የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከመስከረም 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 29
ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆኑ እምነቶችና ልማዶች ራቁ
wp16.06 6 ሣጥን
በሰማይ ስለሚኖሩት አካላት የሚገልጹ ራእዮች
በሰንሰለት እንደታሰሩ እስረኞች፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአጉል እምነትና በክፉ መናፍስት ፍርሃት ተተብትበዋል። ከክፉ መናፍስት እንዲጠብቋቸው ሲሉ ክታቦችንና አስማታዊ የሆኑ መድኃኒቶችን ይጠቀማሉ። አንተ ግን እንዲህ ማድረግ አያስፈልግህም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን የሚያጽናና ሐሳብ ይናገራል፦ “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።” (2 ዜና መዋዕል 16:9) እውነተኛው አምላክ ይሖዋ፣ ከሰይጣን እጅግ የሚበልጥ ኃይል ስላለው በእሱ ከታመንክ ይጠብቅሃል።
ይሖዋ ከክፉ መናፍስት እንዲጠብቅህ ከፈለግክ እሱን ምን እንደሚያስደስተው ማወቅና የሚያስደስተውን ነገር ማድረግ ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ከተማ ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች የአስማት መጽሐፎቻቸውን ሰብስበው አቃጥለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 19:19, 20) አንተም በተመሳሳይ ይሖዋ እንዲጠብቅህ ከፈለግክ እንደ ጨሌ፣ ክታብ፣ የአስማት መጻሕፍት፣ የቡዳ መድኃኒትና የመሳሰሉትን እንዲሁም ጥበቃ ያስገኛሉ የሚባሉ ክሮችን ጨምሮ ከአጋንንታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ያለውን ማንኛውንም ዕቃ ማስወገድ ይኖርብሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በተመለከተ ለሚያስተምረው እውነት ጥብቅና ቁሙ
13 አንድ ልማድ ወይም ድርጊት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ መሆኑን ከተጠራጠራችሁ ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጣችሁ በእምነት ጠይቁት። (ያዕቆብ 1:5ን አንብብ።) ከዚያም በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አድርጉ። አስፈላጊ ከሆነ፣ የጉባኤያችሁን ሽማግሌዎች አማክሩ። ሽማግሌዎቹ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ባይነግሯችሁም እዚህ ላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይጠቁሟችኋል። እነዚህን እርምጃዎች መውሰዳችሁ ‘የማስተዋል ችሎታችሁን ለማሠልጠን’ የሚረዳችሁ ሲሆን ይህም “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር [ለመለየት]” ያስችላችኋል።—ዕብ. 5:14
“በእውነትህ እሄዳለሁ”
12 ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ባሕሎችና ልማዶች። የቤተሰባችን አባላት፣ የሥራ ባልደረቦቻችንና አብረውን የሚማሩ ልጆች በሚያከብሯቸው በዓላት ላይ እንድንካፈል ተጽዕኖ ያደርጉብን ይሆናል። ይሖዋን በማያስከብሩ ባሕሎችና በዓላት ላይ እንድንካፈል የሚደርስብንን ተጽዕኖ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ እንዲህ ላሉት ልማዶች ያለውን አመለካከት ማስታወሳችን ይረዳናል። ታዋቂ የሆኑ ክብረ በዓላትን አመጣጥ አስመልክቶ በጽሑፎቻችን ላይ የወጡ ሐሳቦችን መከለስ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በእነዚህ በዓላት ላይ የማንካፈልባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ማስታወሳችን “በጌታ ዘንድ ተቀባይነት” ባለው መንገድ እየተጓዝን እንዳለ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። (ኤፌ. 5:10) በይሖዋና እውነት በሆነው ቃሉ ላይ እምነት ማሳደራችን ‘ሰውን በመፍራት ወጥመድ’ እንዳንያዝ ይጠብቀናል።—ምሳሌ 29:25
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
“በተግባርና በእውነት” እንዋደድ
ወንድሞችህን ከልብ አመስግን። አንዳችን ሌላውን የምናመሰግንበትን አጋጣሚ በንቃት መከታተል ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን ‘ሌሎችን ያንጻል።’ (ኤፌ. 4:29) ይሁን እንጂ አንድን ሰው ስናመሰግን ከልባችን መሆን ይኖርበታል። ካልሆነ ግን ግለሰቡን እየሸነገልነው ወይም ለግለሰቡ የሚያስፈልገውን ምክር የመስጠት ኃላፊነታችንን ገሸሽ እያደረግን ነው ማለት ነው። (ምሳሌ 29:5) አንድን ሰው ካመሰገንነው በኋላ ከበስተጀርባው ስለ እሱ አሉታዊ ነገር መናገር ግብዝነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ረገድ ጠንቃቃ የነበረ ሲሆን ሌሎችን ያመሰገነበት መንገድ ለእነሱ እውነተኛ ፍቅር እንዳለው የሚያሳይ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያከናወኗቸውን አንዳንድ መልካም ነገሮች በመጥቀስ ከልብ አመስግኗቸዋል። (1 ቆሮ. 11:2) ይሁንና ምስጋና የማይገባውና መታረም ያለበት ተግባር በፈጸሙ ጊዜ ጉዳዩን በግልጽ ሆኖም ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ አስረድቷቸዋል።—1 ቆሮ. 11:20-22
ከመስከረም 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 30
“ድሃም ሆነ ባለጸጋ አታድርገኝ”
እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው ምን ዓይነት ፍቅር ነው?
10 ሁላችንም ገንዘብ እንደሚያስፈልገን የታወቀ ነው። ገንዘብ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ጥበቃ ያስገኛል። (መክ. 7:12) ይሁን እንጂ ለመሠረታዊ ፍላጎቶቹ ብቻ የሚበቃ ገንዘብ ያለው ሰው እውነተኛ ደስታ ማግኘት ይችላል? አዎ ይችላል! (መክብብ 5:12ን አንብብ።) የያቄ ልጅ አጉር “ድሃም ሆነ ባለጸጋ አታድርገኝ። ብቻ የሚያስፈልገኝን ቀለብ አታሳጣኝ” ሲል ጽፏል። አጉር በድህነት መቆራመድ ያልፈለገበትን ምክንያት መረዳት አይከብደንም። ቀጥሎ እንደተናገረው ድህነት ወደ ስርቆት ሊመራው ይችላል፤ ይህ ደግሞ የአምላክን ስም ያሰድባል። አጉር “ባለጸጋ አታድርገኝ” በማለት የጸለየውስ ለምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “አለዚያ እጠግብና እክድሃለሁ፤ ከዚያም ‘ይሖዋ ማን ነው?’ እላለሁ።” (ምሳሌ 30:8, 9) አንተም ከአምላክ ይልቅ በሀብታቸው የሚታመኑ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል።
11 ገንዘብን የሚወዱ ሰዎች አምላክን ማስደሰት አይችሉም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።” ኢየሱስ ይህን ምክር ከመስጠቱ በፊት እንደሚከተለው በማለት ተናግሮ ነበር፦ “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በሚችልበት በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ከዚህ ይልቅ ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በማይችልበት በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።”—ማቴ. 6:19, 20, 24
12 ብዙዎች አኗኗራቸውን ቀላል ማድረጋቸው ይበልጥ ደስተኞች ለመሆን ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ ይሖዋን ለማገልገል ተጨማሪ ጊዜ አስገኝቶላቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ጃክ ከባለቤቱ ጋር በአቅኚነት ለማገልገል ስለፈለገ የነበራቸውን ትልቅ ቤትና ድርጅታቸውን ሸጠ። ጃክ እንዲህ ብሏል፦ “ከከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘውን የሚያምር ቤታችንንና ንብረታችንን ለመሸጥ መወሰን ቀላል አልነበረም። ይሁን እንጂ ለዓመታት፣ በሥራ ቦታ በሚያጋጥሙኝ ችግሮች የተነሳ ወደ ቤት የምመለሰው እየተበሳጨሁ ነበር። የዘወትር አቅኚ የሆነችው ባለቤቴ ግን ምንጊዜም ደስተኛ ናት። ‘የእኔ አለቃ ከማንም የተሻለ ነው!’ ትለኝ ነበር። አሁን እኔም አቅኚ ስለሆንኩ ሁለታችንም የምንሠራው ለአንድ አካል ይኸውም ለይሖዋ ነው።”
w87 5/15 30 አን. 8
ይሖዋን ፍራ፤ ደስተኛ ትሆናለህ
◆ 30:15, 16—የእነዚህ ምሳሌዎች ትርጉም ምንድን ነው?
