል። ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ጎዳናው ጨለምለም ይላል። ሰሎሞን ራሱን ለአደጋ ያጋለጠን አንድ ወጣት አየ። ይህ ወጣት የማስተዋል ወይም የማመዛዘን ችሎታውን መጠቀም ስለተሳነው ልቦና እንደጎደለው ያሳያል። ምን ዓይነት ሠፈር ውስጥ እንደገባና ምን ሊደርስበት እንደሚችል ሳይገነዘብ አልቀረም። ይህ ወጣት የቤትዋን መንገድ ይዞ ‘ቤትዋ አቅራቢያ’ ደረሰ። እሷ ማን ነች? የምትፈልገውስ ምንድን ነው?
“ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ”
ይህች ሴት ከንፈርዋ ልዝብ ነው። ያለ ምንም እፍረት በድፍረት ትናገራለች። የምትናገራቸው ቃላት ሁሉ ሆን ተብለው ወጣቱን ለማታለል የተቀነባበሩ ናቸው። የዚያን ዕለት የደኅንነት መሥዋዕት እንዳቀረበችና ስእለቷን እንዳገባች በመግለጽ በጥሩ መንፈሳዊ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በመጠቆም ጻድቅ መስላ ለመታየት ትሞክራለች። ኢየሩሳሌም ይገኝ በነበረው ቤተ መቅደስ ሥጋ፣ ዱቄት፣ ዘይትና ወይን ለደኅንነት መሥዋዕት ይቀርብ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:5, 6፤ 22:21፤ ዘኁልቁ 15:8-10) የደህንነት መሥዋዕት ያቀረበው ሰው ከመሥዋዕቱ የተወሰነውን ለራሱና ለቤተሰቡ መውሰድ ይችል ስለነበር በቤትዋ የሚበላና የሚጠጣ እንደልብ እንደሚገኝ በተዘዋዋሪ መናገሯ ነው። ሐሳቧ ግልጽ ነው፦ ወጣቱ አስደሳች ጊዜ ያሳልፋል ማለቷ ነው። ከቤቷ የወጣችው ሆን ብላ እሱን ፍለጋ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ማባበያ የሚቀበል ሰው ምንኛ ሞኝ ነው! አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ሲናገሩ “እርግጥ ከቤት የወጣችው አንድ ሰው ለማግኘት ፈልጋ እንደነበረ እሙን ነው። ይሁን እንጂ የወጣችው እውነት ይህን ወጣት ለማግኘት ብላ ነው? እንደዚህ ወጣት ያለ ጅላጅል ካልሆነ በስተቀር ማንም አያምናትም” ብለዋል።
በአለባበስዋ፣ በሚሸነግሉ ቃላቶችዋ፣ በእጆችዋ በመደባበስና በመሳም ታማልለዋለች። እንዲህ ትለዋለች “በአልጋዬ ላይ ማለፊያ ሰርፍ ዘርግቼበታለሁ፣ የግብጽንም ሽመልመሌ ለሀፍ። በመኝታዬ ከርቤንና ዓልሙን ቀረፋም ረጭቼበታለሁ።” (ምሳሌ 7:16, 17) አልጋዋን ከግብጽ በመጣ የሚያምር አልጋ ልብስ ያሳመረች ሲሆን ከከርቤ፣ ከዓልሙንና ከቀረፋ የተሠራ ሽቶ ረጭታበታለች።
ቀጥላም “ና፣ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፣ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን” ትለዋለች። ግብዣው ሁለቱ አብረው እራት ከመብላት ያለፈ ነገር እንዲያደርጉ ነው። የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ እያግባባችው ነው። ይህ ግብዣ ለዚህ ወጣት እንደ ጀብዱ የሚቆጠር አስደሳች ገጠመኝ ነው! አክላም “ባለቤቴ በቤቱ የለምና፣ ወደ ሩቅ መንገድ ሄዶአልና፤ በእጁም የብር ከረጢት ወስዶአል፤ ሙሉ ጨረቃ በሆነች ጊዜ ወደ ቤቱ ይመለሳል” በማለት ታግባባዋለች። (ምሳሌ 7:18-20) ባለቤትዋ ለሥራ ጉዳይ ወደ ሩቅ አገር ስለሄደና በቅርቡም ስለማይመለስ ምንም የሚያሰጋቸው ነገር እንደሌለ ትነግረዋለች። አንድን ወጣት በማታለል ረገድ እንዴት የተካነች ነች! “በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፤ በከንፈርዋ ልዝብነት ትጐትተዋለች።” (ምሳሌ 7:21) እንደዚህ ባለው ማባበያ ላለመሸነፍ የዮሴፍን ዓይነት የሞራል ጥንካሬ ያስፈልጋል። (ዘፍጥረት 39:9, 12) ወጣቱ ማሸነፍ ይችል ይሆን?
“ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ”
ወጣቱ የቀረበለትን ግብዣ እምቢ ማለት አልቻለም። ማስተዋሉ ጠፍቶ ‘ለእርድ እንደሚነዳ በሬ’ ተከትሏት ሄደ። በእግረ ሙቅ የታሰረ ሰው ማምለጥ እንደማይችል ሁሉ ወጣቱም እንዲሁ በማይወጣበት ኃጢአት ውስጥ ሊዘፈቅ ነው። “ፍላጻ ጉበቱን እስኪሰነጥቀው” ማለትም ለሞት ሊዳርገው የሚችል ጉዳት እስኪያገኘው ድረስ አደጋው አይታየውም። በጾታ ግንኙነት ለሚተላለፍ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ራሱን ስለሚያጋልጥ ሞቱ ቃል በቃል አካላዊ ሞት ሊሆን ይችላል። ያጋጠመው ነገር “ለነፍሱ ጥፋት” ስለሚሆንበት ለመንፈሳዊ ሞትም ሊዳርገው ይችላል። መላ እሱነቱንና ሕይወቱን ክፉኛ የሚጎዳ ነገር ከማድረጉም በላይ በአምላክ ላይ ከባድ ኃጢአት ሠርቷል። ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል ወፍ እሱም በሞት መዳፍ ለመያዝ ይጣደፋል!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
“ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ”
ሰሎሞን ‘ትእዛዞቼን በጣቶችህ ላይ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው’ በማለት ይቀጥላል። (ምሳሌ 7:3) ጣቶቻችን ምንጊዜም ከፊታችን እንደማይጠፉና የምንፈልገውን ለመሥራት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጡን ሁሉ ከቅዱሳን ጽሑፎች የምናገኛቸው ትምህርቶች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትም የማይነጥፍ ማሳሰቢያና ማንኛውንም ሥራ ስናከናውን መመሪያ ይሆኑልናል። በልባችን ጽላት ላይ በመጻፍ የባሕርያችን ክፍል እንድናደርገው ተመክረናል።
ከሚያዝያ 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 8
የጥበብን ድምፅ አዳምጡ
‘እኔ አብን እወደዋለሁ’
7 በቁጥር 22 ላይ ጥበብ “ይሖዋ የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ፤ ከብዙ ዘመን በፊት ካከናወናቸው ሥራዎች ቀዳሚው አደረገኝ” በማለት ትናገራለች። ጥበብ በሆነ ወቅት ላይ ‘የተፈጠረ’ ባሕርይ ስላልሆነ እዚህ ላይ ያለው አገላለጽ ከጥበብ ያለፈ ነገርን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖረው ይሖዋ ጥበበኛ ያልነበረበት ጊዜ የለም፤ በመሆኑም ጥበብ ከሆነ ወቅት ጀምሮ ሕልውና እንዳገኘ ተደርጎ ሊገለጽ አይችልም። (መዝሙር 90:2) የአምላክ ልጅ ግን “የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው።” ተፈጥሯል ወይም ወደ ሕልውና እንዲመጣ ተደርጓል፤ ከይሖዋ ሥራዎች ሁሉ ቀዳሚው እሱ ነው። (ቆላስይስ 1:15) በምሳሌ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው የአምላክ ልጅ ምድርና ሰማያት ከመፈጠራቸው በፊት በሕይወት ነበረ። ኢየሱስ ቃል ማለትም የአምላክ ቃል አቀባይ እንደመሆኑ መጠን የይሖዋ ጥበብ ፍጹም መገለጫ ነበር።—ዮሐንስ 1:1
‘እኔ አብን እወደዋለሁ’
8 የአምላክ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በነበረው ረጅም ጊዜ ውስጥ ምን ይሠራ ነበር? ቁጥር 30 “የተዋጣለት ሠራተኛ” በመሆን ከአምላክ ጎን ሲሠራ እንደነበር ይነግረናል። ይህ ምን ማለት ነው? ቆላስይስ 1:16 እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ . . . የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት ነው። ሌሎች ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት በእሱ በኩልና ለእሱ ነው።” በመሆኑም ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ሌሎች ፍጥረታትን ሁሉ ወደ ሕልውና