የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከሐምሌ 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 21
ለሰመረ ትዳር የሚረዱ ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶች
ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ሳይታሰብበት በጥድፊያ የተደረገ ውሳኔ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ምሳሌ 21:5 “የትጉህ አሳብ ወደ ጥጋብ ያደርሳል ችኩል ሰው ሁሉ ግን ለመጉደል ይቸኩላል” በማለት ያስጠነቅቃል። ለምሳሌ ያህል በወረት ፍቅር የተያዙ አፍላ ወጣቶች ተጣድፈው ትዳር ከመመሥረታቸው በፊት ጊዜ ሰጥተው ሊያስቡበት ይገባል። ካለበለዚያ በ18ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የኖረው ዊልያም ኮንግሪቭ የተባለ ጸሐፊ ተውኔት “ተጣድፈን ካገባን የብዙ ዘመን ጸጸት እናተርፋለን” በማለት የተናገረው ሐቅ በእነርሱ ላይ ይፈጸማል።
ትዳር የሰመረ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
ትሕትና አሳዩ። “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ።” (ፊልጵስዩስ 2:3) ብዙ ግጭቶች የሚነሱት የትዳር ጓደኛሞች የተፈጠረውን ችግር በትሕትና ለመፍታት ከመጣር ይልቅ አንዳቸው ሌላውን ተጠያቂ ለማድረግ ስለሚሞክሩ ነው። ራስን ዝቅ የማድረግ መንፈስ ወይም ትሕትና፣ በክርክሩ ለመርታትና ትክክለኛ መሆናችሁን ለማሳወቅ የሚገፋፋችሁን ውስጣዊ ስሜት ለመቆጣጠር ሊረዳችሁ ይችላል።
‘በልጅነት ሚስትህ ደስ ይበልህ’
13 በጋብቻው ውስጥ ውጥረት የሰፈነው የትዳር ጓደኛሞቹ አንዳቸው ሌላውን በሚይዙበት መንገድ የተነሳ ቢሆንስ? መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፣ ደግነት በጎደለው መንገድ መነጋገር አመል ሆኖባቸው ይሆናል። (ምሳሌ 12:18) ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ይህ ዓይነቱ ልማድ በትዳር ውስጥ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ምሳሌ “ከጨቅጫቃና ከቍጡ ሚስት ጋር ከመኖር፣ በምድር በዳ መኖር ይሻላል” ይላል። (ምሳሌ 21:19) በእንደዚህ ዓይነት ትዳር ውስጥ ያለሽ ሚስት ከሆንሽ ‘ባለቤቴ አብሮኝ መሆን እንዲያስጠላው የሚያደርግ ባሕርይ አለኝ?’ ብለሽ ራስሽን ጠይቂ። መጽሐፍ ቅዱስ ለባሎች “ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው” የሚል ምክር ይዟል። (ቈላስይስ 3:19) ስለዚህ ባል ከሆንክ ‘ፍቅሬን የማልገልጽላት በመሆኔ ምክንያት ባለቤቴ ወደ ሌሎች ለመሄድ እንድትፈተን አደርጋታለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በእርግጥ የሥነ ምግባር ብልግና ለመፈጸም የሚያበቃ ምንም ሰበብ ሊኖር አይችልም። ያም ቢሆን ግን እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችል መሆኑ ችግሮችን በግልጽ ለመወያየት የሚያነሳሳ ጥሩ ምክንያት ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ራእይ እውን ሆነ
9 በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ የሚጋልብ ሥጋ ለባሽ ሳይሆን ኃያል ንጉሥ ነው። ደግሞም ፈረስ በመጋለብ ላይ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸ ሲሆን ፈረስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጦርነትን ያመለክታል። (ምሳሌ 21:31) ራእይ 6:2 “እነሆ፤ ነጭ ፈረስ ቆሞ ነበር፤ ተቀምጦበት የነበረውም ቀስት ይዞ ነበር፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እርሱም እንደ ድል አድራጊ ድል ለመንሣት ወጣ” ይላል። ከዚህ በተጨማሪ መዝሙራዊው ዳዊት ኢየሱስን በተመለከተ “እግዚአብሔር ብርቱ በትርህን ከጽዮን ወደ ውጭ ይሰዳል፤ አንተም በጠላቶችህ መካከል ሆነህ ትገዛለህ” ሲል ጽፏል።—መዝሙር 110:2
ከሐምሌ 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 22
ልጆችን ለማሳደግ የሚረዱ ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶች
ልጆቻችሁ ሲያድጉ አምላክን ለማገልገል ይመርጡ ይሆን?
