የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 17—አስቴር
ጸሐፊው:- መርዶክዮስ
የተጻፈበት ቦታ:- ሱሳ፣ ኤላም
ተጽፎ ያለቀው:- በ475 ከክ.ል.በፊት ገደማ
የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ493 እስከ 475 ከክ.ል.በፊት ገደማ
በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ዘገባ ጠቅለል አድርገን ብናስቀምጠው፣ የፋርስ ንጉሥ የነበረው አሀሱሩስ (አንዳንዶች ቀዳማዊ ጠረክሲስ እንደሆነ ይናገራሉ) ትእዛዙን ለመፈጸም ፈቃደኛ ያልነበረችውን ሚስቱን አስጢንን ከሥልጣኗ አውርዶ የመርዶክዮስ የአጎት ልጅ በሆነችው አስቴር የተባለች አይሁዳዊት መተካቱን የሚገልጽ ታሪክ ነው። አጋጋዊው ሐማ መርዶክዮስንና አይሁዳውያንን በሙሉ ለማስገደል ዶልቶ የነበረ ቢሆንም ራሱ ባዘጋጀው እንጨት ላይ ተሰቀለ። መርዶክዮስ ግን እድገት አግኝቶ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ስለተሰጠው አይሁዳውያኑ ከእልቂት ሊተርፉ ችለዋል።
2 እርግጥ፣ የአስቴር መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ሳይሆን እንዲሁ ደስ የሚል አፈ ታሪክ እንደሆነ ለመናገር የሚዳዳቸው ሰዎች አሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት በመጽሐፉ ውስጥ የአምላክ ስም አለመጠቀሱን ነው። አምላክ በቀጥታ አለመጠቀሱ እውነት ቢሆንም በዕብራይስጡ ጽሑፍ ውስጥ ይሖዋ የሚለውን የአምላክን ስም የሚወክሉት የሐወሐ (በዕብራይስጥ יהוה) የሚሉት ፊደላት በአራት የተለያዩ ቦታዎች ተከታትለው በተቀመጡ አራት ቃላት የመጀመሪያ ፊደሎች ላይ ይገኛሉ። እነዚህ የመጀመሪያ ፊደላት ቢያንስ በሦስት የዕብራይስጥ ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ በተለየ መንገድ ጎላ ብለው የተቀመጡ ሲሆን ማሶራ በሚባሉት የዕብራይስጥ ቅጂ የኅዳግ ማስታወሻዎች ላይ ደግሞ ፊደላቱ በቀይ ቀለም ምልክት ተደርጎባቸዋል። እንዲሁም በአስቴር 7:5 ላይ በተከታታይ የተቀመጡት ቃላት የመጀመሪያ ፊደላት ተገጣጥመው ሲነበቡ “እሆናለሁ” የሚለውን መለኮታዊ መግለጫ የያዙ ናቸው።—የአስቴር 1:20፤ 5:4, 13፤ 7:7 እንዲሁም 7:5ን የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
3 በጠቅላላው መጽሐፍ ውስጥ መርዶክዮስ የይሖዋን ሕግ እንደተቀበለና ይታዘዘው እንደነበረ በግልጽ ተንጸባርቋል። አማሌቃዊ ሳይሆን እንደማይቀር ለሚገመት ሰው ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆነም፤ አማሌቃውያን አምላክ እንዲጠፉ የወሰነባቸው ሕዝቦች ነበሩ። (አስ. 3:1, 5፤ ዘዳ. 25:19፤ 1 ሳሙ. 15:3) በአስቴር 4:14 ላይ መርዶክዮስ የተናገረው ነገር የይሖዋን ማዳን ይጠብቅ እንደነበርና ሁኔታዎቹን በአጠቃላይ አምላክ አቅጣጫ እንደሚያስይዝ እምነት እንደነበረው ያሳያል። አስቴር ወደ ንጉሡ ከመግባቷ በፊት በነበሩት ሦስት ቀናት እርሷም ሆነች የተቀሩት አይሁዳውያን መጾማቸው በአምላክ መታመናቸውን የሚያሳይ ነው። (አስ. 4:16) አስቴር በሴቶቹ ጠባቂ በሄጌ ዓይን ሞገስ ማግኘቷ እንዲሁም ንጉሡ እንቅልፍ ባጣበት ሌሊት መዛግብቱን አስመጥቶ መርዶክዮስ ቀደም ሲል ላከናወነው መልካም ተግባር ወሮታ እንዳልተከፈለው ማስተዋሉ፣ አምላክ ሁኔታዎቹን መልክ እያስያዘ እንደነበር የሚያረጋግጥ ነው። (አስ. 2:8, 9፤ 6:1-3፤ ከምሳሌ 21:1 ጋር አወዳድር።) “የጾሙንና የሰቈቃውን ጊዜ” የሚሉት ቃላት ስለ ጸሎት በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጠቅሱ መሆናቸው ምንም አያጠራጥርም።—አስ. 9:31