ያመጣው የተዋጣለት ሠራተኛ በሆነው በልጁ በኩል ነው፤ ይህም በሰማይ ያሉትን መንፈሳዊ ፍጥረታት፣ ግዙፍ የሆነውን ግዑዝ ጽንፈ ዓለም እንዲሁም ምድርንና በላይዋ ያሉትን የተለያዩ አስደናቂ ዕፀዋትና እንስሳት ብሎም የምድር ፍጥረታት ቁንጮ የሆነውን የሰውን ልጅ ያካትታል። በአብና በወልድ መካከል ያለው ይህ ትብብር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአንድ ንድፍ አውጪና በአንድ ግንበኛ ወይም ሕንፃ ተቋራጭ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ የግንበኛው ሚና፣ ንድፍ አውጪው ያወጣው አስደናቂ ንድፍ እውን እንዲሆን ማድረግ ነው። አንድን የፍጥረት ሥራ አይተን ስንደነቅ ለታላቁ ንድፍ አውጪ እውቅና እየሰጠን እንደሆነ የታወቀ ነው። (መዝሙር 19:1) ሆኖም በፈጣሪና “የተዋጣለት ሠራተኛ” በተባለው ልጁ መካከል ስላለው ለረጅም ዘመን የዘለቀ አስደሳች ትብብር ማሰባችንም አይቀርም።
9 ፍጽምና የጎደላቸው ሁለት ሰዎች አብረው ሲሠሩ አንዳንድ ጊዜ በመካከላቸው አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። በይሖዋና በልጁ መካከል ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው! ወልድ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ከአባቱ ጋር ሲሠራ የቆየ ቢሆንም “በፊቱ ሁልጊዜ ሐሴት አደርግ ነበር” ብሏል። (ምሳሌ 8:30) በእርግጥም ወልድ ከአባቱ ጋር አብሮ መሥራት ያስደስተው ነበር፤ አባቱም እንዲሁ ይሰማው ነበር። ወልድ የአባቱን ባሕርያት በመኮረጅ ይበልጥ እሱን እየመሰለ መሄዱ የሚጠበቅ ነው። በአብና በወልድ መካከል ያለው ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየጠነከረ መምጣቱ ምንም አያስገርምም! በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ያህል ረጅም ዘመን ያስቆጠረና ጠንካራ የሆነ የፍቅር ትስስር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ኢየሱስ ታላቁ ዳዊትና ታላቁ ሰለሞን በመሆን የሚጫወተውን ሚና መረዳት
14 ከሰለሞን የላቀ ጥበብ ያለው ሰው አንድ ብቻ ሲሆን እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እሱ ራሱ ‘ከሰለሞን እንደሚበልጥ’ ገልጿል። (ማቴ. 12:42) ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ቃል” ተናግሯል። (ዮሐ. 6:68) ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ በተራራው ስብከት ላይ የተናገራቸው ሐሳቦች የሰለሞን ምሳሌዎች የያዙትን መሠረታዊ ሥርዓት ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉ ናቸው። ሰለሞን ለይሖዋ አምላኪዎች ደስታ የሚያስገኙ በርካታ ነገሮችን ገልጿል። (ምሳሌ 3:13፤ 8:32, 33፤ 14:21፤ 16:20) ኢየሱስም እውነተኛ ደስታ የሚያስገኙት ከይሖዋ አምልኮና አምላክ ከሰጣቸው ተስፋዎች ፍጻሜ ጋር የተያያዙ ነገሮች እንደሆኑ ጎላ አድርጎ ተናግሯል። ኢየሱስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና” ብሏል። (ማቴ. 5:3) በኢየሱስ ትምህርት ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች “የሕይወት ምንጭ” ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ ይቀርባሉ። (መዝ. 36:9፤ ምሳሌ 22:11፤ ማቴ. 5:8) “የአምላክ ጥበብ” በክርስቶስ ተገልጿል። (1 ቆሮ. 1:24, 30) ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሐዊ ንጉሥ በመሆኑ “የጥበብ . . . መንፈስ” አለው።—ኢሳ. 11:2
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
‘ጥበብ ጮኻ ትጣራለች’—ጥሪዋ ይሰማሃል?