7 ባለትዳሮች ከሆናችሁና ልጅ መውለድ የምትፈልጉ ከሆነ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ይሖዋ ውድ የሆነን ሕይወት በኃላፊነት ሊሰጠን የሚችል ትሑትና መንፈሳዊ አመለካከት ያለን ሰዎች ነን?’ (መዝ. 127:3, 4) ወላጆች ከሆናችሁ ደግሞ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ጠንክሮ የመሥራትን አስፈላጊነት ለልጆቼ እያስተማርኩ ነው?’ (መክ. 3:12, 13) ‘ልጆቼን በሰይጣን ዓለም ውስጥ ሊያጋጥማቸው ከሚችለው አካላዊና ሥነ ምግባራዊ አደጋ ለመጠበቅ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ?’ (ምሳሌ 22:3) ልጆቻችሁን ሊያጋጥሟቸው ከሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሁሉ ልትከልሏቸው አትችሉም። ይህ የማይቻል ነገር ነው። ሆኖም ከአምላክ ቃል ምክር ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በማስተማር በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ቀስ በቀስ ልታዘጋጇቸው ትችላላችሁ። (ምሳሌ 2:1-6ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ የቅርብ ዘመዳችሁ ይሖዋን ማገልገሉን ቢያቆም የአምላክን ቃል ተጠቅማችሁ ለይሖዋ ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት ለልጆቻችሁ አስተምሯቸው። (መዝ. 31:23) አሊያም ደግሞ የምትወዱትን ሰው በሞት ካጣችሁ ልጆቻችሁ የአምላክ ቃል ሐዘንን ለመቋቋምና ሰላም ለማግኘት የሚረዳው እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውሉ እርዷቸው።—2 ቆሮ. 1:3, 4፤ 2 ጢሞ. 3:16
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ አሠልጥኗቸው
17 ሥልጠናውን ገና ከልጅነታቸው ጀምሩ። ወላጆች ልጆቻቸውን ገና ከሕፃንነታቸው ማሠልጠን መጀመራቸው የተሻለ ነው። (ምሳሌ 22:6) ከጊዜ በኋላ የሐዋርያው ጳውሎስ የጉዞ አጋር የሆነውን የጢሞቴዎስን ሁኔታ ለማሰብ ሞክሩ። እናቱ ኤውንቄ እና አያቱ ሎይድ ጢሞቴዎስን ‘ከጨቅላነቱ’ ጀምሮ አሠልጥነውታል።—2 ጢሞ. 1:5፤ 3:15
18 በኮት ዲቩዋር የሚኖሩት ዦን ክሎድ እና ፒስ የተባሉ ሌላ ባልና ሚስት ደግሞ ስድስቱም ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱና እሱን የማገልገል ፍላጎት እንዲያድርባቸው አድርገው ማሳደግ ችለዋል። ስኬታማ እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው? የኤውንቄንና የሎይድን ምሳሌ መከተላቸው ነው። እነዚህ ባልና ሚስት “የአምላክን ቃል በልጆቻችን ልብ ውስጥ መቅረጽ የጀመርነው ከጨቅላነታቸው አንስቶ ማለትም ከተወለዱ ብዙም ሳይቆይ ነበር” ብለዋል።—ዘዳ. 6:6, 7
19 የይሖዋን ቃል በልጆቻችሁ ውስጥ ‘መቅረጽ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ‘መቅረጽ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ደግሞ ደጋግሞ በመናገር ማስተማርና ማስገንዘብ” የሚል መልእክት አለው። ይህን ለማድረግ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አዘውትረው ጊዜ ማሳለፍ አለባቸው። መመሪያዎችን ለልጆች ደጋግሞ መናገር አንዳንድ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ወላጆች፣ ልጆቻቸው የአምላክን ቃል እንዲያስተውሉና ተግባራዊ እንዲያደርጉ መርዳት የሚችሉት በዚህ መንገድ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።
ወላጆች ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ
እርግጥ ልጆች የልጅነት ጠባይ እንደሚያሳዩ አይካድም፤ እንዲያውም አንዳንዶች አስቸጋሪ ብሎም ዓመጸኛ ሊሆኑ ይችላሉ። (ዘፍጥረት 8:21) በዚህ ጊዜ ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል፤ የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያርቅለታል” ይላል። (ምሳሌ 22:15) አንዳንዶች ይህን የጭካኔ ተግባር አድርገው በመቁጠር ጊዜ እንዳለፈበት ይናገራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ኃይለ ቃል መናገርንም ሆነ መደብደብን ይቃወማል። ይሁንና “በትር” የሚለው ቃል አንዳንድ ጊዜ ቃል በቃል ሊሠራ ይችላል፤ ይህም አንድ ወላጅ ለልጁ ዘላቂ ደኅንነት በማሰብ በፍቅር ጠበቅ ያለ ተግሣጽ የመስጠት ሥልጣን እንዳለው የሚያሳይ ነው።—ዕብራውያን 12:7-11
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ባገኛችኋቸው መብቶች ተደሰቱ
11 እኛም በተመሳሳይ በይሖዋ አገልግሎት በተሰጠን በማንኛውም ሥራ ላይ ትኩረታችንን ሙሉ በሙሉ በማሳረፍ ደስታችንን መጨመር እንችላለን። በስብከቱ ሥራ ‘በእጅጉ ተጠመድ’፤ እንዲሁም በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ተሳትፎ አድርግ። (ሥራ 18:5፤ ዕብ. 10:24, 25) በስብሰባዎች ላይ የሚያንጹ ሐሳቦች መስጠት እንድትችል በሚገባ ተዘጋጅ። በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ የተሰጠህን ማንኛውንም የተማሪ ክፍል በቁም ነገር ተመልከተው። በጉባኤ ውስጥ አንድ ሥራ ከተሰጠህ ሥራህን በጊዜው አከናውን፤ እንዲሁም እምነት የሚጣልብህ ሁን። በጉባኤ ውስጥ የተሰጠህን የትኛውንም ሥራ ሳትንቅ ጊዜ ሰጥተህ አከናውን። በተመደብክበት ሥራ ችሎታህን ለማሻሻል ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 22:29) በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና በተሰጡህ ኃላፊነቶች ላይ ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ እንዲያርፍ ካደረግህ እድገትህ ይፋጠናል፤ ደስታህም ይጨምራል። (ገላ. 6:4) በተጨማሪም አንተ ለማግኘት የምትመኘውን መብት ሌሎች ሰዎች ቢያገኙ ከእነሱ ጋር አብረህ መደሰት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል።—ሮም 12:15፤ ገላ. 5:26
ከሐምሌ 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 23
ከአልኮል መጠጥ ጋር የተያያዙ ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶች
የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ
5 አንድ ሰው የስካር ምልክት እንዳይታይበት እየተጠነቀቀ የመጠጣት ልማድ ቢኖረውስ? አንዳንዶች ብዙ ጠጥተውም እንኳ የስካር ምልክት ላይታይባቸው ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ልማድ ራስን ማሞኘት ነው። (ኤርምያስ 17:9) አንድ ሰው እንዲህ ያለ ልማድ ካለው ይዋል ይደር እንጂ የአልኮል ጥገኛና ‘ሱሰኛ’ መሆኑ አይቀርም። (ቲቶ 2:3) ካሮላይን ናፕ የተባሉ ጸሐፊ የአልኮል ሱሰኛ ወደመሆን የሚያደርሰውን ሒደት በተመለከተ ሲናገሩ “አንድ ሰው የአልኮል ሱሰኛ የሚሆነው ቀስ በቀስና ምንም ሳይታወቀው ነው” ብለዋል። በእርግጥም የአልኮል መጠጥ አደገኛ ወጥመድ ሊሆን ይችላል!
