የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ይሖዋ ‘ሚስጥር ገላጭ ነው’
    መጠበቂያ ግንብ—2012 | ሰኔ 15
    • ይሖዋ ‘ሚስጥር ገላጭ ነው’

      “በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክና የነገሥታት ጌታ፣ ምስጢርንም ገላጭ ነው።”​—ዳን. 2:47

      ምን ብለህ ትመልሳለህ?

      ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ዝርዝር ጉዳዮችን ገልጦልናል?

      ስድስቱ የአውሬው ራሶች ምን ያመለክታሉ?

      በአውሬውና ናቡከደነፆር በተመለከተው ምስል መካከል ምን ተዛማጅነት አለ?

      1, 2. ይሖዋ ምን ነገር ገልጦልናል? ለምንስ?

      የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን በሚያጠፋበት ወቅት የዓለም ኃያል መንግሥት የሚሆኑት እነማን ናቸው? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ ቀላል ነው፤ ምክንያቱም ‘ሚስጥር ገላጭ’ የሆነው ይሖዋ አምላክ የእነዚህን መንግሥታት ማንነት ነግሮናል። ይህን ያደረገው ነቢዩ ዳንኤል እና ሐዋርያው ዮሐንስ በጻፏቸው መጻሕፍት አማካኝነት ነው።

      2 ይሖዋ ለእነዚህ አገልጋዮቹ በተከታታይ የሚነሱ አራዊትን በራእይ አሳይቷቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ናቡከደነፆር በሕልም የተመለከተው ግዙፍ ምስል ምን ትርጉም እንዳለው ለዳንኤል ገልጦለታል። ይሖዋ እነዚህ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍሩና ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደረገው ለእኛ ጥቅም ሲል ነው። (ሮም 15:4) በተጨማሪም ይህን ያደረገው የእሱ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን በቅርቡ እንደሚያደቃቸው ያለንን ተስፋ ለማጠናከር ነው።​—ዳን. 2:44

      3. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች በትክክል ለመረዳት በቅድሚያ ስለ ምን ነገር መገንዘብ ይኖርብናል? ለምንስ?

      3 የዳንኤልና የዮሐንስ ዘገባዎች በምድር ላይ የሚነሱትን ስምንት ነገሥታት ወይም ሰብዓዊ አገዛዞች ለይተን እንድናውቅ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ነገሥታት የሚነሱበትን ቅደም ተከተል ማስተዋል እንድንችልም ይረዱናል። ይሁንና እነዚህን ትንቢቶች በትክክል መረዳት የምንችለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጀመሪያው ትንቢት ምን ትርጉም እንዳለው መገንዘብ ከቻልን ብቻ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክትም ሆነ በውስጡ ያሉት ትንቢቶች በመጀመሪያው ትንቢት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው። በሌላ አባባል ይህን ትንቢት እንደ ገመድ ብንቆጥረው ሌሎች ትንቢቶች በሙሉ የተንጠለጠሉት በዚህ ገመድ ላይ ነው ሊባል ይችላል።

      የእባቡ ዘርና አውሬው

      4. የሴቲቱ ዘር ክፍል እነማን ናቸው? ይህ ዘርስ ምን ነገር ያከናውናል?

      4 በኤደን ዓመፅ ከተነሳ በኋላ ወዲያውኑ ይሖዋ ‘ሴቲቱ ዘር’ እንደምታስገኝ ቃል ገባ።a (ዘፍጥረት 3:15⁠ን አንብብ።) የሴቲቱ ዘር ወደፊት የእባቡን ማለትም የሰይጣንን ራስ ይቀጠቅጣል። ይህ ዘር በአብርሃም በኩል እንደሚመጣ፣ ከእስራኤል ብሔር ወገን እንደሚሆን እንዲሁም በይሁዳ የዘር ሐረግና በንጉሥ ዳዊት የትውልድ መስመር በኩል እንደሚመጣ ይሖዋ ከጊዜ በኋላ አሳውቋል። (ዘፍ. 22:15-18፤ 49:10፤ መዝ. 89:3, 4፤ ሉቃስ 1:30-33) በኋላም የዚህ ዘር ዋነኛ ክፍል ክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ ተገኘ። (ገላ. 3:16) በመንፈስ የተቀቡ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ደግሞ የዘሩ ሁለተኛ ክፍል ሆኑ። (ገላ. 3:26-29) ኢየሱስና ቅቡዓኑ በአንድነት የአምላክን መንግሥት ይመሠርታሉ፤ አምላክም ሰይጣንን ለመቀጥቀጥ ይህን መንግሥት መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል።​—ሉቃስ 12:32፤ ሮም 16:20

      5, 6. (ሀ) ዳንኤልና ዮሐንስ የጠቀሱት ስንት ኃያላን መንግሥታትን ነው? (ለ) በራእይ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው አውሬ ራሶች ምን ያመለክታሉ?

      5 በኤደን የተነገረው የመጀመሪያው ትንቢት ሰይጣንም የራሱን “ዘር” እንደሚያስገኝ ይገልጻል። ይህ ዘር፣ ለሴቲቱ ዘር ጠላትነት እንደሚኖረውም ያሳያል። ለመሆኑ የእባቡ ዘር ክፍል እነማን ናቸው? የሰይጣንን መንገድ በመከተል አምላክን የሚጠሉና ሕዝቡን የሚቃወሙ ሁሉ ከእባቡ ዘር ክፍል ይመደባሉ። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰይጣን በተለያዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ወይም መንግሥታት አማካኝነት ዘሩን ሲያደራጅ ቆይቷል። (ሉቃስ 4:5, 6) ይሁን እንጂ በአምላክ ሕዝቦች ይኸውም በእስራኤል ብሔርም ሆነ በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩት ሰብዓዊ መንግሥታት በጣም ጥቂት ናቸው። ይህን ሐቅ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ዳንኤልና ዮሐንስ በተመለከቷቸው ራእዮች ላይ ስምንት ኃያላን መንግሥታት ብቻ የተጠቀሱት ለምን እንደሆነ ግልጽ ስለሚያደርግልን ነው።

      6 ከሞት የተነሳው ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ አስደናቂ ራእዮችን ለሐዋርያው ዮሐንስ አሳይቶታል። (ራእይ 1:1) በአንደኛው ራእይ ላይ፣ በዘንዶ የተመሰለው ዲያብሎስ በባሕር አሸዋ ላይ እንደቆመ ዮሐንስ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 13:1, 2⁠ን አንብብ።) በተጨማሪም ዮሐንስ ሰባት ራሶች ያሉት አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣና ከዲያብሎስ ከፍተኛ ሥልጣን ሲቀበል ተመልክቷል። በኋላም ዮሐንስ መልኩ ቀይ የሆነና ልክ እንደ መጀመሪያው አውሬ ሰባት ራሶች ያሉት ሌላ አውሬ የተመለከተ ሲሆን ይህ ቀይ አውሬ በ⁠ራእይ 13:1 ላይ ያለው አውሬ ምስል ነው። የቀዩ አውሬ ሰባት ራሶች ‘ሰባት ነገሥታትን’ ወይም መንግሥታትን እንደሚያመለክቱ አንድ መልአክ ለዮሐንስ ነግሮታል። (ራእይ 13:14, 15፤ 17:3, 9, 10) ዮሐንስ ራእዩን በጻፈበት ወቅት አምስቱ ወድቀው ነበር፤ አንዱ በሥልጣን ላይ የነበረ ሲሆን “ሌላው ደግሞ ገና አልመጣም።” ለመሆኑ እነዚህ የዓለም ኃያላን መንግሥታት እነማን ናቸው? እስቲ በዚህ ራእይ ውስጥ የተጠቀሱትን ራሶች አንድ በአንድ እንመርምር። ከዚህም ሌላ ስለ አብዛኞቹ መንግሥታት ተጨማሪ ማብራሪያ ከዳንኤል መጽሐፍ እንመለከታለን። ዳንኤል ይህን ዝርዝር ሐሳብ የጻፈው እነዚህ መንግሥታት ከመነሳታቸው ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ነው።

      ግብፅና አሦር​—የመጀመሪያዎቹ ሁለት ራሶች

      7. የመጀመሪያው ራስ የሚወክለው ማንን ነው? ለምንስ?

