የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ልጠመቅ?—ክፍል 1፦ የጥምቀት ትርጉም
    የወጣቶች ጥያቄ
    • አንድ ወጣት በይሖዋ ምሥክሮች የክልል ስብሰባ ላይ ገንዳ ውስጥ ሲጠመቅ።

      የወጣቶች ጥያቄ

      ልጠመቅ?—ክፍል 1፦ የጥምቀት ትርጉም

      በየዓመቱ በይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ በርካታ ወጣቶች ይጠመቃሉ። አንተስ ይህን እርምጃ ለመውሰድ እያሰብክ ነው? ከሆነ በመጀመሪያ ራስን መወሰን እና መጠመቅ ምን ትርጉም እንዳለው መረዳት ይኖርብሃል።

      • ጥምቀት ምንድን ነው?

      • ራስን መወሰን ምንድን ነው?

      • መጠመቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      • እኩዮችህ ምን ይላሉ?

      • የተሳሳተ አመለካከት እና እውነታ

      ጥምቀት ምንድን ነው?

      በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ጥምቀት የሚያመለክተው በውኃ መረጨትን ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅን ነው፤ ይህ ደግሞ ልዩ ትርጉም አለው።

      • ስትጠመቅ ውኃ ውስጥ መጥለቅህ ከዚህ በኋላ የምትኖረው ራስህን ለማስደሰት እንዳልሆነ ለሰዎች ያሳያል።

      • ከውኃው መውጣትህ አምላክን በማስደሰት ላይ ያተኮረ አዲስ ሕይወት መምራት እንደጀመርክ ያሳያል።

      መጠመቅህ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ መሥፈርት የማውጣት ሥልጣን ያለው ይሖዋ እንደሆነ አምነህ መቀበልህን በይፋ ያሳያል፤ በተጨማሪም ይሖዋ የሚጠብቅብህን ነገር በፈቃደኝነት ለማድረግ ቃል መግባትህን ለሰዎች ታሳያለህ።

      ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ይሖዋን በመታዘዝ ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት በሕዝብ ፊት ቃል መግባትህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛ ዮሐንስ 4:19⁠ን እና ራእይ 4:11⁠ን ተመልከት።

      ራስን መወሰን ምንድን ነው?

      ከመጠመቅህ በፊት ብቻህን ሆነህ ራስህን ለይሖዋ መወሰን ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

      በግልህ ወደ ይሖዋ ጸሎት በማቅረብ እሱን ለዘላለም ለማገልገል ቃል መግባትህን እንዲሁም ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ወይም ሌሎች ምንም ቢያደርጉ የእሱን ፈቃድ እንደምታደርግ ትነግረዋለህ።

      ጥምቀት ብቻህን ሆነህ ያደረግከውን ይህን ውሳኔ ለሰዎች የምታሳይበት ሥነ ሥርዓት ነው። መጠመቅህ ራስህን መካድህንና ከዚህ በኋላ የይሖዋ ንብረት መሆንህን ለሌሎች ያሳያል።—ማቴዎስ 16:24

      ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የይሖዋ ንብረት መሆንህ የተሻለ ሕይወት እንድትመራ የሚረዳህ እንዴት ነው? ኢሳይያስ 48:17, 18⁠ን እና ዕብራውያን 11:6⁠ን ተመልከት።

      መጠመቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      ኢየሱስ፣ መጠመቅ ከደቀ መዛሙርቱ የሚጠበቅ ብቃት እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ስለዚህ ዛሬም ጥምቀት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት ነው። እንዲያውም ጥምቀት ለመዳን አስፈላጊ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—1 ጴጥሮስ 3:21

      ሆኖም ለመጠመቅ የሚያነሳሳህ ለይሖዋ ያለህ ፍቅርና አድናቆት ሊሆን ይገባል። እንደ መዝሙራዊው ዓይነት አመለካከት ሊኖርህ ይገባል፤ መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለይሖዋ ምን እመልስለታለሁ? [የይሖዋን] ስም እጠራለሁ። . . . ስእለቴን ለይሖዋ እፈጽማለሁ።”—መዝሙር 116:12-14

      ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ይሖዋ ምን መልካም ነገር አድርጎልሃል? ምን ልትመልስለትስ ትችላለህ? ዘዳግም 10:12, 13⁠ን እና ሮም 12:1⁠ን ተመልከት።

      እኩዮችህ ምን ይላሉ?

      ሚጂን።

      “ራስን መወሰን ማለት ለይሖዋ ቃል መግባት ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ነገር ነው። ሆኖም ራሳችንን ለይሖዋ ከወሰንን በኋላ የምንመራው ሕይወት በበረከት የተሞላ ነው። ምክንያቱም ራሳችንን ልንንከባከብ ከምንችለው በላይ ይሖዋ ይንከባከበናል።”—ሚጂን

      ኤምበር።

      “ይሖዋ እስካሁንም አንተን እንደሚወድህ አሳይቷል። ስትጠመቅ አንተም እሱን ከልብህ እንደምትወደው ታሳያለህ። መጠመቅ ትልቅ መብት ነው፤ ብዙ በረከትም ያስገኛል!”—ኤምበር

      ጁሊያን።

      “ልታደርጓቸው ከምትችሏቸው ውሳኔዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ራሳችሁን ለአምላክ ለመወሰንና ለመጠመቅ የምታደርጉት ውሳኔ ነው። ሆኖም ይህ ሊያስፈራችሁ አይገባም። ዝግጁ እስከሆናችሁና ይህን ውሳኔ ለማድረግ ያነሳሳችሁ ምክንያት ተገቢ እስከሆነ ድረስ ጥምቀት በሕይወታችሁ ከምታደርጓቸው ውሳኔዎች ሁሉ የተሻለው ነው።”—ጁሊያን

      የተሳሳተ አመለካከት እና እውነታ

      የተሳሳተ አመለካከት — ለመጠመቅ የሚያስችል ብስለት ያላቸው አዋቂዎች ብቻ ናቸው።

      እውነታው — የአንድ ሰው ብስለት በዋነኝነት የተመካው በዕድሜው ላይ ሳይሆን ግለሰቡ ለይሖዋ ባለው ፍቅርና እሱን ለመታዘዝ ባለው ተነሳሽነት ላይ ነው። ዮሴፍ፣ ሳሙኤል እና ኢዮስያስ ገና በልጅነታቸው እንዲህ ያለ ብስለት አሳይተዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ወጣቶችም እንዲህ ያለ ብስለት ያሳያሉ።

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሕፃን እንኳ ባሕርይው ንጹሕና ትክክል መሆኑ በአድራጎቱ ይታወቃል።”—ምሳሌ 20:11

      የተሳሳተ አመለካከት — ጓደኞችህ ከተጠመቁ አንተም ልትጠመቅ ይገባል።

      እውነታው — ራስን መወሰን እና መጠመቅ በፈቃደኝነት ሊደረግ የሚገባው የግል ውሳኔ ነው። የሆነ ዕድሜ ላይ ስለደረስክ፣ እኩዮችህ ሲጠመቁ ስላየህ ወይም ሌሎች እንደሚጠብቁብህ ስለተሰማህ ብቻ ይህን እርምጃ ልትወስድ አይገባም።

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “[የአምላክ ሕዝብ] በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል።”—መዝሙር 110:3

      የተሳሳተ አመለካከት — እስካልተጠመቅክ ድረስ ብታጠፋም አትጠየቅም።

      እውነታው — በይሖዋ ፊት ተጠያቂ የምትሆነው ስትጠመቅ ሳይሆን በእሱ ዓይን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ስታውቅ ነው።

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አንድ ሰው ትክክል የሆነውን ነገር እንዴት ማድረግ እንዳለበት እያወቀ ሳያደርገው ቢቀር ኃጢአት ይሆንበታል።”—ያዕቆብ 4:17

      ጠቃሚ ምክር፦ ራስን መወሰንና መጠመቅ የሚያስፈራህ ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ ለምን እንደሆነ ለማወቅ እንዲሁም ፍርሃትህን ለማሸነፍ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ። ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 37⁠ን ማንበብህ እንዲህ ለማድረግ ይረዳሃል።

      ክለሳ፦ መጠመቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      • ኢየሱስ፣ መጠመቅ ከደቀ መዛሙርቱ የሚጠበቅ ብቃት እንደሆነ ገልጿል።

      • ጥምቀት ለመዳን አስፈላጊ ነው።

      • ራስን ወስኖ በመጠመቅ የይሖዋ አገልጋይ መሆን ትልቅ መብት ነው።

  • ልጠመቅ?—ክፍል 2፦ ለጥምቀት መዘጋጀት
    የወጣቶች ጥያቄ
    • አንዲት ወጣት መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ተጠቅማ ስለ ጥምቀት ምርምር ስታደርግ።

      የወጣቶች ጥያቄ

      ልጠመቅ?—ክፍል 2፦ ለጥምቀት መዘጋጀት

      የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች እየተከተልክ እንዲሁም ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት እየጣርክ ከሆነ ስለ ጥምቀት ማሰብህ አይቀርም። ታዲያ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆንህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?a

      በዚህ ርዕስ ውስጥ

      • ምን ያህል እውቀት ሊኖረኝ ይገባል?

