የጥናት ርዕስ 51
መዝሙር 132 አንድ ሆነናል
ሠርጋችሁ ይሖዋን የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
“ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን።”—1 ቆሮ. 14:40
ዓላማ
ክርስቲያን ጥንዶች በሠርጋቸው ቀን ለይሖዋ ክብር ማምጣት የሚችሉት እንዴት ነው?
1-2. ይሖዋ ለሠርግ ምን አመለካከት አለው?
ትዳር ለመመሥረት ተጫጭታችኋል? ከሆነ፣ እንኳን ደስ አላችሁ! ምናልባት ለሠርጋችሁ ብዙ ዝግጅት እያደረጋችሁ ሊሆን ይችላል። ይሖዋም በሠርጋችሁa ቀን እንድትደሰቱና የሰመረ ትዳር እንዲኖራችሁ ይፈልጋል።—ምሳሌ 5:18፤ መኃ. 3:11
2 ሠርጋችሁ ይሖዋን የሚያስከብር ሊሆን ይገባል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግ የምትችሉትስ እንዴት ነው? ይህ ርዕስ በዋነኝነት የተዘጋጀው ለመጋባት እየተዘጋጁ ላሉ ጥንዶች ነው። ሆኖም የተጠቀሱት መሠረታዊ ሥርዓቶች ሁላችንም በሠርግ ላይ ስንገኝም ሆነ ሰዎች ስለ ሠርጋቸው ሲያማክሩን ይሖዋን ማስከበር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ይረዱናል።
ሠርጋችሁ ይሖዋን የሚያስከብር መሆን ያለበት ለምንድን ነው?
3. ለሠርጋቸው እየተዘጋጁ ያሉ ክርስቲያን ጥንዶች ምን ነገር ከግምት ማስገባት አለባቸው? ለምንስ?
3 ክርስቲያን ጥንዶች ለሠርጋቸው ዝግጅት ሲያደርጉ በይሖዋ ቃል ላይ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። ለምን? ምክንያቱም የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው ይሖዋ ነው። አዳምና ሔዋን በጋብቻ እንዲጣመሩ በማድረግ የመጀመሪያውን ትዳር አቋቁሟል። (ዘፍ. 1:28፤ 2:24) በመሆኑም ለሠርጋቸው እየተዘጋጁ ያሉ ጥንዶች በመጀመሪያ ሊያሳስባቸው የሚገባው የይሖዋ አመለካከት ነው።
4. ጥንዶች በሠርጋቸው ቀን ለይሖዋ ክብር ለማምጣት የሚያነሳሳ ምን ምክንያት አላቸው?
4 ለሠርጋችሁ ቀን ስትዘጋጁ የይሖዋን አመለካከት ግምት ውስጥ ለማስገባት የሚያነሳሳችሁ ሌላም ወሳኝ ምክንያት አለ፦ ይሖዋ የሰማዩ አባታችሁና የቅርብ ወዳጃችሁ ነው። (ዕብ. 12:9) ይህ ወዳጅነታችሁ እንዲቀጥል እንደምትፈልጉ ጥርጥር የለውም። በሠርጋችሁ ቀንም ሆነ በሌላ በማንኛውም ቀን ወዳጃችሁ የሆነውን ይሖዋን የሚያሳዝን ምንም ነገር ማድረግ አትፈልጉም። (መዝ. 25:14) ይሖዋ እስካሁን ካደረገላችሁም ሆነ ወደፊት ከሚያደርግላችሁ ነገር አንጻር የሠርጋችሁ ቀን እሱን የሚያስከብር ሊሆን ይገባል ቢባል አትስማሙም?—መዝ. 116:12
ሠርጋችሁ ይሖዋን የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
5. ለመጋባት የሚያስቡ ጥንዶች ለሠርጋቸው ሲዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱስ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
5 መጽሐፍ ቅዱስ፣ የክርስቲያኖች የሠርግ ሥነ ሥርዓት ወይም ድግስ ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ዝርዝር ሕግ አይሰጥም። ስለዚህ ጥንዶች ሁኔታቸውን፣ ባሕላቸውንና የግል ምርጫቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ሠርጋቸውን ማቀድ ይችላሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ቄሳር ያወጣቸውን ሕጎችም ያከብራሉ። (ማቴ. 22:21) ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ይሖዋን ያስከብረዋል፤ እንዲሁም ያስደስተዋል። ታዲያ የትኞቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከግምት ማስገባት ይኖርባችኋል?
6. ለመጋባት የሚያስቡ ጥንዶች መንግሥት ያወጣቸውን ሕጎች ማክበር የሚጠበቅባቸው ለምንድን ነው?
6 የመንግሥትን ሕግ አክብሩ። (ሮም 13:1, 2) በአብዛኞቹ አገራት ጥንዶች ከመጋባታቸው በፊት መንግሥት ያወጣቸውን አንዳንድ መሥፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። ለመጋባት የሚያስቡ ጥንዶች እነሱ በሚኖሩበት አካባቢ ያሉትን ሕጎች ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ካላችሁ የሽማግሌዎችን እርዳታ ለመጠየቅ ነፃነት ይሰማችሁ።b
7. የሠርግ ሥነ ሥርዓት ምን ዓይነት መንፈስ ሊሰፍንበት ይገባል?
7 ዝግጅቱ ክብር የተላበሰ እንዲሆን አድርጉ። (1 ቆሮ. 10:31, 32) ሠርጋችሁ የዓለም መንፈስ ሳይሆን የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ለማድረግ ጥረት አድርጉ። (ገላ. 5:19-26) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው የራስነት ሥርዓት መሠረት ሠርጉ አስደሳችና ክብር የተላበሰ እንዲሆን ማድረግ የሙሽራው ኃላፊነት ነው። ሠርጉ እንዲህ ዓይነት መንፈስ እንዲሰፍንበት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የጋብቻ ንግግር በፍቅርና በአክብሮት ከቀረበ አድማጮች አምላክ ላቋቋመው የጋብቻ ዝግጅት አድናቆት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ንግግሩ አድማጮች የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ዝግጅት እንደሆነ እንዲያስታውሱ ይረዳቸዋል። በመሆኑም አብዛኞቹ ክርስቲያን ጥንዶች የሠርጋቸው ሥነ ሥርዓት ከተቻለ በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ እንዲካሄድ ይመርጣሉ። እናንተም ለሠርጋችሁ የስብሰባ አዳራሹን መጠቀም ከፈለጋችሁ በተቻለ ፍጥነት የሽማግሌዎችን አካል በደብዳቤ መጠየቅ ይኖርባችኋል።
8. የሠርጋችሁ ድግስ ክብር የተላበሰ እንዲሆን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? (ሮም 13:13)
8 ሮም 13:13ን አንብብ። ሠርጋችሁ ድግስ እንዲኖረው ከወሰናችሁ ድግሱ የዓለም መንፈስ የሚንጸባረቅበት እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ‘መረን የለቀቀ ፈንጠዝያ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ተጋባዦቹ መጠጥ ያለልክ የሚጠጡበትንና እስከ ሌሊት ድረስ የሚዘፈንበትን ግብዣ ያመለክት ነበር። እናንተም በድግሱ ላይ የአልኮል መጠጥ ለማቅረብ ከመረጣችሁ ከልክ በላይ የሚጠጣ ሰው እንዳይኖር ተገቢውን ጥንቃቄ አድርጉ።c ሙዚቃ የሚኖር ከሆነ የድምፁ መጠን ተጋባዦቻችሁ እንዳይጨዋወቱ የሚያግድ መሆን የለበትም። ማንም ሰው እንዳይሰናከል የሙዚቃውን ዓይነትና ግጥሙን በጥንቃቄ ገምግሙ።
9. በሠርጉ ሥነ ሥርዓት ላይ ለየት ያለ ነገር የሚቀርብ ከሆነ የሚጋቡት ጥንዶች ምን ነገር ከግምት ማስገባት ይኖርባቸዋል?
9 በአንዳንድ አካባቢዎች የሠርጉ ድግስ ላይ የሙሽሮች ቤተሰቦችና ጓደኞች ተነስተው አጭር ሐሳብ ይናገራሉ፤ ወይም ደግሞ በፕሮግራሙ ላይ አንዳንድ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች ይታያሉ። እንዲህ ያሉ ዝግጅቶች ለሠርጉ ድምቀት ሊጨምሩለት ይችላሉ። ሆኖም ዝግጅቱ ላይ የሚቀርቡት ነገሮች የሚያንጹ መሆን ይኖርባቸዋል። (ፊልጵ. 4:8) እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘የሚቀርበው ነገር ለሌሎች አክብሮት እንዳለን ያሳያል? ለጋብቻ ዝግጅትስ አክብሮት እንዳለን የሚያሳይ ነው?’ ከሁሉም በላይ ደግሞ ‘ለይሖዋ ክብር ያመጣል?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ሐሳብ የሚሰጡት ሰዎች የሚያስቅ ነገር መናገራቸው ምንም ችግር ባይኖረውም ተገቢ ያልሆነ ነገር ከመናገር መቆጠባቸው አስፈላጊ ነው፤ ለምሳሌ ከፆታ ጋር የተያያዙ ቀልዶችን መቀለድ አይኖርባቸውም። (ኤፌ. 5:3) ሐሳብ የሚሰጡት ቤተሰቦቻችሁ ወይም ጓደኞቻችሁ ምን ዓይነት ነገር መናገር እንደሌለባቸው ማወቃቸውን አረጋግጡ።
10. ለመጋባት የሚያስቡ ጥንዶች ለሠርጋቸው ሲዘጋጁ ልከኛ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው? (1 ዮሐንስ 2:15-17)
10 ልከኛ ሁኑ። (1 ዮሐንስ 2:15-17ን አንብብ።) ይሖዋ አገልጋዮቹ ወደ ራሳቸው ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ከመሳብ ይልቅ እሱን ለማስከበር ጥረት ሲያደርጉ ይደሰታል። ስለዚህ ልከኛ የሆኑ ክርስቲያኖች በሠርጋቸው ላይ ከልክ ያለፈ ገንዘብ በማውጣት “ኑሮዬ ይታይልኝ” ከማለት ይቆጠባሉ። ሠርጋችሁ ቀለል ያለ እንዲሆን ማድረጋችሁ የሚጠቅማችሁ እንዴት ነው? በኖርዌይ የሚኖር ማይክ የተባለ ወንድም ያገኘውን ዓይነት ጥቅም ታገኙ ይሆናል። እንዲህ ብሏል፦ “ዕዳ ውስጥ ስላልገባን በአቅኚነት ማገልገላችንን መቀጠል ችለናል። ሠርጋችን ቀለል ያለ ቢሆንም አስደሳችና የማይረሳ ነበር።” በሕንድ የምትኖረው ታቢታ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከብዙ ጭንቀት መዳን ችለናል። ሠርጋችንን ቀላል ማድረጋችን የሚያሳስቡንም ሆነ የሚያጋጩን ነገሮች ትንሽ እንዲሆኑ አድርጓል።”
በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሠርጋቸው ልከኛ፣ አስደሳችና የማይረሳ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ (አንቀጽ 10-11ን ተመልከት)
11. ሙሽሮች በሠርጋቸው ቀን አለባበሳቸውና አጋጌጣቸው ምን ዓይነት ሊሆን ይገባል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
11 በሠርጋችሁ ቀን ምን እንደምትለብሱ ወስናችኋል? በዚያ ቀን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አምሮባችሁ መታየት እንደምትፈልጉ ግልጽ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ሙሽሮች በሠርጋቸው ዕለት ለአለባበሳቸውና ለአጋጌጣቸው ትልቅ ትኩረት ይሰጡ ነበር። (ኢሳ. 61:10) በሠርጋችሁ ቀን የምትለብሱት ልብስ በሌሎች ቀናት ከምትለብሷቸው ልብሶች የተለየ እንደሆነ እሙን ነው፤ ሆኖም ይህ ሲባል ልብሳችሁ የሌላውን ጊዜ ያህል ልከኛ መሆን አያስፈልገውም ማለት አይደለም። (1 ጢሞ. 2:9) በሠርጋችሁ ቀን ትልቁን ቦታ የሚይዘው ልብሳችሁም ሆነ ሌላ ቁሳዊ ነገር መሆን የለበትም።—1 ጴጥ. 3:3, 4
12. ለመጋባት የሚያስቡ ጥንዶች በአካባቢያቸው ከተለመዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶች መራቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?
12 ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆኑ ልማዶች ራቁ። (ራእይ 18:4) የምንኖረው በሰይጣን ዓለም ውስጥ ስለሆነ ብዙዎቹ ሠርጎች ከሐሰት ሃይማኖት፣ ከመናፍስታዊ ድርጊቶችና ከአጉል እምነቶች ጋር የተያያዙ ልማዶች ይታዩባቸዋል። ይሖዋ እንዲህ ካሉት ርኩስ ነገሮች እንድንርቅ በግልጽ አስጠንቅቆናል። (2 ቆሮ. 6:14-17) በአካባቢያችሁ አጠያያቂ የሆኑ ልማዶችና ባሕሎች ካሉ በሠርጋችሁ ውስጥ ምን እንደምታካትቱ ከመወሰናችሁ በፊት የእነዚህን ልማዶች አመጣጥና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መርምሩ።
13. ሙሽሮች ስጦታ ሲሰጣቸው የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበር የሚችሉት እንዴት ነው?
13 በምትኖሩበት አካባቢ፣ እንግዶቹ ለሙሽሮቹ ስጦታ መስጠታቸው የተለመደ ነው? የእንግዶቹ የኑሮ ሁኔታ በሚሰጡት ስጦታ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች ለሌሎች እንዲሰጡ ይበረታታሉ፤ ይህን ማድረጋቸውም ደስታ ያስገኝላቸዋል። (ምሳሌ 11:25፤ ሥራ 20:35) ሆኖም እንግዶቻችን የግድ ስጦታ መስጠት እንዳለባቸው እንዲሰማቸው ወይም ውድ ስጦታ ባለመስጠታቸው እንዲሳቀቁ ማድረግ አይኖርብንም። ሰዎች ለሚሰጡን የትኛውም ዓይነት ስጦታ አመስጋኝ በመሆን እንዲሁም ከልባቸው ተነሳስተው አቅማቸው የፈቀደውን ነገር እንዲሰጡ በመፍቀድ ይሖዋን መምሰል እንችላለን።—2 ቆሮ. 9:7
ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ማስቀረትና መቋቋም የምትችሉት እንዴት ነው?
14. አንዳንድ ሙሽሮች ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?
14 ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ ሠርግ ለማዘጋጀት ስትሞክሩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ። ለምሳሌ ሠርጋችሁ ቀለል ያለ እንዲሆን ማድረግ ከባድ ሊሆንባችሁ ይችላል። በሰለሞን ደሴቶች የሚኖረው ቻርሊ እንዲህ ብሏል፦ “በሠርጋችን ድግስ ላይ ማንን እንጋብዝ የሚለውን መወሰን በጣም ከብዶን ነበር። ብዙ ጓደኞች አሉን፤ በእኛ ባሕል ደግሞ ሁሉም ሰው በሠርጉ ድግስ ላይ እንደሚጋበዝ ይጠብቃል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ታቢታ እንዲህ ብላለች፦ “እኔ በምኖርበት አካባቢ በጣም ትልቅ ድግስ ማዘጋጀት የተለመደ ነው። ወላጆቻችን 100 ሰው ብቻ ለመጋበዝ ያደረግነውን ውሳኔ ለመቀበል ጊዜ ወስዶባቸው ነበር።” በሕንድ የምትኖረው ሣራ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ሰዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ለሚሰጣቸው ቦታ ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ። የአጎቶቼና የአክስቶቼ ልጆች ሲያገቡ ድል ያለ ድግስ ተደግሶ ነበር፤ ስለዚህ እኔም ከእነሱ የበለጠ ትልቅ ድግስ እንድደግስ ጫና ተደረገብኝ።” እነዚህንም ሆነ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመወጣት ምን ሊረዳችሁ ይችላል?
