ለጥናት የሚረዱ ሐሳቦች
ጥቅሶችን ማስታወስ
የምትወደውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማስታወስ ከብዶህ ያውቃል? የሚያጽናናህ፣ የተሳሳቱ ሐሳቦችን ለማስተካከል የሚረዳህ ወይም ለሌሎች ማካፈል የምትፈልገው ጥቅስ ሊሆን ይችላል። (መዝ. 119:11, 111) ጥቅሶችን ለማስታወስ ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ ምክሮችን እስቲ እንመልከት።
JW ላይብረሪ ላይ ያለውን “ፈርጅ” የሚለውን ገጽታ ተጠቀም።a “የምወዳቸው ጥቅሶች” የሚል ፈርጅ ፍጠር፤ ከዚያም ማስታወስ የምትፈልጋቸውን ጥቅሶች በዚህ ፈርጅ ሥር አስገባ።
ጥቅሱን በግልጽ ማየት በምትችልበት ቦታ ላይ ለጥፈው። ማስታወስ የምትፈልገውን ጥቅስ ወረቀት ላይ ጻፈው፤ ከዚያም ብዙ ጊዜ ልታየው በምትችልበት ቦታ ላይ አስቀምጠው። አንዳንዶች መስታወታቸው ላይ ሌሎች ደግሞ የፍሪጃቸው በር ላይ ይለጥፋሉ። አንዳንዶች ደግሞ ጥቅሱን ፎቶ ያነሱና ፎቶውን የኮምፒውተራቸው ወይም የስልካቸው ስክሪን ላይ ያደርጉታል።
ለማስታወስ የሚረዱ ካርዶችን አዘጋጅ። ጥቅሱን ከፊት፣ የጥቅሱን ሐሳብ ደግሞ ከጀርባ ጻፍ። ከዚያም ጥቅሱን አይተህ የጥቅሱን ሐሳብ ለማስታወስ ወይም የጥቅሱን ሐሳብ አይተህ ጥቅሱን ለማስታወስ ሞክር።
a ይህን ገጽታ መጠቀም ስለሚቻልበት መንገድ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ድርጅቱ ያከናወናቸው ነገሮች—የJWJW ላይብረሪ አጠቃቀም የሚለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት።