የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bsi08-1 ገጽ 26-28
  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 49—ኤፌሶን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 49—ኤፌሶን
  • “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 16
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
“ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 16
bsi08-1 ገጽ 26-28

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 49​—⁠ኤፌሶን

ጸሐፊው:- ጳውሎስ

የተጻፈበት ቦታ:- ሮም

ተጽፎ ያለቀው:- ከ60–61 ከክ.ል.በኋላ ገደማ

እስር ቤት ውስጥ ነህ እንበል። የታሰርከው በክርስቲያናዊ የሚስዮናዊነት አገልግሎት ቅንዓት የተሞላበት እንቅስቃሴ በማድረግህ ነው። ከአሁን በኋላ ጉባኤዎችን እየተዘዋወርክ መጎብኘትና ማበረታታት አትችልም፤ ምን ታደርጋለህ? በአንተ የስብከት እንቅስቃሴ ምክንያት ክርስቲያን ለሆኑ ሰዎች ደብዳቤ አትጽፍላቸውም? ስለ ደኅንነትህ ማወቅና ማበረታቻ ማግኘት አያስፈልጋቸውም? በእርግጥ ያስፈልጋቸዋል! በመሆኑም ለእነዚህ ሰዎች መጻፍ ትጀምራለህ። አሁን እያደረግህ ያለኸው ጳውሎስ ከ59-61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮም ሲታሰር አድርጎት የነበረውን ነገር ነው። ጳውሎስ ለቄሣር ይግባኝ ብሎ ፍርዱን እየተጠባበቀ ቢሆንም በጥበቃ ሥር ሆኖ አንዳንድ ነገሮችን የማድረግ ነፃነት ነበረው። ጳውሎስ ደብዳቤውን “በኤፌሶን ለሚገኙ” ክርስቲያኖች የጻፈው በ60 ወይም በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ በሮም ሆኖ ነው። ደብዳቤውን ወደ አፌሶን የወሰደው ቲኪቆስ ሲሆን አናሲሞስም አብሮት ተጉዟል።—ኤፌ. 6:21፤ ቈላ. 4:7-9

2 ጳውሎስ የደብዳቤው ጸሐፊ ራሱ መሆኑን በመጀመሪያው ቁጥር ላይ የገለጸ ሲሆን አራት ጊዜ ደግሞ “በጌታ እስረኛ የሆንሁ” በማለት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ማንነቱን ጠቅሷል። (ኤፌ. 1:1፤ 3:1, 13፤ 4:1፤ 6:20) ደብዳቤው በጳውሎስ ስለመጻፉ የተነሳው ክርክር ከንቱ ሆኗል። በ200 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ እንደተጻፈ የሚታመነው ቼስተር ቢቲ ፓፒረስ ቁ. 2 (P46) የጳውሎስ መልእክቶችን ካካተተ ኮዴክስ ውስጥ የተወሰዱ 86 ገጾችን ይዟል። ከእነዚህ ገጾች ውስጥ የኤፌሶን መልእክት የሚገኝ ሲሆን ይህም መልእክቱ በዚያን ጊዜ ከሌሎቹ የጳውሎስ ደብዳቤዎች ጋር ይመደብ እንደነበር ያሳያል።

3 ቀደምት የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች የደብዳቤው ጸሐፊ ጳውሎስ እንደሆነና የጻፈውም “በኤፌሶን ለሚገኙ” ክርስቲያኖች መሆኑን ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ ያህል በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ይኖር የነበረው ኢረንየስ “የተባረከው ጳውሎስ ለኤፌሶን በላከው መልእክት ላይ የአካሉ ብልቶች መሆናችንን ገልጿል” ሲል ኤፌሶን 5:30ን ጠቅሶ ተናግሯል። በዚያው ዘመን የኖረው የእስክንድሪያው ክሌመንት ኤፌሶን 5:21ን በመጥቀስ “በተጨማሪም ለኤፌሶን በተላከው መልእክት ላይ [ጳውሎስ] ለአምላክ ካላችሁ አክብሮታዊ ፍርሃት የተነሳ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ ሲል ጽፏል” በማለት ዘግቧል። ኦሪጀን በሦስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ሲጽፍ ኤፌሶን 1:4ን በመጥቀስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ነገር ግን ሐዋርያው ለኤፌሶን በላከው መልእክትም ላይ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ መረጠን በማለት ተመሳሳይ አነጋገር ተጠቅሟል።”a በቀድሞ የክርስትና ታሪክ ሥልጣን የነበረው ዩሲቢየስ (ከ260-342 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) የኤፌሶንን መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጨመረው ሲሆን ሌሎች በርካታ የጥንት የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎችም በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል በመቁጠር ከኤፌሶን ጠቅሰው ጽፈዋል።b

4 የቼስተር ቢቲ ፓፒረስ፣ የቫቲካን ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ቁ. 1209 እንዲሁም የሳይናይቲክ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች፣ በምዕራፍ 1 ቁጥር 1 ላይ ያለውን “በኤፌሶን ለሚገኙ” የሚለውን ሐረግ በማውጣታቸው ደብዳቤው ለማን እንደተላከ አይጠቁሙም። በተጨማሪም (ጳውሎስ ለሦስት ዓመታት ያህል በዚያ ቢደክምም) በኤፌሶን ለሚኖሩ ግለሰቦች የቀረበ ሰላምታ የለም። በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች የተነሳ አንዳንዶች ደብዳቤው የተላከው ወደ ሌላ ቦታ መሆን አለበት አሊያም ደግሞ ኤፌሶንን ጨምሮ በትንሿ እስያ በሚገኙ ጉባኤዎች በሙሉ እንዲነበብ የተላከ ደብዳቤ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ ሌሎች በርካታ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች “በኤፌሶን ለሚገኙ” የሚሉትን ቃላት ይጨምራሉ፤ እንዲሁም ከላይ እንደተመለከትነው በቀድሞ ዘመን ይኖሩ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ደብዳቤው ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈ መሆኑን አምነው ተቀብለዋል።

5 በወቅቱ የነበሩትን ሁኔታዎች መመርመራችን ደብዳቤው የተጻፈበትን ዓላማ ለመረዳት ያስችለናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኤፌሶን በጥንቆላ፣ በአስማት፣ በኮከብ ቆጠራና የመራባት እንስት አምላክ በሆነችው የአርጤምስ አምልኮ የታወቀች ነበረች።c በዚህች እንስት ጣዖት ሐውልት ዙሪያ ዕጹብ ድንቅ የሆነ ቤተ መቅደስ ተገንብቶ ነበር። ይህ ቤተ መቅደስ በጥንቱ ዓለም ውስጥ ከሚገኙት ሰባት አስደናቂ ነገሮች መካከል አንዱ ተደርጎ ይታይ ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን በቦታው ላይ በተደረገ ቁፋሮ በተገኘ መረጃ መሠረት ቤተ መቅደሱ የተገነባው 73 ሜትር ስፋትና 127 ሜትር ርዝመት ባለው ከፍ ያለ ወለል ላይ ነበር። ቤተ መቅደሱ ራሱ 50 ሜትር ስፋትና 105 ሜትር ርዝመት ነበረው። እያንዳንዳቸው 17 ሜትር ቁመት ያላቸው 100 የእብነ በረድ ዓምዶች ነበሩት። ጣሪያው በትላልቅ ነጭ የእብነ በረድ ጡቦች የተሸፈነ ነበር። የእብነ በረድ ጡቦቹን ለማያያዝ ጥቅም ላይ የዋለው ሲሚንቶ ሳይሆን ወርቅ እንደነበር ይነገራል። ቤተ መቅደሱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ አገር ጎብኚዎችን የሚስብ ሲሆን በበዓላት ወቅት ደግሞ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ወደ ከተማይቱ ይጎርፋሉ። የኤፌሶን አንጥረኞች የአርጤምስ ምስሎችን ከብር እየሠሩ ለሃይማኖት ተጓዦች በማስታወሻነት በመሸጥ አትራፊ የሆነ የንግድ ሥራ ያካሂዱ ነበር።

