የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es25
  • ሚያዝያ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሚያዝያ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 1
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 2
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 3
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 4
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 5
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 6
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 7
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 10
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 11
  • የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
    ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
    ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 12
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 13
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 14
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 15
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 17
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 18
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 19
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 20
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 21
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 22
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 24
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 25
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 26
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 27
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 28
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 29
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2025
es25

ሚያዝያ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 1

ያደረግክብኝ ነገር ምንድን ነው? . . . ለምን አታለልከኝ?—ዘፍ. 29:25

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች ያልጠበቋቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። ያዕቆብን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አባቱ የይሖዋ አምላኪ ከሆነው ከላባ ልጆች መካከል ሚስት እንዲያገባ አዘዘው፤ ይሖዋ አትረፍርፎ እንደሚባርከውም ነገረው። (ዘፍ. 28:1-4) ስለዚህ ያዕቆብ ትክክለኛውን ነገር አደረገ። ከከነዓን ምድር ወጥቶ ወደ ላባ ቤት ተጓዘ። ላባ ሊያና ራሔል የተባሉ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት። ያዕቆብ ታናሽየዋን የላባ ልጅ ማለትም ራሔልን ስለወደዳት እሷን ለማግባት ሲል ሰባት ዓመት አባቷን ለማገልገል ተስማማ። (ዘፍ. 29:18) ሆኖም ሁኔታዎች ያዕቆብ ባሰበው መንገድ አልሄዱም። ላባ ታላቋን ልጁን ሊያን በመዳር ያዕቆብን አታለለው። እርግጥ ከሳምንት በኋላ ራሔልን እንዲያገባ ፈቀደለት፤ ሆኖም በምላሹ ለሰባት ተጨማሪ ዓመታት እንዲያገለግለው ጠየቀው። (ዘፍ. 29:26, 27) ላባ ከሥራው ጋር በተያያዘም ያዕቆብን አጭበርብሮታል። በድምሩ ላባ ያዕቆብን ለ20 ዓመት በዝብዞታል!—ዘፍ. 31:41, 42፤ w23.04 15 አን. 5

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 2

ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ።—መዝ. 62:8

ማጽናኛና መመሪያ ማግኘት የምንችለው ከማን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ እናውቀዋለን። ወደ ይሖዋ አምላክ በጸሎት መቅረብ እንችላለን። ይሖዋ ይህን እንድናደርግ ጋብዞናል። ‘ዘወትር እንድንጸልይ’ ይፈልጋል። (1 ተሰ. 5:17) በነፃነት በመጸለይ ስለ የትኛውም የሕይወታችን ዘርፍ መመሪያ ልንጠይቀው እንችላለን። (ምሳሌ 3:5, 6) ይሖዋ ለጋስ አምላክ ስለሆነ ስንት ጊዜ መጸለይ እንደምንችል ገደብ አላስቀመጠም። ኢየሱስ፣ ይሖዋ ጸሎትን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ያውቃል። ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት አባቱ የታማኝ ወንዶችንና ሴቶችን ጸሎት ሲመልስ ተመልክቷል። ለምሳሌ ይሖዋ ሐና፣ ዳዊት፣ ኤልያስና ሌሎች ያቀረቡትን ልባዊ ጸሎት ሲመልስ ኢየሱስ ከአባቱ ጎን ነበር። (1 ሳሙ. 1:10, 11, 20፤ 1 ነገ. 19:4-6፤ መዝ. 32:5) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ አዘውትረው እንዲጸልዩና ጸሎታቸው እንደሚመለስ እርግጠኛ እንዲሆኑ ያስተማራቸው ለዚህ ነው።—ማቴ. 7:7-11፤ w23.05 2 አን. 1, 3

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 3

ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤ በይሖዋ የሚታመን ግን ጥበቃ ያገኛል።—ምሳሌ 29:25

ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ ይሖዋን ይፈራ ነበር። የኤልዛቤል ልጅ ጎቶልያ በጉልበት ሥልጣን በያዘችበት ወቅት ዮዳሄ ታማኝነቱን አሳይቷል። ጎቶልያ እጅግ በጣም ጨካኝና የሥልጣን ጥመኛ ከመሆኗ የተነሳ የንጉሣውያኑን ቤተሰብ በሙሉ ማለትም የገዛ የልጅ ልጆቿን ለመግደል ሞክራለች! (2 ዜና 22:10, 11) ከልጅ ልጆቿ አንዱ የሆነው ኢዮዓስ፣ የዮዳሄ ሚስት የሆነችው ዮሳቤት ስለደበቀችው ተረፈ። እሷና ባለቤቷ ልጁን ደብቀው አሳደጉት። በዚህ መንገድ ዮዳሄና ዮሳቤት የዳዊት ሥርወ መንግሥት እንዳይቋረጥ አድርገዋል። ዮዳሄ ለይሖዋ ታማኝ ነበር፤ እንዲሁም ጎቶልያን በመፍራት አልተሸበረም። ኢዮዓስ ሰባት ዓመት ሲሆነው ዮዳሄ ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት በድጋሚ አሳየ። አንድ ዕቅድ አወጣ። ዕቅዱ ከተሳካ የዳዊት ሕጋዊ ወራሽ የሆነው ኢዮዓስ ንጉሥ ይሆናል። ካልተሳካለት ግን ዮዳሄ ሕይወቱን ማጣቱ አይቀርም። ይሖዋ ስለባረካቸው ዕቅዱ ተሳካ። w23.06 17 አን. 12-13

ዓርብ፣ ሚያዝያ 4

ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና መንግሥቱንም ለወደደው እንደሚሰጥ [እወቅ]።—ዳን. 4:25

