መጠመቅ ለሚፈልጉ የቀረቡ ጥያቄዎች
ከጥምቀት ዕጩዎች ጋር የሚደረግ የመደምደሚያ ውይይት
የጥምቀት ሥነ ሥርዓት በአብዛኛው የሚከናወነው በይሖዋ ምሥክሮች የወረዳና የክልል ስብሰባዎች ላይ ነው። በጥምቀት ንግግሩ መደምደሚያ ላይ ተናጋሪው የጥምቀት ዕጩዎቹ ከተቀመጡበት እንዲነሱና ለሚከተሉት ሁለት ጥያቄዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መልስ እንዲሰጡ ይጠይቃቸዋል፦
1. ከኃጢአታችሁ ንስሐ በመግባት፣ ራሳችሁን ለይሖዋ በመወሰንና ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያደረገውን የመዳን ዝግጅት በመቀበል ለመጠመቅ ዝግጁ ሆናችኋል?
2. መጠመቃችሁ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ከታቀፉት የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ እንደሚያስቆጥራችሁ ተገንዝባችኋል?
የጥምቀት ዕጩዎቹ ለእነዚህ ጥያቄዎች ‘አዎ’ የሚል መልስ መስጠታቸው በቤዛው ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ መወሰናቸውን ‘በይፋ የሚናገሩበት’ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ሮም 10:9, 10) በመሆኑም የጥምቀት ዕጩዎቹ፣ በግለሰብ ደረጃ ያላቸውን ጽኑ እምነት በሚያሳይ ሁኔታ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት እንዲችሉ ጥያቄዎቹን አስቀድመው በጸሎት ሊያስቡባቸው ይገባል።
ይሖዋን ብቻ ለማምለክ እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ ከምንም ነገር በላይ የእሱን ፈቃድ ለማስቀደም ቃል በመግባት ራስህን ለይሖዋ በጸሎት ወስነሃል?
በቀጣዩ የወረዳ ወይም የክልል ስብሰባ ላይ ለመጠመቅ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ እንደሆንክ ይሰማሃል?
ለጥምቀት ተስማሚ የሚሆነው አለባበስ ምን ዓይነት ነው? (1 ጢሞ. 2:9, 10፤ ዮሐ. 15:19፤ ፊልጵ. 1:10)
ክርስቲያኖች ‘ለአምላክ ያደሩ’ መሆናቸውን ለማሳየት “በልከኝነትና በማስተዋል” መልበስ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ዕጩ ተጠማቂዎች ሰውነትን የሚያጋልጥ የዋና ልብስ አሊያም ጽሑፍ ያለበት ወይም ማስታወቂያ የተለጠፈበት ልብስ መልበስ የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ ያልተዝረከረከ፣ ንጹሕ፣ ጨዋነት የሚንጸባረቅበትና ለሁኔታው ተስማሚ የሆነ አለባበስ ሊኖራቸው ይገባል።
አንድ ሰው በሚጠመቅበት ጊዜ ምን ዓይነት ምግባር ሊያሳይ ይገባል? (ሉቃስ 3:21, 22)
የኢየሱስ ጥምቀት በዛሬው ጊዜ ላለው የክርስቲያኖች ጥምቀት ጥሩ ምሳሌ ነው። ኢየሱስ፣ ጥምቀት በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው እርምጃ መሆኑን የተገነዘበ ሲሆን ይህንንም በአመለካከቱም ሆነ በድርጊቱ አንጸባርቋል። ስለዚህ የጥምቀት ሥነ ሥርዓቱ በሚካሄድበት ሥፍራ ተገቢ ያልሆኑ ቀልዶችን መቀለድ፣ መጫወት፣ መዋኘት ወይም ለዝግጅቱ የሚሰጠውን ክብር የሚቀንስ ማንኛውንም ነገር ማድረግ ተገቢ አይሆንም። በተጨማሪም አንድ አዲስ ክርስቲያን ትልቅ ጀብዱ የፈጸመ የሚያስመስል ድርጊት መፈጸም አይኖርበትም። ጥምቀት አስደሳች ወቅት ቢሆንም ደስታችንን ለሥነ ሥርዓቱ አክብሮት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ መግለጽ ይኖርብናል።
አዘውትረህ መሰብሰብህና በጉባኤው ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረብህ ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል ለመፈጸም የሚረዳህ እንዴት ነው?
