-
ሽማግሌዎች፣ ሌሎችን ስለማሠልጠን ምን አመለካከት አላችሁ?መጠበቂያ ግንብ—2015 | ሚያዝያ 15
-
-
ሽማግሌዎች፣ ሌሎችን ስለማሠልጠን ምን አመለካከት አላችሁ?
“ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።”—መክ. 3:1
1, 2. የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ ምን ነገር አስተውለዋል?
የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ከሽማግሌዎች አካል ጋር የሚያደርገውን ስብሰባ ሊያጠናቅቅ ተቃርቧል። እነዚህን ትጉ እረኞች ሲመለከታቸው በውስጡ ልዩ ስሜት ተሰማው፤ አንዳንዶቹ በዕድሜ ትልቅ በመሆናቸው አባቱ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። በሌላ በኩል ግን አንድ ያሳሰበው ነገር ስለነበር እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “ወንድሞች፣ ሌሎች በጉባኤ ውስጥ ለተጨማሪ ኃላፊነት እንዲበቁ በማሠልጠን ረገድ ምን አድርጋችኋል?” ሽማግሌዎቹ፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ባለፈው ጉብኝቱ ወቅት ሌሎችን ለማሠልጠኑ ሥራ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስቧቸው እንደነበር ትዝ አላቸው። አንደኛው ሽማግሌ “እውነቱን ለመናገር፣ ያን ያህል ጥረት አላደረግንም” በማለት መለሰ። ሌሎቹም ሽማግሌዎች በመልሱ መስማማታቸውን ለማሳየት ራሳቸውን ነቀነቁ።
2 አንተም ሽማግሌ ከሆንክ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ ወጣቶችንም ሆነ በዕድሜ ከፍ ያሉትን ወንድሞች አሠልጥኖ ለኃላፊነት በማብቃት ረገድ ብዙ የሚቀር ነገር እንዳለ አስተውለዋል። ይሁንና ይህን ኃላፊነት መወጣት የራሱ ተፈታታኝ ነገሮች አሉት። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
3. (ሀ) ሌሎችን ማሠልጠን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው እንዴት ነው? ለዚህ ጉዳይ ሁላችንም ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) አንዳንድ ሽማግሌዎች ሌሎችን ማሠልጠን ከባድ የሆነባቸው ለምንድን ነው?
3 እረኛ እንደመሆንህ መጠን ሌሎችን በግለሰብ ደረጃ ማሠልጠን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ሳትገነዘብ አትቀርም።a አሁን ያሉት ጉባኤዎች በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው እንዲቀጥሉ ብሎም አዳዲስ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ ከተፈለገ ተጨማሪ ወንድሞች እንደሚያስፈልጉ የታወቀ ነው። (ኢሳይያስ 60:22ን አንብብ።) በተጨማሪም የአምላክ ቃል ‘ሌሎችን እንድታስተምር’ ማሳሰቢያ እንደሰጠህ ታውቃለህ። (2 ጢሞቴዎስ 2:2ን አንብብ።) ያም ሆኖ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሱት ሽማግሌዎች አንተም ሌሎችን ማሠልጠን ከብዶህ ሊሆን ይችላል። የቤተሰብህን ፍላጎት ማሟላትን፣ ሰብዓዊ ሥራ መሥራትንና የጉባኤ ኃላፊነት መወጣትን ጨምሮ ሌሎች አጣዳፊ ሥራዎች እንዳሉብህ ስታስብ ሌሎችን ለማሠልጠን ጊዜ እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። ይህ ሁሉ ኃላፊነት እያለብህም ሌሎችን ለማሠልጠኑ ሥራ ትልቅ ቦታ መስጠት ያለብህ ለምንድን ነው? እስቲ ምክንያቶቹን እንመልከት።
ሌሎችን ማሠልጠን ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል
4. አንዳንድ ሽማግሌዎች የማሠልጠኑን ሥራ ለሌላ ጊዜ የሚያስተላልፉበት አንዱ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?
4 አንዳንድ ሽማግሌዎች ጊዜ መድበው ሌሎችን ማሠልጠን ከባድ እንዲሆንባቸው የሚያደርገው አንዱ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? አንዳንዶች እንዲህ ብለው ያስቡ ይሆናል፦ ‘ሌሎችን ማሠልጠን አስፈላጊ ቢሆንም ጊዜ ከማይሰጡ ሌሎች የጉባኤ ሥራዎች አንጻር ሲታይ ያን ያህል አጣዳፊ አይደለም። ሥልጠናውን በሌላ ጊዜ ባደርገው ጉባኤው ላይ የሚያመጣው ጉዳት የለም።’ ጊዜ የማይሰጡ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው እውነት ቢሆንም ሥልጠናውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ የጉባኤውን መንፈሳዊ ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል።
5, 6. በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሾፌር መኪናውን የያዘበትን መንገድ እንዴት ትገልጹታላችሁ? ይህ ምሳሌ በጉባኤ ውስጥ ለሌሎች ሥልጠና ከመስጠት ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
5 እስቲ ይህን ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ ሾፌር የመኪናው ሞተር ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን ከፈለገ በየጊዜው ዘይት መቀየር እንዳለበት ያውቃል። ያም ቢሆን ዘይት መቀየር ነዳጅ የመሙላትን ያህል አጣዳፊ እንዳልሆነ ይሰማዋል። ደግሞም ነዳጅ ካልሞላ መኪናው መቆሙ አይቀርም። ሾፌሩ ‘ዘይት መቀየሩን ለሌላ ጊዜ ባስተላልፈው ሞተሩ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን መሥራቱ አይቀርም’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። ይሁንና እንዲህ ማድረጉ ምን አደጋ አለው? ሾፌሩ ዘይት መቀየሩን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉን ከቀጠለ አንድ ቀን ሞተሩ ነክሶ መኪናው መቆሙ አይቀርም። በዚህ ጊዜ መኪናውን ለመጠገን ብዙ ጊዜ ማጥፋትና በርካታ ገንዘብ ማውጣት ግድ ይሆንበታል። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?
