የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es25
  • ሰኔ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሰኔ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • እሁድ፣ ሰኔ 1
  • ሰኞ፣ ሰኔ 2
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 3
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 4
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 5
  • ዓርብ፣ ሰኔ 6
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 7
  • እሁድ፣ ሰኔ 8
  • ሰኞ፣ ሰኔ 9
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 10
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 11
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 12
  • ዓርብ፣ ሰኔ 13
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 14
  • እሁድ፣ ሰኔ 15
  • ሰኞ፣ ሰኔ 16
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 17
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 18
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 19
  • ዓርብ፣ ሰኔ 20
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 21
  • እሁድ፣ ሰኔ 22
  • ሰኞ፣ ሰኔ 23
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 24
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 25
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 26
  • ዓርብ፣ ሰኔ 27
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 28
  • እሁድ፣ ሰኔ 29
  • ሰኞ፣ ሰኔ 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2025
es25

ሰኔ

እሁድ፣ ሰኔ 1

በብዙ መከራ አልፈን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት አለብን።—ሥራ 14:22

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ሁኔታቸው ሲቀየር ማስተካከያ በማድረጋቸው ይሖዋ ባርኳቸዋል። ብዙ ጊዜ ስደት ይደርስባቸው ነበር፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ስደት የደረሰባቸው ጨርሶ ባልጠበቁት ጊዜ ነው። በርናባስና ሐዋርያው ጳውሎስ በልስጥራ አካባቢ ሲሰብኩ ያጋጠማቸውን ነገር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መጀመሪያ ላይ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገላቸው፤ ሰዎቹም ያዳምጧቸው ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ተቃዋሚዎች “ሕዝቡን አግባቡ”፤ በመሆኑም ሞቅ አድርገው የተቀበሏቸው እነዚያው ሰዎች ጳውሎስን በድንጋይ ከወገሩት በኋላ የሞተ መስሏቸው ትተውት ሄዱ። (ሥራ 14:19) ሆኖም በርናባስና ጳውሎስ ሌላ ቦታ መስበካቸውን ቀጠሉ። ታዲያ ምን ውጤት ተገኘ? “በርካታ ደቀ መዛሙርት” አፈሩ። እንዲሁም በንግግራቸውና በምሳሌነታቸው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን አጠናከሩ። (ሥራ 14:21, 22) በርናባስና ጳውሎስ ድንገተኛ ስደት ቢደርስባቸውም መስበካቸውን ስላላቆሙ ብዙዎች ተጠቅመዋል። እኛም ይሖዋ የሰጠንን ሥራ ማከናወናችንን እስካላቆምን ድረስ እንባረካለን። w23.04 16 አን. 13-14

ሰኞ፣ ሰኔ 2

ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴን አዳምጥ፤ እርዳታ ለማግኘት የማቀርበውንም ልመና በትኩረት ስማ። አንተ መልስ ስለምትሰጠኝ፣ በተጨነቅኩ ቀን አንተን እጣራለሁ።—መዝ. 86:6, 7

ዳዊት በመላ ሕይወቱ አደገኛ የሆኑ በርካታ ጠላቶችን ተጋፍጧል። በመሆኑም በተደጋጋሚ የይሖዋን እርዳታ ይጠይቅ ነበር። ዳዊት፣ ይሖዋ ጸሎቱን እንደሰማውና እንደመለሰለት እርግጠኛ ነበር። አንተም ይሖዋ ጸሎትህን እንደሚሰማና እንደሚመልስልህ መተማመን ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያሳየው ይሖዋ ጥበብና ለመጽናት የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። መንፈሳዊ ቤተሰባችንን አልፎ ተርፎም በአሁኑ ወቅት እሱን የማያመልኩ ሰዎችን በመጠቀም በሆነ መንገድ ሊረዳን ይችላል። ይሖዋ ጸሎታችንን በጠበቅነው መንገድ ላይመልስልን ቢችልም ለጸሎታችን መልስ እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን። የሚያስፈልገንን ነገር ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ይሰጠናል። እንግዲያው ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ እንደሚንከባከብህ፣ በመጪው አዲስ ዓለም ደግሞ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያሟላ’ እርግጠኛ በመሆን በእምነት መጸለይህን ቀጥል።—መዝ. 145:16፤ w23.05 8 አን. 4፤ 13 አን. 17-18

ማክሰኞ፣ ሰኔ 3

ላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለይሖዋ ምን እመልስለታለሁ?—መዝ. 116:12

ግብህ ላይ መድረስህ በሚያስገኛቸው በረከቶች ላይ ማተኮርህ ጠቃሚ ነው። በየትኞቹ በረከቶች ላይ ማተኮር ትችላለህ? ያወጣኸው ግብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ወይም ከጸሎት ጋር የተያያዘ ከሆነ ግብህ ላይ መድረስህ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና የሚያጠናክርልህ እንዴት እንደሆነ አስብ። (መዝ. 145:18, 19) ግብህ አንድን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ማዳበር ከሆነ ደግሞ ይህ ባሕርይ ከሌሎች ጋር ያለህን ዝምድና የሚያሻሽለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። (ቆላ. 3:14) ግብህ ላይ ለመድረስ የሚያነሳሱህን ምክንያቶች በሙሉ ዘርዝረህ ለምን አትጽፍም? ከዚያም አልፎ አልፎ ዝርዝሩን ተመልከት። በተጨማሪም ግብህ ላይ እንድትደርስ ከሚያበረታቱህ ሰዎች ጋር ጊዜ አሳልፍ። (ምሳሌ 13:20) እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ ሁላችንም ተነሳሽነት የምናጣበት ጊዜ ይኖራል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ግባችን ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረጋችንን እናቆማለን ማለት ነው? በፍጹም። ተነሳሽነት ባይኖረንም እንኳ ግባችን ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ማድረግ ራስን መገሠጽ ቢጠይቅም ውጤቱ የሚክስ ይሆናል። w23.05 27-28 አን. 5-8