ስግብግብነት ምን ያህል የማይረካ እንደሆነ ያሳያሉ። አልቅቶች ሁልጊዜ ደም እንደሚመጡ ሁሉ ስግብግብ ሰዎች ሁልጊዜ ተጨማሪ ገንዘብ ወይም ሥልጣን ይፈልጋሉ። በተመሳሳይም ሲኦል መቼም ቢሆን አይጠግብም፤ ሁሌም ተጨማሪ የሞት ሰለባዎችን ለመቀበል ክፍት ነው። መሃን የሆነ ማህፀን ልጆች ለማግኘት ‘ይጮኻል።’ (ዘፍጥረት 30:1) በድርቅ የተመታ መሬት የዝናብ ውኃ ቢጠጣም ወዲያውኑ ይደርቃል። በተጨማሪም ብዙ ነገር የበላ እሳት አቅራቢያው ያሉ ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮችን ለመብላት ነበልባሉን ይሰዳል። የስግብግብ ሰዎች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በአምላካዊ ጥበብ የሚመሩ ሰዎች ግን እንዲህ ባለው ራስ ወዳድነት እየተነዱ አይኖሩም።
እንደ አቅም መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?
ከመግዛትህ በፊት ገንዘብ አጠራቅም። አንድን ነገር ከመግዛትህ በፊት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማጠራቀም ጊዜ ያለፈበት አካሄድ ቢመስልም እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ ላለመግባት ከሚረዱት የጥበብ እርምጃዎች አንዱ ነው። ብዙዎች እንዲህ ማድረጋቸው ዕዳ ውስጥ ከመዘፈቅ ያዳናቸው ከመሆኑም ሌላ ከዕዳ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ እንደ ከፍተኛ ወለድ ያሉ ችግሮች ጠብቋቸዋል፤ ነገሮችን በዱቤ ስንገዛ ወለድም ጭምር ስለምንከፍል መጨረሻ ላይ የምናወጣው ገንዘብ ከፍተኛ ይሆናል። ጉንዳን ‘በመከር ወቅት’ ለወደፊት የሚሆነውን ‘ቀለብ ስለሚሰበሰብ’ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጠቢብ” ተብሎ ተጠርቷል።—ምሳሌ 6:6-8፤ 30:24, 25
ለዘላለም የይሖዋ እንግዶች ሆናችሁ ኑሩ!
18 እያንዳንዳችን ለገንዘብ ያለንን አመለካከት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ራሳችንን እንዲህ እያልን ልንጠይቅ ይገባል፦ ‘ስለ ገንዘብና ስለምገዛቸው ነገሮች ብዙ ጊዜ አስባለሁ? ገንዘብ ከተበደርኩ በኋላ አበዳሪዬ ገንዘቡ አያስፈልገውም በማለት ለመክፈል እዘገያለሁ? ገንዘብ ስላለኝ አስፈላጊ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል? ለጋስ ለመሆንስ ይከብደኛል? ወንድሞቼና እህቶቼ ገንዘብ ስላላቸው ብቻ ፍቅረ ነዋይ እንደተጠናወታቸው ይሰማኛል? ከሀብታሞች ጋር ለመወዳጀት እየሞከርኩ ድሆችን ችላ እላለሁ?’ በይሖዋ ድንኳን የመስተናገድ ታላቅ መብት አግኝተናል። አኗኗራችን ከገንዘብ ፍቅር ነፃ እንዲሆን በማድረግ ይህን ልዩ መብታችንን ጠብቀን ማቆየት እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ፈጽሞ አይተወንም።—ዕብራውያን 13:5ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ፍጥረት የይሖዋን ጥበብ በግልጽ ያሳያል
11 በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ትንሽ የሆነው ሌላው ፍጥረት ደግሞ ሽኮኮ ሲሆን ከዚህም ፍጥረት ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። (ምሳሌ 30:26ን አንብብ።) የሽኮኮ ጆሮዎች ክብና ትንንሽ ሲሆኑ እግሮቹ ደግሞ አጫጭር ናቸው። ይህ ትንሽ እንስሳ የሚኖረው አለታማ በሆኑ አካባቢዎች ነው። ከፍተኛ የማየት ችሎታ ያለው መሆኑ ጠላቶቹን ከርቀት ለመለየት ያስችለዋል። አለታማ በሆነው መኖሪያው ያሉት ጉድጓዶችና ስንጥቆች ደግሞ ከጠላቶቹ መሸሸጊያ ይሆኑለታል። ሽኮኮዎች በርከት ብለው አንድ ላይ መኖራቸው በጠላቶቻቸው እንዳይደፈሩ የሚረዳቸው ከመሆኑም ሌላ በክረምት ወራት እርስ በርስ ለመሟሟቅ ያስችላቸዋል።
12 ከሽኮኮ ምን ትምህርት እናገኛለን? በመጀመሪያ፣ ይህ እንስሳ ራሱን ለአደጋ እንደማያጋልጥ ልብ በል። አጥርቶ የማየት ችሎታውን በመጠቀም ጠላቶቹን ከርቀት የሚያይ ሲሆን መሸሸጊያ ከሚሆኑለት ጉድጓዶችና ስንጥቆች ርቆ አይሄድም። በተመሳሳይ እኛም በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉትን አደገኛ ሁኔታዎች ማስተዋል እንድንችል ጥሩ መንፈሳዊ እይታ ሊኖረን ይገባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የማስተዋል ስሜቶቻችሁን ጠብቁ፤ ንቁዎች ሆናችሁ ኑሩ። ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል” ሲል ክርስቲያኖችን አሳስቧል። (1 ጴጥ. 5:8) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሰይጣን ታማኝነቱን ለማጉደፍ በሚያደርገው በማንኛውም ጥረት ላለመሸነፍ ነቅቶ ይኖር ነበር። (ማቴ. 4:1-11) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል።
13 ንቁ ሆነን መኖር የምንችልበት አንደኛው መንገድ ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ በሚያደርጋቸው ዝግጅቶች መጠቀም ነው። የአምላክን ቃል ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ችላ ሊባሉ የማይገባቸው ነገሮች ናቸው። (ሉቃስ 4:4፤ ዕብ. 10:24, 25) በተጨማሪም ሽኮኮዎች በርከት ብለው አንድ ላይ መኖራቸው እንደሚጠቅማቸው ሁሉ እኛም “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” ከክርስቲያን ወንድሞቻችን መራቅ የለብንም። (ሮም 1:12) ይሖዋ እኛን ከአደጋ ለመጠበቅ ባደረጋቸው ዝግጅቶች በመጠቀም “[ይሖዋ] ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤ አምላኬ የምሸሸግበት ዐለቴ . . . ነው” በማለት ከጻፈው መዝሙራዊ ጋር እንደምንስማማ እናሳያለን።—መዝ. 18:2
ከመስከረም 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 31
አንዲት እናት ከሰጠችው ፍቅራዊ ምክር የምናገኛቸው ትምህርቶች
በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ የሥነ ምግባር እሴቶችን ትከሉ
ስለ ፆታ ምንም ሳትደብቁ አስተምሯቸው። ማስጠንቀቂያ መስጠት በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ያዕቆብ 1:14, 15) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ግንኙነትን በዋነኝነት የሚገልጸው የአምላክ ስጦታ እንደሆነ እንጂ የሰይጣን ወጥመድ አድርጎ እንዳልሆነ መዘንጋት የለባችሁም። (ምሳሌ 5:18, 19፤ ማሕልየ መሓልይ 1:2) ለልጆቻችሁ የምትነግሯቸው የፆታ ግንኙነት ስለሚያስከትለው አደጋ ብቻ ከሆነ ስለ ጉዳዩ የተዛባና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አመለካከት ሊይዙ ይችላሉ። በፈረንሳይ የምትኖር ኮሪና የተባለች ወጣት “ወላጆቼ ስለ ፆታ ሲያወሩ ብዙ ጊዜ የሚቀናቸው መጥፎ ጎኑን መናገር ነበር። ይህ ደግሞ ስለ ፆታ ግንኙነት አሉታዊ አመለካከት እንዲኖረኝ አድርጓል” ብላለች።
