-
ክፍል 1፦ የክርስትና ትምህርቶችየይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
-
-
መጠመቅ ለሚፈልጉ የቀረቡ ጥያቄዎች
ክፍል 1፦ የክርስትና ትምህርቶች
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ እውነትን እንድታውቅ አስችሎሃል። ያገኘኸው ትምህርት ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖርህ እንዲሁም በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወትና ሌሎች በረከቶች የመውረስ ተስፋ አስገኝቶልሃል። በአምላክ ቃል ላይ ያለህ እምነት ተጠናክሯል፤ እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በመታቀፍህ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ብዙ በረከቶችን አግኝተሃል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሕዝቦቹን የሚይዝበትን መንገድ መገንዘብ ችለሃል።—ዘካ. 8:23
ለመጠመቅ እየተዘጋጀህ ስለሆነ ክርስቲያኖች ስለሚያምኑባቸው መሠረታዊ ትምህርቶች ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር መወያየትህ ይጠቅምሃል። (ዕብ. 6:1-3) ይሖዋ እሱን ለማወቅ የምታደርገውን ጥረት ሁሉ ይባርክልህ፤ እንዲሁም ቃል የገባውን ሽልማት ለመውረስ ያብቃህ።—ዮሐ. 17:3
1. መጠመቅ የምትፈልገው ለምንድን ነው?
2. ይሖዋ ማን ነው?
• “በላይ በሰማይም ሆነ በታች በምድር እውነተኛው አምላክ፣ ይሖዋ እንደሆነ ዛሬ እወቅ፤ እንዲሁም ልብ በል። ሌላ ማንም የለም።”—ዘዳ. 4:39
• “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል [ነህ]።”—መዝ. 83:18
3. አምላክን በግል ስሙ መጥራትህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• “እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።’”—ማቴ. 6:9
• “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”—ሮም 10:13
4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋን ለመግለጽ የተሠራባቸው አንዳንድ አገላለጾች የትኞቹ ናቸው?
• “የምድር ዳርቻዎች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነው።”—ኢሳ. 40:28
• “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ።”—ማቴ. 6:9
• “አምላክ ፍቅር ነው።”—1 ዮሐ. 4:8
5. ለይሖዋ አምላክ ልትሰጠው የምትችለው ምንድን ነው?
• “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።”—ማር. 12:30
• “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ።”—ሉቃስ 4:8
6. ለይሖዋ ታማኝ መሆን የምትፈልገው ለምንድን ነው?
• “ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ መልስ መስጠት እችል ዘንድ ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው።”—ምሳሌ 27:11
7. የምትጸልየው ወደ ማን ነው? የምትጸልየውስ በማን ስም ነው?
• “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብን ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትጠይቁት ይሰጣችኋል።”—ዮሐ. 16:23
8. ስለ ምን ነገሮች ልትጸልይ ትችላለህ?
• “እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም። የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን፤ የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር በለን። ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’”—ማቴ. 6:9-13
• “በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።”—1 ዮሐ. 5:14
9. ይሖዋ የአንድን ሰው ጸሎት እንዳይሰማ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
• “እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስላቸውም። ክፉ ድርጊት በመፈጸማቸው፣ በዚያን ጊዜ ፊቱን ይሰውርባቸዋል።”—ሚክ. 3:4
• “የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ ጆሮዎቹም ምልጃቸውን ይሰማሉ፤ የይሖዋ ፊት ግን ክፉ ነገሮችን በሚያደርጉ ላይ ነው።”—1 ጴጥ. 3:12
10. ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?
• “ስምዖን ጴጥሮስም ‘አንተ ክርስቶስ፣ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ’ ብሎ መለሰለት።”—ማቴ. 16:16
11. ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለምንድን ነው?
• “የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም።”—ማቴ. 20:28
• “[ኢየሱስ] ግን ‘ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው’ አላቸው።”—ሉቃስ 4:43
12. ለኢየሱስ መሥዋዕት ያለህን አድናቆት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
• “በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ እሱ ለሁሉም ሞቷል።”—2 ቆሮ. 5:15
13. ኢየሱስ ምን ሥልጣን አለው?
• “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል።”—ማቴ. 28:18
• “አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው።”—ፊልጵ. 2:9
14. የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል በኢየሱስ የተሾመው “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሆነ ታምናለህ?