ንጉሥ ናቡከደነጾር ይህን መልእክት እንደ ዓመፅ ሊቆጥረውና ዳንኤልን ሊያስገድለው ይችል ነበር። ያም ቢሆን ዳንኤል በድፍረት መልእክቱን አድርሷል። ዳንኤል በመላ ሕይወቱ ደፋር እንዲሆን የረዳው ምን ሊሆን ይችላል? በልጅነቱ ከእናቱና ከአባቱ ምሳሌ እንደተማረ ምንም ጥያቄ የለውም። (ዘዳ. 6:6-9) ዳንኤል እንደ አሥርቱ ትእዛዛት ያሉትን የሕጉን መሠረታዊ ክፍሎች ብቻ ሳይሆን ዝርዝር ነገሮችንም ያውቅ ነበር፤ ለምሳሌ እስራኤላውያን መብላት የሚፈቀድላቸውንና የማይፈቀድላቸውን ምግብ ለይቶ ያውቃል። (ዘሌ. 11:4-8፤ ዳን. 1:8, 11-13) በተጨማሪም ዳንኤል የአምላክን ሕዝቦች ታሪክ ተምሯል፤ እስራኤላውያን የይሖዋን መሥፈርቶች ሳይከተሉ በቀሩበት ወቅት ምን እንደደረሰባቸው ያውቃል። (ዳን. 9:10, 11) ከዚህም ሌላ በሕይወት ዘመኑ ያጋጠሙት ተሞክሮዎች ይሖዋና ኃያላን መላእክቱ እንደሚደግፉት እርግጠኛ እንዲሆን አድርገውታል።—ዳን. 2:19-24፤ 10:12, 18, 19፤ w23.08 3 አን. 5-6

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 5

ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።—ምሳሌ 11:2

ርብቃ አስተዋይና ቆራጥ ሴት የነበረች ሲሆን በሕይወቷ ውስጥ በራሷ ተነሳሽነት ወሳኝ እርምጃዎችን የወሰደችባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ዘፍ. 24:58፤ 27:5-17) ያም ቢሆን ሰው አክባሪና ታዛዥ ነበረች። (ዘፍ. 24:17, 18, 65) እናንተም እንደ ርብቃ የይሖዋን ዝግጅቶች በትሕትና የምትደግፉ ከሆነ ለቤተሰባችሁም ሆነ ለጉባኤያችሁ ጥሩ ምሳሌ ትሆናላችሁ። ልክን ማወቅ ሁሉም የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሊያዳብሩት የሚገባ ባሕርይ ነው። አስቴር ልኳን የምታውቅና ፈሪሃ አምላክ ያላት ሴት ነበረች። ልኳን የምታውቅ መሆኗ የትዕቢት እርምጃ ከመውሰድ ጠብቋታል። በዕድሜ ከእሷ የሚበልጠው ዘመዷ መርዶክዮስ የሰጣትን ምክር አዳምጣለች፤ እንዲሁም በሥራ ላይ አውላዋለች። (አስ. 2:10, 20, 22) እናንተም ምክር በመጠየቅና የተሰጣችሁን ጥሩ ምክር በሥራ ላይ በማዋል ልካችሁን እንደምታውቁ ማሳየት ትችላላችሁ። (ቲቶ 2:3-5) አስቴር ልኳን እንደምታውቅ በሌላም መንገድ አሳይታለች። አስቴር “ቁመናዋ ያማረ፣ መልኳም ቆንጆ ነበር”፤ ሆኖም ወደ ራሷ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ለመሳብ አልሞከረችም።—አስ. 2:7, 15፤ w23.12 19-20 አን. 6-8

እሁድ፣ ሚያዝያ 6

አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል።—1 ዮሐ. 3:20

ይሖዋ ከመጠን ያለፈ የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማን አይፈልግም። ኃጢአታችንን ከተናዘዝን፣ ንስሐ ከገባንና ጥፋታችንን ላለመድገም ተገቢውን እርምጃ ከወሰድን ይሖዋ ይቅር እንዳለን መተማመን እንችላለን። (ሥራ 3:19) እነዚህን እርምጃዎች ከወሰድን በኋላ ይሖዋ የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማን አይፈልግም። ከመጠን ያለፈ የበደለኝነት ስሜት ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ ያውቃል። (መዝ. 31:10) በሐዘን ከተዋጥን ተስፋ ቆርጠን ለሕይወት የምናደርገውን ሩጫ ልናቋርጥ እንችላለን። (2 ቆሮ. 2:7) ከመጠን ባለፈ የበደለኝነት ስሜት ከተደቆስክ ይሖዋ በሚሰጠው እውነተኛ ይቅርታ ላይ አተኩር። (መዝ. 130:4) ይሖዋ፣ ከልባቸው ንስሐ የገቡ ሰዎችን ይቅር ስለሚልበት ሁኔታ ሲናገር “ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስታውስም” ብሏል። (ኤር. 31:34) ይህም ማለት ይሖዋ አንዴ ኃጢአትህን ይቅር ካለ በኋላ በዚያ ኃጢአት መልሶ አይጠይቅህም ማለት ነው። ቀደም ሲል የሠራኸው ስህተት በአሁኑ ጊዜ በእሱ አገልግሎት ማከናወን የምትችለውን ነገር ቢገድበው ራስህን አትውቀስ። ይሖዋ የፈጸምከውን ኃጢአት እያስታወሰ አይኖርም፤ አንተም እንዲህ ልታደርግ አይገባም። w23.08 30 አን. 14-15

