የጥናት ርዕስ 48
መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን
የኢዮብ መጽሐፍ መከራ ሲያጋጥምህ ይረዳሃል
“በእርግጥም አምላክ ክፋት አይሠራም።”—ኢዮብ 34:12
ዓላማ
አምላክ መከራ እንዲኖር ስለፈቀደበት ምክንያትና መከራ ሲደርስብን መጽናት ስለምንችልበት መንገድ ከኢዮብ መጽሐፍ ምን እንማራለን?
1-2. የኢዮብን መጽሐፍ ማንበባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
የኢዮብን መጽሐፍ በቅርቡ አንብበኸዋል? የተጻፈው ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት ቢሆንም ይህ ጥንታዊ መጽሐፍ በዓለማችን ላይ ካሉት ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች እንደ አንዱ ይቆጠራል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ፣ ይህ መጽሐፍ ለመረዳት ቀላል፣ ማራኪ እንዲሁም ኃይለኛ መልእክት የያዘ በመሆኑ ጸሐፊውን “የሥነ ጽሑፍ ሊቅ” በማለት ጠርቶታል። ይህን አስደናቂ መጽሐፍ የጻፈው ሙሴ ነው፤ ሆኖም የመልእክቱ ምንጭ ይሖዋ አምላክ ነው።—2 ጢሞ. 3:16
2 የኢዮብ መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ወሳኝ ክፍል ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ በሁሉም ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታት ፊት የተደቀነው አንገብጋቢ ጉዳይ ምን እንደሆነ በግልጽ ይናገራል፤ እሱም የይሖዋ ስም መቀደስ ነው። በተጨማሪም እንደ ፍቅር፣ ጥበብ፣ ፍትሕና ኃይል ስላሉት የይሖዋ ግሩም ባሕርያት ያስተምረናል። ለምሳሌ የኢዮብ መጽሐፍ 31 ጊዜ ያህል ይሖዋን “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ” በማለት ጠርቶታል። ይህ አገላለጽ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ የሚገኝበት ቦታ ቢደመር እንኳ እዚህ ላይ አይደርስም። የኢዮብ መጽሐፍ ለሚፈጠሩብን አሳሳቢ ጥያቄዎችም መልስ ይሰጣል። ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዱ “አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?” የሚለው ነው። ይህ ጥያቄ ዛሬም ድረስ ብዙዎችን የሚያስጨንቅ ነው።
3. የኢዮብን መጽሐፍ በማጥናት የትኞቹን ጥቅሞች ማግኘት እንችላለን?
3 ተራራ ላይ ያለ ሰው ዙሪያውን በግልጽ ማየት እንደሚችል ሁሉ የኢዮብም መጽሐፍ በሕይወታችን ለሚያጋጥሙን ፈተናዎች ሰፋ ያለ እይታ እንዲኖረን ማለትም የይሖዋን እይታ እንድናዳብር ያስችለናል። መከራ ሲደርስብን የኢዮብ መጽሐፍ እንዴት እንደሚረዳን እስቲ እንመልከት። እስራኤላውያን ከኢዮብ ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት ይችሉ እንደነበርና በዛሬው ጊዜ እኛም ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመለከታለን። በተጨማሪም ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሌሎችን ለመርዳት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን።
አምላክ ኢዮብ መከራ እንዲደርስበት ፈቀደ
4. በኢዮብና በግብፅ በነበሩት እስራኤላውያን መካከል ምን ሰፊ ልዩነት ነበር?