      7 የአውሬው የመጀመሪያ ራስ ግብፅን ይወክላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለአምላክ ሕዝቦች ጠላትነት ያሳየችው የመጀመሪያዋ ኃያል መንግሥት ግብፅ ነበረች። የሴቲቱ ዘር መገኛ የሆኑት የአብርሃም ዘሮች በግብፅ ቁጥራቸው እጅግ እየበዛ ሄዶ ነበር። በዚህ ጊዜ የግብፅ መንግሥት እስራኤላውያንን መጨቆን ጀመረ። ሰይጣን የሴቲቱ ዘር ከመምጣቱ በፊት የአምላክን ሕዝብ ጨርሶ ለማጥፋት ሞክሮ ነበር። እንዴት? እስራኤላዊ የሆኑ ወንድ ሕፃናትን እንዲገድል ፈርዖንን በማነሳሳት ነው። ይሖዋ ግን ይህ የሰይጣን እቅድ እንዲከሽፍ ያደረገ ሲሆን ሕዝቡንም ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል። (ዘፀ. 1:15-20፤ 14:13) ከጊዜ በኋላም እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር እንዲወርሱ አድርጓቸዋል።

      8. ሁለተኛው ራስ የሚወክለው ማንን ነው? ምን ሙከራስ አድርጓል?

      8 የአውሬው ሁለተኛ ራስ ደግሞ አሦርን ይወክላል። ይህ ኃያል መንግሥትም ቢሆን የአምላክን ሕዝቦች ጠራርጎ ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል። እርግጥ ነው፣ አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ወደ ጣዖት አምልኮ ዘወር ባለበትና ባመፀበት ወቅት ይሖዋ የአሦርን መንግሥት ተጠቅሞ ቀጥቶት ነበር። ይሁንና አሦር በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ሰነዘረ። በዚህ ወቅት ሰይጣን፣ ኢየሱስ የሚመጣበትን ንጉሣዊ የዘር ሐረግ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አስቦ ሊሆን ይችላል። አሦር በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ግን ይሖዋ አልፈለገም፤ በመሆኑም ይሖዋ ይህን ወራሪ ጠላት በማጥፋት ታማኝ ሕዝቦቹን ተአምራዊ በሆነ መንገድ አድኗቸዋል።​—2 ነገ. 19:32-35፤ ኢሳ. 10:5, 6, 12-15

      ባቢሎን​—ሦስተኛው ራስ

      9, 10. (ሀ) ይሖዋ ለባቢሎናውያን ምን እንዲያደርጉ ፈቅዶላቸዋል? (ለ) ይሖዋ የተናገራቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ከተፈለገ ምን ነገር መከናወን ይኖርበታል?

      9 ዮሐንስ በተመለከተው አውሬ ላይ የነበረው ሦስተኛው ራስ የሚወክለው የባቢሎንን መንግሥት ነው። ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፉና ሕዝቧን በግዞት እንዲወስዱ ይሖዋ ፈቅዶላቸው ነበር። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት ግን ይሖዋ ጥፋት እንደሚያመጣባቸው ዓመፀኞቹን እስራኤላውያንን አስጠንቅቋቸዋል። (2 ነገ. 20:16-18) በእሱ “ዙፋን” ላይ እንደተቀመጡ ተደርገው የሚቆጠሩት ሰብዓዊ ነገሥታት፣ በኢየሩሳሌም ሆነው መግዛታቸውን እንደሚያቆሙም አስቀድሞ ተናግሯል። (1 ዜና 29:23) በተጨማሪም ይሖዋ “ባለ መብት” የሆነው የንጉሥ ዳዊት ዘር እንደሚመጣና በእሱ ዙፋን ላይ እንደሚቀመጥ ቃል ገብቷል።​—ሕዝ. 21:25-27

      10 አንድ ሌላ ትንቢት እንደሚጠቁመው ደግሞ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ (የተቀባ የሚል ትርጉም አለው) በሚመጣበት ጊዜም ጭምር አይሁዳውያን ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ይሖዋን ማምለካቸውን ይቀጥላሉ። (ዳን. 9:24-27) ከዚህ ቀደም ሲል ማለትም እስራኤላውያን በምርኮ ወደ ባቢሎን ከመወሰዳቸው በፊት የተጻፈ አንድ ትንቢት ደግሞ መሲሑ በቤተልሔም እንደሚወለድ ተናግሮ ነበር። (ሚክ. 5:2) እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ከተፈለገ አይሁዳውያኑ ከግዞት ነፃ መውጣት፣ ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስና ቤተ መቅደሱን በድጋሚ መገንባት ይኖርባቸዋል። ይሁንና የባቢሎን መንግሥት በግዞት የወሰዳቸውን ሰዎች ነፃ የመልቀቅ ልማድ አልነበረውም። ታዲያ ሕዝቡ ከግዞት ነፃ መውጣት የሚችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ መልሱን ለነቢያቱ ገልጦላቸዋል።​—አሞጽ 3:7

      11. የባቢሎን መንግሥት በምን ነገሮች ተመስሏል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

      11 ነቢዩ ዳንኤል፣ በግዞት ወደ ባቢሎን ከተወሰዱት መካከል አንዱ ነው። (ዳን. 1:1-6) ይሖዋ ከባቢሎን በኋላ በተከታታይ ስለሚነሱት የዓለም ኃያላን መንግሥታት ለዳንኤል ገልጦለታል። ይሖዋ ይህን ሚስጥር ለዳንኤል የገለጠለት ተምሳሌት የሚሆኑ የተለያዩ ነገሮችን በመጠቀም ነው። ለአብነት ያህል፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከተለያዩ ማዕድናት የተሠራ አንድ ግዙፍ ምስል በሕልሙ እንዲመለከት አድርጎ ነበር። (ዳንኤል 2:1, 19, 31-38⁠ን አንብብ።) ይሖዋ ዳንኤልን በመጠቀም የምስሉ የወርቅ ራስ የባቢሎንን መንግሥት እንደሚያመለክት ገለጠ።b ከባቢሎን በኋላ የተነሳው የዓለም ኃያል መንግሥት ደግሞ ከብር በተሠሩት የምስሉ ደረትና ክንዶች ተመስሏል። ይህ ኃያል መንግሥት ማን ነው? በአምላክ ሕዝቦች ላይስ ምን አድርጓል?

      ሜዶ ፋርስ​—አራተኛው ራስ

      12, 13. (ሀ) ይሖዋ፣ ባቢሎን ድል ከምትደረግበት መንገድ ጋር በተያያዘ ምን ነገር ገልጧል? (ለ) ሜዶ ፋርስ በአውሬው አራተኛ ራስ መወከሉ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

      12 ዳንኤል ከኖረበት ጊዜ አንድ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ፣ ይሖዋ ባቢሎንን ድል ስለሚያደርገው የዓለም ኃያል መንግሥት ማንነት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ዝርዝር ጉዳዮችን ገልጦ ነበር። ይሖዋ የባቢሎን ከተማ እንዴት እንደምትያዝ ብቻ ሳይሆን ከተማዋን ድል የሚያደርገውን ሰው ስም ጭምር ጠቅሷል። ይህ ሰው ፋርሳዊው ቂሮስ ነው። (ኢሳ. 44:28 እስከ 45:2) ዳንኤል የሜዶ ፋርስን የዓለም ኃያል መንግሥት አስመልክቶ ሌሎች ሁለት ራእዮችን አይቷል። በአንደኛው ራእይ ላይ ይህ መንግሥት በአንድ ጐኑ ከፍ በሚል ድብ ተመስሏል። ይህ ድብ “እስክትጠግብ ድረስ ሥጋ ብላ!” ተብሎ ተነግሮታል። (ዳን. 7:5) በሌላ ራእይ ላይ ዳንኤል እንደተመለከተው ደግሞ ይህ ጥምር የዓለም ኃያል መንግሥት ሁለት ቀንድ ባለው አውራ በግ ተመስሏል።​—ዳን. 8:3, 20

      13 ይሖዋ በትንቢት ባስነገረው መሠረት ባቢሎናውያንን ለመገልበጥና እስራኤላውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ሜዶ ፋርስን ተጠቅሟል። (2 ዜና 36:22, 23) ይሁንና ይህ መንግሥት ከጊዜ በኋላ የአምላክን ሕዝብ ለማጥፋት ተቃርቦ ነበር። የፋርስ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ሐማ አይሁዳውያንን ለማጥፋት ሴራ ጠንስሶ እንደነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የአስቴር መጽሐፍ ዘግቧል። ሐማ፣ ሰፊ በሆነው የፋርስ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን አይሁዳውያን በሙሉ ለማጥፋት ዝግጅት አድርጎ የነበረ ሲሆን ይህን የዘር ማጥፋት ዘመቻ የሚያደርግበትን ቀን ጭምር ወስኖ ነበር። በዚህ ወቅትም ቢሆን የአምላክ ሕዝቦች የሰይጣን ዘር ከሰነዘረባቸው ጥቃት ማምለጥ የቻሉት ይሖዋ ጣልቃ ስለገባ ነው። (አስ. 1:1-3፤ 3:8, 9፤ 8:3, 9-14) በመሆኑም የሜዶ ፋርስ መንግሥት በራእይ መጽሐፍ ላይ በተገለጸው አውሬ አራተኛ ራስ መወከሉ የተገባ ነው።

      ግሪክ​—አምስተኛው ራስ

      14, 15. ይሖዋ ስለ ጥንቱ የግሪክ መንግሥት ምን ዝርዝር ነገሮችን ገልጦልናል?

      14 በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጸው አውሬ አምስተኛ ራስ ግሪክን ይወክላል። ቀደም ሲል ዳንኤል ናቡከደነፆር ያየውን ሕልም አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ ላይ እንደተገለጸው ይህ አምስተኛ ራስ ከነሐስ በተሠሩት የምስሉ ሆድና ጭን ተመስሏል። በተጨማሪም ዳንኤል ስለዚህ ኃያል መንግሥትና ታዋቂ ስለሆነው የዚህ መንግሥት ገዥ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚገልጹ ሁለት አስደናቂ ራእዮችን ተቀብሏል።

      15 ዳንኤል ባየው አንደኛው ራእይ ላይ ግሪክ አራት ክንፎች ባሉት ነብር የተመሰለ ሲሆን ይህ ደግሞ በፍጥነት ድል በማድረግ ግዛቱን እንደሚያስፋፋ የሚያመለክት ነው። (ዳን. 7:6) በሌላኛው ራእይ ላይ ደግሞ ዳንኤል አንድ ቀንድ ያለው ፍየል፣ ሁለት ቀንድ ያለውን አውራ በግ በፍጥነት ሲገድል ማለትም ሜዶ ፋርስን ሲደመስስ ተመልክቷል። ፍየሉ የግሪክን መንግሥት፣ የፍየሉ ትልቅ ቀንድ ደግሞ ከነገሥታቶቹ አንዱን እንደሚያመለክት ይሖዋ ለዳንኤል ነግሮታል። ዳንኤል ትልቁ ቀንድ እንደሚሰበርና በምትኩም አራት ትናንሽ ቀንዶች እንደሚበቅሉ ጽፏል። ይህ ትንቢት የተጻፈው የግሪክ መንግሥት ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ቢሆንም እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ፍጻሜውን አግኝቷል። የጥንቱ ግሪክ ታዋቂ ንጉሥ የሆነው ታላቁ እስክንድር በሜዶ ፋርስ ላይ የዘመተውን ጦር መርቷል። ይሁንና ትልቁ ቀንድ ብዙም ሳይቆይ ተሰበረ፤ ይህ የሆነው ሰፊ ግዛቶችን የተቆጣጠረው ታላቁ እስክንድር በ32 ዓመቱ ሕይወቱ በአጭሩ በተቀጨ ጊዜ ነው። በኋላም ግዛቱ፣ ለአራት ጄኔራሎቹ ተከፋፈለ።​—ዳንኤል 8:20-22⁠ን አንብብ።

      16. አንታይከስ አራተኛ ምን አድርጓል?

      16 የግሪክ መንግሥት ፋርስን ድል ካደረገ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ይኖሩበት የነበረውን አካባቢ ተቆጣጠረ። በዚህ ወቅት አይሁዳውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር የተመለሱ ሲሆን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ እንደገና ገነቡ። በዚህ ጊዜም ቢሆን አይሁዳውያን የአምላክ የተመረጡ ሕዝቦች ነበሩ፤ እንዲሁም ቤተ መቅደሱ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል መሆኑን ቀጥሎ ነበር። ሆኖም በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የአውሬው አምስተኛ ራስ የሆነው ግሪክ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ሰነዘረ። ከተከፋፈለው የእስክንድር ግዛት ውስጥ ከተነሱት ነገሥታት አንዱ የሆነው አንታይከስ አራተኛ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ የጣዖት መሰዊያ ያቆመ ከመሆኑም በላይ የአይሁድን እምነት መከተል በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል እንደሆነ የሚናገር አዋጅ አወጣ። ይህም ቢሆን የሰይጣን ዘር ክፍል ጠላትነቱን የገለጸበት ድርጊት ነው። ብዙም ሳይቆይ ግሪክ በሌላ የዓለም ኃያል መንግሥት ተተካ። ታዲያ የአውሬው ስድስተኛ ራስ የሚሆነው ማን ነው?

      ሮም​—‘የሚያስፈራውና የሚያስደነግጠው’ ስድስተኛው ራስ

      17. ስድስተኛው ራስ በ⁠ዘፍጥረት 3:15 የሚገኘው ትንቢት እንዲፈጸም ምን ጉልህ ሚና ተጫውቷል?

      17 ዮሐንስ ስለ አውሬው ራእይ በተመለከተበት ወቅት የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረው ሮም ነው። (ራእይ 17:10) የአውሬው ስድስተኛ ራስ በ⁠ዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት እንዲፈጸም ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ሰይጣን የሮም ባለሥልጣናትን በመጠቀም የዘሩን ‘ተረከዝ’ ስለቀጠቀጠ በሴቲቱ ዘር ላይ ጊዜያዊ ጉዳት አድርሶ ነበር። ሮማውያን ይህን ያደረጉት በመንግሥት ላይ ዓመፅ ያነሳሳል በሚል ኢየሱስን በሐሰት ክስ በመወንጀልና በመግደል ነው። (ማቴ. 27:26) ይሁን እንጂ ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት ሲያስነሳው በዘሩ ተረከዝ ላይ የነበረው ቁስል ወዲያውኑ ዳነ።

      18. (ሀ) ይሖዋ የመረጠው አዲስ ብሔር የትኛው ነው? ለምንስ? (ለ) የእባቡ ዘር ለሴቲቱ ዘር ጠላትነቱን ማሳየቱን የቀጠለው እንዴት ነው?

      18 የእስራኤል ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስን በመቃወም ከሮም መንግሥት ጋር የተመሳጠሩ ሲሆን አብዛኛው ሕዝብም መሲሑን አልተቀበለውም። በመሆኑም ሥጋዊ እስራኤላውያን የይሖዋ ሕዝብ የመሆን መብታቸውን አጡ። (ማቴ. 23:38፤ ሥራ 2:22, 23) ይሖዋም በእነሱ ምትክ አዲስ ብሔር ይኸውም ‘የአምላክ እስራኤልን’ መረጠ። (ገላ. 3:26-29፤ 6:16) ይህ ብሔር ከአይሁድና ከአሕዛብ የተውጣጡ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈ ጉባኤ ነው። (ኤፌ. 2:11-18) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም ቢሆን የእባቡ ዘር ለሴቲቱ ዘር ጠላትነት ማሳየቱን ቀጥሏል። የሮም መንግሥት በተለያየ ጊዜ የሴቲቱ ዘር ሁለተኛ ክፍል የሆነውን የክርስቲያን ጉባኤ ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል።c

      19. (ሀ) ዳንኤል ስድስተኛውን የዓለም ኃያል መንግሥት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ የትኞቹን ጉዳዮች እንመረምራለን?

      19 ዳንኤል በፈታው የናቡከደነፆር ሕልም ላይ ሮም በብረት ቅልጥሞች ተመስሎ ነበር። (ዳን. 2:33) እንዲያውም ዳንኤል የተመለከተው ሌላ ራእይ የሮም መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ከሮም የሚወጣውን ቀጣዩን የዓለም ኃያል መንግሥትንም ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። (ዳንኤል 7:7, 8⁠ን አንብብ።) ለበርካታ መቶ ዓመታት ሮም ለጠላቶቹ “የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ በጣም ኀይለኛ” አውሬ ሆኖ ነበር። ይሁንና ትንቢቱ በመቀጠል ከሮም መንግሥት “ዐሥር ቀንዶች” እንደሚወጡ እንዲሁም ከእነዚህ ቀንዶች መካከል ሌላ ትንሽ ቀንድ እንደሚያድግ ብሎም ይህ ቀንድ ጎልቶ እንደሚወጣ ይገልጻል። እነዚህ አሥር ቀንዶች ምን ይወክላሉ? ትንሹስ ቀንድ ማን ነው? ይህ ትንሽ ቀንድ ናቡከደነፆር በሕልም ከተመለከተው ግዙፍ ምስል ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? በገጽ 14 ላይ የሚገኘው ርዕስ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ያብራራል።

  • ይሖዋ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች” ይገልጣል
    መጠበቂያ ግንብ—2012 | ሰኔ 15
    • ይሖዋ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች” ይገልጣል

      “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውና በእሱ የተገለጠው ራእይ ይህ ነው።”​—ራእይ 1:1

      ምን ብለህ ትመልሳለህ?

      የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን የሚወክለው የትኛው የግዙፉ ምስል ክፍል ነው?

      ዮሐንስ፣ በአንግሎ አሜሪካና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መካከል ያለውን ዝምድና የገለጸው እንዴት ነው?

      ዳንኤልና ዮሐንስ የሰብዓዊ አገዛዝ ፍጻሜን የገለጹት እንዴት ነው?

      1, 2. (ሀ) ዳንኤልና ዮሐንስ የጻፏቸው ትንቢቶች ስለ ምን ነገር እንድንገነዘብ ይረዱናል? (ለ) የአውሬው የመጀመሪያ ስድስት ራሶች የሚያመለክቱት ማንን ነው?

      ዳንኤልና ዮሐንስ የጻፏቸው ትንቢቶች በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት በዓለም ላይ ስለሚከሰቱ በርካታ ነገሮች እንድንረዳ ያስችሉናል። ዮሐንስ ባየው አውሬ፣ ዳንኤል በተመለከተው አሥር ቀንዶች ያሉት አውሬና ግዙፉን ምስል አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ መካከል ያለውን ተዛምዶ በመመርመር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? እነዚህን ትንቢቶች በደንብ መረዳታችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

      2 እስቲ በቅድሚያ ዮሐንስ በራእይ ያየውን አውሬ እንመልከት። (ራእይ, ምዕ. 13) ቀደም ሲል በነበረው የጥናት ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው የአውሬው የመጀመሪያዎቹ ስድስት ራሶች የሚያመለክቱት ግብፅን፣ አሦርን፣ ባቢሎንን፣ ሜዶ ፋርስን፣ ግሪክንና ሮምን ነው። ሁሉም ለሴቲቱ ዘር ያላቸውን ጥላቻ አሳይተዋል። (ዘፍ. 3:15) ስድስተኛው ራስ የሆነው ሮም፣ ዮሐንስ ራእዩን ከጻፈ በኋላ ባሉት በርካታ ምዕተ ዓመታት ጭምር የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኖ ቀጥሎ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ሰባተኛው ራስ ሮምን መተካቱ አይቀርም። ታዲያ ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት የሚሆነው ማን ነው? በሴቲቱ ዘር ላይስ ምን ያደርጋል?

      ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ኃያላን ሆኑ

      3. አሥር ቀንዶች ያሉት አስፈሪው አውሬ ምንን ያመለክታል? አሥሩ ቀንዶችስ?

      3 ዮሐንስ የተመለከተውን ራእይ ዳንኤል ካየው አሥር ቀንዶች ካሉት አስፈሪ አውሬ ጋር በማወዳደር በራእይ 13 ላይ የተገለጸውን አውሬ ሰባተኛ ራስ ማንነት ማወቅ እንችላለን።a (ዳን. 7:7, 8, 23, 24⁠ን አንብብ።) ዳንኤል የተመለከተው አውሬ የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረውን ሮምን ይወክላል። (ከገጽ 12-13 ላይ የሚገኘውን ሥዕላዊ መግለጫ ተመልከት።) በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የሮም መንግሥት መፈራረስ ጀመረ። ከሚያስፈራው አውሬ ራስ የወጡት አሥር ቀንዶች ከሮም ግዛቶች የወጡትን መንግሥታት ያመለክታሉ።

      4, 5. (ሀ) ትንሹ ቀንድ ምን አደረገ? (ለ) የአውሬው ሰባተኛ ራስ ማን ነው?

      4 በዚህ አስፈሪ አውሬ ራስ ላይ ከወጡት ቀንዶች ወይም መንግሥታት መካከል አራቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። እነሱም ‘ትንሹ ቀንድ’ እና ይህ ቀንድ የነቃቀላቸው ሦስቱ ቀንዶች ናቸው። ብሪታንያን የሚያመለክተው ትንሹ ቀንድ፣ ሦስቱን ቀንዶች የነቃቀለው መቼ ነው? ቀድሞ የሮም ግዛት ክፍል የነበረችው ብሪታንያ ኃያል በመሆን ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ባለችበት ወቅት ነው። ይሁንና እስከ 17ኛው መቶ ዘመን ድረስ ብሪታንያ ከሌሎቹ አንጻር ስትታይ ያላት ኃይል አነስተኛ ነበር። ከጥንቷ የሮም ግዛት የወጡት ሦስቱ አገሮች ማለትም ስፔን፣ ኔዘርላንድና ፈረንሳይ ከብሪታንያ ይልቅ ኃያላን ነበሩ። ብሪታንያ እነዚህ ኃያላን አገሮች የነበራቸውን ቦታ በመንጠቅ አንድ በአንድ ነቃቅላቸዋለች። በ18ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ብሪታንያ በዓለም መድረክ ላይ ጉልህ ሚና የምትጫወት አገር ለመሆን በጉዞ ላይ ነበረች። ይሁን እንጂ የአውሬው ሰባተኛ ራስ የምትሆንበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር።

      5 ብሪታንያ በዓለም ላይ የበላይነት እያገኘች ብትሄድም በሰሜን አሜሪካ የሚገኙት ቅኝ ግዛቶቿ ተገንጥለው ዩናይትድ ስቴትስ የሚባል መንግሥት መሠረቱ። ያም ሆኖ ዩናይትድ ስቴትስ ኃያል መንግሥት እንዲሆን ብሪታንያ በባሕር ኃይሏ አማካኝነት እገዛ አድርጋለች። የጌታ ቀን በ1914 ሲጀምር ብሪታንያ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሰፊ ግዛት የመሠረተች ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው ጠንካራ ኢንዱስትሪ ገንብታ ነበር።b በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ከብሪታንያ ጋር ልዩ ጥምረት ፈጠረች። የአውሬው ሰባተኛ ራስ ማለትም አንግሎ አሜሪካ፣ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኖ ብቅ ያለው በዚህ ጊዜ ነው። ይህ ራስ በሴቲቱ ዘር ላይ ምን ያደርግ ይሆን?

      6. ሰባተኛው ራስ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ምን አደረገ?

      6 የጌታ ቀን ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ፣ ሰባተኛው ራስ በአምላክ ሕዝብ ላይ ይኸውም ምድር ላይ በሚገኙት የክርስቶስ ወንድሞች ላይ ጥቃት ሰነዘረ። (ማቴ. 25:40) ኢየሱስ፣ በእሱ መገኘት ወቅት የዘሩ ክፍል የሆኑት ቀሪ አባላት በምድር ላይ እንደሚኖሩና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትጋት እንደሚወጡ ተናግሯል። (ማቴ. 24:45-47፤ ገላ. 3:26-29) የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት በእነዚህ ቅዱሳን ላይ ጦርነት አውጆ ነበር። (ራእይ 13:3, 7) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ይህ መንግሥት የአምላክን ሕዝቦች ጨቁኗል፤ አንዳንድ ጽሑፎቻቸውን አግዷል፤ እንዲሁም የታማኝና ልባም ባሪያ ወኪሎችን እስር ቤት ጨምሯቸዋል። በሰባተኛው ራስ ተጽዕኖ ምክንያት የስብከቱ ሥራ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሞተ ያህል ሆኖ ነበር። ይሖዋ ይህ ሁኔታ እንደሚፈጸም አስቀድሞ ለዮሐንስ ገልጦለታል። በተጨማሪም አምላክ፣ የሴቲቱ ዘር ሁለተኛ ክፍል የሆኑት ቅቡዓን መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸውን በድጋሚ እንደሚያቀጣጥሉ ነግሮት ነበር። (ራእይ 11:3, 7-11) ይህ ትንቢት በትክክል እንደተፈጸመ ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ያሳያል።

      አንግሎ አሜሪካ እና የብረትና የሸክላ ድብልቅ የሆነው እግር

      7. በአውሬው ሰባተኛ ራስና በግዙፉ ምስል መካከል ያለው ተዛማጅነት ምንድን ነው?

      7 በአውሬው ሰባተኛ ራስና በግዙፉ ምስል መካከል ያለው ተዛማጅነት ምንድን ነው? ዩናይትድ ስቴትስ የወጣችው ከብሪታንያ ነው፤ ብሪታንያ ደግሞ የወጣችው ከሮም በመሆኑ በተዘዋዋሪ መንገድ ዩናይትድ ስቴትስም የወጣችው ከሮም ግዛት ነው። ስለ ምስሉ እግርስ ምን ማለት ይቻላል? እግሩ የብረትና የሸክላ ድብልቅ እንደሆነ ተገልጿል። (ዳንኤል 2:41-43⁠ን አንብብ።) የምስሉን እግር አስመልክቶ የተነገረው ይህ ሁኔታ የተከሰተው ሰባተኛው ራስ ማለትም አንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል በሆነበት ጊዜ ላይ ነው። ሸክላ የተቀላቀለበት ብረት ከንጹሕ ብረት ጋር እኩል ጥንካሬ እንደማይኖረው ሁሉ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትም ከወጣበት ግዛት ይኸውም ከሮም ያነሰ ኃይል ይኖረዋል። ታዲያ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ደካማ የሆነው እንዴት ነው?

      8, 9. (ሀ) ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት እንደ ብረት ያለ ጥንካሬ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በምስሉ እግር ላይ የሚገኘው ሸክላ የሚያመለክተው ምንድን ነው?

