የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ በፍጻሜው ዘመን
    መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020 | ግንቦት
    • የጥናት ርዕስ 19

      ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ በፍጻሜው ዘመን

      “በፍጻሜው ዘመን የደቡቡ ንጉሥ ከእሱ [ከሰሜኑ ንጉሥ] ጋር ይጋፋል።”—ዳን. 11:40

      መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ

      ማስተዋወቂያa

      1. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምን ይገልጽልናል?

      በቅርቡ የይሖዋ ሕዝቦች ምን ያጋጥማቸዋል? የዚህን ጥያቄ መልስ መገመት አያስፈልገንም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሁላችንንም ስለሚነኩ ወሳኝ ክንውኖች ፍንጭ ይሰጠናል። በተለይ አንድ ትንቢት፣ በምድር ላይ የሚነሱ አንዳንድ ኃያላን መንግሥታት ምን እንደሚያደርጉ ይገልጽልናል። በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ይህ ትንቢት፣ ተቀናቃኝ ስለሆኑ ሁለት የፖለቲካ ኃይሎች ማለትም ስለ ሰሜኑ ንጉሥና ስለ ደቡቡ ንጉሥ ይናገራል። የዚህ ትንቢት አብዛኛው ክፍል ፍጻሜውን አግኝቷል፤ በመሆኑም የቀረው የትንቢቱ ክፍልም እንደሚፈጸም መተማመን እንችላለን።

      2. በዘፍጥረት 3:15 እንዲሁም በራእይ 11:7 እና 12:17 ላይ በተገለጸው መሠረት የዳንኤልን ትንቢት ስንመረምር ግምት ውስጥ ማስገባት ያሉብን ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

      2 በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ለመረዳት፣ ትንቢቱ የሚገልጸው ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላቸው ገዢዎችና መንግሥታት ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ደግሞም የአምላክ አገልጋዮች ከዓለም ሕዝብ አንጻር ሲታዩ ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ በዓለም ላይ የሚፈጸሙት ወሳኝ ክንውኖች በእጅጉ ይነኳቸዋል። ለምን? ምክንያቱም የሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ሥርዓት ዋነኛ ዓላማ፣ የይሖዋንና የኢየሱስን አገልጋዮች ድል መንሳት ነው። (ዘፍጥረት 3:15⁠ን፣ ራእይ 11:7⁠ን እና 12:17⁠ን አንብብ።) ይህን የዳንኤል ትንቢት ስንመረምር ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ሌላው ነገር፣ ትንቢቱ በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ትንቢቶች ጋር መስማማት ያለበት መሆኑን ነው። ደግሞም የዳንኤልን ትንቢት በትክክል መረዳት የምንችለው ከሌሎች የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች ጋር አያይዘን ካየነው ብቻ ነው።

      3. በዚህና በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

      3 እነዚህን ነጥቦች በአእምሯችን ይዘን በዳንኤል 11:25-39 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንመረምራለን። ከ1870 እስከ 1991 ባሉት ዓመታት የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ የነበሩት እነማን እንደሆኑ እናያለን፤ በተጨማሪም የዚህን ትንቢት የተወሰነ ክፍል በምንረዳበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ደግሞ ከዳንኤል 11:40 እስከ 12:1⁠ን እንመረምራለን፤ እንዲሁም ይህ የትንቢቱ ክፍል ከ1990ዎቹ ዓመታት አንስቶ እስከ አርማጌዶን ጦርነት ድረስ ስላለው ጊዜ ምን እንደሚገልጽ የጠራ ግንዛቤ እናገኛለን። እነዚህን ሁለት ርዕሶች ስታጠና “በፍጻሜው ዘመን የተነሱ ተቀናቃኝ ነገሥታት” የሚለውን ሰንጠረዥ መመልከትህ ጠቃሚ ነው። በመጀመሪያ ግን በዚህ ትንቢት ላይ የተጠቀሱትን ሁለት ነገሥታት ማንነት ማወቅ ስለሚቻልበት መንገድ እንመልከት።

      የሰሜኑን ንጉሥ እና የደቡቡን ንጉሥ ማንነት ማወቅ የሚቻልበት መንገድ

      4. የሰሜኑን ንጉሥ እና የደቡቡን ንጉሥ ማንነት ለማወቅ ጥረት ስናደርግ የትኞቹን ሦስት ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን?

      4 ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ እና “የደቡቡ ንጉሥ” የሚሉት መጠሪያዎች መጀመሪያ ላይ የሚያመለክቱት ከእስራኤል ምድር በስተ ሰሜንና በስተ ደቡብ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎችን ነበር። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? መልእክቱን ለዳንኤል ያደረሰው መልአክ ምን እንዳለ ልብ በል፤ መልአኩ “በሕዝብህ ላይ የሚደርሰውን ነገር አስረዳህ ዘንድ መጥቻለሁ” ብሎት ነበር። (ዳን. 10:14) በ33 ዓ.ም. እስከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ድረስ የአምላክ ሕዝብ የነበረው የእስራኤል ብሔር ነው። ከዚያ ወዲህ ግን ይሖዋ፣ ሕዝቡ አድርጎ የመረጠው የኢየሱስን ታማኝ ደቀ መዛሙርት እንደሆነ ግልጽ አደረገ። በመሆኑም በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘው ትንቢት አብዛኛው ክፍል የሚገልጸው ስለ እስራኤል ብሔር ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ተከታዮች ነው። (ሥራ 2:1-4፤ ሮም 9:6-8፤ ገላ. 6:15, 16) በተጨማሪም የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ ማንነት ሲለዋወጥ ቆይቷል። ያም ቢሆን ሁሉንም የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ። አንደኛ፣ ነገሥታቱ ከአምላክ ሕዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ነበራቸው። ሁለተኛ፣ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ያደረሱት ነገር እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን እንደሚጠሉ ያሳያል። ሦስተኛ፣ በሁለቱ ነገሥታት መካከል የበላይ ለመሆን የሚደረግ ሽኩቻ ነበር።

      5. ከ2ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ባለው ጊዜ ውስጥ የተነሱ የሰሜንና የደቡብ ነገሥታት ነበሩ? አብራራ።

      5 በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የሆነ ጊዜ ላይ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ በሐሰተኛ ክርስቲያኖች እየተዋጠ መጣ፤ እነዚህ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች አረማዊ ትምህርቶችን ማስተማርና በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች መሸሸግ ጀመሩ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ በቡድን ሆነው ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች በምድር ላይ አልነበሩም። በእንክርዳድ የተመሰለው የሐሰት ክርስትና የተስፋፋ ሲሆን እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይቶ ማወቅ አይቻልም ነበር። (ማቴ. 13:36-43) ይህን ማወቃችን ምን ጥቅም አለው? ስለ ሰሜኑና ስለ ደቡቡ ንጉሥ የሚገልጸው ትንቢት ከ2ኛው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ የተነሱትን ገዢዎች ወይም መንግሥታት ሊያመለክት እንደማይችል ይጠቁመናል። ምክንያቱም በዚህ ወቅት እነዚህ ነገሥታት ሊያጠቁት የሚችሉት የአምላክ አገልጋዮች ቡድን አልነበረም።b ሆኖም የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በድጋሚ ብቅ እንደሚሉ መጠበቅ እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

      6. የአምላክ ሕዝቦች ማንነት እንደገና የታወቀው መቼ ነበር? አብራራ።

      6 ከ1870 አንስቶ የአምላክ ሕዝቦች በቡድን ሆነው መደራጀት ጀመሩ። ቻርልስ ቴዝ ራስል እና አጋሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ያቋቋሙት በዚህ ዓመት ነው። ወንድም ራስል እና የቅርብ አጋሮቹ፣ መሲሐዊው መንግሥት ከመቋቋሙ በፊት ‘መንገድ እንደሚጠርግ’ በትንቢት የተነገረለት መልእክተኛ ሆነዋል። (ሚል. 3:1) የአምላክ ሕዝቦች ማንነት እንደገና ታወቀ! ታዲያ በዚህ ጊዜ በአምላክ አገልጋዮች ላይ ተጽዕኖ ያደረጉ የዓለም የፖለቲካ ኃይሎች ነበሩ? እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን ማስረጃዎች እንመልከት።

      የደቡቡ ንጉሥ ማን ነው?

      7. ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የደቡቡ ንጉሥ የነበረው ማን ነው?

      7 በ1870 ብሪታንያ በግዛቷ ስፋትና በወታደራዊ ኃይሏ ብርታት ተወዳዳሪ የሌላት ሆና ነበር። በወቅቱ የነበረው የብሪታንያ መንግሥት ሦስት ቀንዶችን ባሸነፈ አንድ ትንሽ ቀንድ ተመስሏል፤ ሦስቱ ቀንዶች ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ኔዘርላንድስ ናቸው። (ዳን. 7:7, 8) አንደኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ በኋላም እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የደቡቡ ንጉሥ የነበረው የብሪታንያ መንግሥት ነው። በዚሁ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ በኢኮኖሚ አንደኛውን ቦታ ይዛ የነበረ ሲሆን ከብሪታንያ ጋር የጠበቀ አጋርነት መመሥረት ጀምራ ነበር።

      8. በመጨረሻዎቹ ቀናት የደቡቡ ንጉሥ የሆነው ማን ነው?

      8 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ ከፍተኛ ኃይል ያለው ወታደራዊ ጥምረት መሠረቱ። በዚህ ጊዜ ብሪታንያና የቀድሞ ቅኝ ግዛቷ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኑ። ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው ይህ ንጉሥ “እጅግ ታላቅና ኃያል የሆነ ሠራዊት” ሰብስቦ ነበር። (ዳን. 11:25) በመጨረሻዎቹ ቀናት የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል የደቡቡ ንጉሥ ሆኖ ቀጥሏል።c ይሁንና የሰሜኑ ንጉሥ የሆነውስ ማን ነው?

      የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን አስመልክቶ የተነገረ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት

      የደቡቡ ንጉሥ የሆነው የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ በተለያየ መንገድ ተገልጿል። ከእነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

      • የብረትና የሸክላ እግር።

        የብረት እና የሸክላ እግር (ዳን. 2:41-43)

      • በራሱ ላይ ቀንዶች ያሉት አውሬ። በቀንዶቹ መካከል ዓይኖች እና አፍ ያሉት ትንሽ ቀንድ ወጣ።

        በአንድ የሚያስፈራ አውሬ ራስ ላይ የወጣ ቀንድ (ዳን. 7:7, 8)

      • አሥር ቀንዶች እና ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ።

        የአውሬው ሰባተኛ ራስ (ራእይ 13:1)

      • ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ።

        ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ (ራእይ 13:11-15)

      • የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን የሚወክሉ የመንግሥት ሕንጻዎች።

        “ሐሰተኛው ነቢይ” (ራእይ 19:20)

      የሰሜኑ ንጉሥ በድጋሚ ብቅ አለ

      9. የሰሜኑ ንጉሥ በድጋሚ ብቅ ያለው መቼ ነው? ዳንኤል 11:25 ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነው?

      9 በ1871 ማለትም ራስል እና አጋሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ካቋቋሙ ከአንድ ዓመት በኋላ የሰሜኑ ንጉሥ በድጋሚ ብቅ አለ። በዚህ ዓመት ኦቶ ቮን ቢስማርክ፣ የተለያዩ ክልሎችን አንድ በማድረግ ኃያል የሆነ የጀርመን ግዛት እንዲቋቋም አደረገ። የጀርመኑ ንጉሥ ቀዳማዊ ቪልሄልም የዚህ ግዛት የመጀመሪያ ንጉሠ ነገሥት ሆነ፤ ንጉሠ ነገሥቱ፣ ቢስማርክን የመጀመሪያው መራሄ መንግሥት አድርጎ ሾመው።d በቀጣዮቹ ጥቂት አሥርተ ዓመታት የጀርመን መንግሥት፣ በአፍሪካ እና በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ የሚገኙ አገሮችን በቅኝ ግዛት የተቆጣጠረ ሲሆን ብሪታንያን መቀናቀን ጀምሮ ነበር። (ዳንኤል 11:25⁠ን አንብብ።) የጀርመን ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ ጠንካራ ሠራዊት የገነባ ከመሆኑም ሌላ የባሕር ኃይሉ በዓለም ላይ ሁለተኛውን ደረጃ ይዞ ነበር። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን መንግሥት ይህን ሠራዊት ጠላቶቹን ለማጥቃት ተጠቅሞበታል።

      10. ዳንኤል 11:25ለ, 26 ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

      10 በመቀጠል ዳንኤል የጀርመን ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛትና የገነባው ወታደራዊ ኃይል ምን እንደሚደርስበት ገልጿል። ትንቢቱ፣ የሰሜኑን ንጉሥ በተመለከተ “መቋቋም አይችልም” በማለት ይናገራል። ለምን? ምክንያቱም ‘ሴራ ይጠነስሱበታል’፤ “የእሱን ምርጥ ምግብ የሚበሉም ለውድቀት ይዳርጉታል።” (ዳን. 11:25ለ, 26ሀ) በዳንኤል ዘመን “[ለንጉሡ] ከሚቀርበው ምርጥ ምግብ” ከሚበሉት መካከል “ንጉሡን ለማገልገል” የተሰማሩ ሰዎች ይገኙበታል። (ዳን. 1:5) ታዲያ ይህ ትንቢት የሚናገረው ስለ እነማን ነው? ትንቢቱ የሚናገረው የንጉሠ ነገሥቱን ጄኔራሎች እና የጦር አማካሪዎች ጨምሮ በጀርመን ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ስለነበራቸው ሰዎች ነው፤ እነዚህ ሰዎች ውሎ አድሮ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዙ እንዲወድቅ አድርገዋል።e ትንቢቱ፣ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዙ እንደሚወድቅ ከመግለጽ ባለፈ የሰሜኑ ንጉሥ ከደቡቡ ንጉሥ ጋር የሚያደርገው ጦርነት ውጤት ምን እንደሚሆን ይናገራል። ስለ ሰሜኑ ንጉሥ ሲናገር “ሠራዊቱ ተጠራርጎ ይወሰዳል፤ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ” ይላል። (ዳን. 11:26ለ) ልክ በትንቢት በተነገረው መሠረት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ሠራዊት ‘ተጠራርጎ የተወሰደ’ ሲሆን ብዙ ሰዎች ‘ተገድለው ወድቀዋል።’ ይህ ጦርነት እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከተካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ በርካታ ሰው ያለቀበት ነው።

      11. የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ ምን አድርገዋል?

      11 ዳንኤል 11:27, 28 እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ስለሚፈጸመው ክንውን ሲናገር የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ “በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እርስ በርስ ውሸት ይነጋገራሉ” ይላል። በተጨማሪም የሰሜኑ ንጉሥ ‘ብዙ ንብረት እንደሚሰበስብ’ ይናገራል። እነዚህ የትንቢቱ ክፍሎችም በትክክል ተፈጽመዋል። ጀርመን እና ብሪታንያ ሰላም እንደሚፈልጉ እርስ በርሳቸው ቢነጋገሩም በ1914 ጦርነቱ ሲፈነዳ ይህ ውሸት መሆኑ ተረጋግጧል። በተጨማሪም ከ1914 በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት የጀርመን አገዛዝ ሀብት ያካበተ ሲሆን በዓለም ላይ በኢኮኖሚ ረገድ ሁለተኛውን ደረጃ ይዞ ነበር። በኋላ ግን በዳንኤል 11:29 እና በቁጥር 30 የመጀመሪያው ሐሳብ ላይ በትንቢት እንደተገለጸው የጀርመን መንግሥት ከደቡቡ ንጉሥ ጋር ባደረገው ውጊያ ተሸንፏል።

      ነገሥታቱ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ

      12. በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሰሜኑም ሆነ የደቡቡ ንጉሥ ምን አድርገዋል?

      12 ከ1914 ወዲህ ሁለቱ ነገሥታት እርስ በርስ የሚያደርጉትን ሽኩቻም ሆነ በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት አፋፍመው ቀጥለዋል። ለምሳሌ ያህል በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን መንግሥትም ሆነ የብሪታንያ መንግሥት፣ በጦርነቱ ሰው ለመግደል ፈቃደኛ ያልሆኑ የአምላክ አገልጋዮችን አሳድደዋል። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥትም ቢሆን የስብከቱን ሥራ የሚመሩት ወንድሞች እስር ቤት እንዲጣሉ አድርጓል። ይህም በራእይ 11:7-10 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ ነው።

      13. በ1930ዎቹ ዓመታትና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሰሜኑ ንጉሥ ምን አድርጓል?

      13 ከዚያም በ1930ዎቹ ዓመታት፣ በተለይም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሰሜኑ ንጉሥ የአምላክን ሕዝቦች ያለምንም ርኅራኄ አሳድዷል። የናዚ ፓርቲ ጀርመንን ከተቆጣጠረ በኋላ ሂትለርና ተከታዮቹ በአምላክ ሕዝቦች ሥራ ላይ እገዳ ጥለዋል። ተቃዋሚዎች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮችን ገድለዋል፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩትን ወደ ማጎሪያ ካምፖች ልከዋል። ዳንኤል ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። የሰሜኑ ንጉሥ፣ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን በሕዝብ ፊት ለማወደስ በሚያከናውኑት ሥራ ላይ ከፍተኛ ገደብ በመጣሉ ‘መቅደሱን አርክሷል’ እንዲሁም ‘የዘወትሩን መሥዋዕት አስቀርቷል።’ (ዳን. 11:30ለ, 31ሀ) እንዲያውም የጀርመን መሪ የነበረው ሂትለር የአምላክ ሕዝቦችን ከአገሪቱ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ ዝቶ ነበር።

      አዲስ የሰሜን ንጉሥ ተነሳ

      14. ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሰሜኑ ንጉሥ ሆኖ የተነሳው ማን ነው? አብራራ።

      14 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሶቪየት ኅብረት የኮሚኒስት መንግሥት በጀርመን አገዛዝ ሥር የነበረውን ሰፊ ግዛት በመቆጣጠር የሰሜኑ ንጉሥ ሆነ። የሶቪየት ኅብረት መንግሥት የአምባገነኑን የናዚ አገዛዝ አካሄድ ተከትሏል፤ ይኸውም ከመንግሥት ይልቅ ለእውነተኛው አምላክ ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎችን አሳድዷል።

      15. ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ የሰሜኑ ንጉሥ ምን አድርጓል?

      15 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ብዙም ሳይቆይ፣ ሶቪየት ኅብረትንና አጋሮቹን የሚያመለክተው አዲሱ የሰሜን ንጉሥ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመረ። በራእይ 12:15-17 ላይ በሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ይህ ንጉሥ በስብከቱ ሥራችን ላይ እገዳ የጣለ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች በግዞት እንዲወሰዱ አድርጓል። በመጨረሻዎቹ ቀናት በሙሉ የሰሜኑ ንጉሥ የአምላክ ሕዝቦችን ሥራ ለማስቆም የስደት “ወንዝ” ሲለቅ ቆይቷል፤ ሆኖም ጥረቱ አልተሳካለትም።f

      16. በዳንኤል 11:37-39 ላይ በትንቢት በተገለጸው መሠረት የሶቪየት ኅብረት መንግሥት ምን አድርጓል?

      16 ዳንኤል 11:37-39⁠ን አንብብ። ልክ በዚህ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው የሰሜኑ ንጉሥ “ለአባቶቹ አምላክ” ምንም ቦታ አልሰጠም። ይህን ያሳየው እንዴት ነው? የሶቪየት ኅብረት መንግሥት፣ ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ ሃይማኖታዊ ተቋማት የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ለማዳከም ጥረት አድርጓል፤ ዓላማውም ሃይማኖትን ማጥፋት ነበር። የሶቪየት መንግሥት ይህን ግቡን ለማሳካት ሲል ገና በ1918 ትምህርት ቤቶችንና ሃይማኖትን የሚመለከት ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፤ ይህም ‘አምላክ የለም’ የሚለው ትምህርት ከጊዜ በኋላ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲሰጥ መንገድ ከፍቷል። ታዲያ ይህ የሰሜን ንጉሥ ‘ለምሽጎች አምላክ ክብር የሰጠው’ እንዴት ነው? የሶቪየት ኅብረት መንግሥት፣ ሠራዊቱን ለመገንባትና ግዛቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የኑክሌር መሣሪያዎችን ለማምረት ከፍተኛ ወጪ አውጥቷል። የሰሜኑ ንጉሥም ሆነ የደቡቡ ንጉሥ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚጨርሱ የጦር መሣሪያዎችን ቀስ በቀስ አከማችተዋል።

      ያልተለመደ ትብብር

      17. ‘ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር’ ምንድን ነው?

      17 የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ የተባበሩበት አንድ ቁልፍ ጉዳይ አለ፤ ይህም ‘ጥፋት የሚያመጣውን ርኩስ ነገር’ ማቋቋም ነው። (ዳን. 11:31) “ርኩስ ነገር” የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው።

      18. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ርኩስ ነገር” ተብሎ የተገለጸው ለምንድን ነው?

      18 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ርኩስ ነገር” ተብሎ የተገለጸው የአምላክ መንግሥት ብቻ ሊያከናውን የሚችለውን ነገር እንደሚያደርግ ይኸውም ዓለም አቀፍ ሰላም እንደሚያመጣ ስለሚናገር ነው። ይህ ርኩስ ነገር ‘ጥፋት እንደሚያመጣ’ ትንቢቱ አክሎ ተናግሯል፤ እንዲህ የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ሁሉንም የሐሰት ሃይማኖቶች በማጥፋት ረገድ ቁልፍ ሚና ስለሚጫወት ነው።—“በፍጻሜው ዘመን የተነሱ ተቀናቃኝ ነገሥታት” የሚለውን ሰንጠረዥ ተመልከት።

      ይህን ታሪክ ማወቃችን ምን ይጠቅመናል?

      19-20. (ሀ) ይህን ታሪክ ማወቃችን ምን ይጠቅመናል? (ለ) በቀጣዩ ርዕስ ላይ የየትኛውን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን?

      19 ይህን ታሪክ ማወቃችን አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ዳንኤል የሰሜኑን ንጉሥና የደቡቡን ንጉሥ አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት ከ1870ዎቹ አንስቶ እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ፍጻሜውን እንዳገኘ ያረጋግጥልናል። በመሆኑም የቀረው የትንቢቱ ክፍልም እንደሚፈጸም መተማመን እንችላለን።

      20 ሶቪየት ኅብረት በ1991 ፈርሷል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ የሰሜኑ ንጉሥ ማን ነው? ቀጣዩ ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።

      ምን ብለህ ትመልሳለህ?

      • ‘የሰሜኑን ንጉሥ’ እና ‘የደቡቡን ንጉሥ’ ማንነት ለማወቅ ጥረት ስናደርግ የትኞቹን ሦስት ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን?

      • ከ1870ዎቹ አንስቶ እስከ 1991 ባለው ጊዜ ውስጥ የሰሜን ንጉሥ እና የደቡብ ንጉሥ ሆነው የተነሱት እነማን ናቸው?

      • ይህን ታሪክ ማወቃችን ምን ይጠቅመናል?