4 እስራኤላውያን ግብፅ ውስጥ ባሪያዎች በነበሩበት ወቅት ኢዮብ የተባለ ሰው በዑጽ ምድር ይኖር ነበር፤ ዑጽ የምትገኘው ከተስፋይቱ ምድር በስተ ምሥራቅና በአረብ አገር ሰሜናዊ ክፍል ሳይሆን አይቀርም። ግብፅ ውስጥ ጣዖት ማምለክ ከጀመሩት እስራኤላውያን በተቃራኒ ኢዮብ በታማኝነት ይሖዋን አገልግሏል። (ኢያሱ 24:14፤ ሕዝ. 20:8) ይሖዋ ስለ ኢዮብ ሲናገር “በምድር ላይ እንደ እሱ ያለ ሰው የለም” ብሏል።a (ኢዮብ 1:8) ኢዮብ እጅግ ባለጸጋ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በምሥራቅ ካሉት ሰዎች ሁሉ የላቀ ክብር ነበረው። (ኢዮብ 1:3) ሰይጣን እንዲህ ያለው ታዋቂና የተከበረ ሰው አምላክን በታማኝነት ሲያገለግል ሲመለከት ምንኛ ተናዶ ይሆን!
5. ይሖዋ ኢዮብ መከራ እንዲደርስበት የፈቀደው ለምንድን ነው? (ኢዮብ 1:20-22፤ 2:9, 10)
5 ሰይጣን፣ ኢዮብ መከራ ቢደርስበት እውነተኛውን አምልኮ እንደሚተው ተናግሯል። (ኢዮብ 1:7-11፤ 2:2-5) ሰይጣን የሰነዘረው ክስ በርካታ ወሳኝ ጥያቄዎችን ያስነሳል። ስለዚህ ይሖዋ ኢዮብን በጣም ቢወደውም የሰይጣን ክስ እውነት መሆን አለመሆኑ እንዲረጋገጥ ሲል ኢዮብ መከራ እንዲደርስበት ፈቀደ። (ኢዮብ 1:12-19፤ 2:6-8) ሰይጣን የኢዮብን ከብቶችና መንጋዎች ወሰደበት፤ አሥሩን ልጆቹን ገደለበት፤ እንዲሁም ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ክፉኛ በሚያሠቃይ እባጭ መታው። ሆኖም ሰይጣን ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ ለማድረግ የተጠቀመበት ጭካኔ የተሞላበት ዘዴ ሳይሳካ ቀርቷል። (ኢዮብ 1:20-22፤ 2:9, 10ን አንብብ።) ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ለኢዮብ ጤናውን፣ ሀብቱንና ክብሩን መልሶለታል፤ እንዲሁም አሥር ልጆች ሰጥቶታል። በተጨማሪም ይሖዋ በኢዮብ ዕድሜ ላይ 140 ዓመት በመጨመር ባርኮታል፤ በመሆኑም የልጅ ልጆቹን እስከ አራት ትውልድ ድረስ ማየት ችሏል። (ኢዮብ 42:10-13, 16) ይህ ዘገባ እስራኤላውያንን ሊጠቅማቸው ይችል የነበረው እንዴት ነው? እኛንስ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
6. የኢዮብ ታሪክ እስራኤላውያንን ሊጠቅማቸው ይችል የነበረው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
6 ይህ ታሪክ እስራኤላውያንን ሊጠቅማቸው ይችል የነበረው እንዴት ነው? እስራኤላውያን በግብፅ የመሩት ሕይወት በመከራ የተሞላ ነበር። ለምሳሌ ኢያሱና ካሌብ ወጣትነታቸውን በባርነት አሳልፈዋል። ከዚያም ያለጥፋታቸው ለ40 ዓመት ያህል በምድረ በዳ ተንከራተዋል። እስራኤላውያን ኢዮብ ስለደረሰበት መከራና በኋላ ስላገኘው በረከት የሚያውቁ ከሆነ ይህ ታሪክ ረድቷቸው መሆን አለበት፤ እነሱም ሆኑ ዘሮቻቸው የመከራ መንስኤ ማን እንደሆነ ከዚህ ታሪክ መገንዘብ ይችላሉ። በተጨማሪም አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ እንዲሁም የሰው ልጆችን ንጹሕ አቋምና ታማኝነት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት በተሻለ ሁኔታ መገንዘብ ይችሉ ነበር።
ለበርካታ ዘመናት በግብፅ በባርነት የቆዩት እስራኤላውያን ከጊዜ በኋላ ከኢዮብ ታሪክ ትምህርት አግኝተው መሆን አለበት፤ እኛም ትምህርት ማግኘት እንችላለን (አንቀጽ 6ን ተመልከት)