• “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?”—ማቴ. 24:45
15. መንፈስ ቅዱስ የራሱ ማንነት ያለው አካል ነው?
• “መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ ‘መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል። ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስና የአምላክ ልጅ ይባላል።’”—ሉቃስ 1:35
• “ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባትማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!”—ሉቃስ 11:13
16. ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን የተጠቀመበት እንዴት ነው?
• “ሰማያት በይሖዋ ቃል፣ በውስጣቸው ያሉትም ሁሉ ከአፉ በሚወጣው መንፈስ ተሠሩ።”—መዝ. 33:6
• “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ . . . እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።”—ሥራ 1:8
• “በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያለው ትንቢት ሁሉ በሰው ሐሳብ ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው ተናገሩ።”—2 ጴጥ. 1:20, 21
17. የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
• “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይጠፋ መንግሥት ያቋቁማል። ይህም መንግሥት ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም። እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።”—ዳን. 2:44
18. የአምላክ መንግሥት ምን በረከት ያስገኝልሃል?
• “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:4
19. የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸው በረከቶች በቅርቡ እውን እንደሚሆኑ እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?
• “ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ መጥተው ‘እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?’ አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ ‘. . . ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል። ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።’”—ማቴ. 24:3, 4, 7, 14
• “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ለአምላክ ያደሩ መስለው ይታያሉ፤ በሥራቸው ግን ኃይሉን ይክዳሉ።”—2 ጢሞ. 3:1-5
20. በሕይወትህ ውስጥ ለአምላክ መንግሥት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
• “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ።”—ማቴ. 6:33
• “ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ ‘ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።’”—ማቴ. 16:24
21. ሰይጣን ማን ነው? አጋንንትስ እነማን ናቸው?
• “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ . . . እሱ በራሱ መንገድ መሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነፍሰ ገዳይ ነበር።”—ዮሐ. 8:44
• “ታላቁ ዘንዶ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ።”—ራእይ 12:9
22. ሰይጣን በይሖዋና ይሖዋን በሚያመልኩ ሰዎች ላይ ምን ክስ ሰንዝሯል?
• “ሴቲቱ እባቡን እንዲህ አለችው፦ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን። ይሁንና በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሚገኘውን ዛፍ ፍሬ በተመለከተ አምላክ “ከእሱ አትብሉ፤ ፈጽሞም አትንኩት፤ አለዚያ ትሞታላችሁ” ብሏል።’ በዚህ ጊዜ እባቡ ሴቲቱን እንዲህ አላት፦ ‘መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም። አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።’”—ዘፍ. 3:2-5
• “ሰይጣን እንዲህ ሲል ለይሖዋ መለሰ፦ ‘ቁርበት ስለ ቁርበት ነው። ሰውም ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል።’”—ኢዮብ 2:4
23. ሰይጣን የሚሰነዝረው ክስ ሐሰት መሆኑን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
• “በሙሉ ልብ [አምላክን] አገልግለው።”—1 ዜና 28:9
• “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!”—ኢዮብ 27:5
24. ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?
• “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።”—ሮም 5:12
25. የሞቱ ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?
• “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም።”—መክ. 9:5
26. የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?
• “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት [ይነሳሉ]።”—ሥራ 24:15
27. ወደ ሰማይ ሄደው ከኢየሱስ ጋር የሚገዙት ሰዎች ምን ያህል ናቸው?