ከተጠመቅክ በኋላም ጥሩ የግል ጥናት ፕሮግራም ያለህ መሆኑና አዘውትረህ በአገልግሎት መካፈልህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ለጉባኤ ሽማግሌዎች የተሰጠ መመሪያ
አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ መጠመቅ እንደሚፈልግ ከተናገረ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከገጽ 185-207 ላይ የሚገኘውን “መጠመቅ ለሚፈልጉ የቀረቡ ጥያቄዎች” የሚለውን ክፍል በጥሞና እንዲከልስ ማበረታቻ ሊሰጠው ይገባል። ከገጽ 182 ጀምሮ የሚገኘውን ከሽማግሌዎቹ ጋር ለሚያደርጋቸው ውይይቶች እንዴት መዘጋጀት እንደሚችል የሚገልጸውን “ላልተጠመቀ አስፋፊ” የሚለውን ክፍል ትኩረት ሰጥቶ እንዲያነብ ሊነገረው ይገባል። እዚያ ላይ እንደተገለጸው ለመጠመቅ ጥያቄ ያቀረበው አስፋፊ ከሽማግሌዎቹ ጋር በሚወያይበት ጊዜ የያዘውን ማስታወሻ መጠቀምና ይህን መጽሐፍ ገልጦ መከታተል ይችላል። ይሁን እንጂ ግለሰቡ ከሽማግሌዎቹ ጋር ውይይት ከማድረጉ በፊት ሌላ ሰው ጥያቄዎቹን ሊከልስለት አያስፈልግም።
አንድ ሰው መጠመቅ ከፈለገ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪውን ሊያነጋግር ይገባል። ግለሰቡ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት “መጠመቅ ለሚፈልጉ የቀረቡ ጥያቄዎች” የሚለውን ክፍል ከከለሰ በኋላ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ግለሰቡን በጸሎት አማካኝነት ራሱን ለይሖዋ በመወሰን የእሱን ፈቃድ ለማድረግ ቃል ገብቶ እንደሆነ ይጠይቀዋል። ግለሰቡ ራሱን እንደወሰነ ከተናገረ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ሁለት ሽማግሌዎች “መጠመቅ ለሚፈልጉ የቀረቡ ጥያቄዎች” በሚለው ክፍል ላይ ተመሥርተው ከግለሰቡ ጋር እንዲወያዩ ዝግጅት ያደርጋል። ሁለቱን ክፍሎች የሚጠይቁት የተለያዩ ሽማግሌዎች መሆን አለባቸው። እነዚህን ውይይቶች ለማድረግ የወረዳ ወይም የክልል ስብሰባ የሚካሄድበት ጊዜ እስኪነገር ድረስ መጠበቅ አያስፈልግም።
ብዙውን ጊዜ ሁለቱ ክፍሎች እያንዳንዳቸው አንድ ሰዓት ገደማ በሚወስዱ ሁለት የተለያዩ ውይይቶች ሊሸፈኑ ይችላሉ። እርግጥ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ውይይቱ ከአንድ ሰዓት በላይ ሊወስድ ይችላል። እያንዳንዱ ውይይት በጸሎት ተጀምሮ በጸሎት መደምደም አለበት። የጥምቀት ዕጩውም ሆነ ሽማግሌዎቹ ጥያቄዎቹን ቶሎ ለመጨረስ መጣደፍ የለባቸውም። የጥምቀት ጥያቄዎቹን እንዲጠይቁ የተመደቡት ሽማግሌዎች ለዚህ ውይይት ቅድሚያ ሰጥተው ፕሮግራም ሊይዙለት ይገባል።
በጥቅሉ ሲታይ፣ በቡድን ከሚሆን ይልቅ ከእያንዳንዱ የጥምቀት ዕጩ ጋር በግለሰብ ደረጃ በጥያቄዎቹ ላይ መወያየት የተሻለ ነው። ሽማግሌዎቹ የጥምቀት ዕጩው በእያንዳንዱ ጥያቄ ላይ ሐሳብ እንዲሰጥ ማድረጋቸው እውቀቱ ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል፤ ይህም ግለሰቡ ለጥምቀት ዝግጁ መሆን አለመሆኑን በእርግጠኝነት ለማወቅ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም ለመጠመቅ ጥያቄ ያቀረበው ሰው ብቻውን በሚሆንበት ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ሐሳቡን ለመግለጽ ሊቀለው ይችላል። ባልና ሚስት የሆኑ የጥምቀት ዕጩዎች አንድ ላይ ሆነው ሊጠየቁ ይችላሉ።