ሰኞ፣ ሚያዝያ 7

ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ።—1 ቆሮ. 15:58

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የድርጅቱን መመሪያ የታዘዙ የይሖዋ ምሥክሮች የተዛባ መረጃ መስማት ከሚያስከትለው አላስፈላጊ ጭንቀት ድነዋል። (ማቴ. 24:45) ትኩረታችን ሊያርፍ የሚገባው “ይበልጥ አስፈላጊ [በሆኑት] ነገሮች” ላይ ነው። (ፊልጵ. 1:9, 10) ማዘናጊያዎች ይበልጥ ጠቃሚ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ የምናውለውን ጊዜና ትኩረት ይሻሙብናል። እንደ ምግብ፣ መጠጥ፣ መዝናኛና ሥራ የመሳሰሉት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ እንዲይዙ ከፈቀድንላቸው ማዘናጊያ ሊሆኑብን ይችላሉ። (ሉቃስ 21:34, 35) ከዚህም ሌላ ስለ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውዝግቦች የሚገልጹ ዜናዎች በየዕለቱ ይዥጎደጎዱብናል። እነዚህ ውዝግቦች ማዘናጊያ እንዲሆኑብን ልንፈቅድ አይገባም። አለዚያ በውስጣችን አንዱን ቡድን መደገፍ ልንጀምር እንችላለን። ሰይጣን የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቀምበት ዓላማ ግልጽ ነው። ትክክል የሆነውን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ማዳከም ይፈልጋል። w23.07 16-17 አን. 12-13

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8

ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።—ሉቃስ 22:19

የይሖዋ ሕዝቦች በዓመቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ቀን የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲያከብሩት በቀጥታ ያዘዘው ብቸኛው በዓል ይሄ ነው። (ሉቃስ 22:19, 20) ለኢየሱስ መሥዋዕት ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች ያስታውሰናል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) በተጨማሪም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” አጋጣሚ ይሰጠናል። (ሮም 1:12) ከዚህም ሌላ፣ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች በዚያ ዕለት የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር በሕይወት መንገድ ላይ መጓዝ እንዲጀምሩ ያነሳሳቸዋል። የመታሰቢያው በዓል ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበራችንን አንድ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነም ለማሰብ ሞክሩ። የመታሰቢያውን በዓል በጣም ከፍ አድርገን የምንመለከተው ለዚህ ነው! w24.01 8 አን. 1-3

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 9) ሉቃስ 19:29-44

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9

አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።—ዮሐ. 3:16

ይሖዋና ኢየሱስ በከፈሉት ዋጋ ላይ ይበልጥ ባሰላሰልን መጠን ለእያንዳንዳችን ያላቸው ፍቅር ይበልጥ ይገባናል። (ገላ. 2:20) ቤዛው የፍቅር ስጦታ ነው። ይሖዋ በእሱ ዘንድ በጣም ውድ የሆነውን ኢየሱስን መሥዋዕት በማድረግ እንደሚወደን አረጋግጦልናል። ይሖዋ ልጁ ለእኛ ሲል ተሠቃይቶ እንዲሞት ፈቅዷል። ይሖዋ ፍቅሩን ከመደበቅ ይልቅ እንደሚወደን በግልጽ ነግሮናል። (ኤር. 31:3) ይሖዋ ስለሚወደን ወደ ራሱ ስቦናል። (ከዘዳግም 7:7, 8 ጋር አወዳድር።) የትኛውም አካል ወይም ማንኛውም ነገር ከዚህ ፍቅር ሊለየን አይችልም። (ሮም 8:38, 39) ስለዚህ ፍቅር ስታስብ ምን ይሰማሃል? w24.01 28 አን. 10-11

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 10) ሉቃስ 19:45-48፤ ማቴዎስ 21:18, 19፤ 21:12, 13

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 10

ፍጥረት . . . በተስፋ . . . ነፃ [ይወጣል]።—ሮም 8:20, 21

ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ተስፋቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በመንፈስ የተቀባ ክርስቲያን የሆነው ወንድም ፍሬድሪክ ፍራንዝ ስለ ተስፋው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ተስፋችን እርግጠኛ ነገር ነው። የትንሹ መንጋ አባላት ለሆኑት 144,000 ሰዎች በሙሉ ከምንገምተው በላይ በሆነ መጠን ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል።” ወንድም ፍራንዝ በ1991 እንዲህ ብሏል፦ “ለዚህ ተስፋ ዋጋማነት ያለንን ከፍተኛ ግምት አላጣንም። . . . ተስፋችንን እየጠበቅን የምንቆይበት ጊዜ በረዘመ መጠን ለተስፋው ያለን አድናቆት ጨምሯል። . . . ሊጠባበቁት የሚገባ ተስፋ ነው። ተስፋችንን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ።” ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምናደርገው በሰማይም ይሁን በምድር አስደሳች የሆነ ክብራማ ተስፋ አለን። ደግሞም ተስፋችን እየተጠናከረ መሄድ ይችላል። w23.12 9 አን. 6፤ 10 አን. 8

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 11) ሉቃስ 20:1-47

ዓርብ፣ ሚያዝያ 11

የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልም።—ዕብ. 10:4

በጥንቱ የማደሪያ ድንኳን መግቢያ ላይ ለይሖዋ የእንስሳት መሥዋዕቶች የሚቀርቡበት የመዳብ መሠዊያ ነበር። (ዘፀ. 27:1, 2፤ 40:29) ይሁንና እነዚህ መሥዋዕቶች የሕዝቡን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ሊያስተሰርዩ አልቻሉም። (ዕብ. 10:1-3) በማደሪያ ድንኳኑ በየጊዜው ይቀርቡ የነበሩት የእንስሳት መሥዋዕቶች የሰው ልጆችን ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ነፃ ለሚያወጣው መሥዋዕት ጥላ ሆነው አገልግለዋል። ኢየሱስ፣ ይሖዋ ወደ ምድር የላከው ሰብዓዊ ሕይወቱን ለሰው ልጆች ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ መሆኑን ያውቅ ነበር። (ማቴ. 20:28) በመሆኑም በተጠመቀበት ወቅት ኢየሱስ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን አቀረበ። (ዮሐ. 6:38፤ ገላ. 1:4) ኢየሱስ በእሱ የሚያምኑ ሰዎችን ኃጢአት ለማስተሰረይ ወይም ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን ሕይወቱን “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል።—ዕብ. 10:5-7, 10፤ w23.10 26-27 አን. 10-11

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 12) ሉቃስ 22:1-6፤ ማርቆስ 14:1, 2, 10, 11

የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 12

አምላክ የሚሰጠው ስጦታ . . . በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።—ሮም 6:23

በራሳችን ጥረት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ መውጣት የምንችልበት ምንም መንገድ የለም። (መዝ. 49:7, 8) በመሆኑም ይሖዋ፣ ኢየሱስ ሕይወቱን ለእኛ ሲል እንዲሰጠን አደረገ፤ ይህም ይሖዋንም ሆነ ውድ ልጁን ትልቅ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ይሖዋና ኢየሱስ በከፈሉልን መሥዋዕት ላይ ባሰላሰልን መጠን ለቤዛው ያለን አድናቆት እያደገ ይሄዳል። አዳም ኃጢአት ሲሠራ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚውን አጣ፤ ልጆቹም ይህን አጋጣሚ እንዲያጡ አደረገ። ኢየሱስ፣ አዳም ያጣውን ነገር መልሶ ለመግዛት ሲል ፍጹም ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ “ምንም ኃጢአት አልሠራም፤ በአንደበቱም የማታለያ ቃል አልተገኘም።” (1 ጴጥ. 2:22) ኢየሱስ በሞተበት ወቅት ልክ እንደ አዳም ፍጹም ሰው ነበር፤ በመሆኑም ሕይወቱን መሥዋዕት በማድረግ አዳም ያጣውን ሕይወት መልሶ መግዛት ችሏል።—1 ቆሮ. 15:45፤ 1 ጢሞ. 2:6፤ w24.01 10 አን. 5-6

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 13) ሉቃስ 22:7-13፤ ማርቆስ 14:12-16 (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ሉቃስ 22:14-65

እሁድ፣ ሚያዝያ 13

ወደ ቅዱሱ ስፍራ የገባው የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የገዛ ራሱን ደም ይዞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ፤ ደግሞም ለእኛ ዘላለማዊ መዳን አስገኘልን።—ዕብ. 9:12

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ገባ። ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ ክህነትና በቤዛዊ መሥዋዕቱ አማካኝነት ያቋቋመው የንጹሕ አምልኮ ዝግጅት የላቀ መሆኑን እዚህ ላይ በግልጽ ማየት እንችላለን። በእስራኤል የነበረው ሊቀ ካህናት፣ መሥዋዕት ሆነው የቀረቡትን እንስሳት ደም ይዞ በሰው እጅ ወደተሠራው ቅድስተ ቅዱሳን ይገባ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ከየትኛውም ቦታ ይበልጥ ቅዱስ ወደሆነው ወደ ሰማይ በመግባት በይሖዋ ፊት ቀርቧል። በዚያም የፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ በአምላክ ፊት አቀረበ፤ ይህን ያደረገው ለእኛ ሲል “ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ኃጢአትን ለማስወገድ” ነው። (ዕብ. 9:24-26) ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ፣ ሁላችንም ይሖዋን በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ማምለክ እንችላለን። w23.10 28 አን. 13-14

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ሉቃስ 22:66-71

ሰኞ፣ ሚያዝያ 14

እንግዲህ . . . ያለምንም ፍርሃት ወደ ጸጋው ዙፋን እንቅረብ።—ዕብ. 4:16

ኢየሱስ በሰማይ ላይ ንጉሥና ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናት ሆኖ ስለሚጫወተው ሚና ለማሰብ ሞክር። በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ ‘የጸጋ ዙፋን’ በጸሎት መቅረብና “በሚያስፈልገን ጊዜ” ምሕረትና እርዳታ ለማግኘት መጠየቅ እንችላለን። (ዕብ. 4:14, 15) ይሖዋና ኢየሱስ ስላደረጉልን እንዲሁም እያደረጉልን ስላለው ነገር ሳናሰላስል አንድም ቀን እንዲያልፍብን ልንፈቅድ አይገባም። ለእኛ ያላቸው ፍቅር ልባችንን በጥልቅ ሊነካው እንዲሁም በአገልግሎታችንና በአምልኳችን ቀናተኞች እንድንሆን ሊያነሳሳን ይገባል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) አድናቆት ማሳየት ከምንችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ፣ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አድርጓል። የይሖዋ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” እንደሆነ ተረድቶ ነበር።—1 ጢሞ. 2:3, 4፤ w23.10 22-23 አን. 13-14

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 15) ማቴዎስ 27:62-66

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 15

ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።—ራእይ 21:4

ብዙዎቻችን ለሌሎች በምንመሠክርበት ጊዜ በገነት ውስጥ ስለሚኖረን ሕይወት የሚገልጸውን ይህን የሚያበረታታ ጥቅስ እንጠቀምበታለን። ሌሎች ሰዎች በራእይ 21:3, 4 ላይ የተጠቀሱት በረከቶች እውን እንደሚሆኑ እንዲተማመኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? እኛስ በዚህ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ይህን የሚያጽናና ተስፋ ከመስጠት ባለፈ በዚህ ተስፋ ላይ እምነት እንድንጥል የሚያነሳሱ አሳማኝ ምክንያቶችን ተናግሯል። ይሖዋ ስለ ገነት የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም የሚያረጋግጡ ምክንያቶችን በዚህ ምዕራፍ ቀጣይ ቁጥሮች ላይ ማግኘት እንችላለን። እንዲህ ይላል፦ “በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ‘እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ’ አለ። ደግሞም ‘እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት ስለሆኑ ጻፍ’ አለኝ። እንዲህም አለኝ፦ ‘እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል! እኔ አልፋና ኦሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነኝ።’”—ራእይ 21:5, 6ሀ፤ w23.11 3 አን. 3-5