      መዝሙር 128 እስከ መጨረሻው መጽናት

      a ዳንኤል ‘የደቡቡን ንጉሥ’ እና ‘የሰሜኑን ንጉሥ’ አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ እንደሆነ የሚጠቁሙ ማስረጃዎችን እያየን ነው። ትንቢቱ እየተፈጸመ መሆኑን እርግጠኛ እንድንሆን የሚያደርገን ምንድን ነው? እንዲሁም የዚህን ትንቢት ዝርዝር ጉዳዮች መረዳት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

      b እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ምክንያት አንጻር የሮም ንጉሠ ነገሥት ኦሬሊየን (270-275 ዓ.ም.) ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ እንደሆነ፣ ንግሥት ዘኖቢያ (267-272 ዓ.ም.) ደግሞ “የደቡቡ ንጉሥ” እንደሆነች መናገራችን ትክክል አይመስልም። ይህ ሐሳብ የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 13 እና 14 ላይ በወጣው ትምህርት ላይ የተደረገ ማስተካከያ ነው።

      c “የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን አስመልክቶ የተነገረ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      d በ1890 ዳግማዊ ቄሳር ቪልሄልም፣ ቢስማርክን ሥልጣኑን እንዲለቅ አስገድዶታል።

      e እነዚህ ሰዎች፣ የንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዙን ውድቀት ለማፋጠን የተለያዩ ነገሮችን አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ለንጉሡ የሚሰጡትን ድጋፍ አቁመዋል፤ ስለ ጦርነቱ በሚስጥር ሊያዙ የሚገቡ መረጃዎችን አውጥተዋል፤ እንዲሁም ንጉሡ ሥልጣኑን እንዲለቅ ጫና አሳድረዋል።

      f በዳንኤል 11:34 ላይ እንደተገለጸው በሰሜኑ ንጉሥ ሥር ያሉ ክርስቲያኖች ከስደት የተወሰነ እፎይታ ያገኙበት ወቅት ነበር። ለምሳሌ፣ ሶቪየት ኅብረት በ1991 ሲፈርስ ስደቱ ጋብ ብሎላቸዋል።

  • በዛሬው ጊዜ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ማን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020 | ግንቦት
    • የጥናት ርዕስ 20

      በዛሬው ጊዜ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ማን ነው?

      “ወደ ፍጻሜው ይመጣል፤ የሚረዳውም አይኖርም።”—ዳን. 11:45

      መዝሙር 95 ብርሃኑ እየደመቀ ነው

      ማስተዋወቂያa

      1-2. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

      የምንኖረው በዚህ ሥርዓት የመጨረሻዎቹ ቀናት ማብቂያ ላይ እንደሆነ የሚጠቁሙ ማስረጃዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በግልጽ እየታዩ ነው። በቅርቡ ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የአምላክን መንግሥት የሚቃወሙ መንግሥታትን በሙሉ ያጠፋሉ። እስከዚያ ድረስ ግን የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ እርስ በርስ መዋጋታቸውንና የአምላክን ሕዝብ ማጥቃታቸውን ይቀጥላሉ።

      2 በዚህ ርዕስ ላይ፣ ከዳንኤል 11:40 እስከ 12:1 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ትንቢት እንመረምራለን። በአሁኑ ወቅት የሰሜኑ ንጉሥ ማን እንደሆነ እናያለን፤ በተጨማሪም ከፊታችን የሚጠብቁንን ፈተናዎች በልበ ሙሉነት መጋፈጥ እንችላለን የምንልባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን።

      አዲስ የሰሜን ንጉሥ ብቅ አለ

      3-4. በዛሬው ጊዜ የሰሜኑ ንጉሥ ማን ነው? አብራራ።

      3 ሶቪየት ኅብረት በ1991 ከፈራረሰ በኋላ ሰፊ በሆነው ግዛቱ የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች “መጠነኛ እርዳታ” ማለትም ለተወሰነ ጊዜ ነፃነት አግኝተው ነበር። (ዳን. 11:34) በመሆኑም በነፃነት መስበክ ችለው ነበር፤ በሶቪየት ኅብረት ሥር በነበሩት አገሮች ውስጥ የአስፋፊዎች ቁጥር ብዙም ሳይቆይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሆነ። ሆኖም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሩሲያ እና አጋሮቿ የሰሜኑ ንጉሥ ሆነው ብቅ አሉ። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አንድ መንግሥት የሰሜኑ ንጉሥ ወይም የደቡቡ ንጉሥ እንዲባል የሚከተሉትን ሦስት መሥፈርቶች ማሟላት አለበት፦ (1) ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል፤ (2) ድርጊቱ፣ ይሖዋንና ሕዝቦቹን እንደሚጠላ ሊያሳይ ይገባል፤ (3) ከተቀናቃኙ ንጉሥ ጋር መፎካከር አለበት።

      4 በዛሬው ጊዜ፣ ሩሲያና አጋሮቿ የሰሜኑ ንጉሥ ናቸው የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት። (1) ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፤ በስብከቱ ሥራ ላይ እገዳ ጥለዋል፤ እንዲሁም በግዛታቸው ሥር በሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ላይ ስደት እያደረሱ ነው። (2) እንዲህ ማድረጋቸው ይሖዋን እና ሕዝቡን እንደሚጠሉ ያሳያል። (3) የደቡቡ ንጉሥ ከሆነው ከአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ጋር እየተፎካከሩ ነው። ሩሲያና አጋሮቿ፣ የሰሜኑ ንጉሥ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ምን ነገር እንዳደረጉ እስቲ እንመልከት።

      የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ እርስ በርስ መጋፋታቸውን ይቀጥላሉ

      5. ዳንኤል 11:40-43 የሚገልጸው ስለ የትኛው ጊዜ ነው? በዚህ ጊዜስ ምን ይፈጸማል?

      5 ዳንኤል 11:40-43⁠ን አንብብ። ይህ የትንቢቱ ክፍል፣ በፍጻሜው ዘመን የሚከናወነውን ነገር ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል። ዘገባው በሰሜኑ ንጉሥና በደቡቡ ንጉሥ መካከል ስለሚኖረው ሽኩቻ ይናገራል። ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው፣ በፍጻሜው ዘመን የደቡቡ ንጉሥ ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር “ይጋፋል” ወይም “ይጣላል።”—ዳን. 11:40 ግርጌ

      6. ሁለቱ ነገሥታት መጋፋታቸውን እንደቀጠሉ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

      6 የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ፣ በዓለም ላይ ኃያል መንግሥት ለመሆን የሚያደርጉትን ሽኩቻ አያቆሙም። ለምሳሌ ያህል፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሶቪየት ኅብረት እና አጋሮቹ በአብዛኛው የአውሮፓ ክፍል ላይ ተጽዕኖ ባሳደሩበት ወቅት ምን እንደተፈጠረ እንመልከት። የሰሜኑ ንጉሥ ያደረገው ነገር፣ የደቡቡ ንጉሥ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የተባለ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ኅብረት እንዲመሠርት ምክንያት ሆኗል። የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ፣ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው የጦር መሣሪያ በማከማቸት እርስ በርስ መፎካከራቸውን ቀጥለዋል። በተጨማሪም በአፍሪካ፣ በእስያና በደቡብ አሜሪካ በተቀሰቀሱ ዓመፆች ውስጥ ተቃራኒ ቡድኖችን በመደገፍ በእጅ አዙር ተዋግተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ሩሲያ እና አጋሮቿ በዓለም ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እየጨመረ መጥቷል። ከዚህም ሌላ በደቡቡ ንጉሥ ላይ የሳይበር ጥቃት (በኮምፒውተር አማካኝነት የሚሰነዘር ጥቃት) ሰንዝረዋል። ሁለቱ ነገሥታት፣ ኢኮኖሚያቸውንና የፖለቲካ ሥርዓታቸውን የሚጎዳ የኮምፒውተር ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው በመግለጽ አንዳቸው ሌላውን ሲወነጅሉ ቆይተዋል። በተጨማሪም ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው የሰሜኑ ንጉሥ የአምላክን ሕዝቦች ማጥቃቱን ቀጥሏል።—ዳን. 11:41

      የሰሜኑ ንጉሥ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ይገባል

      7. ‘ውብ የሆነችው ምድር’ የቷ ነች?

      7 ዳንኤል 11:41 የሰሜኑ ንጉሥ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር እንደሚገባ’ ይናገራል። ይህች ምድር የቷ ነች? በጥንት ዘመን የእስራኤል ምድር “ከሌሎች አገሮች ሁሉ ይበልጥ ውብ” ተደርጋ ትቆጠር ነበር። (ሕዝ. 20:6) ሆኖም ይህችን ምድር ልዩ ያደረጋት የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል የነበረች መሆኗ ነው። በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ወዲህ ግን ይህች “ምድር” ቃል በቃል አንድን ቦታ ልታመለክት አትችልም፤ ምክንያቱም የይሖዋ ሕዝቦች የሚገኙት በመላው ዓለም ነው። በዛሬው ጊዜ፣ ‘ውብ የሆነችው ምድር’ የሚለው አገላለጽ የይሖዋን ሕዝቦች መንፈሳዊ ግዛት የሚያመለክት ነው፤ ይህ መንፈሳዊ ግዛት፣ የይሖዋ ሕዝቦች በስብሰባዎችና በመስክ አገልግሎት ላይ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ ያጠቃልላል።

      8. የሰሜኑ ንጉሥ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ የገባው እንዴት ነው?

      8 በመጨረሻዎቹ ቀናት፣ የሰሜኑ ንጉሥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብቷል። በናዚዎች ይመራ የነበረው የጀርመን መንግሥት የሰሜን ንጉሥ በነበረበት ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ መመልከት ይቻላል፤ ይህ የሰሜን ንጉሥ በተለይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአምላክን ሕዝቦች በማሳደድና በመግደል ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብቷል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሰሜን ንጉሥ የሆነው ሶቪየት ኅብረትም ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብቷል፤ ይህን ያደረገው የአምላክን ሕዝቦች በማሳደድ እና በግዞት እንዲሄዱ በማድረግ ነው።

      9. ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ፣ ሩሲያ እና አጋሮቿ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ የገቡት እንዴት ነው?

      9 ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ሩሲያ እና አጋሮቿ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብተዋል። ይህን ያደረጉት እንዴት ነው? በ2017 ይህ የሰሜን ንጉሥ፣ በይሖዋ ሕዝቦች ሥራ ላይ እገዳ የጣለ ከመሆኑም ሌላ አንዳንድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን አስሯል። ከዚህም ሌላ አዲስ ዓለም ትርጉምን ጨምሮ ጽሑፎቻችንን አግዷል። በተጨማሪም በሩሲያ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሯችንን እንዲሁም የጉባኤ ስብሰባና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን ወርሷል። ይህ ከሆነ በኋላ በ2018 የበላይ አካሉ፣ ሩሲያና አጋሮቿ የሰሜኑ ንጉሥ መሆናቸውን ግልጽ አደረገ። የይሖዋ ሕዝቦች፣ ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም በሰብዓዊ መንግሥታት ላይ ለማመፅ ወይም እነሱን ለመገልበጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ ለመካፈል ፈቃደኛ አይሆኑም። ከዚህ ይልቅ ‘በሥልጣን ላይ ላሉት ሁሉ’ እንድንጸልይ የሚያበረታታውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ፤ በተለይም እነዚህ መንግሥታት የአምልኮ ነፃነታችንን ሊነኩ የሚችሉ ውሳኔዎች በሚያደርጉበት ወቅት እንዲህ ማድረግ አለብን።—1 ጢሞ. 2:1, 2

      የሰሜኑ ንጉሥ የደቡቡን ንጉሥ ያሸንፈዋል?

      10. የሰሜኑ ንጉሥ የደቡቡን ንጉሥ ያሸንፈዋል? አብራራ።

      10 በዳንኤል 11:40-45 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዋነኝነት የሚያተኩረው የሰሜኑ ንጉሥ በሚያደርገው ነገር ላይ ነው። ታዲያ ይህ፣ የሰሜኑ ንጉሥ የደቡቡን ንጉሥ እንደሚያሸንፈው የሚጠቁም ነው? አይደለም። የደቡቡ ንጉሥ፣ ይሖዋና ኢየሱስ በአርማጌዶን ጦርነት ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት በሚያጠፉበት ወቅት “በሕይወት” ይኖራል። (ራእይ 19:20) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በዳንኤልና በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኙት ትንቢቶች ምን እንደሚጠቁሙ እስቲ እንመልከት።

      ከተራራ ተፈንቅሎ የመጣው ድንጋይ የግዙፉን ምስል እግሮች መታ።

      በድንጋይ የተመሰለው የአምላክ መንግሥት፣ በግዙፉ ምስል የተወከሉትን ሰብዓዊ መንግሥታት በአርማጌዶን ጦርነት ያጠፋል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

      11. ዳንኤል 2:43-45 ምን ይጠቁማል? (ሽፋኑን ተመልከት።)

      11 ዳንኤል 2:43-45⁠ን አንብብ። ነቢዩ ዳንኤል፣ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላቸውና በተከታታይ ስለሚነሱ ሰብዓዊ መንግሥታት ገልጿል። እነዚህ መንግሥታት፣ በግዙፉ ምስል የተለያዩ ክፍሎች ተመስለዋል። ከእነዚህ ሰብዓዊ መንግሥታት የመጨረሻው፣ የብረትና የሸክላ ቅልቅል በሆነው የምስሉ እግር ተመስሏል። የምስሉ እግር፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን ያመለክታል። የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን ለማጥፋት እርምጃ በሚወስድበት ወቅት የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት በሥልጣን ላይ እንደሚሆን ትንቢቱ ይጠቁማል።

      12. የአውሬው ሰባተኛ ራስ ማንን ያመለክታል? ይህስ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

      12 ሐዋርያው ዮሐንስም በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ተጽዕኖ ስላሳደሩና በተከታታይ ስለሚነሱ የዓለም ኃያል መንግሥታት ገልጿል። ዮሐንስ፣ እነዚህን መንግሥታት ሰባት ራስ ባለው አውሬ መስሏቸዋል። የዚህ አውሬ ሰባተኛ ራስ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን ያመለክታል። ይህ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም አውሬው ሌላ ራስ እንደሚያወጣ የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም። ክርስቶስና ሰማያዊ ሠራዊቱ ይህን ሰባተኛ ራስ ጨምሮ አውሬውን ለማጥፋት እርምጃ በሚወስዱበት ወቅት ሰባተኛው ራስ በሥልጣን ላይ ይሆናል።b—ራእይ 13:1, 2፤ 17:13, 14

      የሰሜኑ ንጉሥ በቅርቡ ምን ያደርጋል?

      13-14. ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ ማን ነው? የአምላክን ሕዝቦች ለማጥፋት የሚያነሳሳውስ ምን ሊሆን ይችላል?

      13 የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ ከመጥፋታቸው በፊት ምን እንደሚፈጠር የሕዝቅኤል ትንቢት አንዳንድ መረጃ ይሰጠናል። በሕዝቅኤል 38:10-23፣ በዳንኤል 2:43-45፤ 11:44 እስከ 12:1 እንዲሁም በራእይ 16:13-16, 21 ላይ የሚገኙት ትንቢቶች የሚናገሩት ስለ ተመሳሳይ ጊዜ እና ክንውኖች ይመስላል፤ ይህ እውነት ከሆነ፣ የሚከተሉት ነገሮች ይፈጸማሉ ብለን መጠበቅ እንችላለን።

      14 ታላቁ መከራ ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ‘የዓለም ነገሥታት’ ጥምረት ይፈጥራሉ። (ራእይ 16:13, 14፤ 19:19) ይህን ጥምረት፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ ብለው ይጠሩታል። (ሕዝ. 38:2) ጥምረት የፈጠሩት ብሔራት፣ የአምላክን ሕዝቦች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ይህን ጥቃት እንዲሰነዝሩ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ በዚህ ጊዜ ስለሚፈጸመው ነገር ሲናገር እጅግ ታላቅ የበረዶ ድንጋይ በአምላክ ጠላቶች ላይ እንደሚወርድ ገልጿል። ይህ ምሳሌያዊ በረዶ፣ የይሖዋ ሕዝቦች የሚያውጁትን ከባድ የፍርድ መልእክት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። የማጎጉ ጎግ የአምላክን ሕዝቦች ከምድር ገጽ ለማጥፋት የሚነሳው ይህ መልእክት ስለሚያስቆጣው ሊሆን ይችላል።—ራእይ 16:21

      15-16. (ሀ) ዳንኤል 11:44, 45 የሚገልጸው ስለ የትኞቹ ክንውኖች ሊሆን ይችላል? (ለ) የሰሜኑ ንጉሥም ሆነ ሌሎቹ የማጎጉ ጎግ አባላት ምን ይጠብቃቸዋል?