የጥምቀት ዕጩዋ ሴት ከሆነች ውይይቱ ከሰዎች እይታ ባልተሰወረ ቦታ ላይ መደረግ አለበት፤ ያም ሆኖ የሚያደርጉትን ውይይት ሌሎች መስማት አይኖርባቸውም። ሌላ ሰው መጨመር አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በውይይቱ ላይ እንዲገኝ የሚጋበዘው ወንድም የጉባኤ ሽማግሌ ወይም አገልጋይ መሆን ይኖርበታል። በቀጣዩ አንቀጽ ላይ እንደሚብራራው የሚጋበዘው ወንድም የጉባኤ ሽማግሌ ነው ወይስ አገልጋይ የሚለውን ጉዳይ የሚወስነው የሚወያዩበት ክፍል ነው።
የሽማግሌዎች ቁጥር አነስተኛ በሆነባቸው ጉባኤዎች፣ አስተዋይ የሆኑና ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ብቃት እንዳላቸው ያስመሠከሩ የጉባኤ አገልጋዮች “ክፍል 1፦ የክርስትና ትምህርቶች” የሚለውን ርዕስ ከጥምቀት ዕጩዎች ጋር እንዲከልሱ ማድረግ ይቻላል። “ክፍል 2፦ የክርስትና ሕይወት” የሚለውን ርዕስ ማወያየት ያለባቸው የጉባኤ ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው። በጉባኤ ውስጥ ብቃት ያላቸው በቂ ወንድሞች ከሌሉ በአቅራቢያቸው ያለ ጉባኤ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይችል እንደሆነ ለመወሰን የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ሊያነጋግሩ ይችላሉ።
የጥምቀት ዕጩው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ከሆነ ውይይቱ አማኝ የሆኑ ወላጆቹ (ወላጁ) ባሉበት መደረግ ይኖርበታል። ወላጆቹ (ወላጁ) መገኘት ካልቻሉ በእያንዳንዱ ውይይት ላይ ሁለት ሽማግሌዎች (አንድ ሽማግሌና አንድ የጉባኤ አገልጋይ ሊሆንም ይችላል፤ ይህን የሚወስነው የሚወያዩበት ክፍል ነው) መገኘት አለባቸው።
ሽማግሌዎቹ ለመጠመቅ ጥያቄ ያቀረበው ሰው መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ምክንያታዊ በሆነ ደረጃ መቅሰም አለመቅሰሙን ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋሉ። ከዚህም በተጨማሪ የጥምቀት ዕጩው ለእውነት ጥልቅ አድናቆት እንዳለውና ለይሖዋ ድርጅት ተገቢ አክብሮት እንደሚያሳይ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ግለሰቡ መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በሚገባ የማያውቅ ከሆነ ሽማግሌዎች በሌላ ጊዜ ለጥምቀት ብቁ መሆን እንዲችል በግል እርዳታ የሚያገኝበትን መንገድ ያመቻቻሉ። ሌሎች ደግሞ ለመስክ አገልግሎት ያላቸው አድናቆት እየጨመረ መሄዱን ወይም በድርጅቱ ውስጥ ላሉት ዝግጅቶች ይበልጥ ተገዢ መሆናቸውን ማሳየት እንዲችሉ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ለእያንዳንዱ ክፍል የሚውለውን አንድ ሰዓት ገደማ የሚሆን ጊዜ አመጣጥኖ የመጠቀሙ ጉዳይ ለሽማግሌዎቹ የተተወ ነው፤ ሽማግሌዎቹ ግለሰቡ ለመጠመቅ ዝግጁ መሆን አለመሆኑን በሚገባ መረዳት ይችሉ ዘንድ በእያንዳንዱ ጥያቄ ላይ የሚያውሉትን ጊዜ በጥበብ መመጠን አለባቸው። ለአንዳንዶቹ ጥያቄዎች ረዘም ያለ፣ ለሌሎቹ ደግሞ አጠር ያለ ጊዜ ማዋል የሚቻል ቢሆንም በሁሉም ጥያቄዎች ላይ መወያየት ያስፈልጋል።
የጥምቀት ዕጩውን እንዲጠይቁ የተመደቡት ሽማግሌዎች በሁለተኛው ክፍል ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ አንድ ላይ ተገናኝተው ግለሰቡ ለመጠመቅ ብቁ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጉዳይ ይወስናሉ። ሽማግሌዎቹ የእያንዳንዱን የጥምቀት ዕጩ የቀድሞ ሕይወት፣ ችሎታና ሌሎች ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ያስገባሉ። ዋናው ዓላማችን የጥምቀት ዕጩዎቹ ልባቸውን ወደ ይሖዋ የመለሱና መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የተገነዘቡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው። ከእናንተ በሚያገኙት ፍቅራዊ እገዛ የጥምቀት ዕጩዎቹ የምሥራቹ አገልጋይ በመሆን የተሰጣቸውን ትልቅ ኃላፊነት ለመወጣት በበቂ ሁኔታ የተዘጋጁ ይሆናሉ።