ልጆቻችሁ ስለ ፆታ ግንኙነት የተሟላ መረጃ እንዲኖራቸው አድርጉ። በሜክሲኮ የምትኖር ናዲያ የተባለች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “የፆታ ግንኙነት እርካታ የሚሰጥ ተፈጥሯዊ ስሜት እንደሆነና ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጆች የሰጣቸው እንዲደሰቱበት እንደሆነ ልጆቼን ለማስገንዘብ ሁልጊዜ እጥራለሁ። ይሁንና የፆታ ግንኙነት ሊፈጸም የሚገባው በትዳር ውስጥ ብቻ ነው። ይህን ስጦታ የምንጠቀምበት መንገድ ደስታ ሊያመጣልን ወይም ሥቃይ ሊያስከትልብን ይችላል።”
ልጃችሁን ስለ አልኮል መጠጥ ማስተማር
ቅድሚያውን ወስዳችሁ በጉዳዩ ላይ ተወያዩ። በብሪታንያ የሚኖር ማርክ የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ልጆች የአልኮል መጠጥን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ላያውቁ ይችላሉ። የስምንት ዓመት ልጄን ‘አልኮል መጠጣት ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?’ ብዬ ጠየቅኩት። ያናገርኩት ዘና ባለ ሁኔታ ነበር፤ ይህም አመለካከቱን በግልጽ እንዲነግረኝ ረድቶታል።”
የተለያዩ አጋጣሚዎችን ተጠቅማችሁ ከልጃችሁ ጋር ስለ አልኮል መጠጥ አጠቃቀም የምታወሩ ከሆነ ትምህርቱን በልጃችሁ ልብ ላይ መቅረጽ ቀላል ይሆንላችኋል። ዕድሜውን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ስለ አልኮል መጠጥ የምትሰጡትን ትምህርት እንደ ፆታ ሥነ ምግባር ወይም ራስን ከመኪና አደጋ እንደመጠበቅ ካሉ ሌሎች ጠቃሚ ትምህርቶች ጋር አንድ ላይ ልትሰጡት ትችላላችሁ።
ጥሩ ምሳሌ ሁኑ። ልጆች ልክ እንደ ስፖንጅ በአካባቢያቸው ያለውን ነገር የመምጠጥ ባሕርይ አላቸው፤ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ደግሞ በልጆች ላይ ከሁሉ የላቀ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት ወላጆች ናቸው። ለመረጋጋት ወይም ጭንቀታችሁን ለማስታገስ ስትሉ ብዙ ጊዜ የአልኮል መጠጥ የምትጠጡ ከሆነ ልጃችሁም በሕይወቱ ውስጥ የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥመው መፍትሔው የአልኮል መጠጥ መጠጣት እንደሆነ ማሰብ ይጀምራል። እንግዲያው ለልጃችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁሉ። በቅድሚያ እናንተ ራሳችሁ የአልኮል መጠጥን በአግባቡ ተጠቀሙ።
ልጆችን ትሕትና ማስተማር
ለጋስ እንዲሆኑ አበረታቷቸው። ልጃችሁ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ” እንደሚያስገኝ እንዲመለከት አድርጉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ዕቃ በመግዛት፣ በመጓጓዣ ወይም በጥገና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ዝርዝር ከልጃችሁ ጋር አብራችሁ በመሆን አውጡ። ከዚያም እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ስትሄዱ ልጃችሁን ይዛችሁት ሂዱ። ልጃችሁ ሌሎችን በምትረዱበት ጊዜ እናንተ የምታገኙትን ደስታና እርካታ እንዲያይ አድርጉ። ልጃችሁ ትሕትናን እንዲማር የምትረዱበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ራሳችሁ ምሳሌ በመሆን ማስተማር ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሉቃስ 6:38
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው የትምህርት አሰጣጥ
7 በእስራኤል ውስጥ ልጆች ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ አባትና እናታቸው ያስተምሯቸው ነበር። (ዘዳግም 11:18, 19፤ ምሳሌ 1:8፤ 31:26) የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በተባለ የፈረንሳይኛ መዝገበ ቃላት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ኢ መንዡኖ እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ልጅ መናገር እንደቻለ ወዲያው ከሕጉ ጥቂት ክፍሎችን ይማራል። እናቱ አንድ ጥቅስ እየደጋገመች ትነግረዋለች። ያንን ሲያውቀው ደግሞ ሌላ ትነግረዋለች። በኋላም ልጁ የሚያስታውሳቸው ጥቅሶች ተጽፈው በእጁ ላይ ይደረጋሉ። በዚህ መንገድ ማንበብ ይለማመዳሉ። እያደጉ ሲሄዱም ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ማንበብና በጌታ ሕግ ላይ ማሰላሰል ይቀጥላሉ።”
8 ይህም መሠረታዊው የማስተማሪያ ዘዴ ነገሮችን በቃል መያዝ እንደነበር ይጠቁማል። የይሖዋ ሕግጋትና ይሖዋ ከሕዝቦቹ ጋር ያደረገውን ግንኙነት በተመለከተ የተማሯቸው ነገሮች በልብ ውስጥ ዘልቀው መግባት ነበረባቸው። (ዘዳግም 6:6, 7) ሊያሰላስሏቸው የሚገቡ ነገሮች ነበሩ። (መዝሙር 77:11, 12) ወጣቶችም ሆኑ ትልልቆች እነዚህን በቃላቸው ለመያዝ የሚያስችሏቸውን የተለያዩ የማስታወሻ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። እነዚህም ዘዴዎች በየመስመሩ መጀመሪያ ወይም መጨረሻ ያሉት ፊደላት ወደታች ሲነበቡ ትርጉም የሚሰጡ ቃላት ወይም የፊደላት ቅደም ተከተል እንዲሆኑ ማድረግን፤ አንቀጾችን ቅደም ተከተል በያዙ ፊደላት መከፋፈልን፣ ተከታታይ የመዝሙር ጥቅሶች በተለያዩ ፊደላት እንዲጀምሩ ማድረግን፤ በፊደላት ቅደም ተከተል ማስቀመጥን (እንደ ምሳሌ 31:10-31 ያሉ)፤ (በአንድ ዓይነት ፊደላት ወይም ተመሳሳይ ድምፅ ባላቸው ፊደላት የሚጀምሩ ቃላት) መጠቀምንና ከምሳሌ 30 አጋማሽ ጀምሮ እንደሚታየው ጥቅሶችን በቁጥር መከፋፈልን ይጨምሩ ነበር። ለጥንቱ የዕብራይስጥ አጻጻፍ ምሳሌ ከሆኑት ጥንታውያን ጽሑፎች አንዱ ጌዝር የተባለው የቀን መቁጠሪያ ተማሪዎች ለማስታወስ ይጠቀሙበት የነበረ ጽሑፍ እንደሆነ አንዳንድ ምሑራን ይገምታሉ።
ከመስከረም 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መክብብ 1-2
ቀጣዩን ትውልድ አሠልጥኑ
እነዚህን ነገሮች “ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ”
3 ብዙዎቻችን ሥራችንን የምንወደው ከመሆኑም ሌላ ዕድሜ ልካችንን ብንሠራው ደስ ይለናል። የሚያሳዝነው ግን ከአዳም ጊዜ አንስቶ እያንዳንዱ ትውልድ ያረጅና በሌላ ትውልድ ይተካል። (መክ. 1:4) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ እንዲህ ያለው ለውጥ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለየት ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ እንዲያጋጥማቸው አድርጓል። የይሖዋ ሕዝቦች የሚያከናውኑት ሥራ ስፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የይሖዋ ድርጅት፣ ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እየተጠቀመ ነው። አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ወንድሞች እንዲህ ካለው ለውጥ ጋር እኩል መራመድ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። (ሉቃስ 5:39) ይህን ብንተወው እንኳ፣ ወጣቶች በዕድሜ ከገፉት አንጻር ሲታይ የተሻለ ኃይልና ጥንካሬ እንዳላቸው የታወቀ ነው። (ምሳሌ 20:29) በመሆኑም በዕድሜ የገፉ ወንድሞች፣ ወጣቶች ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲቀበሉ ማዘጋጀታቸው ፍቅር የሚንጸባረቅበትና ምክንያታዊ ነው።—መዝሙር 71:18ን አንብብ።
4 በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ወንድሞች፣ ለወጣቶች ኃላፊነት መስጠት ሊከብዳቸው ይችላል። አንዳንዶች የሚወዱትን መብት እንዳያጡ ይሰጋሉ። ሌሎች ደግሞ እነሱ ካልተቆጣጠሩት ሥራው በትክክል እንደማይሠራ ያስባሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሌላ ሰው የሚያሠለጥኑበት ጊዜ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶች ተጨማሪ ኃላፊነት ሳይሰጣቸው ሲቀር ትዕግሥት እንዳያጡ መጠንቀቅ አለባቸው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
si 112 አን. 3
የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 21—መክብብ
ንጉሥ ሰሎሞን ሰብሳቢ የነበረው በምን መንገድ ነው? ሕዝቡንስ የሰበሰበው ለምን ዓላማ ነበር? ሰሎሞን የእስራኤላውያንና በመካከላቸው በጊዜያዊነት ይኖሩ የነበሩት መጻተኞች ሰብሳቢ ነበር። እነዚህን ሕዝቦች በሙሉ ወደ አምላኩ ወደ ይሖዋ አምልኮ ሰብስቧቸዋል። ቀደም ሲል በኢየሩሳሌም የይሖዋን ቤተ መቅደስ ሠርቶ ነበር። ቤተ መቅደሱ በተመረቀበት ጊዜም ሕዝቡን በሙሉ ወደ ይሖዋ አምልኮ ጠርቷቸዋል ወይም ሰብስቧቸዋል። (1 ነገ. 8:1 የ1954 ትርጉም) አሁን ደግሞ በመክብብ መጽሐፍ አማካኝነት ሕዝቦቹ ከዚህ ዓለም ከንቱና ፍሬ ቢስ ሥራ ርቀው ዋጋማ ለሆነ ሥራ እንዲሰባሰቡ ለማድረግ ፈልጓል።—መክ. 12:8-10
ከመስከረም 29–ጥቅምት 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መክብብ 3-4
በሦስት የተገመደውን ገመድ አጠናክሩ
ቴክኖሎጂ ሕይወታችንን እንዳይቆጣጠረው ማድረግ
● የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በጥበብ መጠቀም ለትዳራችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንዳንድ ባለትዳሮች አብረው በማይሆኑበት ሰዓት ለመነጋገር የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይጠቀማሉ።
“‘እወድሻለሁ’ ወይም ‘ናፍቀሽኛል’ የሚል አጭር መልእክት መላክ ብቻ ይበልጥ ለመቀራረብ ይረዳል።”—ጆናታን
● የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በጥበብ አለመጠቀም ትዳራችሁን ይጎዳዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሰዎች ስልካቸውን ወይም ታብሌታቸውን ያለማቋረጥ ስለሚጠቀሙ ለትዳር ጓደኛቸው በቂ ጊዜና ትኩረት አይሰጡም።
“ባለቤቴ ሊያነጋግረኝ ፈልጎ ስልኬን እየተጠቀምኩ በመሆኑ ምክንያት ሳያነጋግረኝ የቀረበት ጊዜ እንደሚኖር ምንም ጥርጥር የለውም።”—ጁሊሳ
● አንዳንድ ሰዎች ስልካቸውን እየተጠቀሙም ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ትርጉም ያለው የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ እንደሚችሉ ይናገራሉ። የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ሼሪ ተርክል ‘በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ማከናወን እችላለሁ ብሎ ማሰብ ሞኝነት’ እንደሆነ ገልጸዋል። ደግሞም በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ማከናወን ጠቃሚ ክህሎት አይደለም። አክለውም “ብዙ ነገር ለማከናወን በሞከርን መጠን ለእያንዳንዱ ነገር የምንሰጠው ትኩረት እየቀነሰ ይመጣል” ብለዋል።
“ከባለቤቴ ጋር መነጋገር ያስደስተኛል፤ ሌላ ነገር እያከናወነ ከሆነ ግን መነጋገር አልፈልግም። ስልኩን እየተጠቀመ ሲያነጋግረኝ፣ እኔን ከማነጋገር ይልቅ ስልኩን መጠቀም እንደሚያስደስተው ይሰማኛል።”—ሳራ
ዋናው ነጥብ፦ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የምትጠቀሙበት መንገድ በትዳራችሁ ላይ አዎንታዊ አሊያም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
‘የያህ ነበልባል’ እንዳይከስም አድርጉ
12 ባለትዳሮች የአቂላንና የጵርስቅላን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? እናንተም ሆናችሁ የትዳር አጋራችሁ ያሉባችሁን የተለያዩ ኃላፊነቶች ለማሰብ ሞክሩ። አንዳንዶቹን ሥራዎች ለብቻችሁ ከማከናወን ይልቅ አብራችሁ ልትሠሩ ትችሉ ይሆን? ለምሳሌ አቂላና ጵርስቅላ አብረው ይሰብኩ ነበር። እናንተስ አዘውትራችሁ አብራችሁ ለማገልገል ፕሮግራም ታወጣላችሁ? አቂላና ጵርስቅላ አብረው ይሠሩም ነበር። እርግጥ ነው፣ እናንተ አንድ ዓይነት ሥራ አይኖራችሁ ይሆናል። ይሁንና የቤት ውስጥ ሥራዎችን አብራችሁ ማከናወን ትችሉ ይሆን? (መክ. 4:9) አንድን ነገር ተባብራችሁ ስታከናውኑ አንድነታችሁ ይጠናከራል፤ አብራችሁ ለማውራት የሚያስችል አጋጣሚም ታገኛላችሁ። ሮበርትና ሊንዳ በትዳር ዓለም ከ50 ዓመት በላይ አሳልፈዋል። ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “እውነቱን ለመናገር በመዝናኛ ያን ያህል ጊዜ አብረን አናሳልፍም። ሆኖም ዕቃ ሳጥብ ባለቤቴ ዕቃዎቹን ስታደርቅ ወይም ደጅ አትክልት ስንከባከብ መጥታ አብራኝ ስትሠራ በጣም ደስ ይለኛል። አብረን መሥራታችን ይበልጥ ያቀራርበናል። ፍቅራችን እያደገ ይሄዳል።”
13 ይሁንና አንድ ላይ ስለሆናችሁ ብቻ አንድነታችሁ ይጠናከራል ማለት እንዳልሆነ አስታውሱ። በብራዚል የምትኖር አንዲት ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “በዛሬው ጊዜ ሕይወታችን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ከመሞላቱ የተነሳ በአንድ ጣሪያ ሥር ስለምንኖር ብቻ አብረን ጊዜ እያሳለፍን እንዳለን ሊሰማን ይችላል። ሆኖም አንድ ላይ መሆናችን ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ። ለባለቤቴ ተገቢውን ትኩረት ልሰጠውም ይገባል።” ብሩኖ እና ባለቤቱ ቴይስ አንዳቸው ለሌላው ትኩረት ለመስጠት ጥረት የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ብሩኖ እንዲህ ብሏል፦ “አብረን ጊዜ በምናሳልፍበት ወቅት ስልካችንን ትተን እርስ በርስ በምናደርገው ጭውውት ላይ ብቻ እናተኩራለን።”