▪ ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በሰፊው የተሠራጨ መጽሐፍ አይገኝም። ከማንኛውም መጽሐፍ በላይ ብዙ ጊዜና በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉሟል።” በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል 2,600 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች የሚገኝ በመሆኑ ከዓለም ሕዝብ መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ሊያገኘው ይችላል።
▪ ጥበብ በሌላም መንገድ ቃል በቃል ‘ድምጿን ከፍ አድርጋ እየጮኸች’ ነው ማለት እንችላለን። በማቴዎስ 24:14 ላይ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው [የዚህ ዓለም መጨረሻ] ይመጣል” የሚል ሐሳብ እናነባለን።
ከሚያዝያ 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 9
ጥበበኛ እንጂ ፌዘኛ አትሁኑ
‘የጥበበኞችን ቃል አዳምጥ’
4 እውነታውን ካየን፣ ብዙ ጊዜ መቀበል የሚከብደን ቀጥተኛ የሆነን ምክር ነው። እንዲያውም እንበሳጭ ይሆናል። ለምን? ፍጹም አለመሆናችንን መቀበል ባይከብደንም አንድ ሰው ድክመታችንን ለይቶ ሲነግረን፣ ብዙውን ጊዜ ምክሩን መቀበል ይተናነቀናል። (መክብብ 7:9ን አንብብ።) ሰበብ አስባብ እንደረድር ይሆናል። ምክሩን በሰጠን ግለሰብ ዝንባሌ ላይ ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን፤ ወይም ደግሞ ምክሩን በሰጠበት መንገድ እንከፋ ይሆናል። ሌላው ቀርቶ ምክር በሰጠን ሰው ላይ እንከን ወደመፈላለግ ልንሄድ እንችላለን፤ ‘እሱ ማን ሆኖ ነው እንዲህ የሚለኝ? እሱ ራሱ ስንት ነገር ያጠፋ የለ!’ እንል ይሆናል። የተሰጠንን ምክር ካልወደድነው ደግሞ ምክሩን ችላ ልንለው ወይም ሌላ የሚስማማንን ምክር ፍለጋ ልንሄድ እንችላለን።
‘የጥበበኞችን ቃል አዳምጥ’
12 ምክር ለመቀበል ምን ይረዳናል? ትሑት መሆን ይኖርብናል፤ ፍጹማን እንዳልሆንንና አንዳንድ ጊዜ የሞኝነት ድርጊት ልንፈጽም እንደምንችል ማስታወሳችን በዚህ ረገድ ይረዳናል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ኢዮብ የተሳሳተ አመለካከት ነበረው። በኋላ ላይ ግን አመለካከቱን አስተካከለ፤ ይሖዋም ባርኮታል። ለምን? ኢዮብ ትሑት ስለነበረ ነው። በዕድሜ በጣም የሚያንሰው ቢሆንም የኤሊሁን ምክር መስማቱ ትሑት እንደሆነ የሚያሳይ ነው። (ኢዮብ 32:6, 7) እኛም ምክሩ ለእኛ እንደማይሠራ ሲሰማን ወይም ምክሩን የሰጠን ሰው በዕድሜ ከእኛ በጣም የሚያንስ በሚሆንበት ጊዜ ትሕትና ምክሩን ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳናል። በካናዳ ያለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ራሳችንን የምናየው ሌሎች እኛን በሚያዩን መንገድ ስላልሆነ የሚመክረን ሰው ከሌለ እንዴት መሻሻል እንችላለን?” ደግሞም የመንፈስ ፍሬ ከማፍራት እንዲሁም ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ከምናከናውንበት መንገድ ጋር በተያያዘ ማሻሻያ ማድረግ የማያስፈልገው ማን አለ?—መዝሙር 141:5ን አንብብ።
13 የሚሰጣችሁን ምክር የአምላክ ፍቅር መገለጫ አድርጋችሁ ተመልከቱት። ይሖዋ የሚመኝልን የሚጠቅመንን ነገር ነው። (ምሳሌ 4:20-22) በቃሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ወይም በአንድ የጎለመሰ የእምነት ባልንጀራችን ተጠቅሞ ሲመክረን ፍቅሩን እየገለጸልን ነው። ዕብራውያን 12:9, 10 “ለጥቅማችን ሲል ይገሥጸናል” ይላል።
