ምዕራፍ 19
ገንዘቤን በቁጠባ መጠቀም የምችለው እንዴት ነው?
የምትፈልገውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንደሌለህ የሚሰማህ ጊዜ አለ?
□ በፍጹም
□ አንዳንድ ጊዜ
□ ብዙ ጊዜ
ከአቅምህ በላይ የሆኑ ነገሮችን የምትገዛበት ጊዜ አለ?
□ በፍጹም
□ አንዳንድ ጊዜ
□ ብዙ ጊዜ
የማያስፈልግህን ዕቃ በቅናሽ ስላገኘኸው ብቻ የምትገዛበት ጊዜ አለ?
□ በፍጹም
□ አንዳንድ ጊዜ
□ ብዙ ጊዜ
የምትፈልገውን ነገር ለማድረግ በቂ ገንዘብ ኖሮህ እንደማያውቅ ይሰማሃል? ተጨማሪ ገንዘብ ብታገኝ ኖሮ ዓይንህ ውስጥ የገባውን ሞባይል መግዛት በቻልክ ነበር። ወይም ደሞዝ ቢጨመርልህ ያስፈልገኛል ያልከውን ያንን ጫማ ትገዛ ነበር። አሊያም ደግሞ አንተም እንደ ዮሐና አጣብቂኝ ውስጥ ገብተህ ይሆናል፤ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ጓደኞቼ ብዙ ወጪ የሚያስወጡ ነገሮችን አብረን እንድናደርግ ይጠይቁኛል። ከጓደኞቼ ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እፈልጋለሁ። ‘ገንዘብ ስለሌለኝ መሄድ አልችልም’ የሚል መልስ መስጠት የሚፈልግ ሰው የለም።”
በሌለህ ነገር ላይ ከመብሰልሰል ይልቅ እጅህ ላይ ያለውን ገንዘብ እንዴት በአግባቡ ልትጠቀምበት እንደምትችል ለምን አትማርም? ስለ ገንዘብ አያያዝ የመማሩን ነገር ከወላጆችህ ቤት ስትወጣ እንደምትደርስበት ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም እስቲ አስበው፦ የፓራሹትን አጠቃቀም ሳትማር ከሄሊኮፕተር ላይ ትወረወራለህ? እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ከሄሊኮፕተር ተወርውሮ ወደ መሬት እየተምዘገዘገ ሳለ ፓራሹቱን እንዴት መጠቀም እንዳለበት ሊደርስበት ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ከሄሊኮፕተሩ ላይ ከመወርወሩ በፊት ስለ ፓራሹት አጠቃቀም መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ቢማር ምንኛ የተሻለ ይሆናል!
በተመሳሳይም ስለ ገንዘብ አያያዝ ለመማር ራስህን ማስተዳደር እስክትጀምር ድረስ መቆየት አያስፈልግህም፤ ከዚህ ይልቅ ይህን ለማድረግ ከሁሉ የተሻለ አጋጣሚ የምታገኘው ከወላጆችህ ጋር እያለህ ነው። ንጉሥ ሰለሞን “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ” ጽፏል። (መክብብ 7:12) ሆኖም ገንዘብ ጥላ ከለላ የሚሆንልህ አያያዙን እስካወቅህበት ድረስ ብቻ ነው። እንዲህ ማድረግህ በራስ የመተማመን ስሜትህን የሚያሳድገው ከመሆኑም በላይ ወላጆችህ ለአንተ ያላቸው አክብሮት እንዲጨምር ያደርጋል።
መሠረታዊ ነገሮችን ተማር
ቤት ማስተዳደር ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ወላጆችህን ጠይቀሃቸው ታውቃለህ? ለአብነት ያህል፣ በየወሩ ለመብራትና ለውኃ እንዲሁም ለስልክ ምን ያህል እንደሚከፍሉ ታውቃለህ? ለመኪና፣ ለአስቤዛ፣ ለቤት ኪራይ ወይም ለባንክ ብድር ክፍያስ ስንት እንደሚያወጡ ታውቃለህ? ለእነዚህ ወጪዎች መኖር አንተም ምክንያት እንደሆንክ አትርሳ፤ ከዚህም በላይ ራስህን ችለህ ከቤት ብትወጣ እነዚህን የመሳሰሉ ወጪዎችን የምትሸፍነው አንተው ራስህ ነህ። ስለዚህ ለእነዚህ ነገሮች የሚወጣው ወጪ ምን ያህል እንደሆነ ከወዲሁ ብታውቅ የተሻለ ነው። ወላጆችህ አንዳንድ ወጪዎቻቸውን እንዲነግሩህ ጠይቃቸው፤ ከዚያም ወጪዎቹን ለመሸፈን በጀት የሚያወጡት እንዴት እንደሆነ ሲያብራሩልህ በጥሞና አዳምጣቸው።
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ፤ አስተዋዮችም መመሪያ ያግኙበት” ይላል። (ምሳሌ 1:5) አና የተባለች ወጣት ከገንዘብ ጋር በተያያዘ መመሪያ ወይም ምክር እንዲሰጧት ወላጆቿን ጠይቃቸው ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ እንዴት አድርጌ በጀት ማውጣት እንደምችል ያስተማረኝ ከመሆኑም ሌላ የቤተሰቡን ገቢ አብቃቅቶ ለመጠቀም የተደራጁ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አሳይቶኛል።”