6 ጳውሎስ በሁለተኛ የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት በኤፌሶን እየመሠከረ ለጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ሥራውን እንዲቀጥሉ አቂላንና ጵርስቅላን በዚያ ትቷቸው ሄደ። (ሥራ 18:18-21) በሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ተመልሶ በመምጣት ለብዙዎች ‘የጌታን መንገድ’ እየሰበከና እያስተማረ ለሦስት ዓመት ያህል ቆየ። (ሥራ 19:8-10፤ 20:31) ጳውሎስ በኤፌሶን በነበረበት ጊዜ ጠንክሮ ሠርቷል። ኤ ኢ ቤይሊ፣ ዴይሊ ላይፍ ኢን ባይብል ታይምስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የጳውሎስ የዘወትር ልማድ ጎህ ሲቀድ ጀምሮ ጢራኖስ ማስተማሩን እስከሚጨርስበት እስከ 5 ሰዓት ድረስ የራሱን ሥራ መሥራት (ሥራ 20:34, 35)፤ ከዚያም ከ5 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ድረስ በአዳራሹ ውስጥ መስበክ፣ እንዲሁም ከሚረዱት ጋር ሆኖ ስብሰባዎችን ማካሄድ፣ . . . በመጨረሻም ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ከ10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ድረስ ወንጌሉን መስበክ ነበር። (ሥራ 20:20, 21, 31) አንድ ሰው ጳውሎስ መቼ ጊዜ አግኝቶ እንደሚበላና እንደሚተኛ ሳይገርመው አይቀርም።”—1943፣ ገጽ 308

7 ጳውሎስ በዚህ ቅንዓት በተሞላበት የስብከት እንቅስቃሴው ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ስህተት መሆኑን አጋልጧል። ይህ ደግሞ ምስሎችን እየሠሩ ይሸጡ የነበሩ እንደ አንጥረኛው ድሜጥሮስ ያሉ ሰዎችን ቁጣ ቀሰቀሰ። በመጨረሻም ጳውሎስ በተነሳው ሁከት ሳቢያ ከተማውን ለቅቆ ለመሄድ ተገደደ።—ሥራ 19:23 እስከ 20:1

8 አሁን፣ ጳውሎስ በእስር ቤት ሆኖ የኤፌሶን ጉባኤ ስለገጠሙት ችግሮች እያሰላሰለ ነው። ይህ ጉባኤ በአረማዊ አምላኪዎች የተከበበና እጅግ አስደናቂ በነበረው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ አቅራቢያ የሚገኝ ነበር። እነዚህ የተቀቡ ክርስቲያኖች ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት የሚያርፍበት “ቅዱስ ቤተ መቅደስ” ክፍሎች ስለመሆናቸው የሚገልጸው ከሁኔታቸው ጋር የሚስማማው የጳውሎስ ምሳሌ እንደሚያስፈልጋቸው ምንም አያጠራጥርም። (ኤፌ. 2:21) በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት አንድነትንና ሰላምን መልሶ ስለሚያሰፍነው ስለ አምላክ አስተዳደር (የቤቱን ጉዳዮች ስለሚያስተዳድርበት መንገድ) ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የተገለጠው ቅዱስ “ምስጢር” በእጅጉ መንፈሳቸውን የሚያነቃቃና የሚያጽናና መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። (1:9, 10) ጳውሎስ አይሁድና አሕዛብ በክርስቶስ አንድ መሆናቸውን ጎላ አድርጎ ገልጿል። ስምምነትና አንድነት እንዲኖር አጥብቆ መክሯል። በመሆኑም አሁን፣ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የዚህን መጽሐፍ ዓላማና ያለውን ከፍተኛ ጥቅም ማድነቅ እንችላለን።

ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት

16 ለኤፌሶን የተላከው መልእክት የማይዳስሰው የክርስቲያን ሕይወት ክፍል የለም ለማለት ይቻላል። በዓለም ውስጥ አሳዛኝ ችግሮችና ወንጀሎች እየተበራከቱ ከመምጣታቸው አንጻር ጳውሎስ የሰጠው ትክክለኛና ተግባራዊ ምክር ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ሕይወት ለመምራት ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ በእርግጥም ጠቃሚ ነው። ልጆች ለወላጆቻቸው እንዲሁም ወላጆች ለልጆቻቸው ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል? ባል ለሚስቱ እንዲሁም ሚስት ለባሏ ያለባቸው ኃላፊነት ምንድን ነው? በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ፍቅራዊ አንድነትንና ክርስቲያናዊ ንጽሕናን ለመጠበቅ ምን ማድረግ አለባቸው? የጳውሎስ ምክር ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። እንዲሁም አዲሱን ሰው መልበስ ምንን እንደሚጨምር ይገልጻል። የኤፌሶንን መልእክት የሚያጠኑ ሁሉ አምላክን ለሚያስደስተው ማለትም ‘እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና አምላክን እንዲመስል ለተፈጠረው’ ስብዕና እውነተኛ አድናቆት ማዳበር ይችላሉ።—4:24-32፤ 6:1-4፤ 5:3-5, 15-20, 22-33