ረቡዕ፣ ሰኔ 4

አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።—ገላ. 6:7

ለውሳኔዎቻችን ኃላፊነት መውሰዳችን ኃጢአታችንን እንድንናዘዝ፣ ስህተታችንን እንድናርም እንዲሁም ጥፋቱን ላለመድገም እንድንጠነቀቅ ያነሳሳናል። እንዲህ ያሉ እርምጃዎችን መውሰዳችን በሕይወት ሩጫ ላይ እንድንቀጥል ይረዳናል። ያደረግከውን መጥፎ ውሳኔ መቀልበስ ካልቻልክ፣ ያለህበትን ሁኔታ አምነህ ተቀበል። ሰበብ በማቅረብ ወይም ራስህንም ሆነ ሌሎችን በመኮነን ጉልበት አታጥፋ። ከዚህ ይልቅ ስህተትህን አምነህ ተቀበል፤ እንዲሁም አሁን ማድረግ በምትችለው ነገር ላይ አተኩር። በሠራኸው ስህተት የተነሳ ሕሊናህ የሚወቅስህ ከሆነ በትሕትና ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ ጥፋትህን እመን፤ እንዲሁም ይቅር እንዲልህ ጠይቀው። (መዝ. 25:11፤ 51:3, 4) የበደልካቸው ሰዎች ካሉ ይቅርታ ጠይቅ፤ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ የሽማግሌዎችን እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ። (ያዕ. 5:14, 15) ከስህተትህ ተማር፤ ጥፋትህን ላለመድገምም ተጠንቀቅ። እንዲህ ካደረግክ ይሖዋ ምሕረቱን እንደሚያሳይህና የሚያስፈልግህን እርዳታ እንደሚሰጥህ መተማመን ትችላለህ።—መዝ. 103:8-13፤ w23.08 28-29 አን. 8-9

ሐሙስ፣ ሰኔ 5

ኢዮዓስ ካህኑ ዮዳሄ ያስተምረው በነበረበት ዘመን ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።—2 ነገ. 12:2

የዮዳሄ መልካም ምሳሌነት ለንጉሥ ኢዮዓስ ጠቅሞታል። በመሆኑም ወጣቱ ንጉሥ ይሖዋን ማስደሰት ይፈልግ ነበር። ዮዳሄ ከሞተ በኋላ ግን ኢዮዓስ ከሃዲ የሆኑትን መኳንንት መስማት ጀመረ። (2 ዜና 24:4, 17, 18) ይሖዋ በዚህ በጣም ስላዘነ “ወደ እሱ እንዲመልሷቸው ነቢያትን ይልክላቸው ነበር፤ . . . ሕዝቡ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም።” የዮዳሄን ልጅ ዘካርያስን እንኳ ለመስማት አሻፈረኝ አሉ። ዘካርያስ የይሖዋ ነቢይና ካህን ብቻ ሳይሆን የኢዮዓስ የቅርብ ዘመድም ነበር። የሚያሳዝነው፣ ንጉሥ ኢዮዓስ ዘካርያስን አስገደለው። (2 ዜና 22:11፤ 24:19-22) ኢዮዓስ ለይሖዋ የነበረውን ጤናማ ፍርሃት ይዞ አልቀጠለም። ይሖዋ “የሚንቁኝ . . . ይናቃሉ” ብሎ ነበር። (1 ሳሙ. 2:30) አነስተኛ ቁጥር ያለው የሶርያ ሠራዊት “እጅግ ብዙ የሆነውን” የኢዮዓስን ሠራዊት ድል በማድረግ ኢዮዓስን ‘ክፉኛ አቆሰሉት።’ (2 ዜና 24:24, 25) ኢዮዓስ የዘካርያስን ደም በማፍሰሱ የገዛ አገልጋዮቹ ገደሉት። w23.06 18-19 አን. 16-17

ዓርብ፣ ሰኔ 6

በአንድ ወቅት ጨለማ ውስጥ ነበራችሁና፤ አሁን ግን . . . ብርሃን ውስጥ ናችሁ።—ኤፌ. 5:8

ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ምሥራቹን እየሰበከና እያስተማረ በዚያ ረዘም ያለ ጊዜ ቆይቷል። (ሥራ 19:1, 8-10፤ 20:20, 21) ለወንድሞቹ ጥልቅ ፍቅር ስላለው ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ሊረዳቸው ፈልጓል። ጳውሎስ የጻፈላቸው የኤፌሶን ሰዎች በአንድ ወቅት የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና የመናፍስታዊ ድርጊቶች ባሪያ ነበሩ። ኤፌሶን መረን በለቀቀ ብልግናና በነውረኛ ምግባር የታወቀች ከተማ ነበረች። በከተማዋ ቲያትር ማሳያ ስፍራዎች ሌላው ቀርቶ በሃይማኖታዊ በዓላት ላይ እንኳ ጸያፍ ንግግር መስማት የተለመደ ነበር። (ኤፌ. 5:3) ብዙዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች “የሥነ ምግባር ስሜታቸው [ደንዝዟል]”፤ ይህ አገላለጽ ቀጥተኛ ትርጉሙ “ምንም ዓይነት ሕመም የማይሰማው” ማለት ነው። (ኤፌ. 4:17-19) የኤፌሶን ክርስቲያኖች ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር እውነቱን ከመማራቸው በፊት የሕሊና ጸጸት የሚሰማቸው ሰዎች አልነበሩም። ጳውሎስ ስለ ኤፌሶን ሰዎች ሲናገር “አእምሯቸው ጨልሟል፤ እንዲሁም ከአምላክ ከሚገኘው ሕይወት ርቀዋል” ያለው ለዚህ ነው። አንዳንድ የኤፌሶን ሰዎች ግን ከጨለማ ወጥተዋል። w24.03 20 አን. 2, 4፤ 21 አን. 5-6

ቅዳሜ፣ ሰኔ 7

ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ . . . ኃይላቸው ይታደሳል። . . . አይደክሙም።—ኢሳ. 40:31

ጌድዮን መስፍን ሆኖ ባገለገለበት ወቅት በጣም አድካሚ የሆኑ ሥራዎችን አከናውኗል። በሌሊት ከተካሄደው ውጊያ በኋላ ምድያማውያን ሲሸሹ ጌድዮን ከኢይዝራኤል ሸለቆ አንስቶ እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ አሳደዳቸው። (መሳ. 7:22) ታዲያ ጌድዮን ዮርዳኖስ ወንዝ ከደረሰ በኋላ ጠላቶቹን ማሳደዱን አቆመ? በፍጹም። እሱና 300ዎቹ ሰዎች ቢደክማቸውም እንኳ ዮርዳኖስን ተሻግረው ጠላቶቻቸውን ማሳደዳቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም ምድያማውያን ላይ ደረሱባቸውና ድል አደረጓቸው። (መሳ. 8:4-12) ጌድዮን፣ ይሖዋ ብርታት እንደሚሰጠው ተማምኖ ነበር፤ ይሖዋም አላሳፈረውም። (መሳ. 6:14, 34) በአንድ ወቅት ጌድዮንና ወታደሮቹ ሁለት ምድያማውያን ነገሥታትን በእግራቸው ሲያሳድዱ ነበር፤ በወቅቱ ነገሥታቱ ግመል እየጋለቡ ሳይሆን አይቀርም። (መሳ. 8:12, 21) ሆኖም ቆራጦቹ እስራኤላውያን በአምላክ እርዳታ ማሸነፍ ችለዋል። ሽማግሌዎችም በተመሳሳይ ‘ፈጽሞ በማይደክመው ወይም በማይዝለው’ በይሖዋ መታመን ይችላሉ። እሱ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ብርታት ይሰጣቸዋል።—ኢሳ. 40:28, 29፤ w23.06 6 አን. 14፤ 7 አን. 16