7-8. የኢዮብ መጽሐፍ መከራ ሲደርስብን የሚረዳን እንዴት ነው? ተሞክሮ ተናገር።
7 እኛስ ምን ጥቅም እናገኛለን? የሚያሳዝነው፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙዎች ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገር የሚያጋጥማቸው ለምን እንደሆነ መረዳት ባለመቻላቸው በአምላክ ላይ እምነት አጥተዋል። በሩዋንዳ የምትኖረውን የሄዘልንb ተሞክሮ እንመልከት። ልጅ እያለች በአምላክ ታምን ነበር። ሆኖም ነገሮች ተቀየሩ። ወላጆቿ ስለተፋቱ የሚያሳድጋት እንጀራ አባቷ ነበር፤ እሱ ደግሞ ይበድላት ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለች ተገዳ ተደፈረች። ማጽናኛ ለማግኘት ወደ አምልኮ ቦታ ብትሄድም የፈለገችውን ማጽናኛ ማግኘት አልቻለችም። በኋላም ሄዘል ለአምላክ ደብዳቤ ጻፈች። ደብዳቤው እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ሆይ፣ ወደ አንተ ጸለይኩ፤ ጥሩ ለማድረግ ሞከርኩ፤ አንተ ግን በመልካም ፋንታ ክፉ መለስክልኝ። ከዚህ በኋላ አንተን ትቼ የሚያስደስተኝን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ወስኛለሁ።” እንደ ሄዘል ለሚደርስባቸው መከራ ተጠያቂው አምላክ እንደሆነ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች በጣም ያሳዝኑናል!
8 እኛ ግን ለሚደርሱብን መከራዎች ተጠያቂው አምላክ ሳይሆን ሰይጣን እንደሆነ ከኢዮብ መጽሐፍ ትምህርት አግኝተናል። በተጨማሪም መከራ የሚደርስባቸው ሰዎች የዘሩትን እያጨዱ እንደሆነ ማሰብ እንደሌለብን ተምረናል። ቅዱሳን መጻሕፍት “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ባልጠበቅነው ሰዓት ማናችንንም ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ ይናገራሉ። (መክ. 9:11፤ ኢዮብ 4:1, 8) በተጨማሪም የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በታማኝነትና በጽናት ስንወጣ ይሖዋ ለሰይጣን ስድብ መልስ መስጠት እንደሚችል ተምረናል። ይህም ለስሙ ጥብቅና ለመቆም ያስችለናል። (ኢዮብ 2:3፤ ምሳሌ 27:11) የተማርነውን ነገር አቅልለን አንመለከተውም። ይህ ትምህርት እኛም ሆንን የምንወዳቸው ሰዎች መከራ የሚደርስብን ለምን እንደሆነ እውነቱን እንድናውቅ አስችሎናል። ከጊዜ በኋላ ሄዘል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ለደረሰባት መከራ ተጠያቂው አምላክ እንዳልሆነ አወቀች። እንዲህ ብላለች፦ “በድጋሚ ለአምላክ ልባዊ ጸሎት አቀረብኩ። ‘ትቼሃለሁ’ ብለውም እሱን መተው እንደማልፈልግ ለይሖዋ ነገርኩት። እንደዚያ ያልኩት እሱን በትክክል ስለማላውቀው ነበር። አሁን ግን ይሖዋ እንደሚወደኝ ተገንዝቤያለሁ። በስተ መጨረሻ እውነተኛ ደስታና እርካታ አግኝቻለሁ።” አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ በማወቃችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! አሁን ደግሞ የኢዮብ ታሪክ መከራ ሲደርስብን በግለሰብ ደረጃ እንዴት እንደሚረዳን እስቲ እንመልከት።
የኢዮብ ታሪክ እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው?