15. ለሠርጋችሁ ዕቅድ ስታወጡ መጸለያችሁ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ለሠርጋችሁ ስትዘጋጁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ። ያጋጠማችሁን ማንኛውንም ችግር ወይም የሚሰማችሁን ስሜት ለይሖዋ በጸሎት መንገር ትችላላችሁ። (ፊልጵ. 4:6, 7) ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ፣ ስትጨነቁ ለመረጋጋትና ድፍረት በሚያስፈልጋችሁ ጊዜ ድፍረት ለማሳየት እንዲረዳችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። (1 ጴጥ. 5:7) ጸሎታችሁ መልስ እንዳገኘ ስትመለከቱ በይሖዋ ላይ ያላችሁ እምነት ያድጋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ታቢታ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና እጮኛዬ እርስ በርሳችንም ሆነ ከቤተሰባችን አባላት ጋር አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል ብለን እንጨነቅ ነበር። በመሆኑም ስለ ሠርጋችን በተወያየን ቁጥር በጸሎት እንጀምር ነበር። የይሖዋን እርዳታ አይተናል፤ እንዲሁም በተረጋጋ ሁኔታ መወያየት ችለናል።”
16-17. ለሠርጋችሁ ስትዘጋጁ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት የሚረዳችሁ እንዴት ነው?
16 ሐሳባችሁን በግልጽና በደግነት አስረዱ። (ምሳሌ 15:22) ሠርጋችሁን በተመለከተ ብዙ ውሳኔዎችን አብራችሁ ማድረግ ይጠበቅባችኋል። ይህም የሠርጋችሁን ቀን፣ ያላችሁን በጀት፣ የሚጋበዙትን ሰዎች ዝርዝር እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ያካትታል። ውሳኔ ከማድረጋችሁ በፊት ያሏችሁን አማራጮች አንድ ላይ ሆናችሁ ገምግሙ፤ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር በተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ባገኛችሁት ምክር ላይ ተወያዩ። የግል ምርጫችሁን ስትገልጹ ደግና ምክንያታዊ ሁኑ፤ እንዲሁም ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ’ ብላችሁ ድርቅ አትበሉ። የቅርብ የቤተሰባችሁ አባላት፣ ለምሳሌ ወላጆቻችሁ ምክንያታዊ የሆነ ጥያቄ ካቀረቡ ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ ጥረት አድርጉ። ሠርጋችሁ ለእነሱም ቢሆን ልዩ ቀን ነው። የጠየቋችሁን ነገር ማድረግ ካልቻላችሁ በደግነት ምክንያታችሁን አስረዷቸው። (ቆላ. 4:6) ዋነኛ ዓላማችሁ ሠርጋችሁ አስደሳችና ይሖዋን የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ እንደሆነ ለቤተሰባችሁ አባላት በግልጽ ንገሯቸው።
17 በተለይ ወላጆቻችሁ እውነት ውስጥ ካልሆኑ ፍላጎታችሁን ለእነሱ ማስረዳት ከባድ ሊሆንባችሁ ይችላል፤ ሆኖም በዚህ ረገድ ሊሳካላችሁ ይችላል። በሕንድ የሚኖር ሳንቶሽ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ቤተሰቦቻችን በሠርጋችን ላይ የሂንዱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን እንድናካትት ፈልገው ነበር። እኔና እጮኛዬ ውሳኔያችንን ለእነሱ ለማስረዳት ረጅም ጊዜ ወስዶብናል። ይሖዋን የሚያሳዝን እስካልሆነ ድረስ አንዳንድ ጥያቄዎቻቸውን ለማስተናገድ ተስማማን። ለምሳሌ በድግሱ ላይ እኛ የምንፈልገውን ትተን እነሱ የሚፈልጉትን ምግብ አቀረብን። እንዲሁም የእነሱን ስሜት ለማክበር ስንል ዘፈንም ሆነ ጭፈራ እንዳይኖር አደረግን።”
18. በሠርጋችሁ ቀን ሁሉም ነገር በታሰበው መንገድ እንዲሄድ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? (1 ቆሮንቶስ 14:40) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
18 በዝርዝር ዕቅድ አውጡ። በደንብ ከተደራጃችሁ በሠርጋችሁ ቀን የሚሰማችሁ ጭንቀት መቀነሱ አይቀርም። (1 ቆሮንቶስ 14:40ን አንብብ።) በታይዋን የሚኖረው ዌይን እንዲህ ብሏል፦ “ከሠርጋችን ከጥቂት ቀናት በፊት፣ በሠርጉ ቀን ሥራ ከተሰጣቸው ሰዎች ጋር አጠር ያለ ስብሰባ አደረግን። ባወጣናቸው ዕቅዶች ላይ ተወያየን፤ እንዲሁም ሁሉም ነገር በታሰበው መንገድ እንዲሄድ በሠርጉ ቀን የሚከናወኑትን አንዳንድ ነገሮች ተለማመድን።” ሰዓት አክባሪ ለመሆን የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ይህም ለጋበዛችኋቸው ሰዎች አክብሮት እንዳላችሁ ያሳያል።
ጥሩ ዕቅድ ማውጣት ሠርጉ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ያስችላል (አንቀጽ 18ን ተመልከት)
19. በሠርጋችሁ ድግስ ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች ለመቆጣጠር ምን ይረዳችኋል?