እሁድ፣ ሰኔ 8

[ይሖዋ] አይጥላችሁም ወይም አይተዋችሁም።—ዘዳ. 31:6

ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ጽኑ ልብ ሊኖረን ይችላል። እንግዲያው በይሖዋ ታመን። ባርቅ፣ ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መታመኑ ውጤታማ ለመሆን የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ከእስራኤላውያን መካከል ጋሻም ሆነ ጦር ያለው ሰው አልነበረም። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ ሲሳራ ከሚመራው በሚገባ የታጠቀ የከነአናውያን ሠራዊት ጋር እንዲዋጋ መመሪያ ሰጠው። (መሳ. 5:8) ነቢዪቱ ዲቦራ፣ ባርቅ ከተራራው ወደ ሜዳው ወርዶ ሲሳራንና 900 የጦር ሠረገሎቹን እንዲገጥም ነገረችው። ሜዳ ላይ መዋጋት ስልታዊ ጠቀሜታ የሚያስገኘው ለሠረገሎቹ ቢሆንም ባርቅ ታዟል። ወታደሮቹ ከታቦር ተራራ ሲወርዱ ይሖዋ ዶፍ ዝናብ እንዲጥል አደረገ። በመሆኑም የሲሳራ ሠረገሎች በጭቃ ተያዙ፤ ይሖዋ ባርቅን ድል አጎናጸፈው። (መሳ. 4:1-7, 10, 13-16) እኛም በተመሳሳይ በይሖዋና ተወካዮቹ በሚሰጡን መመሪያ የምንታመን ከሆነ ድል እናደርጋለን። w23.07 19 አን. 17-18

ሰኞ፣ ሰኔ 9

እስከ መጨረሻው የጸና . . . ይድናል።—ማቴ. 24:13

ትዕግሥት ለመዳናችን ወሳኝ ነው። በጥንት ዘመን እንደነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ እኛም አምላካችን ቃል የገባቸውን ነገሮች እስኪፈጽም በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልገናል። (ዕብ. 6:11, 12) መጽሐፍ ቅዱስ የእኛን ሁኔታ ከአንድ ገበሬ ሁኔታ ጋር ያመሳስለዋል። (ያዕ. 5:7, 8) አንድ ገበሬ ዘር ለመዝራትና ውኃ ለማጠጣት ተግቶ ይሠራል፤ ሆኖም ተክሉ የሚያድግበትን ትክክለኛ ጊዜ አያውቅም። በመሆኑም ገበሬው እህል እንደሚያጭድ ተማምኖ በትዕግሥት ይጠብቃል። እኛም በተመሳሳይ ‘ጌታችን በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ባናውቅም’ እንኳ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በቅንዓት መካፈላችንን እንቀጥላለን። (ማቴ. 24:42) ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች በሙሉ በትክክለኛው ጊዜ እንደሚፈጽም በመተማመን በትዕግሥት እንጠብቃለን። ትዕግሥት ካጣን ግን መጠበቅ ሊሰለቸንና ቀስ በቀስ ከእውነት መራቅ ልንጀምር እንችላለን። ወይም ደግሞ ቅጽበታዊ ደስታ የሚያስገኙ ነገሮችን ማሳደድ እንጀምር ይሆናል። ትዕግሥተኛ ከሆንን ግን እስከ መጨረሻው መጽናትና መዳን እንችላለን።—ሚክ. 7:7፤ w23.08 22 አን. 7

ማክሰኞ፣ ሰኔ 10

የእግሮቹ ጣቶች ከፊሉ ብረት፣ ከፊሉ ሸክላ [ነበሩ]።—ዳን. 2:42

በዳንኤል 2:41-43 ላይ የሚገኘውን ትንቢት በዳንኤልና በራእይ መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ትንቢቶች ጋር ስናወዳድር እግሮቹ የሚያመለክቱት በአሁኑ ጊዜ የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነውን የአንግሎ አሜሪካ ጥምረት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን። ዳንኤል ይህን የዓለም ኃያል መንግሥት አስመልክቶ ሲናገር “በከፊል ብርቱ፣ በከፊል ደግሞ ደካማ ይሆናል” ብሏል። ይህ መንግሥት በከፊል ደካማ የሚሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በሸክላ ጭቃ የተወከለው ተራው ሕዝብ ይህ መንግሥት እንደ ብረት ባለ ጥንካሬ እርምጃ እንዳይወስድ አቅሙን ያዳክመዋል። ዳንኤል ስለ ምስሉ ከሰጠው መግለጫ በርካታ ወሳኝ እውነቶችን እንማራለን። አንደኛ፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት በአንዳንድ መንገዶች ጥንካሬውን አሳይቷል። ለምሳሌ አንደኛውንና ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ካሸነፉት አገሮች መካከል አሜሪካና ብሪታንያ ይገኙበታል። ሆኖም ይህ የዓለም ኃያል መንግሥት በዜጎቹ መካከል ባሉ ግጭቶች የተነሳ ተዳክሟል፤ እንዲሁም መዳከሙን ይቀጥላል። ሁለተኛ፣ የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ ከማጥፋቱ በፊት የሚኖረው የመጨረሻ የዓለም ኃያል መንግሥት ይህ ጥምር መንግሥት ነው። w23.08 11 አን. 12-13

ረቡዕ፣ ሰኔ 11

በጭንቅ ውስጥ ሳለሁ ይሖዋን ጠራሁት፤ እርዳታ ለማግኘት አምላኬን አጥብቄ ተማጸንኩት። በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ።—መዝ. 18:6