6 በተጨማሪም ኢየሱስ “በመብልና በመጠጥ ብዛት በስካርም በመባከንና ስለ ዓለማዊ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ። አለበለዚያ ያ ቀን እንደ ወጥመድ በድንገት ይመጣባችኋል። ምክንያቱም ያ ቀን በምድር ላይ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ በድንገት ያጠምዳቸዋል” ሲል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ በል። (ሉቃስ 21:34, 35 የ1980 ትርጉም) አንድ ሰው ባይሰክርም እንኳ የአልኮል መጠጥ በመጠጣቱ ምክንያት በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሊደብተውና ሊጫጫነው ይችላል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ላይ እያለ የይሖዋ ቀን ቢደርስበትስ?
አምላክ ስለ አልኮል መጠጥ ምን አመለካከት አለው?
አልኮል ከመጠን በላይ መጠጣት ሰዎች አንደበታቸውንም ሆነ ድርጊታቸውን መቆጣጠር እንዲያቅታቸው ሊያደርግ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ዋይታ የማን ነው? . . . ጠብ የማን ነው? ብሶትስ የማን ነው? . . . የወይን ጠጅ በመጠጣት ጊዜያቸውን ለሚያባክኑ ነው፤ እየዞሩ ድብልቅ የወይን ጠጅ ለሚቀማምሱ ሰዎች ነው።” (ምሳሌ 23:29, 30) ከመጠን በላይ መጠጣት ‘በባሕር ላይ እንደተኛህና በመርከብ ምሰሶ ጫፍ ላይ የተጋደምህ እንዲመስልህ’ ሊያደርግ ይችላል። (ምሳሌ 23:34) ከመጠን በላይ የጠጣ አንድ ሰው ከእንቅልፉ ነቅቶ “በእርግጥ ሳልደበደብ አልቀረሁም፤ ነገር ግን መደብደቤ ትዝ አይለኝም” ሊል ይችላል።—ምሳሌ 23:35 የ1980 ትርጉም
ከመጠን በላይ መጠጣት አካላዊ ጤንነትን ሊጎዳ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “[አልኮል] በመጨረሻው እንደ እባብ ይነድፋል፤ እንደ እፉኝትም መርዙን ይረጫል” ይላል። (ምሳሌ 23:32) የሕክምናው ሳይንስ ጥበብ የተንጸባረቀበት ይህ ጥንታዊ አባባል እውነት መሆኑን አረጋግጧል። አልኮል በብዛት መጠጣት ገዳይ የሆኑ መርዞች በሰውነት ውስጥ እንዲከማቹ ሊያደርግ ይችላል፤ ይህ ደግሞ የተለያዩ የካንሰርና የጉበት በሽታዎች፣ የቆሽት መታወክ፣ በስኳር ሕመምተኞች ላይ የስኳር መጠን መቀነስ፣ የደም መርጋት፣ የልብ በሽታ እንዲሁም በፅንስ ላይ የአእምሮ ወይም የአካል ችግር ሊያስከትል ይችላል። እነዚህ አልኮል ከሚያስከትላቸው ብዙ ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። አንድ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ እንኳ ከመጠን በላይ መጠጣቱ ራሱን እንዲስት ሊያደርገው ወይም ለሕልፈተ ሕይወት ሊዳርገው ይችላል። ይሁን እንጂ በሕክምና መጻሕፍት ላይ ያልተጠቀሰ ቢሆንም ከመጠን በላይ መጠጣት የሚያስከትለው አንድ ሌላ ከባድ መዘዝ አለ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ለምሳሌ ከመጠን በላይ መፈወር የሆዳምነት ምልክት ሊሆን ቢችልም ወፍራም ሰው ሁሉ ግን ሆዳም ነው ማለት አይቻልም። አንድ ሰው በጣም የወፈረው በሕመም ምክንያት ሊሆን ይችላል። ውፍረት ከቤተሰብ ሊወረስም ይችላል። ከዚህም በላይ ከመጠን በላይ መወፈር በሰውነታችን ላይ የሚታይ ነገር ሲሆን ሆዳምነት ግን ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል። ከመጠን በላይ መወፈር በሰውነት ውስጥ ብዙ ስብ በመከማቸቱ የተነሳ የሚከሰት ሲሆን ሆዳምነት ግን ‘አልጠግብ ባይነት ወይም ስግብግብነት’ ነው። በመሆኑም አንድ ሰው ሆዳም መሆኑ የሚታወቀው በክብደቱ ሳይሆን ለምግብ ባለው አመለካከት ነው። አንድ ሰው መካከለኛ ሰውነት እያለው እንዲያውም ቀጭን ሆኖም እንኳ ሆዳም ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም መጠነኛ ክብደት ወይም የተስተካከለ የሰውነት ቅርጽ የሚባለው ከቦታ ቦታ ይለያያል።
ከሐምሌ 28–ነሐሴ 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 24
ለመከራ ወቅት ራሳችሁን አጠናክሩ
“ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ”
15 የአምላክን ቃል አጥና እንዲሁም አሰላስልበት። ሥር የሰደደ ዛፍ ጸንቶ እንደሚቆም ሁሉ እኛም እምነታችን በአምላክ ቃል ላይ ሥር የሰደደ ከሆነ ጸንተን መቆም እንችላለን። አንድ ዛፍ እያደገ ሲሄድ ይበልጥ ሥር እየሰደደ ይሄዳል። ስናጠናና ስናሰላስል እምነታችን ይጠናከራል፤ እንዲሁም የአምላክ መንገዶች ከሁሉ የተሻሉ እንደሆኑ ይበልጥ እርግጠኛ እንሆናለን። (ቆላ. 2:6, 7) ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ከይሖዋ ትምህርት፣ መመሪያና ጥበቃ እንዴት እንደተጠቀሙ ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ ሕዝቅኤል በራእይ አንድ ቤተ መቅደስ ተመልክቶ ነበር፤ መልአኩ እያንዳንዱን ነገር ሲለካ ሕዝቅኤል በትኩረት ተመልክቷል። ራእዩ የሕዝቅኤልን እምነት አጠናክሮለታል፤ ለእኛም ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣውን መሥፈርት እንዴት መጠበቅ እንደምንችል ጠቃሚ ትምህርት ይዞልናል። (ሕዝ. 40:1-4፤ 43:10-12) በእርግጥም ጊዜ መድበን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ ነገሮች ስናጠናና ስናሰላስልባቸው እንጠቀማለን።
