የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bt ምዕ. 14 ገጽ 108-115
  • “በአንድ ልብ ወሰንን”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “በአንድ ልብ ወሰንን”
  • ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል” (የሐዋርያት ሥራ 15:13-21)
  • ‘የተመረጡ ሰዎችን ላኩ’ (የሐዋርያት ሥራ 15:22-29)
  • “ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደሰቱ” (የሐዋርያት ሥራ 15:30-35)
  • በዛሬው ጊዜ የበላይ አካሉ ሥራውን የሚያከናውነው እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
  • በዛሬው ጊዜ የአምላክን ሕዝቦች የሚመራው ማን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • “የጦፈ ክርክር” ተነሳ
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
  • “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚጫወተው ሚና
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
ለተጨማሪ መረጃ
‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
bt ምዕ. 14 ገጽ 108-115

ምዕራፍ 14

“በአንድ ልብ ወሰንን”

የበላይ አካሉ ውሳኔ ላይ የደረሰበት መንገድ እንዲሁም ውሳኔው ለጉባኤው አንድነት ያበረከተው አስተዋጽኦ

በሐዋርያት ሥራ 15:13-35 ላይ የተመሠረተ

1, 2. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል ለየትኞቹ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ያስፈልገው ነበር? (ለ) እነዚህ ወንድሞች ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ መድረስ እንዲችሉ የረዳቸው ምንድን ነው?

የሁሉም ልብ ተንጠልጥሏል። በኢየሩሳሌም የተሰበሰቡት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እርስ በርስ እየተያዩ ነው፤ ታሪካዊ ውሳኔ የሚያደርጉበት ሰዓት እንደደረሰ ገብቷቸዋል። የግርዘት ጉዳይ መልስ የሚያሻቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች አስነስቷል። ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ መጠበቅ አለባቸው? አይሁዳውያን በሆኑና ከአሕዛብ ወገን በመጡ ክርስቲያኖች መካከል ልዩነት ሊኖር ይገባል?

2 በአመራር ቦታ ላይ ያሉት እነዚህ ወንድሞች ብዙ ማስረጃዎችን መርምረዋል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ትንቢት ምን እንደሚል ተመልክተዋል፤ በተጨማሪም የይሖዋ በረከት መኖሩን የሚጠቁሙ ተሞክሮዎችን የዓይን ምሥክር ከሆኑ ሰዎች ሰምተዋል። ሐሳባቸውን አውጥተው በነፃነት ተነጋግረዋል። አሁን ለውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን በቂ ማስረጃ አግኝተዋል። የይሖዋ መንፈስ ትክክለኛውን አቅጣጫ በግልጽ እየጠቆማቸው ነው። ታዲያ እነዚህ ወንድሞች የመንፈሱን አመራር ይቀበሉ ይሆን?

3. በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ላይ የሰፈረውን ዘገባ መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

3 ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የመንፈስ ቅዱስን አመራር መከተል ከፍተኛ እምነትና ድፍረት የሚጠይቅ ነው። መመሪያውን መቀበላቸው የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ለእነሱ ያላቸው ጥላቻ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። የአምላክ ሕዝቦች ዳግመኛ የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ለማድረግ ቆርጠው ከተነሱ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ተቃውሞ ሊገጥማቸው ይችላል። ታዲያ የበላይ አካሉ ምን ያደርግ ይሆን? እስቲ እንመልከት። እግረ መንገዳችንን፣ እነዚህ ወንድሞች በዛሬው ጊዜ ላለው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ምን ምሳሌ እንደተዉ እንመረምራለን። እኛም በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውሳኔ የሚያሻቸው ጉዳዮችና ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የእነሱን ምሳሌ መከተላችን ይጠቅመናል።

“የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል” (የሐዋርያት ሥራ 15:13-21)

4, 5. ያዕቆብ ከአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ የትኛውን ሐሳብ ጠቅሶ ተናገረ?

