መጽሐፍ ቅዱስን በጥሩ ሁኔታ ተጠቀሙበት
1. መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ጠቃሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
1 በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን ቃል በጥሩ ሁኔታ መጠቀም እውነትን ግልጽ በሆነ መንገድ እንድናውጅና እንድናስተምር ብሎም የሐሰት ትምህርቶችንና ወጎችን እንድናጋልጥ ያስችለናል።—2 ጢሞ. 2:15፤ 1 ጴጥ. 3:15
2. ጥቅሶችን በቀላሉ እንድናስታውስ ምን ሊረዳን ይችላል?
2 መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ለማወቅ ጣሩ፦ እንደ ማንኛውም መሣሪያ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስንም በጥሩ ሁኔታ መጠቀም የምንችለው ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ማንበባችን አጠቃላይ ይዘቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል። በተጨማሪም ጥቅሶችን በቀላሉ ማስታወስና በተቀላጠፈ ሁኔታ ማውጣት እንድንችል ይረዳናል። ቅዱሳን መጻሕፍትን ይበልጥ እያወቅን በሄድን መጠን መደበኛ ባልሆነ መንገድም ሆነ በመስክ አገልግሎት ላይ በምንመሠክርበት ጊዜ በከፍተኛ ቅንዓትና በእርግጠኝነት ስሜት እንናገራለን።—1 ተሰ. 1:5
3, 4. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ለማወቅ የሚያስችሉን አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ለማወቅ የተጠቀማችሁበት ሌላ ዘዴ አለ?
3 በጉባኤ ስብሰባዎች ወቅት ጥቅሶችን አውጥታችሁ የመከታተል ልማድ አዳብሩ። የግል ጥናት ስታደርጉና ለጉባኤ ስብሰባዎች ስትዘጋጁ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥታችሁ አንብቡ፤ እንዲሁም እንዴት ተግባራዊ ልታደርጓቸው እንደምትችሉ አሰላስሉ። በርካታ አስፋፊዎች፣ ጥቅሶችን ከኮምፒውተር ላይ ወይም በወረቀት አትመው ከማንበብ ይልቅ በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማንበባቸው በአገልግሎት ላይ ጥቅሱን በቀላሉ ለማስታወስ እንደረዳቸው ተናግረዋል።—ዮሐ. 14:26
4 አንዳንድ ቤተሰቦች ጥቅሶችን በቃላቸው ለመያዝ ልምምድ የሚያደርጉበት ጊዜ መድበዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ በኩል የጥቅሱን ምዕራፍና ቁጥር በጀርባው ደግሞ የጥቅሱን ሐሳብ በተጻፈባቸው ቁርጥራጭ ወረቀቶች በመጠቀም የሚለማመዱ ቤተሰቦች አሉ። የቤተሰቡ አባላት ጥቅሱ የሚገኝበትን ቦታና ሐሳቡን ተራ በተራ ይጠያየቃሉ። ለመስክ አገልግሎት መግቢያዎችን መለማመዳችን እንዲሁም ሰዎች ለሚሰነዝሯቸው የተቃውሞ ሐሳቦች ወይም ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን መልስ መስጠታችን ጥቅስ የማስታወስ ችሎታችንን ያሳድግልናል።
5. መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ረገድ ችሎታችንን ማሳደግ ያለብን ለምንድን ነው?
5 ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚተካከል አንድም መጽሐፍ የለም። ምክንያቱም “ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው። (2 ጢሞ. 3:15) በክልላችን ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ውድ ሀብት ስለማያውቁ ቅዱሳን መጻሕፍት ምን እንደያዙ በማሳየት ረገድ ያለንን ችሎታ ማዳበራችን ተገቢ ነው።—ምሳሌ 2:1-5