በችግር ጊዜ ደስታን ጠብቆ መኖር
12 ምሳሌ 24:10 “በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ [“ተስፋ ብትቆርጥ፣” NW] ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!” ይላል። አንድ ሌላ ምሳሌ ደግሞ “የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይሰብራል” ይላል። (ምሳሌ 15:13) አንዳንድ ክርስቲያኖች በጣም ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበባቸውንም ሆነ በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰላቸውን እስከ ማቆም ደርሰዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች በዘልማድ የሚጸልዩ ከመሆኑም ሌላ ራሳቸውን ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ሊያገሉ ይችላሉ። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ሐዘን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።—ምሳሌ 18:1, 14
13 በሌላ በኩል ግን ብሩህ አመለካከት መያዝ ደስታ በሚያስገኙልን ነገሮች ላይ ትኩረት እንድናደርግ ይረዳናል። ዳዊት “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል” በማለት ጽፏል። (መዝ. 40:8 NW) በሕይወታችን ውስጥ አሳዛኝ ነገሮች ሲያጋጥሙን ፈጽሞ ልናደርገው የማይገባን ነገር ቢኖር ከአምልኮታችን ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ማቋረጥ ነው። እንዲያውም ሐዘንን ለመቋቋም መፍትሔው ደስታ ሊያስገኙ በሚችሉ እንቅስቃሴዎች መጠመድ ነው። ይሖዋ ትኩረት ሰጥተን ቃሉን በየዕለቱ ካነበብን ደስታና እርካታ እንደምናገኝ ነግሮናል። (መዝ. 1:1, 2፤ ያዕ. 1:25) ከቅዱሳን መጻሕፍትም ሆነ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች “ደስ የሚያሰኝ ቃል” እናገኛለን፤ ይህ ደግሞ የሚያበረታታን ከመሆኑም በላይ ልባችን በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል።—ምሳሌ 12:25፤ 16:24
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ምሳሌ 24:16 “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ መልሶ ይነሳልና፤ ክፉ ሰው ግን በሚደርስበት መከራ ይሰናከላል” ይላል። ይህ ጥቅስ አንድ ሰው በተደጋጋሚ በኃጢአት ቢወድቅም አምላክ ይቅር እንደሚለው የሚጠቁም ነው?
ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለዚህ ጉዳይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ጻድቅ . . . ቢወድቅ” ሲል መከራ ወይም ችግር በተደጋጋሚ ቢያጋጥመው እንደማለት ሲሆን “ይነሳል” የሚለው ደግሞ መከራውን እንደሚወጣው የሚያሳይ ነው።
ከዚህ አንጻር ምሳሌ 24:16 ‘መውደቅ’ ሲል የሚያመለክተው፣ አንድ ሰው በኃጢአት መውደቁን ሳይሆን ከባድ ችግሮች ወይም መከራዎች በተደጋጋሚ የደረሱበት መሆኑን ነው። በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ጻድቅ ሰው፣ የጤና እክል ወይም ሌሎች ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። አልፎ ተርፎም መንግሥት ከባድ ስደት ሊያደርስበት ይችላል። ሆኖም አምላክ እንደሚደግፈውና ችግሩን ለመቋቋም ብሎም ለመወጣት እንደሚረዳው መተማመን ይችላል። አንተስ የአምላክ አገልጋዮች፣ የኋላ ኋላ ነገሮች መልካም እንደሚሆኑላቸው ብዙ ጊዜ አልተመለከትክም? ይህ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያቱን ሲነግረን “ይሖዋ ሊወድቁ የተቃረቡትን ሁሉ ይደግፋል፤ ያጎነበሱትንም ሁሉ ቀና ያደርጋል” ይላል።—መዝ. 41:1-3፤ 145:14-19
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በጥንት ዘመን አንድ ሰው የራሱን ‘ቤት ለመሥራት’ ማለትም ሚስት አግብቶ ቤተሰብ ለመመሥረት ከፈለገ ‘ሚስቴን እንዲሁም ልጆች ከወለድን እነሱን ለመንከባከብና ለማስተዳደር ዝግጁ ነኝ?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ያስፈልገው ነበር። ቤተሰብ ከመመሥረቱ በፊት እርሻውን ወይም ሰብሉን በመንከባከብ በውጭ መሥራት ነበረበት። በመሆኑም የ1980 ትርጉም ይህንን ጥቅስ እንዲህ በማለት በግልጽ አስቀምጦታል፦ “በመጀመሪያ በርስትህ ላይ ለኑሮህ የሚያስፈልግህን ሁሉ አደራጅ፤ ከዚያ በኋላ ቤት መሥራትና ትዳር ማቋቋም ትችላለህ።” ታዲያ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜም ይሠራል?