14 ይሁንና አብራችሁ ጊዜ ማሳለፍ የማያስደስታችሁ ቢሆንስ? ምናልባት የሚማርካችሁ ነገር የተለያየ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ አንዳችሁ ሌላውን የሚያበሳጭ ባሕርይ ይኖራችሁ ይሆናል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ቀደም ሲል የጠቀስነውን የእሳት ምሳሌ መለስ ብለን እንመልከት። እሳቱ ወዲያውኑ ቦግ ብሎ አይነድም። ከትንሽ ጭራሮ አንስቶ ቀስ በቀስ ተለቅ ተለቅ ያሉ እንጨቶች ሊጨመሩበት ይገባል። እናንተም በተመሳሳይ በየቀኑ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ አብራችሁ በማሳለፍ ለምን አትጀምሩም? ግጭት ሊፈጥር በሚችል ሳይሆን ሁለታችሁንም በሚያስደስታችሁ እንቅስቃሴ ለመካፈል ሞክሩ። (ያዕ. 3:18) በዚህ መንገድ ከትንሹ መጀመራችሁ ፍቅራችሁን ለማቀጣጠል ሊረዳችሁ ይችላል።
‘የያህ ነበልባል’ እንዳይከስም አድርጉ
3 ‘የያህ ነበልባል’ እንዳይከስም ከተፈለገ ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማጠናከር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታቸው ትዳራቸውን የሚያጠናክረው እንዴት ነው? አንድ ባልና ሚስት ከሰማዩ አባታቸው ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ከሆነ ምክሮቹን ወዲያውኑ በሥራ ላይ ያውላሉ። ይህ ደግሞ በመካከላቸው ያለው ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ሊያደርጉ የሚችሉ ችግሮችን ለማስወገድ ወይም ለማሸነፍ ይረዳቸዋል። (መክብብ 4:12ን አንብብ።) በተጨማሪም መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች እንደ ደግነት፣ ትዕግሥትና ይቅር ባይነት ያሉትን ባሕርያት በማዳበር ይሖዋን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። (ኤፌ. 4:32–5:1) ባለትዳሮች እነዚህን ባሕርያት የሚያሳዩ ከሆነ በመካከላቸው ያለው ፍቅር ማደጉ አይቀርም። በትዳር ዓለም ከ25 ዓመት በላይ ያሳለፈች ሌና የተባለች እህት “መንፈሳዊ የሆነን ሰው መውደድና ማክበር ቀላል ነው” በማለት ተናግራለች።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it “ፍቅር” አን. 39
ፍቅር
“ለመውደድ ጊዜ አለው።” ፍቅር ማሳየት ተገቢ ያልሆነው ይሖዋ ፍቅር አይገባቸውም ብሎ ለወሰነባቸው ሰዎች ወይም በክፋት ጎዳና ለሚመላለሱ ሰዎች ብቻ ነው። አምላክን እንደሚጠሉ እስካላሳዩ ድረስ ሁሉንም ሰዎች መውደድ አስፈላጊ ነው። ይህን ካደረጉ ጊዜ ጀምሮ ግን ለእነሱ ፍቅር ማሳየት ተገቢ አይሆንም። ይሖዋ አምላክም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅን ይወዳሉ፤ ዓመፅን ደግሞ ይጠላሉ። (መዝ 45:7፤ ዕብ 1:9) እውነተኛውን አምላክ ለሚጠሉ ሰዎች ፍቅር ማሳየት ተገቢ አይሆንም። ደግሞም እንዲህ ላሉት ሰዎች ፍቅር ማሳየትን መቀጠል ምንም ጥቅም የለውም፤ ምክንያቱም አምላክን የሚጠሉ ሰዎች ለአምላክ ፍቅር ምላሽ አይሰጡም። (መዝ 139:21, 22፤ ኢሳ 26:10) በመሆኑም አምላክ ይጠላቸዋል፤ እንዲሁም በእነሱ ላይ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ቀጥሯል።—መዝ 21:8, 9፤ መክ 3:1, 8
ከጥቅምት 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መክብብ 5-6
ታላቁን አምላካችንን በጥልቅ እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
ክብር ባለው መንገድ በመመላለስ ይሖዋን ማክበር
17 ለይሖዋ አምልኮ ስናቀርብ ለእሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ መመላለሳችን ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። መክብብ 5:1 “ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ” ይላል። ሙሴም ሆነ ኢያሱ በተቀደሰ ቦታ ላይ በቆሙ ጊዜ ጫማቸውን እንዲያወልቁ ታዘው ነበር። (ዘፀ. 3:5፤ ኢያሱ 5:15) ይህንን ማድረጋቸው አክብሮት እንዳላቸው የሚያሳይ ነበር። እስራኤላውያን ካህናት “ሰውነትን የሚሸፍን” የበፍታ ሱሪ መልበስ ነበረባቸው። (ዘፀ. 28:42, 43) እንዲህ ማድረጋቸው በመሠዊያው አጠገብ በሚያገለግሉበት ጊዜ ሰውነታቸው እንዳይጋለጥ ለማድረግ ይረዳል። የካህኑ ቤተሰብ አባላት በሙሉ ክብር ባለው መንገድ በመመላለስ ረገድ አምላክ ያወጣውን መሥፈርት ማሟላት ነበረባቸው።
18 የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ክብር ባለው መንገድ መመላለስ ይኖርብናል። ክብር የሚገባን ሰዎች ሆነን ለመገኘት በሚያስከብር መንገድ መኖር አለብን። ይህም ለይስሙላ ወይም ለታይታ የሚደረግ ሳይሆን ከልብ የመነጨ ሊሆን ይገባል። (1 ሳሙ. 16:7፤ ምሳሌ 21:2) ለይሖዋ አክብሮት በሚያመጣ መንገድ መመላለስ የሕይወታችን ክፍል ሊሆን ይኸውም በባሕርያችን፣ በአመለካከታችን፣ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት አልፎ ተርፎም ስለ ራሳችን ባለን አመለካከትና ስሜት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል። በእርግጥም፣ ለይሖዋ አክብሮት ማሳየት በምንናገረውም ሆነ በምናደርገው በማንኛውም ነገር ሁልጊዜ ሊንጸባረቅ ይገባል። በባሕርያችን፣ በጠባያችን፣ በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ሐሳብ በቁም ነገር እንመለከተዋለን፦ “አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ፣ ለማንም ዕንቅፋት መሆን አንፈልግም። ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን።” (2 ቆሮ. 6:3, 4) ‘በሁሉም መንገድ የአዳኛችን የአምላክ ትምህርት እንዲወደድ እናደርጋለን።’—ቲቶ 2:10
መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የጸሎትህን ይዘት አሻሽል
21 ኢየሱስ ሙሉ እምነት እንዳለው በሚያሳይ መንገድ በአክብሮት ጸልዮአል። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ አልዓዛርን ከማስነሳቱ በፊት “ወደ ሰማይ ከተመለከተ በኋላ እንዲህ አለ፦ ‘አባት ሆይ፣ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። እውነት ነው፣ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ አውቃለሁ።’” (ዮሐ. 11:41, 42) አንተስ የምታቀርበው ጸሎት እንዲህ ያለ ጥልቅ አክብሮትና እምነት እንዳለህ ያሳያል? ጥልቅ አክብሮት የሚንጸባረቅበትን ኢየሱስ የሰጠውን የናሙና ጸሎት በትኩረት አንብበው፤ በዚህ ጸሎት ላይ ጎላ ብለው የሚታዩት ነጥቦች የይሖዋ ስም መቀደስ፣ የመንግሥቱ መምጣትና የፈቃዱ መፈጸም እንደሆኑ መመልከት ትችላለህ። (ማቴ. 6:9, 10) እስቲ አንተ ስለምታቀርባቸው ጸሎቶች አስብ። ጸሎቶችህ ስለ ይሖዋ መንግሥት፣ ስለ ፈቃዱ መፈጸም እንዲሁም ስለ ስሙ መቀደስ በጥልቅ እንደምታስብ የሚያሳዩ ሊሆኑ ይገባል።