      8 የአውሬው ሰባተኛ ራስ እንደ ብረት ያለ ጥንካሬውን ያሳየባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ አንደኛውን የዓለም ጦርነት በድል በማጠናቀቅ ኃይሉን አሳይቷል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም ሰባተኛው ራስ እንደ ብረት ያለ ኃይል ያለው መሆኑ በግልጽ ታይቷል።c ከዚህ ጦርነት በኋላም ቢሆን ሰባተኛው ራስ እንደ ብረት ያለ ጥንካሬውን ማሳየቱን ቀጥሏል። ይሁንና ሰባተኛ ራስ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ብረቱ ከሸክላ ጋር ተደባልቆ ነበር።

      9 የይሖዋ አገልጋዮች የምስሉ እግር ምን ትርጉም እንዳለው ለማወቅ ለረጅም ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ዳንኤል 2:41 የብረቱና የሸክላው ድብልቅ የሚያመለክተው በርካታ መንግሥታትን ሳይሆን አንድን “መንግሥት” ብቻ እንደሆነ ይናገራል። በመሆኑም ሸክላው የሚያመለክተው በንጹሕ ብረት ከተመሰለው ከሮም ግዛት ያነሰ ጥንካሬ ያለው የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ተጽዕኖ በሚያሳድርባቸው የምድር ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን የእሱን አቅም የሚያዳክሙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ነው። ሸክላው ‘የሰው ዘርን’ ማለትም ተራውን ሕዝብ እንደሚያመለክት የዳንኤል መጽሐፍ ይገልጻል። (ዳን. 2:43 የ1954 ትርጉም) በአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ውስጥ ሰዎች በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንቅስቃሴ፣ በሠራተኛ ማኅበራትና ነፃነት ለማግኘት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት መብታቸውን ለማስከበር ሞክረዋል። ተራው ሕዝብ፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት እንደ ብረት ያለ ጥንካሬውን እንዳያሳይ አዳክሞታል። በተጨማሪም የምርጫ ተወዳዳሪዎች የሚያገኙት ተቀራራቢ ውጤትና ተጻራሪ የሆኑ የፖለቲካ አመለካከቶች መኖራቸው ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ መሪዎችም እንኳ ፖሊሲዎቻቸውን ለማስፈጸም የሚያስችል የተሟላ ሥልጣን እንዳይኖራቸው አድርጓል። ዳንኤል ይህ “መንግሥት በከፊሉ ብርቱ በከፊሉ ደካማ” እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል።​—ዳን. 2:42፤ 2 ጢሞ. 3:1-3

      10, 11. (ሀ) የምስሉ “እግሮች” የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው? (ለ) ስለ ጣቶቹ ቁጥር ምን ብለን መደምደም እንችላለን?

      10 በብሪታንያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል የተመሠረተው ልዩ ዝምድና በ21ኛው መቶ ዘመንም የቀጠለ ሲሆን እነዚህ አገሮች ከዓለም ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በአብዛኛው ተመሳሳይ አቋም ያራምዳሉ። ግዙፉን ምስልና አውሬውን በተመለከተ የተነገሩት ትንቢቶች እንደሚያሳዩት የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን የሚተካ ሌላ ኃያል መንግሥት ወደፊት አይነሳም። ይህ የመጨረሻው የዓለም ኃያል መንግሥት፣ በብረት እግር ከተመሰለው ከሮም ይልቅ ደካማ ቢሆንም የሚፈራርሰው በራሱ አይደለም።

      11 የጣቶቹ ቁጥርስ የሚያመለክተው ነገር አለ? ዳንኤል ባያቸው ሌሎች ራእዮች ላይ ትንቢታዊ ትርጉም ያላቸውን ቁጥሮች ለይቶ ተናግሯል፤ ለምሳሌ በተለያዩ አራዊት ራሶች ላይ የታዩትን ቀንዶች ቁጥር ጠቅሷል። ይሁንና ዳንኤል ስለ ምስሉ ሲናገር የጣቶቹን ቁጥር አልገለጸም። በመሆኑም የምስሉ እጆችና እግሮች እንዲሁም የእጆቹ ጣቶች፣ ቁጥራቸው ምንም ዓይነት ትርጉም እንደሌለው ሁሉ የጣቶቹ ቁጥርም ምንም ትርጉም ያለው አይመስልም። ይሁንና ዳንኤል የምስሉ እግር ጣቶች ከብረትና ከሸክላ እንደተሠሩ ተናግሯል። ዳንኤል ከሰጠው መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው የአምላክን መንግሥት የሚወክለው “ድንጋይ” ምስሉን በሚመታበት ጊዜ የዓለም ኃያል መንግሥት የሚሆነው አንግሎ አሜሪካ ነው።​—ዳን. 2:45

      አንግሎ አሜሪካ እና ሁለት ቀንድ ያለው አውሬ

      12, 13. ሁለት ቀንድ ያለው አውሬ ምንን ያመለክታል? ምንስ ያደርጋል?

      12 የአንግሎ አሜሪካ መንግሥት የብረትና የሸክላ ድብልቅ ቢሆንም ኢየሱስ ለዮሐንስ የሰጠው ራእይ እንደሚጠቁመው ይህ ኃያል መንግሥት በመጨረሻዎቹ ቀኖች ቁልፍ ሚና መጫወቱን ይቀጥላል። እንዴት? ዮሐንስ እንደ ዘንዶ የሚናገር ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ በራእይ ተመልክቶ ነበር። ይህ እንግዳ የሆነ አውሬ የሚያመለክተው ምንድን ነው? ሁለት ቀንዶች ያሉት መሆኑ ጥምር መንግሥት እንደሆነ ያሳያል። ዮሐንስ የተመለከተው የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን ሲሆን በዚህ ጊዜ ግን ልዩ ሚና እንደሚጫወት ጠቁሟል።​—ራእይ 13:11-15⁠ን አንብብ።

      13 ሁለት ቀንድ ባለው በዚህ አውሬ አስተባባሪነት የአውሬው ምስል ይፈጠራል። ዮሐንስ የአውሬው ምስል እንደሚገለጥ ከዚያም እንደሚጠፋና በኋላም እንደገና እንደሚገለጥ ጽፏል። በብሪታንያና በዩናይትድ ስቴትስ አስተባባሪነት የዓለምን መንግሥታት አንድ ለማድረግና እነሱን ወክሎ ለመሥራት የተቋቋመው ድርጅት ያጋጠመው ሁኔታ ይኸው ነው።d ይህ ድርጅት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋመ ሲሆን የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በመባል ይጠራ ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀምር ግን ይህ ድርጅት ጠፋ። ጦርነቱ እየተካሄደ ሳለ የአምላክ ሕዝቦች በራእይ መጽሐፍ ላይ በሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት የአውሬው ምስል ድጋሚ እንደሚገለጥ ተናገሩ። እንደተባለውም የአውሬው ምስል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመባል በድጋሚ ብቅ አለ።​—ራእይ 17:8

      14. የአውሬው ምስል፣ “ስምንተኛ ንጉሥ” የሆነው እንዴት ነው?

      14 ዮሐንስ፣ የአውሬውን ምስል “ስምንተኛ ንጉሥ” በማለት ጠርቶታል። ይሁንና ስምንተኛ ንጉሥ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የአውሬው ስምንተኛ ራስ እንደሆነ ተደርጎ እንዳልተገለጸ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ የዚህ አውሬ ምስል ነው። ይህ የአውሬው ምስል ኃይል ሊያገኝ የቻለው ከአባል አገሮች በተለይም ደግሞ የጀርባ አጥንት ከሆነለት ከአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። (ራእይ 17:10, 11) ይሁን እንጂ ይህ ምስል እንደ ንጉሥ በመሆን አንድ ለየት ያለ ነገር ለማከናወን ሥልጣን ይቀበላል፤ ይህ ክንውን የዓለምን ታሪክ የሚለውጡ ተከታታይ ክስተቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል።

      የአውሬው ምስል ጋለሞታይቱን ይቦጫጭቃታል

      15, 16. ጋለሞታይቱ ማንን ታመለክታለች? ደጋፊዎቿስ ምን እየሆኑ ነው?