እናቷም ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን አስተምራታለች። “እናቴ፣ አንድን ዕቃ ከመግዛት በፊት የተለያዩ ቦታዎች ጠይቆ ዋጋውን ማወዳደር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ አሳይታኛለች” ስትል አና ተናግራለች። አክላም “እማማ በትንሽ ገንዘብ ተአምር ትሠራለች” ብላለች። አና ምን ጥቅም አግኝታለች? “አሁን የራሴን ገንዘብ በሚገባ መያዝ እችላለሁ። ገንዘብ እንዳላባክን ስለምጠነቀቅ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ አልገባም፤ ይህ ደግሞ የአእምሮ ሰላም አስገኝቶልኛል” ብላለች።
ገንዘብ እንዳትቆጥብ የሚያደርጉህ ነገሮች
ገንዘብ ላለማባከን ጥንቃቄ ማድረግ የመናገሩን ያህል ቀላል እንደማይሆን የማይካድ ነው፤ በተለይ ደግሞ ከወላጆችህ ጋር እየኖርክ የኪስ ገንዘብ ወይም ደሞዝ የምታገኝ ከሆነ ይህን ለማድረግ ብዙም አትነሳሳ ይሆናል። ለምን? ምክንያቱም አብዛኛውን ወጪ የሚሸፍኑት ወላጆችህ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህም የተነሳ አብዛኛውን ገንዘብህን እንደ ልብህ ታወጣ ይሆናል። ደግሞም በገንዘብህ የፈለግኸውን ነገር ማድረግ የሚያስደስት ሊሆን ይችላል።
ይሁንና ጓደኞችህ ከሚገባው በላይ ወጪ እንድታወጣ ተጽዕኖ የሚያደርጉብህ ከሆነ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። የ21 ዓመቷ ኤሌና እንዲህ ብላለች፦ “ጓደኞቼ ገበያ ወጥቶ ዕቃ መግዛትን እንደ ትልቅ መዝናኛ ይቆጥሩታል። ከእነሱ ጋር አንድ ቦታ ስንሄድ ‘ገንዘብ ካልበተኑ ደስታ ማግኘት አይቻልም’ የሚል ሕግ ያለ ይመስል ገንዘባቸውን መርጨት ይፈልጋሉ።”
ከጓደኞችህ ጋር ተመሳስለህ ለመኖር መፈለግህ ያለ ነገር ነው። ሆኖም እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ከጓደኞቼ ጋር ስሆን ገንዘብ የማወጣው አቅሙ ስላለኝ ነው? ወይስ ማውጣት እንዳለብኝ ስለሚሰማኝ?’ ብዙ ሰዎች ገንዘብ የሚያወጡት በጓደኞቻቸውና በሚቀርቧቸው ሰዎች ዘንድ ለመወደድ ብለው ነው። እነዚህ ሰዎች በማንነታቸው ሳይሆን በገንዘባቸው ሌሎችን ለመማረክ ይሞክራሉ። እንዲህ ያለው አዝማሚያ በተለይ በዱቤ የምትጠቀም ወይም የምትበደር ከሆነ አሊያም የክፍያ ካርድ (ዴቢት ካርድ) ካለህ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ከባድ ችግር ውስጥ እንድትዘፈቅ ሊያደርግህ ይችላል። ይህ እንዳይሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ወጪህን መቆጣጠር ተማር
የክፍያ ካርድህን ወይም የወር ደሞዝህን በአንድ ጀምበር ከማሟጠጥ ይልቅ የኤሌናን ዓይነት ዘዴ ለምን አትጠቀምም? ኤሌና እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ከጓደኞቼ ጋር ወደ አንድ ቦታ ስንሄድ ምን እንደምናደርግ አስቀድሜ በማሰብ ምን ያህል እንደማወጣ እወስናለሁ። ደሞዜ በቀጥታ ወደ ባንክ ሒሳቤ የሚገባ ሲሆን ከጓደኞቼ ጋር ስሆን ከባንክ የማወጣው በዚያ ወቅት የሚያስፈልገኝን ያህል ገንዘብ ብቻ ነው። በተጨማሪም ገበያ በምወጣበት ጊዜ በገንዘብ አያያዝ ረገድ ጠንቃቃ ከሆኑት እንዲሁም የተለያየ ሱቅ ገብቼ ዋጋ ሳላወዳድር አንድን ነገር ገና እንዳየሁት ከመግዛት እንድቆጠብ ከሚያበረታቱኝ ጓደኞቼ ጋር መሄዱን ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።”
የክፍያ ካርድ ካለህ ሊጠቅሙህ የሚችሉ ተጨማሪ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።