6 ሽማግሌዎች ሊያከናውኗቸው የሚገቡ በርካታ አጣዳፊ ጉዳዮች አሉ፤ እነዚህ ጉዳዮች በአስቸኳይ ካልተከናወኑ ጉባኤው በእጅጉ ሊጎዳ ይችላል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሾፌር ነዳጅ መሙላቱ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ሽማግሌዎችም ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተው ማወቅ’ አለባቸው። (ፊልጵ. 1:10) ይሁንና አንዳንድ ሽማግሌዎች ጊዜ በማይሰጡ ሌሎች ጉዳዮች ስለሚጠመዱ ሌሎችን ማሠልጠን በምሳሌያዊ አባባል ዘይት መቀየራቸውን ችላ ይላሉ። ሆኖም ሽማግሌዎች ሥልጠናውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፋቸውን ከቀጠሉ ይዋል ይደር እንጂ ጉባኤው አስፈላጊ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ብቃት ያላቸው ወንድሞችን በማጣት መቸገሩ አይቀርም።
7. ሌሎችን ለማሠልጠን ጊዜያቸውን መሥዋዕት የሚያደርጉ ሽማግሌዎችን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?
7 ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሥልጠና መስጠት ‘ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም’ የሚለውን አስተሳሰብ ማስወገድ ይኖርብናል። ልምድ የሌላቸውን ወንድሞች ለማሠልጠን ጊዜያቸውን መሥዋዕት የሚያደርጉና አርቆ አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች ጥበበኛ መጋቢዎች ከመሆናቸውም በላይ ለጉባኤው በረከት ናቸው። (1 ጴጥሮስ 4:10ን አንብብ።) ለመሆኑ ጉባኤው ጥቅም ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?
ጊዜን በአግባቡ መጠቀም
8. (ሀ) ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? (ለ) እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደው የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ምን አጣዳፊ ሥራ ማከናወን ይኖርባቸዋል? (“አጣዳፊ ሥራ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
8 ተሞክሮ ያካበቱ ሽማግሌዎችም እንኳ በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ በጉባኤ ውስጥ የሚያከናውኑት ሥራ ውስን እየሆነ እንደሚመጣ አምነው በመቀበል ልካቸውን እንደሚያውቁ ማሳየት አለባቸው። (ሚክ. 6:8) በተጨማሪም “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” በሕይወታቸው ውስጥ ድንገተኛ ለውጥ ሊያመጡና የጉባኤ ኃላፊነታቸውን መወጣት ሊያቅታቸው እንደሚችል መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (መክ. 9:11, 12፤ ያዕ. 4:13, 14) ስለሆነም የይሖዋ በጎች ደህንነት የሚያሳስባቸው አርቀው የሚመለከቱ ሽማግሌዎች ያካበቱትን ተሞክሮ ከእነሱ በዕድሜ ለሚያንሱ ወንድሞች በማካፈል ጊዜያቸውን በአግባቡ ይጠቀማሉ።—መዝሙር 71:17, 18ን አንብብ።
9. ሥልጠና መስጠት በጣም አስፈላጊ የሆነው ከፊታችን ምን ስለሚጠብቀን ነው?
9 ሽማግሌዎች ሌሎችን ማሠልጠናቸው ሌላስ ምን ጥቅም ያስገኛል? የጉባኤው መንፈሳዊነት ይጠናከራል። እንዴት? ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን ጥረት ማድረጋቸው ጉባኤውን የሚረዱ ብዙ ወንድሞች እንዲገኙ ያደርጋል፤ እነዚህ ወንድሞች ደግሞ ጉባኤው በአሁኑ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተለይ በታላቁ መከራ ወቅት ጸንቶ እንዲቆምና አንድነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። (ሕዝ. 38:10-12፤ ሚክ. 5:5, 6) በመሆኑም ውድ ሽማግሌዎች፣ የሥራችሁ አንዱ ክፍል እንደሆነ አድርጋችሁ በመቁጠር ከዛሬ ጀምሮ ሌሎችን እንድታሠለጥኑ እንለምናችኋለን።
10. አንድ ሽማግሌ ሌሎችን ለማሠልጠን የሚያስችል ጊዜ ማግኘት ከፈለገ ምን ማድረግ ይኖርበታል?
10 በጉባኤ ውስጥ ያሉ አስፈላጊ የሆኑ ኃላፊነቶችን መወጣት በራሱ ጊዜያችሁን ሊወስድባችሁ እንደሚችል እንረዳለን። ያም ቢሆን ከዚህ ጊዜ ላይ የተወሰነውን በመውሰድ ሌሎችን ለማሠልጠን መጠቀም ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። (መክ. 3:1) እንዲህ ማድረጋችሁ ጊዜያችሁን በአግባቡ እንደምትጠቀሙ የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ጉባኤውን ይጠቅማል።
ለሥልጠና አመቺ ሁኔታ መፍጠር
11. (ሀ) በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሽማግሌዎች ሌሎችን ስለማሠልጠን የሰጡት ሐሳብ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በምሳሌ 15:22 መሠረት ሌሎች ሽማግሌዎች የሰጧቸውን ሐሳቦች መመርመር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
11 ወንድሞችን በመንፈሳዊ እንዲያድጉ በመርዳት ረገድ የተዋጣላቸው አንዳንድ ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን ምን ዓይነት ዘዴዎችን እንደተጠቀሙ በቅርቡ ተጠይቀው ነበር።b እነዚህ ሽማግሌዎች ያሉበት ሁኔታ በእጅጉ የተለያየ ቢሆንም የሰጡት ምክር በሚያስገርም ሁኔታ ይመሳሰላል። ይህ ምን ይጠቁማል? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ለተማሪዎች የሚሰጠው ይህ ሥልጠና በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ብቻ ሳይሆን ዛሬም በሁሉም ‘ስፍራ በሚገኙ ጉባኤዎች’ ውስጥ ይሠራል። (1 ቆሮ. 4:17) በመሆኑም እነዚህ ሽማግሌዎች የሰጧቸውን አንዳንድ ሐሳቦች በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን። (ምሳሌ 15:22) ለአጻጻፍ እንዲመች ስንል በእነዚህ ርዕሶች ውስጥ ሥልጠና የሚሰጡትን ሽማግሌዎች “አስተማሪዎች” ሥልጠና የሚቀበሉትን ደግሞ “ተማሪዎች” እንላቸዋለን።
12. አስተማሪዎች ሥልጠና ከመጀመራቸው በፊት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ለምንስ?
12 አስተማሪዎች ለሥልጠና አመቺ ሁኔታ መፍጠር ይኖርባቸዋል። አንድ ገበሬ ዘር ከመዝራቱ በፊት መሬቱን ማለስለስ እንዳለበት ሁሉ አንድ አስተማሪም ተማሪውን ማሠልጠን ከመጀመሩ በፊት የተማሪውን ልብ ማዘጋጀት ይኖርበታል። ታዲያ አስተማሪዎች ሌሎችን ለማሠልጠን አመቺ ሁኔታ መፍጠር የሚችሉት እንዴት ነው? በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ነቢይ የተጠቀመውን ዘዴ በመከተል ነው። ይህ ዘዴ ምንድን ነው?
13-15. (ሀ) ነቢዩ ሳሙኤል ምን ኃላፊነት ተሰጠው? (ለ) ሳሙኤል ኃላፊነቱን የተወጣው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ሐ) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ሽማግሌዎች ስለ ሳሙኤል ለሚናገረው ለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ልዩ ትኩረት መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው?
13 ይሖዋ ከዛሬ 3,000 ዓመታት በፊት፣ በዕድሜ ለገፋው ለነቢዩ ሳሙኤል እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ነገ በዚህ ጊዜ ገደማ ከቢንያም ምድር የመጣ አንድ ሰው ወደ አንተ እልካለሁ። አንተም በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ አድርገህ ቀባው።” (1 ሳሙ. 9:15, 16) ሳሙኤል እሱን የሚተካ ሰው እንዲቀባ ይሖዋ ተልእኮ ሲሰጠው እስራኤልን የመምራት ኃላፊነቱ እንዳበቃ ተገነዘበ። ሳሙኤል ‘ይህን ሰው ለዚህ ኃላፊነት ማዘጋጀት የምችለው እንዴት ነው?’ ብሎ አስቦ መሆን አለበት። ሳሙኤል አንድ ሐሳብ መጣለት፤ ከዚያም ሐሳቡን ተግባራዊ ማድረግ የሚችልበትን እቅድ አወጣ።
14 በማግስቱ ሳሙኤል ከሳኦል ጋር ተገናኘ፤ በዚህ ጊዜ ይሖዋ ለሳሙኤል “የነገርኩህ ሰው ይህ ነው” አለው። ከዚያም ሳሙኤል አስቀድሞ ባወጣው እቅድ መሠረት፣ አብሮት ምግብ እንዲበላ ሳኦልን ወደ መመገቢያ አዳራሹ ወሰደው። እዚያ ሲደርሱ ሳኦልና አገልጋዩ በክብር ቦታ እንዲቀመጡ አደረገ፤ ከዚያም ሳሙኤል ምርጥ የሆነውን ሥጋ ሳኦል ፊት በማቅረብ “ይህ ለዚህ ጊዜ ብለው ለይተው ያስቀመጡልህ ስለሆነ ብላ” አለው። ከምግብ በኋላ ሳሙኤል ሳኦልን ወደ ቤቱ ወሰደው፤ ወደ ነቢዩ ቤት የሄዱት እየተጨዋወቱ ነበር። ሳሙኤል ጥሩ ምግብ መመገባቸውና እንዲህ ያለ ዘና ያለ ጉዞ የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞበታል። ወደ ቤት ሲደርሱም ሳኦልን ወደ ሰገነቱ ይዞት ወጣ። የምሽቱን ነፋሻማ አየር እያጣጣሙ እንቅልፋቸው እስኪመጣ ድረስ ‘በቤቱ ሰገነት ላይ ሆነው ሲነጋገሩ ቆዩ።’ በማግስቱ ሳሙኤል ሳኦልን ቀባው፤ ከዚያም ከሳመው በኋላ ተጨማሪ መመሪያዎችን ሰጠው። ሳሙኤል በዚህ መንገድ ሳኦልን ከፊቱ ለሚጠብቀው ነገር ካዘጋጀው በኋላ አሰናበተው።—1 ሳሙ. 9:17-27፤ 10:1
15 እርግጥ ነው፣ አንድን ሰው የአንድ ብሔር መሪ እንዲሆን መሾምና አንድን ወንድም ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ እንዲሆን ማሠልጠን የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ያም ቢሆን ሽማግሌዎች ሳሙኤል ከተጠቀመበት ዘዴ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት ይችላሉ። እስቲ ከእነዚህ መካከል ሁለቱን እንመልከት።
በደስታ አስተምሩ፤ እውነተኛ ጓደኛ ሁኑ
16. (ሀ) ሳሙኤል እስራኤላውያን ንጉሥ እንዲሾምላቸው ሲጠይቁት ምን ተሰማው? (ለ) ሳሙኤል ሳኦልን እንዲሾም የተሰጠውን ኃላፊነት የተወጣው በምን ዓይነት መንፈስ ነው?
16 ግዴታ እንደሆነ ተሰምቷችሁ ሳይሆን በደስታ አስተምሩ። ሳሙኤል እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ እንደሚፈልጉ ሲነግሩት መጀመሪያ ላይ ተከፍቶና እሱን እንዳልተቀበሉት ተሰምቶት ነበር። (1 ሳሙ. 8:4-8) እንዲያውም የሕዝቡን ጥያቄ ለመፈጸም አመንትቶ ስለነበር ይሖዋ ሕዝቡን እንዲሰማ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ነግሮታል። (1 ሳሙ. 8:7, 9, 22) ያም ቢሆን ሳሙኤል እሱን በሚተካው ሰው ላይ ጥላቻ ወይም ቅሬታ እንዲያድርበት አልፈቀደም። ይሖዋ ሳኦልን እንዲቀባ ሲነግረው ታዟል፤ ይህን ያደረገው ግዴታ ስለሆነበት ሳይሆን በፍቅር ተነሳስቶና ደስ እያለው ነበር።
17. በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች የሳሙኤል ዓይነት ባሕርይ ማንጸባረቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህስ ምን እርካታ ያስገኝላቸዋል?