ዳዊት ባጋጠሙት ችግሮችና መከራዎች የተነሳ በጭንቀት የተዋጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። (መዝ. 18:4, 5) ሆኖም የይሖዋ ፍቅርና እንክብካቤ ኃይሉን አድሶለታል። ይሖዋ የዛለውን ወዳጁን ‘ወደለመለመ መስክ’ እና “ውኃ ወዳለበት የእረፍት ቦታ” መርቶታል። በዚህም የተነሳ ዳዊት ኃይሉ ታድሶ ይሖዋን ማገልገሉን መቀጠል ችሏል። (መዝ. 18:28-32) ዛሬም በተመሳሳይ በሕይወታችን ውስጥ ችግርና መከራ ቢያጋጥመንም “ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር የተነሳ ሙሉ በሙሉ አልጠፋንም።” (ሰቆ. 3:22፤ ቆላ. 1:11) ዳዊት ሕይወቱ አደጋ ላይ የወደቀበት ብዙ ጊዜ ነበር፤ ደግሞም ኃያል የሆኑ በርካታ ጠላቶች ነበሩት። ሆኖም የይሖዋ ፍቅር ከስጋት ነፃ ሆኖ እንዲኖር ረድቶታል። ዳዊት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ይሖዋ አብሮት እንደሆነ እርግጠኛ ነበር። ይህ ደግሞ ብርታት ሰጥቶታል። “[ይሖዋ] ከምፈራው ነገር ሁሉ ታደገኝ” ብሎ መዘመር የቻለው ለዚህ ነው። (መዝ. 34:4) ዳዊት ፍርሃት የተሰማው ጊዜ ቢኖርም ይሖዋ እንደሚወደው ማወቁ ፍርሃቱን ለማሸነፍ ረድቶታል። w24.01 30 አን. 15-17

ሐሙስ፣ ሰኔ 12

ኃጢአተኞች ሊያግባቡህ ቢሞክሩ እሺ አትበላቸው።—ምሳሌ 1:10

ከኢዮዓስ መጥፎ ውሳኔዎች ተማር። ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ ከሞተ በኋላ ኢዮዓስ መጥፎ ጓደኞችን መረጠ። (2 ዜና 24:17, 18) ይሖዋን የማይወዱትን የይሁዳ መኳንንት ለመስማት ወሰነ። ኢዮዓስ ከእነዚህ መጥፎ ሰዎች መራቅ ነበረበት ቢባል አትስማማም? እሱ ግን ጓደኛ ተብዬዎቹን ለመስማት መረጠ። እንዲያውም የአክስቱ ልጅ የሆነው ዘካርያስ እርማት ሲሰጠው ኢዮዓስ አስገደለው። (2 ዜና 24:20, 21፤ ማቴ. 23:35) እንዴት ያለ ሞኝነትና ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ድርጊት ነው! ኢዮዓስ በልጅነቱ ጥሩ ውሳኔዎችን አድርጓል፤ የሚያሳዝነው ግን በኋላ ላይ ከሃዲና ነፍሰ ገዳይ ሆነ። በመጨረሻም የገዛ አገልጋዮቹ ገደሉት። (2 ዜና 24:22-25) ይሖዋንና እሱን የሚወዱትን ሰዎች መስማቱን ቢቀጥል ኖሮ ሕይወቱ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር! w23.09 9 አን. 6

ዓርብ፣ ሰኔ 13

አይዞህ አትፍራ።—ሉቃስ 5:10

ኢየሱስ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ታማኝነቱን መጠበቅ እንደሚችል ያውቃል። በመሆኑም ኢየሱስ ጴጥሮስን በደግነት “አይዞህ አትፍራ” አለው። ኢየሱስ የተማመነበት መሆኑ የጴጥሮስን ሕይወት ቀይሮታል። ከጊዜ በኋላ ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን በመተው ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው መሲሑን መከተል ጀመሩ። ይህ ውሳኔያቸው አስደናቂ በረከቶች አስገኝቶላቸዋል። (ማር. 1:16-18) ጴጥሮስ የክርስቶስ ተከታይ በመሆኑ በርካታ አስደናቂ ተሞክሮዎችን አግኝቷል። ኢየሱስ የታመሙትን ሲፈውስ፣ አጋንንትን ሲያስወጣ አልፎ ተርፎም ሙታንን ሲያስነሳ ተመልክቷል። (ማቴ. 8:14-17፤ ማር. 5:37, 41, 42) በተጨማሪም ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ወደፊት ንጉሥ ሲሆን የሚኖረውን ክብር በራእይ ተመልክቷል፤ ይህ ራእይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። (ማር. 9:1-8፤ 2 ጴጥ. 1:16-18) ጴጥሮስ ኢየሱስን ባይከተል ኖሮ እነዚህን ሁሉ አስደናቂ ነገሮች የማየት አጋጣሚ አያገኝም ነበር። ስለ ራሱ የነበረው አሉታዊ አመለካከት እነዚህን በረከቶች እንዲያሳጣው ባለመፍቀዱ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! w23.09 21 አን. 4-5

ቅዳሜ፣ ሰኔ 14

ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እስከ 77 ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም።”—ማቴ. 18:22

ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ “የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ” የሚል አገላለጽ ተጠቅሟል። እንዲህ ያለው ፍቅር ትናንሽ ስህተቶችን ብቻ ሳይሆን “የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።” (1 ጴጥ. 4:8) ምናልባትም ጴጥሮስ ከበርካታ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ስለ ይቅር ባይነት የሰጠውን ትምህርት አስታውሶ ሊሆን ይችላል። በዚያ ወቅት ጴጥሮስ “[ወንድሜን] እስከ ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለው?” ሲል በጣም ይቅር ባይ እንደሆነ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ “እስከ 77 ጊዜ” ማለትም ያለገደብ ይቅር ማለት እንዳለበት አስተምሮታል። (ማቴ. 18:21) ይህ ትምህርት እኛንም ይመለከታል። ይህን ምክር በሥራ ላይ ማዋል ከብዷችሁ ከሆነ አይዟችሁ! ፍጹማን ያልሆኑ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ይቅር ማለት የከበዳቸው ጊዜ አለ። ዋናው ነገር ከዚህ በኋላ ወንድማችሁን ይቅር ለማለት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዳችሁና ከእሱ ጋር ሰላም መፍጠራችሁ ነው። w23.09 29 አን. 12

እሁድ፣ ሰኔ 15

ወደ ይሖዋ ተጣራሁ፤ እሱም መለሰልኝ።—ዮናስ 2:2

ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሳለ በትሕትና የሚያቀርበውን የንስሐ ጸሎት ይሖዋ እንደሚሰማውና እንደሚረዳው እርግጠኛ ነበር። በኋላም ዓሣ ነባሪው በደረቅ መሬት ላይ ሲተፋው ቀጥሎ የሚሰጠውን ኃላፊነት ለመቀበልና ለመወጣት ዝግጁ ነበር። (ዮናስ 2:10–3:4) በፈተና ውስጥ ስትሆን በጭንቀት ከመዋጥህ የተነሳ ሐሳብህን አቀናብረህ መጸለይ እንደማትችል ይሰማሃል? ወይም ደግሞ አቅምህ ከመሟጠጡ የተነሳ ማጥናት እንደማትችል ይሰማሃል? ይሖዋ ያለህበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳልህ አስታውስ። በመሆኑም የምታቀርበው ጸሎት በጣም አጭር ቢሆንም እንኳ ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ኤፌ. 3:20) ያጋጠመህ አካላዊ ወይም ስሜታዊ ሥቃይ ማንበብና ማጥናት ከባድ እንዲሆንብህ ካደረገ የመጽሐፍ ቅዱስን ወይም የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን የድምፅ ቅጂ ማዳመጥ ትችላለህ። jw.org ላይ የሚገኙትን መዝሙሮቻችንን ማዳመጥ ወይም ቪዲዮዎቻችንን መመልከትም ሊረዳህ ይችላል። ወደ ይሖዋ ስትጸልይ እንዲሁም እሱ ባደረጋቸው ዝግጅቶች አማካኝነት የጸሎትህን መልስ ለማግኘት ጥረት ስታደርግ እሱ እንዲያጠነክርህ እየጋበዝከው ነው ሊባል ይችላል። w23.10 13 አን. 6፤ 14 አን. 9

ሰኞ፣ ሰኔ 16

የመጀመሪያው ድንኳን ተተክሎ ሳለ ወደ ቅዱሱ ስፍራ የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ግልጽ አድርጓል።—ዕብ. 9:8

የማደሪያ ድንኳኑም ሆነ ከጊዜ በኋላ በኢየሩሳሌም የተገነቡት ቤተ መቅደሶች መሠረታዊ ንድፋቸው ተመሳሳይ ነበር። ከውስጥ ሁለት ክፍሎች አሏቸው—‘ቅድስቱ’ እና ‘ቅድስተ ቅዱሳኑ።’ በመካከላቸው ደግሞ ጥልፍ የተጠለፈበት መጋረጃ አለ። (ዕብ. 9:2-5፤ ዘፀ. 26:31-33) ቅድስቱ ውስጥ የወርቅ መቅረዝ፣ የዕጣን መሠዊያ እንዲሁም የገጸ ኅብስቱ ጠረጴዛ ነበር። ወደ ቅድስቱ ገብተው ቅዱስ አገልግሎት ማከናወን የሚፈቀድላቸው “ቅቡዕ የሆኑት ካህናት” ብቻ ነበሩ። (ዘኁ. 3:3, 7, 10) ቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ደግሞ የይሖዋን መገኘት የሚወክለው ከወርቅ የተሠራው የቃል ኪዳኑ ታቦት ይገኛል። (ዘፀ. 25:21, 22) መጋረጃውን አልፎ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግባት የሚፈቀድለት ሊቀ ካህናቱ ብቻ ሲሆን የሚገባውም በዓመታዊው የስርየት ቀን ላይ ነው። (ዘሌ. 16:2, 17) የራሱንም ሆነ የመላውን ብሔር ኃጢአት ለማስተሰረይ የእንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባል። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ እነዚህ የማደሪያ ድንኳኑ ገጽታዎች ያላቸውን እውነተኛ ትርጉም ግልጽ አደረገ።—ዕብ. 9:6, 7፤ w23.10 27 አን. 12

ማክሰኞ፣ ሰኔ 17

እርስ በርሳችሁ [ተዋደዱ]።—ዮሐ. 15:17

በአምላክ ቃል ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ ‘እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ’ የሚለውን ትእዛዝ እናገኛለን። (ዮሐ. 15:12፤ ሮም 13:8፤ 1 ተሰ. 4:9፤ 1 ጴጥ. 1:22፤ 1 ዮሐ. 4:11) ሆኖም ፍቅር በልባችን ውስጥ ያለ ስሜት ነው፤ ልባችንን ደግሞ ማንም ሰው ከፍቶ ማየት አይችልም። ታዲያ አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅር እንዲታይ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በንግግራችንና በድርጊታችን ነው። ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንደምንወዳቸው ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። “እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ።” (ዘካ. 8:16) “እርስ [በርሳችሁ] ሰላም ይኑራችሁ።” (ማር. 9:50) “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” (ሮም 12:10) “አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ።” (ሮም 15:7) “እርስ በርስ . . . ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።” (ቆላ. 3:13) “አንዳችሁ የሌላውን ከባድ ሸክም ተሸከሙ።” (ገላ. 6:2) “ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።” (1 ተሰ. 4:18) “እርስ በርስ ተናነጹ።” (1 ተሰ. 5:11) “አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ።”—ያዕ. 5:16፤ w23.11 9 አን. 7-8

ረቡዕ፣ ሰኔ 18

በተስፋው ደስ ይበላችሁ።—ሮም 12:12

በየዕለቱ ጠንካራ እምነት የሚጠይቁ ውሳኔዎችን እናደርጋለን። ለምሳሌ ከጓደኛ ምርጫ፣ ከመዝናኛ ምርጫ፣ ከትምህርት፣ ከትዳር፣ ከልጆች እንዲሁም ከሥራ ጋር በተያያዘ ውሳኔ እናደርጋለን። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘የማደርጋቸው ምርጫዎች ይህ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋና በአምላክ አዲስ ዓለም እንደሚተካ እንደምተማመን ያሳያሉ? ወይስ “ሕይወት የአሁኑ ብቻ ነው” ብለው የሚያምኑ ሰዎች የሚያደርጉት ዓይነት ውሳኔ አደርጋለሁ?’ (ማቴ. 6:19, 20፤ ሉቃስ 12:16-21) አዲሱ ዓለም በቅርቡ እንደሚመጣ ያለንን እምነት ካጠናከርን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። በተጨማሪም ጠንካራ እምነት የሚጠይቁ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። ስደት፣ የጤና እክል ወይም ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርግ ሌላ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል። መጀመሪያ አካባቢ ፈተናውን በልበ ሙሉነት እንጋፈጥ ይሆናል። ብዙ ጊዜ ግን ፈተናዎች ረዘም ላለ ጊዜ ይዘልቃሉ፤ በዚህ ወቅት ለመጽናትና ይሖዋን በደስታ ማገልገላችንን ለመቀጠል ጠንካራ እምነት ያስፈልገናል።—1 ጴጥ. 1:6, 7፤ w23.04 27 አን. 4-5

ሐሙስ፣ ሰኔ 19

ዘወትር ጸልዩ።—1 ተሰ. 5:17

ይሖዋ ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ እንድንወስድ ይጠብቅብናል። ለምሳሌ አንድ ወንድም በክልል ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲል ከሥራው እረፍት ለማግኘት እንዲረዳው ይሖዋን ሊጠይቅ ይችላል። ይሖዋ ይህን ጸሎት የሚመልሰው እንዴት ሊሆን ይችላል? ወንድም አሠሪውን እንዲያነጋግር ድፍረት ሊሰጠው ይችላል። ሆኖም ወንድም አሠሪውን በማነጋገር ከጸሎቱ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። በተደጋጋሚ መጠየቅ ሊያስፈልገው ይችላል። ከሌላ ሠራተኛ ጋር ፈረቃ ለመቀያየር ሊሞክር ወይም ያለደሞዝ እረፍት ሊወስድ ይችላል። ይሖዋ ስለሚያሳስበን ነገር በተደጋጋሚ እንድንጸልይ ይጠብቅብናል። ኢየሱስ የምናቀርበው አንዳንድ ጸሎት ወዲያውኑ መልስ እንደማያገኝ ጠቁሟል። (ሉቃስ 11:9) በመሆኑም ተስፋ አትቁረጥ! ከልብህ በተደጋጋሚ ጸልይ። (ሉቃስ 18:1-7) እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ ያንን ነገር በጣም እንደምንፈልገው ማየት ይችላል። በተጨማሪም ይሖዋ እኛን የመርዳት ችሎታ እንዳለው እንደምናምን እናሳያለን። w23.11 22-23 አን. 10-11

ዓርብ፣ ሰኔ 20

[ተስፋው] ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን አይዳርገንም።—ሮም 5:5

ይሖዋ ለወዳጁ ለአብርሃም የምድር ብሔራት ሁሉ በዘሩ አማካኝነት እንደሚባረኩ ቃል ገብቶለት ነበር። (ዘፍ. 15:5፤ 22:18) አብርሃም በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበረው ይህ ቃል እንደሚፈጸም እርግጠኛ ነበር። ያም ቢሆን አብርሃም 100 ዓመት፣ ሣራ ደግሞ 90 ዓመት ሞልቷቸውም እንኳ እነዚህ ታማኝ ባልና ሚስት ልጅ አልነበራቸውም። (ዘፍ. 21:1-7) ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ “[አብርሃም] በተነገረው መሠረት የብዙ ብሔራት አባት እንደሚሆን በተሰጠው ተስፋ አምኗል” ይላል። (ሮም 4:18) የአብርሃም ተስፋ እንደተፈጸመ እናውቃለን። ለረጅም ጊዜ ሲጠብቅ እንደነበረው ይስሐቅን ወልዷል። አብርሃም፣ ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረው የረዳው ምንድን ነው? ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስለነበረው “አምላክ የሰጠውን ተስፋ መፈጸም እንደሚችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር።” (ሮም 4:21) አብርሃም እምነት በማሳየቱ የተነሳ ይሖዋ ሞገሱን አሳይቶታል፤ እንደ ጻድቅ አድርጎም ቆጥሮታል።—ያዕ. 2:23፤ w23.12 8 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ሰኔ 21

በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ ሰው በብዙ ነገርም ታማኝ ነው፤ በትንሽ ነገር ታማኝ ያልሆነ ሰው ደግሞ በብዙ ነገርም ታማኝ አይሆንም።—ሉቃስ 16:10

እምነት የሚጣልበት ወጣት ወንድም የተሰጡትን ኃላፊነቶች በሙሉ በትጋት ይወጣል። ኢየሱስ የተወውን ፍጹም ምሳሌ ልብ በሉ። ኢየሱስ ግድየለሽ ወይም ቸልተኛ ሆኖ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ በአስቸጋሪ ጊዜያትም ጭምር ይሖዋ የሰጠውን ኃላፊነቶች በሙሉ ተወጥቷል። ለሰዎች በተለይም ለደቀ መዛሙርቱ ፍቅር ስለነበረው ለእነሱ ሲል ሕይወቱን በፈቃደኝነት አሳልፎ ሰጥቷል። (ዮሐ. 13:1) እናንተም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የተሰጣችሁን ማንኛውንም ኃላፊነት በትጋት ተወጡ። ሥራውን እንዴት ማከናወን እንዳለባችሁ ግራ ከገባችሁ የጎለመሱ ወንድሞችን እርዳታ በትሕትና ጠይቁ። የግድ የሚጠበቅባችሁን ነገር ብቻ በማድረግ አትወሰኑ። (ሮም 12:11) ከዚህ ይልቅ “ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደምታደርጉት በማሰብ” ኃላፊነታችሁን በአግባቡ ተወጡ። (ቆላ. 3:23) እርግጥ ፍጹም እንዳልሆናችሁ የታወቀ ነው፤ ስለዚህ ስህተት ስትሠሩ በትሕትና ስህተታችሁን አምናችሁ ተቀበሉ።—ምሳሌ 11:2፤ w23.12 26 አን. 8

እሁድ፣ ሰኔ 22

በይሖዋ የሚታመን . . . ሰው የተባረከ ነው።—ኤር. 17:7

ተጠምቆ የይሖዋን ቤተሰብ መቀላቀል በጣም ያስደስታል። ይህን ውድ መብት ያገኙ ሁሉ፣ መዝሙራዊው ዳዊት ስለ ይሖዋ በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ እንደሚስማሙ ጥያቄ የለውም፦ “በቅጥር ግቢዎችህ ይኖር ዘንድ የመረጥከውና ያቀረብከው ሰው ደስተኛ ነው።” (መዝ. 65:4) ይሖዋ ወደ ቅጥር ግቢዎቹ የሚያስገባው ሁሉንም ሰው አይደለም። ይሖዋ የሚመርጠው ከእሱ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት የሚፈልጉ ሰዎችን ነው። (ያዕ. 4:8) ራስህን ለይሖዋ ወስነህ ከተጠመቅክ በኋላ ይሖዋ ‘ማስቀመጫ እስክታጣ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያፈስልህ’ መተማመን ትችላለህ። (ሚል. 3:10፤ ኤር. 17:8) ጥምቀት የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ነው። ፈተና ወይም መከራ ቢያጋጥምህም እንኳ ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል ጠብቀህ ለመኖር አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብሃል። (መክ. 5:4, 5) የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንደመሆንህ መጠን የኢየሱስን አርዓያ እና ትእዛዛቱን የቻልከውን ያህል በጥብቅ ለመከተል ጥረት ታደርጋለህ።—ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ጴጥ. 2:21፤ w24.03 8 አን. 1-3