ከዚህ በኋላ፣ ከተመደቡት ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ብቻ ወይም ሁለቱም አብረው ከግለሰቡ ጋር ተገናኝተው ለጥምቀት ብቁ መሆን አለመሆኑን ይነግሩታል። ለመጠመቅ ብቁ ከሆነ ሽማግሌዎቹ ከገጽ 206-207 ላይ የሚገኘውን “ከጥምቀት ዕጩዎች ጋር የሚደረግ የመደምደሚያ ውይይት” የሚለውን ክፍል አብረውት ሊከልሱ ይገባል። የጥምቀት ዕጩው ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ አጥንቶ ካልጨረሰ፣ ከተጠመቀ በኋላ መጽሐፉን አጥንቶ እንዲጨርስ ሽማግሌዎቹ ሊያበረታቱት ይገባል። ሽማግሌዎቹ ለዕጩ ተጠማቂው፣ የተጠመቀበት ቀን በጉባኤው የአስፋፊ መዝገብ ላይ እንደሚጻፍ ይነግሩታል። ሽማግሌዎች እሱን በተመለከተ እንዲህ ያሉ የግል መረጃዎችን የሚሰበስቡት ድርጅቱ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉትን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በቅርበት መከታተል እንዲችል እንዲሁም ለእሱ መንፈሳዊ ድጋፍ ለመስጠትና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈል ለመርዳት እንደሆነ ይገልጹለታል። በተጨማሪም ሽማግሌዎች ማንኛውንም የግል መረጃ የሚጠቀሙት በjw.org ላይ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ የመረጃ ጥበቃ ፖሊሲ መሠረት እንደሆነ ለአዳዲስ አስፋፊዎች ሊያሳውቋቸው ይችላሉ። ሽማግሌዎቹ ከግለሰቡ ጋር የሚያደርጉት ውይይት ቢበዛ ከአሥር ደቂቃ መብለጥ የለበትም።
አንድ አስፋፊ በተጠመቀ በዓመቱ ሁለት ሽማግሌዎች ማበረታቻና ጠቃሚ ምክር ለመስጠት ሊያነጋግሩት ይገባል። ከሽማግሌዎቹ አንዱ ግለሰቡ ያለበት ቡድን የበላይ ተመልካች መሆን አለበት። አስፋፊው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ከሆነ አማኝ የሆኑ ወላጆቹ በውይይቱ ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል። ውይይቱ ፍቅር በሚንጸባረቅበትና በሚያበረታታ መንፈስ መካሄድ ይኖርበታል። ሽማግሌዎቹ ግለሰቡ ያደረገውን መንፈሳዊ እድገት አንስተው ይወያያሉ፤ እንዲሁም ጥሩ የግል ጥናት ልማድ እንዲያዳብር፣ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ እንዲያነብ፣ ሳምንታዊ የቤተሰብ አምልኮ እንዲኖረው፣ በታማኝነት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝና ተሳትፎ እንዲያደርግ እንዲሁም በየሳምንቱ መስክ አገልግሎት እንዲወጣ በማበረታታት እነዚህን ነገሮች በቀጣይነት እንዴት ማድረግ እንደሚችል የሚያሳዩ ተግባራዊ ሐሳቦች ያካፍሉታል። (ኤፌ. 5:15, 16) ግለሰቡ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ አጥንቶ ካልጨረሰ ሽማግሌዎቹ የሚያስጠናው ሰው ይመድቡለታል። ሽማግሌዎቹ ወንድም የሚመሰገንባቸውን በርካታ ነጥቦች አንስተው ልባዊ የሆነ ምስጋና ሊሰጡት ይገባል። በአብዛኛው፣ አንድ ወይም ሁለት ነጥቦችን ጠቅሶ ምክር መስጠትና ግለሰቡ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መጠቆም በቂ ነው።