      • ምን ዓይነት ምግባር ሊኖረኝ ይገባል?

      • እኩዮችህ ምን ይላሉ?

      ምን ያህል እውቀት ሊኖረኝ ይገባል?

      ለጥምቀት መዘጋጀት ሲባል በትምህርት ቤት ፈተና ለማለፍ እንደሚደረገው አንዳንድ መረጃዎችን መሸምደድ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘የማሰብ ችሎታህን በመጠቀም’ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ነገር እውነት ስለመሆኑ ያለህን እምነት ማጠናከር ይኖርብሃል። (ሮም 12:1) ለምሳሌ ያህል፦

      • አምላክ መኖሩንና ልታመልከው እንደሚገባ ታምናለህ?

        መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታል።”—ዕብራውያን 11:6

        ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በአምላክ የማምነው ለምንድን ነው?’ (ዕብራውያን 3:4) ‘ላመልከው የሚገባውስ ለምንድን ነው?’—ራእይ 4:11

        እገዛ ትፈልጋለህ? “ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?—ክፍል 1፦ አምላክ መኖሩን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

      • መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ታምናለህ?

        መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመገሠጽ ይጠቅማሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16

        ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሐሳብ የያዘ መጽሐፍ እንዳልሆነ የማምነው ለምንድን ነው?’—ኢሳይያስ 46:10፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13

        እገዛ ትፈልጋለህ? “መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅመኝ የሚችለው እንዴት ነው?—ክፍል 1፦ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

      • ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም በክርስቲያን ጉባኤ እንደሚጠቀም ታምናለህ?

        መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “[ለአምላክ] በጉባኤው አማካኝነትና በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት በትውልዶች ሁሉ ለዘላለም ክብር ይሁን።”—ኤፌሶን 3:21

        ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የማገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሰዎች ሳይሆን ከይሖዋ የመጣ እንደሆነ ይሰማኛል?’ (ማቴዎስ 24:45) ‘ወላጆቼ በማይችሉበት ጊዜም በስብሰባዎች ላይ እገኛለሁ? (ወላጆችህ የሚፈቅዱልህ ከሆነ ማለት ነው።)’—ዕብራውያን 10:24, 25

        እገዛ ትፈልጋለህ? “በስብሰባ አዳራሽ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ያለብኝ ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

      ምን ዓይነት ምግባር ሊኖረኝ ይገባል?

      መጠመቅ እንድትችል ፍጹም መሆን አይጠበቅብህም። ሆኖም ‘ክፉ ከሆነ ነገር መራቅና መልካም የሆነውን ማድረግ’ ከልብህ እንደምትፈልግ በምግባርህ ማሳየት ይኖርብሃል። (መዝሙር 34:14) ለምሳሌ ያህል፦

      • አኗኗርህ ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ነው?

        መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ።”—1 ጴጥሮስ 3:16

        ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘“ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት” እንድችል የማስተዋል ችሎታዬን እንዳሠለጠንኩ ያሳየሁት እንዴት ነው?’ (ዕብራውያን 5:14) ‘የእኩዮቼን መጥፎ ተጽዕኖ የተቋቋምኩባቸውን ጊዜያት መጥቀስ እችላለሁ? ጓደኛ የማደርገው ትክክል የሆነውን ነገር እንዳደርግ የሚያበረታቱኝን ሰዎች ነው?’—ምሳሌ 13:20

        እገዛ ትፈልጋለህ? “ሕሊናዬን ማሠልጠን የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

      • ለድርጊትህ ኃላፊነት ትወስዳለህ?

        መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።”—ሮም 14:12

        ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ለራሴም ሆነ ለሌሎች ሐቀኛ ነኝ?’ (ዕብራውያን 13:18) ‘ስህተቴን አምናለሁ? ወይስ ስህተቴን ለመሸፋፈን ወይም በሌሎች ለማሳበብ እሞክራለሁ?’—ምሳሌ 28:13

        እገዛ ትፈልጋለህ? “ስህተት ስሠራ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

      • ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ለማጠናከር ጥረት እያደረግክ ነው?

        መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”—ያዕቆብ 4:8

        ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ስል የትኞቹን እርምጃዎች እየወሰድኩ ነው?’ ለምሳሌ ‘መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሬ አነብባለሁ?’ (መዝሙር 1:1, 2) ‘አዘውትሬ እጸልያለሁ?’ (1 ተሰሎንቄ 5:17) ‘በደፈናው ከመጸለይ ባለፈ ዝርዝር ጉዳዮችን እጠቅሳለሁ? ጓደኞቼ የይሖዋ ወዳጆች ናቸው?’—መዝሙር 15:1, 4

        እገዛ ትፈልጋለህ? “መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅመኝ የሚችለው እንዴት ነው?—ክፍል 2፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን አስደሳች ማድረግ” እና “መጸለይ ጥቅም አለው?” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።

      ጠቃሚ ምክር፦ ለጥምቀት ለመዘጋጀት እንዲረዳህ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 37⁠ን አንብብ። በተለይ በገጽ 308 እና 309 ላይ ለሚገኘው የመልመጃ ሣጥን ትኩረት ስጠው።

      a ራስን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ ስላለው ትርጉም እንዲሁም አስፈላጊነት የሚናገረውን “ልጠመቅ?—ክፍል 1” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

      እኩዮችህ ምን ይላሉ?

      ጋብሪዬላ።

      “የወጣቶች ጥያቄ በሚለው መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ስለ ጥምቀት የሚናገረው የመልመጃ ሣጥን ከመጠመቄ በፊት በየትኞቹ አቅጣጫዎች ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብኝ እንዳስተውል ረድቶኛል። በተጨማሪም ከተጠመቅኩ በኋላ ልደርስባቸው የምፈልጋቸውን ግቦች እንዳወጣ ረድቶኛል። ራስን ለይሖዋ መወሰን ትልቅ ኃላፊነት ያስከትላል፤ ሆኖም አንድ ሰው ሊያገኘው የሚችለው ከሁሉ የላቀ መብት ነው።”—ጋብሪዬላ

      ካሌብ።

      “መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጢሞቴዎስ ‘በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር’ የሚል ምክር እንደተሰጠው ይናገራል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:14) “የአምላክ ቃል የሚያስተምረው ነገር እውነት መሆኑን ሙሉ በሙሉ መተማመን እንድትችሉ ጊዜ ወስዳችሁ መጽሐፍ ቅዱስን አጥኑ። ራሳችሁን የምትወስኑት ለሰዎች ሳይሆን ለይሖዋ ነው፤ ስለዚህ ስለ ጥምቀት ስታስቡ በዋነኝነት ሊያሳስባችሁ የሚገባው ‘ይሖዋ ምን ይሰማዋል’ የሚለው ነው።”—ካሌብ

      ክለሳ፦ ለጥምቀት መዘጋጀት የምችለው እንዴት ነው?

      እምነትህን ፈትሽ። አምላክ መኖሩን ታምናለህ? ልታመልከው እንደሚገባስ ታምናለህ? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ታምናለህ? ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም በድርጅቱ እንደሚጠቀም ታምናለህ?

      ምግባርህን ፈትሽ። አኗኗርህ ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ነው? ለድርጊትህ ኃላፊነት ትወስዳለህ? ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ለማጠናከር ጥረት እያደረግክ ነው?

  • ልጠመቅ?—ክፍል 3፦ ያገደኝ ምንድን ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
    • አንድ ሰው ሐይቅ ውስጥ ሲጠመቅ ሌሎች ሰው ዳር ላይ ቆመው ያዩታል።

      የወጣቶች ጥያቄ

      ልጠመቅ?—ክፍል 3፦ ያገደኝ ምንድን ነው?

      ራስህን ለይሖዋ ስለመወሰንና ስለ መጠመቅ ስታስብ ፍርሃት ፍርሃት ይልሃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ፍርሃትህን ለማሸነፍ ይረዳሃል።

      በዚህ ርዕስ ውስጥ

      • ከተጠመቅኩ በኋላ ከባድ ስህተት ብሠራስ?