17 በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም ለሚያሠለጥኗቸው ወንድሞች ልክ እንደ ሳሙኤል ጥሩ መንፈስ ማሳየት አለባቸው። (1 ጴጥ. 5:2) እንዲህ ያሉ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያሏቸውን አንዳንድ መብቶች ተማሪዎቹ ሊወስዱባቸው እንደሚችሉ በመፍራት እነሱን ከማሠልጠን ወደኋላ አይሉም። ደጎችና ሌሎችን በደስታ የሚረዱ አስተማሪዎች፣ ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ተማሪዎችን የሚመለከቷቸው እንደ ተቀናቃኝ ሳይሆን ‘ከእነሱ ጋር አብረው እንደሚሠሩና’ ለጉባኤው ውድ ስጦታ እንደሆኑ አድርገው ነው። (2 ቆሮ. 1:24፤ ዕብ. 13:16) ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ሌሎችን የሚያሠለጥኑ እንዲህ ያሉ አስተማሪዎች፣ ተማሪዎቹ ችሎታቸውን ተጠቅመው ጉባኤውን ሲያገለግሉ ማየታቸው ልዩ የእርካታ ስሜት እንደሚፈጥርላቸው ግልጽ ነው!—ሥራ 20:35
18, 19. አንድ ሽማግሌ የተማሪውን ልብ ለሥልጠና ማዘጋጀት የሚችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለው አቀራረብ ውጤታማ የሆነውስ ለምንድን ነው?
18 አስተማሪ ብቻ ሳይሆን ጓደኛም ሁኑ። ሳሙኤል ሳኦልን ሲያገኘው ወዲያውኑ የዘይቱን ዕቃ አውጥቶ በሳኦል ራስ ላይ በማፍሰስ ሊሸኘው ይችል ነበር። እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ ሳኦል ንጉሥ መሆኑ አይቀርም ነበር፤ ኃላፊነቱን ለመወጣት ግን ሙሉ በሙሉ ዝግጁ አይሆንም ነበር። ሳሙኤል እንዲህ ከማድረግ ይልቅ የሳኦልን ልብ ለማዘጋጀት ጊዜ ወስዶ አንዳንድ ነገሮችን አድርጓል። ሳኦልን የቀባው ጥሩ ምግብ ከተመገቡ፣ ደስ የሚል የእግር ጉዞ ካደረጉ፣ ለረጅም ጊዜ ሲያወሩ ከቆዩና ጥሩ እረፍት ካደረጉ በኋላ ነው።
አንድ አስተማሪ ሥልጠና መስጠት ከመጀመሩ በፊት ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት ያስፈልገዋል (አንቀጽ 18, 19ን ተመልከት)
19 በዛሬው ጊዜም አንድ አስተማሪ ሥልጠና ከመጀመሩ በፊት ዘና ያለ ሁኔታ እንዲኖርና ከተማሪው ጋር ጥሩ ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ሽማግሌዎች እንዲህ ያለ ጥሩ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚወስዷቸው እርምጃዎች እንደ አካባቢው ሁኔታና ባሕል ሊለያዩ ይችላሉ። ይሁንና የምትኖረው የትም ይሁን የት እንዲሁም ምንም ያህል ሥራ የሚበዛብህ ሽማግሌ ብትሆን ከተማሪው ጋር ጊዜ ማሳለፍህ ‘በእኔ ዘንድ ትልቅ ቦታ አለህ’ የሚል መልእክት ያስተላልፋል። (ሮም 12:10ን አንብብ።) በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ለመማር ፈቃደኛ የሆነ ተማሪ ይህን መልእክት በሚገባ እንደሚያስተውልና በጥልቅ እንደሚነካው ጥርጥር የለውም።
20, 21. (ሀ) አንድ አስተማሪ ውጤታማ ነው የሚባለው ምን ካለው ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኛውን ጉዳይ እንመረምራለን?
20 አንድ አስተማሪ ውጤታማ የሚባለው ሌሎችን የማሠልጠን ፍቅር ስላለው ብቻ ሳይሆን ለሚያሠለጥነው ሰው ጭምር ፍቅር ሲኖረው እንደሆነ ሽማግሌዎች ማስታወስ አለባቸው። (ከዮሐንስ 5:20 ጋር አወዳድር።) አንድ አስተማሪ ለተማሪው ፍቅር ካለው ተማሪው ይህን በቀላሉ ሊያስተውል ይችላል፤ እንዲሁም ለሥልጠናው ጥሩ ምላሽ እንዲሰጥ ያነሳሳዋል። በመሆኑም ውድ ሽማግሌዎች፣ ሌሎችን ስታሠለጥኑ አስተማሪ ብቻ ሳይሆን ጓደኛም ሁኗቸው።—ምሳሌ 17:17፤ ዮሐ. 15:15
21 አንድ ሽማግሌ የተማሪውን ልብ ካዘጋጀ በኋላ ሥልጠናውን መስጠት መጀመር ይችላል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ዓይነት ዘዴዎችን መጠቀም ይችላል? ይህን ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።
a በዚህና በሚቀጥለው ሳምንት የሚጠኑት ርዕሶች በዋነኝነት የተዘጋጁት ለሽማግሌዎች ቢሆንም ሌሎቹ የጉባኤው አባላትም ለትምህርቱ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። ለምን? እነዚህ የጥናት ርዕሶች የተጠመቁ ወንዶች በሙሉ በጉባኤ ውስጥ ለበለጠ ኃላፊነት እንዲበቁ ሥልጠና ማግኘታቸው አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ይረዷቸዋል። እንዲህ ከሆነ ሁሉም ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።
b እነዚህ ሽማግሌዎች የተውጣጡት ከሜክሲኮ፣ ከሩሲያ፣ ከሪዩኒየን፣ ከባንግላዲሽ፣ ከቤልጅየም፣ ከብራዚል፣ ከናሚቢያ፣ ከናይጄሪያ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከኮሪያ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከጃፓን፣ ከፈረንሳይ እና ከፍሬንች ጊያና ነው።
-
-
ሽማግሌዎች ሌሎች ብቃቱን እንዲያሟሉ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው?መጠበቂያ ግንብ—2015 | ሚያዝያ 15
-
-
ሽማግሌዎች ሌሎች ብቃቱን እንዲያሟሉ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው?