4 ዘገባው ትክክለኛና እውነተኛ መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። መጽሐፉ መግሂልላህ ማለትም “ጥቅልል” እያሉ ይጠሩት በነበሩት አይሁዳውያን ዘንድ ተቀባይነት ነበረው። የአስቴርን መጽሐፍ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ዝርዝር ውስጥ የጨመረው ዕዝራ ሳይሆን አይቀርም፤ መጽሐፉ አፈ ታሪክ ቢሆን ኖሮ እንደማይቀበለው ግልጽ ነው። አይሁዳውያን በአስቴር ዘመን ያገኙትን ታላቅ መዳን በማሰብ ፉሪም ወይም ዕጣ የሚሉትን በዓል እስከ ዛሬ ድረስ ያከብራሉ። መጽሐፉ ስለ ፋርሳውያን ልማድና ባሕል የሚያቀርበው ሕያው ዘገባ ከታሪክ ሐቅና ከአርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች ጋር የሚስማማ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የአስቴር መጽሐፍ ፋርሳውያን አንድን ሰው ስለሚያከብሩበት መንገድ ትክክለኛ መግለጫ ይሰጠናል። (6:8) በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ ስለ ንጉሡ ቤተ መንግሥት የተሰጠው መግለጫ ጥቃቅን ዝርዝሮችን ሳይቀር በትክክል ያስቀመጠ መሆኑን አርኪኦሎጂያዊ ቁፋሮዎች አረጋግጠዋል።a—5:1, 2
5 የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣናትና አገልጋዮች ስም እንዲሁም የሐማ አሥር ወንዶች ልጆች ስም ሳይቀር በመጽሐፉ ውስጥ በጥንቃቄ መሥፈሩ መጽሐፉ ዝርዝር ሐሳቦችን በትክክል እንዳስቀመጠ የሚያሳይ ነው። መርዶክዮስና አስቴር ከብንያም ነገድ በሆነው በቂስ የዘር ሐረግ የመጡ መሆናቸው ተገልጿል። (2:5-7) ስለ ፋርስ መንግሥት ኦፊሴላዊ መዛግብት የሚገልጹ ሐሳቦች በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ተጠቅሰዋል። (2:23፤ 6:1፤ 10:2) መጽሐፉ የተጻፈበት ቋንቋ በኋለኛው ዘመን የነበረ ዕብራይስጥ ሲሆን ብዙ የፋርስና የአረማይክ ቃላት እንዲሁም መግለጫዎች ተጨምረውበታል። አጻጻፉ ከዜና መዋዕል፣ ከዕዝራና ከነህምያ መጻሕፍት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ መጽሐፉ ከተጻፈበት ዘመን ጋር በትክክል ይስማማል።
6 በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ክንውኖች የተፈጸሙት ኃያሉ የፋርስ ዘውዳዊ አገዛዝ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ዘመን ሲሆን ይህም ከአሀሱሩስ (ቀዳማዊ ጠረክሲስ) የግዛት ዘመን 18 ዓመታት ገደማ የሚሸፍን ነው። ከግሪክ፣ ከፋርስና ከባቢሎን የታሪክ ምንጮች የተገኘው ማስረጃ እንደሚጠቁመው ይህ ዘመን እስከ 475 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድረስ ቆይቷል።b የመጽሐፉ ጸሐፊ የዓይን ምሥክርና ዋነኛ ባለ ታሪክ የነበረው መርዶክዮስ እንደሚሆን አያጠራጥርም፤ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኘው ጥልቀት ያለውና በዝርዝር የሠፈረ ዘገባ ጸሐፊው እነዚህ ነገሮች ሲከናወኑ በሱሳ ቤተ መንግሥት ውስጥ እንደነበረ ያሳያል።c መርዶክዮስ በሌላ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ተጠቅሶ ባይገኝም በታሪክ ውስጥ በሕይወት የነበረ ሰው መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። ደግሞም የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፈ ዘመኑ በውል የማይታወቅ አንድ ጽሑፍ የተገኘ ሲሆን ጀርመናዊው ኡንግናድ እንዳሉት በቀዳማዊ ጠረክሲስ የግዛት ዘመን በሱሳ ቤተ መንግሥት ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ስለነበረው ስለ ማርዱካ (መርዶክዮስ?) የሚናገር ነው።d መርዶክዮስ ዘገባውን ጽፎ ያጠናቀቀው ታሪኩ ከተፈጸመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በ475 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ በሱሳ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
16 ከአስቴር መጽሐፍ በቀጥታ የጠቀሰ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ባይኖርም መጽሐፉ ከተቀሩት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱና በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ የይሖዋ አምላኪዎች የሚሠሩ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያንጸባርቁ ግሩም ምሳሌዎች ይዟል። የሚከተሉትን ጥቅሶች መመርመራችን ይህ አባባል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ ክርስቲያናዊ እምነታችንን ያጠነክርልናል:- አስቴር 4:5—ፊልጵስዩስ 2:4፤ አስቴር 9:22—ገላትያ 2:10። አይሁዳውያን የንጉሡን ሕግ አልታዘዙም የሚለው ክስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ላይ ከተሰነዘረው ክስ ጋር የሚመሳሰል ነው። (አስ. 3:8, 9፤ ሥራ 16:21፤ 25:7) እውነተኛ የይሖዋ አገልጋዮች መርዶክዮስ፣ አስቴርና አይሁዳውያን ወገኖቻቸው የተዉትን ግሩም ምሳሌ በመከተል በመለኮታዊ ኃይል ነፃ እንደሚወጡ ተማምነው በመጸለይና በድፍረት እንደዚህ ያሉትን ክሶች ይጋፈጣሉ።—አስ. 4:16፤ 5:1, 2፤ 7:3-6፤ 8:3-6፤ 9:1, 2
17 ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን የእኛ ሁኔታ ከመርዶክዮስና ከአስቴር የተለየ እንደሆነ አድርገን ልናስብ አይገባም። እኛም ብንሆን የምንኖረው ‘በሥልጣን ላይ ባሉት ሹማምት’ ሥር እንደ መጻተኞች ነው። በየትኛውም አገር እንኑር ሕግ አክባሪ ዜጎች ሆነን መገኘት እንፈልጋለን። ያም ሆኖ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር” በትክክል ‘መስጠት’ እንፈልጋለን። (ሮሜ 13:1፤ ሉቃስ 20:25) ጠቅላይ ሚኒስትር መርዶክዮስና ንግሥት አስቴር ሰብዓዊ ሥራቸውን በትጋትና በታዛዥነት በመሥራት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተዋል። (አስ. 2:21-23፤ 6:2, 3, 10፤ 8:1, 2፤ 10:2) ይሁን እንጂ መርዶክዮስ በጣም ክፉ በሆነው በአጋጋዊው ሐማ ፊት ተደፍቶ እጅ እንዲነሳ የሚጠይቀውን ንጉሣዊ ትእዛዝ ባለመቀበል ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃ ወስዷል። ከዚህም በላይ ሐማ አይሁዳውያንን ለማጥፋት ባሴረበት ጊዜ መርዶክዮስ ሕጋዊ ከለላ ለማግኘት ይግባኝ እንዲጠየቅ አድርጓል።—3:1-4፤ 5:9፤ 4:6-8
18 ማስረጃዎቹ ሁሉ የአስቴር መጽሐፍ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትና ጠቃሚ’ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆኑን ያረጋግጣሉ። መጽሐፉ አምላክን ወይም ስሙን በቀጥታ ባይጠቅስም ግሩም የእምነት ምሳሌዎችን ይዞልናል። መርዶክዮስና አስቴር አንድ ተራኪ የፈጠራቸው ምናባዊ ሰዎች ሳይሆኑ በይሖዋ የማዳን ኃይል ላይ ጠንካራ እምነት የነበራቸው በገሃዱ ዓለም ኖረው ያለፉ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ናቸው። በባዕድ አገር ለመንግሥት “ሹማምት” እየተገዙ ቢኖሩም የአምላክን ሕዝብ ጥቅምና አምልኳቸውን ለማስጠበቅ ማንኛውንም ሕጋዊ መንገድ ተጠቅመዋል። እኛም ዛሬ የእነርሱን ምሳሌ በመከተል የአምላክን መንግሥት ‘ወንጌል መመከትና በሕግ ማስከበር’ እንችላለን።—ፊልጵ. 1:7 NW
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 764፤ ጥራዝ 2 ገጽ 327-331
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 613-616
c በ1981 በድጋሚ የታተመው የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒዲያ፣ ጥራዝ 3 ገጽ 310
d A. Ungnad, “Keilinschriftliche Beiträge zum Buch Esra und Ester,” Zeitschrift für die alttestamentliche Wissenschaft, LVIII (1940-41), ገጽ 240-244.