14 በምክሩ ላይ እንጂ በአሰጣጡ ላይ አታተኩሩ። አንዳንድ ጊዜ ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ችግር እንዳለው ይሰማን ይሆናል። እርግጥ፣ ምክር የሚሰጥ ማንኛውም ሰው በተቻለ መጠን የሚመከረው ሰው ምክሩን መቀበል ቀላል እንዲሆንለት ሊያደርግ ይገባል። (ገላ. 6:1) ተመካሪዎቹ እኛ ከሆንን ግን ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ባያስደስተንም እንኳ በመልእክቱ ላይ ማተኮራችን ጠቃሚ ነው። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ምክሩ የተሰጠበትን መንገድ ባልወደውም እንኳ ከተናገረው ነገር የማገኘው ትምህርት ይኖር ይሆን? ምክር ሰጪው ያሉትን ድክመቶች በማለፍ ከምክሩ ጥቅም ማግኘት እችል ይሆን?’ ምንም ዓይነት ምክር ቢሰጠን ከምክሩ ጥቅም ለማግኘት ጥረት ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 15:31
‘ጥበብ ረጅም ዘመን ታኖረናለች’
ጥበበኛ ሰው ለእርማት የሚሰጠው ምላሽ ፌዘኛ ሰው ከሚሰጠው ምላሽ ፈጽሞ የተለየ ነው። ሰሎሞን “ጠቢብን ገሥጽ ይወድድህማል። ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፣ ጥበብንም ያበዛል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 9:8ለ, 9ሀ) ጠቢብ ሰው ‘ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ እንዳልሆነ፣ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን እንደሚያፈራላቸው’ ያውቃል። (ዕብራውያን 12:11) ምክር የማያስደስት ቢሆንም እንኳ እሺ ብለን እስከ ተቀበልን ድረስ ይበልጥ ጠቢብ የሚያደርገን ከሆነ የአጸፋ እርምጃ የምንወስድበት ወይም ምክሩን ላለመቀበል የምንከላከልበት ምን ምክንያት አለ?
ሰሎሞን “ጽድቅንም አስተምረው፣ እውቀትንም ያበዛል” በማለት ይቀጥላል። (ምሳሌ 9:9ለ) በጣም ጠቢብ ወይም በዕድሜ የገፋ በመሆኑ ትምህርት የማያስፈልገው ሰው የለም። በዕድሜ በጣም የገፉ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ እውነትን ተቀብለው ራሳቸውን ለይሖዋ ሲወስኑ ማየቱ ምንኛ የሚያስደስት ነው! እኛም ብንሆን ትምህርት የመቅሰምና አእምሯችንን የማሠራት ፍላጎት እንዲኖረን የምንጥር እንሁን።
‘ጥበብ ረጅም ዘመን ታኖረናለች’
ጥበብን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ የእያንዳንዱ ግለሰብ ኃላፊነት ነው። ሰሎሞን ይህን ሃቅ ጎላ አድርጎ ሲናገር “ጠቢብ ብትሆን ለራስህ ጠቢብ ትሆናለህ፣ ፌዘኛም ብትሆን ፌዘኛነትህን ለብቻህ ትሸከማለህ” ብሏል። (ምሳሌ 9:12) ጠቢብ ሰው ጠቢብ በመሆኑ የሚጠቀመው ራሱ ነው፤ ፌዘኛም ለሚደርስበት ሥቃይ ኃላፊነቱን የሚሸከመው ራሱ ነው። በእርግጥም የምንዘራውን ያንኑ እናጭዳለን። እንግዲያው ‘ጥበብ ስትናገር በጥሞና እናዳምጥ።’—ምሳሌ 2:2
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የምሳሌ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
9:17—“የስርቆት ውሃ” የተባለው ምንድን ነው? ‘ጣፋጭ’ የሆነውስ በምን መልኩ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በትዳር ጓደኛሞች መካከል የሚደረግ የጾታ ግንኙነት የሚያስገኘውን ደስታ ከምንጭ የተቀዳ የሚያረካ ውኃ ከመጠጣት ጋር ያመሳስለዋል። በመሆኑም የስርቆት ውኃ የተባለው በድብቅ የሚደረግ የጾታ ግንኙነት ነው። (ምሳሌ 5:15-17) ግለሰቡ፣ ድርጊቱ በሌሎች ዘንድ እንደማይታወቅበት ማሰቡ እንዲህ ያለው ውኃ ጣፋጭ እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል።
ከሚያዝያ 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 10
እውነተኛ ብልጽግና የሚያስገኘው ምንድን ነው?