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 16) ሉቃስ 24:1-12

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16

ወጣት ወንዶች ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው አሳስባቸው።—ቲቶ 2:6

አንድ ወጣት ወንድም በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ረገድ ጥሩ ምርጫ በማድረግ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዳለው ማሳየት ይችላል። ብዙውን ጊዜ፣ የፋሽኑን ዓለም የሚያራምዱት ለይሖዋ አክብሮት የሌላቸው እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር የሚከተሉ ሰዎች ናቸው። የሚመርጧቸው ሰውነት ላይ የሚጣበቁ ወይም ወንዶችን ሴት የሚያስመስሉ ልብሶች ሥነ ምግባር የጎደለውን አስተሳሰባቸውን ያንጸባርቃሉ። ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና መድረስ የሚፈልግ ወጣት ወንድም ልብስ ሲመርጥ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉ መልካም ምሳሌዎችን ከግምት ያስገባል። ራሱን እንዲህ እያለ ይጠይቃል፦ ‘የማደርገው ምርጫ ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለኝና ለሌሎች ስሜት እንደምጠነቀቅ ያሳያል? አለባበሴ የአምላክ አገልጋይ መሆኔን ሌሎች በግልጽ እንዲያዩ ያስችላል?’ (1 ቆሮ. 10:31-33) የማመዛዘን ችሎታ ያለው ወጣት በወንድሞቹና በእህቶቹ ብቻ ሳይሆን በሰማዩ አባቱ ዘንድም አክብሮት ያተርፋል። w23.12 26 አን. 7

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 17

መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ . . . አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር።—ዮሐ. 18:36

ቀደም ሲል “የደቡቡ ንጉሥ” በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ሰንዝሯል። (ዳን. 11:40) ለምሳሌ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በርካታ ወንድሞቻችን በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ታስረዋል፤ እንዲሁም አንዳንድ የይሖዋ ምሥክር ልጆች በዚሁ ምክንያት ከትምህርት ቤት ተባረዋል። ካለፉት አሥርተ ዓመታት ወዲህ ግን በዚህ ንጉሥ አገዛዝ ሥር ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ለአምላክ መንግሥት ያላቸው ታማኝነት ስውር በሆኑ መንገዶች እየተፈተነ ነው። ለምሳሌ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አንድ ክርስቲያን አንድን የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የምርጫ ተወዳዳሪ ለመደገፍ ሊፈተን ይችላል። እርግጥ ነው፣ በምርጫው ላይ ድምፅ አይሰጥ ይሆናል፤ ሆኖም በአእምሮውና በልቡ ወገን ሊይዝ ይችላል። በድርጊታችን ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰባችንና በስሜታችንም ጭምር በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ መሆናችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ዮሐ. 15:18, 19፤ w23.08 12 አን. 17

ዓርብ፣ ሚያዝያ 18

ሸክማችንን በየዕለቱ የሚሸከምልን . . . ይሖዋ ይወደስ።—መዝ. 68:19

የሕይወትን ሩጫ ስንሮጥ ‘ሽልማቱን በሚያስገኝ ሁኔታ መሮጥ’ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 9:24) ኢየሱስ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ” ሸክም ሊበዛብን እንደሚችል ተናግሯል። (ሉቃስ 21:34) ይህም ሆነ ሌሎች ጥቅሶች የሕይወትን ሩጫ ስንሮጥ ማድረግ ያለብንን አንዳንድ ማስተካከያዎች ለማወቅ ያስችሉናል። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ብርታት ስለሚሰጠን የሕይወትን ሩጫ እንደምናሸንፍ መተማመን እንችላለን። (ኢሳ. 40:29-31) በመሆኑም ፍጥነትህን አትቀንስ! ከፊቱ የሚጠብቀውን ሽልማት ለማግኘት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደረገውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ተከተል። (ፊልጵ. 3:13, 14) ይህን ሩጫ ማንም ሊሮጥልህ አይችልም፤ ግን በይሖዋ እርዳታ ሊሳካልህ ይችላል። ይሖዋ የኃላፊነት ሸክምህን እንድትሸከምና አላስፈላጊ ሸክሞችን እንድታስወግድ ሊረዳህ ይችላል። እሱ ከጎንህ ስለሆነ ሩጫውን በጽናት መሮጥና ማሸነፍ ትችላለህ! w23.08 31 አን. 16-17

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 19

አባትህንና እናትህን አክብር።—ዘፀ. 20:12

ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ወላጆቹ ኢየሩሳሌም ትተውት ሄዱ። (ሉቃስ 2:46-52) ከበዓሉ ሲመለሱ ሁሉም ልጆቻቸው አብረዋቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ የዮሴፍና የማርያም ኃላፊነት ነበር። ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ሲያገኙት ማርያም እንዳስጨነቃቸው በመግለጽ ኢየሱስን ወቀሰችው። ኢየሱስ ይህን ማድረጓ ተገቢ እንዳልሆነ መግለጽ ይችል ነበር። እሱ ግን ለወላጆቹ አጭርና አክብሮት የሚንጸባረቅበት መልስ ሰጣቸው። ዮሴፍና ማርያም ግን “ምን እያላቸው እንዳለ አልገባቸውም።” ያም ቢሆን ኢየሱስ ‘እንደ ወትሮው ይገዛላቸው ነበር።’ ወጣቶች፣ ወላጆቻችሁ ስህተት ሲሠሩ ወይም በተሳሳተ መንገድ ሲረዷችሁ እነሱን መታዘዝ ከባድ ይሆንባችኋል? በዚህ ጊዜ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? ይሖዋ ምን እንደሚሰማው አስቡ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወላጆቻችሁን መታዘዛችሁ ‘ጌታን እንደሚያስደስተው’ ይናገራል። (ቆላ. 3:20) ይሖዋ፣ ወላጆቻችሁ ሙሉ በሙሉ ላይረዷችሁ እንደሚችሉ እንዲሁም የሚያወጡት ሕግ አንዳንድ ጊዜ ምክንያታዊ ላይሆን እንደሚችል ይገባዋል። እንደዚያም ሆኖ እነሱን ለመታዘዝ ስትመርጡ ይደሰትባችኋል። w23.10 7 አን. 5-6

እሁድ፣ ሚያዝያ 20

ምክንያታዊ እንዲሆኑና ለሰው ሁሉ ገርነትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያንጸባርቁ አሳስባቸው።—ቲቶ 3:2

አብሮን የሚማር ልጅ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ግብረ ሰዶም ያላቸውን አመለካከት መቀየር እንዳለባቸው ይናገር ይሆናል። እያንዳንዱ ሰው ያለውን የራሱን ምርጫ የማድረግ መብት እንደምናከብር ለልጁ ብንገልጽለት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (1 ጴጥ. 2:17) ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መከተል ስላለው ጥቅም ልንነግረው እንችል ይሆናል። አንድ ሰው ስለ አንድ ጉዳይ ሽንጡን ገትሮ ቢከራከረን ግለሰቡ ምን ብሎ እንደሚያምን እናውቃለን ብለን ለመደምደም መቸኮል የለብንም። ለምሳሌ አብሮህ የሚማር ልጅ በአምላክ ማመን ሞኝነት እንደሆነ ቢናገርስ? ልጁ በዝግመተ ለውጥ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለውና ስለ ዝግመተ ለውጥ ብዙ እንደሚያውቅ ልታስብ ይገባል? እንደ እውነቱ ከሆነ ስለ ጉዳዩ እምብዛም አስቦበት አያውቅ ይሆናል። ምናልባትም ከ​jw.org ላይ ስለ ፍጥረት የሚናገር ሐሳብ እንዲመለከት ልትጋብዘው ትችላለህ። ከጊዜ በኋላ፣ እዚያ ላይ በሚገኝ ቪዲዮ ወይም ርዕስ ላይ ለመወያየት ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም አክብሮት በተሞላበት መንገድ መናገርህ አመለካከቱን መለስ ብሎ እንዲያጤን ሊያነሳሳው ይችላል። w23.09 17 አን. 12-13

ሰኞ፣ ሚያዝያ 21

ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ፤ አንተን ለሚጠሩ ሁሉ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን የለውም።—መዝ. 86:5

ስህተት ብንሠራም እንኳ አካሄዳችንን ለማስተካከል የቻልነውን ሁሉ እስካደረግንና በይሖዋ መታመናችንን እስከቀጠልን ድረስ ይሖዋ በእኛ መጠቀሙን እንደሚቀጥልና እንደሚባርከን መተማመን እንችላለን። (ምሳሌ 28:13) ሳምሶን ፍጹም አልነበረም። ሆኖም ከደሊላ ጋር በተያያዘ ስህተት ከሠራ በኋላም እንኳ ተስፋ ቆርጦ ይሖዋን ለማገልገል ጥረት ማድረጉን አላቆመም። ይሖዋም ተስፋ አልቆረጠበትም። በድጋሚ ሳምሶንን አስደናቂ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። ይሖዋ አሁንም የእምነት ሰው እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ከተዘረዘሩት ታማኝ ሰዎች መካከል አካትቶታል። በተለይ በምንደክምበት ጊዜ እኛን ለማጠናከር የሚጓጓ አፍቃሪ አባት የምናገለግል መሆኑን ማወቃችን ምንኛ የሚያበረታታ ነው! እንግዲያው እኛም ልክ እንደ ሳምሶን ይሖዋን “እባክህ አስበኝ፤ . . . ብርታት ስጠኝ” ብለን እንለምነው።—መሳ. 16:28፤ w23.09 7 አን. 18-19

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 22

የይሖዋን ቀን መምጣት . . . በአእምሯችሁ አቅርባችሁ [ተመልከቱ]።—2 ጴጥ. 3:12

የይሖዋን ቀን በአእምሯችን አቅርበን የምንመለከት ከሆነ ምሥራቹን ለሌሎች ለመናገር እንነሳሳለን። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ምሥራቹን መናገር ሊከብደን ይችላል። ለምን? ለጊዜውም ቢሆን ለሰው ፍርሃት እጅ እንሰጥ ይሆናል። ጴጥሮስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት ምሽት ላይ ጴጥሮስ በፍርሃት ተሸንፎ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆኑን ሳይናገር ቀርቷል፤ ይባስ ብሎም ኢየሱስን “አላውቀውም” ብሎ በተደጋጋሚ ክዶታል። (ማቴ. 26:69-75) ያም ቢሆን ጴጥሮስ ራሱ “እነሱ የሚፈሩትን እናንተ አትፍሩ፤ ደግሞም አትሸበሩ” በማለት በልበ ሙሉነት ሊናገር ችሏል። (1 ጴጥ. 3:14) ጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት የሰው ፍርሃትን ማሸነፍ እንደምንችል ዋስትና ይሰጡናል። የሰው ፍርሃትን እንድናሸንፍ ምን ይረዳናል? ጴጥሮስ “ክርስቶስን እንደ ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት” በማለት መልሱን ነግሮናል። (1 ጴጥ. 3:15) ይህም ጌታችንና ንጉሣችን ክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ሥልጣንና ኃይል ላይ ማሰላሰልን ይጨምራል። w23.09 27 አን. 6-8

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23

የፆታ ብልግናና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት . . . በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ።—ኤፌ. 5:3

“ፍሬ ቢስ በሆኑ የጨለማ ሥራዎች” ላለመጠላለፍ የምናደርገውን ትግል ልናቋርጥ አይገባም። (ኤፌ. 5:11) በተሞክሮ እንደታየው አንድ ክርስቲያን፣ ንጹሕ ያልሆነ ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር ባየ፣ በሰማ ወይም ባወራ ቁጥር ትክክል ያልሆነውን ነገር ላለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት እየተዳከመ ይሄዳል። (ዘፍ. 3:6፤ ያዕ. 1:14, 15) የሰይጣን ዓለም ሊያታልለን ይሞክራል፤ ይሖዋ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ወይም ርኩስ እንደሆነ የሚናገረው ነገር ምንም ስህተት እንደሌለበት ሊያሳምነን ይፈልጋል። (2 ጴጥ. 2:19) ሰዎችን በማምታታት ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲሳናቸው ማድረግ ዲያብሎስ ለረጅም ጊዜ ሲጠቀምበት የቆየ ዘዴው ነው። (ኢሳ. 5:20፤ 2 ቆሮ. 4:4) ብዙዎቹ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ድረ ገጾች ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጩ ነገሮችን እንድናደርግ ቢያበረታቱ ምን ይገርማል! ይህ የሰይጣን ማታለያ ነው፤ ርኩስ የሆኑ ልማዶችና የአኗኗር ዘይቤዎች ጉዳት የሌላቸው እንደሆኑ ሊያሳምነን ይፈልጋል።—ኤፌ. 5:6፤ w24.03 22 አን. 8-10

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 24

እነዚህ ሰዎች ለሰማያዊ ነገሮች ዓይነተኛ አምሳያና ጥላ የሆነ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ።—ዕብ. 8:5

እስራኤላውያን መጀመሪያ ላይ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የማደሪያ ድንኳኑን ተሸክመውት ይሄዱ ነበር። ይህን የማደሪያ ድንኳን ኢየሩሳሌም ውስጥ ቤተ መቅደስ እስከተገነባበት ጊዜ ድረስ ለ500 ዓመት ያህል ተጠቅመውበታል። (ዘፀ. 25:8, 9፤ ዘኁ. 9:22) የማደሪያ ድንኳኑ እስራኤላውያን መሥዋዕትና አምልኮ ማቅረብ የሚችሉበት ማዕከላዊ ቦታ ነበር። (ዘፀ. 29:43-46) ይሁንና የማደሪያ ድንኳኑ ለአንድ የላቀ ነገር ጥላ ሆኖ አገልግሏል። ‘ለሰማያዊ ነገሮች ጥላ’ የነበረ ሲሆን ታላቁን የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ያመለክታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ይህ ድንኳን ለአሁኑ ዘመን ምሳሌ” እንደሆነ ተናግሯል። (ዕብ. 9:9) በመሆኑም ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ተመሥርቷል ማለት ነው። ወደ ሕልውና የመጣው በ29 ዓ.ም. ነው። በዚያ ዓመት ኢየሱስ ተጠመቀ፤ እንዲሁም በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ “ታላቅ ሊቀ ካህናት” ሆኖ ማገልገል ጀመረ።—ዕብ. 4:14፤ ሥራ 10:37, 38፤ w23.10 26 አን. 6-7

ዓርብ፣ ሚያዝያ 25

ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።—ፊልጵ. 4:5

ክርስቲያኖችም በመንፈሳዊ ሁኔታ በተተከሉበት ለመጽናት እንደአስፈላጊነቱ ዘንበል ማለት ወይም ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። እንዴት? በግል ሕይወታቸው ለውጥ ሲያጋጥማቸው ከአዲሱ ሁኔታ ጋር በመላመድ እንዲሁም የሌሎችን አመለካከትና ውሳኔ በማክበር ነው። እኛ የይሖዋ አገልጋዮች ምክንያታዊ መሆን እንፈልጋለን። ትሑትና ሩኅሩኅ መሆንም እንፈልጋለን። ይሖዋ ጽኑና የማይነቃነቅ በመሆኑ “ዓለት” ተብሎ ተጠርቷል። (ዘዳ. 32:4) በሌላ በኩል ግን ምክንያታዊም ነው። ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው የማስተናገድ ችሎታ አለው። ይሖዋ በመልኩ ለፈጠራቸው የሰው ልጆች ለውጥን የመልመድ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። ምንም ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥመን እንደአመጣጡ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ ግልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ሰጥቶናል። ይሖዋ ራሱ ከተወው ምሳሌም ከሆነ ከሰጣቸው መመሪያዎች እንደምንረዳው “ዓለት” የሆነው አምላክ ምክንያታዊም ነው። w23.07 20 አን. 1-3

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 26

በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።—መዝ. 94:19

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ራሱን ከአፍቃሪ እናት ጋር አመሳስሏል። (ኢሳ. 66:12, 13) ሕፃን ልጇን በፍቅር የምትንከባከብን እናት እስቲ ለማሰብ ሞክር። የሚያስፈልገውን ነገር ትሰጠዋለች። እኛም ስንጨነቅ ይሖዋ እንደሚወደን ልንተማመን ይገባል። ስህተት በምንሠራበት ጊዜም ተስፋ አይቆርጥብንም። (መዝ. 103:8) እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ይሖዋን አሳዝነውታል፤ ሆኖም ንስሐ በሚገቡበት ጊዜ ፍቅሩን አረጋግጦላቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አንተ በዓይኔ ፊት ውድ ሆነሃልና፤ የተከበርክም ነህ፤ እኔም ወድጄሃለሁ።” (ኢሳ. 43:4, 5) የአምላክ ፍቅር አሁንም አልተቀየረም። ከባድ ስህተት ሠርተን ቢሆንም እንኳ ንስሐ ገብተን ወደ ይሖዋ ስንመለስ ፍቅሩ ያው እንደሆነ እንገነዘባለን። “ይቅርታው ብዙ” እንደሆነ አረጋግጦልናል። (ኢሳ. 55:7) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ይቅርታ ‘ከእሱ ዘንድ የመታደስ ዘመን እንደሚያመጣልን’ ይገልጻል።—ሥራ 3:19፤ w24.01 27 አን. 4-5