17 በተጨማሪም ደብዳቤው በጉባኤ ውስጥ የሚገኘው ሹመትና የሥራ ድልድል ዓላማ ምን መሆኑን ይገልጻል። ይህም ‘ቅዱሳን እንዲስተካከሉ፣ እንዲያገለግሉና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን በመሆን’ ወደ ጉልምስና እንዲደርሱ ማድረግ ነው። አንድ ክርስቲያን ከእነዚህ የጉባኤ ዝግጅቶች ጋር ሙሉ በሙሉ በመተባበር ‘ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ በፍቅርና በነገር ሁሉ ሊያድግ’ ይችላል።—4:12 [NW], 15

18 ለኤፌሶን ሰዎች የተላከው ደብዳቤ የጥንቱ ጉባኤ ስለ ቅዱሱ ‘የክርስቶስ ምስጢር’ ያለውን ማስተዋል ከፍ ለማድረግ በእጅጉ ጠቅሟል። እዚህ ላይ “አሕዛብ” ካመኑት አይሁድ ጋር ‘አብረው እንዲወርሱ፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች እንዲሆኑ እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው እንዲካፈሉ’ የተጠሩ መሆኑን ግልጽ ያደርጋል። አሕዛብን ከአይሁድ ይለይ የነበረው ግድግዳ ማለትም የሙሴ “ሕግ” በመሻሩ አሁን በክርስቶስ ደም አማካኝነት ሁሉም ቅዱሳን ዜጎችና የአምላክ ቤተሰብ አባላት ሆነዋል። ከአርጤምስ አረማዊ ቤተ መቅደስ በጣም በተለየ መልኩ እነዚህ ሰዎች “[ለይሖዋ] ቅዱስ ቤተ መቅደስ” በመሆን አምላክ በመንፈሱ እንዲያድርባቸው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የሚገነቡ ናቸው።—3:4, 6፤ 2:15, 21

19 በተጨማሪም ጳውሎስ ቅዱሱን “ምስጢር” በተመለከተ ሲናገር “በሰማይም [በሰማያዊ መንግሥቱ እንዲሆኑ የተመረጡትንና] በምድርም ያሉትን [በምድር ላይ በመንግሥቱ ግዛት ሥር የሚኖሩትን] ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል” ስለሚያስችል አንድ አስተዳደር ገልጿል። በመሆኑም አምላክ ሰላምንና አንድነትን መልሶ ለማምጣት ያለው ታላቅ ዓላማ ፍጻሜውን ለማግኘት ተቃርቧል። ጳውሎስ ከዚህ ጋር በማያያዝ ስለ ኤፌሶን ሰዎች ባቀረበው ጸሎት ላይ በአምላክ የተጠሩበትን ተስፋ አጥብቀው መያዝና “በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለ ጠግነት” መረዳት ይችሉ ዘንድ የልቦናቸው ዓይን እንዲበራላቸው ልመና አቅርቧል። እነዚህ ቃላት በዚያ ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች ተስፋቸውን በማለምለም በእጅጉ አበርትተዋቸው መሆን አለበት። ከዚህም በተጨማሪ ለኤፌሶን ሰዎች በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ይህ ደብዳቤ ‘በአምላክ ሙላት ሁሉ ልክ ደርሰው እንዲሞሉ’ ስለሚያደርግ በጊዜያችን የሚገኙትንም ጉባኤዎች ያንጻል።—1:9-11, 18፤ 3:19

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኦሪጅን ኤንድ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ቡክስ ኦቭ ዘ ባይብል፣ 1868፣ ሲ ኢ ስቶው፣ ገጽ 357

b በጄ ዲ ዳግላስ የተዘጋጀው ኒው ባይብል ዲክሽነሪ፣ ሁለተኛ እትም፣ 1986 ገጽ 175

c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1 ገጽ 182

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