19 አስቀድሞ ማሰብ ብዙ ችግሮችን ለማስቀረት ይረዳችኋል። (ምሳሌ 22:3) ለምሳሌ በአካባቢያችሁ ድንኳን ሰባሪዎች የሚበዙ ከሆነ በእናንተ ድግስ ላይ ይህ እንዳይፈጠር መከላከል የምትችሉት እንዴት እንደሆነ አስቡ። ሠርጋችሁ ምን ዓይነት እንደሚሆን እውነት ውስጥ ላልሆኑ ዘመዶቻችሁ ንገሯቸው፤ እንዲሁም ከአንዳንድ የሠርግ ልማዶች ጋር በተያያዘ ያላችሁን አመለካከት አብራሩላቸው። “የይሖዋ ምሥክሮች ሠርግ ምን ይመስላል?” የሚለውን በjw.org ላይ የሚገኘውን ርዕስ ልታሳዩአቸው ትችላላችሁ። በሠርጋችሁ ድግስ ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች ለመቆጣጠር እንዲያስችላችሁ አንድን የጎለመሰ ወንድም ‘የድግሱ አሳዳሪ’ አድርጋችሁ መመደብ ትችላላችሁ። (ዮሐ. 2:8) ከአሳዳሪው ጋር ሠርጋችሁን በተመለከተ ስላደረጋችሁት ውሳኔ በግልጽ ከተነጋገራችሁ አሳዳሪው ሠርጋችሁ ክብር የተላበሰ እንዲሆንና በታቀደው መሠረት እንዲሄድ ሊረዳችሁ ይችላል።
20. ለመጋባት የሚያስቡ ጥንዶች ስለ ሠርጋቸው ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል?
20 ለሠርግ ዝግጅት ማድረግ የሚጠይቀውን ሥራ ስታስቡ ሁኔታው ጭንቀት ሊፈጥርባችሁ ይችላል። ሆኖም ሠርጋችሁ የአንድ ቀን ጉዳይ ብቻ እንደሆነ አስታውሱ። ይሖዋን አብራችሁ በማገልገል የምታሳልፉት አስደሳች ሕይወት የሚጀምርበት ቀን ነው። ሠርጋችሁ ቀላልና ክብር የተላበሰ እንዲሆን የተቻላችሁን አድርጉ። በይሖዋ ታመኑ። የእሱን መመሪያ ከተከተላችሁ፣ መለስ ብላችሁ ስታስቡት የምትደሰቱበትና ምንም የማትጸጸቱበት የሠርግ ሥነ ሥርዓት ሊኖራችሁ ይችላል።—መዝ. 37:3, 4
መዝሙር 107 መለኮታዊው የፍቅር መንገድ
a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በብዙ ባሕሎች ውስጥ ሠርግ የሚባለው ሙሽሮቹ በአምላክ ፊት ቃል ኪዳን የሚገቡበት ሥነ ሥርዓት ነው። ከዚያ በኋላ ድግስ ሊኖረው ይችላል። በአንዳንድ ባሕሎች ግን መደበኛ የሆነ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ወይም ድግስ የለም። በእነዚህ ባሕሎች ውስጥ ያሉ ሙሽሮችም በሠርጋቸው ቀን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማክበራቸው ይጠቅማቸዋል።
b ክርስቲያኖች ከጋብቻ ጋር ለተያያዙ የመንግሥት ሕጎች ያላቸውን አመለካከት ይበልጥ ለማወቅ በጥቅምት 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ክቡር የሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።
c የአልኮል መጠጥ ማቅረብ ይኖርብኝ ይሆን? የሚለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከቱ።