ግንቦት
ሐሙስ፣ ግንቦት 1
ታላቅ ረሃብ [ይከሰታል]።—ሥራ 11:28
“በምድሪቱ ሁሉ ታላቅ ረሃብ” ተከስቶ በነበረበት ወቅት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ከዚህ አላመለጡም። የቤተሰብ ራሶች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር እንዴት ማቅረብ እንደሚችሉ ተጨንቀው መሆን አለበት። አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲያስቡ የነበሩ ወጣቶችስ? እነሱስ ቢሆኑ ዕቅዳቸውን ለሌላ ጊዜ ማሸጋገር እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ይሆን? ሁሉም ክርስቲያኖች ከሁኔታው አንጻር ማስተካከያ አድርገዋል። ሁኔታቸው በፈቀደ መጠን መስበካቸውን ቀጥለዋል። እንዲሁም ያሏቸውን ቁሳዊ ነገሮች በይሁዳ ለሚኖሩ የእምነት አጋሮቻቸው በደስታ አካፍለዋል። (ሥራ 11:29, 30) እርዳታ የደረሳቸው ወንድሞች የይሖዋን እጅ በቀጥታ ማየት ችለዋል። (ማቴ. 6:31-33) የእርዳታ እጃቸውን ከዘረጉላቸው የእምነት አጋሮቻቸው ጋር ይበልጥ እንደተቀራረቡ ተሰምቷቸው መሆን አለበት። መዋጮ ያደረጉ ወይም በሌላ መንገድ በእርዳታ ሥራው የተካፈሉ ክርስቲያኖች ደግሞ በመስጠት የሚገኘውን ደስታ አጣጥመዋል።—ሥራ 20:35፤ w23.04 16 አን. 12-13
ዓርብ፣ ግንቦት 2
የምንጠይቀውንም ነገር ሁሉ እንደሚሰማን ስለምናውቅ የምንጠይቀውን ነገር እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን።—1 ዮሐ. 5:15
አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ፣ አማኝ ያልሆኑ ሰዎች አገልጋዮቹን እንዲረዷቸው በማነሳሳት ጸሎታቸውን ይመልስላቸዋል። ለምሳሌ ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ከተማዋን በመጠገኑ ሥራ ለመካፈል ያቀረበውን ጥያቄ ንጉሥ አርጤክስስ እንዲመልስለት አነሳስቶታል። (ነህ. 2:3-6) በዛሬው ጊዜም እርዳታ ሲያስፈልገን ይሖዋ እሱን የማያመልኩ ሰዎችን ጭምር በማነሳሳት ሊረዳን ይችላል። የምናቀርበው ጸሎት ብዙውን ጊዜ የሚመለሰው ተአምራዊ በሚመስል መንገድ አይደለም። ሆኖም ለሰማዩ አባታችን ታማኝ ለመሆን የሚረዳንን መልስ እናገኛለን። ስለዚህ ይሖዋ ለጸሎትህ የሚሰጥህን መልስ ለማስተዋል ጥረት አድርግ። አልፎ አልፎ ቆም ብለህ ይሖዋ ጸሎትህን እየመለሰልህ ያለው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ይኖርብሃል። (መዝ. 66:19, 20) ወደ ይሖዋ በመጸለይ ብቻ ሳይሆን ለጸሎታችን የሚሰጠንን ማንኛውንም መልስ በመቀበልም ጭምር እምነት ማሳየት ይኖርብናል።—ዕብ. 11:6፤ w23.05 12 አን. 13, 15-16
ቅዳሜ፣ ግንቦት 3
አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል።—መዝ. 40:8
ለይሖዋ ራሳችንን ስንወስን እሱን ለማምለክና ፈቃዱን ለማድረግ ቃል ገብተናል። ይህን ቃላችንን ልንጠብቅ ይገባል። ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ቃል ጠብቀን መኖር ከባድ ሸክም አይደለም። ምክንያቱም ይሖዋ የፈጠረን ፈቃዱን እንድናደርግ ነው። (ራእይ 4:11) በውስጣችን መንፈሳዊ ፍላጎት አኑሯል፤ የፈጠረንም በራሱ መልክ ነው። በዚህም የተነሳ ወደ እሱ መቅረብና የእሱን ፈቃድ በማድረግ ደስታ ማግኘት እንችላለን። በተጨማሪም የአምላክን ፈቃድ ስናደርግና ልጁን ስንከተል ‘ለራሳችን እረፍት እናገኛለን።’ (ማቴ. 11:28-30) እንግዲያው ይሖዋ ባደረገልህ መልካም ነገሮችና ለወደፊቱ ባዘጋጀልህ በረከቶች ላይ በማሰላሰል ለእሱ ያለህን ፍቅር ማጠናከርህን ቀጥል። ለአምላክ ያለህ ፍቅር እያደገ ሲሄድ እሱን መታዘዝ ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። (1 ዮሐ. 5:3) ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ረገድ የተሳካለት ይሖዋ እንዲረዳው ስለጸለየና በሽልማቱ ላይ ስላተኮረ ነው። (ዕብ. 5:7፤ 12:2) አንተም እንደ ኢየሱስ፣ ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ፤ እንዲሁም አእምሮህ በዘላለም ሕይወት ተስፋህ ላይ ያተኮረ ይሁን። w23.08 27-28 አን. 4-5
እሁድ፣ ግንቦት 4
አምላክ በደግነቱ ወደ ንስሐ ሊመራህ እየሞከረ እንዳለ ሳታውቅ የደግነቱን፣ የቻይነቱንና የትዕግሥቱን ብዛት ትንቃለህ?—ሮም 2:4
ሁላችንም ትዕግሥተኛ የሆኑ ሰዎችን እናደንቃለን። ለምን? ሳይበሳጩ አንድን ነገር መጠበቅ ለሚችሉ ሰዎች አክብሮት አለን። ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ሌሎች በትዕግሥት ሲይዙን ደስ ይለናል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለመረዳት፣ ለመቀበል ወይም በሥራ ላይ ለማዋል በተቸገርንበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናን ሰው ትዕግሥት ስላሳየን አመስጋኞች ነን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ አምላክ በትዕግሥት ስለሚይዘን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ትዕግሥተኛ የሆኑ ሰዎችን ብናደንቅም እንኳ እኛ ራሳችን ትዕግሥት ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል ላይሆንልን ይችላል። ለምሳሌ በተለይ ሰዓት ረፍዶብን እያለ የትራፊክ መጨናነቅ ቢያጋጥመን ወይም ለረጅም ሰዓት ለመሰለፍ ብንገደድ ተረጋግተን መጠበቅ ሊከብደን ይችላል። ሌሎች የሚያበሳጭ ነገር ሲያደርጉብን እንቆጣ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይሖዋ ቃል የገባውን አዲስ ዓለም መጠበቅ ሊከብደን ይችላል። ይሁንና ከእነዚህ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ይበልጥ ትዕግሥተኛ መሆን ይኖርብናል። w23.08 20 አን. 1-2