“ስእለትህን ፈጽም”
12 ይሁንና ጥምቀት የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ከተጠመቅንበት ጊዜ አንስቶ አምላክን በታማኝነት በማገልገል ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን መኖር ይገባናል። በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ከተጠመቅኩ ወዲህ ምን ያህል መንፈሳዊ እድገት አድርጌያለሁ? አሁንም ይሖዋን በሙሉ ልቤ እያገለገልኩ ነው? (ቆላ. 3:23) አዘውትሬ እጸልያለሁ? መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ አነባለሁ? በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር እገኛለሁ? አቅሜ በፈቀደ መጠን አዘውትሬ በአገልግሎት እካፈላለሁ? ወይስ በእነዚህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የማደርገው ተሳትፎ በተወሰነ መጠን ቀንሷል?’ ሐዋርያው ጴጥሮስ በእምነታችን ላይ እውቀትን፣ ጽናትን እና ለአምላክ ማደርን እየጨመርን ከሄድን ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደምንችል ገልጿል።—2 ጴጥሮስ 1:5-8ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በመክብብ 5:8 ላይ በድሃ ላይ ግፍ ስለሚፈጽምና ፍትሕ ስለሚያጓድል ገዢ ተጠቅሷል። ይህ ገዢ ከእሱ የበለጠ ቦታ ወይም ሥልጣን ያለው ሰው እየተመለከተው ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ያስፈልገዋል። እንዲያውም የእሱ የበላይ የሆነው ሰውም የበላዮች ሊኖሩት ይችላሉ። የሚያሳዝነው በሰብዓዊ መንግሥታት ውስጥ በተለያየ የሥልጣን ተዋረድ ያሉት ገዢዎች ሁሉ ምግባረ ብልሹ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በመሆኑም ተራው ሕዝብ የተለያየ የሥልጣን እርከን ላይ ባሉ ሰዎች የፍትሕ መጓደል ሊፈጸምበት ይችላል።
ሁኔታዎች ምንም ያህል ተስፋ አስቆራጭ ቢመስሉ፣ ይሖዋ ‘ከፍ ያለ ቦታ ያላቸውን’ ባለሥልጣናት እንኳ እንደሚመለከታቸው ማወቃችን ያጽናናናል። አምላክ እንዲረዳን መለመንና ሸክማችንን በእሱ ላይ መጣል እንችላለን። (መዝ. 55:22፤ ፊልጵ. 4:6, 7) “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ [እንደሚመላለሱ]” እናውቃለን።—2 ዜና 16:9
ነጥቡን ስናጠቃልለው መክብብ 5:8 በሰው ልጆች መንግሥታት ውስጥ የሚታየውን ሁኔታ የሚገልጽ ነው፤ ባለሥልጣን የሆነው አካልም ምንጊዜም ቢሆን የበላይ አለው። ከዚህም ሌላ ጥቅሱ፣ የሁሉ የበላይ የሆነው ባለሥልጣን ይሖዋ መሆኑን እንድናስታውስ ይረዳናል። በአሁኑ ወቅት ይሖዋ የመንግሥቱ ንጉሥ አድርጎ በሾመው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት እየገዛ ነው። ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ እይታ የሚያመልጥ ነገር የለም፤ እሱም ሆነ ልጁ ፈጽሞ ፍትሕ አያጓድሉም።
ከጥቅምት 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መክብብ 7-8
“ወደ ሐዘን ቤት” ሂዱ
ኢየሱስ እንባውን ማፍሰሱ ምን ያስተምረናል?
9 ሐዘን የደረሰባቸውን መደገፍ ትችላለህ። ኢየሱስ ከማርታና ከማርያም ጋር አልቅሷል፤ ከዚህም በተጨማሪ አዳምጧቸዋል እንዲሁም በሚያጽናና መንገድ አነጋግሯቸዋል። እኛም ሐዘን ለደረሰባቸው ይህን ማድረግ እንችላለን። በአውስትራሊያ የሚኖር ዳን የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴን በሞት ካጣሁ በኋላ የሌሎች ድጋፍ አስፈልጎኝ ነበር። ብዙ ባለትዳሮች ቀንም ሆነ ማታ ጊዜያቸውን ሰጥተው ያዳምጡኝ ነበር። ሐዘኔን እንድገልጽ አጋጣሚ ሰጥተውኛል፤ ማልቀሴም አላሳፈራቸውም። ከዚህ በተጨማሪ ተግባራዊ እርዳታ ለማድረግ ራሳቸውን ያቀርቡ ነበር። ለምሳሌ እኔ እንደማልችል በሚሰማኝ ጊዜ መኪናዬን ያጥቡልኝ፣ አስቤዛ ይገዙልኝ እንዲሁም ምግብ ያበስሉልኝ ነበር። ደግሞም ብዙ ጊዜ አብረውኝ ይጸልዩ ነበር። እውነተኛ ወዳጆች እንዲሁም ‘ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም’ ሆነውልኛል።”—ምሳሌ 17:17
የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸውን እርዷቸው
15 ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ባለቤቱን በሞት ያጣው ዊልያም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሌሎች፣ ባለቤቴ ስላደረገቻቸው መልካም ነገሮች ሲናገሩ ደስ ይለኛል፤ ባለቤቴን እንደሚወዷትና እንደሚያከብሯት ያረጋግጥልኛል። እንዲህ ማድረጋቸው በጣም ጠቅሞኛል። ባለቤቴ ለእኔ በጣም ውድ ስለሆነችና በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ ስለነበራት፣ ሰዎች ስለ እሷ ሲናገሩ በእጅጉ እጽናናለሁ።” ቢያንካ የተባለች ባሏ የሞተባት ሴትም እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች አብረውኝ ሲጸልዩና ጥቅሶች ሲያነቡልኝ እጽናናለሁ። ስለ ባለቤቴ አንስተው ማውራታቸው እንዲሁም እኔ ስለ እሱ ሳወራ ማዳመጣቸው ጠቅሞኛል።”
“ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ”
16 ሐዘን ከደረሰበት የእምነት ባልንጀራችሁ ጋር አብራችሁ ስትሆኑ አልፎ ተርፎም እሱ በሌለበት ስለ እሱ ጠቅሳችሁ መጸለያችሁ ትልቅ ጥቅም እንዳለው አትርሱ። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ስሜታችሁ ስለሚረበሽ ሐሳባችሁን በጸሎት መግለጽ ሊከብዳችሁ ይችላል፤ ይሁንና ድምፃችሁ እየተቆራረጠና እያለቀሳችሁም ቢሆን ስለ ግለሰቡ የምታቀርቡት ልባዊ ጸሎት፣ ሐዘኑ ቀለል እንዲልለት ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። ዳሊን እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “አንዳንድ ጊዜ እህቶች እኔን ለማጽናናት ሲመጡ አብረውኝ እንዲጸልዩ እጠይቃቸዋለሁ። መጸለይ ሲጀምሩ አብዛኛውን ጊዜ ሐሳባቸውን መግለጽ ቢያታግላቸውም ቀስ በቀስ ድምፃቸው እየተረጋጋ ይመጣል፤ ከዚያም ልባዊ የሆነ ጸሎት ያቀርባሉ። ያላቸው ጠንካራ እምነት፣ ፍቅራቸውና አሳቢነታቸው እምነቴን በእጅጉ አጠናክሮልኛል።”
“ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ”
17 ከሐዘን ለመጽናናት የሚወስደው ጊዜ ከሰው ወደ ሰው ሊለያይ ይችላል። ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለማጽናናት፣ በርካታ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት አብረዋቸው እንደሚሆኑ ግልጽ ነው፤ ሆኖም በዚህ ጊዜ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ሰው ወደ ዕለታዊ ሕይወቱ ከተመለሰ በኋላ ባሉት ወራትም ጭምር እነሱን ለመርዳት ጥረት ማድረጉ አስፈላጊ ነው። “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።” (ምሳሌ 17:17) ሐዘን የደረሰበት ሰው ለመጽናናት የሚወስድበት ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን፣ የእምነት ባልንጀሮቹ ከጎኑ መሆናቸው በእጅጉ ያጽናናዋል።—1 ተሰሎንቄ 3:7ን አንብብ።
18 የሚወዱትን ሰው በሞት ላጡ ሰዎች አንዳንድ ሙዚቃዎች፣ ፎቶግራፎች ወይም አብረው ያከናውኗቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ሌላው ቀርቶ አንድ ዓይነት መዓዛ፣ ድምፅ አሊያም ወቅቶች ሲቀያየሩ የሚኖረው ሁኔታ እንኳ ሐዘናቸው በድንገት እንዲያገረሽባቸው ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ ሰው፣ አንዳንድ ነገሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለብቻው ሲያደርግ ለምሳሌ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ወይም በመታሰቢያው በዓል ላይ ሲገኝ በሐዘን ሊዋጥ ይችላል። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የተጋባንበትን ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ለብቻዬ ማሳለፍ በጣም እንደሚከብደኝ ጠብቄ ነበር፤ ደግሞም ሁኔታው ቀላል አልነበረም። ሆኖም የተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች በዚያ ዕለት ብቻዬን እንዳልሆን ሲሉ ከቅርብ ጓደኞቼ ጋር አብሬ ጊዜ እንዳሳልፍ ዝግጅት አደረጉ።”
19 ይሁን እንጂ ሐዘን ያጋጠማቸው ሰዎች ማበረታቻ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው በአንዳንድ ለየት ያሉ ወቅቶች ብቻ እንዳልሆነ መዘንጋት የለብንም። ዩኒያ እንዲህ ብላለች፦ “ለየት ባሉ ወቅቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጊዜያትም ሰዎች አብረውን ሲሆኑና ሲረዱን በጣም እንጠቀማለን። እንዲህ ማድረጋቸው ትልቅ ትርጉም ያለው ከመሆኑም ሌላ በእጅጉ ያጽናናናል።” እርግጥ ነው፣ ሐዘናቸውን ጨርሶ ማስወገድ ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው ምክንያት በሕይወታቸው ውስጥ የተፈጠረውን ክፍተት ሙሉ በሙሉ መድፈን እንደማንችል የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰዳችን በተወሰነ መጠን ሊያጽናናቸው ይችላል። (1 ዮሐ. 3:18) ጋቢ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ይሖዋ ሽማግሌዎችን ስለሰጠኝ ከልቤ አመሰግነዋለሁ፤ እነዚህ አፍቃሪ እረኞች እያንዳንዱን አስቸጋሪ ወቅት መወጣት እንድችል ረድተውኛል። አፍቃሪ በሆነው በይሖዋ እቅፍ ውስጥ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርገውኛል።”
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
“ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ”
18 አንዳንድ ጊዜ ቅር ያሰኘንን ግለሰብ ማነጋገር እንዳለብን ሊሰማን ይችላል። በቅድሚያ ግን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ስለ ጉዳዩ በቂ መረጃ አለኝ?’ (ምሳሌ 18:13) ‘ግለሰቡ ያን ነገር ያደረገው ሆን ብሎ ባይሆንስ?’ (መክ. 7:20) ‘እኔስ ተመሳሳይ ስህተት የሠራሁበት ጊዜ የለም?’ (መክ. 7:21, 22) ‘ግለሰቡን ማነጋገሬ ለመፍታት እየሞከርኩ ካለሁት ችግር የከፋ ሌላ ችግር ያስከትል ይሆን?’ (ምሳሌ 26:20ን አንብብ።) እንዲህ ባሉ ጥያቄዎች ላይ ቆም ብለን ካሰብን በኋላ ለወንድማችን ባለን ፍቅር ተነሳስተን በደሉን ችላ ብለን ለማለፍ ልንወስን እንችላለን።
ከጥቅምት 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መክብብ 9-10
ለሚያጋጥሟችሁ ፈተናዎች ተገቢው አመለካከት ይኑራችሁ
ፈጽሞ ‘በይሖዋ ላይ አትቆጡ’
20 ለችግራችሁ ተጠያቂው ማን መሆኑን ለይታችሁ እወቁ። እንዲህ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? ለአንዳንዶቹ ችግሮቻችን ተጠያቂው እኛው ራሳችን ልንሆን ስለምንችል ነው። ሁኔታው ይህ ከሆነ ጥፋታችንን አምነን መቀበል ይኖርብናል። (ገላ. 6:7) ይሖዋን ለችግሮቻችሁ ተጠያቂ ለማድረግ አትሞክሩ። ለምን? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ መኪና በከፍተኛ ፍጥነት የመጓዝ አቅም ሊኖረው ይችላል። የመኪናው አሽከርካሪ ከተፈቀደው የፍጥነት መጠን በላይ መኪናውን እያበረረ ሄዶ ኩርባ ላይ ለመታጠፍ ሲሞክር አደጋ ደረሰበት እንበል። መኪናውን የሠራው ፋብሪካ ለዚህ አደጋ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል? በፍጹም! በተመሳሳይም ይሖዋ ሲፈጥረን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። በሌላ በኩል ደግሞ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ መመሪያዎችም ሰጥቶናል። ታዲያ የራሳችንን ስህተት ፈጣሪያችን ላይ የምናላክከው ለምንድን ነው?
21 እርግጥ ነው፣ ለሚያጋጥሙን ችግሮች ሁሉ መንስኤው ጥሩ ያልሆነ ውሳኔ ማድረጋችን ወይም የተሳሳተ አካሄድ መከተላችን ላይሆን ይችላል። “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ለአንዳንድ ችግሮቻችን መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። (መክ. 9:11 NW) ዞሮ ዞሮ ግን ለክፋት ዋነኛው ተጠያቂ ሰይጣን መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። (1 ዮሐ. 5:19፤ ራእይ 12:9) ጠላታችን፣ ሰይጣን እንጂ ይሖዋ አይደለም።—1 ጴጥ. 5:8
ይሖዋ ትሑት አገልጋዮቹን ከፍ አድርጎ ይመለከታል
10 በተጨማሪም ትሕትና ከአላስፈላጊ ውጥረት ይጠብቀናል። አንዳንድ ጊዜ ፍትሕ የጎደላቸው ወይም ትክክል ያልሆኑ ነገሮች እንደተፈጸሙ ይሰማን ይሆናል። ጠቢብ የሆነው ንጉሥ ሰለሞን ይህን ሐቅ እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “አገልጋዮች በፈረስ ተቀምጠው ሲጓዙ፣ መኳንንት ግን እንደ አገልጋዮች በእግራቸው ሲሄዱ አይቻለሁ።” (መክ. 10:7) ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ተገቢውን እውቅና የማያገኙበት ጊዜ አለ። ያን ያህል ችሎታ የሌላቸው ሰዎች ደግሞ የበለጠ ክብር ሲሰጣቸው እናያለን። ያም ቢሆን ሰለሞን አሉታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ከልክ በላይ ከማተኮር ይልቅ እውነታውን መቀበል ጥበብ እንደሆነ ተገንዝቧል። (መክ. 6:9) ትሑት ከሆንን አንዳንድ ነገሮች እኛ እንዳሰብናቸው ባይሆኑ እንኳ ሁኔታውን ተቀብለን ማለፍ ቀላል ይሆንልናል።
የምትመርጡት መዝናኛ ጠቃሚ ነው?