      15 የአምላክ ሕዝቦች የሚያውጁት ይህ ከባድ መልእክትና የአምላክ ጠላቶች የሚሰነዝሩት የመጨረሻ ጥቃት በዳንኤል 11:44, 45 ላይ በትንቢት የተገለጹት ክንውኖች ሊሆኑ ይችላሉ። (ጥቅሱን አንብብ።) ዳንኤል በዚህ ትንቢት ላይ እንደገለጸው “ከምሥራቅና ከሰሜን የሚመጣ ወሬ [የሰሜኑን ንጉሥ] ይረብሸዋል፤” በመሆኑም “በታላቅ ቁጣ ይወጣል።” የሰሜኑ ንጉሥ የሚወጣው “ብዙዎችን ለመደምሰስ” ነው። በጥቅሱ ላይ “ብዙዎች” የተባሉት የይሖዋ ሕዝቦች ሳይሆኑ አይቀሩም።c ዳንኤል በዚህ ትንቢት ላይ እየተናገረ ያለው፣ የአምላክን ሕዝቦች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ስለሚሰነዘረው ጥቃት ይመስላል።

      16 የሰሜኑ ንጉሥ ከሌሎቹ የዓለም መንግሥታት ጋር በመሆን የሚሰነዝረው ይህ ጥቃት ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ቁጣ ይቀሰቅሰዋል፤ ከዚያም የአርማጌዶን ጦርነት ይጀምራል። (ራእይ 16:14, 16) በዚያን ጊዜ የሰሜኑ ንጉሥም ሆነ ሌሎቹ የማጎጉ ጎግ አባላት ወደ ፍጻሜያቸው ይመጣሉ፤ የሰሜኑን ንጉሥ “የሚረዳውም አይኖርም።”—ዳን. 11:45

      ነጭ ፈረስ እየጋለበ ያለው ኢየሱስ ቀስቱን ለመወርወር ተዘጋጅቶ። ሌሎች መላእክትም ነጭ ፈረስ እየጋለቡ ሲሆን ሰይፎች ይዘዋል።

      ኢየሱስ ክርስቶስ እና ሰማያዊ ሠራዊቱ በአርማጌዶን ጦርነት የሰይጣንን ክፉ ዓለም ያጠፋሉ፤ እንዲሁም የአምላክን ሕዝቦች ይታደጋሉ (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

      17. በዳንኤል 12:1 ላይ የተጠቀሰው “ታላቁ አለቃ ሚካኤል” ማን ነው? ምንስ ያደርጋል?

      17 ዳንኤል በጻፈው ዘገባ ላይ የሚገኘው ቀጣዩ ሐሳብ፣ የሰሜኑ ንጉሥና አጋሮቹ ወደ ፍጻሜያቸው የሚመጡበትንና መዳን የምናገኝበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ይሰጠናል። (ዳንኤል 12:1⁠ን አንብብ።) በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ምን ትርጉም አለው? ሚካኤል፣ የንጉሣችን የክርስቶስ ኢየሱስ ሌላ ስም ነው። ሚካኤል ለአምላክ ሕዝቦች ‘መቆም’ የጀመረው መንግሥቱ በ1914 በሰማይ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ነው። በቅርቡ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ደግሞ “ይነሳል” ማለትም ወሳኝ እርምጃ ይወስዳል። ይህ ጦርነት፣ ዳንኤል ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ “የጭንቀት ጊዜ” በማለት የጠራው ወቅት የመጨረሻ ክንውን ይሆናል። ይህ ጦርነትና ከዚያ በፊት ያለው ጊዜ፣ ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ ላይ ባሰፈረው ትንቢት ላይ ‘ታላቁ መከራ’ ተብሎ ተጠርቷል።—ራእይ 6:2፤ 7:14

      ስምህ ‘በመጽሐፍ ላይ ይጻፍ’ ይሆን?

      18. የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ የምንችለው ለምንድን ነው?

      18 የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን፤ ምክንያቱም ዳንኤልም ሆነ ዮሐንስ፣ ይሖዋንና ኢየሱስን የሚያገለግሉ ሁሉ በታሪክ ውስጥ ሆኖ ከማያውቀው ከዚህ የጭንቀት ጊዜ እንደሚተርፉ ገልጸዋል። ዳንኤል፣ ስማቸው ‘በመጽሐፍ ላይ የተጻፈ’ ሁሉ ከጥፋቱ እንደሚተርፉ ተናግሯል። (ዳን. 12:1) ታዲያ ስማችን በዚህ መጽሐፍ ላይ እንዲጻፍ ምን ማድረግ አለብን? የአምላክ በግ በሆነው በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለን በግልጽ ማሳየት ይኖርብናል። (ዮሐ. 1:29) ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን በጥምቀት ማሳየት አለብን። (1 ጴጥ. 3:21) በተጨማሪም ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን በማድረግ የአምላክን መንግሥት እንደምንደግፍ ማሳየት ይኖርብናል።

      19. አሁኑኑ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

      19 በይሖዋና ታማኝ አገልጋዮቹን ባቀፈው ድርጅቱ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ያለብን አሁን ነው። የአምላክን መንግሥት መደገፍ ያለብንም አሁን ነው። እንዲህ ማድረጋችን የአምላክ መንግሥት የሰሜኑን ንጉሥና የደቡቡን ንጉሥ በሚያጠፋበት ወቅት ለመዳን ያስችለናል።

      ምን ብለህ ትመልሳለህ?

      • በዛሬው ጊዜ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ማን ነው?

      • የሰሜኑ ንጉሥ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ የገባው እንዴት ነው?

      • የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ ምን ይገጥማቸዋል?

      መዝሙር 149 የድል መዝሙር

      a በዛሬው ጊዜ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ማን ነው? ወደ ፍጻሜው የሚመጣውስ እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን እምነታችንን ያጠናክርልናል፤ እንዲሁም በቅርቡ ለሚያጋጥሙን ፈተናዎች እንድንዘጋጅ ይረዳናል።

      b ዳንኤል 2:36-45⁠ን እና ራእይ 13:1, 2⁠ን በተመለከተ ዝርዝር ሐሳብ ለማግኘት የሰኔ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 7-19⁠ን ተመልከት።

      c ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የግንቦት 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 29-30⁠ን ተመልከት።

  • በፍጻሜው ዘመን የተነሱ ተቀናቃኝ ነገሥታት
    መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020 | ግንቦት
    • በፍጻሜው ዘመን የተነሱ ተቀናቃኝ ነገሥታት

      በዚህ ሰንጠረዥ ላይ የተጠቀሱ አንዳንድ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ነው። ትንቢቶቹ በሙሉ፣ የምንኖረው ‘በፍጻሜው ዘመን’ እንደሆነ በተለያየ መንገድ ያረጋግጣሉ።—ዳን. 12:4

      የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እንዲሁም ከ1870 እስከ ዛሬ ድረስ የተነሱ የሰሜን እና የደቡብ ነገሥታትን ማንነት የሚያሳይ ሰንጠረዥ።
      • ሰንጠረዥ 1፦ ከ1870 እስከ 1918 ባሉት ዓመታት በተመሳሳይ ጊዜ የተፈጸሙ የፍጻሜው ዘመን ትንቢቶች። ከ1914 ወዲህ ያሉት ዓመታት የፍጻሜው ዘመን ተብሎ የሚጠራው ጊዜ ክፍል ናቸው። ትንቢት 1፦ በጊዜ ሰሌዳው መጀመሪያ ላይ ሰባት ራስ ያለው አውሬ ይታያል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአውሬው ሰባተኛ ራስ ቆሰለ። ከ1917 በኋላ ሰባተኛው ራስ የዳነ ከመሆኑም ሌላ አውሬው ከጉዳቱ አገገመ። ትንቢት 2፦ በ1871 የሰሜኑ ንጉሥ ማንነት ግልጽ ሆነ፤ በ1870 የደቡቡ ንጉሥ ማንነት ግልጽ ሆነ። በ1871 የጀርመን መንግሥት የሰሜኑ ንጉሥ ሆኖ ብቅ አለ። በዚህ ወቅት የደቡቡ ንጉሥ ሆኖ ብቅ ያለው የታላቋ ብሪታንያ መንግሥት ነው፤ በኋላ ላይ ማለትም በ1917 ግን የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል መንግሥት የደቡቡ ንጉሥ ሆነ። ትንቢት 3፦ ከ1870ዎቹ ዓመታት አንስቶ ቻርልስ ቴዝ ራስል እና አጋሮቹ በትንቢት የተነገረለት “መልእክተኛ” ሆነዋል። በ1880ዎቹ መጀመሪያ ላይ ‘የጽዮን መጠበቂያ ግንብ’ አንባቢዎቹ ምሥራቹን እንዲሰብኩ አበረታታ። ትንቢት 4፦ ከ1914 ወዲህ የመከር ወቅት ተጀመረ። ስንዴው ከእንክርዳዱ ተለየ። ትንቢት 5፦ ከ1917 አንስቶ የብረቱ እና የሸክላው እግር ብቅ አለ። ከእነዚህ በተጨማሪ በሰንጠረዡ ላይ የሚታዩት ነገሮች፦ ከ1914 እስከ 1918 በዓለም ላይ የተከሰቱ ነገሮች፦ አንደኛው የዓለም ጦርነት። የይሖዋን ሕዝቦች የነኩ ክንውኖች፦ ከ1914 እስከ 1918 ባሉት ዓመታት በብሪታንያ እና በጀርመን የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ታስረዋል። በ1918 በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት አባላት ታሰሩ።
        ትንቢት 1።

        ጥቅስ፦ ራእይ 11:7፤ 12:13, 17፤ 13:1-8, 12

        ትንቢት፦ “አውሬው” የምድርን ነዋሪዎች ለበርካታ መቶ ዘመናት ይገዛል። በፍጻሜው ዘመን የአውሬው ሰባተኛ ራስ ይቆስላል። በኋላ ላይ ይህ ራስ ቁስሉ ይድንለታል፤ “ምድርም ሁሉ” አውሬውን ይከተለዋል። ሰይጣን ይህን አውሬ በመጠቀም ‘ቀሪዎቹን ይዋጋል።’

        ፍጻሜ፦ ከጥፋት ውኃ በኋላ ይሖዋን የሚቃወሙ ሰብዓዊ መንግሥታት ተነስተዋል። ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የብሪታንያ መንግሥት በእጅጉ ተዳክሞ ነበር። ሆኖም ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ጥምረት ሲፈጥር ማንሰራራት ቻለ። በተለይ በፍጻሜው ዘመን ሰይጣን በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለውን የፖለቲካ ሥርዓት ተጠቅሞ የአምላክን ሕዝቦች ያሳድዳል።

      • ትንቢት 2።

        ጥቅስ፦ ዳን. 11:25-45

        ትንቢት፦ በፍጻሜው ዘመን በሰሜኑ ንጉሥና በደቡቡ ንጉሥ መካከል የሚኖረው ሽኩቻ።

        ፍጻሜ፦ የጀርመን መንግሥትና የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል ተቀናቃኝ ሆኑ። በ1945 ሶቪየት ኅብረት እና አጋሮቹ የሰሜኑ ንጉሥ ሆኑ። በ1991 ሶቪየት ኅብረት ፈራረሰ፤ ከጊዜ በኋላ ሩሲያና አጋሮቿ የሰሜኑ ንጉሥ ሆኑ።

      • ትንቢት 3።

        ጥቅስ፦ ኢሳ. 61:1፤ ሚል. 3:1፤ ሉቃስ 4:18

        ትንቢት፦ ይሖዋ፣ መሲሐዊው መንግሥት ከመቋቋሙ በፊት ‘መንገድ የሚጠርግ መልእክተኛ’ ይልካል። “መልእክተኛ” የሚሆነው ቡድን “የዋህ ለሆኑ ሰዎች ምሥራች” ይናገራል።

        ፍጻሜ፦ ከ1870ዎቹ ዓመታት አንስቶ ቻርልስ ቴዝ ራስል እና አጋሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማብራራት ትጋት የተሞላበት ጥረት አድርገዋል። በ1880ዎቹ ዓመታት ደግሞ የአምላክ አገልጋዮች መስበክ እንዳለባቸው ጎላ አድርገው መግለጽ ጀመሩ። ካወጧቸው ርዕሶች መካከል “1,000 ሰባኪዎች ያስፈልጋሉ” እና “ለስብከት መቀባት” የሚሉት ይገኙበታል።

      • ትንቢት 4።

        ጥቅስ፦ ማቴ. 13:24-30, 36-43

        ትንቢት፦ አንድ ጠላት በስንዴ ማሳ ላይ እንክርዳድ ይዘራል፤ እስከ መከር ወቅት ድረስ እንክርዳዱ ከስንዴው ጋር እንዲያድግ ይተዋል፤ ስንዴውም በእንክርዳዱ ይዋጣል፤ ከዚያም እንክርዳዱን ከስንዴው የመለየቱ ሥራ ይከናወናል።

        ፍጻሜ፦ ከ1800ዎቹ ዓመታት መገባደጃ አንስቶ በእውነተኛ ክርስቲያኖችና በሐሰተኛ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጣ። በፍጻሜው ዘመን እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሰበሰባሉ፤ እንዲሁም ከሐሰተኛ ክርስቲያኖች ይለያሉ።

      • ትንቢት 5።

        ጥቅስ፦ ዳን. 2:31-33, 41-43

        ትንቢት፦ የብረትና የሸክላ እግር፤ ይህ እግር ከተለያዩ የብረት ዓይነቶች የተሠራው ምስል ክፍል ነው።

        ፍጻሜ፦ ሸክላው፣ በአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ግዛት ውስጥ የሚደረጉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ያመለክታል። እነዚህ ንቅናቄዎች ይህ የዓለም ኃያል መንግሥት እንደ ብረት ያለ ጥንካሬውን እንዳይጠቀምበት ያዳክሙታል።

      • ሰንጠረዥ 2፦ ከ1919 እስከ 1945 በተመሳሳይ ጊዜ የተፈጸሙ የፍጻሜው ዘመን ትንቢቶች። የጀርመን መንግሥት እስከ 1945 ድረስ የሰሜኑ ንጉሥ ሆኖ ቀጥሏል። የደቡቡ ንጉሥ፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። ትንቢት 6፦ በ1919 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደነጻው ጉባኤ ተሰበሰቡ። ከ1919 አንስቶ የስብከቱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጠለ። ትንቢት 7፦ በ1920 የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ተቋቋመ፤ ይህ ድርጅት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ ቀጥሏል። ከእነዚህ በተጨማሪ በሰንጠረዡ ላይ የሚታዩት ነገሮች፦ ትንቢት 1፦ ሰባት ራስ ያለው አውሬ ይቀጥላል። ትንቢት 5፣ የብረቱና የሸክላው እግር ይቀጥላል። ከ1939 እስከ 1945 በዓለም ላይ የተከሰቱ ነገሮች፦ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት። የይሖዋን ሕዝቦች የነኩ ክንውኖች፦ ከ1933 እስከ 1945፣ በጀርመን የሚገኙ ከ11,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ታስረዋል። ከ1939 እስከ 1945 በብሪታንያ የሚገኙ 1,600 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ታሰሩ። ከ1940 እስከ 1944 በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከ2,500 ጊዜ በላይ የሕዝብ ዓመፅ ገጥሟቸዋል።
        ትንቢት 6።

        ጥቅስ፦ ማቴ. 13:30፤ 24:14, 45፤ 28:19, 20

        ትንቢት፦ “ስንዴው” ወደ “ጎተራ” ይሰበሰባል፤ እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” “በቤተሰቦቹ” ላይ ይሾማል። “የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር” መሰበክ ይጀምራል።

        ፍጻሜ፦ በ1919 ታማኙ ባሪያ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ተሾመ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የስብከቱን ሥራ አጧጧፉት። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ እየሰበኩ ነው፤ እንዲሁም ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ያዘጋጃሉ።