“ከእኔ የሰማኸውን . . . ነገር፣ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ።”—2 ጢሞ. 2:2
1. (ሀ) የአምላክ አገልጋዮች ሥልጠና ስለ መስጠት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ምን ተገንዝበው ነበር? በዛሬው ጊዜስ? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
የአምላክ አገልጋዮች ሌሎችን ማሠልጠን ለስኬት እንደሚያበቃ ከጥንት ጀምሮ ተገንዝበዋል። ለምሳሌ አብራም ሎጥን ለማዳን ‘የሠለጠኑ አገልጋዮቹን ሰብስቦ’ ይዞ ሄዶ ነበር፤ ይህም ለስኬት አብቅቶታል። (ዘፍ. 14:14-16) በንጉሥ ዳዊት ዘመን በአምላክ ቤት የነበሩት መዘምራን “ለይሖዋ በሚቀርበው መዝሙር የሠለጠኑ” ነበሩ፤ ይህም ለአምላክ ውዳሴ አምጥቷል። (1 ዜና 25:7) ዛሬ ደግሞ ከሰይጣንና ከተከታዮቹ ጋር መንፈሳዊ ውጊያ እያካሄድን ነው። (ኤፌ. 6:11-13) በተጨማሪም ለይሖዋ ውዳሴ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው። (ዕብ. 13:15, 16) በመሆኑም እንደ ጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች ስኬታማ መሆን ከፈለግን ሥልጠና ማግኘት ይኖርብናል። ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ ሌሎችን የማሠልጠን ኃላፊነት ለሽማግሌዎች በአደራ ሰጥቷል። (2 ጢሞ. 2:2) ታዲያ ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች፣ ሌሎች ወንድሞች መንጋውን የመንከባከብ ብቃት እንዲኖራቸው ለማሠልጠን የትኞቹን ዘዴዎች እየተጠቀሙ ነው?
ተማሪውን በመንፈሳዊ አጠናክሩት
2. አንድ ሽማግሌ ለተማሪው ሥልጠና ከመስጠቱ በፊት ምን ማድረግ ያስፈልገዋል? ለምንስ?
2 ሽማግሌዎች ከገበሬ ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። አንድ ገበሬ አፈሩ ይበልጥ ምርት እንዲሰጥ ከፈለገ ዘሩን ከመዝራቱ በፊት አፈሩ ውስጥ አልሚ ንጥረ ነገሮችን መጨመር ያስፈልገው ይሆናል። በተመሳሳይም ብዙ ተሞክሮ ለሌለው አንድ ተማሪ ሥልጠና ለመስጠት ከመነሳትህ በፊት የተማሪው ልብ ለሥልጠናው ዝግጁ እንዲሆን የሚረዱ ገንቢ የሆኑ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን ማካፈል አስፈላጊ እንደሆነ ትገነዘብ ይሆናል።—1 ጢሞ. 4:6
3. (ሀ) ከተማሪው ጋር ውይይት ስታደርጉ በማርቆስ 12:29, 30 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ሊረዳችሁ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሽማግሌ የሚያቀርበው ጸሎት በተማሪው ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?
3 የመንግሥቱ እውነት በተማሪው አስተሳሰብና ድርጊት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደረ ለማወቅ እንዲህ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ፦ ‘ራስህን ለይሖዋ መወሰንህ ሕይወትህን በምትመራበት መንገድ ላይ ምን ለውጥ አስከትሏል?’ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳት ቅዱስ አገልግሎታችንን በሙሉ ነፍስ ማቅረብ ስለሚቻልበት መንገድ ትርጉም ያለው ውይይት ለመጀመር በር ይከፍታል። (ማርቆስ 12:29, 30ን አንብብ።) ከውይይታችሁ በኋላ ይሖዋ ለተማሪው መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠው ልትጸልይ ትችላለህ፤ ይህም ሥልጠናው ግቡን እንዲመታ ይረዳል። ተማሪው ስለ እሱ ከልብ የመነጨ ጸሎት ስታቀርብ መስማቱ እንደሚያበረታታው ጥርጥር የለውም!
4. (ሀ) ተማሪው መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ የሚያነሳሱት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ናቸው? (ለ) ሽማግሌዎች ሌሎችን ሲያሠለጥኑ ግባቸው ምን መሆን አለበት?
4 ተማሪው ለማገልገል ፈቃደኛ፣ እምነት የሚጣልበትና ትሑት መሆኑ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስገነዝቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በሥልጠናው የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ መጥቀስ ትችላለህ። (1 ነገ. 19:19-21፤ ነህ. 7:2፤ 13:13፤ ሥራ 18:24-26) አልሚ ንጥረ ነገሮች ለአፈር ወሳኝ እንደሆኑ ሁሉ እንዲህ ያሉ ባሕርያትም ተማሪውን ይጠቅሙታል። መንፈሳዊ እድገቱን ያፋጥኑታል። በፈረንሳይ የሚገኝ ዣን ክሎድ የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎችን በማሠለጥንበት ወቅት ዋነኛው ግቤ ተማሪው መንፈሳዊ ሰው እንዲሆን መርዳት ነው። ተማሪው ‘ዓይኖቹ’ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ‘አስደናቂ ነገሮች’ ማየት እንዲችሉ አንዳንድ ጥቅሶችን ለማንበብ አጋጣሚዎችን እፈልጋለሁ።” (መዝ. 119:18) ተማሪውን በመንፈሳዊ ለማጠናከር ሌላስ ምን ማድረግ ይቻላል?
ግብ እንዲያወጡ እርዷቸው፤ ምክንያቱን አስረዷቸው
5. (ሀ) ከተማሪው ጋር ስለ መንፈሳዊ ግብ መነጋገር ምን ያህል አስፈላጊ ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ወንዶችን ከልጅነታቸው ጀምሮ ማሠልጠን ያለባቸው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
5 ተማሪውን ‘ምን መንፈሳዊ ግቦች አሉህ?’ ብለህ ጠይቀው። በግልጽ የተቀመጡ ግቦች ከሌሉት ምክንያታዊና ሊደርስበት የሚችል ግብ እንዲያወጣ እርዳው። አንተ ራስህ በአንድ ወቅት የነበረህን አንድ መንፈሳዊ ግብ ንገረው፤ እዚህ ግብህ ላይ ስትደርስ የተሰማህን ደስታ ሞቅ ባለ ስሜት ግለጽለት። ይህ ቀላል ዘዴ ቢሆንም የሚያስገኘው ውጤት ግን የዋዛ አይደለም። ቪክቶር የተባለ በአፍሪካ የሚኖር አቅኚና ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ልጅ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ሽማግሌ ስለ ግቦቼ አንዳንድ ጥያቄዎች ጠየቀኝ። ይህም ስለ አገልግሎቴ በቁም ነገር እንዳስብ አደረገኝ።” ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ለወንድሞች ከልጅነታቸው ማለትም ከአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አንስቶ በጉባኤ ውስጥ ለዕድሜያቸው የሚመጥን ኃላፊነት በመስጠት ማሠልጠን ጥቅም እንዳለው ይናገራሉ። ልጆች ገና በለጋነታቸው እንዲህ ዓይነት ሥልጠና ማግኘታቸው ትኩረታቸውን የሚሰርቁ ነገሮች በሚዥጎደጎዱባቸው ማለትም በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይም ትኩረታቸውን በመንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።—መዝሙር 71:5, 17ን አንብብ።a
ሥራው ለምን መሠራት እንዳለበት ተናገር፤ እንዲሁም ተማሪው ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት ሲያደርግ አመስግነው (ከአንቀጽ 5-8 ተመልከት)
6. ኢየሱስ የሰጠው ሥልጠና ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት ዘዴዎች አንዱ ምንድን ነው?
6 የተማሪውን የማገልገል ፍላጎት ማነሳሳት የምትችልበት ሌላው ዘዴ ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለበት ብቻ ሳይሆን ለምን እንደሚያደርግ መንገር ነው። አንድን ነገር የሚያደርግበትን ምክንያት የምትነግረው ከሆነ ታላቅ አስተማሪ የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ ትከተላለህ። ለምሳሌ ኢየሱስ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ለሐዋርያቱ ተልእኮ ከመስጠቱ በፊት ይህን ትእዛዝ መፈጸም ያለባቸው ለምን እንደሆነ ነግሯቸዋል። “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 28:18, 19) አንተስ ኢየሱስ ሌሎችን ለማሠልጠን የተጠቀመበትን ይህን ዘዴ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?
7, 8. (ሀ) ሽማግሌዎች የኢየሱስን የሥልጠና ዘዴ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ተማሪውን ማመስገን ምን ያህል አስፈላጊ ነው? (ሐ) ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን የትኞቹ ሐሳቦች ሊረዷቸው ይችላሉ? (“ሌሎችን ማሠልጠን የሚቻልበት መንገድ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
7 ተማሪውን አንድ ነገር እንዲያደርግ ስትጠይቀው ይህን የሚያደርግበትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አብረህ ግለጽለት። በዚህ መንገድ ነገሮችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር እንዲያስብ ታሠለጥነዋለህ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም የመንግሥት አዳራሹን መግቢያ ለእይታ ማራኪ እንዲያደርግና እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ከአካባቢው እንዲያስወግድ ጠየቅከው እንበል። በዚህ ጊዜ ቲቶ 2:10ን በመጥቀስ በመንግሥት አዳራሹ የተሰጠውን ይህን ኃላፊነት መወጣቱ “አዳኛችን የሆነው አምላክ ትምህርት በሁሉም መንገድ ውበት እንዲጎናጸፍ” የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ግለጽለት። በተጨማሪም ተማሪው የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን አረጋውያን የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ ንገረው። ከተማሪው ጋር እንዲህ ያለ ውይይት ማድረግህ ሕግ በመፈጸም ላይ ሳይሆን ለሰዎች በማሰብ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ያሠለጥነዋል። እሱ የሚያከናውነው አገልግሎት በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን ምን ያህል እየጠቀማቸው እንደሆነ ሲመለከት ይደሰታል።
8 በተጨማሪም ተማሪው የሰጠኸውን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥር ማመስገን እንዳለብህ አትርሳ። ይህን ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? አንድ አትክልት ውኃ ማግኘቱ እንዲለመልም እንደሚያደርገው ሁሉ ተማሪውም ልባዊ ምስጋና ማግኘቱ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ይረዳዋል።—ከማቴዎስ 3:17 ጋር አወዳድር።
ሌላው ፈታኝ ነገር
9. (ሀ) በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ አንዳንድ ሽማግሌዎች ሌሎችን ከማሠልጠን ጋር በተያያዘ ምን ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? (ለ) አንዳንድ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ ለእውነት ቅድሚያ መስጠት የሚለው ጉዳይ የማይታያቸው ለምንድን ነው?