      15 አንዲት ጋለሞታ፣ የአውሬው ምስል የሆነውን ቀዩን አውሬ እንደፈለገች በመምራት ስትጋልበው ዮሐንስ ተመልክቷል። ይህች ምሳሌያዊ ጋለሞታ “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚል ስም ተሰጥቷታል። (ራእይ 17:1-6) ጋለሞታይቱ፣ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ፣ በዋነኝነት ደግሞ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትን ትወክላለች። የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች የአውሬውን ምስል ባርከዋል፤ እንዲሁም በእሱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት አድርገዋል።

      16 ታላቂቱ ባቢሎን፣ እሷን የሚደግፉ ሰዎችን የሚያመለክቱት ውኃዎቿ በጌታ ቀን ላይ በአስገራሚ ፍጥነት ሲደርቁ ተመልክታለች። (ራእይ 16:12፤ 17:15) ለምሳሌ የአውሬው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕልውና ሲመጣ በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ የምታሳድረው ሕዝበ ክርስትና የምዕራቡን ዓለም ተቆጣጥራ ነበር። ዛሬ ግን የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትና ቀሳውስቶቻቸው በምዕመኖቻቸው ዘንድ የነበራቸውን አክብሮትና ድጋፍ አጥተዋል። እንዲያውም ብዙ ሰዎች፣ ሃይማኖት ለግጭቶች መንስኤ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሃይማኖት በማኅበረሰቡ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዲቆም ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ የምዕራቡ ዓለም ምሁራን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

      17. የሐሰት ሃይማኖት በቅርቡ ምን ይሆናል? ለምንስ?

      17 የሐሰት ሃይማኖት ግን እንዲህ እንደዋዛ የሚጠፋ አይደለም። አምላክ በመንግሥታት ልብ ውስጥ አንድ ሐሳብ እስኪያኖር ድረስ ጋለሞታይቱ ነገሥታትን እሷ በፈለገችው አቅጣጫ በመምራት በእነሱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት ማድረጓን ትቀጥላለች። (ራእይ 17:16, 17⁠ን አንብብ።) በቅርቡ ይሖዋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወከሉትንና በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉትን ፖለቲካዊ ኃይሎች ተጠቅሞ በሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። እነዚህ መንግሥታት በጋለሞታይቱ ላይ እርምጃ ስለሚወስዱ ተጽዕኖ ማሳደሯ ያከትማል፤ እንዲሁም ሀብቷ ይጠፋል። ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ይህን ማሰብ የማይመስል ነገር ነበር። አሁን ግን ሁኔታዎች መልካቸውን እየቀየሩ ነው፤ በቀዩ አውሬ ላይ የተቀመጠችው ጋለሞታ ሚዛኗን መጠበቅ ስላቃታት ልትወድቅ እየተንገዳገደች ነው። ያም ሆኖ ከተቀመጠችበት የምትወድቀው ሸርተት ብላ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አወዳደቋ ድንገተኛና አስደንጋጭ ይሆናል።​—ራእይ 18:7, 8, 15-19

      የአውሬዎቹ መጨረሻ

      18. (ሀ) አውሬው ምን ያደርጋል? ውጤቱስ ምን ይሆናል? (ለ) በ⁠ዳንኤል 2:44 ላይ የአምላክ መንግሥት የትኞቹን መንግሥታት እንደሚያጠፋ ተገልጿል? (ገጽ 17 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

      18 በምድር ላይ የሚገኘውና የሰይጣን ፖለቲካዊ መሣሪያ የሆነው አውሬ፣ የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ በአምላክ መንግሥት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ይሞክራል። የምድር ነገሥታት ሰማይ በሚኖሩት ላይ ጥቃት መሰንዘር ስለማይችሉ በምድር ላይ በሚገኙና የአምላክን መንግሥት በሚደግፉ ሕዝቦች ላይ ቁጣቸውን ይገልጻሉ። እርግጥ ውጤቱ ሳይታለም የተፈታ ነው። (ራእይ 16:13-16፤ 17:12-14) ዳንኤል ይህ የመጨረሻ ጦርነት የሚኖረውን አንድ ገጽታ ይነግረናል። (ዳንኤል 2:44⁠ን አንብብ።) በ⁠ራእይ 13:1 ላይ የተጠቀሰው አውሬ፣ የዚህ አውሬ ምስልና ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ ድምጥማጣቸው ይጠፋል።

      19. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? አሁን ምን የምናደርግበት ጊዜ ነው?

      19 የምንኖረው የአውሬው ሰባተኛ ራስ ሥልጣን ላይ ባለበት ወቅት ነው። ይህ አውሬ ከመጥፋቱ በፊት ስምንተኛ ራስ እንደሚኖረው አልተገለጸም። በመሆኑም የሐሰት ሃይማኖቶች በሚጠፉበት ጊዜ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኖ የሚቀጥለው አንግሎ አሜሪካ ነው። በዳንኤልና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተመለከትናቸው ትንቢቶች በዝርዝር ተፈጽመዋል። የሐሰት ሃይማኖት ጥፋትም ሆነ የአርማጌዶን ጦርነት በቅርቡ እንደሚመጣ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አምላክ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን አስቀድሞ ገልጦልናል። ታዲያ በትንቢት ለተነገሩት ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት እንሰጣለን? (2 ጴጥ. 1:19) እንግዲያው ከይሖዋ ጎን ለመቆምና የእሱን መንግሥት ለመደገፍ ጊዜው አሁን ነው።​—ራእይ 14:6, 7

      [የግርጌ ማስታወሻዎች]

      a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሥር ቁጥር ብዙውን ጊዜ ሙላትን ለማመልከት ይሠራበታል፤ በዚህ አገባቡም ከሮም ግዛቶች የወጡትን መንግሥታት በሙሉ ያመለክታል።

      b እርግጥ ነው፣ ጥምር ለሆነው የዓለም ኃያል መንግሥት መገኛ የሆኑት ብሪታንያና አሜሪካ በ18ኛው መቶ ዘመን ላይ በየፊናቸው ኃያል መንግሥት ሆነው ነበር፤ ይሁንና ዮሐንስ ይህ መንግሥት ሰባተኛ ራስ በመሆን ብቅ የሚለው በጌታ ቀን ላይ እንደሆነ ተናግሯል። እንዲያውም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘት የጀመሩት ‘በጌታ ቀን’ ላይ ነው። (ራእይ 1:10) ሰባተኛው ራስ የሆኑት ብሪታንያና አሜሪካ ግንባር ፈጥረው የዓለም ኃያል መንግሥት የሆኑት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነው።

      c ዳንኤል ይህ ንጉሥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሚያስከትለውን ጥፋት አስቀድሞ በራእይ የተመለከተ ሲሆን “አሠቃቂ ጥፋት ይፈጽማል” በማለት ጽፏል። (ዳን. 8:24) ለምሳሌ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአንግሎ አሜሪካ ጠላት በሆነ አገር ላይ ሁለት የአቶሚክ ቦንቦችን በመጣል ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ አሰቃቂ ጥፋት አድርሳለች።

      d ራእይ​—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 240, 241, 253 ተመልከት።

      [በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ‘እነዚያ መንግሥታት ሁሉ’ የተባሉት እነማን ናቸው?