ሰኞ፣ ሰኔ 23

ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል።—ዘፍ. 2:24

ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር አብራችሁ ጊዜ ማሳለፍ የማያስደስታችሁ ቢሆንስ? ምን ማድረግ ትችላላችሁ? እሳት ማቀጣጠልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እሳቱ ወዲያውኑ ቦግ ብሎ አይነድም። ከትንሽ ጭራሮ አንስቶ ቀስ በቀስ ተለቅ ተለቅ ያሉ እንጨቶች ሊጨመሩበት ይገባል። እናንተም በተመሳሳይ በየቀኑ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ አብራችሁ በማሳለፍ ለምን አትጀምሩም? ሁለታችሁንም በሚያስደስታችሁ እንቅስቃሴ ለመካፈል ሞክሩ። (ያዕ. 3:18) በዚህ መንገድ ከትንሹ መጀመራችሁ ፍቅራችሁን ለማቀጣጠል ሊረዳችሁ ይችላል። በትዳር ውስጥ መከባበር በጣም ወሳኝ ነው። አክብሮት እሳት በደንብ እንዲነድ ከሚያደርገው ኦክስጅን ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ኦክስጅን ከሌለ እሳቱ ወዲያውኑ ይጠፋል። በተመሳሳይም ባለትዳሮች እርስ በርስ የማይከባበሩ ከሆነ ፍቅራቸው ወዲያውኑ ሊቀዘቅዝ ይችላል። በሌላ በኩል ግን፣ እርስ በርስ ለመከባበር ጥረት የሚያደርጉ ባልና ሚስት ፍቅራቸው እንዳይከስም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ይሁንና ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ነገር አለ። ዋናው ነገር እናንተ አክብሮት እንደምታሳዩ የሚሰማችሁ መሆኑ ሳይሆን የትዳር ጓደኛችሁ እንደምታከብሩት የሚሰማው መሆኑ ነው። w23.05 22 አን. 9፤ 24 አን. 14-15

ማክሰኞ፣ ሰኔ 24

በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።—መዝ. 94:19

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በጠላቶቻቸው ወይም በሌሎች ችግሮች የተነሳ በጭንቀት የተዋጡበትና በፍርሃት የተንቀጠቀጡበት ጊዜ እንዳለ ይናገራል። (መዝ. 18:4፤ 55:1, 5) እኛም በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ ከቤተሰባችን ወይም ከመንግሥት ተቃውሞ ሊያጋጥመን ይችላል። ምናልባትም በጤና እክል የተነሳ ከሞት ጋር እንፋጠጥ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን እንደ ሕፃን ልጅ ምንም ነገር ማድረግ እንደማንችል ይሰማን ይሆናል። ታዲያ ይሖዋ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ የሚረዳን እንዴት ነው? ይሖዋ ያጽናናናል፤ እንዲሁም ያረጋጋናል። እንግዲያው ወደ ይሖዋ በመጸለይና ቃሉን በማንበብ አዘውትረህ ከእሱ ጋር ጊዜ አሳልፍ። (መዝ. 77:1, 12-14) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ውጥረት ውስጥ ስትገባ ወዲያውኑ ወደ ይሖዋ ዞር ለማለት ትነሳሳለህ። ፍርሃትህንና ጭንቀትህን ለይሖዋ ንገረው። በቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት እንዲያነጋግርህና እንዲያጽናናህ ፍቀድለት።—መዝ. 119:28፤ w24.01 24-25 አን. 14-16

ረቡዕ፣ ሰኔ 25

ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ኃይል እንድታገኙ በማድረግ . . . ብርታት የሚሰጣችሁ አምላክ ነው።—ፊልጵ. 2:13

መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ተነሳሽነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ተነሳሽነት ያለው ሰው ግቡ ላይ ለመድረስ ልባዊ ፍላጎት ስላለው ጠንክሮ ይሠራል። ደግሞም ተነሳሽነታችን በጣም ከፍተኛ ከሆነ ግቦቻችን ላይ የመድረሳችን አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል። ታዲያ ተነሳሽነትህን ማሳደግ የምትችለው እንዴት ነው? ተነሳሽነትህ እንዲጨምር ጸልይ። ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ግብህ ላይ እንድትደርስ ሊያነሳሳህ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ግብ የምናወጣው ያንን ግብ ማውጣት እንዳለብን ስለሚሰማን ነው፤ ይህ በራሱ ጥሩ ነገር ነው። ሆኖም ግቡ ላይ ለመድረስ ያን ያህል ፍላጎት ላይኖረን ይችላል። ይሖዋ ባደረገልህ ነገር ላይ አሰላስል። (መዝ. 143:5) ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ ባሳየው ጸጋ ላይ አሰላስሏል፤ ይህም ይሖዋን በትጋት ለማገልገል አነሳስቶታል። (1 ቆሮ. 15:9, 10፤ 1 ጢሞ. 1:12-14) አንተም ይሖዋ ባደረገልህ ነገር ላይ ይበልጥ ባሰላሰልክ መጠን ግብህ ላይ ለመድረስ ያለህ ተነሳሽነት ይበልጥ ይጨምራል።—መዝ. 116:12፤ w23.05 27 አን. 3-5

ሐሙስ፣ ሰኔ 26

የይሖዋን ስም አወድሱ።—መዝ. 113:1

የሰማዩ አባታችን ስሙን ስናወድስ ይደሰታል። (መዝ. 119:108) ታዲያ ይህ ሲባል፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የበታችነት ስሜት እንደሚሰማቸው ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ውዳሴ ያስፈልገዋል ማለት ነው? በፍጹም። የሰማዩን አባታችንን ስናወድስ እኛን የሚመለከትን አንድ ውሸት ለማጋለጥ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። ሰይጣን ማንም ሰው በታማኝነት ለአምላክ ስም ጥብቅና አይቆምም ብሎ ተከራክሯል። እንደ እሱ አባባል ከሆነ ማናችንም ንጹሕ አቋማችንን አንጠብቅም። ለአምላክ ጀርባችንን መስጠት ጥቅም እንደሚያስገኝልን እስከተሰማን ድረስ ማናችንም ብንሆን ይህን ከማድረግ ወደኋላ እንደማንል ተናግሯል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4) ሆኖም ታማኙ ኢዮብ፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን አጋልጧል። አንተስ? እያንዳንዳችን ለአባታችን ስም ጥብቅና የመቆምና እሱን በታማኝነት በማገልገል ልቡን የማስደሰት ውድ መብት አለን። (ምሳሌ 27:11) በእርግጥም ይህ ታላቅ ክብር ነው። w24.02 8-9 አን. 3-5

ዓርብ፣ ሰኔ 27

[በነቢያቱ] እመኑ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ይሳካላችኋል።—2 ዜና 20:20