አዎን። ለማግባት የሚፈልግ ሰው ጋብቻው የሚያስከትልበትን ኃላፊነት ለመሸከም በሚገባ መዘጋጀት አለበት። አካላዊ ሁኔታው የሚፈቅድለት ከሆነ መሥራት ይኖርበታል። እርግጥ ነው፣ አንድ ወንድ ቤተሰቡን ለመንከባከብ ጠንክሮ መሥራት አለበት ሲባል ቁሳዊ ነገሮችን በማሟላት ብቻ ይወሰናል ማለት አይደለም። የቤተሰቡን አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች የማያሟላ ሰው እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ እንደሆነ የአምላክ ቃል ይገልጻል! (1 ጢሞ. 5:8) በመሆኑም አንድ ወጣት ለማግባትና ቤተሰብ ለመመሥረት በሚዘጋጅበት ወቅት ራሱን እንዲህ እያለ መጠየቅ ይኖርበታል፦ ‘በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ለማሟላት ዝግጁ ነኝ? በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ ቤተሰቤን ለመምራትስ ዝግጁ ነኝ? ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ኃላፊነቴን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ?’ የአምላክ ቃል ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን እነዚህን ኃላፊነቶች የመወጣትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል።—ዘዳ. 6:6-8፤ ኤፌ. 6:4
በመሆኑም ለማግባት የሚፈልግ አንድ ወጣት በምሳሌ 24:27 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በጥንቃቄ ሊያስብበት ይገባል። በተመሳሳይም አንዲት ወጣት ለማግባት ስታስብ ሚስትና እናት መሆን የሚያስከትሏቸውን ኃላፊነቶች ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ራሷን መጠየቅ ይኖርባታል። ለማግባት የሚያስቡ ሰዎች ወይም በቅርቡ የተጋቡ ባልና ሚስትም ልጆች ስለመውለድ ሲያስቡ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ራሳቸውን ሊጠይቁ ይችላሉ። (ሉቃስ 14:28) የአምላክ ሕዝቦች በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን እንዲህ ያለውን መመሪያ መከተላቸው ብዙ ችግሮችን ማስወገድ እንዲችሉ የሚረዳቸው ከመሆኑም ሌላ አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት ለመምራት ያስችላቸዋል።
ከነሐሴ 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 25
ከአነጋገር ጋር የተያያዙ ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶች
አንደበታችሁ ያለውን ኃይል ለመልካም ነገር ተጠቀሙበት
6 ምሳሌ 25:11 ለመናገር ተገቢውን ጊዜ የመምረጥን አስፈላጊነት ያጎላል፤ ጥቅሱ “በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም ነው” ይላል። የወርቅ ፖም በራሱ የሚያምር ነገር ነው። ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ ሲቀመጥ ደግሞ ውበቱ ይበልጥ ደምቆ ይታያል። በተመሳሳይም ተስማሚ የሆነውን ጊዜ መርጠን መናገራችን፣ የምንናገረው ነገር ይበልጥ ማራኪና ውጤታማ እንዲሆን ያደርጋል። እንዴት?
7 የምንናገረው ነገር ለሚሰማን ሰው በጣም አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ መቼ መናገር እንዳለብን ካላወቅን ንግግራችን ዋጋ ሊያጣ ይችላል። (ምሳሌ 15:23ን አንብብ።) መጋቢት 2011 በጃፓን ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በዚያ ወቅት የምሥራቃዊ ጃፓን የተወሰነ ክፍል በምድር መናወጥና በሱናሚ የተመታ ሲሆን አንዳንድ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ወደሙ። ከ15,000 የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ልክ እንደ ሌሎቹ ሰዎች በአደጋው የተጠቁ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው ያዘኑትን ለማጽናናት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመዋል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች የቡድሂዝምን እምነት በጥብቅ የሚከተሉ ከመሆናቸውም ሌላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አያውቁም፤ አሊያም እውቀታቸው በጣም ውስን ነው። ወንድሞቻችን፣ ለአካባቢው ሰዎች ስለ ትንሣኤ ተስፋ ለመናገር ጥሩ የሆነው ጊዜ ሱናሚው የተከሰተበት ወቅት እንዳልሆነ አስተዋሉ። በመሆኑም ወንድሞች በንግግር ስጦታቸው ተጠቅመው ሰዎችን በማጽናናትና እንዲህ ያለው መከራ በንጹሐን ሰዎች ላይ የሚደርሰው ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ በማብራራት ላይ ትኩረት አደረጉ።
አንደበታችሁ ያለውን ኃይል ለመልካም ነገር ተጠቀሙበት
15 የምንናገርበትን መንገድ ከምንናገረው ነገር ባልተናነሰ ልናስብበት ይገባል። ኢየሱስ ባደገበት በናዝሬት በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ባስተማረበት ወቅት ሕዝቡ “ከአፉ በሚወጡት የሚማርኩ ቃላት” ተደንቀዋል። (ሉቃስ 4:22) የሚማርክ ወይም ለዛ ያለው ንግግር ልብን ደስ ያሰኛል፤ እንዲህ ያለው አነጋገር፣ የምንናገረውን ነገር ኃይል ያሳጣዋል ብለን መስጋት አይኖርብንም። እንዲያውም ማራኪ የሆኑ ቃላት ንግግራችን ይበልጥ አሳማኝ እንዲሆን ያደርጋሉ። (ምሳሌ 25:15) እኛም ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በመከተል ንግግራችን ደግነት፣ አክብሮትና ለሌሎች ስሜት አሳቢነት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። ኢየሱስ ሕዝቡ እሱን ለማዳመጥ ሲሉ ያደረጉትን ጥረት ሲመለከት በጣም ስላዘነላቸው ‘ብዙ ነገር አስተምሯቸዋል።’ (ማር. 6:34) ኢየሱስ ሌሎች ቢሰድቡትም እንኳ ኃይለ ቃል አልተናገረም።—1 ጴጥ. 2:23
16 በጣም የምንቀርበውን ሰው በለሰለሰ አንደበትና ዘዴኛነት በተሞላበት መንገድ ማነጋገር ሊከብደን ይችላል። እንዲያውም የፈለግነውን የመናገር ነፃነት እንዳለን ይሰማን ይሆናል። ለምሳሌ ከቤተሰባችን አባል ወይም በጉባኤ ውስጥ ከምንቀርበው ጓደኛችን ጋር ስናወራ እንዲህ እናደርግ ይሆናል። ይሁንና ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ስለሚቀርባቸው እነሱን በኃይለ ቃል ለመናገር ነፃነት እንዳለው ተሰምቶት ነበር? በፍጹም! የቅርብ ተከታዮቹ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲከራከሩ ኢየሱስ አንድን ትንሽ ልጅ እንደ ምሳሌ በመጠቀም ደግነት በተሞላበት መንገድ እርማት ሰጥቷቸዋል። (ማር. 9:33-37) ሽማግሌዎች “በገርነት መንፈስ” ምክር በመስጠት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይችላሉ።—ገላ. 6:1
ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ማነቃቃት ያለባችሁ እንዴት ነው?