‘ጻድቅ በረከት ያገኛል’
ጻድቅ ሰው በሌላም መንገድ ይባረካል። “የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች። በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል።”—ምሳሌ 10:4, 5
ንጉሡ በመከር ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሠራተኞች የተናገራቸው ቃላት ይበልጥ ትርጉም አላቸው። የመከር ወቅት ያለ ሐሳብ የሚተኛበት ጊዜ አይደለም። ረጅም ሰዓት ተግቶ የሚሠራበት ወቅት ነው። በእርግጥም የጥድፊያ ጊዜ ነው።
ኢየሱስ እህል የሚሰበሰብበትን የመከር ወቅት ሳይሆን ሰዎች የሚሰበሰቡበትን ጊዜ በአእምሮው በመያዝ ደቀ መዛሙርቱን “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ [ይሖዋ አምላክ] ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።” (ማቴዎስ 9:35-38) በ2000 ዓመት ከ14 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ይኸውም የይሖዋ ምሥክሮችን በሁለት እጥፍ የሚበልጡ ሰዎች በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል። ታዲያ ‘አዝመራው ነጥቶ ለአጨዳ መድረሱን’ ማን ሊክድ ይችላል? (ዮሐንስ 4:35) እውነተኛ አምላኪዎች ከጸሎታቸው ጋር በሚስማማ መንገድ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ በትጋት እየተካፈሉ የመከሩ ጌታ ተጨማሪ ሠራተኞች እንዲልክ ይለምናሉ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይሖዋ ጥረታቸውን ምንኛ ባርኮላቸዋል! በ2000 የአገልግሎት ዓመት ከ280,000 የሚበልጡ አዳዲስ ሰዎች ተጠምቀዋል። እነዚህም በበኩላቸው የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በሙሉ አቅማችን በመካፈል በዚህ የመከር ወቅት ደስታና እርካታ እናግኝ።
‘ቀና በሆነው መንገድ’ ሂድ
ሰሎሞን “የባለጠጋ ሀብት ለእርሱ የጸናች ከተማ ናት፤ የድሆች ጥፋት ድህነታቸው ነው። የጻድቅ ደመወዝ ለሕይወት ነው፤ የኀጥእ ፍሬ ግን ለኃጢአት ነው” በማለት የጽድቅን አስፈላጊነት ተናግሯል።—ምሳሌ 10:15, 16
በቅጥር የተከበበች ከተማ በውስጧ የሚኖሩ ሰዎች በተወሰነ መጠን ደኅንነት እንዲሰማቸው እንደምታደርግ ሁሉ ሃብትም በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ አንዳንድ ስጋቶች ሊያሳርፍ ይችላል። ድህነት ያልተጠበቁ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ከባድ ችግር ላይ ሊጥል ይችላል። (መክብብ 7:12) ይሁን እንጂ ጠቢቡ ንጉሥ ከሃብትም ከድህነትም ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችል አደጋ እንዳለ እየጠቆመም ሊሆን ይችላል። ባለጠጋ ሀብቱን “እንደ ጸናች ከተማ” አድርጎ በማሰብ ትምክህቱን ሙሉ በሙሉ በሀብቱ ላይ ወደ ማድረግ ያዘነብል ይሆናል። (ምሳሌ 18:11) እንዲሁም ድሃ በድህነቱ የተነሳ ምንም የወደፊት ተስፋ እንደሌለው አድርጎ ሊያስብ ይችላል። በዚህ ምክንያት ሁለቱም በአምላክ ዘንድ መልካም ስም ሳያተርፉ ይቀራሉ።
it-1 340
በረከት