● የገዛሃቸውን ነገሮች መዝግብ፤ ይህንንም ከባንክ ሒሳብ መግለጫው ጋር በሚገባ አመሳክረው፤ እንዲህ ማድረግህ ላልገዛኸው ነገር እንዳላስከፈሉህ ለማረጋገጥ ያስችልሃል።
● የካርድህን መለያ ቁጥር የባንኩን ሠራተኞች ጨምሮ ለማንም ሰው አትስጥ።
● የማያስፈልግህን ነገር ለመግዛት በካርድህ ከመጠቀም ተቆጠብ፤ አለበለዚያ ከሚገባው በላይ ልታወጣ ትችላለህ።
● በካርድህ በመጠቀም ሳያስፈልግህ ገንዘብ አታውጣ፤ ምክንያቱም ገንዘቡን ባላሰብከው ነገር ላይ በማዋል ልታጠፋው ትችላለህ።
● የክፍያ ካርድህን ማንም ሰው ጓደኛህም እንኳ ቢሆን እንዲጠቀምበት አትስጥ።
ይሁን እንጂ ብዙ ገንዘብ ኖሮህ ያለ ምንም ሐሳብ ማውጣት ብትችል ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ያሉብህ ችግሮች በሙሉ አይወገዱም? ላይወገዱ ይችላሉ! ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ መኪና ስትይዝ ዓይንህን ጨፍነህ የመንዳት ልማድ ቢኖርህ ወይም መኪናውን መቆጣጠር የማትችል ቢሆን ተጨማሪ ነዳጅ መቅዳትህ አደጋ ሳያጋጥምህ የፈለግኸው ቦታ ለመድረስ ያስችልሃል? በተመሳሳይም ወጪዎችህን እንዴት መቆጣጠር እንዳለብህ እስካልተማርክ ድረስ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘትህ በራሱ ሁኔታዎችን ሊያስተካክልልህ አይችልም።
እርግጥ ነው፣ ገንዘብህን በአግባቡ እንደምትጠቀምበት ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ባለፈው ወር ያወጣሁት ገንዘብ ምን ያህል ነው? ገንዘቡን ያጠፋሁት በምንድን ነው?’ መልሱን እርግጠኛ አይደለህም? እንግዲያው ገንዘብህን የማባከን ልማድህ ሕይወትህን ከመቆጣጠሩ በፊት አንተ ወጪህን መቆጣጠር የምትችልበት ዘዴ እነሆ፦
1. መዝገብ ይኑርህ። ቢያንስ ለአንድ ወር ያህል ገቢህንና ይህን ገቢ ያገኘህበትን ቀን መዝግበህ ያዝ። የገዛኸውን እያንዳንዱን ዕቃ ከነዋጋው ጻፍ። ከዚያም በወሩ መጨረሻ ላይ፣ ያገኘኸውን ገንዘብም ሆነ ወጪዎችህን ደምር።
2. በጀት አውጣ። በገጽ 163 ላይ የሚገኘውን ሠንጠረዥ ተመልከት። በመጀመሪያው ረድፍ ላይ በወሩ ውስጥ ልታገኛቸው የምትችላቸውን ገቢዎች በሙሉ መዝግብ። ከዚያም ገንዘብህን ለምን ነገሮች ለማውጣት እንዳቀድክ በሁለተኛው ረድፍ ላይ ጻፍ፤ ለዚህም በመዝገብህ ላይ (ተራ ቁጥር 1) የጻፍከውን ዝርዝር መሠረት ማድረግ ትችላለህ። ወሩ እየገፋ ሲሄድ፣ አስቀድመህ ላቀድካቸው ነገሮች ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጣህ በሦስተኛው ረድፍ ላይ ጻፍ። በተጨማሪም ከእቅድህ ውጪ ያወጣኸውን ገንዘብ በሙሉ መዝግብ።
3. ማስተካከያ አድርግ። ለአንዳንድ ነገሮች አስቀድመህ ካሰብከው የበለጠ ወጪ ካወጣህና ዕዳ ውስጥ ከገባህ ከወጪ ጋር በተያያዘ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልግሃል። ዕዳህን ክፈል፤ ምንጊዜም ወጪህን ተቆጣጠር።
ገንዘብ በአግባቡ ከተጠቀምክበት ጥሩ አገልጋይ ሊሆን ይችላል። በብዙ ባሕሎች ውስጥ ሰዎች ገንዘብ ማግኘትና ያገኙትን ገንዘብ በአግባቡ መያዝ በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ነገሮች አንዱ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ያም ቢሆን ግን ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖርህ ይገባል። ማቲው የተባለ ወጣት “ገንዘብ ጠቃሚ ቢሆንም ሕይወታችንን ሊቆጣጠረው አይገባም” ብሏል። “ገንዘብ በምንም ዓይነት ከቤተሰባችን ወይም ከይሖዋ ሊበልጥብን አይገባም።”
አንተና ቤተሰቦችህ በድህነት እንደምትኖሩ ይሰማሃል? ከሆነ ባሉህ ነገሮች ላይ በማተኮር ደስታህን ጠብቀህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?
ቁልፍ ጥቅስ
“ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው።”—መክብብ 7:12
ጠቃሚ ምክር
ገበያ ከመውጣትህ በፊት ለመግዛት ያሰብካቸውን ነገሮች በዝርዝር ጻፍ። የሚያስፈልግህን ገንዘብ ብቻ ያዝ፤ እንዲሁም ከጻፍከው ውጪ ሌላ ነገር ላለመግዛት ጥረት አድርግ።
ይህን ታውቅ ነበር?
ከአንድ አበዳሪ ድርጅት በዓመት ከፍለህ የምትጨርሰው 2,000 ብር በ16 በመቶ ወለድ ብትበደርና በውሉ መሠረት ሳትከፍል ሁለት ዓመት ቢያልፍብህ የአገልግሎት ክፍያውንና ቅጣቱን ጨምሮ ከተበደርከው ገንዘብ ሌላ 1,314 ብር ወለድ መክፈል ይኖርብሃል።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
ወጪዬን ለመቆጣጠር እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
በክፍያ ካርዴ ተጠቅሜ ወይም በዱቤ አንድ ነገር ከመግዛቴ በፊት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● ስለ ገንዘብ አያያዝ ለመማር ከሁሉ የተሻለው አጋጣሚ ከወላጆችህ ጋር እያለህ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
● ገንዘብህን በቁጠባ መጠቀም አስቸጋሪ ሊሆንብህ የሚችለው ለምንድን ነው?
● ገንዘብህን ሌሎችን ለመርዳት ልታውለው የምትችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
[በገጽ 162 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በበጀቴ መሠረት ገንዘብ ሳወጣ የበለጠ እቆጥባለሁ። የማያስፈልጉኝን ነገሮች አልገዛም።”—ሊያ
[በገጽ 158 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ገንዘብህን የምትጠቀምበት መንገድ ስለ ማንነትህ ይናገራል
ገንዘብህን የምታጠፋው በምንድን ነው? ገንዘብህን ሌሎችን ለመርዳት የማዋል ልማድ ካለህ በአንደበትህ ብቻ ሳይሆን ገንዘብህን በምትጠቀምበት መንገድም ለሌሎች ከልብ እንደምታስብ ታሳያለህ። (ያዕቆብ 2:14-17) እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ አዘውትረህ መዋጮ በማድረግ ‘ይሖዋን በሀብትህ አክብረው።’ (ምሳሌ 3:9) በሌላ በኩል ግን ሁልጊዜ ገንዘብህን የምታውለው የራስህን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ከሆነ ገንዘብህን የምትጠቀምበት መንገድ ስለ አንተ ማንነት ምን ይናገራል?
[በገጽ 163 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ/ሥዕል]
የመልመጃ ሣጥን
ወርኃዊ በጀት
ፎቶ ኮፒ አድርገው!
ገቢ
የኪስ ገንዘብ
የትርፍ ሰዓት ሥራ
ሌሎች
ድምር
ብር․․․․․
በጀት
ለምግብ
․․․․․
ለልብስ
․․․․․
ለስልክ
․․․․․
ለመዝናኛ
․․․․․
ገቢ
․․․․․
የማጠራቅመው
․․․․․
ሌሎች
․․․․․
ድምር
ብር․․․․․
ያወጣሁት ወጪ
ለምግብ
․․․․․
ለልብስ
․․․․․
ለስልክ
․․․․․
ለመዝናኛ
․․․․․
ገቢ
․․․․․
የማጠራቅመው
․․․․․
ሌሎች
․․․․․
ድምር
ብር․․․․․
[በገጽ 160 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጪን አለመቆጣጠር ዓይንን ጨፍኖ እንደ መንዳት ነው