የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ግንቦት ገጽ 14-19
  • ቋሚ የሆነችውን ከተማ ተጠባበቁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ቋሚ የሆነችውን ከተማ ተጠባበቁ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በምንም ዓይነት በማይጥላችሁ በይሖዋ ታመኑ
  • አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ
  • የወንድማማች መዋደድና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ
  • ወደፊት ምን ይጠብቀናል?
  • እስከ መጨረሻው ለመጽናት የሚረዳን ደብዳቤ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • እርስ በርስ መቀራረባችን ይበጀናል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ግንቦት ገጽ 14-19

የጥናት ርዕስ 21

መዝሙር 21 አስቀድማችሁ መንግሥቱን ፈልጉ

ቋሚ የሆነችውን ከተማ ተጠባበቁ

“ወደፊት የምትመጣዋን ከተማ በጉጉት እንጠባበቃለን።”—ዕብ. 13:14

ዓላማ

ዕብራውያን ምዕራፍ 13 አሁንም ሆነ ወደፊት ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?

1. ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም ምን ተናግሮ ነበር?

ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ዝርዝር ሐሳቦችን የያዘ አንድ ትንቢት ተናግሯል። ይህ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው የአይሁድ ሥርዓት መጥፊያ በቀረበበት ወቅት ነው። ኢየሱስ የኢየሩሳሌም ከተማ ‘በጦር ሠራዊት እንደምትከበብ’ አስጠንቅቆ ነበር። (ሉቃስ 21:20) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ይህን የጦር ሠራዊት ባዩ ጊዜ ወዲያውኑ አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ነግሯቸዋል። የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ሲከብ ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ።—ሉቃስ 21:21, 22

2. ሐዋርያው ጳውሎስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጥቷቸዋል?

2 የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከመክበቡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ክርስቲያኖች አስፈላጊ መልእክት የያዘ አንድ ደብዳቤ ጻፈላቸው። ይህ ደብዳቤ በአሁኑ ጊዜ የዕብራውያን መጽሐፍ ተብሎ ይጠራል። በደብዳቤው ላይ ጳውሎስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች ወደፊት ለሚያጋጥማቸው ሁኔታ እንዲዘጋጁ የሚረዳ ወሳኝ ምክር ሰጥቷቸዋል። ታዲያ ወደፊት የሚያጋጥማቸው ምንድን ነው? ኢየሩሳሌም ትጠፋለች። እነዚህ ክርስቲያኖች ከጥፋቱ መትረፍ ከፈለጉ መኖሪያቸውንና ሥራቸውን ለመተው ዝግጁ መሆን ነበረባቸው። በመሆኑም ጳውሎስ ስለ ኢየሩሳሌም ከተማ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “በዚህ ቋሚ ከተማ የለንምና፤ ከዚህ ይልቅ ወደፊት የምትመጣዋን ከተማ በጉጉት እንጠባበቃለን።”—ዕብ. 13:14

3. ‘እውነተኛ መሠረት ያላት ከተማ’ ምንን ታመለክታለች? በጉጉት ልንጠባበቃት የሚገባውስ ለምንድን ነው?

3 ኢየሩሳሌምንና ይሁዳን ለቀው ለመሄድ የወሰኑት ክርስቲያኖች ፌዝና ነቀፋ ደርሶባቸው ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ይህ ውሳኔ ሕይወታቸውን ታድጎላቸዋል። በዛሬው ጊዜ እኛም በሰዎች ስለማንታመን እንዲሁም በዚህ ዓለም ውስጥ የተደላደለ ሕይወት ለመምራት ስለማንሞክር እንደ ሞኝ እንታያለን። ታዲያ እንዲህ ያለ ምርጫ የምናደርገው ለምንድን ነው? ይህ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋ ስለምናውቅ ነው። “ወደፊት የምትመጣዋን” “እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ” ማለትም የአምላክን መንግሥት እንጠባበቃለን።a (ዕብ. 11:10፤ ማቴ. 6:33) በዚህ ርዕስ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ንዑስ ርዕስ የሚከተሉትን ነጥቦች ያብራራል፦ (1) ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠው ምክር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች “ወደፊት የምትመጣዋን ከተማ” እንዲጠባበቁ የረዳቸው እንዴት ነው? (2) ጳውሎስ ወደፊት ለሚያጋጥማቸው ሁኔታ እንዲዘጋጁ የረዳቸው እንዴት ነው? እንዲሁም (3) ምክሩ በአሁኑ ጊዜ እኛን የሚረዳን እንዴት ነው?

በምንም ዓይነት በማይጥላችሁ በይሖዋ ታመኑ

4. ክርስቲያኖች ለኢየሩሳሌም ትልቅ ቦታ ይሰጡ የነበረው ለምንድን ነው?

4 ኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ትልቅ ቦታ የሚሰጧት ከተማ ነበረች። በ33 ዓ.ም. የመጀመሪያው የክርስቲያን ጉባኤ የተቋቋመው በኢየሩሳሌም ነው፤ የበላይ አካሉም የነበረው በዚያው ነው። በተጨማሪም በርካታ ክርስቲያኖች በዚያች ከተማ ውስጥ ቤት ንብረት አፍርተው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ተከታዮቹን ከኢየሩሳሌም ብሎም ከይሁዳ እንዲወጡ አሳስቧቸዋል።—ማቴ. 24:16

5. ጳውሎስ በወቅቱ የነበሩትን ክርስቲያኖች ወደፊት ለሚጠብቃቸው ሁኔታ ያዘጋጃቸው እንዴት ነው?

5 ጳውሎስ ክርስቲያኖች ወደፊት ለሚያጋጥማቸው ነገር እንዲዘጋጁ ስለፈለገ ይሖዋ ለኢየሩሳሌም ያለውን አመለካከት እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ይሖዋ ቤተ መቅደሱን፣ የክህነት ሥርዓቱንና በኢየሩሳሌም የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች ቅዱስ አድርጎ መመልከቱን እንዳቆመ አስታውሷቸዋል። (ዕብ. 8:13) አብዛኞቹ የከተማዋ ነዋሪዎች መሲሑን አልተቀበሉም። የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ማዕከል መሆኑ አብቅቷል፤ ደግሞም በቅርቡ ይጠፋል።—ሉቃስ 13:34, 35

6. በዕብራውያን 13:5, 6 ላይ ጳውሎስ የሰጠው ማሳሰቢያ ለክርስቲያኖች ወቅታዊ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

6 ጳውሎስ ደብዳቤውን ለዕብራውያን በጻፈበት ወቅት ኢየሩሳሌም ሞቅ ያለች ከተማ ነበረች። በዘመኑ የነበረ አንድ ሮማዊ ጸሐፊ እንደገለጸው ኢየሩሳሌም “በምሥራቁ ዓለም ካሉ ከተሞች ሁሉ ዝነኛዋ” ነበረች። በዓላትን ለማክበር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በየዓመቱ የሚመጡ አይሁዳውያን ነበሩ። ይህም ከተማዋ በኢኮኖሚ እንድታድግ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ሁኔታ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ሀብት እንዲያካብቱ ረድቷቸው ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ጳውሎስ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ” ያላቸው ለዚህ ሊሆን ይችላል። በመቀጠልም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በግለሰብ ደረጃ የሰጣቸውን ዋስትና የያዘውን የሚከተለውን ጥቅስ ጠቀሰላቸው፦ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም።” (ዕብራውያን 13:5, 6⁠ን አንብብ፤ ዘዳ. 31:6፤ መዝ. 118:6) በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች ይህ ማረጋገጫ ያስፈልጋቸው ነበር። ለምን? ምክንያቱም ደብዳቤው ከደረሳቸው ብዙም ሳይቆይ ቤታቸውን፣ ንግዳቸውንና አብዛኛውን ንብረታቸውን ትተው መሄድ ይኖርባቸዋል። ከዚያም በሌላ አካባቢ አዲስ ሕይወት መጀመር አለባቸው፤ ይህ ደግሞ ቀላል እንደማይሆን ግልጽ ነው።

7. ከአሁኑ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ያለብን ለምንድን ነው?

7 የምናገኘው ትምህርት፦ እኛስ በቅርቡ ምን ይጠብቀናል? ‘ታላቁ መከራ’ ይጀምራል፤ ከዚያም ይህ ክፉ ዓለም ይጠፋል። (ማቴ. 24:21) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ነቅተንና ተዘጋጅተን ልንጠብቅ ይገባል። (ሉቃስ 21:34-36) በታላቁ መከራ ወቅት ይሖዋ ሕዝቡን ፈጽሞ እንደማይጥል በመተማመን አንዳንድ ንብረቶቻችንን ይባስ ብሎም ያለንን ነገር በሙሉ መተው ሊኖርብን ይችላል። ‘ታላቁ መከራ’ ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን በይሖዋ መታመናችንን ማሳየት የምንችልበት አጋጣሚ አለን። ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘የማደርጋቸው ውሳኔዎችና ግቦቼ የምታመነው በሀብት ሳይሆን እንደሚንከባከበኝ ቃል በገባልኝ በይሖዋ እንደሆነ ያሳያሉ?’ (1 ጢሞ. 6:17) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ካጋጠመው ነገር የምናገኘው ትምህርት በታላቁ መከራ ወቅት ታማኝነታችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። ሆኖም ‘ታላቁ መከራ’ በክርስቲያኖች ታሪክ አጋጥሞ የማያውቅ ተፈታታኝ ጊዜ ይሆናል። ከዚህ አንጻር ታላቁ መከራ ሲጀምር ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ

8. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል?

8 ዕብራውያን ክርስቲያኖች የጳውሎስ ደብዳቤ ከደረሳቸው ከጥቂት ዓመታት በኋላ የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከበበ። ይህን ሲያዩ የኢየሩሳሌም መጥፊያ ስለቀረበ ከተማዋን ለቀው መውጣት እንዳለባቸው ተገነዘቡ። (ማቴ. 24:3፤ ሉቃስ 21:20, 24) ይሁንና መሸሽ ያለባቸው ወዴት ነው? ኢየሱስ “በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ” የሚል መመሪያ ብቻ ነው የሰጠው። (ሉቃስ 21:21) በአካባቢው ብዙ ተራሮች ነበሩ። ታዲያ ወደ የትኛው ይሸሹ ይሆን?

9. ክርስቲያኖች ወደ የትኞቹ ተራሮች እንደሚሸሹ አሳስቧቸው ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ካርታውንም ተመልከት።)

9 እስቲ ክርስቲያኖች ወደ የትኞቹ ተራሮች ሊሸሹ ይችሉ እንደነበር አስቡ። ለምሳሌ የሰማርያ ተራሮች፣ የገሊላ ተራሮች፣ የሄርሞን ተራራና የሊባኖስ ተራሮች እንዲሁም ከዮርዳኖስ ማዶ ያሉ ተራሮች ነበሩ። (ካርታውን ተመልከት።) በእነዚህ ተራሮች ላይ የሚገኙት አንዳንዶቹ ከተሞች ደህንነታቸው የተጠበቁ ቦታዎች ሊመስሉ ይችላሉ። ለምሳሌ የጋምላ ከተማ የምትገኘው በአንድ ረጅም ተራራ ላይ ስለነበር ወደዚያ መድረስ በጣም አስቸጋሪ ነበር። አንዳንዶቹ አይሁዳውያን ከተማዋ አስተማማኝ መሸሸጊያ እንደምትሆን ይሰማቸው ነበር። ሆኖም ጋምላ ውስጥ በአይሁዳውያንና በሮማውያን መካከል ከባድ ውጊያ ተካሄደ፤ በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ነዋሪዎቿ ሞቱ።b

በመጀመሪያው መቶ ዘመን እስራኤል ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ተራሮችንና ከተሞችን የሚያሳይ ካርታ። ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን የሊባኖስ ተራሮች፣ የገሊላ ተራሮች፣ የሰማርያ ተራሮችና የጊልያድ ተራሮች እንዲሁም የሄርሞን ተራራና የታቦር ተራራ ይገኛሉ። ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን ያሉት ከተሞች ጋምላ፣ ቂሳርያ እና ፔላ ናቸው። ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ የይሁዳ ተራሮች፣ የአባሪም ተራሮች እንዲሁም የመሳዳ ከተማ ይገኛሉ። በተጨማሪም ካርታው ሮማውያን ዘመቻ ያካሄዱበትን መስመርና ከ67 ዓ.ም. እስከ 73 ዓ.ም. የተቆጣጠሯቸውን ቦታዎች ያሳያል።

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሊሸሹባቸው የሚችሉ በርካታ ተራሮች ቢኖሩም አስተማማኝ የነበሩት ሁሉም አይደሉም (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)


10-11. (ሀ) ይሖዋ ክርስቲያኖችን የመራቸው እንዴት ሊሆን ይችላል? (ዕብራውያን 13:7, 17) (ለ) ክርስቲያኖች አመራር ለሚሰጧቸው ወንድሞች በመታዘዛቸው ምን ጥቅም አግኝተዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

10 ይሖዋ ክርስቲያኖችን ወዴት መሄድ እንዳለባቸው ለመምራት በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡ ወንድሞችን ተጠቅሞ የነበረ ይመስላል። ዩሲቢየስ የተባለው የታሪክ ምሁር ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በኢየሩሳሌም ጉባኤ ውስጥ የነበሩት ሰዎች፣ አምላክ ለተሾሙ ወንዶች በገለጠው ራእይ አማካኝነት ከጦርነቱ በፊት ከከተማዋ ወጥተው ፔላ በተባለች የፔሪያ ከተማ እንዲሰፍሩ መመሪያ ተሰጣቸው።” በወቅቱ ለነበሩት ክርስቲያኖች ፔላ የተሻለች አማራጭ ነበረች። ከኢየሩሳሌም ብዙም ስለማትርቅ እዚያ መድረስ በአንጻራዊ ሁኔታ ቀላል ነው። አብዛኞቹ የከተማዋ ነዋሪዎች አሕዛብ ነበሩ፤ በመሆኑም በአክራሪ አይሁዳውያንና በሮማውያን መካከል የሚደረገው ጦርነት እምብዛም አያሰጋትም።—ካርታውን ተመልከት።

11 ወደ ተራሮች የሸሹት ክርስቲያኖች ጳውሎስ “በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ” በማለት የሰጠውን ምክር ተከትለዋል። (ዕብራውያን 13:7, 17⁠ን አንብብ።) በመሆኑም የአምላክ ሕዝቦች መትረፍ ችለዋል። አምላክ “እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ” ማለትም የአምላክን መንግሥት የሚጠባበቁትን እንዳልጣላቸው ታሪክ ያረጋግጣል።—ዕብ. 11:10

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የተወሰኑ ክርስቲያኖች ጓዛቸውን ይዘው በተራራማ አካባቢ ሲጓዙ።

ፔላ ቅርብና ከአደጋ ቀጠና ውጭ ነበረች (አንቀጽ 10-11⁠ን ተመልከት)


12-13. በአስቸጋሪ ወቅቶች ይሖዋ ሕዝቡን የመራው እንዴት ነው?

12 የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ አመራር የሚሰጡ ወንድሞችን በመጠቀም ለሕዝቡ ዝርዝር መመሪያ ይሰጣል። ይሖዋ በአስቸጋሪ ወቅቶች ሕዝቡን ለመምራት እረኞችን እንዳስነሳ የሚገልጹ በርካታ ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። (ዘዳ. 31:23፤ መዝ. 77:20) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ አመራር የሚሰጡ ወንድሞችን እየተጠቀመ እንዳለ የሚያሳይ ብዙ ማስረጃ አለ።

13 ለምሳሌ ያህል፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት አመራር የሚሰጡ ወንድሞች አስፈላጊውን መመሪያ አስተላልፈው ነበር። ሽማግሌዎች የወንድሞቻቸውንና የእህቶቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። ወረርሽኙ ከተከሰተ ብዙም ሳይቆይ በኢንተርኔት፣ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ከ500 በሚበልጡ ቋንቋዎች ታሪካዊ የክልል ስብሰባ አካሂደን ነበር። መንፈሳዊ ምግብ አልተቋረጠብንም። በዚህም ምክንያት አንድነታችንን መጠበቅ ችለናል። ወደፊት ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ይሖዋ አመራር የሚሰጡን ወንድሞች የተሻለውን አካሄድ እንዲያውቁ እንደሚረዳቸው መተማመን እንችላለን። ለታላቁ መከራ ለመዘጋጀትና በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ በይሖዋ መታመንና መመሪያዎቹን መታዘዝ እንደሚያስፈልግ ተመልክተናል። ሆኖም ከዚህ በተጨማሪ የትኞቹ ባሕርያት ያስፈልጉናል?

የወንድማማች መዋደድና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ

14. በዕብራውያን 13:1-3 መሠረት ክርስቲያኖች የአይሁድ ሥርዓት መጥፊያ ሲቃረብ የትኞቹን ባሕርያት ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር?

14 ታላቁ መከራ ሲጀምር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ለወንድሞቻችን ፍቅር ማሳየት ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። እነዚህ ክርስቲያኖች ቀድሞውንም ቢሆን እርስ በርስ ይዋደዱ ነበር። (ዕብ. 10:32-34) ሆኖም የአይሁድ ሥርዓት መጥፊያ በተቃረበበት ወቅት ክርስቲያኖች ከቀድሞው የበለጠ ‘እንደ ወንድማማች መዋደድ’ እና ‘የእንግዳ ተቀባይነት’ መንፈስ ማሳየት ነበረባቸው።c (ዕብራውያን 13:1-3⁠ን አንብብ።) እኛም በተመሳሳይ፣ የዚህ ሥርዓት መጥፊያ በተቃረበ መጠን ከበፊቱ የበለጠ ለወንድሞቻችን ፍቅር ማሳየት ይኖርብናል።

15. ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከሸሹ በኋላ የወንድማማች መዋደድና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

15 ኢየሩሳሌምን ከብቦ የነበረው የሮም ሠራዊት በድንገት ሲያፈገፍግ ክርስቲያኖች ጥቂት ንብረቶቻቸውን ብቻ ይዘው ሸሹ። (ማቴ. 24:17, 18) ስለሆነም ወደ ተራሮች ለመሸሽና በአዲሱ አካባቢ ሕይወትን “ሀ” ብለው ለመጀመር እርስ በርስ መደጋገፍ ያስፈልጋቸው ነበር። በዚህ ጊዜ በርካታ ‘አሳሳቢ ችግሮች ተፈጥረው’ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም፤ ይህም ለክርስቲያኖች እርስ በርስ በመረዳዳት እንዲሁም ያላቸውን ነገር በማካፈል እውነተኛ የወንድማማች መዋደድና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት የሚችሉበት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።—ቲቶ 3:14

16. የእኛ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው የእምነት አጋሮቻችን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 የምናገኘው ትምህርት፦ ፍቅር የእምነት አጋሮቻችን እገዛ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ እንድንደርስላቸው ያነሳሳናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋዎች የተነሳ ከመኖሪያቸው የተሰደዱ ብዙ ወንድሞችና እህቶች አሉ። በርካታ የአምላክ ሕዝቦች እነዚህ የእምነት አጋሮቻቸው የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊና ቁሳዊ እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኞች ሆነዋል። በጦርነቱ የተነሳ ከመኖሪያዋ የተሰደደች አንዲት ዩክሬናዊት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ በወንድሞቻችን አማካኝነት እንደመራንና የእርዳታ እጁን እንደዘረጋልን ተሰምቶናል። በዩክሬን፣ በሃንጋሪ፣ አሁን ደግሞ በጀርመን ያሉት ወንድሞቻችን ተቀብለውናል፤ እንዲሁም ተንከባክበውናል።” እኛም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ስናሳይና በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ስንረዳቸው በይሖዋ እጅ እንዳለ ጠቃሚ መሣሪያ እንሆናለን።—ምሳሌ 19:17፤ 2 ቆሮ. 1:3, 4

አረጋዊ የሆኑ ባልና ሚስት ከመኖሪያቸው የተሰደዱ ቤተሰቦችን ቤታቸው ሲቀበሉ። የቤተሰቡ አባላት አንድ ሻንጣና የተወሰኑ ቦርሳዎችን ይዘዋል።

በዛሬው ጊዜ ከመኖሪያቸው የተሰደዱ ክርስቲያኖች የእኛ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)


17. የወንድማማች መዋደድንና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስን ከአሁኑ ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

17 ወደፊት ከአሁኑ ይበልጥ እርስ በርስ መረዳዳት እንደሚያስፈልገን ጥያቄ የለውም። (ዕን. 3:16-18) ይሖዋ የወንድማማች ፍቅር እንድናሳይና እንግዳ ተቀባይ እንድንሆን ከአሁኑ እያሠለጠነን ነው። እነዚህ ባሕርያት በታላቁ መከራ ወቅት በጣም አስፈላጊ ናቸው።

ወደፊት ምን ይጠብቀናል?

18. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ዕብራውያን ክርስቲያኖች መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

18 ታሪክ እንደሚያረጋግጠው ወደ ተራሮች የሸሹት ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው ጥፋት መትረፍ ችለዋል። ከተማዋን ጥለው ቢወጡም ይሖዋ ግን ፈጽሞ አልጣላቸውም። እኛስ ከእነሱ ታሪክ ምን እንማራለን? የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ በዝርዝር አናውቅም። ሆኖም ኢየሱስ ዝግጁ ሆነን እንድንጠብቅ አስጠንቅቆናል። (ሉቃስ 12:40) በተጨማሪም ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በሰጣቸው ምክር ላይ ማሰላሰልና ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። ይህ ምክር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ያህል ዛሬም ጠቃሚ ነው። እንዲሁም ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወንና በምንም ዓይነት እንደማይጥለን በግለሰብ ደረጃ ዋስትና ሰጥቶናል። (ዕብ. 13:5, 6) እንግዲያው ቋሚ የሆነችውን ከተማ ማለትም የአምላክን መንግሥት በጉጉት እንጠባበቅ። እንዲህ ካደረግን መንግሥቱ የሚያመጣውን ዘላለማዊ በረከት ማጨድ እንችላለን።—ማቴ. 25:34

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ከአሁኑ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

  • በታላቁ መከራ ወቅት ታዛዥነት በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

  • ከአሁኑ የወንድማማች መዋደድና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

መዝሙር 157 የናፈቀን ሰላም!

a በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በንጉሥ የሚመሩ ብዙ ከተሞች ነበሩ። እንዲህ ያሉት ከተሞች እንደ መንግሥት ሊቆጠሩ ይችላሉ።—ዘፍ. 14:2

b ይህ የሆነው በ67 ዓ.ም. ማለትም ክርስቲያኖች ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ከሸሹ ብዙም ሳይቆይ ነው።

c “የወንድማማች መዋደድ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ለቅርብ ቤተሰቦቻችን የምናሳየውን ፍቅር ሊያመለክት ይችላል፤ ሆኖም ጳውሎስ ይህን ቃል እዚህ ላይ የተጠቀመበት በጉባኤ ውስጥ ያለውን የቀረበ ትስስር ለማመልከት ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