9 በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሽማግሌዎች በ20ዎቹና በ30ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ የተጠመቁ ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት እንዲቀበሉ ለማነሳሳት ጥረት ሲያደርጉ የሚያጋጥማቸው ሌላም ፈታኝ ነገር አለ። በምዕራባውያን አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወጣት ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ከመቀበል ወደኋላ የሚሉት ለምን እንደሆነ እንዲህ ባሉ 20 አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ተሞክሮ ያካበቱ ሽማግሌዎችን ጠይቀን ነበር። በብዛት የሰጡት መልስ ‘አንዳንድ ወጣቶች በልጅነታቸው መንፈሳዊ ግብ እንዲያወጡ ማበረታቻ ስላልተሰጣቸው ነው’ የሚል ነው። እንዲያውም እንዲህ ያለ ግብ የነበራቸው አንዳንድ ወጣቶች ዓለማዊ ግብ እንዲያወጡ በወላጆቻቸው ተጽዕኖ ተደርጎባቸዋል! እንዲህ ያሉ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ ለእውነት ቅድሚያ መስጠት የሚለው ጉዳይ ፈጽሞ አይታያቸውም።—ማቴ. 10:24
10, 11. (ሀ) አንድ ሽማግሌ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ወስዶ የማገልገል ፍላጎት የሌለውን ወንድም ቀስ በቀስ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል መርዳት የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሽማግሌ ከተማሪው ጋር በየትኞቹ ጥቅሶች ላይ ሊወያይ ይችላል? እንዲህ ማድረጉ ምን ጥቅም አለው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
10 አንድ ወንድም በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ወስዶ የማገልገል ፍላጎት ከሌለው፣ አስተሳሰቡን ለማስተካከል ብዙ ጥረትና ትዕግሥት ይጠይቃል፤ ያም ቢሆን የማይቻል ነገር አይደለም። አንድ ገበሬ ተጣምሞ ያደገን አንድ ተክል ቀስ በቀስ ግንዱ ቀጥ ያለ እንዲሆን ማድረግ እንደሚችል ሁሉ አንተም አንዳንድ ወንድሞች ኃላፊነት ስለመቀበል ያላቸውን አመለካከት ቀስ በቀስ እንዲያስተካክሉ መርዳት ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
11 ከተማሪው ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጊዜ መድብ። በጉባኤ ውስጥ ተፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘብ አድርግ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ በአንዳንድ ጥቅሶች ላይ በመወያየት ለይሖዋ የገባውን ቃል እንዲያስታውስ እርዳው። (መክ. 5:4፤ ኢሳ. 6:8፤ ማቴ. 6:24, 33፤ ሉቃስ 9:57-62፤ 1 ቆሮ. 15:58፤ 2 ቆሮ. 5:15፤ 13:5) ‘ራስህን ለይሖዋ ስትወስን ምን ቃል ገብተህ ነበር?’ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ‘በተጠመቅክ ጊዜ ይሖዋ ምን ተሰምቶት የነበረ ይመስልሃል?’ ብለህ በመጠየቅ የቀድሞ ፍቅሩ እንዲቀሰቀስ አድርግ። (ምሳሌ 27:11) ከዚያም ‘ሰይጣንስ ምን ተሰምቶት ነበር?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ትችላለህ። (1 ጴጥ. 5:8) በደንብ የታሰበበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበብህ በተማሪው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በፍጹም አቅልለህ አትመልከት።—ዕብራውያን 4:12ን አንብብ።b
ተማሪዎች፣ ታማኝ መሆናችሁን አስመሥክሩ
12, 13. (ሀ) ኤልሳዕ ተማሪ በነበረበት ወቅት ምን ዓይነት ባሕርይ አሳይቷል? (ለ) ኤልሳዕ ታማኝ በመሆኑ ይሖዋ የባረከው እንዴት ነው?
12 እናንተ ወጣት ወንድሞች፣ ጉባኤው የእናንተን እርዳታ ይፈልጋል። ጉባኤውን በመርዳት ረገድ ስኬታማ ለመሆን ምን ዓይነት ባሕርይ ማዳበር ያስፈልጋችኋል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በጥንት ዘመን የኖረን የአንድ ተማሪ ሁኔታ እንመልከት።
13 ወደ 3,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ነቢዩ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ የተባለን አንድ ወጣት አገልጋዩ እንዲሆን ጠይቆት ነበር። ኤልሳዕም ግብዣውን ወዲያውኑ በመቀበል ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን በማከናወን በዕድሜ የገፋውን ነቢይ በታማኝነት ማገልገል ጀመረ። (2 ነገ. 3:11) ኤልሳዕ ለስድስት ዓመት ያህል ከሠለጠነ በኋላ ኤልያስ በእስራኤል ውስጥ የሚያከናውነው አገልግሎት ሊያበቃ እንደሆነ ተገነዘበ። በዚህ ወቅት ኤልያስ በደንብ የሠለጠነው አገልጋዩ እሱን መከተሉን እንዲያቆም ጠየቀው፤ ኤልሳዕ ግን ከአንዴም ሦስቴ “ከአንተ አልለይም” አለው። ኤልሳዕ ከአስተማሪው ጋር የሚችለውን ያህል ረጅም ጊዜ ለማሳለፍ ቆርጦ ነበር። ኤልሳዕ ታማኝና የእምነት ሰው በመሆኑ ኤልያስ ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ ሲወሰድ እንዲመለከት በማድረግ ይሖዋ ባርኮታል።—2 ነገ. 2:1-12
14. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ተማሪዎች የኤልሳዕን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ተማሪ ታማኝ መሆኑ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
14 ተማሪ ከሆንክ የኤልሳዕን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? ዝቅ ተደርገው የሚቆጠሩ ሥራዎችን ጨምሮ ማንኛውም ኃላፊነት ሲሰጥህ ሥራውን ለማከናወን ፈጣን እርምጃ ውሰድ። አስተማሪህን እንደ ጓደኛ ተመልከተው፤ እንዲሁም አንተን ለመርዳት የሚያደርገውን ጥረት እንደምታደንቅ ንገረው። ለሥልጠናው ጥሩ ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ ለአስተማሪህ “ከአንተ አልለይም” እያልከው ያለ ያህል ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የተሰጠህን ማንኛውንም ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ታማኝ መሆንህን አሳይ። ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት እንድትቀበል የሚፈልግ መሆኑን ሽማግሌዎቹ እርግጠኞች የሚሆኑት ታማኝና እምነት የሚጣልበት ሰው መሆንህን ስታስመሠክር ነው።—መዝ. 101:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:2ን አንብብ።
ተገቢውን አክብሮት አሳዩ
15, 16. (ሀ) ኤልሳዕ ለአስተማሪው አክብሮት እንዳለው ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ኤልሳዕ ሌሎቹ ነቢያት በእሱ እንዲተማመኑ ምን አድርጓል?