      • ትንቢት 7።

        ጥቅስ፦ ዳን. 12:11፤ ራእይ 13:11, 14, 15

        ትንቢት፦ ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ፣ ‘ለአውሬው ምስል እንዲሠራ’ ትእዛዝ ያስተላልፋል፤ ‘ለምስሉም እስትንፋስ ይሰጠዋል።’

        ፍጻሜ፦ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት፣ ቅድሚያውን ወስዶ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የተባለ ድርጅት እንዲቋቋም አድርጓል። ሌሎች አገራትም ይህን ድርጅት ተቀላቅለዋል። ከጊዜ በኋላ የሰሜኑ ንጉሥም ይህን ማኅበር ተቀላቅሏል፤ ሆኖም ኅብረት ፈጥሮ የቆየው ከ1926 እስከ 1933 ብቻ ነበር። በኋላ ላይ እንደተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁሉ ይህ ማኅበርም ለአምላክ መንግሥት ብቻ የሚገባው እውቅና ተሰጥቶታል።

      • ሰንጠረዥ 3፦ ከ1945 እስከ 1991 በተመሳሳይ ጊዜ የተፈጸሙ የፍጻሜው ዘመን ትንቢቶች። እስከ 1991 ድረስ የሰሜኑ ንጉሥ የሆኑት ሶቪየት ኅብረትና አጋሮቿ ናቸው፤ በኋላም ሩሲያ እና አጋሮቿ ይህን ቦታ ያዙ። የደቡቡ ንጉሥ፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። ትንቢት 8፦ አቶሚክ ፍንዳታ የፈጠረው ደመና፤ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ያስከተለውን ውድመት የሚያሳይ ነው። ትንቢት 9፦ በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋቋመ፤ ይህ ድርጅት የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን የሚተካ ነበር። ከእነዚህ በተጨማሪ በሰንጠረዡ ላይ የሚታዩት ነገሮች፦ ትንቢት 1፦ ሰባት ራስ ያለው አውሬ ይቀጥላል። ትንቢት 5፦ የብረቱና የሸክላው እግር ይቀጥላል። ትንቢት 6፦ በ1945 ከ156,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች ነበሩ። በ1991 ከ4,278,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች ነበሩ። የይሖዋን ሕዝቦች የነኩ ክንውኖች፦ ከ1945 እስከ 1950ዎቹ ባሉት ዓመታት፣ በሶቪየት ኅብረት የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሳይቤሪያ ተግዘዋል።
        ትንቢት 8።

        ጥቅስ፦ ዳን. 8:23, 24

        ትንቢት፦ አስፈሪ መልክ ያለው ንጉሥ “ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጥፋት ያደርሳል።”

        ፍጻሜ፦ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ብዙ ጥፋት አድርሷል። ለምሳሌ ያህል፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት፣ የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል ጠላት በሆነ አገር ላይ ሁለት አቶሚክ ቦምቦች ጥሏል፤ ይህም ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ ጥፋት አስከትሏል።

      • ትንቢት 9።

        ጥቅስ፦ ዳን. 11:31፤ ራእይ 17:3, 7-11

        ትንቢት፦ አሥር ቀንዶች ያሉት “ደማቅ ቀይ” አውሬ ከጥልቁ ይወጣል፤ ስምንተኛ ንጉሥም ይሆናል። ይህ ንጉሥ፣ በዳንኤል መጽሐፍ ላይ ‘ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር’ ተብሎ ተጠርቷል።

        ፍጻሜ፦ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆኖ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋቋመ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከእሱ በፊት እንደነበረው የቃል ኪዳኑ ማኅበር ሁሉ ለአምላክ መንግሥት የሚገባው ክብር ተሰጥቶታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በሃይማኖት ላይ ጥቃት ይሰነዝራል።

      • ሰንጠረዥ 4፦ ከአሁኑ ጊዜ አንስቶ እስከ አርማጌዶን በተመሳሳይ ጊዜ የሚፈጸሙ የፍጻሜው ዘመን ትንቢቶች። የሰሜኑ ንጉሥ የሆኑት ሩሲያ እና አጋሮቿ ናቸው። የደቡቡ ንጉሥ፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። ትንቢት 10፦ የዓለም መንግሥታት ‘ሰላምና ደህንነት ሆነ’ ብለው ያውጃሉ። ከዚያም ታላቁ መከራ ይጀምራል። ትንቢት 11፦ ብሔራት በሐሰት ሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ትንቢት 12፦ የዓለም መንግሥታት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። የቀሩት ቅቡዓን ወደ ሰማይ ይሰበሰባሉ። ትንቢት 13፦ አርማጌዶን። በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠው፣ ድሉን ያጠናቅቃል። ሰባት ራስ ያለው አውሬ ይጠፋል፤ ግዙፉ ምስል፣ የብረትና የሸክላ ድብልቅ በሆነው እግሩ ላይ ተመትቶ ይደቅቃል። ከእነዚህ በተጨማሪ በሰንጠረዡ ላይ የሚታዩት ነገሮች፦ ትንቢት 1፦ ሰባት ራስ ያለው አውሬ እስከ አርማጌዶን ይቀጥላል። ትንቢት 5፣ የብረቱና የሸክላው እግር እስከ አርማጌዶን ይቀጥላል። ትንቢት 6፦ በዛሬው ጊዜ ከ8,580,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች አሉ። የይሖዋን ሕዝቦች የነኩ ክንውኖች፦ በ2017 የሩሲያ ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮችን አስረዋል እንዲሁም የቅርንጫፍ ቢሮውን ሕንፃዎች ወርሰዋል።
        ትንቢት 10 እና 11።

        ጥቅስ፦ 1 ተሰ. 5:3፤ ራእይ 17:16

        ትንቢት፦ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ብለው ያውጃሉ፤ “አሥሩ ቀንዶች” እና “አውሬው” “አመንዝራዋን” ያጠቋታል እንዲሁም ያጠፏታል። ከዚያም በብሔራት ላይ ጥፋት ይመጣል።

        ፍጻሜ፦ ብሔራት፣ ሰላም እና ደህንነት ማስፈን እንደቻሉ ይናገራሉ። ከዚያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል የሆኑ ብሔራት፣ የሐሰት ሃይማኖት ተቋማትን ያጠፋሉ። ይህም ታላቁ መከራ እንደጀመረ የሚያሳይ ምልክት ይሆናል። ይህ መከራ የሚያበቃው መላው የሰይጣን ሥርዓት በአርማጌዶን ሲደመሰስ ነው።

      • ትንቢት 12።

        ጥቅስ፦ ሕዝ. 38:11, 14-17፤ ማቴ. 24:31

        ትንቢት፦ ጎግ የአምላክን ሕዝቦች ምድር ይወርራል። ከዚያም መላእክት “የተመረጡትን” ይሰበስባሉ።

        ፍጻሜ፦ የሰሜኑ ንጉሥ ከሌሎቹ የዓለም መንግሥታት ጋር በመሆን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። ይህ ጥቃት ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ የቀሩት ቅቡዓን ወደ ሰማይ ይሰበሰባሉ።

      • ትንቢት 13።

        ጥቅስ፦ ሕዝ. 38:18-23፤ ዳን. 2:34, 35, 44, 45፤ ራእይ 6:2፤ 16:14, 16፤ 17:14፤ 19:20

        ትንቢት፦ ‘በነጭ ፈረስ’ ላይ “የተቀመጠው” ጋላቢ፣ ጎግንና ሠራዊቱን በማጥፋት ‘ድሉን ያጠናቅቃል።’ “አውሬው” ‘ወደ እሳት ሐይቅ ይወረወራል’፤ ትልቁ ምስልም ይደቅቃል።

        ፍጻሜ፦ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ የአምላክ ሕዝቦችን ይታደጋል። ከ144,000 ተባባሪ ገዢዎችና ከመላእክት ሠራዊት ጋር በመሆን ኢየሱስ፣ ጥምረት የፈጠሩ ብሔራትን ያጠፋል፤ መላው የሰይጣን ሥርዓት በዚህ መንገድ ይጠፋል።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