4 አሁን የኢየሱስ ወንድም የሆነው ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ መናገር ጀመረ።a ያዕቆብ ይህን ስብሰባ በሊቀ መንበርነት እየመራ የነበረ ይመስላል። ጠቅለል አድርጎ የተናገረው ሐሳብ የበላይ አካሉ የደረሰበትን መደምደሚያ የሚገልጽ ሳይሆን አይቀርም። በዚያ ተሰብስበው የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ለእነሱ ትኩረት እንደሰጠ ሲምዖን በሚገባ ተርኳል። . . . የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል።”—ሥራ 15:14, 15

5 ያዕቆብ፣ ሲምዖን ወይም ስምዖን ጴጥሮስ የተናገረውን ሐሳብ እንዲሁም በርናባስና ጳውሎስ ያቀረቡትን ማስረጃ ሲሰማ ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉ ጥቅሶች ወደ አእምሮው ሳይመጡ አልቀሩም። (ዮሐ. 14:26) “የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል” ካለ በኋላ በአሞጽ 9:11, 12 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ጠቀሰ። ይህ መጽሐፍ የሚገኘው በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ “ነቢያት” ተብሎ በሚጠራው ክፍል ውስጥ ነው። (ማቴ. 22:40፤ ሥራ 15:16-18) ያዕቆብ ጠቅሶ የተናገረው ሐሳብ ዛሬ በአሞጽ መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሮ ከሚገኘው ሐሳብ የተወሰነ ልዩነት እንዳለው አስተውለህ ይሆናል። ያዕቆብ የጠቀሰው ከሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ማለትም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የግሪክኛ ትርጉም ላይ ሳይሆን አይቀርም።

6. የተነሳውን ጉዳይ ይበልጥ ግልጽ ያደረጉት የትኞቹ ትንቢቶች ናቸው?

6 ይሖዋ “የዳዊትን ዳስ” የሚያቆምበት ጊዜ እንደሚመጣ በነቢዩ አሞጽ በኩል አስቀድሞ ተናግሯል፤ ይህ አገላለጽ ከመሲሐዊው መንግሥት መቋቋም ጋር የተያያዘ ነው። (ሕዝ. 21:26, 27) ታዲያ ይሖዋ ሥጋዊ እስራኤላውያንን ብቻ እንደገና ለእሱ የተለየ ብሔር አድርጎ ሊወስድ ነው ማለት ነው? በፍጹም! ትንቢቱ በመቀጠል ‘ከብሔራት የመጡ ሰዎች’ አንድ ላይ ተሰባስበው በአምላክ ‘ስም የተጠሩ ሰዎች’ እንደሚሆኑ ይገልጻል። ጴጥሮስ ጥቂት ቀደም ብሎ የሰጠውን ምሥክርነት አስታውስ፤ አምላክ “በእኛና [በአይሁዳውያን ክርስቲያኖችና] በእነሱ [ከአሕዛብ በመጡት ክርስቲያኖች] መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው የተነሳ ልባቸውን አነጻ” ብሎ ነበር። (ሥራ 15:9) በሌላ አባባል አይሁዳውያንም ሆኑ ከአሕዛብ የመጡት ሰዎች የመንግሥቱ ወራሾች እንዲሆኑ የአምላክ ፈቃድ ነው። (ሮም 8:17፤ ኤፌ. 2:17-19) ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች መጀመሪያ መገረዝ ወይም ወደ ይሁዲነት መለወጥ እንዳለባቸው የሚጠቁም ሐሳብ በመንፈስ መሪነት በተጻፉት ትንቢቶች ላይ አይገኝም።

7, 8. (ሀ) ያዕቆብ ምን ሐሳብ አቀረበ? (ለ) ያዕቆብ “እንደ እኔ ውሳኔ ከሆነ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

7 ያዕቆብ ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃና ሌሎች የሰጡትን አሳማኝ ምሥክርነት መሠረት በማድረግ የሚከተለውን ሐሳብ አቀረበ፦ “ስለዚህ እንደ እኔ ሐሳብ [“ውሳኔ፣” ግርጌ] ከሆነ፣ ተለውጠው አምላክን ማምለክ የጀመሩትን አሕዛብ ባናስቸግራቸው ይሻላል፤ ከዚህ ይልቅ በጣዖት ከረከሱ ነገሮች፣ ከፆታ ብልግና፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከደም እንዲርቁ እንጻፍላቸው። ምክንያቱም ከጥንት ዘመን ጀምሮ በየከተማው በሰንበት ቀናት ሁሉ በምኩራቦች ውስጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከሙሴ መጻሕፍት በማንበብ በውስጡ የሰፈረውን ቃል የሚሰብኩ ሰዎች ነበሩ።”—ሥራ 15:19-21

8 የስብሰባው ሊቀ መንበር እንደሆነ የሚገመተው ያዕቆብ “እንደ እኔ ውሳኔ ከሆነ” ብሏል፤ ታዲያ እንዲህ ሲል ሥልጣኑን ተጠቅሞ የራሱን ውሳኔ በሌሎቹ ወንድሞች ላይ ለመጫን እየሞከረ ነው? በፍጹም! “እንደ እኔ ውሳኔ ከሆነ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “እንደ እኔ አመለካከት” ወይም “እንደ እኔ አስተያየት” የሚል መልእክትም ያስተላልፋል። ስለዚህ ያዕቆብ ሁሉንም ወክሎ ውሳኔ እያሳለፈ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ የቀረበውን ማስረጃና ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን ሐሳብ መሠረት በማድረግ ጉዳዩን እንዲያጤኑት ሐሳብ እያቀረበ ነው።

9. ያዕቆብ ያቀረበው ሐሳብ ምን ጥቅሞች ነበሩት?