15 የኤልያስ ተተኪ ስለሆነው ስለ ኤልሳዕ የሚናገረው ዘገባ ወንድሞች ተሞክሮ ላካበቱ ሽማግሌዎች ተገቢውን አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነም ይጠቁማል። ኤልያስና ኤልሳዕ በኢያሪኮ የሚገኙ ነቢያትን ከጎበኙ በኋላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዱ። በዚያም “ኤልያስ የነቢይ ልብሱን አውልቆ በመጠቅለል ውኃውን መታው፤ ውኃውም ግራና ቀኝ ተከፈለ።” የደረቀውን ወንዝ ከተሻገሩ በኋላ ‘እየተጨዋወቱ መሄዳቸውን’ ቀጠሉ። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኤልሳዕ ሁሉንም ነገር ተምሮ እንደጨረሰ አልተሰማውም። ኤልያስ ከእሱ እስከተለየበት ጊዜ ድረስ አስተማሪው የሚናገረውን ሁሉ በጥሞና ይከታተል ነበር። ከዚያም ኤልያስ አውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ወደ ሰማይ ወጣ። በኋላም ኤልሳዕ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ተመልሶ ውኃውን በኤልያስ ልብስ በመምታት “የኤልያስ አምላክ ይሖዋ የት አለ?” አለ። ውኃውም በድጋሚ ለሁለት ተከፈለ።—2 ነገ. 2:8-14
16 ኤልሳዕ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጸመው ተአምር ኤልያስ ለመጨረሻ ጊዜ ከፈጸመው ተአምር ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን ልብ አልክ? ይህ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? ኤልሳዕ አሁን በኃላፊነት ላይ ያለው እሱ ስለሆነ ኤልያስ ይጠቀምበት የነበረውን መንገድ ወዲያውኑ መቀየር እንዳለበት አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ አገልግሎቱን ኤልያስ ያከናውን በነበረበት መንገድ ማከናወኑን ቀጥሏል፤ ይህም ለአስተማሪው አክብሮት እንዳለው የሚያሳይ ሲሆን ሌሎች ነቢያትም በእሱ ላይ እንዲተማመኑ ረድቷቸዋል። (2 ነገ. 2:15) ከጊዜ በኋላ ግን ኤልሳዕ ለ60 ዓመታት በነቢይነት ባገለገለበት ወቅት በይሖዋ እርዳታ ከኤልያስ የበለጠ ብዙ ተአምራት ፈጽሟል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉ ተማሪዎች ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
17. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ተማሪዎች የኤልሳዕን ዓይነት ባሕርይ ማንጸባረቅ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ታማኝ የሆኑ ተማሪዎችን በጊዜ ሂደት እንዴት ሊጠቀምባቸው ይችላል?
17 በጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት ኃላፊነት ስትቀበል ቶሎ ብለህ የራስህን መንገድ ለመከተል አትሞክር፤ በሌላ አባባል ከዚህ በፊት የነበረውን አሠራር ሙሉ በሙሉ መቀየር እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። አንድ አሠራር መለወጥ ያለበት በአንተ ፍላጎት መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጉባኤው ጥቅምና ከይሖዋ ድርጅት የምናገኘው መመሪያ ነው። ኤልሳዕ የኤልያስን ዘዴ መጠቀሙን በመቀጠል ሌሎቹ ነቢያት እንዲተማመኑበት ማድረግና ለኤልያስ ያለውን አክብሮት ማሳየት እንደቻለ አስታውስ፤ አንተም በተመሳሳይ ሽማግሌዎቹ ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ዘዴዎች ተግባራዊ ማድረግህን በመቀጠል የእምነት ባልንጀሮችህ እንዲተማመኑብህ ማድረግ እንዲሁም ተሞክሮ ላካበቱ ሽማግሌዎች አክብሮት እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 4:17ን አንብብ።) ተሞክሮ እያገኘህ ስትሄድ ጉባኤው ወደፊት እየገሰገሰ ከሚሄደው የይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል እንዲራመድ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ግልጽ ነው። እንዲያውም ይሖዋ ለኤልሳዕ እንዳደረገው ሁሉ አንተም ታማኝ እስከሆንክ ድረስ ውሎ አድሮ አስተማሪዎችህ ካከናወኑት የበለጠ ነገር እንድትሠራ ሊጠቀምብህ ይችላል።—ዮሐ. 14:12
18. በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችን ማሠልጠን ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው?
18 በዚህና ባለፈው ርዕስ ላይ የወጡት ሐሳቦች ጊዜ መድቦ ሌሎችን በማሠልጠን ረገድ በርካታ ሽማግሌዎችን ለተግባር እንደሚያነሳሱ ተስፋ እናደርጋለን። ብቃት ያላቸው ወንድሞች ደግሞ የሚሰጣቸውን ሥልጠና በጉጉት እንደሚቀበሉና ሥልጠናውን ማስተዋል በተሞላበት መንገድ ተጠቅመው የይሖዋን በጎች እንደሚንከባከቡ ተስፋ እናደርጋለን። ይህም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጉባኤዎች እንዲጠናከሩና ከፊታችን የሚጠብቁን ወሳኝ ክንውኖች በሚፈጸሙበት ጊዜ ሁላችንም ታማኝ ሆነን እንድንገኝ ይረዳናል።
a አንድ ወጣት መንፈሳዊ ብስለት ካለው፣ ትሑት ከሆነ እንዲሁም ሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ካሟላ 20 ዓመት ባይሞላውም እንኳ ሽማግሌዎች የጉባኤ አገልጋይ እንዲሆን ዕጩ አድርገው ሊያቀርቡት ይችላሉ።—1 ጢሞ. 3:8-10, 12፤ የሐምሌ 1, 1989 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 29ን ተመልከት።
b በሚያዝያ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 14 አንቀጽ 8 እስከ ገጽ 16 አንቀጽ 13 እና ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 16 ከአንቀጽ 1-3 ላይ የወጡትን ሐሳቦች በውይይታችሁ ወቅት መጠቀም ትችላለህ።
-