ይሖዋ፣ በሕይወት እንድንኖር ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ደስተኞች እንድንሆን እንደሚፈልግ የሚጠቁሙ በርካታ ሐሳቦችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 104:14, 15 ይሖዋ “ከምድር ምግብን [እንደሚያወጣ]” እንዲሁም “የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ ወይን፣ ፊቱን የሚያወዛ ዘይት፣ ልቡን የሚያበረታ እህል” እንደሚያዘጋጅ ይናገራል። አዎን፣ ይሖዋ እንደ እህል፣ ዘይትና ወይን ያሉ ለሕይወታችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንድናገኝ ሲል ዕፅዋትን ያበቅላል። ወይን ደግሞ “የሰውን ልብ ደስ [ያሰኛል]።” ወይን በሕይወት ለመኖር የግድ አስፈላጊ ባይሆንም ለደስታችን አስተዋጽኦ ያደርጋል። (መክ. 9:7፤ 10:19) በእርግጥም ይሖዋ ሐሴት እንድናደርግና ልባችን ‘በደስታ እንዲሞላ’ ይፈልጋል።—ሥራ 14:16, 17
2 በመሆኑም አልፎ አልፎ “የሰማይን ወፎች” እና ‘የሜዳ አበቦችን’ ልብ ብለን ብንመለከት ወይም መንፈሳችንን በሚያድሱና ሕይወታችንን አስደሳች በሚያደርጉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ብንካፈል ስህተት እንደሠራን ሊሰማን አይገባም። (ማቴ. 6:26, 28፤ መዝ. 8:3, 4) በሕይወት መደሰት የይሖዋ “ችሮታ ነው።” (መክ. 3:12, 13) እንግዲያው መዝናኛን አምላክ ከሰጠን ችሮታዎች መካከል እንደ አንዱ አድርገን መመልከታችን በመዝናናት የምናሳልፈውን ጊዜ እሱን በሚያስደስት መንገድ እንድናውለው ያነሳሳናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የሞቱ ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
ኢየሱስ ሞትን ከከባድ እንቅልፍ ጋር አመሳስሎታል። ሞት ከእንቅልፍ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ጭልጥ ያለ እንቅልፍ የወሰደው ሰው በዙሪያው የሚከናወነውን ነገር አያውቅም። በተመሳሳይም አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ምንም ሥቃይ አይሰማውም። ለጓደኞቹና ለቤተሰቦቹ ምንም ያህል ፍቅር የነበረው ቢሆን እንኳ ከሞተ በኋላ የብቸኝነት ስሜት ሊሰማው አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” ይላል።—መክብብ 9:5ን አንብብ።
ከጥቅምት 27–ኅዳር 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መክብብ 11-12
ጤናማና አስደሳች ሕይወት ምሩ
ንጹሕ አየርና የፀሐይ ብርሃን—የተፈጥሮ “አንቲባዮቲክ”
የፀሐይ ብርሃንም ተፈጥሯዊ ፀረ ጀርም ነው። ዘ ጆርናል ኦቭ ሆስፒታል ኢንፌክሽን የተባለው መጽሔት እንደገለጸው “አየር ወለድ ኢንፌክሽን ከሚያመጡት ተሕዋስያን መካከል አብዛኞቹ የፀሐይ ብርሃንን መቋቋም አይችሉም።”
ከእነዚህ ነገሮች ተጠቃሚ ልትሆን የምትችለው እንዴት ነው? ከቤትህ ወጣ ብለህ ፀሐይ ለመሞቅና ንጹሕ አየር ለመተንፈስ የተወሰነ ጊዜ መመደብ ትችላለህ። ይህም ለጤንነትህ ጠቃሚ መሆኑ አይካድም።
ከአምላክ ላገኘኸው የሕይወት ስጦታ አድናቆት ይኑርህ
6 ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ጤንነትን ለመንከባከብ ወይም የአመጋገብ መመሪያ ለመስጠት የተጻፈ መጽሐፍ ባይሆንም ይሖዋ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ለማወቅ ይረዳናል። ለምሳሌ ይሖዋ ‘ጎጂ ነገሮችን ከሰውነታችን እንድናርቅ’ አሳስቦናል። (መክ. 11:10) መጽሐፍ ቅዱስ ከልክ በላይ እንደ መብላትና እንደ መጠጣት ያሉ ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ልማዶችን ያወግዛል። (ምሳሌ 23:20) ይሖዋ የምንበላውንና የምንጠጣውን ነገር መጠን ስንወስን ራሳችንን እንድንገዛ ይጠብቅብናል።—1 ቆሮ. 6:12፤ 9:25
7 አምላክ ለሰጠን የሕይወት ስጦታ ከፍተኛ አድናቆት እንዳለን የሚያሳዩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የማመዛዘን ችሎታችንን ልንጠቀም ይገባል። (መዝ. 119:99, 100፤ ምሳሌ 2:11ን አንብብ።) ለምሳሌ የምንበላቸውን ምግቦች ስንመርጥ የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም ያስፈልገናል። አንድ የምንወደው ምግብ እንደሚያሳምመን የምናውቅ ከሆነ ያን ምግብ ከመብላት እንቆጠባለን። በቂ እንቅልፍ ማግኘታችን፣ አዘውትረን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጋችን፣ የግል ንጽሕናችንን መጠበቃችንና ቤታችንን ማጽዳታችንም ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለን ያሳያል።
“ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ”
2 እኛ የይሖዋ አገልጋዮች ደስተኛ ሕዝብ ነን። ለምን? ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ አንዱ ምክንያት ግን የአምላክን ቃል አዘውትረን ማንበባችንና የተማርነውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ማድረጋችን ነው።—ያዕቆብ 1:22-25ን አንብብ።
3 ‘ቃሉን የምናደርግ መሆናችን’ በብዙ መንገዶች ይጠቅመናል። አንደኛ፣ ከአምላክ ቃል የተማርነውን ነገር ተግባራዊ ስናደርግ ይሖዋን እናስደስተዋለን። ይህን ማወቃችን ደግሞ እኛን ያስደስተናል። (መክ. 12:13) በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ላይ ያነበብነውን ነገር በተግባር ስናውል የቤተሰብ ሕይወታችን ይሻሻላል፤ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለን ወዳጅነትም ይጠናከራል። አንተም ይህን በሕይወትህ ተመልክተኸው ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ፣ የይሖዋን መመሪያዎች የማይከተሉ ሰዎች ከሚደርሱባቸው ብዙ ችግሮች እንጠበቃለን። ንጉሥ ዳዊት ከተናገረው ሐሳብ ጋር እንደምንስማማ ጥያቄ የለውም። ዳዊት በመዝሙሩ ላይ ስለ ይሖዋ ሕግ፣ መመሪያዎችና ፍርዶች ከጠቀሰ በኋላ “እነሱን መጠበቅ ትልቅ ወሮታ አለው” ብሏል።—መዝ. 19:7-11
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ሐሳብ ሰዎች ያመነጩት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት ተጽፏል ሲባል ጸሐፊዎቹ ምንም ዓይነት ጥረት አላደረጉም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የመክብብ መጽሐፍ ጸሐፊ ‘ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት እንደተመራመረ እንዲሁም ቅንና እውነት የሆነውን እንደጻፈ’ ገልጿል። (መክብብ 12:10) ዕዝራ ታሪካዊ ዘገባዎቹን ለማጠናቀር ቢያንስ 14 የሚያህሉ ጽሑፎችን አመሳክሯል፤ ከእነዚህም መካከል ‘የንጉሥ ዳዊት መዝገብ’ እንዲሁም ‘የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መዛግብት’ ይገኙበታል። (1 መዋዕል 27:24፤ 2 ዜና መዋዕል 16:11) ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስም ‘ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመረ በኋላ፣ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ጽፏል።’—ሉቃስ 1:3
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጸሐፊውን ማንነት ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረው ማቴዎስ ዘገባውን በአኃዝ አስደግፎ ያቀርብ ነበር። ከወንጌል ጸሐፊዎች መካከል ኢየሱስ አልፎ የተሰጠው ‘በሠላሳ ጥሬ ብር’ መሆኑን የዘገበው እሱ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 27:3፤ ማርቆስ 2:14) ሐኪም የነበረው ሉቃስ ከሕክምና ሙያ አንጻር ዝርዝር ሐሳቦችን ይጠቅስ ነበር። ኢየሱስ የፈወሳቸው አንዳንድ ሰዎች የነበሩበትን ሁኔታ ሲገልጽ “ኀይለኛ ትኩሳት” እና “ለምጽ የወረሰው” እንደሚሉት ያሉ አባባሎችን ተጠቅሟል። (ሉቃስ 4:38፤ 5:12፤ ቈላስይስ 4:14) ከዚህ መመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ ጸሐፊዎቹ መልእክቱን በራሳቸው አባባልና የአጻጻፍ ስልት ተጠቅመው እንዲያሰፍሩት ፈቅዶላቸዋል፤ ያም ሆኖ ግን እሱ የሚፈልገውን ሐሳብ በትክክል እንዲጽፉ ለማድረግ አእምሯቸውን ይመራ ነበር።—ምሳሌ 16:9