• “እነሆ፣ በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሟል፤ ከእሱም ጋር የእሱ ስምና የአባቱ ስም በግንባራቸው ላይ የተጻፈባቸው 144,000 ነበሩ።”—ራእይ 14:1
-
-
ክፍል 2፦ የክርስትና ሕይወትየይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
-
-
መጠመቅ ለሚፈልጉ የቀረቡ ጥያቄዎች
ክፍል 2፦ የክርስትና ሕይወት
መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምን እንደሆነና የጽድቅ መሥፈርቶቹን እንዴት ማሟላት እንደምትችል ተምረሃል። የተማርከውን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል ስትል ለሕይወት ያለህን አመለካከትም ሆነ ሥነ ምግባርህን በተወሰነ ደረጃ ማስተካከል አስፈልጎህ ይሆናል። አሁን ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ በማድረግህ የምሥራቹ አገልጋይ ሆነህ ተቀባይነት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ በሚያስችል ሁኔታ ላይ ትገኛለህ።
ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች መከለስህ ይሖዋ ያወጣቸው የጽድቅ መሥፈርቶች አእምሮህ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ እንዲቀረጹ ለማድረግ የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ የእሱን ተቀባይነት ካገኙት አገልጋዮቹ አንዱ ለመሆን ልታደርጋቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮችን እንድታስታውስ ይረዳሃል። እዚህ ላይ የቀረበው ሐሳብ ሁሉንም ነገር በንጹሕ ሕሊናና ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ የማድረግን አስፈላጊነት እንድትገነዘብ ያስችልሃል።—2 ቆሮ. 1:12፤ 1 ጢሞ. 1:19፤ 1 ጴጥ. 3:16, 21
በጥናትህ ገፍተህ እዚህ ደረጃ ላይ ስለደረስክ በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ ለማበርከትና ለይሖዋ አመራር ተገዢ ለመሆን እንደምትጓጓ ጥርጥር የለውም። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ጥያቄዎችና ጥቅሶች ከጉባኤ አደረጃጀት፣ ከቤተሰብ ሕይወትና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በተያያዘ ይሖዋ ለሰጠው መመሪያ የምታሳየውን ተገዢነት በተመለከተ ግንዛቤህን እንድትመረምር ይረዱሃል። በተጨማሪም ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ለማስተማርና ለመገንባት ላደረገው ዝግጅት ያለህ አድናቆት እንዲጨምር እንደሚረዳህ ምንም ጥያቄ የለውም። ይሖዋ ሕዝቡን ከሚያስተምርባቸው መንገዶች መካከል የጉባኤ ስብሰባዎች የሚገኙበት ሲሆን አንተም በተቻለህ መጠን በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብሃል።
ከዚህም ሌላ ይህ ክፍል በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ቋሚ የሆነ ተሳትፎ በማድረግ ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁና ለሰው ልጆች እያደረገ ያለውን ነገር እንዲገነዘቡ የመርዳትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) በመጨረሻም ራስህን ለይሖዋ አምላክ ስትወስንና ስትጠመቅ የገባኸው ቃል ምን ያህል ክብደት እንዳለው እንድትገነዘብ ያስችልሃል። ይሖዋ፣ እሱ ላሳየህ ጸጋ የሰጠኸውን ከልብ የመነጨ ምላሽ እንደሚያደንቅ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
1. ጋብቻን በተመለከተ ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባው መሥፈርት ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ለመፍታት የሚያስችለው ብቸኛው ምክንያት ምንድን ነው?
• “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም? ‘ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ብሎ እንደተናገረስ አላነበባችሁም? በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው። . . . በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።”—ማቴ. 19:4-6, 9
2. አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንደ ባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ከሆነ ሕጋዊ ጋብቻ መፈጸም ያለባቸው ለምንድን ነው? ያገባህ ከሆንክ ጋብቻህ ሕጋዊና በመንግሥት ዘንድ እውቅና ያለው ነው?
• “ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንዲገዙና እንዲታዘዙ . . . አሳስባቸው።”—ቲቶ 3:1
• “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን፤ አምላክ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ይፈርድባቸዋልና።”—ዕብ. 13:4
3. በቤተሰብ ውስጥ ያለህ ድርሻ ምንድን ነው?
• “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ተግሣጽ አዳምጥ፤ የእናትህንም መመሪያ አትተው።”—ምሳሌ 1:8
• “ክርስቶስ [የጉባኤው] ራስ እንደሆነ ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ ነው። ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደ . . . ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።”—ኤፌ. 5:23, 25
• “አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።”—ኤፌ. 6:4
• “ልጆች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ ጌታን ያስደስተዋልና።”—ቆላ. 3:20
• “እናንተ ሚስቶች፣ . . . ለባሎቻችሁ ተገዙ።”—1 ጴጥ. 3:1
4. ለሕይወት አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
• “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው [አምላክ ነው]። . . . ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው።”—ሥራ 17:25, 28
5. በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ ጨምሮ የማንንም ሰው ሕይወት ማጥፋት የሌለብን ለምንድን ነው?