      • ጥምቀት የሚያስከትለው ኃላፊነት ቢያስፈራኝስ?

      • ይሖዋን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆንኩ ቢሰማኝስ?

      • እኩዮችህ ምን ይላሉ?

      ከተጠመቅኩ በኋላ ከባድ ስህተት ብሠራስ?

      አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? ከባድ ኃጢአት በመሥራቱ የተነሳ ከጉባኤ የተወገደ ሰው ታውቅ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13) በመሆኑም አንተም ተመሳሳይ ነገር እንዳያጋጥምህ ትፈራ ይሆናል።

      “መጀመሪያ ላይ ስለ መጠመቅ ሳስብ ‘ጥፋት ባጠፋስ’ የሚለው ጉዳይ ያስፈራኝ ነበር። እንዲህ ባደርግ ወላጆቼን በጣም እንደማሳፍራቸው ይሰማኝ ነበር።”—ሬቤካ

      ቁልፍ ጥቅስ፦ “ክፉ ሰው መንገዱን . . . ይተው፤ ምሕረት ወደሚያሳየው አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።”—ኢሳይያስ 55:7

      እስቲ አስበው፦ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤ እንደሚወገዱ አይካድም፤ ሆኖም ይሖዋ በትሕትና ንስሐ ለሚገቡና የተሰጣቸውን እርማት ለሚቀበሉ ሰዎች ምሕረት ያሳያል።—መዝሙር 103:13, 14፤ 2 ቆሮንቶስ 7:11

      በዚያ ላይ አንድ እውነታ አትዘንጋ፦ ፍጹም ባትሆንም እንኳ በአምላክ እርዳታ ፈተናን መቋቋም ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ደግሞስ ምን እንደምታደርግ የሚወስነው ማን ነው? አንተ ራስህ ነህ? ወይስ ሌላ ሰው?

      “ከተጠመቅኩ በኋላ ከባድ ስህተት ልሠራ እንደምችል በማሰብ እፈራ ነበር፤ በኋላ ግን ከመጠመቅ ወደኋላ ማለት ራሱ ስህተት እንደሆነ ተገነዘብኩ። ነገ ምን ይሆናል የሚለውን በማሰብ ዛሬ ማድረግ ያለብኝን ነገር ከማድረግ ወደኋላ ማለት እንደሌለብኝ አስተዋልኩ።”—ካረን

      ዋናው ነጥብ፦ አንተ እስከመረጥክ ድረስ ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም መቆጠብ ትችላለህ፤ አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲህ አድርገዋል።—ፊልጵስዩስ 2:12

      ተጨማሪ ሐሳብ ማግኘት ትፈልጋለህ? “ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

      ጥምቀት የሚያስከትለው ኃላፊነት ቢያስፈራኝስ?

      አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? ምናልባትም አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ ከቤተሰባቸውና ከጓደኞቻቸው ርቀው የሄዱ ወጣቶችን ታውቅ ይሆናል። በመሆኑም ሰዎች አንተም ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ እንደሚጠብቁብህ በማሰብ ትጨነቅ ይሆናል።

      “የተጠመቁ ክርስቲያኖች ተጨማሪ ኃላፊነት የመቀበል አጋጣሚ አላቸው፤ ግን አንዳንዶች ራሳቸውን በዚህ መልኩ ለማቅረብ ዝግጁ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ ሁኔታቸው ላይፈቅድላቸው ይችላል።”—መሪ

      ቁልፍ ጥቅስ፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላትያ 6:4

      እስቲ አስበው፦ ራስህን ከሌሎች ጋር ከማወዳደር ይልቅ ማርቆስ 12:30 እንደሚለው “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ” ለመውደድ ጥረት ብታደርግ የተሻለ አይሆንም?

      ይሖዋ ማገልገል ያለብህ በሙሉ ልብህ እንጂ በሌላ ሰው ልብ እንዳልሆነ አስታውስ። ይሖዋን ከልብህ የምትወደው ከሆነ ለእሱ ምርጥህን መስጠት የምትችልባቸው መንገዶች ማግኘትህ አይቀርም።

      “ጥምቀት በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው እርምጃ ቢሆንም ከባድ ሸክም አይደለም። ጥሩ ጓደኞች ካሉህ እነሱ ያግዙሃል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ቀስ በቀስ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን መሸከም ይበልጥ ደስተኛ ያደርግሃል። ከመጠመቅ ወደኋላ ብትል ብዙ ነገር ይቀርብሃል።”—ጁልያ

      ዋናው ነጥብ፦ ይሖዋ ላሳየህ ፍቅር አድናቆት አዳብር። ይህም በምላሹ ለእሱ ምርጥህን ለመስጠት ያነሳሳሃል።—1 ዮሐንስ 4:19

      ተጨማሪ ሐሳብ ማግኘት ትፈልጋለህ? “ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ነኝ?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

      ይሖዋን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆንኩ ቢሰማኝስ?

      አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ነው። ከእሱ አንጻር ሰው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም! በመሆኑም ይሖዋ ከነመፈጠርህ እንኳ የሚያውቅህ መሆኑን ትጠራጠር ይሆናል።

      “ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆኑ ከይሖዋ ጋር ያለኝ ወዳጅነት ከእነሱ ‘የወረስኩት’ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፤ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሳበኝ አይሰማኝም ነበር።”—ናታሊ

      ቁልፍ ጥቅስ፦ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም።”—ዮሐንስ 6:44

      እስቲ አስበው፦ ስለ ጥምቀት እያሰብክ መሆኑ በራሱ ይሖዋ ወደ እሱ ይበልጥ እንድትቀርብ እየሳበህ መሆኑን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ግብዣውን ልትቀበል አይገባም?

      ደግሞም ይሖዋ የሚስባቸውን ሰዎች በተመለከተ መሥፈርት የሚያወጣው እሱ ራሱ እንጂ አንተም ሆንክ ሌላ ሰው እንዳልሆነ አትዘንጋ። መጽሐፍ ቅዱስም ‘ወደ አምላክ ከቀረብክ እሱም ወደ አንተ እንደሚቀርብ’ ዋስትና ይሰጣል።—ያዕቆብ 4:8

      “ይሖዋን ማወቅህና ወደ እሱ መቅረብህ በራሱ እሱ እንደሚወድህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ስለዚህ አእምሮህ ይሖዋን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆንክ በሚነግርህ ጊዜ ይሖዋ እንደዚያ እንደማይሰማው አስታውስ። ይሖዋ ደግሞ አይሳሳትም።”—ሰሊና

      ዋናው ነጥብ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የጥምቀት ብቃት ካሟላህ ይሖዋን ለማምለክ ብቁ ነህ ማለት ነው። ደግሞም ይሖዋ አምልኮህ ይገባዋል።—ራእይ 4:11

      ተጨማሪ ሐሳብ ማግኘት ትፈልጋለህ? “መጸለይ ጥቅም አለው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

      እኩዮችህ ምን ይላሉ?

      ስካይ።

      “ጥፋት እንዳታጠፋ በመፍራት ከመጠመቅ ወደኋላ ማለት የለብህም። ጥምቀት እንደ ሩጫ ውድድር ነው። ‘እወድቃለሁ’ ብለህ በመፍራት ላለመሮጥ ትወስን ይሆናል። ግን ብትወድቅም መነሳት ትችላለህ። መጀመሪያውኑ መሮጥ ካልጀመርክ ግን ውድድሩን ማጠናቀቅ አትችልም።”—ስካይ

      ቪኒሲዮ።

      “አንድ ወጣት አደጋ እንዳይደርስበት በመስጋት መንጃ ፈቃድ ከማውጣት ወደኋላ እንደማይል የታወቀ ነው። ከጥምቀት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ‘ምን ሊፈጠር ይችላል’ የሚለውን በማሰብ ከመጨነቅ ይልቅ ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት በመመሥረት ላይ ማተኮር ይኖርብናል።”—ቪኒሲዮ

      ክለሳ፦ እንዳልጠመቅ ያገደኝ ምንድን ነው?

      • ‘ስህተት ብሠራስ’ የሚል ፍርሃት። አንተ እስከመረጥክ ድረስ ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም መቆጠብ ትችላለህ፤ አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲህ አድርገዋል።

      • ኃላፊነትን መፍራት። ይሖዋ ላሳየህ ፍቅር አድናቆት አዳብር። ይህም በምላሹ ለእሱ ምርጥህን ለመስጠት ያነሳሳሃል።

      • ‘ብቁ አይደለሁም’ የሚል ፍርሃት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የጥምቀት ብቃት ካሟላህ ይሖዋን ለማምለክ ብቁ ነህ ማለት ነው። ደግሞም ይሖዋ አምልኮህ ይገባዋል።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