እሁድ፣ ሚያዝያ 27

የአምላኬ የይሖዋ እጅ በላዬ [ነበር]።—ዕዝራ 7:28

ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ በክልል ስብሰባ ላይ መገኘት እንድንችል እረፍት እንዲሰጠን ወይም በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንድንችል የሥራ ፕሮግራማችንን እንዲያስተካክልልን አለቃችንን ስንጠይቅ የይሖዋን እጅ በሕይወታችን ውስጥ የምናይበት አጋጣሚ እንፈጥራለን። በዚህ ጊዜ አስገራሚ ውጤት ልናገኝ እንችላለን። በዚህም የተነሳ በይሖዋ ላይ ያለን ትምክህት ይጠናከራል። ዕዝራ በትሕትና የይሖዋን እርዳታ ጠይቋል። ዕዝራ ኃላፊነቱ ከአቅሙ በላይ እንደሆነበት ሲሰማው በትሕትና ወደ ይሖዋ ይጸልይ ነበር። (ዕዝራ 8:21-23፤ 9:3-5) ዕዝራ በዚህ መንገድ በይሖዋ መታመኑ በዙሪያው ያሉት ሰዎችም እንዲደግፉትና እምነቱን እንዲኮርጁ አነሳስቷቸዋል። (ዕዝራ 10:1-4) እኛም ቁሳዊ ፍላጎታችንን ወይም የቤተሰባችንን ደህንነት በተመለከተ በጭንቀት ስንዋጥ በይሖዋ በመታመን ወደ እሱ መጸለይ ይኖርብናል። w23.11 18 አን. 15-17

ሰኞ፣ ሚያዝያ 28

[አብርሃም] በይሖዋ አመነ፤ አምላክም ይህን ጽድቅ አድርጎ ቆጠረለት።—ዘፍ. 15:6

ይሖዋ ጻድቅ ሆነን ለመቆጠር አብርሃም ያደረገውን እያንዳንዱን ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። እምነታችንን በሥራ ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ወደ ጉባኤያችን የሚመጡ አዲሶችን ጥሩ አድርገን መቀበል፣ የተቸገሩ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መርዳት እንዲሁም ለቤተሰቦቻችን መልካም ነገር ማድረግ እንችላለን፤ ይህም አምላክን የሚያስደስትና የእሱን በረከት የሚያስገኝ ነገር ነው። (ሮም 15:7፤ 1 ጢሞ. 5:4, 8፤ 1 ዮሐ. 3:18) እምነታችንን ማሳየት የምንችልበት ሌላው ወሳኝ መንገድ ምሥራቹን ለሌሎች በቅንዓት ማካፈል ነው። (1 ጢሞ. 4:16) ሁላችንም ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እንዲሁም የእሱ መንገዶች ከሁሉ የተሻሉ እንደሆኑ እምነት እንዳለን በሥራችን ማሳየት እንችላለን። እንዲህ ካደረግን አምላክ ጻድቅ አድርጎ እንደሚቆጥረን እንዲሁም ‘ወዳጆቼ’ ብሎ እንደሚጠራን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w23.12 2 አን. 3፤ 6 አን. 15

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 29

በርታ፤ ወንድ ሁን።—1 ነገ. 2:2

ንጉሥ ዳዊት ሊሞት በተቃረበበት ወቅት ከላይ ያለውን ሐሳብ በመናገር ሰለሞንን መክሮታል። (1 ነገ. 2:1, 3) በዛሬው ጊዜ ያሉ ሁሉም ክርስቲያን ወንዶች ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ እንዲሳካላቸው ከፈለጉ በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፎች የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር ይኖርባቸዋል። (ሉቃስ 2:52) ወጣት ወንድሞች እድገት አድርገው የጎለመሱ ክርስቲያኖች መሆናቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ክርስቲያን ወንዶች በቤተሰባቸውም ሆነ በጉባኤያቸው ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ወጣት ወንድሞች፣ ወደፊት ስለምትቀበሏቸው ኃላፊነቶች አስባችሁ እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የመግባት፣ የጉባኤ አገልጋይ የመሆን፣ በኋላም በጉባኤ ሽማግሌነት የማገልገል ግብ ይኖራችሁ ይሆናል። ትዳር መመሥረትና ልጆች መውለድ ትፈልጉም ይሆናል። (ኤፌ. 6:4፤ 1 ጢሞ. 3:1) እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስና ስኬታማ ለመሆን ክርስቲያናዊ ጉልምስና ያስፈልጋችኋል። w23.12 24 አን. 1-2

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30

ስለ ጌድዮን . . . እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል።—ዕብ. 11:32

ክርስቲያን ሽማግሌዎች የይሖዋን ውድ በጎች እንዲንከባከቡ አደራ ተሰጥቷቸዋል። እነዚህ ታታሪ ወንዶች፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን የማገልገል መብታቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። እንዲሁም መንጋውን ‘በሚገባ የሚጠብቁ እረኞች’ ለመሆን ተግተው ይሠራሉ። (ኤር. 23:4፤ 1 ጴጥ. 5:2) በጉባኤዎቻችን ውስጥ እንዲህ ያሉ ወንዶች በመኖራቸው ምንኛ አመስጋኞች ነን! ሽማግሌዎች መስፍኑ ጌድዮን ከተወው ምሳሌ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። (ዕብ. 6:12) ጌድዮን የአምላክን ሕዝቦች የታደጋቸው ከመሆኑም ሌላ እረኛ ሆኖላቸው ነበር። (መሳ. 2:16፤ 1 ዜና 17:6) እንደ ጌድዮን ሁሉ፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎችም በጣም አስቸጋሪ በሆነ ዘመን ውስጥ የአምላክን ሕዝቦች የመንከባከብ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። (ሥራ 20:28፤ 2 ጢሞ. 3:1) ጌድዮን ልክን በማወቅ፣ በትሕትናና በታዛዥነት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ኃላፊነቱን በተወጣበት ወቅት ጽናቱ ተፈትኖ ነበር። ሽማግሌዎች ሆንንም አልሆንን ሁላችንም ለሽማግሌዎች ያለንን አድናቆት ማሳደግ እንችላለን። ታታሪ የሆኑትን እነዚህን መንፈሳዊ ወንዶች ልንደግፋቸው እንችላለን።—ዕብ. 13:17፤ w23.06 2 አን. 1፤ 3 አን. 3

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