9 ያዕቆብ ያቀረበው ሐሳብ ጥሩ ነበር? በሚገባ! ምክንያቱም በኋላ ላይ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ውሳኔ አድርገው ያስተላለፉት እሱ ያቀረበውን ሐሳብ ነው። ምን ጥቅሞችስ ነበሩት? በአንድ በኩል ከአሕዛብ የመጡት ክርስቲያኖች ‘እንዲቸገሩ’ የሚያደርግ አይደለም፤ ምክንያቱም በሙሴ ሕግ ላይ የሰፈሩትን ደንቦች እንዲጠብቁ አያስገድድም። (ሥራ 15:19) በሌላ በኩል ደግሞ የአይሁዳውያን ክርስቲያኖችን ሕሊና ግምት ውስጥ ያስገባ ነው፤ እነዚህ ወንድሞች ለዓመታት ‘በሰንበት ቀናት ሁሉ በምኩራቦች ውስጥ ከሙሴ መጻሕፍት ሲነበብ’ ሲሰሙ እንደኖሩ ይታወቃል።b (ሥራ 15:21) በእርግጥም የቀረበው ሐሳብ አይሁዳውያን በሆኑና ከአሕዛብ በመጡ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን ወዳጅነት የሚያጠናክር ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን የሚያስደስት ነው፤ ምክንያቱም ወደፊት ከሚገሰግሰው ዓላማው ጋር የሚስማማ ነው። መላውን የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤ አንድነትና ደህንነት ስጋት ላይ ጥሎ የነበረው ጉዳይ እልባት ያገኘበት መንገድ አስደናቂ ነው! ዛሬ ላለው የክርስቲያን ጉባኤም እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

በ1998 በተደረገ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ወንድም አልበርት ሽሮደር ንግግር ሲያቀርብ

10. ዛሬ ያለው የበላይ አካል በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የበላይ አካል ምሳሌ የሚከተለው እንዴት ነው?

10 ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ የተጠቀሰን አንድ ነጥብ እንደገና እናንሳ፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው የበላይ አካል ሁሉ ዛሬ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካልም ማንኛውንም ጉዳይ በተመለከተ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢ ከሆነው ከይሖዋና የጉባኤው ራስ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ መመሪያ ለማግኘት ይጥራል።c (1 ቆሮ. 11:3) የበላይ አካሉ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ከ1974 አንስቶ ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት እስከ መጋቢት 2006 ድረስ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም አልበርት ሽሮደር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የበላይ አካሉ ረቡዕ ላይ ይሰበሰባል፤ በጸሎት አማካኝነት የይሖዋን መንፈስ አመራር በመጠየቅ ስብሰባውን ይጀምራል። እያንዳንዱ ጉዳይና እያንዳንዱ ውሳኔ የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል።” በተመሳሳይም መጋቢት 2003 ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ለረጅም ጊዜ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ሚልተን ሄንሼል ለ101ኛው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች ይህን ወሳኝ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፦ “አስፈላጊ ውሳኔዎችን ከማድረጉ በፊት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መመሪያ ለማግኘት የሚጥር የበላይ አካል ያለው ሌላ ድርጅት በዚህች ምድር ላይ ይገኛል?” መልሱ ግልጽ ነው!

‘የተመረጡ ሰዎችን ላኩ’ (የሐዋርያት ሥራ 15:22-29)

11. የበላይ አካሉ ያሳለፈውን ውሳኔ ጉባኤዎቹ እንዲያውቁት የተደረገው እንዴት ነው?