9. ኢዮብ የነበረበትን ሁኔታ ግለጽ። (ያዕቆብ 5:11)
9 ኢዮብ የነበረበትን ሁኔታ ለማሰብ ሞክር። ሰውነቱን ቁስል ወርሶት አመድ ላይ ብቻውን ተቀምጧል። ከባድ ሥቃይ ውስጥ ነው። በበሽታው የጠቆረው ቆዳው ከመነመነው ሰውነቱ ላይ ተቀርፎ እየተነሳ ነው። ኢዮብ ምንም ነገር ለማድረግ አቅም አልነበረውም። በገል ሰውነቱን እያከከ ብሶቱን ያሰማል። ሆኖም ኢዮብ ሥቃዩን ችሎ ከመኖር ባለፈ እየጸና ነበር። (ያዕቆብ 5:11ን አንብብ።) ታዲያ ኢዮብን እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው?
10. ኢዮብ ከይሖዋ ጋር የነበረው ዝምድና ምን ዓይነት ነበር? አብራራ።
10 ኢዮብ ስሜቱን አውጥቶ ለይሖዋ ተናግሯል። (ኢዮብ 10:1, 2፤ 16:20) ለምሳሌ ምዕራፍ 3 ላይ ስለደረሰበት መከራ በምሬት እንደተናገረ እናነባለን። ኢዮብ መከራውን ያመጣበት ይሖዋ እንደሆነ አስቦ ነበር። ከዚያም ኢዮብ ለሦስቱ ጓደኞቹ መልስ ሲሰጥ ንጹሕ አቋሙን እንደጠበቀ በመግለጽ ተከራክሯል፤ እንዲያውም አብዛኛው ንግግሩ ይሖዋ ላይ ያነጣጠረ ነበር። ኢዮብ የተናገረው ነገር ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ራሱን ከአምላክ በላይ ጻድቅ አድርጎ እንደቆጠረ ይጠቁማል። (ኢዮብ 10:1-3፤ 32:1, 2፤ 35:1, 2) ሆኖም የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ባደረገው ጥረት አንዳንድ ጊዜ ‘እንዳመጣለት’ እንደተናገረ እሱ ራሱ አምኖ ተቀብሏል። (ኢዮብ 6:3, 26) በምዕራፍ 31 ላይ ኢዮብ አምላክ ከክሱ ነፃ እንዲያደርገው እንደሚፈልግ ተናግሯል። (ኢዮብ 31:35) እርግጥ ነው፣ ኢዮብ ለደረሰበት መከራ መንስኤው ምን እንደሆነ አምላክ በቀጥታ እንዲነግረው መጠየቁ ስህተት ነበር።
11. ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በተመለከተ ለተናገረው ነገር ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ?
11 ታሪኩን መለስ ብለን ስናየው፣ ኢዮብ በዚህ መልኩ የተናገረው ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና ስለነበረውና እሱ ፍትሐዊ ፍርድ እንደሚሰጠው ስለተማመነ መሆኑን እንረዳለን። በኋላም ይሖዋ በአውሎ ነፋስ ውስጥ ለኢዮብ መልስ ሲሰጠው ኢዮብ መከራ የደረሰበት ለምን እንደሆነ በዝርዝር አልነገረውም። እንዲሁም ኢዮብ ስሜቱን በመግለጹና ‘ንጹሕ ነኝ’ በማለቱ አላወገዘውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ኢዮብን ልክ እንደ አባት አስተምሮታል። ደግሞም ኢዮብን ለመርዳት ይህ የተሻለው መንገድ ነው። በውጤቱም ኢዮብ ምንም እንደማያውቅ በትሕትና አምኖ ተቀብሏል፤ እንዲሁም በችኮላ በመናገሩ ንስሐ ገብቷል። (ኢዮብ 31:6፤ 40:4, 5፤ 42:1-6) ይህ ዘገባ እስራኤላውያንን ሊጠቅማቸው ይችል የነበረው እንዴት ነው? እኛስ በዛሬው ጊዜ ምን ትምህርት እናገኛለን?
