የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bm ክፍል 7 ገጽ 10
  • አምላክ እስራኤላውያንን ነፃ አወጣቸው

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ እስራኤላውያንን ነፃ አወጣቸው
  • መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው?
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የይሖዋን መንገድ መማር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ሙሴ ይሖዋን ለማምለክ መረጠ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • ሙሴና አሮን ፈርዖንን አነጋገሩት
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
  • የዘፀአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
ለተጨማሪ መረጃ
መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው?
bm ክፍል 7 ገጽ 10
ሙሴ አሥሩ ትእዛዛት የሰፈሩባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ይዞ

ክፍል 7

አምላክ እስራኤላውያንን ነፃ አወጣቸው

ይሖዋ ግብፅን በተለያዩ መቅሰፍቶች ሲመታ ሙሴ የእስራኤልን ልጆች እየመራ ከዚያ አወጣቸው። አምላክ በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን ሕግ ሰጣቸው

የእስራኤል ልጆች በግብፅ ውስጥ ለብዙ ዓመታት የኖሩ ሲሆን ቁጥራቸው እየጨመረና እየበለጸጉ ሄዱ። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ሌላ ፈርዖን ሥልጣን ያዘ። ይህ ንጉሥ ዮሴፍን አያውቀውም ነበር። እስራኤላውያን መብዛታቸው ያስፈራው ይህ አረመኔና አምባገነን ገዥ፣ እነዚህን ሕዝቦች ባሪያዎች ያደረጋቸው ከመሆኑም በላይ የሚወልዷቸው ወንዶች ልጆች በሙሉ አባይ ወንዝ ውስጥ ተጥለው እንዲሞቱ አዘዘ። ይሁንና ደፋር የሆነች አንዲት እናት፣ ሕፃን ልጇን በቅርጫት ውስጥ አስቀምጣ በወንዙ ዳር ባለው ቄጠማ መካከል በመደበቅ እንዳይገደል አደረገች። የፈርዖን ሴት ልጅ ይህን ሕፃን አገኘችው፤ እሷም ሕፃኑን ሙሴ ብላ የሰየመችው ሲሆን በግብፅ የንጉሣውያን ቤተሰብ መካከል አሳደገችው።

ሙሴ 40 ዓመት ሲሞላው፣ አንድን እስራኤላዊ ጨቋኝ ከሆነው ግብፃዊ አሠሪው ለማዳን ባደረገው ጥረት ችግር ውስጥ ገባ። በዚህም የተነሳ ከግብፅ ሸሽቶ ሩቅ አገር በመሄድ በግዞት መኖር ጀመረ። ሙሴ 80 ዓመት ሲሆነው ፈርዖን ፊት ቀርቦ የአምላክን ሕዝቦች እንዲለቃቸው እንዲጠይቅ ይሖዋ ወደ ግብፅ ላከው።

ፈርዖን ግን እስራኤላውያንን ለመልቀቅ አሻፈረኝ አለ። በዚህም ምክንያት አምላክ ግብፅን በአሥር መቅሠፍቶች መታ። እያንዳንዱ መቅሠፍት ከመምጣቱ በፊት ፈርዖን ሐሳቡን እንዲቀይርና ሌላ መቅሠፍት እንዳይመጣባቸው የማድረግ አጋጣሚ እንዲያገኝ ሲል ሙሴ በፊቱ ቀርቦ ቢያነጋግረውም ፈርዖን እሱንም ሆነ የላከውን አምላክ ባለመስማት በእምቢተኝነቱ ገፋበት። በመጨረሻም በአሥረኛው መቅሠፍት በአገሪቱ የነበሩት የበኩር ልጆች በሙሉ ሞቱ፤ በዚህ መቅሠፍት ያልተነኩት መሥዋዕት የሆነውን ጠቦት ደም በበሮቻቸው መቃንና ጉበኖች ላይ በመቀባት ይሖዋን የታዘዙት ቤተሰቦች ብቻ ነበሩ። የበኩር ልጆችን እንዲያጠፋ አምላክ የላከው መልአክ እነዚህን ቤተሰቦች ሳይነካቸው አለፈ። ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን አስደናቂ በሆነ መንገድ የዳኑበትን ይህን ቀን ለማሰብ ፋሲካ ተብሎ የሚጠራውን በዓል በየዓመቱ ማክበር ጀመሩ።

ፈርዖን የበኩር ልጁ ከሞተ በኋላ ሙሴም ሆነ እስራኤላውያን በሙሉ ግብፅን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ። ወዲያውኑ ሥፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብ ከግብፅ ወጣ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ፈርዖን ሐሳቡን ለወጠ። ብዙ ጦረኞችንና ሠረገሎችን አስከትሎ እስራኤላውያንን ያሳድዳቸው ጀመር። እስራኤላውያን የቀይ ባሕር ዳርቻ ጋ ሲደርሱ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ይመስል ነበር። ሆኖም ይሖዋ ቀይ ባሕርን በመክፈል ውኃው በቀኝና በግራ እንደ ግድግዳ እንዲቆምና ሕዝቡ በባሕሩ መካከል በደረቅ መሬት ላይ እንዲሻገሩ አደረገ! ግብፃውያን ከኋላቸው ተከትለው ወደ ባሕሩ ሲገቡ አምላክ ውኃውን ወደ ቦታው እንዲመለስ ስላደረገው ፈርዖንና ሠራዊቱ ሰጠሙ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን በሲና ተራራ አጠገብ ሲሰፍሩ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባ። አምላክ ሙሴን እንደ መካከለኛ በመጠቀም ለእስራኤላውያን በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፎች መመሪያና ጥበቃ የሚሆኗቸውን ሕጎች ሰጣቸው። ሕዝቡ የአምላክን አመራር በታማኝነት እስከተቀበሉ ድረስ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ይሆናል፤ እንዲሁም ብሔሩን ለሌሎች ሕዝቦች በረከት እንዲሆን ያደርገዋል።

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ እስራኤላውያን እምነት የለሾች በመሆን አምላክን አሳዘኑት። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ያንን ትውልድ ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ እንዲንከራተት አደረገው። ከዚያም ሙሴ፣ ጻድቅ ሰው የነበረውን ኢያሱን በእሱ ምትክ ሕዝቡን እንዲመራ ሾመው። በመጨረሻም እስራኤላውያን፣ አምላክ ለአብርሃም ቃል ገብቶለት ወደነበረው ምድር ለመግባት ዝግጁ ሆኑ።

—በዘፀአት፤ በዘሌዋውያን፤ በዘኍልቍና በዘዳግም መጻሕፍት እንዲሁም በመዝሙር 136:10-15 እና በሐዋርያት ሥራ 7:17-36 ላይ የተመሠረተ።

  • አምላክ እስራኤላውያንን ነፃ ለማውጣት በሙሴ የተጠቀመው እንዴት ነበር?

  • የፋሲካ በዓል የሚከበረው ለምን ነበር?

  • ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ያወጣቸው እንዴት ነበር?

ከሁሉ የሚበልጠው ሕግ

አምላክ በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን ከሰጣቸው 600 ያህል ሕጎች መካከል በብዙዎች ዘንድ ይበልጥ የሚታወቁት በዘፀአት 20:1-17 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት አሥርቱ ትእዛዛት ሳይሆኑ አይቀሩም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአምላክ ሕጎች መካከል ከሁሉ የሚበልጠው የትኛው እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” የሚለውን ሕግ መርጧል።—ማርቆስ 12:28-30፤ ዘዳግም 6:5

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