• “ሰዎች እርስ በርስ ሲታገሉ በአንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ላይ ጉዳት ቢያደርሱባትና . . . ለሞት የተዳረገ ካለ ሕይወት ስለ ሕይወት . . . እንዲመለስ ማድረግ አለብህ።”—ዘፀ. 21:22, 23, 25
• “ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤ የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ፤ አንዳቸውም ወደ ሕልውና ከመምጣታቸው በፊት፣ የተሠሩባቸውን ቀኖች በተመለከተ በዝርዝር ተጻፈ።”—መዝ. 139:16
• “ይሖዋ . . . ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች [ይጠላል]።”—ምሳሌ 6:16, 17
6. አምላክ ደምን በተመለከተ ምን ትእዛዝ ሰጥቷል?
• “ከደም [እና] ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ . . . ራቁ።”—ሥራ 15:29
7. ክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?
• “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐ. 13:34, 35
8. ተላላፊ በሆነና ለሞት ሊዳርግ በሚችል በሽታ የተያዘ ሰው በሽታውን ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳያስተላልፍ (ሀ) ሌሎችን ማቀፍና መሳም የሌለበት ለምንድን ነው? (ለ) አንዳንዶች ቤታቸው ሳይጋብዙት ቢቀሩ ቅር መሰኘት የሌለበት ለምንድን ነው? (ሐ) ተላላፊ ለሆነ በሽታ በሚያጋልጥ ሁኔታ ውስጥ የነበረ ሰው ለጋብቻ መጠናናት ከመጀመሩ በፊት በራሱ ፈቃድ የደም ምርመራ ማድረግ ያለበት ለምንድን ነው? (መ) ተላላፊ በሽታ የያዘው ሰው ከመጠመቁ በፊት ሁኔታውን ለሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ማሳወቅ ያለበት ለምንድን ነው?
• “እርስ በርስ ከመዋደድ በቀር በማንም ላይ ምንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ . . . ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ። . . . ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም።”—ሮም 13:8-10
• “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵ. 2:4
9. ይሖዋ ሌሎችን ይቅር እንድንል የሚጠብቅብን ለምንድን ነው?
• “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።”—ቆላ. 3:13
10. አንድ ወንድም ስምህን ቢያጠፋ ወይም ቢያጭበረብርህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
• “ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ጥፋቱን በግልጽ ንገረው። ከሰማህ ወንድምህን ታተርፋለህ። የማይሰማህ ከሆነ ግን ማንኛውም ጉዳይ ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል ስለሚጸና አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ ሂድ። እነሱንም ካልሰማ ለጉባኤ ተናገር። ጉባኤውንም እንኳ የማይሰማ ከሆነ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ አድርገህ ቁጠረው።”—ማቴ. 18:15-17
11. ይሖዋ ለሚከተሉት የኃጢአት ድርጊቶች ምን አመለካከት አለው?
▪ የፆታ ብልግና
▪ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም
▪ ግብረ ሰዶም
▪ ስርቆት
▪ ቁማር
▪ ስካር
• “አትታለሉ፤ ሴሰኞችም ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ግብረ ሰዶማውያን ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።”—1 ቆሮ. 6:9, 10
12. ከጋብቻ ውጭ የሚፈጸሙ የተለያዩ ፆታዊ ድርጊቶችን የሚጨምረውን የፆታ ብልግናን በተመለከተ ቁርጥ አቋምህ ምንድን ነው?
• “ከፆታ ብልግና ሽሹ!”—1 ቆሮ. 6:18
13. ለሕክምና ካልሆነ በቀር ሱስ የሚያስይዙ ወይም አስተሳሰብን የሚያዛቡ ተፈጥሯዊም ሆኑ ሰው ሠራሽ ንጥረ ነገሮችን ከመውሰድ መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?
• “ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ]፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው። በተጨማሪም ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።”—ሮም 12:1, 2
14. አምላክ ከሚከለክላቸው አጋንንታዊ ድርጊቶች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
• “ሟርተኛ፣ አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ።”—ዘዳ. 18:10, 11
15. አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ቢሠራና የይሖዋን ሞገስ መልሶ ማግኘት ቢፈልግ ወዲያውኑ ምን ማድረግ ይኖርበታል?