12. እስራኤላውያን ከኢዮብ ታሪክ ምን ጥቅም ሊያገኙ ይችሉ ነበር?
12 ይህ ታሪክ እስራኤላውያንን ሊጠቅማቸው ይችል የነበረው እንዴት ነው? እስራኤላውያን በኢዮብ ላይ ከደረሰው ነገር መማር ይችሉ ነበር። የሙሴን ምሳሌ እንመልከት። የእስራኤል ብሔር መሪ በሆነበት ወቅት በርካታ ፈተናዎችንና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን በጽናት መቋቋም አስፈልጎታል። በይሖዋ ላይ ከሚያጉረመርሙት ዓመፀኛ እስራኤላውያን በተለየ መልኩ ሙሴ የሚያሳስቡትን ነገሮች ለይሖዋ ይነግር ነበር። (ዘፀ. 16:6-8፤ ዘኁ. 11:10-14፤ 14:1-4, 11፤ 16:41, 49፤ 17:5) ሙሴ እርማት በተሰጠው ጊዜም መጽናት አስፈልጎታል። ለምሳሌ እስራኤላውያን በቃዴስ ሰፍረው በነበረበት ወቅት ‘በከንፈሮቹ በችኮላ በመናገር’ የይሖዋን ስም ሳያከብር ቀርቷል፤ ይህ የሆነው በምድረ በዳ ባሳለፉት 40ኛ ዓመት ላይ ሳይሆን አይቀርም። (መዝ. 106:32, 33) በዚህም ምክንያት ይሖዋ፣ ሙሴን ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ከለከለው። (ዘዳ. 32:50-52) ይህ ተግሣጽ ሙሴን አሳዝኖት እንደነበር ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም በትሕትና ተቀብሎታል። የኢዮብ ታሪክ ከሙሴ ዘመን በኋላ የኖሩ እስራኤላውያንንም መከራ ሲያጋጥማቸው እንዲጸኑ ሊረዳቸው ይችል ነበር። ታማኝ እስራኤላውያን በኢዮብ ታሪክ ላይ ካሰላሰሉ ለይሖዋ ስሜታቸውን እንዴት መግለጽ እንደሚችሉ እንዲሁም በእሱ ፊት ራሳቸውን እጅግ ጻድቅ አድርገው መቁጠር እንደሌለባቸው ይማራሉ። በተጨማሪም የይሖዋን ተግሣጽ በትሕትና መቀበል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይማራሉ።
13. የኢዮብ ታሪክ እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው? (ዕብራውያን 10:36)
13 እኛስ ምን ጥቅም እናገኛለን? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እኛም መጽናት ያስፈልገናል። (ዕብራውያን 10:36ን አንብብ።) ለምሳሌ አንዳንዶቻችን አካላዊ ወይም ሥነ ልቦናዊ ሕመም፣ ከባድ የቤተሰብ ችግር፣ የምንወደውን ሰው በሞት ማጣት ወይም ሌላ ከባድ ፈተና አጋጥሞናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሌሎች የሚናገሩት ወይም የሚያደርጉት ነገር ያለንበትን ሁኔታ መቋቋም ይበልጥ ከባድ እንዲሆንብን ሊያደርግ ይችላል። (ምሳሌ 12:18) ሆኖም የኢዮብ መጽሐፍ ይሖዋ እንደሚሰማን በመተማመን ውስጣዊ ስሜታችንን አውጥተን ወደ እሱ መቅረብ እንደምንችል ያስተምረናል። (1 ዮሐ. 5:14) ምልጃ በምናቀርብበት ጊዜ እንደ ኢዮብ አልፎ አልፎ ‘እንዳመጣልን’ ብንናገር አይኮንነንም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ለመጽናት የሚያስችለንን ጥንካሬና ጥበብ ይሰጠናል። (2 ዜና 16:9፤ ያዕ. 1:5) ለኢዮብ እንዳደረገው ሁሉ በሚያስፈልገን መጠን እርማት ሊሰጠንም ይችላል። የኢዮብ መጽሐፍ ከይሖዋ ቃል፣ ከድርጅቱ ወይም ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ምክር ወይም ተግሣጽ በሚሰጠን ጊዜ እንዴት መጽናት እንደምንችልም ትምህርት ይሰጠናል። (ዕብ. 12:5-7) ኢዮብ የተሰጠውን እርማት በትሕትና መቀበሉ ጥቅም እንዳስገኘለት ሁሉ እኛም ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች ከሆንን እንጠቀማለን። (2 ቆሮ. 13:11) በእርግጥም ከኢዮብ መጽሐፍ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን እናገኛለን! አሁን ደግሞ የኢዮብን ታሪክ ሌሎችን ለመርዳት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
የኢዮብን መጽሐፍ ሌሎችን ለመርዳት ተጠቀምበት
14. መከራ የሚደርስብን ለምን እንደሆነ በአገልግሎት ላይ ለማብራራት የትኛውን ዘዴ መጠቀም ትችላለህ?
14 አገልግሎት ላይ ያገኘኸው ሰው መከራ የሚያጋጥመን ለምን እንደሆነ ጠይቆህ ያውቃል? ታዲያ ለጥያቄው ምን ምላሽ ሰጠህ? ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስ በኤደን ገነት ስለተፈጠረው ነገር የሚናገረውን ሐሳብ ጠቅሰህለት ሊሆን ይችላል። ሐሳብህን የጀመርከው፣ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር የሆነው ሰይጣን ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ውሸት በመንገር በአምላክ ላይ እንዲያምፁ እንዳደረጋቸው በመግለጽ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 3:1-6) ከዚያም አዳምና ሔዋን ካመፁ በኋላ ዓለማችን በመከራና በሞት እንደተሞላች ነገርከው። (ሮም 5:12) በመጨረሻም፣ አምላክ ሰይጣን ውሸታም መሆኑ እንዲረጋገጥና የሰው ልጆች ወደፊት በድጋሚ ፍጹማን እንደሚሆኑ የሚገልጸው ምሥራች እንዲሰበክ ሲል በቂ ጊዜ እንዲያልፍ እንደፈቀደ አብራራህለት። (ራእይ 21:3, 4) ይህ፣ ግለሰቡ ያነሳውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ግሩም ዘዴ ነው፤ ደግሞም መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።
15. መከራ የሚደርስብን ለምን እንደሆነ ለማስረዳት የኢዮብን ታሪክ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
15 ይህን ጥያቄ መመለስ የምትችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ የኢዮብን ታሪክ በመጠቀም ነው። በመጀመሪያ ግለሰቡ እንዲህ ያለ ጥሩ ጥያቄ በመጠየቁ ልታመሰግነው ትችላለህ። ከዚያም ኢዮብ የተባለ ታማኝ ሰው በደረሰበት ከባድ መከራ የተነሳ እንዲህ ያለ ጥያቄ እንዳነሳ ልትነግረው ትችላለህ። እንዲያውም ኢዮብ መከራውን ያመጣበት አምላክ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። (ኢዮብ 7:17-21) የምታነጋግረው ግለሰብ፣ በጥንት ዘመን የነበሩ ሰዎችም ይህን ጥያቄ ማንሳታቸው ሊያስገርመው ይችላል። ከዚያም ኢዮብ ላይ መከራ ያመጣበት አምላክ ሳይሆን ዲያብሎስ እንደሆነ በዘዴ ልታብራራለት ትችላለህ። ሰይጣን ይህን ያደረገው ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ጥቅም ፈልገው ብቻ እንደሆነ ለማሳየት ስለፈለገ ነው። በኢዮብ ላይ መከራ ያመጣበት አምላክ ባይሆንም መከራው እንዲደርስበት ፈቅዷል፤ ይህም አምላክ የሰው ልጆች ታማኝነታቸውን መጠበቅና ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ማጋለጥ እንደሚችሉ እንደሚተማመንባቸው ያሳያል። በመጨረሻም፣ ኢዮብ ታማኝነቱን በመጠበቁ አምላክ ከጊዜ በኋላ እንደባረከው ልትገልጽለት ትችላለህ። በዚህ መንገድ፣ የመከራ መንስኤ ይሖዋ እንዳልሆነ በመግለጽ ሌሎችን ማጽናናት እንችላለን።
የኢዮብን መጽሐፍ ‘አምላክ ክፋት እንደማይሠራ’ ለሌሎች ለማስረዳት ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 15ን ተመልከት)
16. የኢዮብ መጽሐፍ መከራ እየደረሰባቸው ያሉ ሰዎችን ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
16 የኢዮብ መጽሐፍ ማሪዮ የተባለን ሰው እንዴት እንደረዳው እንመልከት። በ2021 አንዲት እህት የስልክ ምሥክርነት እየሰጠች ነበር። የመጀመሪያውን ስልክ ስትደውል ማሪዮን አገኘችው። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ካነበበችለት በኋላ አምላክ ጸሎታችንን እንደሚሰማ ብሎም የተሻለ ሕይወትና ተስፋ እንዳዘጋጀልን ነገረችው። ሐሳብ እንዲሰጥ ስትጋብዘው ማሪዮ እሷ በደወለችበት ሰዓት ራሱን ለማጥፋት ወስኖ የመጨረሻ ደብዳቤ እየጻፈ እንደነበር ነገራት። እንዲህ አላት፦ “በአምላክ አምናለሁ። ግን ዛሬ ጠዋት ራሱ አምላክ ትቶኛል ብዬ እያሰብኩ ነበር።” በቀጣይ ጊዜ ሲደዋወሉ በኢዮብ ላይ ስለደረሰው መከራ ተወያዩ። ማሪዮ ሙሉውን የኢዮብ መጽሐፍ ለማንበብ ወሰነ። በመሆኑም እህታችን የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን ሊንክ ላከችለት። ውጤቱ ምን ሆነ? ማሪዮ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተስማማ ሲሆን በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ስለሰጠው አፍቃሪ አምላክ ይበልጥ ለመማር ወሰነ።
17. ይሖዋ የኢዮብን ታሪክ በመንፈስ መሪነት ባጻፈው ቃሉ ውስጥ በማካተቱ አመስጋኝ የሆንነው ለምንድን ነው? (ኢዮብ 34:12)
17 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ የአምላክ ቃል መከራ የሚደርስባቸውን ጨምሮ ሁሉንም ሰዎች ለመርዳት የሚያስችል ታላቅ ኃይል አለው። (ዕብ. 4:12) ይሖዋ በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃሉ ላይ የኢዮብን ታሪክ በማካተቱ ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ኢዮብ 19:23, 24) የኢዮብ መጽሐፍ እንደሚያረጋግጠው “በእርግጥም አምላክ ክፋት አይሠራም።” (ኢዮብ 34:12ን አንብብ።) በተጨማሪም መጽሐፉ፣ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነና መከራ ሲደርስብን እንዴት መጽናት እንደምንችል ያስተምረናል። መከራ እየደረሰባቸው ያሉትን ለማጽናናትም ይረዳናል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ፣ ጠቃሚ ምክር መስጠት የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ከኢዮብ መጽሐፍ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመለከታለን።
መዝሙር 156 በእምነት ዓይኔ
a ኢዮብ የኖረው ታማኙ ዮሴፍ ከሞተ (1657 ዓ.ዓ.) በኋላና ሙሴ የእስራኤል ብሔር መሪ ሆኖ ከመሾሙ (1514 ዓ.ዓ. ገደማ) በፊት እንደሆነ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። በይሖዋና በሰይጣን መካከል የተደረገው ውይይት የተካሄደው እንዲሁም በኢዮብ ላይ መከራ የደረሰው በዚህ ጊዜ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም።
b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።