ይሖዋ ለሰዎች የሚሰጠው በረከት። “የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤ እሱም ከበረከቱ ጋር ሥቃይን አይጨምርም።” (ምሳሌ 10:22) ይሖዋ የሚደሰትባቸውን ሰዎች በመጠበቅ፣ በማበልጸግ፣ በመምራት፣ ስኬት በመስጠት እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማሟላት ይባርካቸዋል፤ ይህም የኋላ ኋላ ጥሩ ውጤት ያስገኝላቸዋል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ያለ ነቀፋ መኖር የሚያስገኘው ደስታ
18 “የእግዚአብሔር በረከት” ሕዝቦቹ መንፈሳዊ ብልጽግና እንዲኖራቸው አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ “መከራንም አያክልባትም” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ምሳሌ 10:22) ይህ ከሆነ ታዲያ በርካታ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ብዙ ሥቃይና መከራ የሚያስከትል ፈተና የሚደርስባቸው ለምንድን ነው? ችግሮችና የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙን በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ ነው። (1) ኃጢአተኛው ዝንባሌያችን። (ዘፍጥረት 6:5፤ 8:21፤ ያዕቆብ 1:14, 15) (2) ሰይጣንና አጋንንቱ። (ኤፌሶን 6:11, 12) (3) ክፉው ዓለም። (ዮሐንስ 15:19) ይሖዋ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱብን ቢፈቅድም እነዚህን ነገሮች የሚያመጣብን እርሱ አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ” ይላል። (ያዕቆብ 1:17) የይሖዋ በረከት መከራን አይጨምርም።
ከሚያዝያ 28–ግንቦት 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 11
አትናገሩ!
ጽኑ አቋም ቅኖችን ይመራቸዋል
በተጨማሪም ቅን ሰው የሚያሳየው ጽኑ አቋምና የክፉ አድራጊዎች ክፋት በሌሎች ሰዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም። የእስራኤል ንጉሥ “ዝንጉ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፤ ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ” ይላል። (ምሳሌ 11:9) ስም ማጥፋት፣ ጎጂ ሐሜት፣ ጸያፍ አነጋገርና ከንቱ ልፍለፋ ሌሎችን እንደሚጎዳ ማን ይክዳል? በሌላ በኩል ግን የጻድቅ ሰው አነጋገር ንጹሕ፣ የታሰበበትና አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ነው። እንዲህ ያለ ሰው ያለው ጽኑ አቋም ከሳሾቹ እየዋሹ እንደሆነ ለማሳየት የሚያስችለውን የማሳመኛ ነጥብ እንዲያቀርብ ስለሚያስችለው በእውቀት ይድናል።
ጽኑ አቋም ቅኖችን ይመራቸዋል
ቀና የሆነውን መንገድ የሚከተሉ የከተማ ሰዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ሰላምና ደህንነት ያስገኛሉ። በዚህም ምክንያት ከተማዋ ከፍ ከፍ ትላለች ወይም ትበለጽጋለች። ስም የሚያጠፉ፣ ጎጂና የተሳሳቱ ነገሮችን የሚናገሩ ሰዎች አለመረጋጋት፣ ሐዘን፣ ክፍፍልና ችግር ይፈጥራሉ። በተለይ ደግሞ እነዚህ ሰዎች በሌሎች ዘንድ ተደማጭነት ካላቸው እንዲህ ያለው ነገር መከሰቱ የማይቀር ነው። እንዲህ ያለች ከተማ ረብሻ፣ ምግባረ ብልሹነትና የሥነ ምግባር ምናልባትም የኢኮኖሚ ውድቀት አያጣትም።