• “ኃጢአቴን ለአንተ ተናዘዝኩ፤ ስህተቴን አልሸፋፈንኩም። ‘የፈጸምኳቸውን በደሎች ለይሖዋ እናዘዛለሁ’ አልኩ።”—መዝ. 32:5
• “ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ፤ እነሱም በይሖዋ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ይሖዋም ያስነሳዋል። በተጨማሪም ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባላል።”—ያዕ. 5:14, 15
16. አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ብታውቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
• “አንድ ሰው ሰዎች የምሥክርነት ቃል እንዲሰጡ ጥሪ እየቀረበ መሆኑን ቢሰማና እሱ መመሥከር እየቻለ ወይም ደግሞ ጉዳዩን አይቶ አሊያም አውቆ ሳለ ሳይናገር ቢቀር በሠራው ጥፋት ይጠየቅበታል።”—ዘሌ. 5:1
17. አንድ ሰው ከእንግዲህ በኋላ የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆነ ማስታወቂያ ቢነገር ከዚህ ሰው ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ምን ማስተካከያ ማድረግ አለብን?
• “ወንድም ተብሎ እየተጠራ ሴሰኛ ወይም ስግብግብ ወይም ጣዖት አምላኪ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካራም ወይም ቀማኛ ከሆነ ማንኛውም ሰው ጋር መግጠማችሁን [ተዉ]።”—1 ቆሮ. 5:11
• “ማንም ሰው ወደ እናንተ ቢመጣና ይህን ትምህርት ይዞ ባይመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ወይም ሰላም አትበሉት።”—2 ዮሐ. 10
18. ጓደኛ የምታደርጋቸው ሰዎች ይሖዋን የሚወዱ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?
• “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል።”—ምሳሌ 13:20
• “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።”—1 ቆሮ. 15:33
19. የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ የሆኑት ለምንድን ነው?
• “እኔ [ኢየሱስ] የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።”—ዮሐ. 17:16
20. የመንግሥት ባለሥልጣናትን መታዘዝ ያለብህ ለምንድን ነው?
• “ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ፤ ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነውና፤ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው።”—ሮም 13:1
21. አንድ ሰብዓዊ ሕግ ከአምላክ ሕግ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ ምን ታደርጋለህ?
• “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል።”—ሥራ 5:29
22. የምትመርጠው ሥራ ከዚህ ዓለም ጋር የሚያነካካህ እንዳይሆን የሚረዱህ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው?
• “አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ሰይፍ አያነሳም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም።”—ሚክ. 4:3
• “ሕዝቤ ሆይ፣ የኃጢአቷ ተባባሪ መሆን የማትፈልጉና የሚደርስባት መቅሰፍት ተካፋይ መሆን የማትፈልጉ ከሆነ ከእሷ [ከታላቂቱ ባቢሎን] ውጡ።”—ራእይ 18:4
23. የምትመርጠው መዝናኛ ምን ዓይነት ሊሆን ይገባል? ከየትኞቹ መዝናኛዎችስ ልትርቅ ይገባል?
• “ይሖዋ . . . ዓመፅን የሚወድን ማንኛውንም ሰው ይጠላል።”—መዝ. 11:5
• “ክፉ የሆነውን ተጸየፉ፤ ጥሩ የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ።”—ሮም 12:9
• “እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን አታቋርጡ።”—ፊልጵ. 4:8
24. የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች የሃይማኖት ቡድኖች ጋር በአምልኮ ሥርዓት መካፈላቸው ተገቢ የማይሆነው ለምንድን ነው?
• “‘ከይሖዋ ማዕድ’ እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል አትችሉም።”—1 ቆሮ. 10:21
• “‘ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ርኩስ የሆነውንም ነገር አትንኩ’፤ ‘እኔም እቀበላችኋለሁ።’”—2 ቆሮ. 6:17
25. አንድን በዓል ማክበር ይኖርብህ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የሚረዱህ የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?
• “በዚያ ከነበሩት ብሔራት ጋር ተቀላቀሉ፤ የእነሱንም መንገድ ተከተሉ። ጣዖቶቻቸውን አመለኩ፤ እነሱም ወጥመድ ሆኑባቸው።”—መዝ. 106:35, 36
• “ሙታን . . . ምንም አያውቁም።”—መክ. 9:5
• “እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።”—ዮሐ. 17:16
• “ዓይን ባወጣ ምግባር፣ ልቅ በሆነ የሥጋ ፍላጎት፣ ከልክ በላይ በመጠጣት፣ መረን በለቀቀ ድግስ፣ በመጠጥ ግብዣዎችና በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ በመካፈል የአሕዛብን ፈቃድ የፈጸማችሁበት ያለፈው ጊዜ ይበቃል።”—1 ጴጥ. 4:3
26. የልደት በዓልን ማክበር ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የሚረዱህ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?
• “ሦስተኛው ቀን ደግሞ ፈርዖን የልደት በዓሉን የሚያከብርበት ዕለት ነበር፤ እሱም ለአገልጋዮቹ በሙሉ ግብዣ አዘጋጀ። አገልጋዮቹ ባሉበትም የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃና የዳቦ ጋጋሪዎቹን አለቃ ከእስር ቤት አስወጣቸው። የመጠጥ አሳላፊዎቹንም አለቃ ወደ መጠጥ አሳላፊነት ሹመቱ መለሰው። . . . የዳቦ ጋጋሪዎቹን አለቃ ግን . . . ሰቀለው።”—ዘፍ. 40:20-22
• “የሄሮድስ ልደት በተከበረበት ዕለት የሄሮድያዳ ልጅ በግብዣው ላይ በመጨፈር ሄሮድስን እጅግ ደስ አሰኘችው፤ በመሆኑም የጠየቀችውን ሁሉ ሊሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። ከዚያም እናቷ በሰጠቻት ምክር መሠረት ‘የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በዚህ ሳህን ስጠኝ’ አለችው። ሰው ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ ቤት አስቆረጠ።”—ማቴ. 14:6-8, 10
27. ሽማግሌዎች የሚሰጡትን አመራር እንድትከተል የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?
• “ተግተው ስለሚጠብቋችሁና ይህን በተመለከተ ስሌት ስለሚያቀርቡ በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ፤ ይህን የምታደርጉት ሥራቸውን በደስታ እንጂ በሐዘን እንዳያከናውኑ ነው፤ አለዚያ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በሐዘን ይሆናል፤ ይህ ደግሞ እናንተን ይጎዳችኋል።”—ዕብ. 13:17
28. አንተም ሆንክ ቤተሰብህ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትራችሁ የምታነብቡበትና የምታጠኑበት ጊዜ መመደባችሁ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• “በይሖዋ ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል። በጅረቶች ዳር እንደተተከለ፣ ፍሬውን በወቅቱ እንደሚሰጥ፣ ቅጠሉም እንደማይጠወልግ ዛፍ ይሆናል። የሚሠራውም ሁሉ ይሳካለታል።”—መዝ. 1:2, 3
29. በስብሰባዎች ላይ መገኘትና ተሳትፎ ማድረግ የሚያስደስትህ ለምንድን ነው?
• “ስምህን ለወንድሞቼ አሳውቃለሁ፤ በጉባኤ መካከልም አወድስሃለሁ።”—መዝ. 22:22
• “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።”—ዕብ. 10:24, 25
30. ኢየሱስ የሰጠን ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሥራ ምንድን ነው?
• “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ . . . እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴ. 28:19, 20
31. የመንግሥቱን ሥራ ወይም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመደገፍ መዋጮ ስናደርግ የትኛውን ዝንባሌ ማሳየታችን ይሖዋን ያስደስተዋል?
• “ባሉህ ውድ ነገሮች . . . ይሖዋን አክብር።”—ምሳሌ 3:9
• “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።”—2 ቆሮ. 9:7
32. ክርስቲያኖች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው ይጠብቃሉ?
• “ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና። በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁና ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ። በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።”—ማቴ. 5:10-12
33. ተጠምቆ ከይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ መቆጠር ልዩ መብት የሆነው ለምንድን ነው?
• “ይሖዋ ሆይ፣ በስምህ ተጠርቻለሁና፣ ቃልህ ሐሴት፣ ለልቤም ደስታ ሆነልኝ።”—ኤር. 15:16
-
-
ከጥምቀት ዕጩዎች ጋር የሚደረግ የመደምደሚያ ውይይትየይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
-
-
መጠመቅ ለሚፈልጉ የቀረቡ ጥያቄዎች
ከጥምቀት ዕጩዎች ጋር የሚደረግ የመደምደሚያ ውይይት
የጥምቀት ሥነ ሥርዓት በአብዛኛው የሚከናወነው በይሖዋ ምሥክሮች የወረዳና የክልል ስብሰባዎች ላይ ነው። በጥምቀት ንግግሩ መደምደሚያ ላይ ተናጋሪው የጥምቀት ዕጩዎቹ ከተቀመጡበት እንዲነሱና ለሚከተሉት ሁለት ጥያቄዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መልስ እንዲሰጡ ይጠይቃቸዋል፦
1. ከኃጢአታችሁ ንስሐ በመግባት፣ ራሳችሁን ለይሖዋ በመወሰንና ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያደረገውን የመዳን ዝግጅት በመቀበል ለመጠመቅ ዝግጁ ሆናችኋል?
2. መጠመቃችሁ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ከታቀፉት የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ እንደሚያስቆጥራችሁ ተገንዝባችኋል?
የጥምቀት ዕጩዎቹ ለእነዚህ ጥያቄዎች ‘አዎ’ የሚል መልስ መስጠታቸው በቤዛው ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ መወሰናቸውን ‘በይፋ የሚናገሩበት’ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ሮም 10:9, 10) በመሆኑም የጥምቀት ዕጩዎቹ፣ በግለሰብ ደረጃ ያላቸውን ጽኑ እምነት በሚያሳይ ሁኔታ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት እንዲችሉ ጥያቄዎቹን አስቀድመው በጸሎት ሊያስቡባቸው ይገባል።
ይሖዋን ብቻ ለማምለክ እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ ከምንም ነገር በላይ የእሱን ፈቃድ ለማስቀደም ቃል በመግባት ራስህን ለይሖዋ በጸሎት ወስነሃል?
በቀጣዩ የወረዳ ወይም የክልል ስብሰባ ላይ ለመጠመቅ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ እንደሆንክ ይሰማሃል?
ለጥምቀት ተስማሚ የሚሆነው አለባበስ ምን ዓይነት ነው? (1 ጢሞ. 2:9, 10፤ ዮሐ. 15:19፤ ፊልጵ. 1:10)
ክርስቲያኖች ‘ለአምላክ ያደሩ’ መሆናቸውን ለማሳየት “በልከኝነትና በማስተዋል” መልበስ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ዕጩ ተጠማቂዎች ሰውነትን የሚያጋልጥ የዋና ልብስ አሊያም ጽሑፍ ያለበት ወይም ማስታወቂያ የተለጠፈበት ልብስ መልበስ የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ ያልተዝረከረከ፣ ንጹሕ፣ ጨዋነት የሚንጸባረቅበትና ለሁኔታው ተስማሚ የሆነ አለባበስ ሊኖራቸው ይገባል።
አንድ ሰው በሚጠመቅበት ጊዜ ምን ዓይነት ምግባር ሊያሳይ ይገባል? (ሉቃስ 3:21, 22)
የኢየሱስ ጥምቀት በዛሬው ጊዜ ላለው የክርስቲያኖች ጥምቀት ጥሩ ምሳሌ ነው። ኢየሱስ፣ ጥምቀት በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው እርምጃ መሆኑን የተገነዘበ ሲሆን ይህንንም በአመለካከቱም ሆነ በድርጊቱ አንጸባርቋል። ስለዚህ የጥምቀት ሥነ ሥርዓቱ በሚካሄድበት ሥፍራ ተገቢ ያልሆኑ ቀልዶችን መቀለድ፣ መጫወት፣ መዋኘት ወይም ለዝግጅቱ የሚሰጠውን ክብር የሚቀንስ ማንኛውንም ነገር ማድረግ ተገቢ አይሆንም። በተጨማሪም አንድ አዲስ ክርስቲያን ትልቅ ጀብዱ የፈጸመ የሚያስመስል ድርጊት መፈጸም አይኖርበትም። ጥምቀት አስደሳች ወቅት ቢሆንም ደስታችንን ለሥነ ሥርዓቱ አክብሮት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ መግለጽ ይኖርብናል።
አዘውትረህ መሰብሰብህና በጉባኤው ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረብህ ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል ለመፈጸም የሚረዳህ እንዴት ነው?
ከተጠመቅክ በኋላም ጥሩ የግል ጥናት ፕሮግራም ያለህ መሆኑና አዘውትረህ በአገልግሎት መካፈልህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
-