      በ⁠ዳንኤል 2:44 ላይ የሚገኘው ትንቢት የአምላክ መንግሥት “እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል” ይላል። እዚህ ጥቅስ ላይ የተጠቀሱት መንግሥታት የሚያመለክቱት በምስሉ የተለያዩ ክፍሎች የተመሰሉትን መንግሥታት ብቻ ነው።

      ስለ ሌሎቹ ሰብዓዊ መንግሥታትስ ምን ማለት ይቻላል? ተመሳሳይ ስለሆነ ጉዳይ የሚናገረው በራእይ መጽሐፍ ላይ ያለው ትንቢት ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጠናል። ትንቢቱ መላው ‘የዓለም ነገሥታት’ በይሖዋ ላይ ለመነሳት “ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን” እንደሚሰበሰቡ ይገልጻል። (ራእይ 16:14፤ 19:19-21) በመሆኑም በአርማጌዶን የሚጠፉት በምስሉ ላይ የተገለጹት መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ መላው ሰብዓዊ አገዛዝ ነው።

  • የስምንቱ ነገሥታት ማንነት ተገለጠ
    መጠበቂያ ግንብ—2012 | ሰኔ 15
    • የስምንቱ ነገሥታት ማንነት ተገለጠ

      በመንፈስ መሪነት የተጻፉት የዳንኤልና የዮሐንስ ዘገባዎች በምድር ላይ የሚነሱትን ስምንት ነገሥታት ወይም ሰብዓዊ አገዛዞች ለይተን እንድናውቅ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ነገሥታት የሚነሱበትን ቅደም ተከተል ማስተዋል እንድንችልም ይረዱናል። ይሁንና የእነዚህን ትንቢቶች ሚስጥር መረዳት የምንችለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመጀመሪያ ትንቢት ማስተዋል ከቻልን ብቻ ነው።

      በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰይጣን በተለያዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ወይም መንግሥታት አማካኝነት ዘሩን ሲያደራጅ ቆይቷል። (ሉቃስ 4:5, 6) ይሁን እንጂ በአምላክ ሕዝቦች ይኸውም በእስራኤል ብሔርም ሆነ በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩት ሰብዓዊ መንግሥታት በጣም ጥቂት ናቸው። ከዚህ አንጻር ዳንኤልና ዮሐንስ በተመለከቷቸው ራእዮች ላይ የተጠቀሱት ኃያላን መንግሥታት ስምንት ብቻ ናቸው።

      [በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/​ሥዕል]

      (መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

      በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ

      የሚገኙ ትንቢቶች የሚገኙ ትንቢቶች

      1. ግብፅ

      2. አሦር

      3. ባቢሎን

      4. ሜዶ ፋርስ

      5. ግሪክ

      6. ሮም

      7. ብሪታንያና

      ዩናይትድ ስቴትስa

      8. የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና

      የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትb

      የአምላክ ሕዝብ

      2000 ዓ.ዓ.

      አብርሃም

      1500

      የእስራኤል ብሔር

      1000

      ዳንኤል 500

      ዓ.ዓ./ዓ.ም.

      ዮሐንስ

      የአምላክ እስራኤል 500

      1000

      1500

      2000 ዓ.ም.

      [የግርጌ ማስታወሻዎች]

      a በፍጻሜው ዘመን ላይ ሁለቱም ይኖራሉ። ገጽ 19⁠ን ተመልከት።

      b በፍጻሜው ዘመን ላይ ሁለቱም ይኖራሉ። ገጽ 19⁠ን ተመልከት።

      [ሥዕሎች]

      ግዙፉ ምስል (ዳን. 2:31-45)

      ከባሕር የወጡት አራት አራዊት (ዳን. 7:3-8, 17, 25)

      አውራው በግና ፍየሉ (ዳን. ምዕ. 8)

      ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ (ራእይ 13:1-10, 16-18)

      ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ፣ የአውሬው ምስል እንዲፈጠር ያስተባብራል (ራእይ 13:11-15)

      [የሥዕል ምንጭ]

      Photo credits: Egypt and Rome: Photograph taken by courtesy of the British Museum; Medo-Persia: Musée du Louvre, Paris

  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    መጠበቂያ ግንብ—2012 | ሰኔ 15
    • የአንባቢያን ጥያቄዎች

      የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ የተገለጸው ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነው መቼ ነው?

      ▪ ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልም ያየው ግዙፉ ምስል በዓለም ላይ የተነሱ ኃያላን መንግሥታትን በሙሉ የሚወክል አይደለም። (ዳን. 2:31-45) ከዚህ ይልቅ ምስሉ የሚያመለክተው በዳንኤል ዘመንና ከዚያ ወዲህ የተነሱ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ አምስት ኃያላን መንግሥታትን ብቻ ነው።

      ዳንኤል ስለ ምስሉ የሰጠው ማብራሪያ እንደሚያመለክተው የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ወደ ዓለም መድረክ ብቅ የሚለው ሮምን ድል አድርጎ ሳይሆን ከራሱ ከሮም መንግሥት በመውጣት ነው። የምስሉ ቅልጥሞች ላይ ያለው ብረት እግሮቹን ጨምሮ እስከ ጣቶቹ ድረስ እንደሚዘልቅ ዳንኤል ተመልክቷል። (እግሮቹና ጣቶቹ ላይ ብረቱ ከሸክላ ጋር ተቀላቅሏል።)a ይህም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ከብረት እግሮቹ እንደሚወጣ ያመለክታል። ታሪክም ቢሆን የዚህን ማብራሪያ ትክክለኛነት ያረጋግጣል። ቀደም ሲል የሮም ግዛት ክፍል የነበረችው ብሪታንያ በ1700ዎቹ መጨረሻ ላይ በዓለም መድረክ ጎላ ብላ መታየት ጀመረች። በኋላም ዩናይትድ ስቴትስ ኃያል መንግሥት መሆን ጀመረች። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ የተገለጸው ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት ገና አልተቋቋመም ነበር። ለምን? ምክንያቱም ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ ልዩ የሆነ ጥምረት ገና አልፈጠሩም። ይህ ጥምረት የተፈጠረው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነው።

      በዚያ ጊዜ “የመንግሥቱ ልጆች” ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘው በብሩክሊን ኒው ዮርክ ስለሆነ በአብዛኛው እንቅስቃሴ የሚያደርጉት በዩናይትድ ስቴትስ ነበር። (ማቴ. 13:36-43) ቅቡዓኑ በብሪታንያ መንግሥት ሥር በሚገኙ አገሮች ውስጥ በቅንዓት እየሰበኩ ነበር። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብሪታንያና አሜሪካ የጋራ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት ልዩ የሆነ ጥምረት ፈጠሩ። በተጨማሪም እነዚህ አገሮች ‘የሴቲቱ’ ዘር ክፍል የሆኑት ቅቡዓን የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች በማገድና የስብከቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይመሩ የነበሩትን በማሰር ጠላትነታቸውን አሳይተዋል፤ በጦርነቱ ምክንያት የተቀሰቀሰው ብሔራዊ ስሜት በጣም እየተጋጋለ መምጣቱ ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።​—ራእይ 12:17

      በመሆኑም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አኳያ ስንመለከተው ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት የተቋቋመው ብሪታንያ በዓለም መድረክ ጎላ ብላ መታየት በጀመረችበት በ1700ዎቹ መጨረሻ ላይ ሳይሆን በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ ነው።b

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