በምሳሌ 11:11 ላይ የተገለጸው መሠረታዊ ሥርዓት ከተማ መሰል በሆነው ጉባኤያቸው ውስጥ እርስ በርስ በሚቀራረቡ የይሖዋ ሕዝቦች ላይም በእኩል ደረጃ ይሠራል። መንፈሳዊ ሰዎች በሌላ አነጋገር በጽኑ አቋማቸው የሚመሩ ቅን ሰዎች በጎ ተጽእኖ የሚያሳድሩበት ጉባኤ ለአምላክ ክብር የሚያመጡ ደስተኛ፣ ንቁና እርዳታ ለማበርከት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችን ያቀፈ ጉባኤ ይሆናል። ይሖዋ ጉባኤውን ስለሚባርክ በመንፈሳዊ ይበለጽጋል። አልፎ አልፎ፣ አንዳንድ ነገሮች የሚከናወኑበት መንገድ ቅር ያሰኛቸውና በሁኔታው ያልተደሰቱ፣ የሚተቹና በምሬት የሚናገሩ ጥቂት ሰዎች ብቅ ብቅ በማለት ቀስ በቀስ ሊዛመትና ጤነኛ የነበሩትን ሊመርዝ የሚችል “መራራ ሥር” ይሆናሉ። (ዕብራውያን 12:15) እንዲህ ያሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ፍላጎታቸው ተጨማሪ ሥልጣንና ክብር ማግኘት ነው። በጉባኤው ውስጥ ወይም በሽማግሌዎች ላይ አድሏዊነት፣ ዘረኝነት ወይም ይህን የመሰለ ችግር እንደሚታይ የሚገልጽ ወሬ ከወዲያ ወዲህ ያናፍሳሉ። በእርግጥም አፋቸው በጉባኤው ውስጥ መከፋፈልን ሊፈጥር ይችላል። ለወሬያቸው ጆሮ ባለመስጠት ለጉባኤው ሰላምና አንድነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ የምናበረክት መንፈሳዊ ሰዎች ለመሆን መጣር አይኖርብንም?
ጽኑ አቋም ቅኖችን ይመራቸዋል
ማስተዋል ወይም “አእምሮ የጎደለው” ሰው የሚፈጥረው ጉዳት ምንኛ የከፋ ነው! ለአንደበቱ ገደብ ስለማያበጅ ስም እስከማጥፋት ወይም እስከመሳደብ ይደርሳል። የተሾሙ ሽማግሌዎች እንዲህ ያለ ሰው የሚያሳድረውን መጥፎ ተጽእኖ ለማስቆም ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል። አስተዋይ ሰው ‘አእምሮ ከጎደለው’ ሰው በተቃራኒ መቼ ዝም ማለት እንዳለበት ያውቃል። የሌላውን ምስጢር ከማውጣት ይቆጠባል። አስተዋይ ሰው እንዳመጣለት የሚናገር ምላስ ብዙ ጉዳት እንደሚያስከትል በመገንዘብ “በመንፈስ የታመነ” ይሆናል። ለእምነት ባልንጀሮቹ ታማኝ ሲሆን አደጋ ላይ ሊጥላቸው የሚችለውን ምስጢር አያወጣባቸውም። እንዲህ ያሉ ጽኑ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ለአንድ ጉባኤ ምንኛ በረከት ናቸው!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
g20.1 11 ሣጥን
ውጥረትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
“ደግነት በማሳየት ውጥረትን ተዋጋ”
“ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል፤ ጨካኝ ሰው ግን በራሱ ላይ መከራ ያመጣል።”—ምሳሌ 11:17
ውጥረትን መቋቋም (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ “ደግነት በማሳየት ውጥረትን ተዋጋ” የሚል ምዕራፍ አለው። የመጽሐፉ ደራሲ የሆኑት ዶክተር ቲም ካንቶፈር እንደገለጹት ለሌሎች ደግነት ማሳየት ጤናማና ደስተኛ ለመሆን ይረዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ደግነት የጎደለው ወይም ጨካኝ የሆነ ሰው ሌሎች ሰዎች ስለማይቀርቡት ደስታ ይርቀዋል።
ለራሳችንም ደግነት ማሳየታችን ውጥረታችንን ለመቀነስ ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ በራሳችን ላይ መጨከን ወይም ከአቅማችን በላይ መጠበቅ አይኖርብንም። ራሳችንን ማቃለል ወይም ማጣጣልም የለብንም። ኢየሱስ ክርስቶስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል።—ማርቆስ 12:31