11 በኢየሩሳሌም ያለው የበላይ አካል በግርዘት ጉዳይ ላይ በአንድ ድምፅ ውሳኔ አስተላለፈ። ይሁን እንጂ በየጉባኤዎቹ ያሉት ወንድሞችም ስለ ጉዳዩ አንድ ዓይነት አቋም እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ ውሳኔው በግልጽ፣ አዎንታዊ በሆነና በሚያበረታታ መንገድ ሊነገራቸው ይገባል። ታዲያ ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከመላው ጉባኤ ጋር ሆነው ከመካከላቸው የተመረጡ ሰዎችን ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ በወንድሞች መካከል ግንባር ቀደም የሆኑትን በርስያን የሚባለውን ይሁዳንና ሲላስን ላኩ።” በተጨማሪም በአንጾኪያ፣ በሶርያና በኪልቅያ ባሉት ጉባኤዎች ውስጥ የሚነበብ ደብዳቤ በእነዚህ ሰዎች በኩል ላኩላቸው።—ሥራ 15:22-26

12, 13. (ሀ) ይሁዳና ሲላስ መላካቸው ምን ጥሩ ውጤት ነበረው? (ለ) የበላይ አካሉ የላከው ደብዳቤ ምን ጥሩ ውጤት አስገኝቷል?

12 ይሁዳና ሲላስ “በወንድሞች መካከል ግንባር ቀደም” እንደሆኑ ተገልጿል፤ በመሆኑም የበላይ አካሉ ተወካዮች የመሆን ሙሉ ብቃት ነበራቸው። ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር እነዚህ ሁለት ሰዎች መላካቸው የግርዘትን ጥያቄ መልስ ብቻ ሳይሆን ከበላይ አካሉ አዲስ መመሪያ ይዘው እንደመጡም ግልጽ ያደርጋል። እነዚህ “የተመረጡ ሰዎች” ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች ወዳሉባቸው ጉባኤዎች መሄዳቸው፣ ኢየሩሳሌም ባሉት አይሁዳውያን ክርስቲያኖችና ከአሕዛብ በመጡ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን አንድነት ያጠናክራል። በእርግጥም ይህ ጥበብና ፍቅር የተንጸባረቀበት ዝግጅት ነው! በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሰላምና ስምምነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እንዳደረገ ምንም ጥርጥር የለውም።

በዛሬው ጊዜ ያለው የበላይ አካል የተዋቀረው እንዴት ነው?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም የይሖዋን ሕዝቦች የሚመራ የበላይ አካል አለ፤ ይህ የበላይ አካል በመንፈስ የተቀቡ ታማኝ ወንድሞችን ያቀፈ ነው። የበላይ አካሉ በየሳምንቱ አንድ ላይ ይሰበሰባል። አባላቱም በሚከተሉት ስድስት ኮሚቴዎች የተደራጁ ሲሆን እያንዳንዱ ኮሚቴ የራሱ የሆነ የሥራ ድርሻ አለው።

  • የሕትመት ኮሚቴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የማተሙንና የማሰራጨቱን ሂደት በበላይነት ይከታተላል። የይሖዋ ምሥክሮች በሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ኮርፖሬሽኖች ይዞታ ሥር ያሉትንና ኮርፖሬሽኖቹ የሚገለገሉባቸውን የሕትመት መሣሪያዎችና ሌሎች ንብረቶች ይቆጣጠራል፤ በተጨማሪም የቅርንጫፍ ቢሮዎችን፣ የጉባኤ ስብሰባ አዳራሾችንና የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሾችን ግንባታ ይከታተላል። ይህ ኮሚቴ ለስብከቱ ሥራ የሚደረጉት መዋጮዎች ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ ይቆጣጠራል።

  • የትምህርት ኮሚቴ በወረዳ፣ በክልልና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ትምህርቶች ይከታተላል፤ እንዲሁም የድምፅና የቪዲዮ ቀረጻ ሥራዎችን ይመራል። ለጊልያድ ትምህርት ቤት፣ ለአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤትና ለሌሎች ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ይቀርጻል፤ በየቅርንጫፍ ቢሮው ለሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞችም የተለያዩ መንፈሳዊ ፕሮግራሞችን ያዘጋጃል።

  • የአስተባባሪዎች ኮሚቴ ሕግ ነክ ጉዳዮችን ይከታተላል፤ ሰዎች ስለ እምነታችን ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ደግሞ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በኃላፊነት ይመራል። በተጨማሪም በየትኛውም የምድር ክፍል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አደጋ፣ ስደት እንዲሁም ሌሎች ድንገተኛ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው አስፈላጊውን እርዳታ ይሰጣል።

  • የአገልግሎት ኮሚቴ የስብከቱን ሥራ በበላይነት ይከታተላል፤ ከጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ከወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ከሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም በዚህ ኮሚቴ ኃላፊነት ሥር ናቸው። በተጨማሪም ኮሚቴው፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጉባኤዎችን ለማነጽና ለማጠናከር ታስቦ በተዘጋጀው የጊልያድ ትምህርት ቤት ላይ የሚካፈሉ ተማሪዎችን ይጋብዛል፤ ከዚያም ተማሪዎቹን ወደተለያየ ቦታ ይመድባል።

  • የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ ለጉባኤዎችም ሆነ ለሕዝብ የሚዘጋጀውን መንፈሳዊ ምግብ በበላይነት ይከታተላል። ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፤ በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የትርጉም ሥራ ይከታተላል፤ እንዲሁም የድራማ ጽሑፎችን፣ የንግግር አስተዋጽኦዎችንና እንዲህ ያሉ ሌሎች ነገሮችን ገምግሞ ያጸድቃል።

  • የፐርሶኔል ኮሚቴ በዓለም ዙሪያ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚያገለግሉ የቤቴል ቤተሰብ አባላትን መንፈሳዊም ሆነ አካላዊ ደህንነት ለመጠበቅ የሚደረጉ ዝግጅቶችን በበላይነት ይከታተላል። ከዚህም ባሻገር አዳዲስ አባላትን በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ እንዲያገለግሉ ከመጋበዝ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይቆጣጠራል።

የበላይ አካሉ ሥራውን ሲያከናውን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አመራር ለማግኘት ጥረት ያደርጋል። አባላቱ ራሳቸውን የይሖዋ ሕዝቦች መሪዎች አድርገው አይቆጥሩም። ከዚህ ይልቅ ምድር ላይ እንዳሉት ሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሁሉ እነሱም ‘ምንጊዜም በጉን [ኢየሱስ ክርስቶስን] በሄደበት ሁሉ ይከተሉታል።’—ራእይ 14:4

13 ደብዳቤው ግርዘትን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ብቻ አይደለም፤ ከአሕዛብ የመጡት ክርስቲያኖች የይሖዋን ሞገስና በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግልጽ መመሪያ የያዘም ነበር። ደብዳቤው ላይ እንዲህ የሚል ቁልፍ ሐሳብ ተጠቅሷል፦ “ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር፣ ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና እኛ ወስነናል፦ ለጣዖት ከተሠዉ ነገሮች፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋና ከፆታ ብልግና ራቁ። ከእነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከራቃችሁ መልካም ይሆንላችኋል። ጤና ይስጣችሁ!”—ሥራ 15:28, 29

14. መከፋፈል በነገሠበት ዓለም ውስጥ የይሖዋ ሕዝቦች አንድነት ሊኖራቸው የቻለው እንዴት ነው?

14 በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ100,000 በላይ በሚሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ ከ8,000,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ፤ ይሁንና በእምነታቸውም ሆነ በድርጊታቸው ፍጹም አንድነት አላቸው። ሁከትና መከፋፈል በነገሠበት ዓለም ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አንድነት ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው? ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የጉባኤው ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ ይኸውም በበላይ አካሉ አማካኝነት የሚሰጠው ግልጽና የማያሻማ መመሪያ ነው። (ማቴ. 24:45-47) ሌላው ምክንያት ደግሞ ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር የበላይ አካሉ የሚሰጠውን መመሪያ በፈቃደኝነት መታዘዙ ነው።

“ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደሰቱ” (የሐዋርያት ሥራ 15:30-35)

15, 16. ግርዘትን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ የመጨረሻ ውጤት ምን ነበር? ይህ ጥሩ ውጤት እንዲገኝ ምክንያት የሆነውስ ምንድን ነው?

15 ከኢየሩሳሌም የተላኩት ወንድሞች አንጾኪያ ደረሱ፤ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ዘገባ ቀጥሎ የሆነውን ሲገልጽ “እዚያ የሚገኙትንም ደቀ መዛሙርት በአንድነት ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጧቸው” ይላል። ታዲያ በዚያ ያሉት ወንድሞች የበላይ አካሉ ላስተላለፈው መመሪያ ምን ምላሽ ሰጡ? “[ደብዳቤውን] ካነበቡት በኋላ ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደሰቱ።” (ሥራ 15:30, 31) በተጨማሪም ይሁዳና ሲላስ “ብዙ ቃል በመናገር ወንድሞችን አበረታቷቸው፤ እንዲሁም አጠናከሯቸው።” በዚህም የተነሳ እነዚህ ሁለት ሰዎች እንደ በርናባስ፣ ጳውሎስና ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ “ነቢያት” ተብለው ተጠርተዋል፤ ምክንያቱም ነቢይ የሚለው ቃል የአምላክን ፈቃድ ለሌሎች የሚያውጅን ወይም የሚያሳውቅን ሰው ያመለክታል።—ሥራ 13:1፤ 15:32፤ ዘፀ. 7:1, 2