8 አምላክን በማገልገል ረገድ ሁላችንም ምሳሌ በመሆን እርስ በርስ መነቃቃት እንችላለን። ኢየሱስ አድማጮቹን አነቃቅቷል። ክርስቲያናዊ አገልግሎትን ይወድ ነበር፤ አገልግሎቱንም ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል። አገልግሎቱ ለእርሱ ልክ እንደ መብል እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:34፤ ሮሜ 11:13) እንዲህ ዓይነቱ የጋለ ስሜት ከአንዱ ወደ ሌላው ሊጋባ የሚችል ነው። አንተም በተመሳሳይ በአገልግሎቱ የምታገኘው ደስታ ለሌሎች እንዲታይ ልታደርግ ትችላለህን? በአነጋገርህ ላይ የጉራ መንፈስ እንዳይንጸባረቅ እየተጠነቀቅህ ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎችህን በጉባኤው ውስጥ ለሚገኙት ለሌሎች አካፍላቸው። ሌሎች ከአንተ ጋር እንዲያገለግሉ ስትጋብዛቸው ስለ ታላቁ ፈጣሪያችን ስለ ይሖዋ ለሌሎች በመናገር ረገድ እውነተኛ ደስታ እንዲያገኙ ለመርዳት ሞክር።—ምሳሌ 25:25
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ስሜታዊ ጤንነት
ምን ማለት ነው? ስሜታችንን የመቆጣጠር ችሎታ ካዳበርን በእጅጉ እንጠቀማለን። ሁላችንም አንዳንድ ጊዜ እንደምንቆጣ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ቁጣችንን ካልተቆጣጠርነው የከፋ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። አብዛኞቹ ሰዎች በተበሳጩበት ሰዓት በተናገሩት ወይም ባደረጉት ነገር የተነሳ በኋላ ላይ እንደሚቆጩ ተመራማሪዎች ገልጸዋል።
ከነሐሴ 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 26
‘ከሞኝ ሰው’ ራቁ
it-2 729 አን. 6
ዝናብ
ወቅቶች። በተስፋይቱ ምድር የነበሩት ሁለት ዋና ዋና ወቅቶች በጋ እና ክረምት ናቸው፤ እነሱም ደረቅ ወቅትና ዝናባማ ወቅት ተብለው ሊገለጹ ይችላሉ። (መዝ 32:4፤ መኃ 2:11) ከሚያዝያ አጋማሽ አንስቶ እስከ ጥቅምት አጋማሽ ድረስ ጨርሶ ዝናብ የለም ሊባል ይችላል። የመከር ሥራ በሚከናወንበት በዚህ ጊዜ ውስጥ ዝናብ የተለመደ ነገር አይደለም። ምሳሌ 26:1 በመከር ወቅት ዝናብ መዝነቡ እንግዳ ነገር ተደርጎ እንደሚቆጠር ያሳያል። (ከ1ሳሙ 12:17-19 ጋር አወዳድር።) በዝናቡ ወቅትም ቢሆን ሁልጊዜ አይዘንብም፤ አንዳንዶቹ ቀናት ፀሐያማ ናቸው። ይህ ወቅት የቅዝቃዜ ወቅትም ስለሆነ በዝናብ መመታት ለብርድ ያጋልጣል። (ዕዝራ 10:9, 13) በመሆኑም አመቺ የሆነ መጠለያ ያስፈልጋል።—ኢሳ 4:6፤ 25:4፤ 32:2፤ ኢዮብ 24:8
w87 10/1 19 አን. 12
ተግሣጽ ሰላማዊ ፍሬ ያፈራል
12 ከአንዳንድ ሰዎች ጋር በተያያዘ ይበልጥ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል፤ ምሳሌ 26:3 እንደሚለው “አለንጋ ለፈረስ፣ ልጓም ለአህያ፣ በትርም ለሞኞች ጀርባ ነው።” ይሖዋ ሕዝቦቹ የሆኑት እስራኤላውያን በራሳቸው ላይ ባመጡት መከራ ተቀጥተው እንዲመለሱ ያደረገበት ጊዜ አለ፦ “በአምላክ ቃል ላይ ዓምፀዋልና፤ የልዑሉን አምላክ ምክር ንቀዋል። ስለዚህ በደረሰባቸው መከራ ልባቸው እንዲለሰልስ አደረገ፤ ተሰናከሉ፤ የሚረዳቸውም አንዳች ሰው አልነበረም። በተጨነቁ ጊዜ እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ተጣሩ፤ እሱም ከደረሰባቸው መከራ አዳናቸው።” (መዝ 107:11-13) ሆኖም አንዳንድ ሞኞች ልባቸውን ከማደንደናቸው የተነሳ የትኛውም ተግሣጽ ሊፈውሳቸው አይችልም፦ “ብዙ ጊዜ ተወቅሶ አንገቱን ያደነደነ ሰው፣ ሊፈወስ በማይችል ሁኔታ በድንገት ይሰበራል።”—ምሳሌ 29:1
it-2 191 አን. 4
ሽባ
ምሳሌያዊ አገላለጽ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “አንድን ጉዳይ ለሞኝ በአደራ የሚሰጥ እግሩን ከሚያሽመደምድና [በሌላ አባባል እግሩን ሽባ ከሚያደርግና] ራሱን ከሚጎዳ ሰው ተለይቶ አይታይም።” በእርግጥም አንድን ሥራ እንዲሠራለት ሞኝን የሚቀጥር ሰው ሽባ የመሆን ያህል የራሱን ጥቅም ይጎዳል። ያቀደው ሥራ መክሸፉ አይቀርም፤ ይህም ጉዳት ያመጣበታል።—ምሳሌ 26:6
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ገር በመሆን ጥንካሬያችሁን አሳዩ
18 እርግጥ ነው፣ አሳማኝ ማስረጃ ብናቀርብም እንኳ አንዳንዶቹ አድማጮች ላይቀበሉን ይችላሉ። ያም ቢሆን በዘዴና በገርነት መናገራችን ጠቃሚ ነው። (ቆላስይስ 4:6ን አንብብ።) ስለ እምነታችን መናገር ኳስ ከመወርወር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ኳሱን ቀስ ብለን ልናቀብል ወይም በኃይል ልንወረውር እንችላለን። ኳሱን ቀስ አድርገን ከወረወርነው ሌላኛው ተጫዋች ኳሱን ተቀብሎ ጨዋታውን የመቀጠሉ አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። በተመሳሳይም በዘዴና በገርነት የምንናገር ከሆነ ሰዎች እኛን ለማዳመጥና ውይይቱን ለመቀጠል ይበልጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ፍላጎቱ በክርክር ማሸነፍ ወይም በእምነታችን ላይ ማሾፍ ብቻ ከሆነ ለግለሰቡ ምላሽ የመስጠት ግዴታ የለብንም። (ምሳሌ 26:4) ይሁንና እንዲህ የሚያደርጉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። አንዳንዶች ምናልባትም ብዙዎች ለመስማት ፈቃደኛ መሆናቸው አይቀርም።
ከነሐሴ 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 27
እውነተኛ ጓደኞች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?