ሰኞ፣ ግንቦት 5
ጌድዮን 300ዎቹን ብቻ አስቀርቶ ሌሎቹን እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ቤታቸው አሰናበታቸው።—መሳ. 7:8
ጌድዮን የይሖዋን ትእዛዝ ተከትሎ ሠራዊቱን ከ99 በመቶ በላይ ለመቀነስ ፈቃደኛ ሆኗል። ‘ይሄ ለውጥ በእርግጥ አስፈላጊ ነው? ደግሞስ ያስኬዳል?’ በማለት አስቦ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ጌድዮን ታዟል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም የይሖዋ ድርጅት በቲኦክራሲያዊ አሠራሮች ላይ ለውጥ ሲያደርግ ለውጡን ተግባራዊ በማድረግ የጌድዮንን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። (ዕብ. 13:17) ጌድዮን ፍርሃት ቢሰማውም እንዲሁም የተሰጠው ኃላፊነት አደገኛ ቢሆንም ይሖዋን ታዟል። (መሳ. 9:17) ጌድዮን፣ ይሖዋ ዋስትና ከሰጠው በኋላ የአምላክን ሕዝቦች በሚታደግበት ወቅት እሱ እንደሚረዳው እርግጠኛ ሆነ። ሥራችን በታገደበት አካባቢ የሚኖሩ ሽማግሌዎች የጌድዮንን ምሳሌ ይከተላሉ። ሊታሰሩ፣ የወንጀል ምርመራ ሊደረግባቸው፣ ሥራቸውን ሊያጡ ወይም እንግልት ሊደርስባቸው እንደሚችል ቢያውቁም በስብሰባዎችና በአገልግሎት ላይ ግንባር ቀደም ሆነው በመካፈል ድፍረት ያሳያሉ። በታላቁ መከራ ወቅት ሽማግሌዎች የሚሰጣቸው መመሪያ አደጋ ሊያስከትልባቸው የሚችል ቢሆንም እንኳ መመሪያውን ለመታዘዝ ድፍረት ያስፈልጋቸዋል። w23.06 5-6 አን. 12-13
ማክሰኞ፣ ግንቦት 6
የሚያከብሩኝን አከብራለሁ።—1 ሳሙ. 2:30
ይሖዋ የሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ መልካም ሥራ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን በቃሉ ላይ እንዲሰፍር አድርጓል። (ሮም 15:4) በተጨማሪም ዮዳሄ በሞተበት ወቅት “ከእውነተኛው አምላክና ከአምላክ ቤት ጋር በተያያዘ በእስራኤል መልካም ነገር ስላደረገ በዳዊት ከተማ ከነገሥታት ጋር” የመቀበር ልዩ መብት አግኝቷል። (2 ዜና 24:15, 16) ስለ ዮዳሄ የሚናገረው ዘገባ ሁላችንም አምላካዊ ፍርሃት እንድናዳብር ሊረዳን ይችላል። ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ምንጊዜም ንቁ ሆነው የአምላክን መንጋ በታማኝነት በመጠበቅ የዮዳሄን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። (ሥራ 20:28) አረጋውያን ይሖዋን እስከፈሩና ለእሱ ታማኝ እስከሆኑ ድረስ ዓላማውን ለመፈጸም ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ከዮዳሄ ምሳሌ መማር ይችላሉ። ወጣቶች፣ ይሖዋ ዮዳሄን የያዘበትን መንገድ በመኮረጅ ታማኝ አረጋውያንን በአክብሮት ሊይዟቸው ይገባል፤ በተለይ ይሖዋን ለረጅም ጊዜ በታማኝነት ያገለገሉ አረጋውያንን ማክበራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 16:31) ‘አመራር ለሚሰጡን’ በመታዘዝ በታማኝነት እንደግፋቸው።—ዕብ. 13:17፤ w23.06 17 አን. 14-15
ረቡዕ፣ ግንቦት 7
የጻድቅ ከንፈሮች ብዙዎችን ይመግባሉ።—ምሳሌ 10:21
በስብሰባዎች ላይ እጃችሁን ምን ያህል ጊዜ እንደምታወጡ በምትወስኑበት ወቅት አስተዋይ ሁኑ። እጃችንን አሁንም አሁንም የምናወጣ ከሆነ ሌሎች አንዴም የመመለስ አጋጣሚ ባያገኙም እንኳ መሪው በተደጋጋሚ እንዲጠይቀን ጫና ልናሳድርበት እንችላለን። ይህ ደግሞ ሌሎች እጃቸውን ለማውጣት እንዳይነሳሱ ሊያደርግ ይችላል። (መክ. 3:7) በውይይቱ ወቅት ብዙ አስፋፊዎች እጃቸውን ካወጡ የምንፈልገውን ያህል ሐሳብ የመስጠት አጋጣሚ ላናገኝ እንችላለን። አንዳንድ ጊዜም መሪው ጨርሶ ላይጠይቀን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን እናዝን ይሆናል። ሆኖም መሪው ያልጠየቀን ሆን ብሎ እንደሆነ ልናስብ አይገባም። (መክ. 7:9) የምትፈልጉትን ያህል ሐሳብ መስጠት ካልቻላችሁ ሌሎች ተሳትፎ ሲያደርጉ በጥሞና በማዳመጥ ከስብሰባው በኋላ እነሱን ለማመስገን ለምን ጥረት አታደርጉም? የምትሰጡት ምስጋና ልትሰጡ ያሰባችሁትን መልስ ያህል ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ሊያበረታታቸው ይችላል። w23.04 23-24 አን. 14-16
ሐሙስ፣ ግንቦት 8
አምላክ ሆይ፣ ልቤ ጽኑ ነው።—መዝ. 57:7
የአምላክን ቃል አጥና እንዲሁም አሰላስልበት። ሥር የሰደደ ዛፍ ጸንቶ እንደሚቆም ሁሉ እኛም እምነታችን በአምላክ ቃል ላይ ሥር የሰደደ ከሆነ ጸንተን መቆም እንችላለን። አንድ ዛፍ እያደገ ሲሄድ ይበልጥ ሥር እየሰደደ ይሄዳል። ስናጠናና ስናሰላስል እምነታችን ይጠናከራል፤ እንዲሁም የአምላክ መንገዶች ከሁሉ የተሻሉ እንደሆኑ ይበልጥ እርግጠኛ እንሆናለን። (ቆላ. 2:6, 7) ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ከይሖዋ ትምህርት፣ መመሪያና ጥበቃ እንዴት እንደተጠቀሙ ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ ሕዝቅኤል በራእይ አንድ ቤተ መቅደስ ተመልክቶ ነበር፤ መልአኩ እያንዳንዱን ነገር ሲለካ ሕዝቅኤል በትኩረት ተመልክቷል። ራእዩ የሕዝቅኤልን እምነት አጠናክሮለታል፤ ለእኛም ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣውን መሥፈርት እንዴት መጠበቅ እንደምንችል ጠቃሚ ትምህርት ይዞልናል። (ሕዝ. 40:1-4፤ 43:10-12) ጊዜ መድበን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ ነገሮች ስናጠናና ስናሰላስልባቸው እንጠቀማለን። በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ጽኑ ልብ እንዲኖረን ማድረግ እንችላለን።—መዝ. 112:7፤ w23.07 18 አን. 15-16
ዓርብ፣ ግንቦት 9
የማመዛዘን ችሎታን ጠብቅ።—ምሳሌ 3:21
መጽሐፍ ቅዱስ ወጣት ወንዶች ሊኮርጇቸው የሚችሏቸውን በርካታ ግሩም ምሳሌዎች ይዟል። በጥንት ዘመን የኖሩት እነዚህ ወንዶች አምላክን ይወዱ ነበር፤ በተጨማሪም የአምላክን ሕዝቦች ለመንከባከብ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ተወጥተዋል። በቤተሰባችሁ ወይም በጉባኤያችሁ ውስጥ ካሉ ክርስቲያን ወንዶች መካከልም ግሩም ምሳሌዎችን ማግኘት ትችላላችሁ። (ዕብ. 13:7) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወው ፍጹም ምሳሌ አለላችሁ። (1 ጴጥ. 2:21) እነዚህ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ በጥንቃቄ ስታጠኑ ያንጸባረቋቸውን ግሩም ባሕርያት ለማስተዋል ሞክሩ። (ዕብ. 12:1, 2) ከዚያም እነሱን መኮረጅ የምትችሉባቸውን መንገዶች አስቡ። የማመዛዘን ችሎታ ያለው ሰው እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ ያጤናል። ስለዚህ ይህን ችሎታ ለማዳበርና ይዛችሁ ለመቀጠል ከፍተኛ ጥረት አድርጉ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመማር እንዲሁም ያላቸውን ጥቅም በማሰብ ጀምሩ። ከዚያም እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅማችሁ ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን አድርጉ። (መዝ. 119:9) ይህ ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና የሚያደርስ ወሳኝ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 2:11, 12፤ ዕብ. 5:14፤ w23.12 24-25 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ ግንቦት 10
እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ሁኑ፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።—1 ጴጥ. 3:15
ልጆች አንድ ሰው የሚያምኑበትን ነገር በተመለከተ በጥያቄ ቢያፋጥጣቸው በገርነት መልስ መስጠት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ወላጆቻቸው ሊያሠለጥኗቸው ይችላሉ። (ያዕ. 3:13) አንዳንድ ወላጆች በቤተሰብ አምልኮ ወቅት የልምምድ ፕሮግራም ያካሂዳሉ። በትምህርት ቤት ውስጥ ሊነሱ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ይመርጣሉ፤ መልስ መስጠት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ይወያያሉ እንዲሁም ይለማመዳሉ፤ በተጨማሪም ልጆቻቸው ገርነት በሚንጸባረቅበትና ማራኪ በሆነ መንገድ መናገር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ያሠለጥኗቸዋል። ክርስቲያኖች ልምምድ ማድረጋቸው አሳማኝ የሆኑ ማስረጃዎችን ለማቅረብ እንዲሁም የሚያምኑባቸው ነገሮች ጠንካራ መሠረት እንዳላቸው ራሳቸውን ለማሳመን ይረዳቸዋል። jw.org ላይ “የወጣቶች ጥያቄ” የሚል ዓምድና ለወጣቶች የተዘጋጁ የመልመጃ ሣጥኖች አሉ። እነዚህ መልመጃዎች የተዘጋጁት ወጣቶች እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ እንዲሁም በራሳቸው አባባል መልስ ለመስጠት እንዲዘጋጁ ለመርዳት ታስበው ነው። በቤተሰብ ደረጃ ይህን ክፍል ማጥናታችን ሁላችንም ገርነት በሚንጸባረቅበትና ማራኪ በሆነ መንገድ ለእምነታችን ጥብቅና እንድንቆም ሊረዳን ይችላል። w23.09 16 አን. 10፤ 18 አን. 15-16
እሁድ፣ ግንቦት 11
ካልታከትን ጊዜው ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።—ገላ. 6:9
መንፈሳዊ ግብ ካወጣህ በኋላ ግብህ ላይ መድረስ አታግሎህ ያውቃል? ከሆነ፣ እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠመህ አንተ ብቻ አይደለህም። ለምሳሌ ፊሊፕ ይበልጥ አዘውትሮ ለመጸለይና የጸሎቱን ይዘት ለማሻሻል ፈልጎ ነበር፤ ሆኖም ለጸሎት የሚሆን ጊዜ ማግኘት ተቸግሯል። ኤሪካ በስምሪት ስብሰባዎች ላይ በሰዓቱ ለመገኘት ግብ አውጥታ ነበር፤ ሆኖም በሰዓቱ መድረስ ሊሳካላት አልቻለም። አንድ መንፈሳዊ ግብ ላይ ለመድረስ ከተቸገርክ ተስፋ ልትቆርጥ አይገባም። ቀላል ግብ ላይ መድረስ እንኳ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። አሁንም ግብህ ላይ ለመድረስ መፈለግህ በራሱ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ከፍ አድርገህ እንደምትመለከተውና ለእሱ ምርጥህን መስጠት እንደምትፈልግ ያሳያል። ይሖዋ ጥረትህን በእጅጉ ያደንቃል። ደግሞም ከአቅምህ በላይ እንድትሰጠው አይጠብቅብህም። (መዝ. 103:14፤ ሚክ. 6:8) ስለዚህ ግብህ ምክንያታዊና ሁኔታህን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። w23.05 26 አን. 1-2
ሰኞ፣ ግንቦት 12
አምላክ ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል?—ሮም 8:31
ደፋር የሆኑ ሰዎች ፍርሃት ሊሰማቸው ይችላል፤ ሆኖም በፍርሃት ተሽመድምደው ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ዳንኤል በጣም ደፋር ወጣት ነበር። የኤርምያስን ትንቢቶች ጨምሮ የአምላክ ነቢያት የጻፏቸውን መልእክቶች ያጠና ነበር። ትንቢቶችን ማጥናቱ አይሁዳውያን በባቢሎን የሚያሳልፉት ረጅም የግዞት ዘመን በቅርቡ እንደሚያበቃ እንዲገነዘብ ረድቶታል። (ዳን. 9:2) ዳንኤል፣ አምላክ የተናገራቸው ትንቢቶች ሲፈጸሙ ማየቱ በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት እንዳጠናከረለት ምንም ጥያቄ የለውም። በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎች ደግሞ አስደናቂ ድፍረት ማሳየት ይችላሉ። (ከሮም 8:32, 37-39 ጋር አወዳድር።) ከሁሉ በላይ ደግሞ ዳንኤል ወደ ሰማዩ አባቱ አዘውትሮ ይጸልይ ነበር። (ዳን. 6:10) ኃጢአቱን ለይሖዋ ተናዟል፤ እንዲሁም ስሜቱን አውጥቶ ነግሮታል። በተጨማሪም ዳንኤል የይሖዋን እርዳታ ጠይቋል። (ዳን. 9:4, 5, 19) እንደ ማናችንም ሁሉ ዳንኤልም ሰው እንደመሆኑ መጠን ሲወለድ ጀምሮ ደፋር አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በማጥናት፣ በመጸለይ እንዲሁም በይሖዋ በመታመን ይህን ባሕርይ ማዳበር ችሏል። w23.08 3 አን. 4፤ 4 አን. 7
ማክሰኞ፣ ግንቦት 13
ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።—ማቴ. 5:16
የበላይ ባለሥልጣናትን ስንታዘዝ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን እንጠቅማለን። እንዴት? አንደኛ፣ ሕጉን የሚተላለፉ ሰዎች ከሚደርስባቸው ቅጣት እንድናለን። (ሮም 13:1, 4) በግለሰብ ደረጃ ታዛዥነት ማሳየታችን ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮችን በቡድን ደረጃ በሚያዩበት መንገድ ላይ ለውጥ ያመጣል። ለምሳሌ ያህል፣ ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በፊት ናይጄርያ ውስጥ ወታደሮች ስብሰባ እየተካሄደ ሳለ ወደ አንድ የስብሰባ አዳራሽ ገቡ። ወታደሮቹ ግብር መክፈልን የሚቃወሙ ዓመፀኞችን እየፈለጉ ነበር። ሆኖም ኃላፊያቸው “የይሖዋ ምሥክሮች ግብር መክፈልን አይቃወሙም” በማለት ወታደሮቹን እንዲወጡ አዘዛቸው። አንድን ሕግ በታዘዝክ ቁጥር የይሖዋ ምሥክሮች በሰዎች ዘንድ ላላቸው መልካም ስም አስተዋጽኦ ልታበረክት ትችላለህ፤ ይህ መልካም ስም ደግሞ አንድ ቀን የእምነት አጋሮችህን ሊያድናቸው ይችላል። w23.10 9 አን. 13
ረቡዕ፣ ግንቦት 14
የአምላክን ፈቃድ ከፈጸማችሁ በኋላ የተስፋው ቃል ሲፈጸም ማየት እንድትችሉ መጽናት ያስፈልጋችኋል።—ዕብ. 10:36
አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች የዚህን ሥርዓት መጨረሻ ለረጅም ጊዜ ሲጠባበቁ ኖረዋል። በሰዎች ዓይን፣ አምላክ የገባው ቃል ፍጻሜ የዘገየ ሊመስል ይችላል። ይሖዋ አገልጋዮቹ እንዲህ እንደሚሰማቸው ያውቃል። እንዲያውም ለነቢዩ ዕንባቆም እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቶታል፦ “ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ገና ይጠብቃልና፤ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፤ ደግሞም አይዋሽም። ቢዘገይ እንኳ በተስፋ ጠብቀው! ያላንዳች ጥርጥር ይፈጸማልና። ራእዩ አይዘገይም!” (ዕን. 2:3) ይሖዋ ይህን ማረጋገጫ የሰጠው ለዕንባቆም ብቻ ነው? ወይስ እነዚህ ቃላት ለእኛም ይሠራሉ? ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ይህን ሐሳብ አዲሱን ዓለም ከሚጠባበቁ ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘ ተጠቅሞበታል። (ዕብ. 10:37) በእርግጥም መዳናችን እንደዘገየ ሆኖ ቢሰማንም እንኳ “ያላንዳች ጥርጥር [ይፈጸማል]። ራእዩ አይዘገይም!” w23.04 30 አን. 16
ሐሙስ፣ ግንቦት 15
እስራኤላውያንም በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ ያጉረመርሙ ጀመር።—ዘኁ. 14:2
እስራኤላውያን ይሖዋ በሙሴ እየተጠቀመ እንዳለ የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። (ዘኁ. 14:10, 11) የሙሴን ሚና ለመቀበል በተደጋጋሚ እንቢተኞች ሆነዋል። በዚህም የተነሳ ያ የእስራኤላውያን ትውልድ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ አልተፈቀደለትም። (ዘኁ. 14:30) ይሁንና የይሖዋን አመራር የተከተሉ አንዳንድ እስራኤላውያን ነበሩ። ለምሳሌ ይሖዋ ‘ካሌብ በሙሉ ልቡ ተከትሎኛል’ በማለት ተናግሯል። (ዘኁ. 14:24) አምላክ ለካሌብ ወሮታውን ከፍሎታል፤ እንዲያውም በከነአን ምድር የፈለገውን መሬት ሰጥቶታል። (ኢያሱ 14:12-14) ቀጣዩ የእስራኤላውያን ትውልድም የይሖዋን አመራር በመከተል ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። ኢያሱ በሙሴ ምትክ የእስራኤላውያን መሪ ሆኖ በተሾመበት ወቅት እነዚህ እስራኤላውያን ‘በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በጥልቅ አክብረውታል።’ (ኢያሱ 4:14) በዚህም የተነሳ ይሖዋ፣ ቃል ወደገባላቸው ምድር በማስገባት ባርኳቸዋል።—ኢያሱ 21:43, 44፤ w24.02 21 አን. 6-7
ዓርብ፣ ግንቦት 16
አምላክን የሚወድ ሁሉ ወንድሙንም መውደድ ይገባዋል።—1 ዮሐ. 4:21