16 ይሖዋ ለጉዳዩ ጥሩ እልባት ለመስጠት የተደረገውን ጥረት ሁሉ እንደባረከው ግልጽ ነው። ታዲያ ለዚህ ጥሩ ውጤት ቁልፉ ምን ነበር? የበላይ አካሉ ያስተላለፈው ግልጽና ወቅታዊ መመሪያ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ የአምላክን ቃልና የመንፈስ ቅዱስን አመራር መሠረት ያደረገ ውሳኔም ነው። የበላይ አካሉ ውሳኔው ለጉባኤዎቹ እንዲተላለፍ ያደረገበት መንገድም ለተገኘው ጥሩ ውጤት አስተዋጽኦ አድርጓል፤ የተመረጡ ወንድሞች ወደየጉባኤዎቹ ሄደው ውሳኔውን ፍቅርና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዲነግሯቸው አድርጓል።

17. የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጳውሎስ፣ በርናባስ፣ ይሁዳና ሲላስ የተዉትን ምሳሌ የሚከተሉት በምን መንገድ ነው?

17 ዛሬ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካልም ይህንኑ ምሳሌ በመከተል ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ወቅታዊ መመሪያ ያስተላልፋል። ውሳኔዎች በሚደረጉበት ጊዜ፣ ግልጽ በሆነና በማያሻማ መንገድ ጉባኤዎች እንዲያውቁት ይደረጋል። ይህ የሚደረግበት አንዱ መንገድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት ነው። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉት እነዚህ ወንድሞች የተለያዩ ጉባኤዎችን በመጎብኘት ግልጽ መመሪያዎችንና ማበረታቻዎችን ይሰጣሉ። ጳውሎስና በርናባስ እንዳደረጉት ሁሉ እነሱም “እያስተማሩና ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ሆነው ምሥራቹን ይኸውም የይሖዋን ቃል እየሰበኩ” በአገልግሎት ረጅም ሰዓት ያሳልፋሉ። (ሥራ 15:35) በተጨማሪም እንደ ይሁዳና እንደ ሲላስ “ብዙ ቃል በመናገር ወንድሞችን” ያበረታታሉ እንዲሁም ያጠናክራሉ።

18. የአምላክ ሕዝቦች የይሖዋ በረከት እንደማይለያቸው እርግጠኞች መሆን የሚችሉት ምን ካደረጉ ብቻ ነው?

18 ስለ ጉባኤዎችስ ምን ማለት ይቻላል? በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ በምድር ዙሪያ የሚገኙት ጉባኤዎች ሰላምና አንድነት እንዲኖራቸው ያደረገው ምንድን ነው? ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ቆየት ብሎ የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል፦ “ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ። . . . ከዚህም በላይ የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ይዘራል።” (ያዕ. 3:17, 18) ያዕቆብ ይህን የጻፈው በኢየሩሳሌም የተደረገውን ስብሰባ በአእምሮው ይዞ ይሁን አይሁን የምናውቀው ነገር የለም። ይሁንና አሁን ከመረመርነው የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ዘገባ የምንረዳው አንድ ነገር አለ፤ ይሖዋ ሊባርከን የሚችለው በመካከላችን አንድነትና የትብብር መንፈስ እስካለ ድረስ ብቻ ነው።

19, 20. (ሀ) በአንጾኪያ ጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት ሰፍኖ እንደነበር የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) አሁን ጳውሎስና በርናባስ በምን ላይ ማተኮር ይችላሉ?

19 አሁን በአንጾኪያ ጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት መስፈኑ በግልጽ ይታያል። የአንጾኪያ ወንድሞች ከኢየሩሳሌም ከመጡት ወንድሞች ጋር አልተከራከሩም፤ ከዚህ ይልቅ ይሁዳና ሲላስ መጥተው ስለጎበኟቸው ተደስተዋል። ምክንያቱም ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “በዚያም የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደላኳቸው ሰዎች [ወደ ኢየሩሳሌም] እንዲመለሱ ወንድሞች በሰላም አሰናበቷቸው።”d (ሥራ 15:33) በኢየሩሳሌም ያሉት ወንድሞችም፣ ሁለቱ ወንድሞች ስለ ጉዟቸው በሚነግሯቸው ነገር እንደሚደሰቱ ጥርጥር የለውም። የይሖዋ ጸጋ ስላልተለያቸው ተልእኳቸውን በደስታ አጠናቀው መመለስ ችለዋል!

20 አሁን የግርዘት ጉዳይ እልባት ስላገኘ ጳውሎስና በርናባስ ትኩረታቸውን በወንጌላዊነቱ ሥራ ላይ ማድረግ ይችላሉ፤ ዛሬ ያሉት የወረዳ የበላይ ተመልካቾችም ጉባኤዎችን ሲጎበኙ የሚያደርጉት ይህንኑ ነው። (ሥራ 13:2, 3) ይህ ለይሖዋ ሕዝቦች እንዴት ያለ በረከት ነው! ይሁንና ይሖዋ እነዚህን ሁለት ቀናተኛ ወንጌላውያን ይበልጥ የተጠቀመባቸውና የባረካቸው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይህን እንመለከታለን።

አንዲት እናትና ሴት ልጇ በትልቅ ስብሰባ ላይ፤ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች” የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 እየተመለከቱ።

በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በበላይ አካሉና በሚወክላቸው ወንድሞች አማካኝነት ከሚቀርቡላቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች ይጠቀማሉ

ያዕቆብ—‘የጌታ ወንድም’

ያዕቆብ የዮሴፍና የማርያም ልጅ ነው፤ ስለ ኢየሱስ ታናናሽ ወንድሞች ሲነሳ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው እሱ ነው። (ማቴ. 13:54, 55) በመሆኑም ያዕቆብ የማርያም ሁለተኛ ልጅ ሳይሆን አይቀርም። ያዕቆብ ከኢየሱስ ጋር አብሮ ያደገ ሲሆን አገልግሎቱን ሲያከናውንም ተመልክቷል፤ ደግሞም ኢየሱስ “ተአምራት” ሲፈጽም በዓይኑ የማየት አጋጣሚ ማግኘቱን እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ተአምራት እንደሚፈጽም ግን ያውቃል። ያም ሆኖ ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናውን በነበረበት ወቅት ያዕቆብም ሆነ ሌሎች ወንድሞቹ በታላቅ ወንድማቸው “አላመኑበትም ነበር።” (ዮሐ. 7:5) ምናልባትም ያዕቆብ፣ ኢየሱስ “አእምሮውን ስቷል” ብለው እንዳሰቡት የኢየሱስ ዘመዶች ተሰምቶት ሊሆን ይችላል።—ማር. 3:21

ያዕቆብ ከጥቅልል ላይ እያነበበ።

ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ግን ይህ ሁሉ ተቀየረ። ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ምድር ላይ በቆየባቸው 40 ቀናት ውስጥ ለያዕቆብ እንደተገለጠለት እናነባለን። እርግጥ ነው፣ በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያዕቆብ ተብለው የተጠሩ ሌሎች ሦስት ሰዎች አሉ፤ ይሄኛው ያዕቆብ ግን የኢየሱስ ወንድም ያዕቆብ እንደሆነ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። (1 ቆሮ. 15:7) ይህ አጋጣሚ የታላቅ ወንድሙን እውነተኛ ማንነት በትክክል እንዲገነዘብ ሳያደርገው አልቀረም። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ አሥር ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያዕቆብ፣ እናቱና ወንድሞቹ ከሐዋርያቱ ጋር ሆነው ደርብ ላይ ባለ አንድ ክፍል ውስጥ ለጸሎት ተሰብስበው ነበር።—ሥራ 1:13, 14

ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ ኢየሩሳሌም ባለው ጉባኤ ውስጥ ከፍተኛ አክብሮት አተረፈ፤ የዚያ ጉባኤ ሐዋርያ (ማለትም “የተላከ ሰው”) ተደርጎ መታየት የጀመረም ይመስላል። (ገላ. 1:18, 19) ሐዋርያው ጴጥሮስ በተአምር ከእስር ቤት ነፃ ከወጣ በኋላ “ይህን ነገር ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሯቸው” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ መናገሩ ለያዕቆብ የሚሰጠውን ላቅ ያለ ቦታ ይጠቁማል። (ሥራ 12:12, 17) የግርዘት ጉዳይ ኢየሩሳሌም ባሉት “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች” ፊት በቀረበበት ጊዜ ስብሰባውን የመራው ያዕቆብ ሳይሆን አይቀርም። (ሥራ 15:6-21) ሐዋርያው ጳውሎስም ያዕቆብ፣ ኬፋ (ጴጥሮስ) እና ሐዋርያው ዮሐንስ በኢየሩሳሌም በነበረው ጉባኤ ውስጥ “እንደ ዓምድ የሚታዩ” እንደሆኑ ገልጿል። (ገላ. 2:9) ሌላው ቀርቶ ከዓመታት በኋላ ጳውሎስ ሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን አጠናቆ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ሪፖርት ያደረገው ለያዕቆብ ነው፤ በዚህ ጊዜ “ሽማግሌዎቹም ሁሉ በዚያ ነበሩ።”—ሥራ 21:17-19

ጳውሎስ ‘የጌታ ወንድም’ በማለት የጠራው ይህ ያዕቆብ በስሙ የተጠራውን ደብዳቤ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ እንደጻፈ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። (ገላ. 1:19) በዚህ ደብዳቤ ላይ ያዕቆብ ራሱን ሲያስተዋውቅ ሐዋርያ ወይም የኢየሱስ ወንድም አላለም፤ ከዚህ ይልቅ “የአምላክና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ” በማለት ራሱን በትሕትና ጠርቷል። (ያዕ. 1:1) ያዕቆብ እንደ ኢየሱስ ሁሉ፣ ተፈጥሮንና የሰዎችን ባሕርይ በደንብ ያስተውል እንደነበር ከደብዳቤው መረዳት ይቻላል። መንፈሳዊ እውነቶችን በምሳሌ ለማስረዳት ተፈጥሮ ላይ የሚታዩ ነገሮችን ጠቅሷል፤ በነፋስ የሚናወጥ ባሕር፣ በከዋክብት የተሞላ ሰማይ፣ የሚያቃጥል ፀሐይ፣ የሚረግፍ አበባ፣ ሰደድ እሳት፣ የሚገሩ እንስሳት ከጠቀሳቸው ነገሮች መካከል ይገኙበታል። (ያዕ. 1:6, 11, 17፤ 3:5, 7) ያዕቆብ፣ ሰዎች ስለሚያሳዩት ዝንባሌና ድርጊት በአምላክ መንፈስ እርዳታ ጥልቅ ማስተዋል አግኝቶ ነበር፤ በመሆኑም ደብዳቤው ላይ የሰጣቸው ግሩም ምክሮች ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር ይረዳሉ።—ያዕ. 1:19, 20፤ 3:2, 8-18

በአንደኛ ቆሮንቶስ 9:5 ላይ የሰፈረው የጳውሎስ ሐሳብ ያዕቆብ ባለትዳር እንደነበር ይጠቁማል። መጽሐፍ ቅዱስ ያዕቆብ መቼና እንዴት እንደሞተ በግልጽ አይናገርም። ይሁንና አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ፣ ሮማዊው ገዢ ጶርቅዮስ ፊስጦስ በ62 ዓ.ም. ገደማ ከሞተና በምትኩ አልባይነስ ሥልጣን ከመጨበጡ በፊት የሆነውን ነገር ሲዘግብ እንዲህ ብሏል፦ “[ሊቀ ካህናቱ ሐና (ሐናንያ)] የሳንሄድሪንን ዳኞች ሰበሰበ፤ ክርስቶስ እየተባለ የሚጠራውን የኢየሱስን ወንድም ያዕቆብንና ሌሎች ሰዎችን በፊታቸው አቀረበ።” ጆሴፈስ እንደዘገበው ሐና “እነዚህን ሰዎች በሕግ ተላላፊነት ከወነጀላቸው በኋላ በድንጋይ እንዲወገሩ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል።”

a “ያዕቆብ—‘የጌታ ወንድም’” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b ያዕቆብ ከሙሴ መጻሕፍት ላይም ማጣቀሱ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው። እነዚህ መጻሕፍት ሕጉን ብቻ ሳይሆን ከሕጉ በፊት አምላክ ከሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጹ ዘገባዎችን ይዘዋል፤ ዘገባዎቹ፣ የሙሴ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት የአምላክ ፈቃድ ምን እንደነበረ ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ስለ ደም፣ ስለ ምንዝርና ስለ ጣዖት አምልኮ ያለው አመለካከት በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ሰፍሯል። (ዘፍ. 9:3, 4፤ 20:2-9፤ 35:2, 4) በመሆኑም ይሖዋ አይሁዳዊ፣ አሕዛብ ሳይል መላው የሰው ዘር ሊጠብቃቸው የሚገቡ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቷል።

c “በዛሬው ጊዜ ያለው የበላይ አካል የተዋቀረው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

d አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቁጥር 34 ላይ ሲላስ በአንጾኪያ ለመቅረት እንደወሰነ የሚገልጽ ሐሳብ አስገብተዋል። (ለምሳሌ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ይሁንና ይህ ሐሳብ ከጊዜ በኋላ የተጨመረ ሳይሆን አይቀርም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