ይሖዋ ትሑት አገልጋዮቹን ከፍ አድርጎ ይመለከታል
12 ትሑት ሰው ምክር ሲሰጠው በደስታ ይቀበላል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተሃል እንበል። ከተለያዩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ስትጫወት ከቆየህ በኋላ አንድ ወንድም ለብቻህ ወስዶ ጥርስህ ላይ የሆነ ነገር ስላለ እንድታጸዳው ይነግርሃል። ሁኔታው ሊያሳፍርህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም ወንድም እንዲህ ብሎ ስለነገረህ አመስጋኝ አትሆንም? እንዲያውም ‘ምነው የሆነ ሰው ቀደም ብሎ በነገረኝ ኖሮ!’ ብለህ ልታስብ ትችላለህ። በተመሳሳይም አንድ የእምነት ባልንጀራችን ድፍረት በማሳየት አስፈላጊውን ምክር ሲሰጠን ትሑት በመሆን ምክሩን በአመስጋኝነት መቀበል ይኖርብናል። እንዲህ ያለ ምክር የሰጠንን ሰው እንደ ወዳጃችን እንጂ እንደ ጠላታችን አናየውም።—ምሳሌ 27:5, 6ን አንብብ፤ ገላ. 4:16
it-2 491 አን. 3
ጎረቤት
ይሁንና የምሳሌ መጽሐፍ በወዳጆቻችን እንድንተማመን እንዲሁም በምንቸገርበት ጊዜ እነሱን እንድንጠራ ይመክረናል፦ “መከራ ባጋጠመህ ቀን የራስህንም ሆነ የአባትህን ወዳጅ ትተህ ወደ ገዛ ወንድምህ ቤት አትግባ፤ ሩቅ ቦታ ካለ ወንድም ይልቅ በቅርብ ያለ ጎረቤት [ሻኬን] ይሻላል።” (ምሳሌ 27:10) እዚህ ላይ ጸሐፊው የቤተሰባችን የቅርብ ወዳጅ የሆነን ሰው ከፍ አድርገን መመልከት እንዲሁም እርዳታውን መጠየቅ እንዳለብን እየተናገረ ይመስላል፤ እንደ ወንድም ያለ የቅርብ ዘመድ እንኳ የሚኖረው ሩቅ ቦታ ከሆነ ከእሱ ይልቅ የቤተሰባችንን ወዳጅ እርዳታ መጠየቃችን ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ወንድማችን የቤተሰባችንን ወዳጅ ያህል እኛን ለመርዳት ዝግጁ ላይሆን ወይም ሁኔታው ላይፈቅድለት ይችላል።
ወጣቶች—የወደፊት ሕይወታችሁ ምን ይመስል ይሆን?
7 ኢዮዓስ ካደረገው መጥፎ ውሳኔ የምናገኘው አንዱ ትምህርት፣ ይሖዋን የሚወዱና እሱን ማስደሰት የሚፈልጉ ጓደኞችን መምረጥ እንዳለብን ነው። እንዲህ ያሉ ጓደኞች በጎ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። ጓደኛ የምናደርገው የግድ እኩዮቻችንን መሆን የለበትም። ኢዮዓስ ከጓደኛው ከዮዳሄ በዕድሜ በጣም ያንስ እንደነበር አስታውስ። ጓደኛ አድርገህ ከምትመርጣቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት እንዳጠናክር ይረዱኛል? በአምላክ መሥፈርቶች እንድመራ ያበረታቱኛል? ስለ ይሖዋና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት እውነቶች ያወራሉ? ለአምላክ መሥፈርቶች አክብሮት ያሳያሉ? የሚነግሩኝ መስማት የምፈልገውን ነገር ብቻ ነው ወይስ ትክክል ያልሆነ ነገር ሳደርግ በድፍረት እርማት ይሰጡኛል?’ (ምሳሌ 27:5, 6, 17) እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ጓደኞችህ ይሖዋን የማይወዱ ከሆነ ለአንተም አይበጁህም። ይሖዋን የሚወዱ ጓደኞች ካሉህ ግን አጥብቀህ ያዛቸው፤ ይጠቅሙሃል!—ምሳሌ 13:20
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የምሳሌ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
27:21፦ የሚቀርብልን ምስጋና ማንነታችን ግልጽ ሆኖ እንዲታይ ሊያደርግ ይችላል። ስንመሰገን ምሥጋናውን ያገኘነው በራሳችን ጥረት ሳይሆን በይሖዋ እርዳታ መሆኑን በማመን እርሱን ይበልጥ ለማገልገል የምንነሳሳ ከሆነ ትሑት መሆናችን ይታያል። ሆኖም ምሥጋና ሲቀርብልን ከሌሎች እንደበለጥን ሆኖ የሚሰማን ከሆነ ትሕትና እንደሚጎድለን ይጠቁማል።
ከነሐሴ 25-31
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 28
በክፉ ሰውና በጻድቅ ሰው መካከል ያሉት ልዩነቶች
ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ትከተላለህን?
“ጻድቃን . . . እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራሉ።” (ምሳሌ 28:1) ምንም ዓይነት አደጋ ከፊታቸው ቢደቀንም በይሖዋ አገልግሎት በድፍረት ወደፊት ይገፋሉ፤ እምነት አላቸው፤ በአምላክ ቃል ላይም ትምክህት ጥለው ይመሩበታል።
it-2 1139 አን. 3
ማስተዋል
ከምንጩ ዘወር የሚሉ ሰዎች። ወደ ኃጢአት ዘወር የሚል ሰው ውሳኔ በሚያደርግበትና ዕቅድ በሚያወጣበት ጊዜ አምላክን ከግምት ማስገባቱን ያቆማል። (ኢዮብ 34:27) እንዲህ ያለው ሰው ልቡ እንዲያሳውረው ስለሚፈቅድ ድርጊቱ ምን ያህል ስህተት እንደሆነ አይገነዘብም፤ እንዲሁም ማስተዋሉን ያጣል። (መዝ 36:1-4) አምላክን አመልካለሁ ቢልም የሰዎችን መሥፈርት ከአምላክ ያስበልጣል፤ እንዲያውም በዚያ መመራት ይመርጣል። (ኢሳ 29:13, 14) ልቅ ምግባሩን እንደ “ጨዋታ” በመቁጠር አቅልሎ ይመለከተዋል (ምሳሌ 10:23) እንዲሁም አስተሳሰቡ ከመበላሸቱ፣ ከመሞኘቱና ማመዛዘን ከማጣቱ የተነሳ የማይታየው አምላክ ማስተዋል የሌለው ይመስል ኃጢአቱን እንደማያይበት ወይም እንደማያውቅበት እስከማሰብ ይደርሳል። (መዝ 94:4-10፤ ኢሳ 29:15, 16፤ ኤር 10:21) በሚከተለው ጎዳናና በምግባሩ በተዘዋዋሪ መንገድ “ይሖዋ የለም” ይላል (መዝ 14:1-3) እንዲሁም እሱን ከግምት አያስገባም። አምላክ ባወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለማይመራ ነገሮችን በትክክል ማመዛዘን፣ ጉዳዩን አጥርቶ ማየት፣ ሁኔታውን በአግባቡ መገምገምና ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረስ አይችልም።—ምሳሌ 28:5
it-1 1211 አን. 4
ንጹሕ አቋም
አንድ ሰው በዚህ መልኩ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መመላለስ የሚችለው በራሱ ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬ ሳይሆን በይሖዋና እሱ ባለው የማዳን ኃይል ላይ ጥልቅ እምነት በማሳደር ነው። (መዝ 25:21) አምላክ በንጹሕ አቋም ለሚመላለሱት “ጋሻ” እና “መሸሸጊያ” በመሆን መንገዳቸውን እንደሚጠብቅላቸው ቃል ገብቷል። (ምሳሌ 2:6-8፤ 10:29፤ መዝ 41:12) ምንጊዜም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ጥረት ስለሚያደርጉ ሕይወታቸው የተረጋጋ ይሆናል፤ እንዲሁም ቀና መንገድ ተከትለው ወደ ግባቸው መድረስ ይችላሉ። (መዝ 26:1-3፤ ምሳሌ 11:5፤ 28:18) ኢዮብ ግራ በመጋባት እንደገለጸው ነቀፋ የሌለባቸው ሰዎች በክፉዎች አገዛዝ የተነሳ ለመከራ ሊዳረጉና ከክፉዎች ጋር አብረው ሊሞቱ ቢችሉም ይሖዋ ነቀፋ የሌለባቸውን ሰዎች የሕይወት ጎዳና እንደሚያውቅ፣ እንዲህ ያሉት ሰዎች ርስታቸው ለዘላለም እንደሚኖር፣ የወደፊት ሕይወታቸው ሰላማዊ እንደሚሆን እንዲሁም መልካም ነገርን እንደሚወርሱ ቃል ገብቷል። (ኢዮብ 9:20-22፤ መዝ 37:18, 19, 37፤ 84:11፤ ምሳሌ 28:10) በኢዮብ ሁኔታ እንደታየው አንድ ሰው እውነተኛ ዋጋ እንዲኖረውና አክብሮት እንዲገባው የሚያደርገው ሀብቱ ሳይሆን ንጹሕ አቋም ይዞ መመላለሱ ነው። (ምሳሌ 19:1፤ 28:6) እንዲህ ያለ ወላጅ ያላቸው ልጆች ደስተኞች ናቸው (ምሳሌ 20:7)፤ አባታቸው የመራው የሕይወት ጎዳና ግሩም ውርሻ ይሆንላቸዋል፤ ካተረፈው መልካም ስምና አክብሮት ተካፋይ ይሆናሉ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
መንፈሳዊ የልብ ድካም እንዳይዝህ መከላከል ትችላለህ
ከልክ በላይ በራስ መተማመን። አብዛኞቹ የልብ ድካም በሽታ ሰለባዎች ሕመሙ እንዳለባቸው ከመገንዘባቸው በፊት ስለ ጤንነታቸው በጣም እርግጠኞች ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ የጤና ምርመራ ማድረግ ችላ ይባላል አሊያም አላስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። በተመሳሳይም አንዳንዶች በክርስትና ጎዳና የተወሰነ ጊዜ በማሳለፋቸው ምክንያት ምንም ነገር እንደማይደርስባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። አንድ ዓይነት አደጋ እስኪደርስባቸው ድረስ መንፈሳዊ ምርመራም ሆነ በራሳቸው ላይ ፍተሻ ማድረጋቸውን ችላ ይሉ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከመጠን በላይ በራስ የመተማመንን አደጋ አስመልክቶ የሰጠውን ጥሩ ምክር ልብ ማለቱ በጣም አስፈላጊ ነው። “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” ስለዚህ ፍጽምና የሌለን መሆናችንን አምኖ መቀበልና በራሳችን ላይ ዘወትር መንፈሳዊ ምርመራ ማድረግ ጥበብ ነው።—1 ቆሮንቶስ 10:12፤ ምሳሌ 28:14