አንድ ሐኪም የልብ ምታችንን በማየት ስለ ልባችን ጤንነት የተወሰነ መረጃ ማግኘት እንደሚችለው ሁሉ እኛም ለሌሎች ያለንን ፍቅር በማየት ለአምላክ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ማወቅ እንችላለን። ለእምነት አጋሮቻችን ያለን ፍቅር በተወሰነ መጠን እንደቀነሰ ካስተዋልን ይህ ሁኔታ ለአምላክ ያለን ፍቅርም እንደቀነሰ ሊያሳይ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ለእምነት አጋሮቻችን አዘውትረን ፍቅር ማሳየታችን ለአምላክ ያለን ፍቅር ጠንካራ እንደሆነ ይጠቁማል። ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር እየቀነሰ ከሄደ ጉዳዩ ሊያሳስበን ይገባል። ለምን? ምክንያቱም በመንፈሳዊ አደጋ ላይ ነን ማለት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልም” በማለት አደጋውን በግልጽ ጠቁሞናል። (1 ዮሐ. 4:20) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ የሚደሰትብን ‘እርስ በርሳችን የምንዋደድ’ ከሆነ ብቻ ነው።—1 ዮሐ. 4:7-9, 11፤ w23.11 8 አን. 3፤ 9 አን. 5-6
ቅዳሜ፣ ግንቦት 17
አባትህና እናትህ ሐሴት ያደርጋሉ።—ምሳሌ 23:25
ንጉሥ ኢዮዓስ በልጅነቱ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አድርጓል። ኢዮዓስ አባት ባይኖረውም ታማኝ ሊቀ ካህናት የሆነው ዮዳሄ የሰጠውን አመራር ተቀብሏል። ዮዳሄ ኢዮዓስን ልክ እንደ ገዛ ልጁ አስተምሮታል። ኢዮዓስም በምላሹ ንጹሑን አምልኮ ለማራመድና ይሖዋን ለማገልገል ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አደረገ። እንዲያውም ኢዮዓስ የይሖዋ ቤተ መቅደስ እንዲጠገን ዝግጅት አደረገ። (2 ዜና 24:1, 2, 4, 13, 14) ወላጆችህ ወይም ሌሎች ሰዎች ይሖዋን እንድትወድና በእሱ መሥፈርቶች እንድትመራ እያስተማሩህ ከሆነ ውድ ስጦታ ሰጥተውሃል። (ምሳሌ 2:1, 10-12) ወላጆችህ በተለያዩ መንገዶች ሥልጠና ሊሰጡህ ይችላሉ። የሚሰጥህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ ስታደርግ ወላጆችህን ታስደስታለህ። ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክን ታስደስተዋለህ፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ትመሠርታለህ። (ምሳሌ 22:6፤ 23:15, 24) ይህ፣ ኢዮዓስ በልጅነቱ የተወውን ምሳሌ ለመከተል የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት አይደለም? w23.09 8-9 አን. 3-5
እሁድ፣ ግንቦት 18
እሰማችኋለሁ።—ኤር. 29:12
ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ ቃል ገብቶልናል። አምላካችን ታማኝ አገልጋዮቹን ስለሚወዳቸው ጸሎታቸውን ፈጽሞ ችላ አይልም። (መዝ. 10:17፤ 37:28) ይህ ማለት ግን የጠየቅነውን ነገር ሁሉ ይሰጠናል ማለት አይደለም። የጠየቅናቸውን አንዳንዶቹን ነገሮች ለማግኘት እስከ አዲሱ ዓለም ድረስ መጠበቅ ሊኖርብን ይችላል። ይሖዋ ጸሎታችንን ሲሰማ ዓላማውን ከግምት ያስገባል። (ኢሳ. 55:8, 9) የይሖዋ ዓላማ፣ ምድር በደስታ ለእሱ በሚገዙ ወንዶችና ሴቶች እንድትሞላ ማድረግን ያካትታል። ሆኖም ሰይጣን፣ ሰዎች ራሳቸውን ቢያስተዳድሩ የተሻለ እንደሆነ ተከራክሯል። (ዘፍ. 3:1-5) ይሖዋ የዲያብሎስ ክስ ሐሰት መሆኑ እንዲረጋገጥ ሲል የሰው ልጆች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ፈቀደላቸው። የሰው ልጆች አገዛዝ በዛሬው ጊዜ የምናያቸውን አብዛኞቹን ችግሮች አስከትሏል። (መክ. 8:9) ይሖዋ እነዚህን ችግሮች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ እንደማያስወግዳቸው እንገነዘባለን። w23.11 21 አን. 4-5
ሰኞ፣ ግንቦት 19
ለብዙ ብሔራት አባት አድርጌሃለሁ።—ሮም 4:17
ይሖዋ በአብርሃም አማካኝነት ብዙ ብሔራት እንደሚባረኩ ቃል ገብቶ ነበር። ይሁንና አብርሃም 100 ዓመት፣ ሣራ ደግሞ 90 ዓመት ሞልቷቸውም ልጅ አልወለዱም። ከሰብዓዊ እይታ አንጻር አብርሃምና ሣራ ልጅ መውለድ የሚችሉ አይመስልም ነበር። ይህ ለአብርሃም ትልቅ ፈተና ነበር። ያም ቢሆን አብርሃም “የብዙ ብሔራት አባት እንደሚሆን በተሰጠው ተስፋ አምኗል።” (ሮም 4:18, 19) ደግሞም ይህ ተስፋ ተፈጽሞለታል። ለረጅም ጊዜ ተስፋ ሲያደርግ እንደቆየው ይስሐቅን መውለድ ችሏል። (ሮም 4:20-22) እንደ አብርሃም የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንዲሁም የእሱ ወዳጆች በመሆን እንደ ጻድቃን መቆጠር እንችላለን። እንዲያውም ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “‘ተቆጠረለት’ ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ ጻድቃን ስለምንቆጠረው ስለ እኛም ጭምር ነው፤ ምክንያቱም ጌታችንን ኢየሱስን ከሞት ባስነሳው በእሱ እናምናለን።” (ሮም 4:23, 24) እንደ አብርሃም ሁሉ እኛም እምነትና ሥራ እንዲሁም ተስፋ ያስፈልገናል። w23.12 7 አን. 16-17
ማክሰኞ፣ ግንቦት 20
ጉስቁልናዬን አይተሃልና፤ በጭንቀት መዋጤን ታውቃለህ።—መዝ. 31:7
ፍርሃት እንዲሰማህ የሚያደርግ ፈተና ሲያጋጥምህ ይሖዋ እየደረሰብህ ያለውን ፈተና ብቻ ሳይሆን ፈተናው ያሳደረብህን ስሜትም እንደሚያስተውል አስታውስ። ለምሳሌ ይሖዋ፣ እስራኤላውያን በግብፅ የደረሰባቸውን በደል ብቻ ሳይሆን የተሰማቸውን ሥቃይም ተመልክቷል። (ዘፀ. 3:7) ይሁንና አስፈሪ ፈተና በምትጋፈጥበት ወቅት ይሖዋ እየደገፈህ ያለው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ሊከብድህ ይችላል። ስለዚህ እያደረገልህ ያለውን ድጋፍ ለማስተዋል እንዲረዳህ ጠይቀው። (2 ነገ. 6:15-17) ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦ በጉባኤ ስብሰባ ላይ የቀረበ ንግግር ወይም ሐሳብ አበረታቶሃል? አንድ ጽሑፍ፣ ቪዲዮ ወይም ኦሪጅናል መዝሙር ብርታት ሰጥቶሃል? የሚያጽናና ሐሳብ ወይም ጥቅስ ያካፈለህ ሰው አለ? አፍቃሪ ከሆነው የወንድማማች ማኅበራችን እንዲሁም ከሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ የምናገኘውን እርዳታ አቅልለን እንመለከተው ይሆናል። ያም ቢሆን እነዚህ ዝግጅቶች ከይሖዋ ያገኘናቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው። (ኢሳ. 65:13፤ ማር. 10:29, 30) ይሖዋ እንደሚያስብልህ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ናቸው። (ኢሳ. 49:14-16) ልትተማመንበት የሚገባ አምላክ እንደሆነ ዋስትና ይሰጡሃል። w24.01 4-5 አን. 9-10
ረቡዕ፣ ግንቦት 21
[ባሪያዎችህ] ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው።—ሥራ 4:29
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ “በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ” ስለ እሱ ምሥክርነት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው አስታውሷቸዋል። (ሥራ 1:8፤ ሉቃስ 24:46-48) ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ሐዋርያው ጴጥሮስንና ዮሐንስን በሳንሄድሪን ፊት አቅርበው መስበካቸውን እንዲያቆሙ አዘዟቸው፤ አልፎ ተርፎም አስፈራሯቸው። (ሥራ 4:18, 21) ጴጥሮስና ዮሐንስ እንዲህ አሉ፦ “አምላክን ከመስማት ይልቅ እናንተን መስማት በአምላክ ፊት ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ። እኛ ግን ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።” (ሥራ 4:19, 20) ጴጥሮስና ዮሐንስ ከተለቀቁ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ በይሖዋ ፈቃድ ላይ ያተኮረ ጸሎት አቀረቡ። ይሖዋ ለዚህ ልባዊ ጸሎት ምላሽ ሰጥቷል።—ሥራ 4:31፤ w23.05 5 አን. 11-12
ሐሙስ፣ ግንቦት 22
የምወደው ልጄ ይህ ነው።—ማቴ. 17:5
ይሖዋና የሚወደው ልጁ ኢየሱስ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት አብረው ሲኖሩ እጅግ በጣም የጠበቀ ዝምድና መሥርተዋል። በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ይሖዋ ለኢየሱስ ያለውን ፍቅር በግልጽ ተናግሯል። ይሖዋ በኢየሱስ ‘በጣም እንደሚደሰትበት’ በመግለጽ ሊወሰን ይችል ነበር። ሆኖም ኢየሱስን ምን ያህል እንደሚወደው እንድናውቅ ስለፈለገ “የምወደው ልጄ” በማለት ጠርቶታል። ይሖዋ በኢየሱስ ይኮራ ነበር፤ የሰጠውን ተልእኮ የተወጣበት መንገድም አስደስቶታል። (ኤፌ. 1:7) ኢየሱስም ቢሆን አባቱ እንደሚወደው ተጠራጥሮ አያውቅም። የይሖዋ ፍቅር ለኢየሱስ እውን ነበር። አባቱ እንደሚወደው በተደጋጋሚ በእርግጠኝነት ተናግሯል።—ዮሐ. 3:35፤ 10:17፤ 17:24፤ w24.01 28 አን. 8
ዓርብ፣ ግንቦት 23
መልካም ስም ከብዙ ሀብት ይመረጣል።—ምሳሌ 22:1
አንድ የምትቀርበው ሰው ስለ አንተ መጥፎ ነገር ተናገረ እንበል። አንተ ወሬው ውሸት እንደሆነ ታውቃለህ፤ አንዳንዶች ግን አመኑት። ይባስ ብሎ ደግሞ ያንን ውሸት ማሰራጨት ጀመሩ። በዚህም የተነሳ ሌሎች ብዙ ሰዎች ውሸቱን አመኑ። በዚህ ጊዜ ምን ይሰማሃል? ስምህ መጥፋቱ እንደሚያናድድህ ጥያቄ የለውም። ይህ ሁኔታ ይሖዋ ስሙ በጠፋ ጊዜ ምን እንደተሰማው እንድንረዳ ያግዘናል። ከመንፈሳዊ ልጆቹ አንዱ ለመጀመሪያዋ ሴት ለሔዋን ይሖዋን በተመለከተ ውሸት ነገራት። እሷም ይህን ውሸት አመነች። ይህ ውሸት የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን በይሖዋ ላይ እንዲያምፁ አደረጋቸው። በዚህም የተነሳ የሰው ልጆች በኃጢአትና በሞት ቀንበር ሥር ወደቁ። (ዘፍ. 3:1-6፤ ሮም 5:12) ሞትን፣ ጦርነትንና መከራን ጨምሮ በዓለም ላይ የምናያቸው ችግሮች በሙሉ የጀመሩት ሰይጣን ይህን ውሸት በመናገሩ ነው። ይሖዋ ስሙ በመጥፋቱና በዚህም የተነሳ በሰው ልጆች ላይ መከራ በመምጣቱ ምን ተሰማው? በጣም እንዳዘነ ምንም ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን ይሖዋ ብስጩ አልሆነም። እንዲያውም አሁንም ‘ደስተኛ አምላክ’ ነው።—1 ጢሞ. 1:11፤ w24.02 8 አን. 1-2
ቅዳሜ፣ ግንቦት 24
እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?—ዘፍ. 39:9
የዮሴፍ ዓይነት ቁርጠኝነት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምን እንደምታደርግ ከአሁኑ መወሰን ትችላለህ። ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች ወዲያውኑ እንቢ ማለትን ተማር፤ እነዚህን ነገሮች በአእምሮህ እንኳ ለማውጠንጠን ፈቃደኛ አትሁን። (መዝ. 97:10፤ 119:165) እንዲህ ካደረግክ ፈተና ሲያጋጥምህ አቋምህን አታላላም። እውነትን እንዳገኘህና ይሖዋን በሙሉ ልብህ ማገልገል እንደምትፈልግ ብታውቅም እንኳ ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ዝግጁ እንዳልሆንክ ሊሰማህ ይችላል። ከሆነ የንጉሥ ዳዊትን ምሳሌ መከተል ትችላለህ። ይሖዋን እንዲህ ብለህ ለምነው፦ “አምላክ ሆይ፣ በሚገባ ፈትሸኝ፤ ልቤንም እወቅ። መርምረኝ፤ የሚያስጨንቁኝንም ሐሳቦች እወቅ። በውስጤ ጎጂ የሆነ ዝንባሌ ካለ እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።” (መዝ. 139:23, 24) ይሖዋ ‘ከልብ የሚፈልጉትን’ ይባርካቸዋል። ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግህ ይሖዋን ከልብ እንደምትፈልገው ያሳያል።—ዕብ. 11:6፤ w24.03 6 አን. 13-15
እሁድ፣ ግንቦት 25
በየዕለቱ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም።—ዕብ. 7:27
ሊቀ ካህናቱ ሕዝቡን ወክሎ በአምላክ ፊት የመቅረብ ሥልጣን ነበረው። የእስራኤል የመጀመሪያ ሊቀ ካህናት የነበረውን አሮንን የሾመው ይሖዋ ሲሆን የተሾመውም የማደሪያ ድንኳኑ በተመረቀበት ወቅት ነው። ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው “ካህናት አገልግሎታቸውን እንዳይቀጥሉ ሞት ስለሚያግዳቸው አንዱ ሌላውን እየተካ እንዲያገለግል ብዙዎች ካህናት መሆን ነበረባቸው።” (ዕብ. 7:23-26) ደግሞም እነዚያ ሊቃነ ካህናት ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ስለነበሩ ለራሳቸው ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ ነበረባቸው። በእስራኤል በነበሩት ሊቃነ ካህናትና በታላቁ ሊቀ ካህናት በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት ይህ ነው። ሊቀ ካህናታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የእውነተኛው ድንኳን አገልጋይ ነው፤ ይህም ድንኳን በሰው ሳይሆን በይሖዋ የተተከለ ነው።” (ዕብ. 8:1, 2) ጳውሎስ፣ ኢየሱስ “ለዘላለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖር ክህነቱ ተተኪ የለውም” ብሏል። በተጨማሪም ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ‘ያልረከሰና ከኃጢአተኞች የተለየ’ እንደሆነ እንዲሁም ከእስራኤል ሊቃነ ካህናት በተለየ መልኩ ለራሱ ኃጢአት ‘በየዕለቱ መሥዋዕት ማቅረብ እንደማያስፈልገው’ ገልጿል። w23.10 26 አን. 8-9
ሰኞ፣ ግንቦት 26
የቀድሞው ሰማይና የቀድሞው ምድር አልፈዋል።—ራእይ 21:1
“የቀድሞው ሰማይ” የሚለው አገላለጽ በሰይጣንና በአጋንንቱ ተጽዕኖ ሥር ያሉትን መንግሥታት ያመለክታል። (ማቴ. 4:8, 9፤ 1 ዮሐ. 5:19) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ምድር” የሚለው ቃል የምድርን ነዋሪዎች ሊያመለክት ይችላል። (ዘፍ. 11:1፤ መዝ. 96:1) በመሆኑም “የቀድሞው ምድር” የሚለው አገላለጽ በዛሬው ጊዜ ያሉትን ክፉ ሰዎች ያመለክታል። ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ሰማይና ምድር ከመጠገን ይልቅ ሙሉ በሙሉ አጥፍቶ ይተካቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ያሉትን “ሰማይ” እና “ምድር” ‘በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር’ ማለትም በአዲስ መንግሥትና በአዲስ ሰብዓዊ ማኅበረሰብ ይተካቸዋል። ይሖዋ ምድርንና የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ደረጃ በማድረስ አዲስ ያደርጋቸዋል። ኢሳይያስ በትንቢት እንደተናገረው መላዋ ምድር እንደ ኤደን ያለች ውብ ገነት ትሆናለች። እኛም በግለሰብ ደረጃ እንታደሳለን። አንካሶች፣ ዓይነ ስውራንና መስማት የተሳናቸው ሰዎች ይፈወሳሉ፤ ሙታን እንኳ ሕያው ይሆናሉ።—ኢሳ. 25:8፤ 35:1-7፤ w23.11 4 አን. 9-10
ማክሰኞ፣ ግንቦት 27
ዝግጁ ሁኑ።—ማቴ. 24:44
‘ታላቁ መከራ’ የሚጀምረው በድንገት ነው። (ማቴ. 24:21) ከሌሎቹ አደጋዎች በተለየ ግን ታላቁ መከራ ድንገተኛ የሚሆነው ለሁሉም ሰው አይደለም። ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ተከታዮቹን ለዚህ ቀን እንዲዘጋጁ አሳስቧቸዋል። ዝግጁ ከሆንን ይህን የመከራ ጊዜ ማለፍ ያን ያህል አይከብደንም፤ እንዲያውም ከራሳችን አልፈን ሌሎችን ለመርዳት እንበቃለን። (ሉቃስ 21:36) ይሖዋ እንደሚጠብቀን ተማምነን ትእዛዙን መፈጸም ጽናት ይጠይቃል። ወንድሞቻችን ንብረታቸውን ቢያጡ አልፎም ባዷቸውን ቢቀሩ ምን እናደርጋለን? (ዕን. 3:17, 18) ርኅራኄ በችግራቸው እንድንደርስላቸው ያነሳሳናል። ግንባር የፈጠሩ ብሔራት በሰነዘሩት ጥቃት የተነሳ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በአንድ ቦታ እፍግፍግ ብለን ለመኖር ብንገደድስ? (ሕዝ. 38:10-12) ያንን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ለእነሱ ጥልቅ ፍቅር ሊኖረን ይገባል። w23.07 2 አን. 2-3
ረቡዕ፣ ግንቦት 28
የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።—ኤፌ. 5:15, 16
ባለትዳሮች በጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ተወዳጅ የነበሩት አቂላና ጵርስቅላ ከተዉት ምሳሌ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። (ሮም 16:3, 4) አብረው ይሠሩ፣ ይሰብኩና ሌሎችን ይረዱ ነበር። (ሥራ 18:2, 3, 24-26) እንዲያውም አቂላና ጵርስቅላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለየብቻ ተጠቅሰው አያውቁም። ባለትዳሮች የእነሱን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? እናንተም ሆናችሁ የትዳር አጋራችሁ ያሉባችሁን የተለያዩ ኃላፊነቶች ለማሰብ ሞክሩ። አንዳንዶቹን ሥራዎች ለብቻችሁ ከማከናወን ይልቅ አብራችሁ ልትሠሩ ትችሉ ይሆን? ለምሳሌ አቂላና ጵርስቅላ አብረው ይሰብኩ ነበር። እናንተስ አዘውትራችሁ አብራችሁ ለማገልገል ፕሮግራም ታወጣላችሁ? አቂላና ጵርስቅላ አብረው ይሠሩም ነበር። እርግጥ ነው፣ እናንተ አንድ ዓይነት ሥራ አይኖራችሁ ይሆናል። ይሁንና የቤት ውስጥ ሥራዎችን አብራችሁ ማከናወን ትችሉ ይሆን? (መክ. 4:9) አንድን ነገር ተባብራችሁ ስታከናውኑ አንድነታችሁ ይጠናከራል፤ አብራችሁ ለማውራት የሚያስችል አጋጣሚም ታገኛላችሁ። w23.05 22-23 አን. 10-12
ሐሙስ፣ ግንቦት 29
ፍርሃት በሚሰማኝ ጊዜ በአንተ እታመናለሁ።—መዝ. 56:3
ሁሉም ሰው አልፎ አልፎ ፍርሃት ይሰማዋል። ለምሳሌ ንጉሥ ሳኦል ሊገድለው አስቦ እያሳደደው በነበረበት ወቅት ዳዊት የፍልስጤም ከተማ ወደሆነችው ወደ ጌት ለመሸሽ ወሰነ። ብዙም ሳይቆይ ግን የጌት ንጉሥ የሆነው አንኩስ፣ ዳዊት “አሥር ሺዎችን ገደለ” ተብሎ የተዘፈነለት ኃያል ተዋጊ መሆኑን አወቀ። በዚህ ጊዜ ዳዊት “እጅግ ፈራ።” (1 ሳሙ. 21:10-12) አንኩስ እንዳይገለው ፈርቶ ነበር። ታዲያ ዳዊት ፍርሃቱን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው? በመዝሙር 56 ላይ ዳዊት በጌት ሳለ የተሰማውን ስሜት ጽፏል። ይህ መዝሙር ዳዊት የተሰማውን ፍርሃት በግልጽ ይናገራል፤ ሆኖም ፍርሃቱን ያሸነፈበትን መንገድም ይገልጻል። ዳዊት ፍርሃት በተሰማው ወቅት በይሖዋ ታምኗል። (መዝ. 56:1-3, 11) ደግሞም እምነቱ ክሶታል። በይሖዋ እርዳታ ዳዊት ያልተለመደ ሆኖም ውጤታማ ዘዴ ቀየሰ፤ እንደ እብድ ሆነ። በዚህ ጊዜ አንኩስ ዳዊትን ለመግደል ከማሰብ ይልቅ ከፊቱ እንዲባረርለት ጠየቀ። በመሆኑም ዳዊት ማምለጥ ቻለ።—1 ሳሙ. 21:13–22:1፤ w24.01 2 አን. 1-3
ዓርብ፣ ግንቦት 30
ከእሱ ጋር ያሉት የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም ድል ያደርጋሉ።—ራእይ 17:14
የዛሬው የዕለት ጥቅስ የሚናገረው ስለ እነማን ነው? ትንሣኤ ስላገኙት ቅቡዓን ነው። ስለዚህ በታላቁ መከራ መገባደጃ አካባቢ ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ሄደው ካለቁ በኋላ ከሚሰጧቸው የመጀመሪያ ሥራዎች አንዱ መዋጋት ነው። ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ ከክርስቶስና ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ሆነው ከአምላክ ጠላቶች ጋር በሚካሄደው የመጨረሻ ጦርነት ላይ ይዋጋሉ። እስቲ አስበው። አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ ሳሉ አረጋውያን፣ ምናልባትም አቅመ ደካሞች ነበሩ። ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ ግን ኃያልና የማይሞቱ መንፈሳዊ ፍጥረታት ሆነው ከተዋጊው ንጉሣቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጎን ተሰልፈው ይዋጋሉ። የአርማጌዶን ጦርነት ካበቃ በኋላ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ደረጃ በማድረሱ ሥራ ይካፈላሉ። በእርግጥም ሰማይ ከሄዱ በኋላ በምድር ላይ ላሉት ውድ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ማከናወን የሚችሉት ነገር በምድር ላይ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ሆነው ሊያከናውኑ ከሚችሉት ነገር ጋር ጨርሶ አይወዳደርም! w24.02 6-7 አን. 15-16
ቅዳሜ፣ ግንቦት 31
በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ፤ . . . እንዲህ ካደረጋችሁ የሥጋን ምኞት ከቶ አትፈጽሙም።—ገላ. 5:16
አንዳንዶች ራሳቸውን ለመወሰንና ለመጠመቅ ዝግጁ ቢሆኑም እንኳ ይህን እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ ይላሉ። ‘ከተጠመቅኩ በኋላ ከባድ ኃጢአት ፈጽሜ ብወገድስ?’ ብለው ይሰጉ ይሆናል። አንተም እንዲህ ያለ ስጋት ካደረብህ ይሖዋ ‘ለእሱ በሚገባ ሁኔታ እንድትመላለስና እሱን ሙሉ በሙሉ እንድታስደስት’ አስፈላጊውን እርዳታ ሁሉ እንደሚሰጥህ መተማመን ትችላለህ። (ቆላ. 1:10) በተጨማሪም ትክክል የሆነውን ነገር እንድታደርግ ጥንካሬ ይሰጥሃል። በርካታ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንዲህ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። (1 ቆሮ. 10:13) ከክርስቲያን ጉባኤ የሚወገዱት ሰዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ይሖዋ ሕዝቦቹን ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በሙሉ መጥፎ ነገር ለማድረግ ይፈተናሉ። (ያዕ. 1:14) ሆኖም በፈተናው መሸነፍ አለመሸነፍ የምርጫ ጉዳይ ነው፤ ይህን ምርጫ የምታደርገው አንተ ራስህ ነህ። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ሕይወትህን የምትመራበትን መንገድ የምትመርጠው አንተ ራስህ ነህ። አንዳንዶች እንዲህ ማድረግ እንደማይቻል ቢናገሩም እንኳ ምኞቶችህን መቆጣጠርን መማር ትችላለህ። w24.03 5 አን. 11-12