ከሙሴና ከኢያሱ በኋላ ይሖዋ ሕዝቡን ለመምራት መሳፍንትን አስነሳላቸው። ከዚያም በነገሥታት ዘመን ይሖዋ ሕዝቡን ለመምራት ነቢያትን ሾሞላቸዋል። ታማኝ የሆኑ ነገሥታት የነቢያቱን ምክር ይከተሉ ነበር። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት፣ ነቢዩ ናታን የሰጠውን እርማት በትሕትና ተቀብሏል። (2 ሳሙ. 12:7, 13፤ 1 ዜና 17:3, 4) ንጉሥ ኢዮሳፍጥ፣ ነቢዩ ያሃዚኤል የሰጠውን መመሪያ ተከትሏል፤ በተጨማሪም ‘በአምላክ ነቢያት እንዲያምኑ’ የይሁዳን ሕዝብ አበረታቷቸዋል። (2 ዜና 20:14, 15) ንጉሥ ሕዝቅያስ በጭንቀት በተዋጠበት ወቅት ከነቢዩ ኢሳይያስ ምክር ጠይቋል። (ኢሳ. 37:1-6) ነገሥታቱ የይሖዋን አመራር በተከተሉበት ዘመን ሁሉ በረከት ያገኙ ነበር፤ ብሔሩም ጥበቃ አግኝቷል። (2 ዜና 20:29, 30፤ 32:22) ይሖዋ ሕዝቦቹን ለመምራት ነቢያቱን እየተጠቀመ እንዳለ ግልጽ ነበር። w24.02 21 አን. 8

ቅዳሜ፣ ሰኔ 28

ከእነዚህ ሰዎች ጋር አትተባበሩ።—ኤፌ. 5:7

ሰይጣን የይሖዋን መሥፈርቶች መጠበቅ ከባድ እንዲሆንብን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር እንድንወዳጅ ይፈልጋል። በዚህ ረገድ እኛ ከጥንቶቹ የኤፌሶን ክርስቲያኖች ይበልጥ መጠንቀቅ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም በዛሬው ጊዜ ከሰዎች ጋር የምንገናኘው በአካል ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሚዲያም ጭምር ነው። ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት መፈጸም ምንም ስህተት እንደሌለው የሚገልጸው የዓለም አስተሳሰብ እንዳይጋባብን መጠንቀቅ አለብን። እኛ ይህ አስተሳሰብ ስህተት እንደሆነ እናውቃለን። (ኤፌ. 4:19, 20) እንግዲያው ራሳችንን እንዲህ ብለን እንጠይቅ፦ ‘የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ከማያከብሩ የሥራ ባልደረቦቼ፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ወይም ሌሎች ሰዎች ጋር ሳያስፈልግ ጊዜ ላለማሳለፍ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ? አንዳንዶች ጠባብ አስተሳሰብ እንዳለኝ አድርገው ቢመለከቱኝም እንኳ ለይሖዋ መሥፈርቶች በድፍረት ጥብቅና እቆማለሁ?’ ከዚህም ሌላ በ2 ጢሞቴዎስ 2:20-22 ላይ እንደተመከርነው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም እንኳ የቅርብ ጓደኛ የምናደርጋቸውን ሰዎች በጥንቃቄ መምረጥ አለብን። አንድ ሰው ክርስቲያን ስለሆነ ብቻ ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንድንጸና ያግዘናል ማለት እንዳልሆነ ልናስታውስ ይገባል። w24.03 22-23 አን. 11-12

እሁድ፣ ሰኔ 29

ይሖዋ እጅግ አፍቃሪ [ነው]።—ያዕ. 5:11

ይሖዋ ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክረህ ታውቃለህ? ይሖዋ በዓይን ባይታይም መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ መንገዶች ይገልጸዋል። ይሖዋ “ፀሐይና ጋሻ” እንዲሁም “የሚባላ እሳት” ተብሎ ተጠርቷል። (መዝ. 84:11፤ ዕብ. 12:29) ሕዝቅኤል ስለ ይሖዋ ባየው ራእይ ላይ የሰንፔር ድንጋይ፣ እንደ ብረት የሚያብረቀርቅ ነገር እንዲሁም ደማቅ ቀስተ ደመና ተመልክቷል። (ሕዝ. 1:26-28) ይሖዋን ልናየው ስለማንችል እሱ እንደሚወደን ማመን ሊከብደን ይችላል። አንዳንዶች በሕይወታቸው ካጋጠሟቸው ነገሮች በመነሳት ይሖዋ ፈጽሞ ሊወዳቸው እንደማይችል ይሰማቸዋል። ይሖዋ እንዲህ ያሉት ስሜቶች የሚያሳድሩብንን ተጽዕኖ ይረዳል። እኛን ለመርዳት ሲል ማራኪ የሆኑትን ባሕርያቱን በቃሉ አማካኝነት ገልጾልናል። ይሖዋን ከሁሉ በተሻለ መንገድ የሚገልጸው ቃል ፍቅር የሚለው ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ ፍቅር ነው። ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። የአምላክ ፍቅር በጣም ታላቅና ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ እሱን ለማይወዱት ሰዎች ጭምር ፍቅር ያሳያል።—ማቴ. 5:44, 45፤ w24.01 26 አን. 1-3

ሰኞ፣ ሰኔ 30

በደመና ዓምድ ውስጥ ሆኖ ያነጋግራቸው ነበር።—መዝ. 99:7

ይሖዋ እስራኤላውያንን እየመራ ከግብፅ እንዲያወጣ ሙሴን ሾሞት ነበር። በተጨማሪም እስራኤላውያን እየመራቸው ያለው እሱ መሆኑን እንዲያስተውሉ በዓይን የሚታይ ማስረጃ ሰጥቷቸዋል። ቀን ቀን የደመና ዓምድ፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ የእሳት ዓምድ ያሳያቸው ነበር። (ዘፀ. 13:21) ሙሴ ዓምዱን ተከትሏል፤ ሆኖም ዓምዱ እሱንና እስራኤላውያንን ወደ ቀይ ባሕር መራቸው። ሕዝቡ በቀይ ባሕርና በሚያሳድዳቸው የግብፅ ሠራዊት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ስለተሰማቸው በፍርሃት ተዋጡ። ሆኖም ይህ ስህተት አልነበረም። ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ሕዝቦቹን ወደዚያ የመራቸው በዓላማ ነው። (ዘፀ. 14:2) አምላክ እስራኤላውያንን እጅግ አስደናቂ በሆነ መንገድ ታደጋቸው። (ዘፀ. 14:26-28) ከዚያ በኋላ ላሉት 40 ዓመታት ሙሴ የደመናውን ዓምድ እየተከተለ የአምላክን ሕዝቦች በምድረ በዳው ውስጥ መምራቱን ቀጥሏል። (ዘፀ. 33:7, 9, 10) ይሖዋ ከደመናው ዓምድ ሙሴን ያነጋግረዋል፤ ሙሴ ደግሞ መመሪያውን ለሕዝቡ ያስተላልፋል። እስራኤላውያን በሙሴ አማካኝነት እየመራቸው ያለው ይሖዋ መሆኑን መገንዘብ የሚችሉበት አጥጋቢ ማስረጃ ነበራቸው። w24.02 21 አን. 4-5

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